ሻምበል ግዛው ዳኜ /1941-1993/
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡
የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ሻምበል ግዛው ዳኜ ይጠቀሳል፡፡ ሻምበል ግዛው ዳኜ በተለይ የፖሊስና ህብረተሰብ ሳምንታዊ የቲቪ መሰናዶ በ1989 እንዲጀመር ካደረጉ ባለውለታዎች አንዱ ነው፡፡ ከ1989 ቀደም ብሎ በፖሊስ ሬድዮ ላይ የማይረሳ ጉልህ አሻራ ማኖር የቻለ ነው፡፡ ይህንን የሻምበል ግዛው ታሪክን ስንሰራ ቤተሰቦቹ እና የስራ ባለደረቦቹ ላደረጉልን ትብብር ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡ የሻምበል ግዛው ዳኜን የህይወት ታሪክ ሀና ምንዳሁን እና እዝራ እጅጉ አጠናክረውታል፡፡
ትውልድ እና ልጅነት
ሻምበል ግዛው ዳኜ አባቱ አቶ ዳኜ በዳኔ ሲባሉ እና እናቱ ደግሞ ወ/ሮ የአቡንደጅ ገሰሰ ይባላሉ፡፡ ሻምበል ግዛው ዳኜ በ1941 ዓ.ም በስላሴ አውራጃ ፍቼ ተወለደ። እድሜው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ አስፋው ወሰን ትምህርት ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲከታተል ከቆየ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ተከታትሏል ።
ሻምበል ግዛው ሀገሩን በፖሊስነት ለማገልገል ስሜት እና ፍላጎት ስላደረበት ሀምሌ 1 ቀን በ1960 ዓ.ም በፖሊስ ሰራዊት ፈጥኖ ደራሽ በወታደርነት ደንብ ተቀጠረ፡፡ ሙያው የሚጠይቀውን የፖሊሳዊ ትምህርት ተከታትሎም ነበር፡፡ ሻምበል ግዛው በወቅቱ በነበረው ችሎታ በአጠቃላይ የፅህፈት ቤት ስራ አገልግሎት ትምህርት ከሰለጠነ በኋላ የፖሊስን ሙያ ለማዳበር በነበረው ከፍተኛ ጉጉት ራሱን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ በዚህ ሰአትም ባሳየው ችሎታ እና ጥረት ተመርጦ -በቀድሞ አጠራር አባዲና ፖሊስ ኮሌጅ በመግባት በኮሌጁ ለአንድ መኮንን የሚሰጠውን ፖሊሳዊ ሳይንስ አካዳሚክ ትምህርቱን አጠናቅቆ ህዳር 26 1974 ዓ.ም በም/መ አለቅነት ማዕረግ ለመመረቅ ችሏል።
ሻምበል ግዛው ከተመረቀ በኋላ ተዘዋውሮ የሰራባቸው ክፍሎች እንደሚመለከተው ናቸው
- በፈጥኖ ደራሽ ፖሊስነት መምሪያ ፀሃፊ
- በሸዋ ክፍለ ሃገር መናገሻ አውራጃ
- ኢሉባቡር ክ/ሀገር በፖለቲካ ሀላፊነት
- ኤርትራ ክ/ሀገር አሰብ አውራጃ ፖሊስ በወታደራዊ ግዳጅ
- በፖሊስ ሰራዊት ሬዲዮ ዝግጅት ክፍል በፕሮግራሙ አንባቢነት
- በምክትል ኃላፊነት በዋና አዘጋጅነትና በሬዲዮ ክፍል መሪነት እንዲሁም በፌዴራል ፖሊስ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን አገልግሎት በም/ክ አዘጋጅነት በዋና አዘጋጅነት ሙያዊ አደራውን ተወጥቷል፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በመደበኛ ፕሮግራም በዜና አንባቢነት እንዲሁም በፕሮግራም አዘጋጅነት ቅን አገልግሎት አበርክቶ ነበር። መኮንኑ በዚህ የረጅም ጊዜ አገልግሎት ዘመን ደረጃ በደረጃ ያገኘው የማዕረግ እድገት ህዳር 26 ቀን በ1974 የም/መ አለቅነት ታህሳስ 1 በ1976 የመ/ አለቅነት ታህሳስ 1 በ1981 የሻምበልነት ማዕረግ
ተወዳጁ እና አንጋፋው ጋዜጠኛ ሻምበል ግዛው ዳኜ በተለይ የሰራዊቱን መገናኛ ብዙሃን ለማጠናከር ከፍተኛ ትግል እና ጥረት አድርጓል ። ለረጅም አመታት በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን ባገለገለባቸው ጊዜያት በአድማጭ ተመልካቹ ዘንድ አንቱታን እና ከበሬታ ያገኘ እውቅ ሙያተኛ ነበር። ሻምበል ግዛው ዳኜ በረጅም ጊዜ የአገልግሎት ዘመኑ በፈፀማቸው መልካም ተግባራት በርካታ ሽልማቶችን እና የምስጋና ደብዳቤዎች ከእጁ ማስገባት ችሎ ነበር ። በተጨማሪ ለትምህርታዊ ጉብኝት ወደ አሜሪካ ሄዶ ልዩ ልዩ የምስክር ወረቀቶችን ተቀብሏል፡፡
ሻምበል ግዛው ከሀምሌ 1 ቀን 1960 ዓ. ም ህይወቱ እስካለፈበት ጥር 6 1993 ዓ.ም ድረስ ለ33 አመታት ያህል ሰራዊቱን በቅንነትና በታማኝነት አገልግሏል ። ሻምበል ግዛው ባደረበት ህመም ምክንያት መንግስት ባደረገለት ከፍተኛ ድጋፍ በሳውዲ አረቢያ ህክምና ሲያደርግ ቆይቶ ወደ ሀገሩ ከተመለሱ በኋላም ከህመሙ ስላልዳነ በፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ52 ዓመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል ። ሻምበል ግዛው ዳኜ የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር፡፡
ምክትል ኮማንደር ብርቄ ወልደገብርኤል የሰጠችው ምስክርነት
ሻምበል ግዛው በሬድዮ ክፍል ከሪፖርተርነት አንስቶ እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት ቀጥሎም በቴሌቪዥን ዝግጅት ክፍል በዋና አዘጋጅነት ሲሰራ ቆይቷል። በባህሪው ስራ ወዳድ ፣ ቅን ፣ሰዎችን በቀላሉ መግባባት የሚችል ፣ በፖሊስ ስነ-ምግባር የተካነ በሙያው የተመረጠ ጎበዝ ሰው ነበር። ሻምበል ግዛው በስራ ጉዳይ ላይ ቀልድና ቸልተኝነት አያውቅም፡፡ ልግመኝነትና ስንፍና በግዛው ፊት ቦታ የሌላቸው ሲሆን እጅግ በጣም በስራው ላይ ኮስታራ ነው። የሬዲዮም ይሁን የቴሌቭዥን ዝግጅት ክፍል ስራ በአብዛኛው የቡድን ስራ እንደመሆኑ መጠን ለግዛው በቡድን ይሁን በተናጠል ስራ ችግር አይታይበትም ነበር። ተለይቶ ከሁሉም የሚታወቅበት ስራው ሁሉም ፅሁፎች በሚማርክ እና ወርቃማ በሆነው ድምፁ ማንበቡ ግንባር ቀደም ያደርገዋል። ለዚህም የምርመራ ማህደር ፣ የአድማጮች ደብዳቤ ፣ በሬድዮ መሰንበቻው ፣በቴሌቪዥን ፖሊሳዊ ዜና ፣ እንዲሁም የጠፉ ቤተሰቦችን የማፈላለግ ስራው የሚጠቀሱ እና በአድማጭ ተመልካቹ ዘንድም የማይረሱ ስራዎቹ ናቸው።
ሻምበል ግዛው ስለ ሃገር ፣ ስለ ጀግና ፣ ስለ እናት ፣ ስለ ፍቅር በአጠቃላይ ስሜቱን ይዞ ያነሳሳውን ሃሳብ በግጥም ሲፅፍ እና ሲያነብ ባለወኔውን ወኔውን ይጨምርለታል፡፡ ጀግኖችን ይበልጥ ያጀግናል፡፡ ሆደ ባሻውን ይበልጥ ያስለቅሳል። የግዛው መለያዎች ግጥም ከመውደዱ እና ከመዝናናት ባለፈ ጥሩ ሳቢ ድምፅ ነበረው። የግዛው ሌላው ያኖረው ትልቅ አሻራ የፖሊስና ህብረተሰብ የቲቪ ፕሮግራም እንዲጀመር ማድረጉ ነው፡፡ የፖሊስ የሬድዮ ፕሮግራም እንደተቋቋመ ሁሉ ቀደም ባሉት የስራ ሃላፊዎች የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመጀመር አቅደው ነበር፡፡ ነገር ግን እንዲህ በቀላሉ ሊሳካላቸው ስላልቻለ ሻምበል ግዛው ዳኜ አንድ ነገር ማድረግ ነበረበት፡፡
ሻምበል ግዛው የኢቲቪ ዜና አንባቢ ሆኖ በሚሰራበት ወቅት በቀላሉ ከአለቆቹ ጋር በነበረው ተደማጭነት እና ተቀባይነት የፖሊስ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመጀመር ክፍሉ እንደሚፈልግ ተናግሮ በቀላሉ ተቀባይነት አገኘ፡፡ ተገቢው ፈቃድ ከተገኘ በኋላም ፕሮግራሙ አየር ላይ እንዲውል እና ሙያተኛ እንዲመደብ አድርጓል። በፕሮግራሙ ዝናን እንዲሁም በተመልካቾች ዘንድ የማይረሳ የቴሌቪዥን ዝግጅትን ፈጥሯል። ፕሮግራሙ እስካሁንም በዝግጅት ክፍሉ ስራው እንደቀጠለ የሚገኝ ነው::
አበበ ሙሉጌታ ስለ ሻምበል ግዛው ዳኜ
ከሻምበል ግዛው ዳኜ ጋር እዚሁ አዲስ አበባ የእኔም የእርሳቸውም ቤተሰቦች የአንድ ቀበሌ እና መንደር ማለትም ኮልፌ ቀበሌ 06 ውስጥ በመሆናቸው የመቀራረብ እድል ነበረን፡፡ በይበልጥ ግን በተለየ ትኩረት ላውቃቸው የቻልኩት በእኔ የታዳጊነት እድሜዬ ነበር፡፡ ያኔ ጋዜጠኝነት በጣም የሚከበር ሙያ ስለነበር እኔም ዝንባሌው ነበረኝ፡፡ ሻምበል ግዛው ደግሞ በጊዜው ዝነኛ ነበሩ፡፡ የሻምበል ግዛው ሳቢነት ፣ አቋም እና ግርማ ሞገስ የድምፃቸው ለዛ እና አስገምጋሚነት ይስበኝ ነበር፡፡ እርሳቸውን የመሆን ምኞቴንም ለማሳካት እጥር ነበር፡፡
1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ በተከሰተ ጊዜ አቋርጦ የነበረው የሬዲዮ ፕሮግራም እንደገና እንዲቀጥል ተወስኖ ነበር፡፡ የአየር ስርጭቱን ለመጀመር ሲሰናዱ እኔም መስፈርቱን አሞልቼ የሬዲዮ ጀማሪ ሪፖርተር ሆኜ ከሻምበል ግዛው ጋር ባላቸው ትልቅ ብቃት እያስተማሩ በተግባር እየፈተኑ ያበቁን ታላቅ ሙያተኛ ነበሩ። ከሻምበል ግዛው ዳኜ ጋር በሬዲዮ ፕሮግራም ላይ በተጨማሪ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተጀምሮ ለስርጭት እንዲበቃ ያደረጉ ትልቅ ሰው ሲሆኑ የማይረሳ ታሪክ የሰሩ የሃገር ባለውለታ ናቸው።
ኮማንደር አሰበ ፃዲቅ ኮስትሬ ስለ ሻምበል ግዛው ዳኜ
ከሻምበል ግዛው ጋር ከ1977 ጀምሮ አብረው በስራ የቆዩ ነበሩ፡፡ ሻምበል ግዛው ዳኜ ታማኝ እና ታታሪ ነበር፡፡ባለው ዕውቀት ስራውን በትጋት የሚመራ እንዲሁም የጀመረውን ጉዳይ በትጋት የሚፈፅም እና ለውጤት የሚያበቃ ነበር።ከሻምበል ግዛው ጋር ረጅም አመት አብረን ሰርተናል፡፡ እንደ ስራ ባልደረባም የሚመክረን በተሰማረንበት የስራ መስክ ውጤታማ እንድንሆን እና በአግባቡ እንድንሰራ ይገስፀን እና ስራችንን ወደነው እንድንሰራ ምክር ይለግሰን ነበር፡፡ ከሻምበል ግዛው ዳኜ ጋር የመጨረሻ ጊዜያችን መደበኛ ስራችን በመስራት ላይ እያለን በአጋጣሚ ታሞ ነበር፡፡ ወድያው ህክምና ሲረዳም ቆይቶ ለተሻለ ህክምና ወደ ዉጪ ሀገር በመሄድ ህክምናውን ጨርሶ መጣ። ህክምናውን ከጨረሰ በኃላም ከኢትዮጵያ አምባሳደር ጋር ኢንተርቪው አድርጎ የነበረ ሲሆን ከ ሻምበል ግዛዉ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተለያየነዉ በዚህ ነዉ።
ሻምበል ግዛዉ ሁለገብ የሚዲያ ዕዉቀቱ በጣም ጥሩ የነበረ እና ዕውቀቱንም ለጓዶቹ የሚያካፍል የሚመክር ደካማ እንዳንሆን እና የተቋማችንን ስም በመልካም እንድናስጠራ ስራችንንም በአግባቡ እንድንሰራ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና በሬዲዮ ተወዳጅ እና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ነበረው። በዚህም እወደው እና አክብረው ነበር። ከሻምበል ግዛው ዳኜ ጋር ለብዙ አመታት በፌዴራል ፓሊስ ውስጥ አብረው የሰሩ ሲሆን ወ/ሮ እምወድሽ በቀለ ስለ ሻምበል ሲናገሩ ከሩቅ ለሚያየው ኮስተር ያለ ቢመስልም ቀርቦ ካዩት በኋላ ግን በጣም ቀለል ያለ ቁምነገር የሚያውቅ ፣ መልካም ሰው ነበር ማለት ይቻላል። በተለይም ስራ ወዳድ መሆኑ በስራው ወደኋላ የማይል እንደማሳያም ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ ፕሮግራም ከሃሳቡ አንስቶ እስከ መጨረሻው ዳር አድርሶ ማሳየት የቻለ ሲሆን ይህም ቁርጠኛነቱን ያሳያል። በአለቅነቱ ከሱ በታች ያሉት የስራ ባልደረባዎች ወደእሱ እንዲቀርቡ ያደርግም ነበር። በተለይም በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን ስራ ውስጥ ብዙዎች እንዲሰሩ አድርጓል። ሻምበል ግዛው ተግቶ የሚያተጋ የስራ ሰው ነው።
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ-አእምሮ የቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ሻምበል ግዛው ዳኜ ከ25 አመት በፊት በዜና አንባቢነቱ ከብዙዎች ልብ የማይጠፋ በተለይ የዛን ጊዜዎቹ የቲቪ ተመልካቾች ፈጽሞ የማይዘነጉት ነው፡፡ ሻምበል ግዛው ዜና አንባቢ ብቻ ሳይሆን የፖሊስና ህብተረሰብ ዝግጅት እንዲጀመር ትልቁን አሻራ ያኖረ ነው፡፡ የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ በመሆንም አዘጋጆችን መርቷል፡፡ ህይወቱ ካለፈ 22 አመት የሆነው ሻምበል ግዛው በተለይ የፖሊስ ሚና በሚድያ ላይ ምን ሊሆን እንደሚገባ በግልጽ ያሳየ ነው፡፡ ነገር ግን ህይወቱ ካለፈ በኋላ እንኳን ብዙም ሲነገርለት አንሰማም፡፡ ኢትዮጵያ የሰሩላትን ማስታወስ አለባት፡፡ ትናንት የተሄደበትን መንገድ ማወቁ ለአዲሱ ትውልድ ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም፡፡ የቀደሙ ባለውለታዎችን ማስታወስ መሰልጠን ነው ብለን እናምናለን፡፡
በተለይ እንደ ሻምበል ግዛው ስማቸው ብዙም የማይነሳ ሰዎችን ማንሳት ትልቅ ሃላፊነት ነው ብለን እናምናለን፡፡ ሻምበል ግዛው ብዙም ሲነገርለት አንሰማም ስንል በሚድያዎች እና በማህበራዊ ትስሰር ገጾች ማለታችን እንጂ የቅርቦቹ እና ቤተሰቦቹ ሁሌም ያስታውሱታል፡፡ የእኛም ግብ አስታውሶ መሰነድ ነውና ለባለእዳነት ለመላቀቅ የቤት ስራችንን ሰርተናል፡፡ ሌሎች ስለ ግዛው ዳኜ መረጃ ያላቸው ሀሳብ እና ምስክርነት ሲያክሉበት የስነዳ ስራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የሻምበል ግዛው ዳኜ የቀድሞ ብዙም ያልታዩ ምስሎች የተካተቱ ሲሆን በቅርብ የሚያውቁትም ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ ይህም ለሻምበል ግዛው ዳኜ እንደ መነሻ ትልቅ ማስታወሻ ይሆናል፡፡ ይህ ጽሁፍ በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች እና በመዝገበ-አእምሮ ቅጽ 2 መጽሀፍ የሚካተት ይሆናል፡፡