ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል ፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ዲፕሎማት ፣ደራሲ እና ፈላስፋ የሆኑት ራስ ካሳ ኃይሉ ይነሳሉ ። በአድዋ እና በማይጨው ጦርነት ውጊያ አውድማ ላይ የነበሩት ራስ ካሳ ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴን በማማከርም ትልቅ ውለታ ውለዋል። ዕዝራ እጅጉ እና ባንቺአየሁ አሰፋ የህይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንደውታል።
ልጅነት
ዓለማዊውን ሥርዓት የናቁ መንፈሳዊው የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት ሹም፤ ከፍተኛ የጦር አዛዥና መሪ፤ የዲፕሎማሲ ባለሙያ፣ የንጉሰነገስቱ አማካሪ፣ የቤተመንግስቱ ሁለተኛ ቁልፍ ሰው፣ ደራሲ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ።
እንዲህ እንደዛሬው ሳይሆን ቀደም ባለው ዘመን ግዛትን የሚያስተዳድር፤ ሀገርን የሚመራ ሹም ፈሪሐ እግዚአብሔርን የያዘና ጠቢብ ነበርና እሳቸውም ናቸው።
ራስ ካሳ በወሎ ክፍለሀገር በላስታ ምድር ሙጃ 1873 ዓ.ም ነበር የተወለዱት። በኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግስት ግንባታ ሂደት ታላቅ ሚና የነበራቸው ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ ከተወለዱ 143 ኛ ዓመታቸው ህዳር 3 2016 ዓ.ም ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ራስ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ ወዲህ መስፍን ወዲያ ሀይማኖተኛ ናቸው። ታላቅ ስብዕናን የተላበሱ የሹም ልጅ ሹም፣ በቤተክህነት ሥርዓት ያደጉና የተማሩ የሀገረ-መንግስት እውቀትን ከና በጧቱ ከአባታቸው ደጃዝማች ኃይሉ ወልደኪሮስ እግር ስር የተማሩ። ከአፄምኒልክ አጎት ራስ ዳርጌ በኋላም በአጤ ምኒልክ ቤት ገብተው እውቀትን ከባህሩ የጨለፉ ናቸው።
ልዑል ራስ ካሳ አስተዋይና ብልሃተኛ መሪ ሲሆኑ መንፈሳዊውን ዓለም ከዓለማዊው ጋር አጣምረው መጓዛቸው አጀብ ሳያሰኝ አልቀረም።
ልዑሉ የበጌምድር ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ በነበሩበት ወቅት ከዱበር እስከ መተማ ያለውን ግዛት አስተዳድረዋል። እንኳን ሰው እግር ይጋጫልና የጠቅላይ ግዛቱ ነዋሪዎች ፍርድ እንዳይጓደልባቸውና በዳይና ተበዳይ ቂም ቋጥሮ እርስበእርሱ እንዳይጫረስ መዘገብ ይዘው የዳኝነት የተቀመጡ ናቸው።
በኋላም ምዕራባዊያን ሀገራት አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሲከፋፈሉ በፋሺስት ኢጣሊያ መዳፍ ገብታ የመመተር እጣ የደረሳት ኢትዮጵያ ነበረች። በወቅቱ ማለትም 1888 ዓ.ም. ” ወረኢሉ ከተህ ባላገኝህ ማሪያምን አልምርህም ” የሚለው የአጤ ምኒልክ አዋጅ ከጫፍ ጫፍ ሲያስተጋባ የጦር ነጋሪቱን ጎስመው የሀገሪቱን የከፍተኛው ጦር ይዘው የዘመቱት እኒሁ ራስ ካሳ ሀይሉ ስለመሆናቸው የታሪክ መዛግብቶች ይመስክራሉ።
