ጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሀንስ

ዘውድ ሳይደፉ መንገስ /ከእዝራ እጅጉ / ክፍል አንድ

ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሀንስ

ዘውድ ሳይደፉ መንገስ አዳጋች ይመስለኛል፡፡ በአገራችን ግን በአንድ ወቅት ያለ በአለ ሲመት የነገሱ ነበሩ፡፡ መንገስ ሲባል አድራጊ ፈጣሪነት እና ተፈሪነትን የሚያመለክት ሲሆን በቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ታሪካችንም ውስጥ ድምጻቸውን አጥፍተው ከኋላ በመሆን የንጉስ ወይም የርእሰ ብሄር ያህል የሚፈሩ ነበሩ ይኖራሉም፡፡

በዚህ ጽሁፍ ስለ እነርሱ በዝርዝር ማውራቱን ለጊዜው ትቼ ከ 80 አመት በፊት የተሰጣቸውን የመንግስት የሥራ ኃላፊነት ይዘው ፣ እጅግ ወሳኝ የአገሪቱ ቁልፍ ሰው በመሆን አሻራ ማኖር ስለቻሉ አንድ ሰው ላጫውታችሁ ፈልጌ ነው፡፡

ሰውየው ጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሀንስ ሲባሉ ከ1933 እስከ 1947 አ.ም ለ 14 አመታት የንጉስ ኃይለስላሴን ማህተም በመያዝ በወሳኝ ጉዳይ ላይ አደራቸውን ሲወጡ የነበሩ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡

ንጉስ ኃይለስላሴ ስልጣናቸውን ከማጋራት ባልተናነሰ እንዴት ለእኒህ ሰው እድል ሰጡ? እያልኩ ጥያቄ የምጠይቅበት ጊዜ አለ፡፡ ጃንሆይ ወልደጊዮርጊስን ፈርተው ይሆን? የሚል ጥያቄ ሳነሳ ደግሞ አንዷ ባህር ማዶ ያለች ወዳጄ ‹‹ንጉሱ እንኳን ማንንም አይፈሩም ብላ እንደመለሰችልኝ አስታውሳለሁ፡፡

የንጉሱ ዘመን ሰዎች ይመስጡኛል፡፡ የድሮ ዘመንን በመናፈቄ ሳይሆን አብሮ ከመዋል እና ከመሥራት አንዳንድ ጠቃሚ ነገር የቀሰምኩ በመሆኑ ነው፡፡ሁሉን ነገር ያሟሉ ብቁ ናቸው ብዬ ከፍ ከፍ ላደርጋቸው ሳይሆን ከጊዜ እና ከቋንቋ አጠቃቀም አንጻር ያላቸውን ልዩ አቅምና ክህሎት ለማድነቅ ፈልጌ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በንጉስ ኃይስላሴ ለነበረው የትምህርትና የሀገር አስተዳደር ዘይቤ ልዩ ቦታ አለኝ፡፡ ንጉሱ ፊውዳሊዝምን አንግሰዋል ተብለው ቢታሙም ትምህርት ላይ የበራቸው ልዩ ትኩረት ዛሬ ድረስ ምስጋና ያሰጣቸዋል፡፡

ባለፉት 7 አመታት ‹‹የንጉሱ ዘመን ባለውለታዎች›› በሚል መነሻ ሀሳብ የብዙዎቹን ታሪክ ስመረምር፤ ሰነድ ሳገላብጥ ስለቆየሁ የእነዚህን ታላላቅ ሰዎች ድንቅ አቅም መመስከር ችላለሁ፡፡ አሁንም በዚህ መጣጥፌ ስለ ጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሀንስ ሳጫውታችሁ የሰውየውን አበርክቶ ለማውሳት እና እናንተም ተጨማሪ ንባብ አካሂዳችሁ እንድታውቋቸው ለማድረግ ነው፡፡

ጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ ከንጉሱ በመቀጠል አድራጊ ፈጣሪ የሆኑበት ሚስጥር ምንድነው? ንጉሱ በስደት ወደ እንግሊዝ በሄዱበት ጊዜ አብረዋቸው የነበሩት ወልደጊዮርጊስ ራሳቸውን በማስተማር ለንጉሱ ታማኝነታቸውን ያሳዩበት ሂደት ምን ይመስላል? በስተ ፍጻሜ ደግሞ ወልደጊዮርጊስ ከንጉሱ ጋር ተቀያይመው ግዞት የመላካቸው አሳዛኝ ሁነት እንዴት ሆነ? እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡ ያኔ የነበረው አንዱ ሌላውን የሚጥልበት በሴራ የታገዘ የፖለቲካ ጥሎ ማለፍ በወልደጊዮርጊስም ዘመን የታየ በመሆኑ ያኔም ኮንስፓይረሲ ቲዮሪ ወይም የሴራ ፖለቲካ ነበር እንዴ? ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርገን ነው፡፡ ልጃቸውን ቃለ-ምልልስ በማድረግ በእርሳቸው ዙሪያ መጽሀፍ የደረሰ ሰውን በማነጋገር ራሳቸው ወልደጊዮርጊስ የጻፏቸውን ደብዳቤዎች በማጤን ዘውድ ሳይደፉ የነገሱትን ወልደጊዮርጊስን ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡

እኒህ ሰው ትውልዳቸው አዲስ አበባ አራት ኪሎ በተለምዶ ስሙ ‹‹አባታችን ሰፈር ›› ሲሆን የልጅነት ዘመናቸው በዚሁ አካባቢ ያለፈ ነበር፡፡ በእለተ ጊዮርጊስ ጥቅምት 23 1893 አ.ም ወልደጊዮርጊስ ተወለዱ፡፡ ወልደጊዮርጊስ በልጅነታቸው በጣም ቁጡ እንደነበሩና ይህም ባህሪያቸው ከእናታቸው ጋር ይመሳሰላል የሚሉ አሉ፡፡ አባት አቶ ወልደዮሀንስ ናዳቸው በአንጻሩ ትእግስትን የተላበሱ ነበሩ፡፡

እናት ወይዘሮ ወደር የለሽ ልጃቸው ከቤተክርስቲያን ተጠግቶ በመንፈሳዊ ህይወት እንዲበረታ የዘወትር ምኞታቸው ነበር፡፡ በወቅቱ የሀገሪቱ የትምህርት ስርአት በአብነት ትምህርት ቤቶች ቅኝት የተሰራ ስለነበር እናትም ልጃቸው ከዘመናዊ ትምህርት ይልቅ የቤተክርስቲያን ትምህርቱ ውስጥ በቶሎ እንዲገባ ሰርክ ይጎተጉቱ ነበር፡፡

ገና በልጅነት የፈረንሳይኛ ቋንቋን ያዳበሩት ወልደጊዮርጊስ በቋንቋ የልዩ ክህሎት ባለቤት ለመሆን የግል ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ በኋለኛው የሥራ ዘመናቸው ከንጉስ ቀጥሎ ወሳኝ ሰው ለመሆን የቻሉት ወልደጊዮርጊስ ገና በልጅነት ለማደግ ያደርጉት የነበረው ታላቅ ጥረት ትልቅ ሰው እንደሚሆኑ ተስፋን ያመላከተ ነበር፡፡ የመሳፍንት ወገን፣የመኳንንት ዘር፣የጨዋ እና የደሀ ልጅ በሚል ክፍፍል ዘመኑ ይጓዝ በነበረበት ጊዜ ወልደጊዮርጊስ ግን ድምጻቸውን አጥፍተው ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለሟል ለመሆን ሌት ተቀን ይተጉ ነበር፡፡

ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ውስጥ ጎበዝ ከነበሩት አንዱ ወልደጊዮርጊስ ይጠቀሳሉ፡፡

በ1912 አ.ም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ወልደጊዮርጊስ በንግስት ዘውዲቱ እና በአልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ፈቃድ ሰኔ 4 1912አ.ም በጉምሩክ መስሪያ ቤት ተቆጣጣሪ ሆነው እንዲሰሩ ተመደቡ፡፡ ወጣቱ ወልደጊዮርጊስ ግን የጉምሩኩን ሥራ ፈጽሞ አልወደዱትም፡፡ በእርግጥ በንግስት ዘውዲቱ ዘመን የጉምሩክ ባልደረባ መሆን እንደ ቀልድ የሚገኝ እድል አልነበረም፡፡ ደሞዙም ጠቀም ያለ ነበር፡፡ የ19 አመቱ ወልደጊርጊስ ግን ርካታን አስቀደመ፡፡

ወልደጊዮርጊስ ከጉምሩክ ሥራው ይበልጥ ከፈረንሳይኛ ቋንቋ ጋር በተያያዘ ቢሰሩ ደስታውን አይችሉትም ነበር፡፡ ትምህርታቸውንም ባህር ማዶ የመቀጠል ልዩ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ በዚያው አመት በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ውስጥ በአስተርጓሚነት ሥራቸውን ጀመሩ፡፡ በዚህ ሆስፒታል ውስጥ ለመታከም ይመጡ የነበሩ ባለሙያዎች ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ስለነበሩ ለወጣቱ ወልደጊዮርጊስ አመቺ እድል ተፈጠረላቸው፡፡ በወር 80 እየተከፈላቸው የአስተርጓሚነት ስራን ሲሰሩ ከከፍያው ይልቅ ውስጣዊ ፍላጎታቸውን አረካው፡፡ በፈረንሳይኛ ችሎታቸው ብዙዎች ጥሩ ምስከርነት ይሰጧቸውም ነበር፡፡

የንጉሰ ነገስቱ አማካሪ በመሆን ከአሜሪካ የመጣው ጆን ስፔንሰር ከወልደጊዮርጊስ ጋር በመጀመሪያ የተገናኘው ደሴ ላይ ነበር፡፡ እናም ‹‹ኢትዮጵያ አት ቤይ›› መጽሀፍ ላይ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡

‹‹….. 12 አመታት ያህል በተለያዩ ኮሚቴዎች አብረን በመሳተፍ ጠንካራ ውይይቶች አካሂደናል፡፡ ወልደጊዮርጊስን በተለይ የማስታውሰው በፈረንሳይኛ የንግግር የተለየ ችሎታው ነው ›› በማለት ጽፎ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ከሆስፒታል የተነሳው ወጣቱ አስተርጓሚ ወልደጊዮርጊስ በአለም አቀፍ መድረኮች እና ውይይቶች ላይ በፈረንሳይኛ የነበረውን ችሎታ የሚነግረን ነው፡፡

ወልደጊዮርጊስ፣ በሆስፒታል ውስጥ ያሳዩት ቅልጥፍና ወደ ቤተ- መንግስት አስጠጋቸው፡፡ አንድ ቀን የወቅቱ የጉምሩክ እና የገቢዎች ባለስልጣን የበላይ ኃላፊ ክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ ህክምና ለመከታተል ወደ ምኒሊክ ሆስፒታል ያቀናሉ፡፡ እዛም ለማስተርጎም ላይ ታች ሲል በነበረው ወልደጊዮርጊስ ክህሎት ተደነቁ፡፡ በተለይ ለማስተርጎም ሲያደርግ የነበረውን ጥረት አቶ መኮንን ልብ ብለው አዩ፡፡

‹‹ …ይህ አፍላ ወጣት በመንግስት ሥራ ውስጥ ገብቶ ቢሰራ የተሻለ ይሆናል ሲሉ ክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ ወልደጊዮርጊስን ወደ ቤተመንግስት ሥራ እንዲገባ አደረጉት፡፡ በዚህም አጋጣሚ የአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን እና የአልጋ ወራሽ ትውውቅ አንድ ብሎ ጀመረ፡፡

ወልደጊዮርጊስም በ20ዎቹ የመጀመሪያ እድሜ ላይ የአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንንን የትርጉም ሥራ ለማከናወን ከቤተ-መንግስት ተሰየሙ፡፡

‹‹ዘውድ ያልደፋው ንጉስ የለውጥ ሀዋርያ›› የተሰኘውን በጸሀፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሀንስ ህይወት ላይ ያተኮረውን መጽሀፍ የጻፈው ደራሲ ደረጀ ተክሌ ወልደ ጊዮርጊስ ከልጅነት ጀምሮ ለማደግ ሲያደርጉት የነበረው ልፋት ያስገርመዋል፡፡

ይህንን መጣጥፍ ለመጻፍ ስል ያነጋገርኩት ደረጀ እንዳጫወተኝ ወልደጊዮርጊስ ያገኙትን እውቀት ወደ ሥራ ተርጉመው የመገኘት ብቃታቸው በቶሎ ከስኬት ማማ ላይ አቃርቧቸዋል ብሎ ያምናል፡፡ በተለይ ደግሞ ወልደጊዮርጊስ ገና በልጅነት ከራስ ብሩ ጋር ፈረንሳይ ባቀኑበት ጊዜ ያነበቧት ባለ 100 ገጽ መጽሀፍ ትልቅ ተጽእኖ እንዳሳደረችባቸው ደራሲ ደረጀ ያስረዳል፡፡

ወልደጊዮርጊስ፣ ገና የቤተመንግስት ሥራውን ሳይጀምሩ ለመጀመሪያ በሙከራ ጊዜ ላይ ሳሉ ፈረንሳይ ለማስተርጎም አቅንተው በነበረ ጊዜ ዣን አዊኒ የሚባል ፈረንሳዊ ስለ ወልደጊዮርጊስ ይህንን ተናግሮ ነበር፡፡

‹‹…. ወልደጊዮርጊስ የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አደረጃጀት እና የዲፕሎማሲ አመራር እንዴት እንደሆነ ለማወቅ አጥብቆ ጠየቀኝ፡፡በነበረኝ ኃላፊነት መሰረትየፈረንሳይን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በየዲፓርትመንቱ እየተዘዋወረ ጥናት እንዲያደርግ ፈቀድኩለት፡፡ የዲፕሎማሲ ሀሁ የምትሰኝ 100 ገጽ የማትሞላ መጽሀፍም በማስታወሻነት አበረከትኩለት ፡፡ ያ ሰው ከብዙ አመት በኋላ ከፍተኛ ስልጣን ላይ ደርሶ ሳገኘው ተገረምኩ›› ብሏል፡፡

ራሳቸውን በማስተማር ሳይታክቱ የደከሙት ወልደጊዮርጊስ ከጣሊያን ወረራ አስቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የክፍል ሹም ቀጥሎም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ጸሀፊ ፤ በመጨረሻም የንጉሰ ነገስቱ ልዩ ጸሀፊና የጽህፈት ሚኒስቴር ዋና ዲሬክተር በመሆን አገልግለዋል፡፡ በንጉስ ኃይለስላሴ ዘመን አንድ ሰው አቅሙን ሳይቆጥብ ለንጉሱ ታማኝ ሆኖ ካገለገለ ለስኬታማነት እንደሚበቃ የወልደጊዮርጊስ የሥራ ተሞክሮ ይነግረናል፡፡

ገና በ33 ዓመታቸው የንጉስ ኃይለስላሴ የጽህፈት ሚኒስቴር ዋና ዲሬክተር የሆኑት ወልደጊዮርጊስ ስልጣን ያገኙት በደጅ ጥናትና በልመና ሳይሆን ንጉሱ መርጠዋቸው እና ችሎታቸውን ፈልገውት ነው፡፡ ጣሊያን በ1928 ኢትዮጵያን በግፍ በወረረ ጊዜ ረዳኢ ንጉስ የሚል ስም የተሰጣቸው ወልደጊዮርጊስ በውጊያ ሜዳ ወደ አዲስ አበባ በተደረገው ስልታዊ ማፈግፈግ በእውቀታቸው አማክረዋል፡፡ እንደ ልጅ በመላላክ የንጉሱን ትእዛዝ ተፈጻሚ ለማድረግ አደራቸውን በሚገባ ተወጥተዋል፡፡የንጉሱ የቅርብ ዘመድ ሳይሆኑ የአገሪቱ ተጽእኖ ፈጣሪ 2ኛ ሰው ሆኑ፡፡ በስደት ዘመን ንጉስ ኃይለስላሴ ወደ ጄኔቫ ባቀኑ ጊዜ ወልደጊዮርጊስ የልኡካን ቡድኑ አባል ነበሩ፡፡

