የዝና ወርቁ
የመጀመሪያዋ ሴት የአጭር ልቦለድ ደራሲ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት በ2014 አ.ም ታሪኮቹን አሳትመን ያሰራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ? የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያስነበብን ፤እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያሉ ታሪካቸው የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ካለፉም በኋላ አበርክቷቸው እንዳይዘነጋ የተቻለንን እያደረግን እንገኛለን፡፡ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡
በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል የዝና ወርቁ አንዷ ናት፡፡የዝና በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት የአጭር ልቦለድ ደራሲ ናት፡፡ ይህም ልቦለድ ድርሰቷ የዛሬ 37 አመት በ1978 ‹‹የተሸጠው ሰይጣን›› በሚል ርእስ ከጀማል ሱሌይማን ጋር አሳትማ ለንባብ አብቅታለች፡፡ ባለፉት 37 አመታት ከስነ-ጽሁፍ ፈጽሞ ያልራቀችው የዝና ወርቁ እስከዛሬ 7 መጽሀፎችን ወደ አንባቢ አድርሳለች፡፡ ዛሬም ትጽፋለች፡፡ ከባለ ታሪኳ የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግም እዝራ እጅጉ የህይወት ታሪኳን ሰንዶታል፡፡
ልጅነት እና እድገት
የዝና፣ በቀድሞ መጠሪያው፣ በጌምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት፣ ጐንደር ከተማ፣ ልዩ ስሙ ፊት ሚካኤል በተባለ ሠፈር፣ ከወይዘሮ ሙጭት ወርቁ እና ከመቶ አለቃ አለባቸው ወንድይራድ መስከረም 12 ቀን 1954 ዓ.ም. ነበር የተወለደችው፡፡ ለቤታቸው በጣም ቅርብ በነበረው በፊት ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ግቢ ፊደል ቆጠረች፡፡ አቶ ወርቁ ደስታ፣ አያቷ ሲሆኑ፣ መስከረም ወር ላይ ልጆቻቸውንና እርሷን ይዘው ወደ ጻዲቁ ዮሐንስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሄዱ በመንገድ ላይ ከሰው ጋር ይገናኙና እነዚህ ልጆቼ ናቸው፡፡ እርሷ ደግሞ የልጄ ልጅ ናት ሲሉ ሰምታ አልቅሳለች፤ አኩርፋለች፡፡ ምክንያቱን ስትጠየቅ “እኔስ ልጅህ አይደለሁም?” ብላ ያላሰቡትን ጥያቄ ሰነዘረች፡፡ አባብለው ለቅሶዋን አስቆሙና እንደልጆቻቸው እሷንም በእሳቸው ስም አስመዘገቧት፡፡ የመኖሪያ ቤታቸውም ከወላጆቿ ቤት ተቀራራቢ ስለነበር አብዛኛውን የልጅነት ጊዜዋን በእናቷና በምትወዳቸው አያቶቿ ቤት ነበር ያሳለፈችው፡፡
የቤተሰብ ሁኔታ
ወላጅ አባቷ፣ በፓርላማ አባልነት፣ በወረዳና በአውራጃ ገዥነት፣ በመተሐራና በወንጂ ስኳር ፋብሪካዎች በአስተዳደር ኃላፊነት፣ ባገለገሉባቸው ዓመታት በተለያዩ ቦታዎች ይዘዋወሩ ስለነበር ሁል ጊዜ በክረምት ትምህርት ቤት ሲዘጋ ከእርሳቸው ጋር እንድትከርም ይወስዷት ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ በልጅነቷ ለመጽሐፍ፣ ለተፈጥሮና ለገጠር ኑሮ የነበራትን ፍቅር እየታዘቡ የሚሰማትን እንድትጽፍና፣ በርትታ ከጻፈችም እንደሚያሳትሙላት ይነግሯት ነበር፡፡ እርሳቸውም “ማዘዝ ብቻ አይበቃም” እና “የሰላም ጐዳና” የተሰኙ ሁለት መጻሕፍትን ደርሰው ለኅትመት አብቅተዋል፡፡
ትምህርት እና የስራ አለም
የዝና፣ ከሰባተኛ እስከ ዘጠነኛ ክፍል የተማረችው ያን ጊዜ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይባል በነበረው (በኋላ ፋሲለ ደስ) ነው፡፡ ከአሥረኛ እስከ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ያለውን ትምህርት አዳማ(ናዝሬት) በዓፄ ገላውዲዎስ ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡ እዚያም በ1972 ዓ.ም. በተሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለዲግሪ በሚያስቀጥል ውጤት ካለፉት በጣት ከሚቆጠሩ ተማሪዎች መካከል አንዷ ሆና በማለፍ አዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ ገብታ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ በዲግሪ እንዲሁም በአልፋ ዩኒቨርስቲ በሥራ አመራር (ማኔጅመንት) ቢ.ኤ. ዲግሪ ተመረቀች፡፡ ከዚያም የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎርን በማጥናት በማስተርስ ዲግሪ ተመረቀች፡፡
በመደበኛ የሥራ ቦታ አገልግሎት በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መ/ቤት ለ31 ዓመታት በተለያዩ የሥራ መደቦች ከባለሙያነት እስከ መምሪያ ኃላፊነት አገልግላ፣ ከጊዜው ሁለት ዓመት ቀድማ ባቀረበችው ጥያቄ በፈቃዷ በጡረታ ክብር ተሰናብታለች፡፡ ይህ ጽሑፍ በሚዘጋጅበት ጊዜ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር በሥራ አስኪያጅነት በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ በልጅነቷ፣ ጨዋታ ወዳድ ስለነበረች ለምግብ እንኳ ካʼልተጠራች አስታውሳ እቤት አትገባም ነበር፡፡ ሰፋፊ መጫዎቻ ቦታዎች በነበሩት መንደር ውስጥ ከእድሜ እኩዮቿ ጋር ገበጣ፣ ቅልቦሽ፣ ገመድ ዝላይ፣ ዕቃ ዕቃ… ወዘተ እስክትጠግባቸው ተጫውታለች፡፡ በወጣትነት እድሜዋም ካርታ እና የጠረጴዛ ቴኒስ ጨዋታ ትወድ ነበር፡፡
የሥነ-ጽሁፍ ዝንባሌ
የዝና፣ የሥነ ጽሑፍ ፍቅር የአደረባት ገና በልጅነቷ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ለዚህ ከአበቋት የተለያዩ ምክንያቶች መካከል የመጀመሪያው የእናቷ ተረት አዋቂነት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ “በጊዜ የሚተኛ ፍቅር የሌለበት ቤተሰብ ነው” ይሏት የነበሩት እናቷ ማታ ማታ ለእሷና ለታናሽ እህቷ ተረት ያወሩላቸው ነበር፡፡ የሥነ ጽሑፍ ፍቅሯ ሥር እንዲሰድ የአደረገው፣ በዘመኑ ለንባብ ይሰጥ የነበረው ክብር ነው፡፡ በእሷ የልጅነት እና የወጣትነት ዘመን የተማሩ ናቸው በሚባሉ ሰዎች የእንግዳ መቀበያ ክፍል (ሳሎን) ውስጥ መጻሕፍት ዳር እስከ ዳር ግጥም ያለባቸውን መደርደሪያዎች ማየት የተለመደ ነበር፡፡ በጓደኛሞች መሐል የነበረው መጽሐፍ የማንበብ ውድድርም ጠንካራ ነበር፡፡ “አንባቢ ናቸው” የሚባሉ ሰዎች ሁሉ ይከበራሉ፡፡ ከዚህም ሌላ የሁለት ዓመት ታላቋ የነበረችው ፈለግ ወርቁ የመጀመሪያውን ድርሰቷን እንድትጽፍ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለች ምክንያት እንደሆነቻት ታስታውሳለች፡፡ በሕይወት ዘመኗ ለተወሰኑ ዓመታት ደርሶባት የነበረውን አስጨናቂ ሁኔታ ለማለፍ፣ መጽሐፍ ማንበብ ያደረገላትን ውለታ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ በአስተማሪነት ገጽታው ታወሳዋለች፡፡ “መጽሐፍ ማንበብ ለእውቀት ብቻ ሳይሆን ጤናና ሰላም ነው” በማለት ትመሰክራለች፡፡
ትውውቅ ከህይወት አጋር ጋር
የዝና፣ በሕይወት ጉዞዋ ሌላው ገጠመኟ፣ ከጀማል ሱለይማን ጋር በዩኒቨርስቲ ተማሪነት ጀምረዉት፣ መጽሐፍ በጋራ እስከ ማሳተም የደረሱበት የፍቅር ግንኙነትና በትምህርት ቤት ውስጥ በጋብቻ እስከመጣመር፣ ከዚያም አንድ ልጅ እስከማፍራት የአበቃቸው ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን የሁለት ልጆች አያት ሆናለች፡፡
ተጨማሪ አስተዋጽኦ
ከመደበኛ ሥራዋና ከድርሰት ተግባሯ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢነት፣ በዜማ ብዕር ኢትዮጵያ የሴቶች የሥነ ጽሑፍ ማኅበር በኘሬዚዳንትነት፣ በሆሄ ሽልማት በአስተባባሪነትና በቦርድ አባልነት፣ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር የመማክርት ጉባኤ አባል፣ የአካባቢ ልጆች የንባብ ክበብ በማቋቋም እና የተሰጥኦ ማሳያ ዝግጅቶች በመኖሪያ ቤቷ ማካሄድ፣ ለጀማሪ ደራሲዎች ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ፤ ይኼውም በብዙ ጀማሪ ደራሲዎች መጽሐፎች ውስጥ በምስጋና ተገልጾ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን በተለያዩ መድረኮች አቅርባለች፡፡
እንዲሁም በሌሎች በርካታ አገራዊ ዝግጅቶች በመምራትና በማስተባበር፣ በልማት ማኅበሮች ሰብሳቢነትና በዕድር ዳኛነት ማኅበረሰቡን አገልግላለች፡፡ በእነዚህ ከሕይወት ዘመኗ በርካታ ዓመታትን ባስቆጠሩ አገልግሎቷ በጠቅላይ ሚኒስትር “የአገር ባለውለታ አንጋፋ ከያኒያን በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ የ2013 የሚዳሊያ ሽልማትን እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማትም በርካታ የምስጋና የምስክር ወረቀት አግኝታለች፡፡ በአገራችን በዘመናዊ አጭር ልቦለድ የመጀመሪያዋ ሴት ደራሲ ሆና የምትጠቀሰው የዝና ወርቁ የመጀመሪያዎቹ አጫጭር ልቦለዶቿ የታተሙት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ የትምህርት ክፍል የአራተኛ ዓመት ተማሪ እያለች፣ ባለቤቷ ከነበረው ከጀማል ሱለይማን ጋር በ1978 ዓ.ም. በጋራ ባሳተሙት ‹‹የተሸጠው ሰይጣን እና ሌሎች አጫጭር ልቦለዶች›› በተባለው መድበል ነው፡፡
ሌሎች የአጫጭር ልቦለዶቿ ስብስብ ለሁለተኛ ጊዜ ከጀማል ጋር፣ ‹‹ያልተመቻት ችግኝ›› በተባለ መድበል ውስጥ ተካትተው በ1982 የታተሙት ናቸው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከተካተቱት ሥራዎቿ ‹‹የመመረቂያው ልብስ›› የሚለው ድርሰቷ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል ተመርጦ በጀርመን ኤምባሲ የባሕል ዘርፍ ወጪ በእንግሊዝኛ እንዲተረጐም ተደርጓል፡፡ በኤምባሲው አንድ የምሽት ሁነት (event) በማዘጋጀትም በመድረክ ቀርቦ ውይይት እንዲካሄድበት ተደርጓል፡፡
ሌሎች በውድድር የተመረጡ አጫጭር ልቦʼለዶቿና እውነተኛ ትረካዎቿ ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ባሳተማቸው ‹‹ክንፋም ህልሞች››፣ ‹‹አዙሪት›› እና ‹‹ዛሬን ከተጉበት ነገን ያነጉበት›› በሚል መድበል ውስጥ ከሌሎች ደራስያን ሥራዎች ጋር ታትመውላታል፡፡ እንዲሁም በዜማ ብዕር ቁ.1 የአጫጭር ልቦ’ለዶች መድብል እና በዜማ ብዕር ቁ.2 የግጥሞች መድበል ውስጥ ሥራዎቿ ተካተው ታትመዋል፡፡ “ዘመን ተሻጋሪ” የሕይወት ታሪክ(ከደራሲት ፀሐይ መልአኩ ጋር በጋራ)፣ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ትምህርት ክፍል የሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ መጽሐፍ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በጋራ፣ “ሳሮን ደንሺ ሳሮን” የተረቶች ስብስብ ውስጥ አንድ የሕጻናት ተረት ታትሟል፣ “አበባ እና አበበ በሚል ርዕስ በተከታታይ በቴሌቭዥን ይተላለፉ ለነበሩ የሕፃናት ካርቱን ፊልሞች በግል እና በጋራ ስክሪኘቶችን አዘጋጅታለች፡፡
የዝና ከሌሎች ደራሲያን ጋር በጋራ ካሳተመቻቸው ድርሰቶቿ ባሻገር በግሏም ከዚህ በታች የተገለጹትን መጻሕፍት አሳትማለች፡፡
- የደራሲዋ ፋይል ረዥም ልቦለድ በ2ዐዐ2 ዓ.ም. ታተመ፡፡ በሥነ ጽሑፍ ፍቅር፣ በድርሰት ተሰጥኦ፣ በማኅበረሰቡ ግንዛቤ እና በኢኮኖሚ አቅም መካከል ያለው ግንኙነት እና ቀውስ የተገለፀበትና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስና ሌሎች ማኀበራዊ ጉዳዮችን የያዘ ነው፡፡
- የአፍንጮ በር ወፎች(ለሕፃናት) 2ዐዐዐ ዓ.ም. ታተመ፡፡
- ይቅርታ (ለሕፃናት) 2ዐዐዐ ዓ.ም. ታተመ፡፡
- መፍቻውና ሌሎች አጫጭር ልቦለዶች መድብል(ለታዳጊዎች)፤ በ2ዐዐ4 ዓ.ም. ታተመ፡፡ መጽሐፉ፣ የሀገራችን ሥነ ጽሑፍ ትኩረት ያላደረገበትን የኅብረተሰብ ክፍል ለይቶ ለመድረስ ታስቦ የተዘጋጅ ነው፣ ቋንቋው ጭብጡና አተራረኩ ለታዳጊዎች በሚሆን ደረጃ የተመጠነ ሲሆን፣ የሥነ ልቦና እና የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡
- አቅመ ቢሱ አሸባሪ፤ በ2ዐ1ዐ ዓ.ም. ታተመ፡፡ በአገራችን ሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ሕይወት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ “THE PLEASING UNSPOKEN VOICES” ከተባለው መጽሐፍ ተወስደው የተተረጐሙና ሌሎች አዳዲስ ታሪኮችም ተካተውበት የተዘጋጀ ነው፡፡ ገቢው ለኢትዮጵያ ሥጋ ደዌ ማኅበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንዲውል ታስቦ የተዘጋጀ፡፡
- የኢትዮጵያ ግብር ታሪክ 2ዐ11 ዓ.ም. ጥንት በንጉሦች አዳራሽ ይዘጋጅ ከነበረው (የገዥዎች ግብር) እስከ ዘመናዊ የግብር ሥርዓት ታሪክና አገራዊ ፋይዳ፣ የሚተርክና የሚተች ይዘት ያለው መጽሐፍ፡፡ በ34ዐ ገጾች የተዘጋጀ፡፡
- የዘመን መስታውት የግጥም መድበል፣ በ2ዐ14 የታተመ፡፡
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ የዝና ወርቁ፣ በሀገራችን የመጀመሪያዋ ሴት የአጭር ልቦለድ ደራሲ ናት፡፡ ከ37 አመት በፊት ለህትመት በበቃ ስራዋ ጠንካራ የልቦለድ ደራሲ መሆኗን በተግባር አስመስክራለች፡፡ 31 አመት በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥራ ብታገለግልም ከሥነ-ጽሁፍ ግን ብዙም አልራቀችም፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሥነ-ጽሁፍ ፍቅሯን ስትወጣ ነበር፡፡ በተለይም በደራሲያን ማህበር ውስጥ በምታደርጋቸው ልዩ ልዩ ተሳትፎዎች ትልቅ አሻራ ለማኖሯ በቂ ምስክሮች አሉ፡፡ የዝና፣ በተለይ ‹‹የኢትዮጵያ የግብር ታሪክ›› በሚል ርእስ ከ 4 አመት ቀደም ብሎ ያዘጋጀችው መጽሀፍ ከፈጠራ ስራዎች ባሻገር በታሪክ መጽሀፎችም ላይ ያላትን ችሎታ ያስመሰከረችበት ነው፡፡ የዝና ለኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ ደማቅ አሻራዋን ያኖረች በመሆኗ በመዝገበ-አእምሮ ታሪኳ ሊሰነድ ይገባል፡፡ የእኛም ዋና ግብ ለሀገር የሰሩ ሰዎችን በአግባቡ መሰነድ እንደመሆኑ የዝናም ታሪኳ ሁሉንም ስለሚያስተምር እነሆ ለአንባቢ አቅርበነዋል፡፡ ይህ ጽሁፍ÷ ከባለታሪኳ የተገኙ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ የተጻፈ ሲሆን ጽሁፉም በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተሰነደ ነው፡፡ ይህ የህይወት ታሪክ ዛሬ መስከረም 10 2016 አ.ም ከሌሊቱ 5 ሰአት ግድም በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ፖስት ተደረገ፡፡