አድነው ወንድራድ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡
ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡200 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል አድነው ወንድራድ(አዱኒስ) ይጠቀሳል ።የአዱኒስን ታሪክ ቅድስት ወልዴ ሰንዳዋለች።
መግቢያ
ብዙዎች መልኩን ሳይሆን የሚያውቁት አዶኒስ በሚለውን የብዕር ስሙ ነው፤ሙሉ ስሙ ግን አድነው ወንድይራድ ወልደ ጊዮርጊስ ይባላል፤አዶኒስ የመጀመሪ ልጁ ስምም ነው፡፡በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ይተላለፍ በነበረው ተወዳጁ ገመና ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ብዙዎች ስሙን ይወቁት እንጂ ብዙ ክህሎቶች የነበረው ደራሲ፣አርክቴክት፣ሙዚቀኛ ፣የህፃናት መዝሙር ደራሲ፣ሰዓሊ እና ቀራፂ ፣ብዙዎች እንደሚመሰክሩለት ደግሞ ጥልቅ አንባቢ እና ተርጓሚም ጭምር ነበር፡፡ልታይ ልታይ ሳይል ተሸሽጎ በስራዎቹ የታየ የኪነጥበብ ወዳጆችን ልብ በጥበቡ ያገኘ፣ ስራዎቹ ያወሩለት ድንቅ ሙያተኛ ነው፡፡የአዶኒስ የህይወት ታሪክ እና የኪነጥበብ ጉዞው ይህንን ይመስላል፡፡
ትውልድ እና ልጅነት
አድነው ወንድራድበ1956 በናዝሬት ከተማ ቀበሌ 16 ነው ተወልዶ ያገደው፡፡ከአባቱ እና ከአያቶቹ ጋር ያደገ ሲሆን አባቱ ፊደል የቆጠሩ ስለሆኑ ያነቧቸው የነበሩ መፅሀፍትን ከልጅነቱ ጀምሮ ያነብ ነበር፡፡ገና ከልጅነቱ ልጆች ሲጫወቱ የእርሱ ትኩረት ሌላ ነበር፤በአሸዋ ላይ ስዕልን ይስላል፣ከቀንድ ቅርፃ ቅርፅ ይሰራል፡፡ ‹‹ማሞ ይለኛል፤ማሞ እለዋሁ፡፡›› እንጂ ለ35 ዓመታት በስማችን እንኳ ተጠራርን አናውቅም ነበር የሚለው ታላቅ ወንድሙ ደራሲ እና አዘጋጅ ኃይሉ ጸጋዬ የተለየ የልጅነት ጊዜ ከወንድሙ ጋር እንዳሳለፈ ያስታውሳል፡፡‹‹የልጅነት ዝንባሌያችንም የተለያየ ነበር፤እኔ ኳስ እጫወታለሁ፣እዋኛለሁ፣ረዥም ርቀት እሮጣለሁ፤እሱ አሸዋ ላይ ይስላል፤በጣም ትንንሾች ሳለን ከበቆሎ አገዳና ከልጣጩ ሽጉጥና መነጽር ይሰራልኝ ነበረ፡፡›› ሲል ነው የልጅነት ጊዜያቸውን እና አዶኒስ ከልጅነቱ ጀምሮ ለጥበቡ በጣም የቀረበ መሆኑን የሚመሰክረው፡፡
ትምህርት
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ለትምህርቱ ግዴለሽ ተማሪ የነበረው አድነው ትምህርት ቤት ብዙም አይሄድም ነበር፡፡በአንድ ደብተርም ብዙ ትምህርቶችን ይማር ነበር፡፡የአስራአንደኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ግን ነገሮች ተቀያየሩ፡፡ጓደኞቹ ሁሉ ለማትሪክ ሲዘጋጁ፣የተቀሩት ዩኒቨርሲቲ መግባታቸውን ሲመለከት ሙሉ ትኩረቱን ትምህረርቱ ላይ አደረገ፡፡ጥሩ ውጤትን አምጥቶም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርክቴክቸር ትምህርትን ለማጥናት በቅቶቷል፡፡የቅርብ ጓደኛው እና አብረው የተማሩት አርክቴክትና ደራሲ ሚካኤል ሽፈራው በዩኒቨርሲቲ ቆይታው አዶኒስ ‹‹ሊዝናና፣ከጓደኞቹ ጋር ጊዜ ሊያሳልፍ ይችላል፤ግን ለፈተና አንድ ወር ሲቀረው በደንብ ነው የሚዘጋጀው፡፡መጨረሻ ላይ የሚሰራውም ውጤቱ የሚደንቅ ይሆናል፡፡እንደውም ቦርድ ላይ ለማሳያነት ከሚቀርቡ ስራዎች መካከል የአዶኒስ ቀዳሚው ነው፡፡››በማለት ነው፡፡አዶኒስ በ1979 ዓ.ም ከአርክቴክቸር ትምህርት ክፍል በጥሩ ውጤት ተመርቋል፡፡
የስራ ጅማሮ
ትምህርቱን ጨርሶ እንደተመረቀ በደርግ ዘመነ መንግስት ይደረግ እንደነበረው በግብርና ሚኒስቴር ተመደበ፡፡በዚህም የተለያዩ ሃገራት ይጓዝ ነበር፤ለስራ ወደ ጎጃም በሄደበት ወቅት የጣና በለስ ፕሮጀክት ስራ ትልቁን ቦታ ወስዶ ይሰራ በነበረው ስቱዲዮ ፔትራንጀሊ ውስጥ ተቀጠረ፤ግን ጠፍቶ ነው እንጂ ደርግ ወደ ግብርና ሚኒስቴር ይመልሰው ነበር፡፡በጣና በለስ ፕሮጀክት ላይም አማካሪ ሆኖ የራሱን አሻራ አሳርፏል፡፡
የጥበብ ጅማሮ እና ጉዞ
ከሰለጠኑበት ሙያ ውጪ ለኪነጥበቡ ግዙፍ አስተዋፅኦ አድርገው ከተሳካላቸው ከያንያን መካከል አዶኒስ አንዱ ነው፡፡የሚካኤል ሾሎኆቭን ‹‹ቨርጂን፣ሶይል አፕተርንድ›› ካነበበ በሁዋ ነው የተለየ ክላሲክ አንባቢ የሆነው፡፡ታላቅ ወንድሙሃይሉ ፀጋዬ እንደሚለውም ‹‹በጮርቃ እድሜያችን በንባብ ፍቅር ተለክፈን በምናነባቸው መጽሐፍ ላይ እንነጋገር ነበር ››በማለት ነው፡፡ከሃያ ዓመት በላይ የሚተዋወቅት የመጽሃፍ ነጋዴ የሆነው ሙስጠፋ ናስር‹‹አድነው መጽሀፍ በጣም ይመርጣል፣ሲገዛም የተለያየ ዘርፍን ነው የሚገዛው፡፡የመጽሀፍቱ ብዛት ግን እንዲህ በቀላሉ ሳይሆን በቁጥር መፅሀፍን ስለማይፈራ ተሰብስቦ ሆነ በማዳበሪያ ተሞልቶ በላዳ ወይም በታክሲ ሲሞላ ነው የሚወስደው››በማለት አዶኒስ ምን ያህል ከመፅሀፍ ጋር ቁርኝት እንደነበረው ያሳያል፡፡
አድነው ወንድራድ አዶኒስ ከልጅነቱ ጀምሮ በማንበብ እና በእጅ የሚሰሩ ነገሮችን በመገጣጠም፣ስዕልን በመሳል ነው ያደገው፡፡በርካታ የሳላቸው የስዕል ስራዎችም አሉት፡፡ በበርካታ ተውኔቶችን እና ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማዎችን፣ፊልሞች ላይ በደራሲነትም ተሳትፏል፡፡በአንባቢያን ተወዳጅ የነበሩ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ይወጡ የነበሩ የተለያዩ ረዣዥም ታሪኮችን ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ይፅፍ ነበር፡፡ከነዚህም መካከል የአና ማስታወሻ አንዱ ነው ፡፡በሁዋላም በአለማችን በብዙ ሚሊየኖች የተነበበውን የአና ማስታወሻ መፅሀፍን በአማርኛ ተርጉሞ አቅርቦ በብዙዎች የተወደደ እና ተነባቢ እንዲሆን አስችሏል፤ከመፅሀፉ በተጫማሪ ለመድክ ተውኔት የበቃ ስራው ሆኖለታል፤ይህ ተውኔት ለመጀመሪያ ግዜ ለመድረክ ሲበቃም መድረኩን ዲዛይን ያደረገው እሱ ነበር፡፡
በ1993 ለመድረክ የበቃው ይህ የአና ማስታወሻ ተውኔት አሁን ደግሞ በተሻለ አሰፋ (ዶ/ር) አዘጋጅነት በድጋሜ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ዘወትር ረቡዕ መታየት ጀምሯል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ፣በራስ ቴአትር፣በሐገር ፍቅር ቴአትር እና በአዲስ አበባ ባህል አዳራስ(ማዘጋጃ) ለረዥም ጊዜያት በመድረክ የቆዩ እና ተወዳጅ የሆኑ እንደ ኪሊዮፓትራን፣ቀስተደመና፣ጣውንቶቹ፣አጋምና ቁልቋል፣ሞትና ትንሳኤ የተሰኙ ተውኔቶች ለመድረክ ያበቃቸው ወጥ እና የትርጉም ስራዎቹ ናቸው፡፡በፊልሙ መንትዮቹ፣አንድ እድል፣የማይታረቁ ቀለማት፣መልኅቅ የሚጠቀሱ የድርሰት ስራዎቹ ሲሆኑ በመጽሀፍት ደረጃ ከአና ማስታወሻ በተጨማሪ አዶልፍ ኤክማን ተወዳጅ የትርጉም መፅሀፉ ነው፤ ፕሮፌሰሩ ደግሞ ወጥ ስራው ሲሆን አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም እና ኤልሳቤጥ መላኩ በትረካ መልክም አቅርበውታል፡፡
በፊት ኢቲቪ 2 በሚባለው ጣቢያም የተለያዩ አጫጭር ከአስራ አምስት በላይ የሚሆኑ ድራማዎችን ላይ በድርሰት ተሳትፏል፡፡ ሜጋ ኪነጥበባት ማዕከል ከኢቲቪ ጋር ለመስራት በተስማማው ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ብዙ ደራሲያን ተሞክረው ነበር፤ግን እንደተፈለገው አልሆነም፡፡ከብዙ ፍለጋ በሁዋላ በኢትዮጵያ ድራማ ታሪክ ፈር ቀዳጅ የሆነው ‹‹ገመና 1›› ድራማን መስራት ችሏል፡፡የገመና ድራማ በመላው ሃገሪቱ ተወዳጅ እና ተጠባቂም መሆን የቻለ ነው፡፡በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የተለያዩ ጥናቶች እና ውይይቶችም የተደረጉበት ድራማ ነው፡፡የድራማው ዳይሬክተር የሆነው አሸብር ካብታሙ‹‹ገመናን ዛሬ መለስ ብሎ ለሚያስተውለው በአንድ ሰው የተፃፈ ለመሆኑ እስከመጠራጠር የሚያደርሱ ተውኔቶች አሉት፡፡›› ሲል ነው ድራማውን እና የአዶኒስን ችሎታ የሚያስታውሰው፡፡
የሃገራችን የቴሌቭዥን ድራማዎች ውሃ ልክ የሚሉት አዶኒስ ከገመና ድራማ በማስከተል ደግሞ ሌላው ረዥሙ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የተላለፈውም መለከት የተሰኘ ድራማ ላይም በድርሰት ተሳትፏል፡፡የገመና እና መለከት ድራማ አዘጋጅ የሆነው አሸብር ካብታሙ‹‹ለእኔ ደጋግሜ እንደምለው ትልቁ የአድነው ማስተር ፒስ የምለው መለከትን ነው፡፡መለከት የነገዋን ኢትዮጵያን ያየንበት ድራማ ነው፡፡››በማለት ነው የሚገልጸው፡፡በሮህቦት ፕሮሞሽን የተሰራው ይህ ድራማ በሚያዝያ በ2010 ዓ.ም የተጠናቀቀው ሲሆን 104 ክፍሎችን ይዞ ተጉዟል፡፡ በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ በማንያዘዋል እንደሻው አዘጋጅነት በፍቅሩ ካሳ ደራሲነት በተሰራው አሸክታብ የተሰኘ ማስተማሪያ የአንድ ሰዓት ፊልም ለዓለም ዓቀፍ ተመልካቾች ወደ እንግሊዘኛ መመለስ ነበረበት እና አዶኒስ ይህንን ሰርቷል፡፡ ማንያዘዋል እንደሻው እንደሚመሰክርለትም የሰሜን ሸዋ ዘዬ ያለውን ይህንን ፊልም አዶኒስ በሚደንቅ መልኩ የአማርኛውንም አሳጥሮ ምስል በመፍጠር በተለየ መልኩ ነው የተረጎመው በማለት ነው፡፡በአጠቃላይ እጁን ያሳረፈበት ነገር ጥሩ ሆኖ ይወጣለታል፤የአዶኒስ ችሎታ በርካታ ነገሮችን ይከውኑ ከነበሩት የሬናይሰንስ ዘመን ላይ የነበሩ ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ነው ይለዋል፡፡
አድነው ወንድራድ አዶኒስ እና ሙዚቃ
አድነው ወንድራድ አዶኒስ ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር ነበረው፤ጊታርን መጫወት የለመደው ቁመቱ ከጊታሩ ብዙም በማይበልጥበት ጊዜ ነበር፡፡የጊታር ችሎታውን አጎልብቶ ለናዝሬት የከፍተኛ አንድ የኪነት ቡድን ለብዙ ዓመታት በጊታር ተጫዋችነት አሳልፏል፡፡በሁዋላ ግን መድረክ ላይ ሆኖ መጫወትም ሆነ መታወቅን በመሸሽ ከነዚህ እርቋል ፤በዚህም ለቤተሰቦቹ እና ቅርብ ሰዎቹ ካልሆነ ጊታር አይጫወትም፡፡
ሙዚቃ ከልጅነቱ ጀምሮ ማዳመጥ እና መጫወት የጀመረው አዶኒስ ለሙዚቃ ያለው ፍቅር እና ችሎታም የተለየ ነው::የቅርብ ጓደኛው አርክቴክት እና ደራሲ ሚካኤል ሽፈራው ስለሙዚቃ ችሎታው ሲገልጽም ‹‹ለሙዚቃ ያለው ጆሮ በጣም አስደናቂ ነው፤ሙዚቃ በጣም ይወዳል፤ሙዚቃ ማዳመጥ የሚችል የተረጋጋ መንፈስ አለው፡፡በዩኒቨርሲቲ ቆይታችንም በዶርም ውስጥ ክላሲካል፣ካንትሪ፣ብሉስ እና ጃዝ ሙዚቃዎችን ያዳምጥ ነበር፡፡በስምም ታዋቂዎቸን ያውቃቸውም ነበር ››በማለት ነው፡፡አዶኒስ ከወጣትነቱ ጀምሮ ከ3000 በላይ የሰበሰባቸው እና ያዳምጣቸው የነበሩ የሙዚቃ ካሴቶችን በቤቱ ይገኛሉ፡፡
ድምፃዊ ዣን ስዩም ሄኖክ የተጫወተው ጉድ የተሰኘው አልበም በጣም ተወዳጅ ሙዚቃነው፡፡የአልበሙ መጠሪያ የሆነውን ጉድን ጨምሮ ሌላኛውን በአልበሙ የተካተተውን ተስፋ የተሰኘ የሙዚቃ ግጥምን እና ዜማውንም ጭምር የሰራው አዶኒስ ነው፡፡
የልጆች መዝሙር ላይ በደንብ መስራት ይፈልግ ነበር፤በአንድ ወቅት በሀገራችን ያሉ የኢትዮጵያ ልጆች መዝሙሮች ካደመጠ በሁዋላ ብዙዎቹ መስተካከል አለባቸው ብሎ ስላሰበ በራሱ ለማስተካከል ስራ ጀምሮ ነበር፤በዚህ መነሻነት ከ30 ያላነሱ የልጆች መዝሙሮችን በጥቂት ሳምንታት ፅፎ ልጆችን በድምፅ አሳትፎ ራሱ ጊታር እየተጫወተ ዝግጅት እያደረገ ነበር፤በወቅቱ ከነበሩበት የተለያዩ የተከታታይ ቴሌቭዥን ድራማ ስራዎች ይህንን ጅምር ሃሳቡን ከዳር እንዳያደርስ አድርገውታል፡፡በዣን ስዩም ሄኖክ ጉድ በተሰኘው ሙዚቃ ግን የልጆች መዝሙርን በመሃል አካቶ ሰርቷል፡፡ከዚህ በተጨማሪ ቾምቤ፣ባልደራሱ እና ፍቅር የተሰኙ የህፃናት መዝሙሮችን ከድንቅ የግጥም አፃፃፍ ጋር ለኢትዮጵያን ልጆች አበርክቷል፡ አዶኒስ ሁሉም የቅርብ ሰዎቹ እና ጓደኞቹ እንደሚሉት ለማንም ያላጋራው እና ያላሳየው የራሱ የሆነ ሚስጥር ያለው ነው የሚመስለው፤ያንንም በስነጥበብ ስራው አልገለፀውም እንጂ አሁን ከሰራው በላይ በህይወት ኖሮ ዘመን አይሽሬ ታሪካዊ ስራን መስራት ይችል ነበር ይሉለታል፡፡
ቤተሰባዊ ህይወት
ጣና በለስ ፕሮጀክት በሚሰራበት ወቅት ከተዋወቁት ባለቤቱ ዘርፌ አለሙ ጋር ከጣና በለስ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ተጋብተው አብረው ኖረዋል፡፡አዶኒስ እና ፓንዶራ የተሰኙ ሁለት ልጆችንም አፍርተዋል፡፡ ባለቤቱ ‹‹አድነው ድራማም፣ቴአትርም ሆነ መጽሀፍም ሲፅፍ መጀመሪያ ለእኛ ለቤተሰቦቹ አስነብቦን ስሜታችንን ከነገርነው በሁዋላ ነበር ወደ አደባባይ የሚያወጣው›› ስትል ለቤተሰቡ ያለውን ቅርበት እና በስራዎቹ እንኳ ሳይቀር ለቤተሰቡ የሚሰጠውን ቅድሚያነት ታነሳለች፡፡
ልጆቹን በጣም የሚያቀርበው አዶኒስ፤እንቁዎቹ ልጆቼ፣ወርቆቹ ልጆቼ በማለት በስስት ነበር የሚያያቸው፡፡የመጀመሪያ ልጁ አዶኒስ እንደ እራሱ መታየት ሆነ ከፊት መምጠት የማይፈልግ ሲሆን ሁለተኛ ልጁን ፓንዶራን ግን በገመና ድራማ አብረው ሰርተዋል፡፡በሙዚቃ ስራም የ12 ክፍል ትምህርቷን ስትጨርስ አብረው የመስራት ትልቅ ህልም ነበረው፡፡
የ አድነው ወንድራድ አዶኒስ ስንብት
መድረክ እና ካሜራ የማይወደው በዚህ ሁሉም በሚጋፋበት እይታን በሚፈልግበት ዓለም እንደ መነኩሴ ተነጥሎ ፍፁም ሰላም ባለው መልኩ በመኖር ህይወቱን አሳልፏል፡፡ በኒሞኒያ ህመም ምክንያት በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ህክምናውን ሲከታተል የቆየው አዶኒስ ነሐሴ 19 /2012 ዓ.ም ሕይወቱ አልፏል፡፡በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ነሀሴ 20 ቀን የቀብር ስነስርዓቱም ተፈፅሟል፡፡
የመጽሀፍ ነጋዴ እና የአዶኒስ የቅርቢ ሰው የሆነው ሙስጠፋ ናስር ‹‹አድነው ተዝቆ፣ተነቦ የማያልቅ መጽሀፍ ማለት ነው፡፡እኛ የተጠቀምንበት የመፅሀፉን መግቢያ ነው ማለት እችላለሁ፡፡መግቢያውን አንብበን ምዕራፎቹን ሳንጀምር ነው ያጣነው መጽሀፍ ማለት ነው እሱ፡፡ይህንን ምርጥ ሰው በዚህ መልኩ በማጣታችን ብናዝንም ለወደፊቱ 50 ዓመታት አብረውን የሚቆዩ ሥራዎችን ስላስቀመጠልን እንጽናናለን ፡፡››በማለት የአዶኒስ ስራዎች ገና የሚዘልቁ መሆናቸውን ምስክር ነው፡፡
በዚህች ምድር ከ1956 -2012 የቆየውን አዶኒስን ለመዘከር ጓደኞቹ የሙት ዓመቱ አንደኛ ዓመትን ጋዜጠኛ እና የቅርብ ወዳጁ ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳንን እና ወዳኞቹ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ተሰባስበው ነበር፡፡በዕለቱም የመጨረሻ ስራው የሆነውን 52 ክፍል ተከታታይ ፅሁፉንም ለጨረታ አቅርበው የአዶኒስ ህይወት ቢያልፍም መንፈሱ እና የጥበብ ስራው በምድር እንዲቆይ አስተዋፅኦቸውን አድርገዋል፡፡