ኢትዮጵያ ጣሊያንን አሸንፋ የነጻነት አየር ሲገባ ወልደጊዮርጊስ ከጠላት በኋላ ከተሾሙ 7 የካቢኔ ሚኒስትሮች አንዱ ነበሩ፡፡ በዚህ ወቅት የ40 አመት ጎልማሳ የነበሩት ወልደጊዮርጊስ ፣ኢትዮጵያን በአዲስ የእድገት ጎዳና ላይ ለማራመድ መንገድ ቀያሽ ሆኑ፡፡ የጽህፈት ሚኒስትር ሆነው የንጉሱን ማህተም በመያዝ ፤ የቤተ መንግስቱን የክብር መዝገብ በክብር በማስቀመጥ ፣ የመንግስትን ውሎችና ስምምነቶች መልክ በማስያዝ የጸሀፌ ትእዛዝ ሚና ትልቅ ነበር፡፡ ጣሊያን የኢትዮጵያን ግዛት ለቆ ከወጣ በኋላ ወዳጅ መስሎ እንግሊዝ ለዳግም ቅኝ ግዛት በቀረበን ጊዜ ወልደጊዮርጊስ ለእንግሊዞች ፊት ባለመስጠት ለእናት አገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር አሳይተዋል፡፡ በዚህም እንግሊዞች ወልደጊዮርጊስ ጸረ እንግሊዝ ነው እስከማለት ደርሰው ነበር፡፡

‹‹ዘውድ ያልደፋው ንጉስ›› የተሰኘው መጽሀፍ ላይ የጸሀፌ ትእዛዝ አገራዊ አበርክቶ በዝርዝር የቀረበ ሲሆን በተለይ ዘመናዊ ትምህርት የተማሩ ሰዎች የስልጣን ቦታውን እንዲይዙ ቆራጥ አመራር ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ እንደ ከተማ ይፍሩ ፣አካለወርቅ ሀብተወልድ ያሉት ሰዎች ወደ አመራር ቦታ እንዲመጡ የወልደጊዮርጊስ አስተዋጽኦ ትልቅ ነበር፡፡

ተራማጅ የነበሩት ወልደጊዮርጊስ በጊዜ ሂደት በተለይ በ1947 ግድም ከወግ አጥባቂው የመሳፍንት ወገን ተቃውሞ በረታባቸው፡፡ ‹‹….ይህ ሰው በአገሪቱ በሁሉ ጉዳይ አድራጊ ፈጣሪ ሆነ ፡፡ መፈንቅለ ጃንሆይ ማድረጉ አይቀርም›› የሚለው ወሬ ንጉሱ ዘንድ እየተዋዛ መድረስ ጀመረ፡፡ በእርግጥም ወልደጊዮርጊስ ተሰሚነት ያላቸው ፣ በየቦታው የራሳቸውን ሰው ያስቀመጡ ፣ ንጉሱ ላይ ሂስ ለመሰንዘር ወደ ኋላ የማይሉ ሞገደኛ ሰው ሆነው ነበር፡፡ ይህን ሞገደኝነት እያዩ እንዳላዩ ማለፍ ለንጉሱም ሆነ ለወግ አጥባቂው የመሳፍንት ወገን የሚታገሱት አልነበረም፡፡ 30 አመት ከንጉስ ኃይለስላሴ ጋር የደከሙት ወልደጊዮርጊስ ከ1933 እስከ 1947 በጸሀፌ ትእዛዝነት የሰሩት ታላቅ ሰው ከኃላፊነት ተነስተው ዝቅ ባለ ደረጃ የአሩሲ ጠቅላይ ግዛት ጠቅላይ ገዥ እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ ይህም ብዙዎችን አስደነገጠ፡፡ ግን ምንም ማድረግ አልተቻለም፡፡

የወልደጊዮርጊስ ደጋፊ የሆኑ ባለስልጣናት በግዞት መልክ ከደረጃቸው ዝቅ በሚያደርግ መልኩ ሽረት ሲደረግባቸው በሌሎቹ ላይ ደግሞ አዳዲስ ሹመቶች ተሰጡ፡፡ አምባሳደር ዘውዴ ረታ የጻፉት የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት በሚለው መጽሀፍ ውስጥ እነማን ተሾሙ? እነማን ተሻሩ? የሚለው በዝርዝር የቀረበ ሲሆን አምባሳደር ዘውዴ ረታ ከጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ያደረጉት ቆይታ በመጽሀፉ ውስጥ ተካቶ ይገኛል፡፡

አሩሲ በግዞት መልክ እንዲያስተዳድሩ እድል የተሰጣቸው ወልደጊዮርጊስ ዋናው የግዞቱ ግብ ከንጉሱ ፊት ገለል እንዲሉ ለማድረግ ነበር፡፡ እርሳቸውም ወደ አሩሲ ገለል አሉ፡፡

ከደረጃ ዝቅ ብሎ መሥራት ምን ያህል እንደሚያም የደረሰበት ብቻ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ ወልደጊዮርጊስ አሰላ ከሄዱም በኋላ ሰላይ እየተላከ ፈጽሞ አላሰራ ብለዋቸው ነበር፡፡ ለመሆኑ ወልደጊዮርጊስ አሰላ አሩሲ ሳሉ ምን አይነት ውሳኔዎችን ሲወስኑ ነበር ? በሥራ መደባቸው ላይ ሆነው የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች ምን መልክ አላቸው? ስል የአገር ግዛት ሚኒስቴር የቆዩ ኦሪጅናል መዝገቦችን ማገላበጥ ነበረብኝ፡፡

ወልደጊዮርጊስ ጠቅላይ ገዥ በሆኑ በ3 አመቱ በነሀሴ 27 1950አ.ም የጻፉት ደብዳቤ ብዙ እውነታዎችን የያዘ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ከቀድሞ ወዳጃቸው ከክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ ጋር እንደ ሥራ መሪ የተለዋወጡት ደብዳቤ የሚከተለው ነው፡፡ ስካን የተደረገው ኦሪጅናል ደብዳቤ ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብሮ የተያያዘ ስለሆነ ያነቡት ዘንድ እጋብዛለሁ፡፡

ለክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ

ያገር ግዛት ሚኒስትር

ክቡር ሆይ በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት ያለው ህዝብ እህል አጥቶ ስለተራበ

1ኛ አሰላ ከተማ ካለው ህዝብ የቀረበውን ማመልከቻ

2ኛ ከዋናው መስሪያ ቤታችን ያሉት ሰራተኞች ያቀረቡትን ማመልከቻ

3ኛ ከጠቅላይ ግዛቱ በጅሮንድ ነሀሴ 1 1950 በቁጥር 1124 ሀ/1/11 የተጻፈው ደብዳቤና ያባሪውንም ግልባጭ በድምሩ 6 ገጽ የሆነ ከዚሁ ጋር ልኬልዎታለሁ፡፡ በህዝቡና በሰራተኞች ላይ የደረሰውን ችግር ለማስታገስ እንዲቻልም መንግስት ለህዝብ ካስመጣው ዱቄትና እህል አሰላ ከተማ ድረስ እንዲላክልን በማክበር አሳስባለሁ፡፡

ከማክበር ሰላምታ ጋር ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሀንስ ፊርማ

ዘውድ ሳይደፉ የነገሱት ወልደጊዮርጊስ የዛሬ 66 አመት ረሀብ በአሰላ ለመንገስ ባንዣበበበት ጊዜ ቀድሞ ለመድረስ የቀድሞ ወዳጃቸው ጋር ብእር ከወረቀት አቆራኝተው ደብዳቤ ጻፉ፡፡ የዛሬውን መጣጥፍ በዚህ ገታ ላድርግ፡፡ በቀጣዩ ሳምንት ቀሪ ሀሳቦችን ከወልደጊዮርጊስ ደብዳቤዎች እና ቀሪ ሰነዶች ጋር እንገናኛለን፡፡ ይቀጥላል

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ከዛሬ 20 አመት በፊት ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽንን የመሰረተ ሲሆን የ44 ባለውለታዎችን ታሪክ በሲዲ የ14 ሰዎችን ታሪክ በመጽሀፍ አዘጋጅቶ ያቀረበ ነው፡፡ በተጨማሪም የመጀመሪያውን የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ‹‹መዝገበ አእምሮ የሚድያ ሰዎች ታሪክን›› ያሳተመ ሲሆን የመጽሀፍ፣ የሪል ስቴት ፣የሆቴል የተቋማት መውረቃ የክብረ በአል ስነስርአቶችን የሚያዘጋጅ ባለሙያ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት የ185 የኪነጥበብ ሰዎችን ታሪክ ለማሳተም መሰናዶ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ አስተያየት ካለዎ tewedajemedia@gmail.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *