ታሪክን በድምፅና በቪዲዮ ራዕዩ ምን ይመስላል?

እዝራ እጅጉ ወደ 18 ዓመት ገደማ በጋዜጠኝነት ሙያ ቆይቷል፡፡ ታሪካዊ ይዘት ያላቸው መሰናዶዎችን በተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎችና በማህበራዊ ሚዲያ ያቀርባል፡፡ ሙያው በአገሪቱ ታሪክ ተጠቃሽ ከሆኑ ታዋቂ ሰዎች ጋር ያገናኘዋል፡፡ ስለእነዚህና እሱ በዘመን ልዩነት ያልደረሰባቸው ታዋቂ ሰዎችን ታሪክ ሲያገላብጥ በብዛት የሚያገኘው የጽሑፍ ሰነዶችን ነው፡፡

ታሪካዊ ሰነዶች በድምፅና በቪዲዮ ያለመገኘታቸው ጉዳይ ክፍተት መፍጠሩንም አስተዋለ፡፡ በሥራው አማካይነት ከሰበሰባቸው የድምፅ ሰነዶች በተጨማሪ ከተለያዩ መገናኛ ብዝኃን የድምፅና የቪዲዮ ሰነዶች ማከማቸት ጀመረ፡፡እዝራ እንዲህ አይነት ታሪካዊ ስራዎችን በፍቅር ነው የሚሰራው፡፡ ስለሆነም በደስታ ስለሚሰራው ድካም የሚባል ነገር አይነካውም፡፡

ሰነዶቹን ሕዝብ እንዲገለገልባቸው በሚልም ተወዳጅ ሚዲያና ኮምዮኒኬሽን የተሰኘ ተቋም መሥርቶ ታሪክን በድምፅ (ኦዲዮ ሲዲ) ማቅረብ ጀመረ፡፡ ከ14 ዓመት በፊት በመሠረተው ተቋም ሥር ከድሬ ቲዩብ ጋር በመጣመር ከ50 በላይ የድምፅና የቪዲዮ የታሪክ መሰናዶዎች አሰራጭቷል፡፡ በማኅበረሰብ ድረ ገጽ ከ350,000 በላይ ሰዎች ከተከታተሏቸው የድምፅና ቪዲዮ ዘገባዎች መካከለል የአበበ ቢቂላ፣ የይድነቃቸው ተሰማና የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ታሪክ ይገኙበታል፡፡ ‹‹ተወዳጅ ሚድያ›› ሲመሰረት በ1996 አትራፊ በሆነው የሚድያ ፕሮሞሽን ስራ ላይ የተሰማራ ሲሆን በአሁኑ ሰአት ደግሞ ግለ-ታሪክ ላይ ሙሉ ትኩረቱን በማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡

ድርጅቱ በ2009 የታሪካዊ ሰነዶቹን ተደራሽነት ለማስፋት በሲዲ እያሳተመ ማቅረብ ጀመረ ፡፡ ‹‹ብዙዎች የድምፅና ቪዲዮ የታሪክ ሰነድ በቀላሉ አያገኙም ስለዚህ ታሪክን በድምፅና በቪዲዮ (ኦዲዮቪዥዋል) እያዘጋጀሁ ማሠራጨት ጀመርኩ፤›› ይላል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የማይዘነጋ አስተዋጽኦ ያበረቱ እንዲሁም በሥራዎቻቸው እሱንና ሌሎችንም ማነሳሳት የቻሉ ሰዎችን መርጦ ወደ ሥራ እንደገባ ያስረዳል፡፡

‹‹በታሪካቸውና በሥራዎቻቸው እኔን ያነቃቁ ሰዎችን መርጫለሁ፡፡ ሰዎቹ በመገናኛ ብዙኃን ምን ያህል ሽፋን ተሰጥቷቸዋል? የሚለውም መስፈርት ነው፤›› ይላል፡፡ በቂ ሽፋን አልተሰጣቸውም ብሎ ላመነባቸው ሰዎች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ታሪካቸው በድምፅና በቪዲዮ የሚቀርበው ሰዎች፣ ሽፋን ያገኙ ከሆኑ በብዙሀኑ ዘንድ ያልታየ የታሪካቸውን ገጽታ ይፈትሻል፡፡

በግንባር ቀዳሚነት የሕግ ምሁሩ ተሾመ ገብረማርምን ታሪክ በሲዲ ያሳተመ ሲሆን፣ በመቀጠል የጸሐፌ- ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ-ወልድ፣ የከያንያኑ ተስፋዬ ሳህሉና ተስፋዬ ገሰሰ እንዲሁም የቀድሞው የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮን ታሪክ ታትመዋል፡፡ እነዚህ በሲዲ የቀረቡ መሰናዶዎች ስለ ባለታሪኮቹ ምስክርነት የሚሰጡ ሰዎችን በማካተት የቀረቡ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ብዙም በሚድያ ያልተደመጡ የባለታሪኮቹ ድምጾች በሲዲው ውስጥ ተካተዋል፡፡

ሲዲዎቹ ‹‹የአገር ታላቅ ባለውለታ›› በሚል ስያሜ ቀርበዋል፡፡ ሲዲዎቹን ከባለታሪኮቹ ቤተሰቦችና ወዳጆች በተጨማሪ እንደ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ የኢትየጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ላሉ ተቋሞች እንዳበረከተ ይናገራል፡፡ በቡክ ላይትና በሊትማን የመጻሕፍት መደብሮች ደግሞ ለሽያጭ ቀርበዋል፡፡ ሲዲዎቹን ኦንላን ማግኘትም ይችላል፡፡

የተስፋዬ ሳህሉና ተሾመ ገብረማርያምን ታሪክ በሲዲ በማዘጋጀት ላይ ሳለ ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለዩ፣ ካለፉ በኋላ ታሪካቸውን ለሕዝብ አድርሷል፡፡ የቀድሞው የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮም ህልፈታቸው ከተሰማ በኋላ ነበር ታሪካቸውን በሲዲ ያቀረበው፡፡ የተስፋዬ ገሰሰ ግለ- ታሪክ የታተመው አምና ልደታቸውን ባከበሩበት ወቅት ነበር፡፡

የአገር ባለውለታ የሆኑ ሰዎች ታሪክ በአንድም በሌላም መንገድ ይመዘገባል፡፡ ሆኖም ለህብረተሰቡ የሚቀርበው በጽሑፍ መልክ ብቻ ሲሆን፣ በሰዎቹ ዙሪያ የተሠሩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በብዛት የሚገለገሉት ተመራማሪዎች ናቸው፡፡ ‹‹በየቤተ መጻሕፍቱና ገበያ ላይም በቂ የታሪክ መጻሕፍት አሉ፡፡ ነገር ግን በአንድ ጊዜ ብዙ ሰው ጋር በሚደርሰው የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ሲቀርቡ አይታይም፤›› ሲል ይገልጻል፡፡

በአገሪቱ ግዙፍ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ እንኳን የታላላቅ ሰዎች ድምፅና ቪዲዮ በቀላሉ አይገኝም፡፡ ማንኛውም ሰው ሊያገኘው በሚችለው ገበያ ሰነዶቹን ማግኘትም የበለጠ ይከብዳል፡፡ እዝራ እንደሚናገረው፣ የጽሑፍ መረጃን ማግኘት ለማይችሉ ወይም መረጃው በአጭሩ ተጠናቅሮ በድምፅና በቪዲዮ እንዲቀርብላቸው የሚፈልጉ ሰዎችን ታሳቢ በማድረግ ይሠራል፡፡

ዘመኑ ያመጣቸውን የድምፅና ቪዲዮ አማራጮች መጠቀም በአጭር ጊዜ መረጃ በስፋት በማስተላለፍ ረገድም ተመራጭ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ዘመኑ ከሲዲ ወደ ፍላሽና ወደ ሌሎችም መረጃ ማስተላለፊያዎች እያቀና በመሆኑ፣ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ‹‹ታሪክን በሲዲ›› ከሚለው ሐሳብ ወደ ‹‹ታሪክን በፍላሽ›› እንደሚሸጋገር ይገልጻል፡፡ ይህም ሲባል ፍላሾች በአነስተኛ ዋጋ ከቀረቡ ታሪክ በሲዲ እንደታተመው ሁሉ ታሪክ በፍላሽ ይቀርባል ማለት ነው፡፡

እስካሁን የታትሙትን የታሪክ ሲዲዎች በብዙ ሺህ ኮፒዎች አሳትሞ የማሠራጨት አቅም ባያገኝም፣ መድረስ አለበት ብሎ ያመነባቸው ቦታዎች አድርሷል፡፡ ለታሪክ ፍቅር ካላቸው ሰዎች ውጪ በርካታ ተቋሞች ሥራውን ስፖንሰር እንዲያደርጉ ማሳመን እንደሚከብድም ይናገራል፡፡ ነገር ግን በግብረ መልስ ረገድ፣ የድምፅ የታሪክ ሰነዶቹን ካገኙ መምህራንና ተመራማሪዎች ቀና አስተያየት ማግኘቱን ይገልጻል፡፡ ሰነዶቹ፣ በተለይም ጥናት የሚሠሩ ሰዎች የድምፅና ቪዲዮ ሰነድ በማግኘት በኩል ለሚገጥማቸው መሰናክል መፍትሔ እንደሚሆኑ ያምናል፡፡

የሰዎችን ታሪክ በድምፅና በቪዲዮ ወይም ሰዎቹ ያደረጓቸውን ንግግሮች ቅጂ ለማግኘት ውጣ ውረዱ ቀላል አይሆንም፡፡ ‹‹የታሪክ ሰነዶችን ማግኘት ጠለቅ ያለ ቁፋሮ ይጠይቃል፡፡ በአግባቡ ከተፈተሸ በብዙዎቻችን ጓዳ ብዙ ሰነዶች አሉ፤›› ይላል፡፡ እንደምሳሌ የሚያነሳው የጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ኃብተወልድን ታሪክ በሲዲ ለማዘጋጀት ከቤተሰቦቻቸው መረጃ ለማግኘት ሲሞክር ከጠበቀው በላይ ሰነዶች ማግኘቱን ነው፡፡ የድምፅ፣ የምስልና የቪዲዮ ሰነዶቹን ካገኘ በኋላ ታረካቸውን በድምፅ ብቻ ሳይሆን በቪዲዮ ለማቅረብም ይወሰናል፡፡

ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመተባበር የጀመረው የአንድ ሰዓት ዘጋቢ ፊልም በሦስት ወራት ተጠናቆ፣ ታኅሣሥ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በራስ ሆቴል ሊመረቅ ችሎአል፡፡ ይህ ዲቪዲ በዛ እለት ሲመረቅ የታደሙ ሰዎች ራእዩ ትልቅ መሆኑን መስክረዋል፡፡ በተጨማሪም ባለራእዩ እዝራ ብዙ መስራት እንደሚችል ተስፋ ተደርጎአል፡፡ ‹‹የጸሐፌ- ትዕዛዝ አክሊሉ ታሪክ በ2008 ፤ለ45 ደቂቃ ያህል በቪድዮ ተሰርቶ ነበር፡፡ ተወዳጅ ሚድያ ይህን ታሪክ በድሬ- ቲዩብ ሲያስተላለፍ 60,000 ሰዎች ተመልክተውታል፡፡ ቪዲዮውንና ሌሎች የሰበሰብኳቸው ሰነዶችንም ወደ ፊልም ለመለወጥም ወሰንኩ፤›› ሲል ይገልጻል፡፡

የቪዲዮ መረጃ በሚያሰባስብበት ወቅት ከቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ክምችት ክፍል ቪዲዮዎች መግዛቱን ይናገራል፡፡ የጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ታሪክ በድምፅ በማኅበረሰብ ድረ ገጽ ከተለቀቀ በኋላ ብዙዎች ዘንድ መድረሱም፣ ታሪካቸውን በቪዲዮ ለማቅረብ ሥራ መጀመሩን የሰሙ ሰዎች በተለያየ ወቅት የሰበሰበቧቸውን መረጃዎች ይሰጡት ጀመር፡፡ ‹‹የአክሊሉ ማስታወሻ››ን የጻፉት ዶ/ር ጌታቸው ተድላ ደግሞ በፊልሙ አማካሪነት ተሳተፉ፡፡

የተለያዩ አገሮች መገናኛ ብዙኃን ከጸሐፌ- ትዕዛዝ አክሊሉ ጋር ያደረጓቸው ቃለ- መጠይቆች ቪዲዮዎችን በፊልሙ እንዳካተተ ይናገራል፡፡ በቀጣይ ፊልሙ በእንግሊዘኛ ትርጓሜ (ሰብ ታይትል) በድጋሚ የሚታተም ሲሆን፣ የሰበሰባቸውን ሰነዶች በመጽሐፍ እንደሚያወጣም ይናገራል፡፡ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ የዓለም አቀፍ የቴሌኮምዩኒኬሽን ዩኒየን የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊ ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅን ታሪክ ጨምሮ የ25 ግለሰቦችን ታሪክ እንደሚያሳትምም ያክላል፡፡

ከድምፅ ሲዲዎች በተጨማሪ የኢንጂነር ተረፈን ግለ ታሪክ በመጽሐፍ ያሳትማል፡፡ የ‹‹አካፑልኮ ቤይ›› ፊልም ትርጉም መጽሐፍና ‹‹ኔትወርክ ማርኬቲንግ›› ከዚህ ቀደም ለንባብ ካበቃቸው መጻሕፍት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ሥራው ያን ያህል ትርፋማ ባያደርግም፣ ታሪክን መሰነድ የሁሉም ሰው ኃላፊነት በመሆኑ፣ ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች ዘርፉን ቢቀላቀሉ መልካም ነው ሲል ይናገራል፡፡ በተለያየ ሙያ ውስጥ ያሉ ሰዎችም ታሪካቸውን ይፋ በማውጣት መሳተፍ እንዳለባቸውም ያክላል፡፡ ‹‹ታሪካቸውን በድምፅና በቪዲዮ መቅረፅና ማስቀመጥ አለባቸው፤›› ይላል፡፡

በድምፅና በቪዲዮ የሚቀርቡ ታሪኮችን በቤተ- መጻሕፍት ከማስቀመጥ ባለፈ፣ ኅብረተሰቡ ታሪኮቹን የሚከታተልበት መንገድ መመቻቸት እንዳለበት ያምናል፡፡ በቀጣይ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምርና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ የድምጽና የቪዲዮ የታሪክ ሰነዶች ተደራሽ እንዲሆኑ፣ የሲዲ ማጫወቻ የማበርከት ዕቅድ እንዳለውም ያክላል፡፡







Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *