ኢያሱ አለማየሁ

ኢያሱ አለማየሁ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
እስከ ዛሬ 310 ሰዎችን ኣፈላልገን ታሪካቸውን ሰንደናል፤ ለወደፊትም በዚህ ስራችን ጠንክረን እንቀጥላለን፡፡ በ 2014 “የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ” በማለት ታሪኮችን ዳጎስ ያለ ጥራዝ የወጣውን መጽሃፍ አሳትመን ያሰራጨን ሲሆን፤ ባለታሪኮቹን ጨምሮ፤ ብዙ ሰዎች ማጣቀሻ ሰንድ እያደረጉ እንደሚጠቀሙበት መረጃ አለን። በዚህም ተበረታትተናል።

ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ “ምን ታሪክ አለኝና?” የሚሉና ታሪካቸው በስፋት ተደራሽ ያልነረ፤ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን፤ የህይወት ገጽ እያስነበብን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ የበርካታ ባለመልካም ተሞክሮ ዜጎችን ታሪኮችን መሰነዳችንን እንቀጥልበታለን፡፡ በህይወት የማይገኙትን አበርክቶም ለማስነበብ የተቻለንን እናደርጋለን፤ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ነው ብለን ስለምናምን፡፡ መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡

ከባለታሪኮቹ መካከል ኢያሱ አለማየሁ ወይም ሀማ ቱማ ነው፡፡ በኢቢሲ ሲታይ የነበረው ግራና ቀኝ ወይም የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ ድራማ ደራሲ ሀማ ቱማ ነው፡፡ ሀማ ቱማ መኖሪያውን በአሁኑ ሰአት በፈረንሳይ ሀገር ያደረገ ሲሆን በርካታ የድርሰት ስራዎችንም በእንግሊዝኛ እና በአማርኛ በመድረስ ይታወቃል፡፡ የህይወት ታሪኩንም እዝራ እጅጉ እና አማረ ደገፋው እንደሚከተለው አጠናክረውታል፡፡ “ ሁሉም ሰላም ነው” ባዩ አብዮተኛ ጸሐፊ
አንድ የሀገሩን ፖለቲካ ነገሬ ብሎ የያዘ ደመ ፍሉ ወጣት… ስልጣን ላይ ያለን አገዛዝ ለማውረድ ፓርቲ መስርቶ፣ ትጥቅ አንግቶ ሲታገል ቆይቷል። ይሄው ትግሉ ቀጥሎ በአንድ ወቅት በኤርትራ እና ትግራይ መካከል ባለ አንድ መንደር አደረሰው። እግሩ በረገጣት መንደር ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በሰላምታ ልውውጣቸው መሃል ‘ሁሉም ነገር ሰላም ነው’ ለማለት “ሃማ ቱማ” ሲሉ ይሰማል። እንግዳ ቃሉን በልቡ ፃፈ። በኋላ ጠመንጃውን ለአፍታ አውርዶ በብዕሩ ለፃፋቸው ስራዎቹ የብዕር ስም ሲፈልግ ‘ሁሉም ነገር ሰላም ነው’ ማለት አማረው እና “ሃማ ቱማ” ብሎ በመጽሐፎቹ ተገለጠ። ተወዳጅ ሚዲያ ደግሞ ሃማ ቱማን ለመጀመሪያ በመዝገብ ስሙ ገልጦ፣ እያሱ አለማየሁ ብሎ ታሪኩን ይሰንዳል።

እያሱ አለማየሁ ግንቦት 19 ቀን 1949 ዓ.ም በአዲስ አበባ ነው ውልደቱ። የቤቱ አራተኛ ልጅ ሲሆን ነጋዴ እና አስተርጓሚ የነበሩት አባቱ አለማየሁ አስፋው ገና የ8 ዓመት ልጅ እያለ መሞቱን ተከትሎ ‘ህይወቴን ቃኘችው’ የሚላቸው እናቱ እህትአፈራሁ ኃይለማርያም አሳድገውታል። ዘመናዊ ትምህርት ከመጀመሩ አስቀድሞ ቄስ ትምህርት ቤት ዘልቆ የኔታ እግር ስር ቁጭ ብሎ ፊደል ቆጥሯል። በመቀጠል፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን አርበኞች ትምህርት ቤት ከተከታተለ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጨርሷል። የኔታ ከፊደል ጋር ካስተዋወቁት ዕለት ጀምሮ ንባብ መዝናኛው ሁኗል። ንባቡ ቋንቋ የገደበው አልነበረም፤ በአማርኛም በእንግሊዝኛም የተፃፉትን መጽሐፍትን አንብቧል። ‘መጽሐፍት ማንበብ ጀምሮ ማቆምን እንደ ሃጥያት እቆጥራለሁ’ የሚለው ደራሲ ኢያሱ በተለይ ተፈሪ መኮንን እየተማረ በቤተ- መጽሐፍቱ በኩል ንባቡን አጠንክሯል። በማስከተል በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብቶ የከፍተኛ ትምህርቱን ቀጥሏል። እያሱ ዩኒቨርስቲውን ከመቀላቀሉ አንድ ዓመት ቀድሞ የተማሪዎች አመጽ ተቀስቅሶ፣ የዩኒቨርስቲው የተማሪዎች ማህበርም ተመስርቶ ነበር። በዚህም እያሱ ወደ ፖለቲካው የገባው ልክ ዩኒቨርስቲውን እንደተቀላቀለ ነበር።

ከአንድ ዓመት የዩኒቨርስቲ ቆይታው በኋላም የህግ ትምህርት ቤትን ተቀላቅሎ ጎን ለጎን ደግሞ የፖለቲካ ተሳትፎውን ቀጥሎ ንጉሱን ሲቃወም ከቆየ በኋላ ይህ ተሳትፎው የህግ ትምህርቱን ሳያጠናቅቅ ገና የአራተኛ ዓመት ተማሪ እያለ ከዩኒቨርሲቲው እንዲሰናበት አድርጎታል። መባረሩን አምኖ ተቀብሎ ይግባኝ ሳይል እስከ አራተኛ ዓመት ድረስ ህግ መማሩን የሚጠቅስ መሸኛ ደብዳቤ ብቻ ቢጠይቅም ማግኘት አልቻለም። ከትምህርቱ የተባረረው እያሱ ሙሉ ለሙሉ ትኩረቱን ፖለቲካው ላይ አደረገ። ይሳተፍበት የነበረውን የተማሪዎች ንቅናቄ ዓለም እንዲያውቀው እና የትጥቅ ዝግጅት አድርጎ ጠንከር ብሎ ወደ ትግል ለመግባት ከትግል አጋሮቹ ጋር አንድ ጠንከር ያለ መላ ዘየዱ። አውሮፕላን ጠልፎ ከሃገር መውጣት።

እያሱ ብርሃነ መስቀል ረዳን ጨምሮ ከገዛኸኝ እንዳለ፣ አማኑኤል ገብረ እየሱስ፣ አብዲሳ አያና እና ቢንያም አዳነ ጋር በመሆን ከባህር ዳር ወደ ጎንደር ይጓዝ የነበረን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ጠልፈው ሱዳን ገቡ። በዚያ ለስድስት ወራት ከታሰሩ በኋላ በነፃ ተለቀቁ። ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት በወቅቱ የነበረውን የሱዳን መንግስት አውሮፕላን ጠላፊዎቹን አሳልፎ እንዲሰጠው ካልሆነ ከሀገር እንዲያስወጧቸው በጠየቀው መሰረት ከሱዳን ተባረሩ። ከሱዳን ያለምንም የእነርሱ እውቅና አልጀሪያ ተወሰዱ። የአልጀሪያ ቆይታቸው አስቸጋሪ ቢሆንም ከሌሎች ሀገራት የነፃነት ታጋይ ቡድኖች ጋር ጥሩ ልምድ መለዋወጣቸውን እያሱ ዛሬም ያስታውሳል። ከ 3 ዓመታት በላይ በአልጀሪያ ከቆየ በኋላ ወደ ሱዳን ተመለሰ።

የተማሪዎች ንቅናቄ አድጎ ወደ ፓርቲ ሲያድግ እያሱ በእዚያ ነበር። የኢህአፓ መስራች እንደሆነ ይናገራል። የእያሱ የፓርቲ ተሳትፎው በከተማ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን አሲምባ ዘልቆ ከሰራዊቱ ጋር በአፈሙዝ ታግሏል። “ማንን እንደመታሁ አላውቅም እንጂ ተኩሻለሁ” ይላል። ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላም አሁንም “ኢህአፓ ነኝ” ይላል። እ.ኤ.አ በ1993 ቢቢሲ ራዲዮ የአጭር ልቦለድ ውድድር ያወጣል። ሱዳን ሁኖ ይህንን የሰማው ኢያሱ አጭር ልቦለድ ፅፎ ተወዳደረ። የረዥም ጊዜ የንባብ ልምዱ አግዞት ይሁን በፖለቲካው ተመስጦ ያላስተዋለው ተሰጥዖው ረድቶት አሸነፈ። 75 ፓውንድ ተሸለመ። መፃፍን በቁም ነገር ስራዬ ብሎ የያዘው ከዚህ ውድድር በኋላ ሳይሆን አይቀርም።

ሌሎች ታሪኮችን እዚያው ሱዳን ሁኖ ከፃፈ በኋላ በአንድ ኬንያዊ ጓደኛው አማካኝነት ለተጠቆማቸው አሳታሚዎች ልኮ መጽሐፍ ታተመለት። ይሄው መጽሐፍ በኋላ “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ” ተብሎ በተርጓሚና የህግ ባለሙያ ህይወት ታደሰ ወደ አማርኛ ተተርጉሞለታል። ከዚያ በኋላ ዘግይቶ የመጣ የጽሑፍ ችሎታው በረታ። በተለይ ፖለቲካዊ ሽሙጦችን እና ግጥሞችን ደጋግሞ ፃፈ። ለዚህ ማሳያ the case of the criminal walk እና “አፍሪካን አብዘርዲትስ” የሚሉትን የፖለቲካ ሽሙጥ መጽሐፎቹን እና ሀበሽኛ ብሎ የሰየማቸውን የግጥም መድብሎቹ ማንሳት በቂ ነው። አሁንም አስራ አንድ መጽሐፍትን ለአንባብያን ካደረሰ በኋላ “ራሴን እንደ ስነ ጽሑፍ ሰው አልመለከተትም” ይላል። በተለይ በፖለቲካ ተሳትፎው ወቅት አጠገቡ የነበሩ የሥነ ጽሑፍ ሰዎችን እያነሳ ራሱን ከእነርሱ ጋር በማነፃፀር “እኔ መቼ እፅፋለሁ” በሚል ትህትና ይከለላል።

ባንድ ወቅት “ግጥም የት አወቄ” በሚል ርዕስ የሰበሰባቸው ግጥሞቹን ለሃይሉ ገሞራው አሳይቶት “ቀጥልበት” ሲለው ‘ግጥም መፃፍ ቻልኩ ማለት ነው’ ብሎ በራሱ እንደተደነቀ ያስታውሳል። The Homeless Prime Minister ፣ Why Don’t They Eat Coltan? ፣ Democratic Cannibalism: African Absurdities III ፣ The Case of the Criminal Walk and Other Stories ፣ Give Me a Dog’s Life Any Day: African Absurdities II ፣ African Absurdities: Politically Incorrect Articles ፣ Case of the Socialist Witchdoctor and other stories እና ቀዳዳ ጨረቃ የሚሉ የፖለቲካ ሽሙጥ መጽሐፍትን በተለያዩ ጊዜ ያሳተመ ሲሆን Of Spades and Ethiopians ፣ Eating an American and Other Poems ፣ ሀበሽኛ 1 እና ሀበሽኛ 2 የተሰኙ የግጥም መድብሎችንም ለአንባብያን አድርሷል። በትግል ወቅት ያገኛት እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ልጅ ከሆነችው ገነት ግርማ ጋር አንድ ልጅ አፍርተው ከ50 ዓመት በላይ አብረው ቆይተዋል። ‘ከስራዎቼ ሽራፊ ሳንቲም አግኝቼ አላውቅም’ የሚለው እያሱ የሶሻሊስቱ ጠንቋይ መጽሐፉን ተመርኩዞ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን “ግራ ቀኝ” በሚል ርዕስ ሲተላለፍ የቆየውን ድራማ እያየው እና በዚህም ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል።

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ደራሲ ኢያሱ ራሱን እንደ ፖለቲከኛ እንጂ እንደ ደራሲ አይቆጥርም፡፡ እኛ ግን ባሳተማቸው ስራዎቹ ለኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ ማደግ አንዳች አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ በማሰብ የህይወት ታሪኩን ሰንደነዋል፡፡ ደራሲ ኢያሱ ወይም በተለምዶ የብእር ስሙ ሀማ ቱማ ዘመኑን ሲያነብ ነው የኖረው፡፡ ይህ ንባቡ ደግሞ በሳል ስራ እንዲያቀርብ አግዞታል፡፡ ከሰሞኑ በኢቢሲ መስኮት የቀረበውን ግራና ቀኝ የተሰኘውን የቲቪ ተከታታይ ድራማ ብንመለከት ደራሲው ሀማ ቱማ ያለውን ድንቅ እይታ ማየት እንችላለን፡፡ እርግጥ ነው ሀማ ቱማ የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ ከተሰኘው መጽሀፉ ሌላ ሌሎች በርካታ ድርሰቶችን ለአንባቢ አቅርቧል፡፡ እኛ ግን ያወቅነው ግራና ቀኝ በቲቪ መታየት ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቅ ድርሻ የሚኖራት መጽሀፉን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የመለሰችው ህይወት ታደሰ ናት፡፡ ሀማ ቱማ ኑሮውን በፈረንሳይ ካደረገ ቆይቷል፡፡ እዚያ ሆኖ ባለፉት ጊዜያት የድርሰት እና የጋዜጠኝነት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ኢያሱ አለማየሁ ለሀገሩ በድርሰት ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ በመሆኑ ልናመሰግነው እንወዳለን፡፡ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ እና በጋዜጠኛ አማረ ደገፋው የተጻፈ ሲሆን በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ዛሬ መስከረም 23 2016 ተጫነ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *