ጀማል አህመድ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ‹‹መዝገበ-አዕምሮ›› በሚል ርዕስ የ180 የሚድያ ሰዎችን ታሪክ በመጽሀፍ አሳትሞ ሀምሌ 30 2014 ዓ.ም ማስመረቁ ይታወቃል፡፡ በቀጣይ ደግሞ መዝገበ-አዕምሮ ቅጽ ሁለት በሚል ርዕስ በቅጽ 1 ያልተካተቱ ሰዎች በቅጽ 2 ይካተታሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱ ጀማል አህመድ ነው፡፡ ጀማል ላለፉት 26 አመታት በሚድያው አለም የቆየ ሲሆን በተለይም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አማካይነት ባኖረው ትልቅ አሻራ ይታወቃል፡፡ የጀማል አህመድን የህይወት ገጽ እንዲህ እንፈትሻለን፡፡
ውልደትና እድገት
ጀማል አህመድ በ1964 ዓ.ም አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ነበር የተወለደው ፡፡ አንበሳ ግቢ ጀርባ ካለው ነዳጅ ማደያ ፊት ለፊት የተወለደበት መኖሪያ ቤት በኋላ መገናኛ ሻይ ቤት በሚል ንግድ ቤት ሆኗል ፡፡ አባቱ አቶ አህመድ ሹሬና እናቱ ወ/ሮ ሐጀር አብደላ በንግድ ስራ ነበር የሚተዳደሩት፡፡ በ1960ዎቹ መጨረሻ ቤተሰቦቹ መሳለሚያ እህል በረንዳ 01 ቀበሌ መኖሪያ ቤት ሲገዙ የጀማል እድገትና ውሎ ስድስት ኪሎና መሳለሚያ ሆነ ፡፡ አባቱ ከንግድ ስራው ባሻገር በወቅቱ በነበረው ፖለቲካ ጠንካራ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡
ትምህርት ቤት
በ1970ዎቹ መጀመሪያ አባቱ አህመድ ሹሬ ጸረ-አብዮተኛ ተብለው በድንገት በደርግ ታጣቂዎች ተይዘው እንደወጡ ቀሩ ፡፡ የአባቱ ድንገት ወጥቶ መቅረት ቤተሰቡ ውስጥ በፈጠረው ችግር ጀማል ትምህርቱን አንድ ቦታ ተረጋግቶ መማር አልቻለም ፡፡ በልጅነቱ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ገብቶ ተምሯል ፡፡ ስድስት ኪሎ አካባቢ ንጋት ኮከብ ፣ ሽሮ ሜዳ ድላችን ፣ መሳለሚያ ዳግማዊ ብርሃን ፣ ፒያሳ አፍሪካ አንድነት ፣ የካቲት 23 ት/ቤት ፣ አራት ኪሎ ብሄራዊ ቤተ- መንግስት ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ከፍተኛ 12 አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱንም በ1984 ዓ.ም አጠናቀቀ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪውን በቋንቋና ሥነ-ጽሁፍ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ በዶክመንተሪ ሊንጉስቲክስ ኤንድ ካልቸር አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተምሯል ፡፡
ስድስት ኪሎ ፣መሳለሚያና ጀማል
ስድስት ኪሎ መገናኛ ሻይ ቤት ከትምህርት መልስ እናቱን እያገዘ ይውላል፡፡ ተጨማሪ ጊዜ ሲያገኝና በእረፍት ጊዜው ጃንሜዳ ከሠፈር ጓደኞቹ ጋር ኳስ ይጫወታል ፡፡ በእግር ኳሱ አልገፋበትም እንጂ ለትምህርት ቤቱ ፣ለቀበሌና ለአንድ የእግር ኳስ ክለብ የታዳጊዎች ቡድን ተሰልፎ መጫወት ችሎ ነበር ፡፡
ስድስት ኪሎ ሻይ ቤት ውስጥ የሚሰባሰቡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በሥነ-ጽሁፍ ጉዳይና በሀገራዊ ጉዳዮች የሚያደርጉት ውይይት ፣ አዳዲስ መጽሐፍት ሲወጡ ለአይነ- ስውራን ማራኪ ድምጽ ባላቸው ወጣቶች ሲተረክ ቁጭ ብሎ ማዳመጡ፣በተመሳሳይ መልኩ መሳለሚያ እህል በረንዳ 01 ቀበሌ ያለው ማህበራዊ ሕይወትና የተለያዩ ክስተቶች ጋዜጠኛና የሥነ-ጽሁፍ ሰው እንዲሆን አዎንታዊ ተጽእኖ አሳድረውበታል ፡፡
ፍካት የስነ-ጽሁፍ ክበብ
በ1980 ዎች አጋማሽ ፍካት የሥነ-ጽሁፍ ክበብን ተቀላቀለ፡፡ ስለሥነ-ጽሁፍ ያለው ግንዛቤ ይበልጥ ከፍ ያለው ፣የአጻጻፍ ክህሎቱን ያዳበረውና እውቅ የሥነ-ጽሁፍ ሰዎችንና ጋዜጠኞችን ያወቀው እዚህ ክበብ ውስጥ ከገባ በኋላ ነበር ፡፡ አሁን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በኃላፊነትና በሙያቸው የሚሰሩ ጓደኞቹን ነብዩ ጥኡመልሳንን፣ በቀለ ሙለታን(አንቀፀ ደስታን ) ፣ አለማየሁ ገላጋይን ፣ ታደሰ ማሞን ፣ አሰፋ መኮንን፣ ዳንኤል ብርሃኑን ፣ አለማየሁ ታዬን ፣ ጌታቸው ሠናይን ፣ስንዱ ኃይሌን ፣ዮሴፍ ኃ/ማርያምን፣ ፍሬው አበበን ፣ ብዙነህን ፣ አስቴር በዳኔንና ሌሎችንም የተዋወቀው ፍካት የሥነ-ጽሁፍ ክበብ ውስጥ ነው ፡፡ መጣጥፎቹንና አጫጭር ልቦለዶቹን እውቅ ደራሲያንንና ጋዜጠኞች ገምግመውለታል፡፡ ፍካት በሚያዘጋጀው መድረክም እያገኛቸው ልምዳቸውንና ምክራቸውን ስምቷል ፡፡ ደራሲና ጋዜጠኛ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ፣ የሺጥላ ኮከብ ፣ ደምሴ ጽጌ፣ አብርሃምረታ አለሙ ፣ ኃይለመለኮት መዋዕል ፣ ጋሽ አስፋው ዳምጤንና፣ ብርሃኑ ገበየሁ ፣ ጎበና ዳንኤል እና ሌሎቹም በፍካት አማካይነት የተዋወቃቸው ናቸው ፡፡
የፍካት ሥነ-ጽሁፍ አባል መሆን ብቻ ሳይሆን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣና የዛሬዬቱ ኢትዮጵያ የመጽሐፍ ግምገማዎችን ፣ ማህበራዊ ትችቶችን ፣የተለያዩ የውጭ የሥነ-ጽሁፍና ታዋቂ ሰዎች ግለ-ታሪክ ላይ የሚያተኩሩ መጣጥፎች በተለያዩ አምዶች ላይ በማውጣት ተነበውለታል ፡፡ ጀማል ለጋዜጦች ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሬዲዮና ለሬዲዮ ፋና ጽሁፎች በመላክ ይሳተፍ ነበር ፡፡
ጀማል ፍካት የሥነ-ጽሁፍ ክበብ አባል እያለ በራሱ ተነሳሽነት ያዘጋጀውና እነ ፊርማዬ አለሙ፣ አረጋሽ ሠይፉ ፣ መስከረም አበራ፣ ስመኝ ግዛው ፣ ስንዱ ኃይሌ፣ሄለን መሐመድና ቤተልሄም ክፍሌ የተሳተፉበት የሴት ገጣሚያን ምሽት ከፍተኛ ተወዳጅነት ከማግኘቱ በተጨማሪ በኋላ የሴት ደራሲያን ማህበር እንዲቋቋም ምክንያት ሆኗል ፡፡ የፍካት አባላት በጋራ በ1994 ዓ.ም በሳተሙት ‹‹ዜማ›› የአጭር ልቦለዶች ስብስብ ውስጥ የጀማል 2 የአጭር ልቦለድ ሥራዎቹን አካቷል ፡፡
የጋዜጠኝነት ስራ አጀማመር
ዜና አዲስ
ጀማል ለመጀመሪያ ጊዜ የጋዜጠኝነት ስራውን የጀመረው በ1988 ዓ.ም ጋዜጠኛ ደረጀ ደስታና አለማየሁ ገላጋይ ጋር በመሆን ‹‹ዜና አዲስ›› የምትል ጋዜጣ በጋራ በማዘጋጀት ነበር ፡፡ ሰፊ የጋዜጠኝነት ልምድና እውቀት ከነበረው ደረጀ ደስታ ስለዜና አዘጋገብ ፣ አጀንዳ ቀረጻና ስራ በአጭር ጊዜ ስለመስራት ትምህርት ያገኘበት ጊዜ ነበር ፡፡ ዜና አዲስ ጋዜጣ ጀማል አህመድ ለመጀመሪያ ጊዜ ደሞዝ ያገኘበት ስራ ነው ፡፡ በመጀመሪያ ወር የተከፍለው 300 ብር ሳያጠፋው ለረጅም ጊዜ በኪስ ቦርሳው ላይ አስቀምጦታል ፡፡ ከወራት በኃላ ገንዘቡን መጠቀሙ ግድ ሲሆን የብሮቹ ኖት ላይ ያሉ ቁጥሮቹን መዝግቦ አስቀምጦ ነበር፡፡
ኢቲቪ
ጀማል ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የተቀጠረው በ1989 ሰኔ 1 ቀን ነበር ፡፡ በወቅቱ የሥራ ቅጥር ፈተናውን አልፈው ከጀማል ጋር የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ስራ የጀመሩት ስለሺ ሽብሩ ፣በቃሉ ዘመነ ፣ እስክንድር ፍሬው ፣ ፋሲካ ከበደ ፣ ታደሰ በላቸው ፣ ገለታ ፋንታውና በፍቃዱ አሰፋ ነበሩ፡፡ መጀመሪያ ዜና ክፍል የተመደበው ጀማል ገና በጥቂት ቀናት ውስጥ ነበር ታላላቅ ሁነቶችን መዘገብ የጀመረው ፡፡
በጋምቤላ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒሰትር የነበሩት አቶ መለስ ፤ አቶ ተፈራ ዋልዋና ሌሎች ባለሥልጣናት የተገኑበት ረጅም ቀናት የፈጀ የክልሉን የመገምገሚያ መድረክ ላይ በመገኘት ተከታታይ ሪፖርት በማቅረብ ፣ በሱማሌ ክልል ከባድ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ ጎዴ ፣ ቀላፎ ፣ ፊርፌር እና ከሱማሌ በሚያዋስን ጠረፍ ድረስ በሄሊኮፕተር በመሄድ እጅግ አድካሚና ፈታኝ ስራዎችን ሰርቷል ፡፡ ከሁሉም በላይ አስከፊውን የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ለመዘገብ በጾረና ግንባርና በዛላንበሳ የጦር ግንባር ተመድቦ የጋዜጠኝነት ሙያዊ አገልግሎቱን አበርክቷል ፡፡ ከትግራይ ክልል እንትጮን ፣ አክሱምን ፣ አድዋን ፣ አዲግራትንና መቀሌን በሚገባ ያውቃቸዋል ፡፡
ጀማል ዜና ክፍል በሪፖርተርነት፣ በዜና አዘጋጅነት ፣ ከየአቅጣጫው ፣ ልዩ ወቅታዊ ዝግጅቶች በማዘጋጀትና አፍሪካ ጆርናል ተርጉሞ በማቅረብ የሰራቸው ስራዎች ይጠቀሳሉ ፡፡ ከዜና ክፍል በኋላ ረጅሙን የስራ ጊዜ ያሳለፈው በ120 መዝናኛ ክፍል ነው ፡፡ በወቅቱ በመዝናኛ ዝግጅት ክፍል መልካም ስም የነበራቸውን ለቀው የወጡትን የግርማ ደገፋና ኃይሉ ታምራት ስራዎችን ለማስቀጠል ሞክሯል ፡፡ በተለይ ግርማ ደገፋ የሚታወቅበትን ከአድማስ ባሻገርን ለተወሰነ ጊዜ እያዘጋጀ አቅርቧል ፡፡በ 120 ዝግጅት የታዋቂ ሰዎች ግለ- ታሪከ ላይ ትኩረት በማድረግ ከኪነ- ጥበብ ባለሙያዎች ጥላሁን ገሠሠን ፣ ታምራት ሞላን ፣ የሐመልማል አባተን ፣ የቴዎድሮስ ካሳሁንን፣ በዛወርቅ አስፋው ፣ ይሁኔ በላይ ፣ ፍቅር አዲስን ፣ ህብስት ጥሩነህን ፣ ፀሐዬ ዮሐንስን ፣ ደረጄ ደገፋን ፣ተሾመ ወልዴን ፣ ጌታቸው መኩሪያን ፣ኮ/ሌ ሰሃሌ ደጋጎን ፣ ግርማ ይፈራሸዋን ፣ ተሾመ አሰግድን ፣ ራሄል ዮሐንስን ፣ ኩኩ ሰብስቤን ፣ ዳዊት መለሰን ፣ ሠራዊት ፍቅሬንና ሙሉዓለም ታደሠን ፣ ክበበው ገዳን፣ ሠይፉ ፋንታሁንና ብርሃኔ ንጉሴንና ሌሎችንም ቃለመጠይቅ በማድረግ በልዩ አቀራረብ ለ120 ታዳሚዎች በማድረስ ትኩረትን ስቦ ነበር ፡፡ በቁንጅና የውድድር መድረኮች በመገኘትም ሐያት አህመድ ፣ ሳያት ደምሴና ሳራ መሐመድን ከህዝብ ጋር አስተዋውቋል፡፡
ከመንግስት የሥራ ኃላፊዎች የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ አርክበ እቁባይ ፣የአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴን ፣ አምባሳደር መሐመድ ድሪር ፣ የሐርሪ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሙራድ አብዱላሂ እንዲሁም ከጋዜጠኞች እና ደራሲያን የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኛው አዲሱ አበበን፣ ሚሚ ሰብሃቱን ፣ ዘነበ ወላን ፣ ሲሳይ ንጉሱን ፣ ሀዲስ አለማየሁን ፣ ቃለ-መጠይቅ አድርጎላቸዋል ፡፡
አትሌት ኃይሌ ገብረ ስላሴ ፣ ደራርቱ ቱሉን ፣ ቀነኒሳ በቀለን ፣ መሠረት ደፋርን ፣ ጌጤ ዋሚን ፣ አሰፋ መዝገቡ ፣ ገረመው ደንቦባና ሌሎችንም ከአትሌቶች የጀማል አህመድ እንግዳ ሆነው በፕሮግራሙ ቀርበዋል ፡፡ የበዓል ልዩ የመዝናኛ ዝግጅቶችን በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች በማዘጋጀትና በማስተባበር ከባልደረቦቹ ጋር አዘጋጅቶ አቅርቧል ፡፡
ከእነዚህ ስራዎች በተጨማሪ አንድሪው ሎረንስ የተባለ አሜሪካዊ ስዩም ቻቻ የተባለና በአካል የማያውቀውን አባቱን ፍለጋ መጥቶ አፈላልጎት ስለቤተሰቦቹና ስለአባቱ አማሟት የሰራው ፕሮግራም ፣ ሐና የተባለችና በልጅነቷ ለማደጎ ተሰጥታ ቤተሰቦቿ የት እንዳሉ የማታውቅ ኢትዮጵያዊት ፣ እንዲሁም ማይክ ኤሊስ የተባለ አሜሪካዊ አርቲስት በልጅነት ያሳደገችውን ኢትዮጵያዊት ፍለጋ መጥተው ጀማል ቤተሰባቸውን እንዲያገኙ ያስቻለና ለተመልካችም አዝናኝና አስገራሚ ፕሮግራም ለመስራት ችሏል ፡፡
ጋዜጠኛ ጀማል አህመድ ቃለ-መጠይቅ በሚያደርግበት ወቅት በሚያቀርባቸው ለየት ያሉ ጥያቄዎች ይታወቃል ፡፡ ለምሳሌ ከይሁኔ በላይ ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ የባለቤቱና የይሁኔን ሰፊ የእድሜ ልዩ ጠይቆ መነጋገሪያ መሆኑ ፣ አቶ አርከበ እቁባይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ጊዜ ‹‹ የመርካቶ ነጋዴዎች እርስዎን በአምቦ ውሀ ነው የሚመስሎት ምግብ ቤት ገብተው አምቦ ውሀ ለማዘዘት ‹አንድ አርከበ አምጣልኝ › ይላሉ ይህን ሰምተው ይሆን ? ›› በሚል ጥያቄ በማቅረቡ መነጋሪያ ሆኖ ነበር ፡፡ ጀማል ይህን ጥያቄ መጠየቅ ነበረበት ወይስ አልነበረበትም? በሚል ጋዜጣ ላይ አከራካሪ ሆኖ ሲጻፍበት ነበር ፡፡
ሌላው በአንድ ወቅት ልጃገረዶች የሚሸለሙበት ‹‹የድንግልና›› ውድድር መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር ፡፡ ዓላማው ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከል በማሰብ ነበር ፡፡ ይህን ውድድር ያዘጋጀችውን ወጣት ድንገት በቃለመጠይቁ መሐል ‹‹ ለመሆኑ አንቺ ድንግል ነሽ ወይ? ›› ብሎ ጠይቆ አስደንግጧታል ፡፡ እርሷም ‹‹ አይደለሁም ›› በማለት በግልጽ በማናገሯ አመስግኗታል ፡፡ እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎቹ በ120 ተመልካቾች ዘንድ አነጋጋሪና ጀማል አህመድ እንግዳ ይዞ ሲቀርብ ዛሬ ደግሞ ምን የተለየ ነገር ሊጠይቃቸው ይሆን? በሚል የሚጠበቅ ነበር ፡፡
ጀማል እንደ ተዋናይ
ጀማል አህመድ ከጋዜጠኝነት ሙያው ውጭ በፊልም አዘጋጆች ጋባዥነት በሁለት ፊልሞች በተዋናይነት ሰርቷል ፡፡ ጀማል በ1997 የካቲት ወር በገዛ ፍቃዱ ኢቲቪን እስከ ለቀቀበት ጊዜ ድረስ ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ በተለያዩ የኃላፊነትና የኮሚቴ ስራዎችን በመምራትና በአባልነት አገልግሏል ፡፡
ጀማልና በአዲስ አመት ልዩ የበዓል ዝግጅት አሳዛኝ የሽብር ዜና
እንደ ሁሌም የበዓል ቀናት ጀማል የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ህንፃ ውስጥ በሥራ ላይ ነበር ። ከዝግጅት ክፍሉ ወደ ኤዲቲንግ ከዚያም ወደ ስቱዲዮ ይራወጣል ። ወቅቱ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር መስከረም 1 ቀን 1994ዓ.ም እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 2001 ነበር ። ጀማል ድንገት ወደ ኤዲቲንግ ክፍል ሲሄድ መግቢያው ላይ ካለው የቪዲዮ ኤዲተሮች ማረፊያ የተከፈተው የሲኤንኤን ቴሌቭዥን ላይ አስደንጋጭ ክስተት ተመለከተ ። ክፍሉ ውስጥ ያሉ ሰዎች ፊልም ይሆን እውነተኛ ክስተት ግራ በተጋባ ሁኔታ እየተመለከቱ ነው ።
ጀማል ወደ ቴሌቭዥኑ ተራምዶ በመቅረብ በቀጥታ ስርጭት ሪፖርተሩ የሚለውን ማድመጥና ማንበብ እንደ ጀመረ ሪፖርተሩ በአንደኛው አውሮፕላን የተመታውን ሕንፃ ከጀርባ አድርጎ ገለፃ በሚያደርግበት ወቅት ሌላ አውሮፕላን ሕንፃውን ሰንጥቆ ሲገባ በቴሌቭዥን ውስጥ ተመለከተ። በጣም ደነገጠ ። ኤዲቲንግ ክፍል የሄደበትን ጉዳይ ትቶ ዜና ክፍል ሮጠ ። ዜና አዘጋጆች የሚያውቁት ነገር አልነበረም ። ቢቢሲና ሲኤንኤን ቴሌቭዥንን እንዲከፍቱ ነግሯቸው ዜናውን በአጭሩ ወዲያው ፅፎ ስቱዲዮ ገባ ። የበዓል ልዩ ስርጭቱን በማቋረጥ የመስከረም አስራ አንዱን የሽብር ጥቃት ለኢትዮጵያዊያ በአሳዛኝ ሁኔታ በቀጥታ ስርጭት መጀመሪያ የማርዳቱ አጋጣሚ እሱ ላይ ወደቀ። የበዓል ልዩ የመዝናኛ ዝግጅቱንና የበዓል መንፈሱን ረበሸው ። ተመልካቾች ስለቀረበው ዜና እውነተኝነት እየደወሉ በመጠየቅ ስልኩን አጨናነቁት ። ጀማል እያዘነ ወደቤቱ ገባ። አዲስ አመት በመጣ ቁጥር ይህን ክስተት እንዳስታወሰው ነው።
ከኢቲቪ በኋላ
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን እንደለቀቀ መስራት የፈለገው የግል ስራውን ቢሆንም አሁን በሕይወት የሌለው ደምጻዊና የሚዩዚክ ሜይዴይ በጎ አድራጎት ድርጅት ስራ አስኪያጅ የነበረው በድምጻዊ ሽመልስ አራርሶ አጥብቆ ጠያቂነት ሚዩዚክ ሜይዴይ ውስጥ የወጣቶች ፕሮጀክቶችን በማስተባበር ለ6 ወራት አገልግሏል ፡፡
ኢትዮጵያን አይዶል
ጀማል፣ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከወጣ በኋላና ሚዩዚክ ሜይዴይ እየሰራ ለረጅም አመታት ውጭ ቆይቶ የመጣው ኢሳቅ ጌቱ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የአየር ሰዓት እንዳገኘና የድምጻዊያን ውድድር ማዘጋጀት እንደሚፈልግ ነገር ግን ብቻውን መስራት እንደማይችልና አብረው እንዲሰሩ ይጠይቀዋል ፡፡ ጀማል በሀሳቡ ይስማማና በፕሮዳክሽን የሚያግዛቸውን የሻሎም ቪዲዮግራፊ ባለቤትን አቶ ጥላሁንን በማነጋገር ለ3 በስማቸው መጀመሪያ ፊደል በመውሰድ ጄይአይቲ ሚዲያና ኢንተርቴንመንት የሚል ድርጅት ያቋቁማሉ ፡፡ የቴሌቭዥኑን የድምጻዊያ ውድድርን ‹‹ኢትዮጵያን አይዶል›› በሚል ይስይሙታል ፡፡ ጊዜውም 1997 ነበር፡፡
ተሰጥኦና ፍላጎት ያላቸው የጀማሪ ድምጻዊያን ውድድር በሌላው ዓለም የተለመደ ማራኪ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ቢሆንም ለአገራችን ግን አዲስ ስለነበር ብዙ ትኩረት ስቧል ፡፡ ይህ ልዩ የመዝናኛ ዝግጅት ከፍተኛ ትኩረት የሳበ አነጋጋሪ ስለነበር የዝግጅቱ የባለቤትነት ጥያቄ ከተለያዩ አካላት ይነሳበት ነበር ፡፡ ጀማል ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቆ ‹‹ ይህ የመዝናኛ ፕሮግራም የእኔ የፈጠራ ውጤት ነው ብዬ አላውቅም ፡፡ ፕሮግራሙን እንድሰራ ኃላፊነት ተሰጠኝ በምችለው አቅም የህዝብን ትኩረት የሚስብና ተወዳጅ እንዲሆን አደረኩኝ ፡፡ ያኔ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሌላ ተመሳሳይ ስራ ለማቅረብ የሚቻልበት የቴሌቭዥን ጣቢያ ስላልነበረ ውጭ ቆይተው የመጡና የመስራት ፍላጎት የነበራቸው የባለቤትነት ጥያቄ አነሱበት ፡፡ በወቅቱ የነበሩ በርካታ የግል ጋዜጦችም መነጋገሪያ አደረጉት ፡፡ የእኔ ስህተት በወቅቱ ተገቢ የሆነ ምላሽ አልመስጠቴ ነው ›› ብሏል ፡፡
ጀማል አህመድ ይህን ዝግጅት ለ3 አመታት ካዘጋጀ በኋላ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጨረታ በማውጣት ሌሎች እንዲወዳደሩበት አድርጎ ጀማል ጨረታውን ቢያሸንፍም ኃላፊዎቹ ፕሮግራሙን ለሌላ አካል በመስጠታቸው ተበሳጭቶና ከዚያ በኃላ ፍላጎቱም ስለጠፋ የመዝናኛ ዝግጅቱን በመተው ወደ ሌላ ስራ ገባ ፡፡ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋር እንደገና ስምምነት በማድረግ በስራ ፈጠራ ላይ ትኩረት ያደረገ ላምባዲና የተሰኘ ትምህርታዊ ፕሮግራም እንዲሁም አዲስ ላይፍ የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም ጀምሮ ጥሩ እየሰራና አድማጭና ተመልካች እያገኘ ቢሄድም ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ኃላፊዎች ጋር ባለመግባባቱ መቀጠል አልቻለም ፡፡
ኢቢኤስና ጀማል አህመድ
ኢቢኤስ በሐገር ውስጥ ስርጭት ከመጀመሩ በፊት የጀማል አህመድ ያኔ አዲስ ካቋቋመው ጄይሉ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን አማካይነት ኢንቨስተር ካፌ ፣ ኑሮ በከተማ ፣ ቢዝነስ ሪፖርት ፣ ሪል ስቴት የተባሉና ሌሎች የመዝናኛ ዝግጅቶች አዘጋጅቶ ይልክ ነበር ፡፡ በመላው ዓለም የሳተላይት ስርጭት ከጀመረ በኃላም የተለያዩ ዝግጅቶችን በማቅረብ በተለይ ደግሞ የበዓል ዝግጅቶች በመስራት ከ10 አመታት በላይ ከኢቢኤስ ጋር አብሮ ዘልቋል ፡፡ ኢስላማዊ የበዓል ዝግጅቶች ከይዘትና ከአቀራረብ አንጻር ሌሎችም እየተከተሉት እንዲሰሩት ምሳሌ ሆኗል ፡፡ በሙስሊም በዓላት በስራቸው መልካም ስም ያተረፉና ተመልካች ይማርባቸዋል ያላቸውን እንግዶች ቃለ-መጠይቅ በማድረግ ፣ በተለያዩ ክልልች በመዘዋወር የአካባቢውን ባህልና እምነት የሚያንጸባርቁ ዶክመንተሪዎችን በመስራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ፡፡ የዳና እስላሚዊ ማእከል ፣ የሃላባ ባህላዊና ተፈጥሮአዊ ገጽታዎች ፣ የቀቤና የሠርግ ስርዓት ፣የጉራጌና የስልጤ የአረፋ በዓል አከባበር ፣የሐረር ታሪካዊ ቅርሶችና የከተማዋ አመሰራረት ከስራቸው ስራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ፡፡
እስላማዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች
እስላማዊ የቴሌቭዥን ፕሮግራሞችን አዘጋጅቶ ለህዝበ- ሙስሊሙ በማቅረብ ጀማል ባለውለታ ነው ፡፡ኢቢኤስ ሃይማኖታዊ ፕሮግራሞች እንዲሰሩ የአየር ሰዓት ለሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ሲፈቅድ ጄይሉ ሚዲያና ቢላል ኮሚኒኬሽን የአየር ሰዓቱን ለመሸፈን ሲስማሙ ‹‹ቢላል ሾው›› የተሰኘ ኢስላማዊ ፕሮግራም በ2002 ዓ.ም . መቅረብ የጀመረው በጀማል አህመድ አማካይነት ነበር ፡፡ ቢላል ሾው እስከ ዛሬ በየሳምንቱ እሁድ ጠዋትና አርብ ከሰዓት በኃላ በድጋሚ በኢቢኤስ ቴሌቭዥን በመቅረብ ላይ ይገኛል ፡፡
ጀማል አህመድ ከኢቢኤሱ ‹‹ቢላል ሾው›› በኋላም አፍሪካ ቲቪ እስላማዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ስርጭት ሲጀምር አብዛኛውን የጣቢያውን ፕሮግራሞች በትብብር አዘጋጅቶ በማቅረብ ጄይሉ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን በህዝብ- ሙስሊሙ ዘንድ በግንባር ቀደምነት ይታወቃል ፡፡ በአፍሪካ ቲቪ ከተለያዩ እስላማዊ ፕሮግራሞች በተጨማሪ ‹‹ሐኪም›› ፣ ‹‹ከልጆች አለም››፣ ‹‹ሐላል መዝናኛ›› ፣‹‹ ከእስላም ማህደር›› እና ሌሎች በማህበራዊና ትምህርታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ፕሮግራሞችን በጀማል አህመድ የሚመራው ጄይሉ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡
ሬዲዮ ቢላል
ከቢላል ኮሚኒኬሽን ጋር በመተባባር በኢንተርኔት በአማርኛና በኦሮሚፋ ለበርካታ ዓመታት ሲቀርብ የነበረው ሬዲዮ ቢላል በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መርጠው የሚያዳምጡት መረጃ ላይ ትኩረት ያደረገ ሬዲዮ ነበር ፡፡ ህዝበ-ሙስሊሙ በ2004 በወቅቱ ሥልጣን ላይ ለነበረው የኢሕአዴግ መንግስት ባቀረው የመብት ጥያቄ በርካቶች ሲታሰሩና የተለያየ በደል ሲደርስባቸው ድምጽ ሆኖ ያገለገለ ሬዲዮ ነበር ፡፡ የመንግስት ባለሥልጣናት ይህን በጀማል አህመድ የሚመራን ሬዲዮ ጣቢያና በኢቢኤስ የሚቀርበውን ‹‹ቢላል ሾው››ን እንዲዘጋ በወቅቱ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ሽመልስ ከማል ቢሮ ጠርተው ይነግሩታል ፡፡ ጀማልም ስርጭቱን ከፈለጉ ማቆም እንደሚችሉና የሚሰሩት የሚዲያ ስራ ከሙያ ስነምግባርም ሆነ ከመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ አንጻር የሚያስጠይቅ ነገር አለመስራቱን ምላሽ በመስጠት ፣ ከዚህ በኃላ በጀማልም ሆነ በቢላል ኮሚኒኬሽን ስም ከሐገር ውጭም ሐገር ውስጥ በድብቅ የሚሰራ ቢኖር ኃላፊነት እንደማይወስድ ይናገራል ፡፡ ይልቁንም መረጃዎችን ሚዛናዊ በማድረግ ለማቅረብ የመንግስት ትብብር ቢኖር የሚያስጠይቅም ነገር ከሰራ መጠየቅን እንድንችል ህጋዊ ፈቃድና እውቅና እንዲሰጠው ይጠይቃል ፡፡
የአቶ ሽመልስ ቢሮን ለቆ ከወጣ ከጥቂት ደቂቃዎች በኃላ ከወቅቱ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ከሆኑት ከአቶ በረከት ቢሮ ይደወልለትና በነጋታው ቢሯቸው እንዲመጣ ይጠየቃል ፡፡ በነጋታው አቶ በረከት ስምኦንን አግኝቶ ለአቶ ሽመልስ ከማል የነገራቸውን ሀሳብ በድጋሚ ያቀርብና ከብዙ ክርክር በኃላ ሬዲዮ ቢላልና ቢላል ሾው ስርጭታቸው እንዳይቋረጥ ይደረጋል ፡፡ ትክክለኛና ሚዘናዊ ዘገባዎችን እያቀረበ ተደማጭነቱም እየጨመረ ሬዲዮ ቢላል ለወራት ስርጭቱን ቀጠለ፡፡ ነገር ግን የህዝበ- ሙስሊሙ የመብት ጥያቄና ተቃውሞ ይበልጥ እየተቀጣጠለና በርካታ የሃይማኖት መሪዎች እየታሰሩ መጡ ፡፡ የሃይማኖት መሪዎች ብቻ አይደሉም የሬዲዮ ቢላል ጋዜጠኞች በደህንነቶች እየታፈኑ እስር ቤት ተወረወሩ ፡፡ ጀማል ከተወሰኑ ባለሙያዎች ጋር እየሰራ ሬዲዮ ቢላልን ለማስቀጠል ቢሞክርም የተለያዩ የማስፈራሪያ መልዕክት ይደርሰው ጀመር ፡፡ ቤተሰብ ፣ ወዳጅና ጓደኞቹ ተጨነቁ ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ኳታር ተሰደደ ፡፡ ሬዲዮ ቢላልም በዚያው ተቋርጦ ቀረ ፡፡
ስደት
ጀማል አህመድ የኳታር ዋና ከተማ በሆነችው ዱሃ በስደት በቆየበት ጊዜ አብዛኛውን ጊዜ በማንበብ ያሳለፈ ሲሆን በየሳምንቱ አርብ በእረፍት ቀን እዚያው አገር ለሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን አስተማሪና አነቃቂ ፕሮግራሞች ያቀርብ ነበር ፡፡ እዚያው ሆኖ የሰራቸው የትርጉም ስራዎችም አሉት ፡፡ ጀማል ሁኔታዎች እየተሻሻሉ ሲመጡና በርካታ ኡስታዞች ከእስር ሲፈቱ ከስደት ተመልሶ ሬዲዮ ቢላልና አፍሪካ ቲቪ ዝግጅቶች ለማስቀጠል ቢሞክርም ቢሮው በተደጋጋሚ እየተዘረፈ ሙያውን ለማቆም እስኪገደድ ድረስ ተስፋ የሚያስቆርጥ ችግር ውስጥ ገብቶ ነበር ፡፡
የስልጤ ማህበረሰብ
የስልጤ ልማት ማህበር በ1999 ዓ.ም በዞኑ አንድ ሆስፒታል ለማስገንባት የገቢ ማሰባሰቢያ ለማካሄድ ባቀደበት ወቅት ተወላጁና የልማት ደጋፊዎች ያለውን እውነታ በትክክል መገንዘብ እንዲችሉ ዶክመንተሪ እንዲያዘጋጅ ኃላፊነት የተሰጠው ለጀማል አህመድ ነበር ፡፡ እያንዳንዱ የስልጤ ዞን ቀበሌ በመግባት ህዝቡ የንጹህ መጠጥ ውሀ እጦት ከከብት ጋር እየተጋፋ ቆሻሻ ውሀ እንደሚጠጣ ምን ያህል ለበሽታ እንደሚጋለጥ ፣ በመንገድ አለመሰራት እናቶች ለወሊድ ጤና ጣቢያ መሄድ እንደሚቸገሩ ፣ እናቶች የሕክምና ተቋም ባለመኖሩ በሠላም መገላገል በእድል ቁጭብለው የሚያዩት እንጂ ሆስፒታል መሄድ እንደማይችሉና በርካቶች ሆስፒታል በአቅራቢያቸው ባለመኖሩ መሞታቸውን የሚያሳይ ዶክመንተሪ አዘጋጅቶ አቀረበ ፡፡ ብዙዎችን እንባ ያራጨ ሆስፒታሉን ለመገንባት ከፍተኛ እገዛ ያደረገ ዶክመንተሪ ሰርቷል ፡፡ ጀማል ከዚህ ሌላ ከከድር ኬሪ ፣ከሐይደር አብደላና ከሌሎች በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ስነጥበብና ዲዛይን ባለሙያዎቹ ሙዜ አወልና ኤልሳቤጥ ጋር በመሆን የብሄረሰቡን መለያ አልባሳት በማዘጋጀት ተሳትፎአል ፡፡ የስልጤ ባህላዊ ሙዚቃዎች ለብሄረሰብ ባህል ፣ እምነትና እሴት ያለውን አስተዋጽኦ የሚያመለክት ጥናት በማዘጋጀት በስልጤ አመታዊ የታሪክ፣ የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም ላይ አቅርቧል
ዶክመንተሪዎች እና የማስታወቂያ ስራዎች
ጀማል፣ ለበዓል ዝግጅቶች ለኢቢኤስና ለሌሎች ሚዲያዎች ካቀረባቸው ዶክመንተሪዎች በተጨማሪ ለአክሽን ኤድ ኢትዮጵያ ፣የወራቤ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ፣ በወራቤ ዩኒቨርስቲ ፣ እስላሚክ ሪሊፍ ፣ ለኢትዮጵያ ሙስሊም የበጎ አድራጎት ማህበር ፣ ለአልቢር የልማት ድርጅት ፣ ለአላፊያ አክሲዮን ማህበር ፣ ለሱመያ አክሲዮን ማህበር ፣ ለስልጤ ዞንና ለወራቤ ከተማ ፣ ለእፎይታ አክሲዮን ማህበር ፣ ለቢላሉ ሐበሺና ለሌሎችም በመስራት መልካም ስም አትርፏል ፡፡ ጀማል አህመድ የማስታወቂያ ስራን የጀመረው ገና የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እያለ ከመስታወት አራጋው ጋር በትብብር በመስራት ነበር ፡፡ ከኢቲቪ ከወጣም በኃላ ለግልና ለአንዳንድ የመንግስት ተቋማት በቁጥር በርካታ የሆኑ ማስታወቂያዎች አዘጋጅቶ ለተለያዩ ሚዲያዎች ለስርጭት አብቅቷል፡፡
ጄይሉ ቲቪ
ከዓለማዊና ከእስላማዊ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ጋር በትብብር በመስራት የረጅም ጊዜ ልምድ ያካበተው ጀማል አህመድ ‹‹ጄይሉ ቲቪ›› በሚል የራሱን እስላሚዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ከ2013 አ.ም ጀምሮ ለስርጭት አብቅቷል ፡፡ ጄይሉ ቲቪ እስላማዊ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን ወቅታዊ መረጃዎችን ፣ ማህበራዊ ጉዳዮችን ፣ ሠላምና አንድነት የሚሰብኩና መቀራረብን የሚያበረታቱ ዝግጅቶችንም እንዲሁም የመዝናኛ ፕሮግራሞች በማቅረብ ይታወቃል ፡፡
ጀማል በእነዚህ ዓመታት ልምዱን በማካፈል ፣ የጋዜጠኝነት መሠረታዊ ስልጠናዎችን በመስጠት በርካታ ወጣት ባለሙያዎች ሙያውን እንዲወዱትና ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ አግዟቸዋል ፡፡ ከእርሱ ጋር የሰሩ ልምድና እውቀቱን ያካፈላቸው ጋዜጠኞች በኢቢሲ ፣ በኢቢኤስና በሌሎችም ሚዲያዎች በማገልገል ላይ ይገኛሉ ፡፡
ትዳርና ቤተሰብ
ጀማል እና የትዳር ጓደኛው ለይላ ሙዜ አራት ልጆችን አፍርተዋል ፡፡ ሪም ጀማል ፣ ዩስራ ጀማል ፣ አህመድ ጀማልና አድል ጀማል ፡፡
እቅድ
በሚዲያው ዘርፍ ዘላቂና አስተማማኝ ሚዲያ የመገንባትና ሚዲያው ማህበራዊ ለውጥ ከማምጣት ባለፈ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኝ እንዲሆን ባለሙያዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች አቅዶ እየሰራ ነው ፡፡ በሥነጽሁፍ ዘርፍም በጅምር የቀሩ የአጭር ልቦለድና ሌሎች መጽሐፍትን አጠናቆ በአጭር ጊዜ ወስጥ ለህትመት የማብቃት እቅድ አለው ፡፡
መልካም ምኞቱ
ልዩነትን የሚያከብር ፣ የሚደማመጥ ፣ በሰከነና በማስተዋል ተከባብሮና ተደጋገፍ የሚኖር ማህበረሰብ ተፈጥሮ ማየትና ለዚህም መስራት የጀማል አህመድ ምኞት ነው ፡፡