ታሪክን በትክክል ሰንዶ የማስቀመጥ ልምዳችን ደካማ በመሆኑ ብዙ ማህደሮችን ለማጣቀስ አስቸጋሪ ቢሆንም በወቅቱ ገና በ15 ዓመታቸው በወርሃ መስከረም 1888 በአድዋ ጦርነት ላይ በተንቤን ጦር ግንባር ዘምተው ከልዑል ራስ ስዩም ጋር የተዋጉ ብላቴና ነበሩ።
ራስ ካሳ ኃይሉ ዋና አዛዥ በመሆን በዚህ ጦርነት ሲዘምቱ በኮሎኔል አዲቫ የተፃፈው ቀዩ አምበሳ ከ 45 ሺ እስከ 50 ሺህ የሚደርስ የጦር ሰራዊት ይዘው መዝመታቸውን ያነሳል።
የልዑሉ ዋና የጦር አማካሪ ሆኖ የዘመተው አዶልፍ ፖስላክ የሀበሻ ጀብዱ መፅሐፍ ደራሲ ከ150 ሺህ በላይ የጦር ሰራዊት ይዘው መዝመታቸውን የሚያትት ሲሆን በሌላ በኩል ደጃዝማች ከበዴ ተሰማ ቀዩ አምበሳን በሚደግፍ መልኩ ከ 45 እስከ 50 ሺህ የጦር ሰራዊት ይዘው መዝመታቸው ላይ ይስማማሉ።
በ2ኛው የማይጨው ጦርነት ወቅት ራስ ካሳ ኃይሉ ሀገራቸውን ከጠላት መንጋጋ ለማስጣል ሲሉ በጦር ዋና አዛዥነት ከቀዳማዊ አፄ ኀይለስላሴ ቀጥሎ 2ኛ ሰው በመሆን መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም የጦር ሰራዊቱን ብቻ ሳይሆን 3 ወንድ ልጆቻቸውን ማለትም ደጃች ወንድወሰን ካሳ ፣ ደጃች አበራ ካሳ፣ ደጃች አስፋወሰንን ካሳ ጨምረው ነበር የዘመቱት።በዚህ የ 5 ዓመት ጦርነት ፓልዋሪና ቀጨም መልፋ በተባለ ቦታ የካቲት 11 ቀን 1928 ከጠላት ጋር ውጊያ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ትጥቁ በሌለበት የጣሊያንን የ40 ዓመት የበቀል ጦር ዝግጅት ባደረገበት ራስ ካሳ ባለቸው እውቀት ተጠቅመው ጦሩን ለመከላከል ችለዋል። ይሁን እንጂ በጦር ሚኒስትሩና በጦሩ ዋና አዛዥ አማካኝነት በተፈጠረ መፍረግረግና አለመግባባት የተነሳ በአምባራዶ ጦርነት ላይ ሚንስትሩ ራስ ሙሉጌታና ልጃቸው እያፈገፈጉ ሳለ ህይወታቸው አልፏል።
በዚህ ጦርነት ከኢትዮጵያ ከ 275 ሺህ በላይ ተዋጊ ሲገደል ከማሽ ሚሊዮን በላይ ጦረኛ ቆስሎሏል። ከፋሽስቱ ጣሊያን በኩል 208 ሺህ ወታደር ሙትና ቁስለኛ ሆኗል።
ራስ ካሳ ከጣሊያን ጀት በሚዘንበው የእሳት ነበልባል ወታደሮቻቸውን ላለማስፈጀት በተጠቀሙት ታክቲክ ከጦር ድብደባው ተርፈው ከአፄ ኃይለስላሴ ጦር ጋር መደባለቅ ችለዋል።
ይሁን እንጂ ደጃዝማቾቹ ልጆቻቸው በአዲስአበባ በመሸገውና 3000 ኢትዮጵያውያንን በአሰቃቂ ሀኔታ በጨፈጨፈው ፋሽስት ላይ ጥቃት ያደረሱ ሲሆን ሁለቱ ወንድማማቾች ደጃዝማች አስፋወሰንና ደጃዝማች አበራ በጣሊያን የጦር ሰራዊት ተይዘው ሲገደሉ ወንድማቸው ደጃዝማች ወንደሰን ካሳ ወደላስታ ሸሽቶ ከፋሽስቱ እየታገለ ባለበት ወቅት በላሊበላ ጥራሪ በተሰኘ ወንዝ ላይ እንደተሰዋ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ።
ደጅ አዝማች ወንደወሰን ካሳ ከሞተ በኋላ በላስታ ምድር ኩልመስክ በምትባል ቦታ የሚገኘው የጥርብ ድንጋይ ሕንጻ መኖሪያው ወደ ትምህርት ቤት ተቀይሮ በዛሬው ጊዜ ወንደወሰን ካሳ አንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ት/ቤት በመባል ይታወቃል።
የአፄ ኃይለስላሴ ኢትዮጵያና የህይወቴ እርምጃ በተሰኘው ቁጥር 1 መፅሐፋቸው ላይ 1928ቱ የኢትዮጣሊያን ጦርነት ራስ ካሳ በአቢያዳና በአርባወያኔ ድል ማስመዝገባቸውን መስክረውላቸዋል።
ራስ ካሳ የንጉሰ ነገስቱ አፄ ኃይለስላሴ አማካሪና የቤተመንግስቱ ሁለተኛ ሰው የነበሩ ሲሆኑ አንዳንዴም ሲሶ መንግስት እየተባሉም ይጠራሉ።
ሀገር ወዳድና ቁጥብ ራስ ለሀገር ክብር ወልዶ ገባር ራስ ካሳ ኃይሉ የሀገር ራስ ናቸው።
በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያውያን ጠበቃ ናታን ማርቪንና ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ በኢየሩሳሌም በ1928/1929 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን መያዙን ተከትሎ በኢየሩሳሌም ያለውን የኢትዮጵያ ገዳም በእጁ ለማድረግና የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ እንዳይውለበለብ ለመከልከል በፓልስታይንና በእንግሊዝ ባለስልጣናት በመታገዝ እንቅስቃሴ ጀመረ።
በዚህ ጊዜ ራስ ካሳ ኃይሉ ከለንደን ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣት በኢትዮጵያ ገዳም ጉዳይ ከስደተኛው ማህበርና ከተለያዩ ወገኖች ጋር ተነጋገሩ።
በጉዳዩ ላይ ከተወያየን በኋላ ደጃዝማች መኮንን እንዳልካቸው፥ እኔ አዛዥ ከበደ ተሰማና ልጅ ታምራት ይገዙ ከእስራኤላዊው ጠበቃ ናታን ጋር ተገናኝተን በጉዳዩ ላይ እንድንወያይ ተወሰነ።
በመጨረሻም ጠበቃችን በኢየሩሳሌም ከተማ ባለስልጣኖች ላይ ክስ በማቅርብ የኢየሩሳሌም ባለስልጣናት ከእንግዲህ በኋላ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን መብትንና ጥቅም እንዳይነኩ የሚል ውሳኔ ፍ/ቤቱ እንዲሰጥ አደረገ። በማለት ደጃዝማች ከበደ ተሰማ የታሪክ ማስታወሻ በሚለው መፅሐፋቸው ላይ ኸገጽ 184-194 ሰፍሮ ይገኛል።
የራስ ካሳ ኃይሉ የቅርብ ቤተሰብ የሆነው የህግ ባለሙያ ሰለሞን ተሾመ ረታ እንደሚናገረው በልጃቸው ባለቤት በፊት አውራሪ ነብዬ ልዑል 1933 ዓ.ም በእጅ ተፅፎ ገና ያላለቀና ያልታተመ ታሪክ ረቂቅ ፅሑፍ እንዳለ ይገልጻል ።በ ገፅ 191 ያለውን ደብዳቤ እንዲህ ይነበባል ።
ደብዳቤ 1፦ ” አስራተ ቦረና በኢጣሊያ ጦር ይዝመት የተባለጊዜ የተላከ። ትላንት አስራተ ከጀነራል ዊንጌት ጋር ቦረና እንዲዘምት ስለተነጋገርነው ተሰልፎም አሰልፎም የማያውቅ ልጅ በመላክ የእኔ መቅረት አግባብ አይደለምና ለትዕዛዙ አጋፋሪ ያረጋል ይጨመርበትና ካሚዮንም እዚያ ላለው ሰው ይታዘዝና እኔም እንዲሄድ ለመነጋገር ጠዋት እመጣለሁ። “
ደብዳቤ 2:- ከልዑል ራስ ካሳ፦ ይድረስ ለበላይ ዘለቀ ጃንሆይ ለሹም ትዛዝ ተላልፎለታልና ቀድሞ ይቆይሀል ብለውኝ ይሄንኑ ቃል ሰምቼ መጥቼ ነበር። አንተ ግን አጣሁህ እንጂ በእግዜአብሔር ቼርነት ግንቦት 8 ቀን ተዋግተን አስለቅቀን ያያ ከተማ ገብተናል። እዚህ ከደረስን በኋላ ግን ኢጣሊያኑ ሸሽቶ ወደ ጎበና ስለሄዴ ይሄው እኛም ተከታትለን አንተም በፍጥነት መጥተህ ለግንቦት ሚካኤል ጫቃታ እንዳንገናኝ ይሁን። ግንቦት 8 ቀን 1932
ደብዳቤ 3፦ ይድረስ ለልጅ በላይ ዘለቀ ከጣሊያ እኛ ተጋጥመን ጎበጅን አስለቅቀን ተከፋፍለነዋልና በአንተ በኩል የምትሰራውን እስክንልክብህ ድረስ ወደዚህ መሻገርህ ቆይቶ ተሰናድተህ ከዚያው ከሀገርህ ላይ እንዲትጠባበቅ ይሁን። ” ግንቦት 10 1933 ዓ.ም ገፅ 198 “
የልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ ያልታተመ ረቂቅ የተገኙት ደብዳቤዎች ከራሳቸው የጦሩ ሽማምንት የተላኩ ናቸው። ይህ ማለት ራስ ካሳ ኢትዮጵያ ነፃ የወጣች ቢሆን ቀሪ የማፅዳት ሥራዎችን ከኋላ በመሆን ይሰሩ እንደነበር ያመላክታል።
የግል ህይወት
ቀደም ባለው ዘመን የነበሩ የሀገር መሪዎችና ሹማምንቶች ፀሐፈ ትዕዛዛትና ባለቅኔ መሆናቸው የሚታወቅ ነውና እንደሌሎቹም ራስ ካሳ ፀሐፊ ነበሩ።
በአፄዎቹ ጊዜ « ፍኖተ አዕምሮ » የሚል አርዕስት ያለው መፅሀፍ እንደተደረሰ ይነገራል ። ይህም መፅሐፍ ስለ ቤተሰብ፣ እምነት፣ ልጆች አስተዳደግ፣ ስለ መልካም ባህርይ ግንባታ ወዘተ ብዙ ነገሮችን የሚያስተምር ነው።
ይህ መፅሐፍ የአፄ ምኒልክ አጎት የራስ ዳርጌ ሣህለሥላሴ ልጅ ወ/ሮ ትሰሜ ዳርጌ ልጅ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ የተፃፈው ፍኖተ አዕምሮ መፅሐፍ የተፃፈው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግስት ነበር፡፡
ልዑሉ በአጠቃላይ ወደአምስት መጽሓፍት እንደፃፉ የሚነገር ሲሆን ይህኛዉ በክርስትና አስተምህሮት ላይ የሚያተኩር ፣ በ301 ገፆች የተቀነበበ ታዋቂ ስራቸዉ ነዉ፡፡
ልዑሉ የኢትዮጵያ ራስ ራስ ካሳ ሀይሉ ዓለማዊ ሹመት ሽረት እንዳለበት አልዘነጉም። ቤተክርስቲያንን ሲሳለሙ ከባለሥልጣኑ ይልቅ ለምስኪን የኔ ቢጤው እጅ የሚነሱ ትሁት ነበሩ።
ራስ ከሳ ከአዛኝነታቸው የተነሳ በአንድ ወቅት አንድ ዛፍ ከጓሮው ሲቆርጥ የተመለከቱትን ሰው እንዲህ ብለውት ነበር ይባላል ” እንደው ልጄ ይሄንን ስትቆርጥ ሌላ ተክለሃል? ካልተከልክ እኔ እልክልሃለሁ ትከል” ዓለምን ስትረዳት ለራስህ ሳይሆን ለፍጡራኑ ሁሉ ታስባለህ። እሳቸው የሹመት ሞተሩን በመዳፋቸው ስላስገቡ ብቻ አዛዥ ናዛዥ ልሁን አላሉም። ሹም ሽረት ለማይነካው ፈጣሪ ተግተው ይፀልዩ ነበር ሲል የቅርብ ቤተሰባቸው ሰለሞን ተሾመ ረታ ይናገራል።
ውስጡን ለቄስ የሚለውን የሀገር ብሂል እንያዝና የዘውዱ የቅርብ ሰው ራስ ካሳ ለታይታ፣ ለዝና፣ ለጭብጨባ ሲሉ ከሹም ጋር ሲያሸረግዱ አይታዩም ነበር። እሰይ አበጀህ ለሚላቸው ሳይሆን ይቅር ለአምላክ የሚሉ በጎ ረው ናቸው። በትዳር ህይወታቸውም ገና ከመጀመሪያው በሐይማኖታዊ ሥርዓት ያገቡ ቁጥብ ሰው ናቸው።
ታሪክን በልጆቻቸው ደም የፃፉት ራስ ካሳ ዞሮ ከቤት ኖሮ ከሞት አይቀርምና ብሞት እንኳን ሞቴን በ” ዜጋበል ” ያድረገው አሉ። በኋላም ወደዜጋበል ሄደው በዚያ በልብ ህመም ሳቢያ በ1949 ዓ.ም ከድካማቸው አረፉ።
**
ያለፉትን መዘከር ላለነው ህያውያን ያልበከነ ዕድል ነውና እነሆ ራሳ ካሳ ኃይሉ