ዓለማየሁ ታደሰ

ዓለማየሁ ታደሰ

ዓለማየሁ ታደሰ የቴአትር ተዋናይ፤ አዘጋጅ፤ደራሲ እና መምህር


የሕይወት ታሪክ አዘጋጅ ዓይናለም ሀድራ

ዓለማየሁ ታደሰ፤ ከአባቱ አቶ ታደሰ ደምሴ ፤ከእናቱ ወ/ሮ ስንቅነሽ አዘነ ሐምሌ 19 ቀን 1964 ዓ.ም በሐረር ከተማ ቀበሌ 12 (ቀላድ አምባ) ተወለደ። የፊደል ትምህርቱን አጠናቅቆ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በቀላድ አምባ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፤7ኛና 8ኛ ክፍልን በአርበኞች መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ከ9ኛ እስከ 12ተኛ ክፍል በሐረር መድኃኔዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል። በትምህርቱም ጎበዝና ተወዳጅ የደረጃ ተሸላሚ ተማሪ ነበር።


መፅሐፍትን ማንበብ፤ሬድዮ ማዳመጥ፤ፊልም እና ቴአትሮች መመልከት እና መልሶ ለጓደኞቹ መተረክ የሚወደው ዓለማየሁ ከትወና ጋር የተዋወቀው መድሐኔ ዓለም ት/ቤት 40ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ባከበረበት ወቅት ነው፡፡ የተ.መ.ድ.ን መሰል (simulation) የስብሰባ ትርኢት ላይ የደቡብ አፍሪካ ተወካይ ሆኖ ባቀረበው የንግግር ትወና እና የፀጋዬ ገ/መድህን ‹‹የመቅደላ ስንብት›› ዐፄ ቴዎድሮስን ሆኖ ባቀረበው መነባንብ አድናቆትን አትርፎ ትወናን ተዋወቀ።
በ1982 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የገባው ዓለማየሁ፤ በ1983 ዓ.ም የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍልን አንደኛ ምርጫው አድርጎ ተቀላቀለ። በቆይታውም በአ.አ.ዩ. ባህል ማዕከል እና በ5 ኪሎ ድህረ ምረቃ አዳራሽ በቀረቡ በርካታ ተውኔቶች ላይ የትወና አቅሙን አስመስክሯል፡፡ በ1986 ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲው ተመርቆ እስኪወጣ ድረስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ‹‹ኤዲፐስ ንጉስ›› እና ‹‹ከአድማስ ባሻገር›› እና በሐገር ፍቅር ቴአትር ‹‹ተውኔቱ›› እና ‹‹የኮከቡ ሰው›› ቴአትሮች ላይ ባሰየው የትወና ክህሎቱ አድናቆትን አትርፏል፡፡
ጥቅምት 1፤1987 ዓ.ም የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽን Picninc on the Battle Field በተሰኘ የእንግሊዘኛ ቴአትር የተቀላቀለው ዓለማየሁ በ1988 ዓ.ም. በ‹‹ቼዝ ዓለም›› ቴአትር በትወና ውድድር 1ኛ በመውጣት በ15 ግራም ወርቅ ሽልማትን ሀ ብሎ ጀመረ፡፡ ከ1990 ጀምሮ ለአራት ዓመታት በቆየበት ሜጋ ኪነ-ጥበባት ማዕከል የትወና ጣራ የደረሰባቸውን ‹‹አንቲገን›› እና ‹‹ጓደኛሞቹ››ን ጨምሮ በርካታ ቴአትሮችን ሲያቀርብ፤በ1994 ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በመግባት በትወና፤በድርሰት፤ በዝግጅት፤በማስተማር፤መርጃ መፃሐፍትን በማዘጋጀት፤ተውኔቶችን በመገምገም የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡


በታሪክ ነገራ (Story-Telling) በስዊድን እና ኡጋንዳ የአንድ ሰው ትርኢት በእንግሊዘኛ ካቀረበው፤ በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ለ22 አመታት በመድረክ የቆየውን እና በአውሮፓ ከተሞችም አድናቆት ያተረፈበትን ‹‹ባቢሎን በሣሎን››ን ጨምሮ 35 በሚደርሱ ቴአትሮች ላይ ምርጥ ተዋናይነቱን አስመስክሯል፡፡ በደራሲነት ‹‹ያልተወለደው ልጅ››፣‹‹የጨጓራ ፍቅር››፣‹‹የሰው ዓይን›› የተሰኙ አጫጭር ተውኔቶች፣‹‹የሚተኑ አበቦች››(በቡድን)፤‹‹በትረ-አዳም››(የብዕር ሥም)፣‹‹ሚስጢረኞቹ››፣‹‹ትዳር ሲታጠን››፣‹‹ጣሴ››(የህፃናት) የሙሉ ጊዜ ተውኔቶችን ፅፎ ሲያቀርብ፤ ‹‹ደመ-ነፍስ›› እና ‹‹ጀነራሉ››ን በአዛማጅ ትርጉም ለህዝብ አበርክቷል፡፡‹‹የብዕር ሥም››፤‹‹ይግባኝ››፤‹‹ባተሌው›› ያዘጋጃቸው ሲሆኑ በረዳት እና ቴክኒካል ዳይሬክተርነትም በርካታ ቴአትሮችን ለመድረክ አብቅቷል፡፡


ከጓደኞቹ ጋር ‹‹ሆሊላንድ የጥበብ አካዳሚ››ን በማቋቋም ወጣቶችን ከሞያው ጋር ያጨባበጠ ሲሆን፤ በብሔራዊ ቴአትር፤በክልል ከተሞች ከሰጣቸው ስልጠናዎች በተጨማሪ በአ.አ. ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ክፍልም በተጋባዥ መምህርነት ለተተኪዎች ዕውቀቱን አጋርቷል፡፡
የቴአትር፤የፊልም፤የቴሌቪዥን፤የሬድዮ ተዋናይ፤ተራኪ፤ አዘጋጅ ፤ደራሲ፤መምህር፤የማስታወቂያ ባለሙያ፤ የበርካታ ድርጅቶች የብራንድ አምባሳደር ዓለማየሁ ታደሰ በቴአትሩም በፊልሙም ‹‹የበጎ ሰው››፤‹‹ለዛ››፤ ‹‹ጉማ››፤‹‹የኢ.ፊ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር››ን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን የተጎናፀፈ ሲሆን ‹‹አድዋ መልቲ ሚዲያ›› በተሰኘ ድርጅቱ ቴአትር ፤ፊልም እና የማስታወቂያ ሥራዎችን እየሰራ ሲሆን ከጥር 1/1995 ጀምሮ ከተዋናይት ማርታ ጌታቸው ጋር በትዳር ተጣምሮ በእምነት፤አሜን እና ማርያማዊት የተባሉ ሁለት ወንዶች እና አንዲት ሴት ልጅ አፍርቷል፡፡

ል።