ዛሬ፤ ማክሰኞ መስከረም 15 2016 ዓ ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቀብራቸው ስነ ስርዓት ይፈፀማል ።
የአንጋፋው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የአቶ ሽመልስ አዱኛ ታናሽ እህት ወይዘሮ ምንትዋብ አዱኛ ከአባታቸው ከአቶ አዱኛ ካሳ እና ከእናታቸው ሴት አርበኛ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ኃይለሥላሴ በወርሃ ታህሳስ በዕለተ ሰንበት፥ በቀን 27, 1928 ዓ ም በኬንያ ናይሮቢ ከተማ ተወለዱ። ወይዘሮ ምንትዋብ አዱኛ ፣ከወላጆቻቸው እና ከታላቅ ወንድማቸው ጋር በልጅነታቸው ወደ ሐገራቸው ተመልሰው በሐረር ከተማ አደጉ።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሐረር በየሺ እመቤት የአዳሪ ትምህርት ቤት ተከታተሉ። በእሳቸው ትውልድ ለሴት ልጅ የማይታሰብ የሚባለውን የትምህርት ዕድል አግኝተው ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን፥ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም በቡልጋሪያ ሐገር በሶፊያ ከተማ ተማሩ።
በሪጅናል ፕላኒንግ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩትና የሰማንያ ስምንት አመት የዕድሜ ባለጸጋዋ ወይዘሮ ምንትዋብ፥ ለሐገራችን ኢትዮጵያ ምናልባትም ለአፍሪካ ብሎም ለመላም የጥቁር ሴቶች የመጀመሪያዋ ፋና ወጊ ሴት የስነ ሕንጻ ንድፍ ባለሙያ ናቸው። አርክቴክት ምንትዋብ አዱኛ በአውሮፓ በተለይም በጀርመን ሐገር ወደ ሐገራቸዉ ተመልሰው ከማገልገላቸው በፊት ለአመታት በሙያቸው ሠርተዋል።
በወቅቱ ምዕራብ ጀርመን በሚባለው በተለይም በሙኒክ ከተማ ከሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በቡድን እንዲሁም በግላቸው አፓርትመንቶችን፤ ልዩ ልዩ መኖሪያዎችን፥ የሕጻናት መዋያዎችን፥ ሌሎች የተለያዩ አገልግሎት ያላቸውን ግንባታ ንድፎችን ሠርተዋል። ከነዚህም ውስጥ የጀርመን ሙኒክ ኦሎምፒክ የተካሔደበት ስታዲየም ንድፍ ስራ የነበራቸው ተሳትፎ ተጠቃሽ ነው።
አርክቴክት ምንትዋብ አዱኛ በትምህርትና በልምድ ያካበቱትን እውቀት ወደሐገራቸው ይዘው በመምጣት ከሐይለ ስላሴ ዘመን እስከ ኢህአዴግ ዘመን ድረስ በውጭ ድርጅቶች፥ በመንግሥት መስሪያ ቤቶችና በግላቸው በበጎ ፈቃደኝነትና በቅጥር በልዩ ልዩ የሓላፊነት ደረጃ ለአስርት አመታት አገልግለዋል። ከሚጠቀሱት ሥራዎች መካከል
- የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ የአሁኑ የአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ ንድፍ ስራ ቡድን አባልነት
- በዩኒቨርሲቲው የሚገኘው የኬኔዲ ቤተመጻሕፍት የማንበቢያ ቦታዎች ነዳፊነት
- በከተማና ቤቶች ልማት ሚኒስትር መስሪያ ቤት የኪራይ ቤቶች አስተዳደር የአርክቴክቸር ባለሞያነት
- ለ German Relief Operation እና Norwegian Save the Children በበጎ ፈቃደኝነት
- ለ Pan African Housing Group ለመቀሌ የልጆች መንደር ንድፍ ስራ የቡድን ተሳትፎ
- በዘመነ ደርግ የሕጻናት አምባ ንድፍ ስራ እና አማካሪነት
- በገጠር ግብርና ቦታ ልማት ሚኒሰቴር መስሪያ ቤት የአረዳይታ ተቋም ግቢ መልክዓ ምድር ዲዛይነር እና የግንባታ ሱፐርቫይዘር
- በብሔራዊ መሐንዲሶች እና ኮንትራክተሮች ድርጅት በፕሮግራም እና ቴክኒክ ክፍል ልዩ ልዮ የሀላፊነት ስራዎች
በዋናነት የሚጠቀሱ ስራዎቻቸው ናቸው።
አርክቴክት ምንትዋብ የአንዲት ሴትና የአንድ ወንድ ልጆች እናት፥ የአራት ወንድ ልጆች አያት ነበሩ። የመጀመሪያዋ ሴት አርክቴክት ምንትዋብ አዱኛ ካደጉበት ሐገርና ከተማሩበት ከሰሩበት የተለያየ ሐገር የተነሣ የአማርኛ የኦሮምኛ የሶማሊኛ ቋንቋዎችን ከሐገር ውስጥ ከውጭ ደግሞ የእንግሊዝኛ የጀርመንኛ እና የቡልጋሪያ ቋንቋን አቀላጥፈው መናገር የሚችሉ የስድስት ቋንቋ አዋቂ ነበሩ።
አርክቴክት ምንትዋብ አዱኛ ከሴት ልጃቸው ጋር አብረው በጡረታ ዕድሜያቸው ኖረው በትላንትናው ዕለት በክብር በተወለዱ በሰማንያ ስምንት አመታቸው በዕለተ ሰኞ መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ ም አርፈዋል። ወይዘሮ ምንትዋብ አዱኛ 2 ልጆችን ያፈሩ ሲሆን የመጀመሪያ ልጃቸው ከ3 ዓመት በፊት ነበር ህይወቱ ያለፈው ። ሁለተኛ ሴት ልጃቸው ወይዘሮ ህይወት ዳንኤል በዛሬው ዕለት ለተወዳጅ ሚድያ በሰጡት መግለጫ እናታቸው ወይዘሮ ምንትዋብ ከሙያቸው ባሻገር ሰዎችን በመርዳት እና በማገዝ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል።
ይህን የእርሳቸውን የህይወት ታሪክ በተደራጀ መልኩ ያወጣው የጌጡ ተመስገን ገጽ ሲሆን እኛም ተጨማሪ መረጃ እንድናገኝ ጌጡ ላደረገልን ትብብር ምስጋናችን የላቀ ነው። ዛሬ፤ ማክሰኞ መስከረም 15 2016 ዓ ም በመንበረ ጸባኦት ቅስድስ ሥላሴ ካቴድራል የቀብራቸው ስነ ስርዓት በ9 ሰዐት ይፈጸማል።