አቶ መሰረት መኮንን

የስራ ፈጣሪው – ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል

አቶ መሰረት መኮንን

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በንግድና ስራ ፈጠራ መስክ ለሀገራቸው ትልቅ ስራ የሰሩ ሰዎችን የህይወት ታሪክ እያስነበበ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም የ180 የሚድያ ሰዎችን የስራ እና የህይወት ተሞክሮ መዝገበ-አእምሮ በሚል ርእስ በጠንካራ ሽፋን የተዘጋጀ መጽሀፍ አሳትመን ለገበያ ማቅረባችን አይዘነጋም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በቢዝነሱ አለምም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ እድል የፈጠሩ ዜጎችን በመጽሀፍ አሰባስበን ማሳተማችን የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የነገው ትውልድ ከየሙያው አንድ ትልቅ ስራ የሰሩ ሰዎች ያስፈልጉታልና ላልተነገረላቸው ቅድሚያ እየሰጠን ታሪካቸውን ለንባብ እናበቃለን፡፡

ዛሬ በዚህ ጽሁፍ ታሪካቸውን የምናቀርበው ባለሀብት አቶ መሰረት መኮንን ይባላሉ፡፡ የኤን.ኤም ሲ ሪል ስቴት መስራች እና ባለቤት ሲሆኑ በቅርቡ በ8ነጥብ 5 ቢልዮን 600 በላይ ቤቶችን ለመገንባት ግንባታ ጀምረዋል፡፡ ቤቶቹ 35000ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ ሲሆን ከ 2 አመት በኋላ የግንባታ ስራቸው ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ አቶ መሰረት በተጨማሪም የቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤት የሆኑት አቶ መሰረት በቱሪዝም ፤ በትራንስፖርት እና በአስመጪ እና ላኪነት ስራም ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በበጎ አደርጎት እና በልማት ስራዎች ላይ ቀንደኛ ተሳታፊ የሆኑት እኒህ ስራ ፈጠሪ ባለትዳርና የ6 ልጆች አባትም ናቸው፡፡ ሰኔ 17 2015 ዓ.ም አቶ መሰረት መኮንን የተረከቡት 35,000 መሬት ላይ ግንባታውን የጀመሩ ሲሆን ለዚህም ማስታወሻ ይሆን የግንባታ ስራውን ከሚያከናውነው የቻይናው ኩባንያ ጋር ተፈራርመዋል፡፡

ይህ በሁለቱ ተቋማት መካከል የሚደረግ ስምምነት 21 የሚድያ ባለሙያዎች በታደሙበት ተከናውኗል ፡፡ የእለቱን የሚድያ እና የጋዜጣዊ መግለጫ ዝግጅት እንዲሁም የዘገባ ሥራዎቹን ይዘት በዋና አዘጋጅነት ያስተባበረው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሲሆን ወደፊትም ከድርጅቱ ጋር በብዙ ጉዳዮች አብረው እንደሚሰሩ ይታመናል፡፡ አሁን በቀጥታ የኤን.ኤም.ሲ ሪል ስቴት መስራት ማናቸው? መነሻቸው ምንድን ነው? በምን አይነት ፈተናዎች አለፉ? ለሚለው ይህ ከዚህ በታች የሚቀርበው የህይወት ታሪካቸው መልስ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ እዝራ እጅጉ የህይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡

ልጅነትና የቢዝነስ ዝንባሌ

አቶ መሰረት መኮንን ትውልዱ ደቡብ ጎንደር ነው፡፡ በቤት ውስጥ ሃላፊነትን መቀበል ሲጀምር እድሜው 10 አመት አልሞላም ነበር፡፡ እናቱን መርዳት ከምንም በላይ ደስታን ይሰጠው ነበር፡፡ ገና በታዳጊነቱ ተግባቢ የነበረው መሰረት ለሁሉ የሚታዘዝ ታታሪ ልጅ ነበር፡፡ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በደቡብ ጎንደር መካነኢየሱስ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የተማረው መሰረት አንድ ቀን ትልቅ ቦታ እንደሚደርስ ያልም ነበር፡፡ በ1980 የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በሀገሪቱ ጦርነት የተከሰተ በመሆኑ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ ትምህርቱን ገታ በማድረግ ፊቱን ወደ ንግድ አዞረ፡፡ የ19 አመቱን ባከበረ ማግስት ወደ ንግድ አለም የመግባት ፍላጎቱ አየለ፡፡ በመሆኑም በ500 ብር ካፒታል የቢዝነሱን አለም ተቀላቀለ፡፡

ወጣቱ መሰረት ባገኘው ገንዘብ ጥራጥሬ ወደ ሱዳን እየወሰዱ መሸጡን ተያያዘው፡፡ ከሱዳን ደግሞ ጨው በማምጣት ጎንደርና ባህርዳር አካባቢ መሸጥ ጀመረ፡፡ ይህን አይነቱን ንግድ ለ3 አመታት ከሰራበት በኋላ ጥሪት ማጠራቀም ችሎ ነበር፡፡ ከዚያም ጦርነቱ ጋብ ሲል በ1983 ወደ መዲናይቱ አዲስ አበባ መምጣት ነበረበት፡፡ ከዚያም ወደ ቶጎ ውጫሌ፤ ኬንያ ፤ ሞያሌ ፤ ጅቡቲ በመጓዝ እቃዎችን እያመጣ የመሸጡን ስራ ጀመረ፡፡

የራስን ድርጅት መክፈት

አቶ መሰረት እንደሚናገረው ይህን ሁሉ ሲሰራ ነገሮች አልጋ በአልጋ አልነበሩም፡፡ በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጦ ነው ለስኬት የበቃው፡፡ በረሀ ለበረሀ ከመንከራተቱ ሌላ ሙቀቱ ፈትኖታል፡፡ ነገር ግን ይህን ሁሉ ተቋቁሞ አንድ ቀን ትልቅ ቦታ ሊደርስ እንደሚችል በልቡ ያምን ነበር፡፡ ከ1983-1994 ለ 11 አመታት እንዲሁ የራሱን ኩባንያ ሳይከፍት ሲጥር ከቆየ በኋላ በ1994 ቤዝ ኢትዮጵያ ድርጅቱን በይፋ መመስረት ችሏል፡፡ በአሁኑ ሰአት ቤዝ ኢትዮጵያ 21 አመት ያለፈው ድርጅት ሲሆን ለበርካታ ዜጎችም የስራ እድል የፈጠረ ተቋም ነው፡፡ አቶ መሰረት በ1990ዎቹ ቤዝ ኢትዮጵያ የተሰኘ ሱፐርማርኬት ነበረው፡፡ ከዚህ ሱፐር ማርኬት ስም በመነሳት ነበር ለድርጅቱ ስም ያወጣው ፡፡ አቶ መሰረት በጊዜው የመኪና ማከራየት ስራዎችንም ይሰራ ነበር፡፡

የሳኡዲው ኤግዚቢሽን

አቶ መሰረት ከዛሬ 23 አመት በፊት ካከናወናቸው ታላላቅ ተግባራት አንዱ በሳኡዲ አረቢያ ያዘጋጀው ኤግዚቢሽን ይጠቀሳል ፡፡ የሀሳቡ ፍሬ ነገርም የንግድ ተቋማት ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት እድልን ማመቻቸት ነበር፡፡ በዚህ ኤግዚቢሽን በአቶ መሰረት አስተባባሪነት ከተሳተፉት ድርጅቶች ውስጥ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ፤ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ፤አያት መኖሪያ ቤቶች ይገኙበታል፡፡ አቶ መሰረት እንደሚያስታውሰው እነዚህ ድርጅቶች ከኤግዚቢሽኑ ብዙ ጥቅም አግኝተዋል፡፡ ታዲያ አቶ መሰረት ይህን ጥረት በማድረጉና ጥረቱም ፍሬ በማግኘቱ በሳኡዲ አረቢያ ልዩ ተሸላሚ ለመሆን ችሎ ነበር፡፡በነገራችን ላይ አቶ መሰረት በዚህ ስራ ላይ ትልቅ ኪሳራ ገጥሞት ነበር፡፡ ይልቁንም በዚህ ስራ መልካም ስም ማግኘት ችሏል፡፡

ጠንክሮ መቀጠል

የስራ ፈጣሪው አቶ መሰረት በመቀጠል ከሌሎች ባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት ጥራጥሬ ፣ የቅባት እህሎች፣የስጋ ውጤቶችና ቅመማ ቅመም ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ቀጥለውም በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ፤ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በሪል ስቴት ፕሮጀከት ፣ በመኪና ኪራይ በህንጻ ሽያጭና ኪራይ በአስመጪነትና ላኪነት የተሰማሩ ሀገር በቀል ድርጅት ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡ አቶ መሰረት በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ በ130ሚልዮን ብር ካፒታል የታይልስ ፋብሪካ ያቋቋመ ሲሆን ይህም ፋብሪካ ለ230 ሰዎች የስራ እድል መፍጠር የቻለ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት አቶ መሰረት 15 የትራንስፖርት ተሸከርካሪዎች ፤ በአዲስ አበባም በኩባንያው ስር የተመዘገቡ የ3 ህንጻዎች ባለቤትም ለመሆን የቻለ ነው፡፡

በ500 ብር የተጀመረው የአቶ መሰረት ቢዝነስ በአሁኑ ሰአት 10ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መድረስ ችሏል፡፡

ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ሆቴል

አቶ መሰረት በልማት ስራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሽልማት በልዩ ልዩ ጊዜያት ተበርክቶለታል፡፡ አቶ መሰረት ከ 3 አመት በፊት በ2013 ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ሆቴልን ለመጀመር ሀሳብ ያደረገበት ቀዳሚው ምክንያት በቱር ኤንድ ትራቭል የሚመጡ የቤዝ ኢትዮጵያ እንግዶችን በወጉ ለማስተናገድ እንዲያመቸው ነበር፡፡ የራስን እንግዳ ራስህ በሰራኸው ሆቴል ማስተናገድ አስፈላጊ ስለሆነ ሆቴሉን ጀምረናል ይላል አቶ መሰረት፡፡

በጎ አድራጎት እና ልማታዊ ስራዎች

አቶ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባቀረበለት ጥሪ መሰረት ለአቅመ-ደካሞችና ለድሀ ድሀ ነዋሪዎች የሚያገለግሉ ቤቶች ሰርቶው አስረክቧል፡፡ በተጨማሪም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ-ከተማ የባለሀብቶች ኮሚቴ በመሆን 180 ቤቶችን ለመገንባት ችሏል፡፡ ለድሀ ድሀ 4 የዳቦ ፋብሪካዎችን በ87 ሚሊዮን ብር አቋቁሟል፡፡

ከሸገር ዳቦ ፋብሪካ ጋር በመዋዋልም በቀን 30ሺህ ዜጎች ዳቦ እንዲያገኙ በማድረግ የአቶ መሰረት አስተዋጽኦ ትልቅ ነበር፡፡ከዚህም ባሻገር የሸገር ዳቦ ሱቆችን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ-ከተማ በሚገኙ 13ቱም ወረዳዎች እንዲገነባ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም በ90 ቀን ሰው ተኮር ፕሮጀክት ባለሀብቶችን በማስተባበር አቶ መሰረት ለሀገር የሚጠቅም በጎ ተግባር ማከናወን ችሏል፡፡

አቶ መሰረት ከሰራቸው በጎ ልማታዊ ስራዎች አንዱ የቱሉ ዲምቱን አደባባይ በ10ሚልዮን ብር ማስገንባቱ ነው፡፡

የስራ ፈጣሪው እና ለምንም አይነት ፈተና የማይበገረው አቶ መሰረት ከዘመናዊ አፓርታማዎች ባሻገር ከ 5 እስከ 10 አመታት ለሚሆን ጊዜ ከመንግስት ጋር በመሆን አንድ ሚሊዮን አነስተኛ እና ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ አቶ መሰረት እንደሚናገረው ይህን ግንባታ ለማከናወን የሚያስችሉ ሁሉንም ግብአቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ማምረት እንደሚቻል ይናገራል፡፡ ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል በ10 የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች እያንዳንዳቸው ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የቱሪስት የመዝናኛ ማእከላት የመገንባት ራእይ አለው፡፡

ቤተሰብ

አቶ መሰረት በ1992 ጋብቻ የመሰረተ ሲሆን ባለቤቱም ወይዘሮ ገነት ተፈራ ትባላለች፡፡ ወይዘሮ ገነት ተፈራ የምታበረታታ እና ከጎን የምትቆም ሚስት እንደሆነች አቶ መሰረት ይናገራል፡፡ እርሱ እንደሚለው ለእኔ ስኬት ቀዳሚዋ ተጠቃሽ ባለቤቴ ናት ይላል፡፡ አቶ መሰረት ልጆቹን ጥሩ አድርጎ አስተምሯል፡፡ የመጀመሪያ ልጁ ሊዲያ መሰረት 2 ዲግሪ ያላት ሲሆን የቤዝ ኢንተርናሽናል ሆቴል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናት፡፡ ሁለተኛ ልጁ የሊዲያ ተከታይም ጺዮንም በሆቴል ውስጥ በከፍተኛ የማኔጅመንት ቦታ ትሰራለች፡፡ አቶ መሰረት ልጆቹ ለቁምነገር በቅተው በዚህ መልኩ ሲያገለግሉ ሲመለከት ርካታው ይጨምራል፡፡ በልጆች በመባረኬ ደስ ይለኛል ሲልም ልጆቹን ያመሰግናል፡፡ የጥሩ ስነ-ምግባር ባለቤት የሆኑት ልጆቹ ሀገራቸውን በመልካም ጎን እንደሚያስጠሩም ሙሉ ለሙሉ ይተማመንባቸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *