የምወድሽ በቀለ

በጋዜጠኝነት ዘርፍ የዘንድሮው የበጎ ሰው ዕጬ

የምወድሽ በቀለ ወ/ገብርኤል

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሙኒኬሽን ፣ የሽልማት ፕሮግራሞች ሲዘጋጁ የዕጬዎችን ታሪክ በማዘጋጀት ይታወቃል። በተለይም ከመምረጥ በፊት ማወቅ የሚለውን መርህ ይዘን የታታሪ ሰዎችን የህይወት ታሪክ ስናስተዋውቅ ቆይተናል። ዘንድሮ በሚደረገው 12ኛው የበጎ ሰው ሽልማት በጋዜጠኝነት ዘርፍ ደራሲና ጋዜጠኛ የምወድሽ በቀለ ዕጬ ሆናለች። ለመሆኑ፣ የምወድሽ በቀለ ማናት? ዕዝራ እጅጉ እና ባንቺአየሁ አሰፋ ታሪኳን ሰንደውታል።

ሳቂታዋ ሲቪል መርማሪ ፖሊስ በርካታ አሰቃቂና ዘግናኝ የወንጀል ማህደሮችን በአደባባይ ያጋለጠች ፣ ለዘመናት ተቀብረው የቆዩ ዶሴዎችን አነፍንፋ ያወጣች ፣ ለበርካታ ወንጀሎች ሕጋዊ ፍትሕ እንዲያገኙ የተጋች፣ ዜጎች የዳበረ አስተሳሰብና የላቀ ንቃተ ህሊና እንዲኖራቸው ለማድረግ ከ 3 በላይ የሚሆኑ መጽሐፍቶችን በመጽሀፍ አሳትማ ተቋማት በሚያደርጉላት እገዛ በነጻ በመስጠትና በማስተማር ከ 31 ዓመታት በላይ በፖሊስ ሬዲዮና ጋዜጣ ላይ እንዲሁም በአሐዱ ሬዲዮ ከአድማጭ ጋር እየተገናኘች ያለች ጋዜጠኛ የ 16 መጽሐፎች ደራሲ ነች። የምወድሽ በቀለ ወ/ገብርኤል፡፡

ጋዜጠኛ የምወድሽ በቀለ ወ/ገብርኤል ትውልዷ በአዲስ አበባ ከተማ ተክለሀይማኖት አካባቢ ነው፡፡ ከእናቷ ወ/ሮ ወርቅነሽ ወልደማሪያም እና ከአባቷ ሻምበል ባሻ በቀለ ወ/ገብርኤል ነሐሴ 19 1952 ዓ.ም ነበር የተወለደችው። ዛሬ የ 64 ዓመት ጎልማሳ ሴት ነች።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በአፍሪካ አንድነት ትምህርትቤት ስትማር የ 2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ አዲስ ከተማ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ተምራለች።

የምወድሽ ለእናቷ ብቸኛ ልጅ በመሆኗ እናቷ እንደ ዓይናቸው ብሌን ሰስተው የሚጠብቋት እጅግ ቀበጥ ፣ ጥርሷ ሳቅን የማይፆም ፣ የስስት ልጅ እንደነበረች ፣ ይኸ በነጻነት ላይ የተገነባ የልጅነት ማንነቷ ታዲያ ዛሬ ያለችበትን ህይወትና ስኬት የገነባ ስለመሆኑ ታምናለች። በልጅነቷ ትኩረት ታደርግ የነበረውም በሲኒማና ዳንስ ላይ እንደነበር የልጅነት አስተዳደግ ትዝታዋን ታወጋለች። አልችልምን የማትችል የጠየቀችው ፣ ያሰበችው ፣ የተናገረችው ልክ ነው የተባለች ነበረች።

የምወድሽ፣ እጅግ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነገርግን እረባሽ፣ በትንሽ ነገር ስቃ ተማሪን የምታስቅ ስትሆን ግጥም መጻፍ የጀመረችው ታዲያ በትምህርት ቤት የሚያበሽቋትን ለማብሸቅ ስትል ነበር።

የስነጽሑፍ ስራዋን በአደባባይ መስራት የጀመረችው ጌታቸው ተካልኝ በሚያሳትመው ፀደይ መጽሔት ላይ አርቲክሎችን በመጻፍ እና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በፍሪላንስ በመጻፍ ነበር ። ወደ ግቧ የሚያደርሳት ሌላኛው ክስተት ደግሞ ይህ ነው። ዘመኑ የሥነጽሑፍ ሥራዎች በውድድር የሚቀርቡበትና ወጣት ጸሐፊያን የሚበረታታበት ነበርና የምወድሽ በቀለ ባህልና ቱሪዝም ባዘጋጀው የጽሑፍ ውድድር ላይ በመሳተፍ አሸንፋ የመጀመሪያ የግጥም መጽሐፏን በ 1972 ዓ.ም አብዮታዊ ግጥሞች ብለው በማጭድና መዶሻ አጅበው አሳትመውላት ነበር።

መጽሐፉ በአሳታሚዎቹ ተሸጦ የተረፋቸውን ሲሰጧት ይህንን ለመሸጥ ወደ አንድ ቦታ ጎራ ትላለች። ቦታው ፖሊስ መስሪያ ቤት ነው። መጽሐፍ ልትሸጥ ሄዳ 27 ዓመታትን ያገለገለችበት ተቋም። ፍልቅልቋ እምወድሽ እንደስሟ ሁሉ ልትሸጥ የወሰደችው መጽሐፏ በሺ አለቃው ተወዶላት ስለነበር ምን መስራት ትፈልጊያለሽ የሚል ጥያቄ ያኔውኑ ጠየቋት። ለቀድሞው ሺ አለቃና የበኋላው ኮ/ል ሙሉጌታ ዲጆ ጋዜጠኛ ስትል ህልሟን ተናገረች። ጋዜጠኝነት ስትል የተናገረችበት ሌላ ምክንያትም ነበር። አባቷ ሻምበል ባሻ በቀለ ወልደገብርኤል ፖሊስ የነበሩ ሲሆን በርካታ የወንጀል ማህደሮችን የያዙ ጋዜጦች ወደ ቤት ሲወስዱ የምወድሽ ታነባለች። አንብባም ወዳቸዋለች።

እነዚህን ጋዜጦች እና በውስጣቸው ያሉት ታሪኮች ልቧን ሰርቀዋት እና ሰቅዘዋት ስለነበር ዛሬ ስትጠየቅ የሚያስደስተኝ ሙያ ጋዜጠኝነት ነው እንድትል አድርጓታል ።

ለወራቶች ወደ ፖሊስ መስሪያ ቤት እየሄደች ልምምድ እንድታደርግ ሺ አለቃው በነገሯት ጊዜ ልምምድ ማድረጉን ተያያዘችው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ፣ በመሀል ዋርነር ላፐር ኢንስቲቲዩት የተባለ የጀርመን ድርጅት በሰጠው የትምህርት ዕድል ለ 4 ወራት የጋዜጠኝነት ሥልጠና እንድትወስድ በአለቃዋ ተመርጣ 12 ኛ ክፍል ያጠናቀቀችበትን ወረቀት በማስገባት ወደ ዋርነር ላፐር አቀናች። ከትልልቅ ጋዜጠኞች ጋር በመሆን ስልጠናውን ለመውሰድ ቻለች።

የስልጠና ትምህርቱን አጠናቃ ስትመለስ በ 1974 ዓ.ም መጨረሻ 1975 መጀመሪያ አካባቢ በ 230 ብር በፖሊስ ሚዲያ ውስጥ ሥራ ጀመረች። በመጀመሪያ በሪፖርተርነት ፣ አምድ አዘጋጅ ፣ አዘጋጅነት፣ ምክትል አዘጋጅ ፣ ዋና አዘጋጅነት የፕሬስ ኃላፊ እስከመሆን ድረስ ደርሳለች።

ምንምኳን ፖሊስ ሆና ያገለገለች ባይሆንም የፖሊስነትን ህግና ስርዓትን ግን ጠንቅቃ ታውቅ ነበር። ለፖሊስ መስሪያ ቤት ግማሽ ዕድሜዋን የገበረችው የመጀመሪያዋ ሴት ሲቪልና መርማሪ ጋዜጠኛ የምወድሽ በቀለ በሀገራችን ውስጥ ጣሪያና ግድግዳን እንዲሁም ጨለማን ተገን አድርገው የሚፈጸሙ አሰቃቂ የወንጀል ሰነዶችን አገላብጣ በማጋለጥ ፣ እጇን ከእግር በማቀናጀት ወንጀሎችን በማነፍነፍ ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ ላይ በመገኘት ስለወንጀሎቹ መርምራ በመጠየቅ ፣ ወንጀሉ የሚያደርሰውን ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ሰብዓዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ከህግ አንጻር እና ከባለሙያ አንጻር በመፈተሽ ፣ ከባለሙያዎች ጋር ውይይት በማድረግ ጥንቅቅ ያለ ስራን ስትሰራ ቆይታለች።

“ጠንቀቅ ” እና ” እይታ” የተሰኙ ሁለት የሬዲዮ ፕሮግራሞች የነበሯት ሲሆን በፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ ደግሞ ” ህግ አስከባሪዎች ህግ ጥሰው ይሆን? ” የጋራ ችግሮች እንዴት ይቃለላሉ መድረክ ፣ ምርጥ የምርመራ ሥራዎች ( የውጭ ሀገር የወንጀል ታሪኮች ተተርጉመው የሚወጡበት ” በጥቅሉ 1 ርዕስ አንቀጽ እና 3 አምድ ይዛ ትሰራ ነበር። ጠንቀቅ በተሰኘው ፕሮግራሟ ደግሞ ሳምንቱን በሙሉ ስለተፈጠሩ ዝርፊያና ወንጀሎች ሰዎች አውቀው ራሳቸውን እንዲከላከሉ ለማስቻል ግንዛቤ ትሰጣለች ። የፖሊስና ርምጃ በ2 ሳምንት 126,000 ኮፒ ድረስ የሚሸጥ ጋዜጣም ነበር።

“ህግ አስከባሪዎች ህግ ጥሰው ይሆን? ” በሚል አምድ ስር በፖሊስና እርምጃ ላይ ስትጽፍ…

የምወድሽ የፖሊስ አባል ሆና በፖሊስ ሬዲዮና ጋዜጣ ላይ የፖሊሶችን ወንጀል በማጋለጧ እጅግ ብዙ ትችቶች ከፖሊስ አባላቱ ይደርሱባት ነበር። በሙስና ወንጀል የተዘፈቁ የፖሊስ አባላትን ዝርዝር ጉዳይ ፣ ወጣት እስረኞች ላይ በፖሊስ አባሎች የተደረጉ የግብረሰዶም ወንጀሎችን ከተዳፈኑ በኋላ በሚደርሳት ጥቆማ መሰረት በማጣራት ጉዳዩን ከህግ አንጻር እና ጉዳቱን ከህክምና ባለሞያዎች በመጠየቅ ጋዜጣ ላይ የምታወጣ ሲሆን ይህን የወንጀል ታሪክ እንዳትሰራ የፖሊስ ስም ማጥፋት ነው ስትባል ወንጀለኛ ወንጀለኛ ነው ብላ የሚደርስባትን ሁሉ በመቋቋም ሰርታለች።

በቅርቡ የጀመረችው ” ቡና ለገበና ” የተሰኘ መርሃግብር ስለመኖሩና መርሃግብሩ ሴቶች ቡና እየጠጡ ገመናዎቻቸውን አውርተው ችግራቸው እንዲያወጡ እና መፍትሔ ለመፈለግ እንዲያመች እንዲሁም እነርሱም አውርተው ሸክማቸውን በማጋራት እንዲቀላቸው ለማድረግ የሚያስችል ውጥን አላት።

በፕላን ኢንተርናሽናል እገዛ የታተመው ” ነገን በተስፋ እናፍቃለሁ ” የተሰኘ የእውነተኛ ታሪክ መጽሐፏን የጻፈችው በአሁኑ የኮቪድ ጊዜ ሲሆን ታሪኩም በኮቪድ ሳቢያ የተጣለውን ማዕቀብ ጥሰው የወጡ ሴተኛ አዳሪዎች በአንድ አንድ ህግ አስከባሪዎች እየተደፈሩ መሆናቸውን በቃለመጠይቅ ካገኘች በኋላ ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *