የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ታሪክ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የካቲት 2 1996 ዓ.ም የተመሰረተ ድርጅት ነው፡፡ የድርጅቱ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋዜጠኛ ዕዝራ እጅጉ ነው፡፡ ተወዳጅ ሲመሰረት በርካታ ዓላማዎችን ሰንቆ የተነሳ ሲሆን ከእነዚህ አንዱ በነጻ የሚሰራጭ የማስታወቂያ ጋዜጣ ለህትመት ማብቃት ነበር፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ሰአት የህይወት ታሪክ ዝግጅት ፣ የታሪካዊ አርካይቭ ፣ የድምጸ-መጽሀፍት እና የስልጠና ፣ የማማከር ስራዎችን በብቃት የሚያከናውን ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት የካቲት 2 2015አ.ም ሲመጣ 19 አመቱን የሚያከብር ሲሆን በ19 አመት ያለፈበትን ሂደት በዝርዝር በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የሚቀርብ ይሆናል፡፡

1. ‹‹ተወዳጅ›› ጋዜጣ

ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ‹‹ተወዳጅ›› የተሰኘችውን ባለ 20 ገጽ ጋዜጣ በመጋቢት 1996 ዓ.ም አሳተመ፡፡ በርካታ የንግድ ድርጅቶችንም አስተዋወቀ፡፡ ‹‹ተወዳጅ››፣ በወቅቱ እየተገነቡ አገልግሎት ለሚሰጡ የገበያ ማዕከሎች ገጽ በመስጠት የማስተዋወቅ ስራውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የደምበል ገጽ ፤ የፍሬንድሽፕ ገጽ ፣የከሊፋ ገጽ ፣ የጌቱ ኮሜርሻል ገጽ ይገኙበታል፡፡በተጨማሪም የሚሸጡ የሚከራዩ ቤት እና እቃዎችን በማስተዋወቅ ስራም ላይ የጎላ ድርሻ አበርክቷል፡፡

ተወዳጅ ጋዜጣ ሲመሰርት ዋና አዘጋጅ የነበረው ናይእግዚ ህሩይ ሲሆን ምክትል ዋና አዘጋጅ እሌኒ እጅጉ ነበረች፡፡ የድርጅቱ የማስታወቂያ ወኪል ደግሞ ቅድስት ደበበ ነበረች፡፡ ተወዳጅ እስከ 2000 ዓ.ም ህዳር ድረስ ከ310 በላይ ማስታወቂያዎችን ያስተናገደ ሲሆን ለብዙዎችም የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ ተወዳጅ በየወሩ እየታተመ የሚወጣ ጋዜጣ ሲሆን አስተማሪ መጣጥፎች እና ቃለ-ምልልሶችም ሲቀርቡበት ነበር፡፡ ቃለ-ምልልስ ከተደረጉ ባለሙያዎች መካከልም ነፍሳቸውን ይማርና አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ፣ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ ፣ ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ፣ አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ ይገኙበታል፡፡ የተወዳጅ ጋዜጣ የመጀመርያውን የሌይአውት ንድፍ የሰራችው ራሄል ዘውዱ ስትሆን በመቀጠልም ሚካኤል ህዝቅኤል የግራፊክስ ስራውን ማከናወን ችሏል፡፡ ቀጥሎም ሀኒ ኮምፒውተር ፤ በፈቃዱ ሞረዳ ፤የተወዳጅ ሚድያን የሌይ አውት ንድፍ ሰርተዋል፡፡

‹‹ተወዳጅ›› ጋዜጣ ከ1996-2000 ባሉት ጊዜያት ስለ ማስታወቂያ አሰራር ፣ የደንበኛ አያያዝ ጥበብ ፣ በወቅቱ የነበሩት የንግድ ዓይነቶች ላይ በቂ ልምድ የቀሰመች ሲሆን ይህም ጋዜጣዋ በብዙዎች እንድትታወቅ አድርጓል፡፡ ብዙም የማስታወቂያ ጋዜጦች በመዲናይቱ ባልነበሩበት በዛ ወቅት ተወዳጅ ጥሩ አማራጭ በመሆን ስራዋን ሰርታለች፡፡በወቅቱ አትርፍ እና ሳብ ገጾች የተሰኙት የማስታወቂያ ህትመቶች በጊዜው ይታተሙ ነበር፡፡ ተወዳጅ የቢዝነስና የማስታወቂያ ጋዜጣ እንደመሆኗ ሌሎች የቢዝነስ አማራጮችንም በማየትእና በማጥናት እነርሱን ለማስተዋወቅ ተወዳጅ አዲስ መርሀ-ግብር ነድፋ ነበር፡፡ ይህም በኢንተርኔት የሚደረግ ግብይት ነበር፡፡ በቀዳሚነት ስለ ኢንተርኔት ግብይት ማወቅ መሰረታዊ ስለነበር የድርጅቱ መስራች ጋዜጠኛ ዕዝራ እጅጉ ጎልድ ኩዌስት ኢንተርናሽናል ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር ውል በመፈጸም የቢዝነሱን አሰራር ከ1997 ነሀሴ -1999 ለማጥናት ቻለ፡፡

2. የኢንተርኔት ግብይት ጥናት

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በአንድ በኩል ተወዳጅን እያሳተመ በሌላ ደግሞ ስለ ኢንተርኔት ግብይት የሚያስረዱ መጽሀፍትን በማሰባሰብ ለማጥናት ችሎ ነበር፡፡ በወቅቱ ከነበሩ ስለ ቢዝነስ ከሚያስረዱ መጽሀፍት መካከል ሪች ዳድ ፑር ዳድ ፤ ሁ ሙቭድ ማይ ቺዝ ፤ ዘ ፓሬብል ኦፍ ዘፓይፕ ላይን የተሰኙትና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ስለ ቢዝነሱ አሰራር የበለጠ ግንዛቤ ለመያዝም በርካታ አለም አቀፍ ስልጠናዎች ላይ ትልቅ ተሳትፎ በማድረግ ስለ ጽንሰ-ሀሳቡ ላይ በቂ ግንዛቤ መያዝ ተችሏል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ ከዚህ በኋላ በኢንተርኔት ግብይት ላይ ጥናት የሚያደርግ ፕሮጀክት በመንደፍ በርካታ ስራዎችን አከናውኗል፡፡በ1999 አ.ም በጉዳዩ ላይ ትኩረቱን ያደረገ መጽሀፍ ለህትመት ማብቃት ተችሏል፡፡

በተጨማሪም ፣ ኢትዮቪዥን የችሎታ ማግኛ ተቋምን ተመስርቷል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ በጥናቱ ቀጥሎበት በሀገር ውስጥ ያሉ የኢንተርኔት ግብይት ተቋማት እንዲስፋፉ የበኩሉን አድርጓል፡፡ በዚህም መሰረት ቤስትኔት ፤ እንዲሁም አታዋ ኔት እና የመሳሰሉት የሀገር ውስጥ ምርት እያቀረቡ ያሉ ተቋማትን ከደንበኛ ጋር እንዲገናኙ ማድረግ ተችሏል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አንዱ ዓላማው ከጋዜጣ እና ከኢንተርኔት ግብይት ጥናቱ ባሻገር የኢትዮጵያዊያን የህይወት ታሪክ ላይ ጥናት የሚያደርግ ፕሮጀክትን ዕውን ማድረግ ነበር፡፡ በተጨማሪም፣ ታሪካዊ ቪድዮ እና ድምጾችን ፤ ምስሎችን፣ ሰነዶችን በማሰባሰብ ጥቅም ላይ ማዋል ነበር፡፡

በዚህም መሰረት የጥናት ስራው በነሀሴ 30 2000 አ.ም በታላቅ ጥረት መሰራት ተጀመረ፡፡ ይህን ጥናት ለማከናወንም የድርጅቱ መስራች ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ በፋና ሬድዮ ላይ በመቀጠር በርካታ ታሪካዊ ሰነዶችን ማጠራቀም ችሏል፡፡ በተጨማሪም፣ ለፕሮጀክቱ ስራ የሚያግዙ ተቋማትን እና ብቁ ባለሙያዎችን ሲገናኝ ቆይቷል፡፡ ከ2000-2005 ባሉት ዓመታት የጥናት ስራው በብቃት የተከናወነ በመሆኑ ተወዳጅ ሚድያ ለሌሎች የሚድያ ተቋማት ይዘቶችን በማቅረብ ስራ ላይ በመሰማራት የተወዳጅን ሰፊ እቅድ እውን ማድረጉን ተያያዘው ፡፡ በዚህም መሰረት አእምሮ ሚድያ ፤ ድሬቲዩብ ፣ የአለም ቋንቋ፤ የኛ ፕሬስ ከመሳሰሉ ተቋማት ጋር አንድ ላይ በመሆን ተወዳጅ የበለጠ ወደ ሚድያው በመቅረብ በርካታ ስራዎችን መስራት ቻለ፡፡ በተለይም ከ2006-2009 ባሉት ጊዜያት ከድሬ-ቲዩብ ጋር በመሆን ከ300 በላይ ታሪክ ነክ ጽሁፎችን ማቅረብ ችሏል፡፡

በተጨማሪም የሀገር ባለውለታዎችን ታሪክ በቪድዮ በማቅረብ የብዙዎች ታሪክ እንዲወጣ አስችሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር በፋና ሬድዮ 1486 የሬድዮ ፕሮግራሞች በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ አማካይነት አየር ላይ የዋሉ ሲሆን እነዚህም ፕሮግራሞች ለተወዳጅ ሚድያ ትልቅ ግብአት መሆን የቻሉ ነበሩ፡፡ ተወዳጅ ሚድያ ከበርካታ ሰዎች ጋር የሰራ በመሆኑ አዳዲስ ሀሳቦችን እውን ለማድረግ ጊዜ አይፈጅበትም ነበር፡፡ በተለይ የህይወት ታሪክ ላይ መሰረት በማድረግ የሚሰራውን ስራ ለማጠናከር ብዙ ጥናት ማድረግ አስፈልጎት ነበር፡፡የድርጅቱ መስራች ዕዝራ እጅጉም ከ2000-2008 ባሉት ጊዜያት ድርጅቱን ለማጠናከር ሲያስብበት ቆይቷል፡፡

3. ታሪክን በሲዲ

በ2008 ላይም ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እንደ አዲስ ተዋቅሮ ‹‹ታሪክን በሲዲ›› የሚለውን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ተንቀሳቀሰ፡፡ ‹‹ታሪክን በሲዲ›› አዲስ የሆነ በተወዳጅ ሚድያ ፓተንት የተገኘበት ፕሮጀክት ሲሆን ከዚህ ቀደም በድምጽ እና በቪድዮ የሚቀርቡ ታሪኮች በሲዲ በአልበም መልክ አሳትሞ የማሰራጨት ጽንሰ-ሀሳብ ነው፡፡ ይህ ሀሳብ በሂደት ብስለት እያገኘ ሄዶ ቀደም ሲል ተሰባስበው የነበሩትን ግለ-ታሪኮች በመምረጥ የበለጠ ቅድሚያ የሚሰጠው የቱ እንደሆነ ተወሰነ፡፡ የኔልሰን ማንዴላ አሰልጣኝ የሆኑትን የኮሎኔል ፈቃዱ ዋኬኔን ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በድምጽ ቅንብር በመስራት ተወዳጅ ሚድያ በነጻ ስጦታ ለቤተሰቡ አበረከተ፡፡በመቀጠልም በታህሳስ 9 2009 አ.ም የአቶ ተሾመ ገብረማርያምን ግለ-ታሪክ በኦድዮ ሲዲ በማሳተም በይፋ ታሪክን በሲዲ የሚለውን ስራ አሃዱ ተብሎ ተጀመረ፡፡

በወቅቱ የህግ ምሁር የነበሩት አቶ ተሾመ ገብረማርያም ህይወታቸው አልፎ ስለነበር ሲዲው ታትሞ ለቤተሰቡ ትልቅ ቅርስ ለመሆን የቻለ ነበር፡፡ከዚያም የጸሀፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ታሪክ በኦድዮ ሲዲ የወጣ ሲሆን በተለይ ለዚህ ሲዲ መውጣት የአቶ አምዴ አካለወርቅ እገዛ ትልቅ እንደነበር እዚህ ጋር ማውሳቱ የግድ ነው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከታህሳስ 2009- ነሀሴ 2014 ባሉት 5 አመት ከ8 ወር ጊዜ ውስጥ የ45 ሰዎችን ታሪክ በሲዲ ያወጣ ሲሆን 15 ያህሉ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተመረቁ ናቸው፡፡ በጠቅላላ ከ10000 በላይ ሲዲዎች ለህትመት የበቁ ሲሆን ከ29 በላይ መገናኛ ብዙሀን ለሲዲ ምረቃው የሚድያ ሽፋን ሰጥተዋል፡፡

በሲዲ ምረቃ መርሀ-ግብሩም ላይ ከ4000 በላይ ሰዎች በጠቅላላ የታደሙ ሲሆን 30 ሰዎችም በዚህ 5 አመት ውስጥ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ታሪክን በሲዲ ላይ ልዩ ተሳትፎ ከነበራቸው የሚድያ ባለሙያዎች መካከል ቤርሳቤህ ጌቴ ፤ ዘሪሁን አሰፋ ፤ ጸጋ ታሪኩ ፤ በላይ እለፋቸው፤ ሳምራዊት ተወልደ፤ በእምነት ዘላለም ፤ ቅድስት ወልዴ አቤል እንዳቅሙ ፤ አንተነህ ዘለቀ፤ አቢይ ተመስገን ፤ ሀሰን አብራር ይገኙበታል፡፡ ታሪክን በሲዲ የሚለው የፕሮጀክት ሀሳብ በቶሎ ሰው ዘንድ ለመግባት የቻለ ሲሆን ሲዲዎቹም በባህር ማዶ ለመደመጥና ለመታየት የበቁ ነበሩ፡፡ በተለይ የአክሊሉ ሀብተወልድ ግለ-ታሪክ ከ 3 ጊዜ በላይ ለመታተም የቻለ ተወዳጅ ስራ ነበር፡፡

4. መጽሀፍት

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ይህ ታሪክ ተጠናክሮ እስከቀረበበት ድረስ 7 መጽሀፎችን ያዘጋጀ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ የ2 ሰዎችን ግለ-ታሪክ ለማዘጋጀት እየጣረ ይገኛል፡፡

4.1 አካፑልኮ ቤይ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለመጀመርያ ጊዜ መጽሀፍ አዘጋጅቶ ያሳተመው በ1996አ.ም ሲሆን የመጽሀፉም ርዕስ አካፑልኮ ቤይ የሚል ርእስ የሰጠው ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ ቲቪ ከ1988-1989 ለአንድ አመት የታየ ፊልም የአማርኛ ትርጉም ነበር፡፡ ይህ መጽሀፍ በ11000 ብር የታተመ ሲሆን አጠቃላይ የታተመውም 3000ቅጂ ነበር፡፡ ለአንዱ መጽሀፍ የወጣው ዋጋም 3ብር 32 ሳንቲም ሲሆን የመሸጫ ዋጋውም 12 ብር ነበር፡፡ ይህ መጽሀፍ በህትመት ውጤቶች ላይና በቲቪ በበቂ መልኩ የተዋወቀ በመሆኑ በ17 ቀን ውስጥ ተሸጦ አለቀ፡፡ ይህ መጽሀፍ 193 ገጽ የነበረው ሲሆን የዛሬ 18 አመት ከ 5 ወር ከአንድ መጽሀፍ ሽያጭ 36000 / ሰላሳ ስድስት ሺህ ብር/ ማግኘት ምን ያህል ብዙ እንደሆነ ማሰብ አያዳግትም፡፡ በመሆኑም አካፑልኮ ቤይ ለተወዳጅ ሚድያ የመጀመርያውም የመጽሀፍ ስራው ሆኖ ብቅ አለ፡፡

4.2 ኔትወርክ ማርኬቲንግ

ሁለተኛ በተወዳጅ ሚድያ አማካይነት ታትሞ የቀረበው መጽሀፍ ኔትወርክ ማርኬቲንግን ለመስራት የሚያግዝ የመጀመርያው መጽሀፍ ነው፡፡ ይህ መጽሀፍ በ1999 ህዳር ወር ላይ ታትሞ በሀሎሚ ባርና ሬስቶራንት ለመመረቅ የበቃ ነው፡፡ የዚህ መጽሀፍ ይዘት ስለ ኔትወርክ ማርኬቲንግ ምንነት ማስረዳትና ታሪካዊ ዳራውን መዳሰስ ሲሆን ቢዝነሱ በኢትዮጵያ ውስጥ የገባበትንም መንገድ ይጠቁማል፡፡ ይህ መጽሀፍ በ10000/ አስር ሺህ ብር / የታተመ ሲሆን አጠቃላይ የታተመውም 1000 ቅጂ ነበር፡፡ መጽሀፉን ማዳመጥ ለሚሹ ሰዎች በካሴት ቀርቦ በወቅቱ ቢዝነሱን ለሚሰሩ ሰዎች ጥሩ አማራጭና የአሰራር ዘይቤን ያመላከተ ስራ ነበር፡፡ ይህ መጽሀፍ 200 በላይ ገጾች ሲኖሩት የአንዱ መጽሀፍ መሸጫ ዋጋም 15 ብር ነበር፡፡ መጽሀፉ በ1 አመት ጊዜ ውስጥ ከገበያ ተሸጦ ለማለቅ የቻለ ነበር፡፡

4.3 የአንኮበሩ ሰው በጂኒቫ

ሶስተኛው በተወዳጅ ሚድያ አማካይነት የቀረበው የግለ-ታሪክ ስራ የኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ታሪክን የሚተርከው ‹‹የአንኮበሩ ሰው በጂኒቫ›› የተሰኘው መጽሀፍ ነው፡፡ ይህ መጽሀፍ 2006 ላይ ተጀምሮ 2011 ላይ ለመታተም የበቃ ስራ ሲሆን በ1000 ቅጂ የታተመ ነው፡፡ የዚህ መጽሀፍ አሰሪ ኢንጂነር ተረፈ ሲሆኑ በእንግሊዝኛ እና በአማርኛ የቀረበ በቂ አባሪዎችና ምስሎችን የያዘ ባለ 400 ገጽ መጽሀፍ ነው፡፡ በዚህ መጽሀፍ ስራ ላይ ጸጋ ታሪኩና ስላባት ማናዬ ትልቅ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን መጽሀፉ ከታሰበበት ቀን ጀምሮ 5 አመት በላይ የወሰደ ነው፡፡ ይህ መጽሀፍ ኢንጂነር ተረፈ ከትውልድ ቦታቸው አንኮበር እስከ ስራ ቦታቸው አንኮበር ጂኒቫ ያሳለፉትን ህይወት የሚተርክ ሲሆን በተለይ ባለታሪኩ በአለም ቴሌኮም ስራ ውስጥ የነበራቸውን ትልቅ ስፍራ የምናይበት ስራ ነው፡፡ የአንኮበሩ ሰው በጄኒቫ የመጽሀፍ ንድፍ ስራውን የሰራው ዘሪሁን አሰፋ ነው፡፡ የአንኮበሩ ሰው በጂኒቫ መጽሀፍ በብዙዎች ለመወደድ የቻለ በደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲም ለመመረቅ የበቃ ነው፡፡ የመጽሀፉ ባለ ታሪክ ኢንጂነር ተረፈ መጽሀፉ ከተመረቀ 3 አመት በኋላ በግንቦት 2014 ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡

4.4 በኦቲዝም ጥላ ስር የሚኖሩ ልጆች እንድናውቃቸው የሚፈልጉት 10 ነገሮች

አራተኛው በተወዳጅ ሚድያ አማካይነት ለአንባቢ የቀረበው ስራ ‹‹በኦቲዝም ጥላ ስር የሚኖሩ ልጆች እንድናውቃቸው የሚፈልጉት 10 ነገሮች የሚለው መጽሀፍ ሲሆን ይህም መጽሀፍ በ100 ገጾች የቀረበ ነበር፡፡ 10 ነገሮች ከትዕግስት ሀይሉ ካሳ ጋር በትብብር የታተመ ሲሆን ኦድዮ ሲዲም አብሮ የተሰራለት ነው፡፡ መጽሀፉ ኤለን ኖትቦህም ከጻፈችው መጽሀፍ ላይ ኢትዮጵያዊ ለዛውን በጠበቀ መልኩ የተተረጎመ ነው፡፡ በ300 ብርም ለሽያጭ የቀረበ ስራ ነው፡፡ ይህን መጽሀፍ ከተወዳጅ ሚድያ ጋር አንድ ላይ በመሆን ተተርጉሞ ለአንባቢ እንዲቀርብ ያደረገችውም ወይዘሮ ትእግስት ኃይሉ ነበረች፡፡ መጽሀፉ በ2014 ሚያዝያ ወር ላይ ድጋሚ ለህትመት የበቃ ሲሆን በርካታ መገናኛ ብዙሀንም የሚድያ ሽፋን የሰጡት ነው፡፡

4.5 ‹‹ወደ ራስ መመለስ

አምስተኛው መጽሀፍ ‹‹ወደ ራስ መመለስ ሲሆን የመጽሀፉ ደራሲ ሄኖክ አምዴ አካለወርቅ ነው፡፡ የመጽሀፉ ተርጓሚዎች ደግሞ እዝራ እጅጉና ሲሳይ ገብረማርያም ናቸው፡፡ በ1000 ቅጂ ለመታተም የበቃው ይህ መጽሀፍ በቅድስት ስላሴ ቤተ-ክርስቲያን ለመመረቅ የበቃ ነው፡፡ መጽሀፉ በእንግሊዝኛ እና በአማርኛ የቀረበ ሲሆን የሄኖክ አምዴ ህይወት በከፊል የሚያቀርብ ስራ ነው፡፡ የዚህ መጽሀፍ የዝግጅትና የህትመት ስራ አጠቃላይ 50 ቀናትን የፈጀ ሲሆን በዚህ ም የመጽሀፉ አሳታሚ ደስ መሰኘቱን የምረቃው ዕለት ታላላቅ እንግዶች በተገኙበት ተናግሮ ነበር፡፡ወደ ራስ መመለስ በአሁኑ ሰአት በአሜሪካ ሀገር ጭምር በበርካታ አንባቢያን እየተወደደ ያለ ስራ ነው፡፡ የመጽሀፉም ዋጋ ብር 300 መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

4.6 ‹‹መዝገበ-አዕምሮ››

ስድስተኛው መጽሀፍ ‹‹መዝገበ-አዕምሮ›› የሚል ሲሆን የ180 የሚድያ ሰዎችን የህይወትና የስራ ታሪክ የያዘ ነው፡፡ የሚድያ ሰዎቹም ከ1950-2004 የነበሩ ትልቅ አሻራ የነበራቸው ባለሙያዎች ናቸው፡፡ መዝገበ -አዕምሮ በኢንሳይክሎፒዲያ ቅርጽ የተሰራ 600 ገጾች ያሉት በጠንካራ ሽፋን ታትሞ የወጣ የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ሲሆን ከኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ባለስልጣን ፓተንት ያገኘ ነው፡፡ የመዝገበ-አእዕምሮ ሀሳብ አመንጪ እና አደራጅ ጋዜጠኛ ዕዝራ እጅጉ ሲሆን ከ1987 ጀምሮ ገና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ሲያብሰለስለው የነበረ ሀሳብ ነበር፡፡ ነገር ግን ሚያዝያ 13 2013 ሀሳቡ ዕውን ለመሆን በተግባር ተጀመረ፡፡ መዝገበ-አዕምሮ መጽሀፍ ከመሆኑ በፊት የተጀመረው በአማርኛ ዊኪፒዲያ ላይ እና በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ነበር፡፡ የሚድያ ሰዎቹ የስራ እና የህይወት ታሪክ ቀደም ብሎ በድረ-ገጾቹ ላይ ይጫን ነበር፡፡

ከሚያዝያ 13 2013- ነሀሴ 2013 ባሉት 4 ወራት ውስጥ ወደ መጽሀፍ የመለወጡ ሀሳብ አልመጣም፡፡ ነገር ግን ከመስከረም 2014 አንስቶ በመድብል መልክ መታተም እንዳለበት የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ማኔጅመንት ወሰነ፡፡በመሆኑም ቀድሞ የነበሩ የዊኪፒዲያ ቦርድ አባላትን እንደ አዲስ በማዋቀር የመዝገበ-አዕምሮ ስራ አንድ ተብሎ መሰራት ተጀመረ፡፡ መዝገበ -አዕምሮ 6 የመማክርት አባላት፣ 5 ተባባሪ አማካሪዎች፣ 11 ጥቆማ የሚሰጡ ፤ 12 የጽሁፍ አስተዋጽኦ አቅራቢዎችን በመያዝ የስነዳ ተግባሩን ከመስከረም 2014 ጀምሮ አጠናክሮ ቀጠለበት፡፡መዝገበ-አዕምሮ ላይ ታሪካቸው የሚወጣ ሰዎችን ለመምረጥ 10 መስፈርቶች የተቀመጡ ሲሆን ሁሉም መለኪያዎች ስራ እና ለሀገር የተበረከተ አስተዋጽኦ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ በተለይም ፕሮፌሽናሊዝም ዳብሮ እንዲገኝ የጣሩ በዚህ መጽሀፍ ውስጥ እንዲሰነዱ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ጠቅላላ ታሪካቸው እንዲሰነድ ጥያቄ ከቀረበላቸው 700 ሰዎች ውስጥ 200 ያህሉ ፈቃደኛ በመሆናቸው የ20 ባለታሪኮችን ታሪክ በማስቀረት የ180 የሚድያ ሰዎችን ታሪክ ለመጽሀፍ ዝግጁ አድርጓል፡፡

መዝገበ-አእምሮ ማተሚያ ቤት ከገባበት ቀን ጀምሮ እስኪወጣ ድረስ 74ቀናት ወይም 2 ወር ከ10 ቀናት የወሰደ ሲሆን የህትመት ስራውም በቂ ክትትል የተደረገበትና የመጽሀፉም ጥራት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በተለይም የሌይ አውት ንድፉ በብዙዎች ለመደነቅ የቻለ ነው፡፡
መጽሀፉ ግንቦት 6 2014 ወደ ማተሚያ ቤት የገባ ሲሆን የወጣውም ሀምሌ 16 2014 ነው፡፡ ይህ መጽሀፍ እንዲወጣ ተገቢውን ሙያዊ እገዛ ካደረጉት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ዕዝራ እጅጉ ፤ ዘሪሁን አሰፋ፣ ቤርሳቤህ ጌቴ ፣ዶክተር አየለ አዲስ ፤ ጥበቡ በለጠ ፤ ታምራት ኃይሉ፣ ባንቺአየሁ አሰፋ ፣ አማረ ደገፋው ፣ እስክንድር መርሀጽድቅ ፣ አንተነህ ደመላሽ ይጠቀሳሉ፡፡ መዝገበ አዕምሮ ሀምሌ 30 2014 በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ከጠዋቱ 3 ሰአት እስከ 6 ሰአት የተመረቀ ሲሆን በዕለቱም ከ650 በላይ ሰዎች ታድመው ነበር፡፡ ሁሉም በሚባል ደረጃ በስነስርአቱ የተደነቁና ደስ የተሰኙ ነበሩ፡፡ የመዝገበ-አዕምሮ የምረቃ ስነ-ስርአትን 28 መገናኛ ብዙሀን የዘገቡት ሲሆን የዘገባው ማስረጃም በተወዳጅ አርካይቭ ማዕከል ውስጥ በወጉ ተቀምጦ ይገኛል፡፡ መዝገበ-አዕምሮ መጽሀፍ ሲመረቅ ታሪካቸው የተሰነደላቸው 103 የሚድያ ሰዎች የታደሙ ሲሆን ምርቃቱ በሁሉም ዘንድ መነቃቃትን የፈጠረ ነበር፡፡በዕለቱ በመዝገበ-አእምሮ ላይ ሀሳብ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድ ፣ አቶ ማዕረጉ በዛብህ ፣ አቶ ፀጋዬ ኃይሉ ተፈራ አቶ አማረ አረጋዊ ፣ አቶ ጥበቡ በለጠ የሚድያ ሰው መታሰቢያ ሸዋዬ ይልማ ይገኙበታል፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ተወካይ አቶ ዝናቡ ቱኑም መንግስት ለመዝገበ-አእምሮ ትልቅ ድጋፍ የሚያደርግለት መሆኑን ቃል ገብተዋል፡፡

መዝገበ-አዕምሮ በ700 ቅጂ 2 ጊዜ ታትሞ ቅጂው በአሁኑ ሰአት ያለቀ ሲሆን የአንዱም ዋጋ ብር 2000 / ሁለት ሺህ ብር/ ነው፡፡ መዝገበ-አዕምሮ የሚድያ ሰዎች ቅጽ ሁለት በአሁኑ ሰአት እየተዘጋጀ ሲሆን ቦርዱ የመረጣቸው ሰዎች የህይወት ታሪክ በመሰባሰብ ላይ ይገኛል፡፡ በ2015 መጨረሻ ላይ መዝገበ-አዕምሮ የሚድያ ሰዎች ታሪክ ቅጽ 2 ለንባብ የሚበቃ ይሆናል፡፡

ስለ መዝገበ-አዕምሮ አንዳንድ እውነታዎች

  1. መዝገበ-አዕምሮ የሚድያ ሰዎችን የህይወት ታሪክ በመያዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሜ ሀምሌ 30 2014አ.ም ለንባብ የበቃ ሲሆን ወደፊት ሌሎች ሙያዎችንም ይዳስሳል፡፡
  2. በዚህ ለመጀመርያ ጊዜ በወጣ መጽሀፍ ላይ የ180 የሚድያ ሰዎች ታሪክ የተካተተ ሲሆን 144 ያህሉ መጽሀፉ እስከወጣበት ቀን ድረስ በህይወት ያሉ ናቸው፡፡
  3. መዝገበ-አዕምሮ ‹‹የሚጻፍ ታሪክ የለኝም›› ብለው የሚያምኑ የሚድያ ሰዎችን ሀሳብ ያስቀየረና ያኖሩትን አሻራ እንዲመለከቱ የረዳ ፕሮጀክት ነው፡፡
  4. የ180 ሰዎችን አጭር ታሪክ በ600 ገጽ ውስጥ በጠንካራ እና ደረጃውን በጠበቀ ሽፋን አዘጋጅቶ ማሳተም እንደሚቻል ለሌሎች ሰዎችም መንገድ ያመላከተ ስራ ነው፡፡
  5. እንደ ስራ ፈጠራ ራሱን የቻለ ፕሮጀክት ሆኖ ገቢ ለመፍጠር እና ለወጣት ባለሙያዎችም አቅም የሚያወጡበት መድረክ ያመቻቸ ነው ፡፡
  6. በመዝገበ-አዕምሮ ዝግጅት ላይ 29 ባለሙያዎች በቀጥታ የተሳተፉ ሲሆን ከዚህ ቁጥር ውስጥ 48 .2 ከመቶው ወይም 14 ያህሉ ሴቶች ናቸው፡፡ በመጽሀፉ ላይ የህይወት-ታሪካቸው ከተሰራላቸው 180 ሰዎች መካከል የሴቶች ቁጥር 52 ነው፡፡
  7. በሀገር ውስጥ እና በባህር ማዶ በሚድያ ላይ ለሚሰሩ ተቋማት አንድ ጠቃሚ ሰነድ ነው፡፡
  8. መዝገበ-አዕምሮ በአማርኛ ፤ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ ፤ በአገው በአፋርኛ እና በሶማሊኛ እንዲሁም በአረቢኛ የሚድያ ስራን የሚሰሩ ባለሙያዎች ታሪክ አውጥቷል፡፡
  9. መዝገበ-አዕምሮ ላይ ታሪካቸው የወጣ ሰዎች በማህበራዊ ድረ-ገጽም ላይ ታሪካቸው ይገኛል፡፡ ታሪካቸውን ማድመጥ ለሚፈልጉ ሰዎች በኦድዮ ቡክ ተቀርጾ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡
  10. ብዙም ታሪካቸው ያልወጣ የቀድሞ እና ያሁን በሕይወት ያሉና የሌሉ የሚድያ ሰዎች እንዲታወሱ ፤ እንዲመሰገኑ ፤ ለሽልማት እንዲታጩም መንገድ የሚከፍት ነው፡፡
  11. ታማኙ እግዚአብሄር / ያልታተመ ግን ስራው 70 ከመቶ ያለ ይህ መጽሀፍ የወይዘሮ አታልፍም መንግስቱን የህይወት ታሪክ የሚዳስስ ሲሆን በተለይም በመንፈሳዊ አገልግሎት የሄዱበትን እና እግዚአብሄር ያደረገላቸውን ውለታ የሚያወሱበት ነው፡፡ ወይዘሮ አታልፍም መንግስቱ ከልጅነት እድሜያቸው አንስቶ ፈጣሪ በብዙ ውጣ ውረድ ያለፉበትን አጋጣሚ በመጽሀፉ ውስጥ ይተርካሉ፡፡ መጽሀፉ በአሁኑ ሰአት ባይታተምም ከጥር 26 2014-መጋቢት 2014 ድረስ የመጽሀፍ ዝግጅቱ ስራ በወጉ ሊሰራ ችሏል፡፡

5 . ድምጸ-መጽሀፍት

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከሚሰራቸው በርካታ ስራዎች መካከል መጽሀፎችን ወደ ድምጽ መቀየር ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜም የአምባሳደር ዘውዴ ረታ ስራ የሆነውን የኤርትራ ጉዳይ የተሰኘውን በ525 ገጽ የቀረበ ሥራ ወደ ድምጽ በመቀየር ስራውን በህዳር 2011 አንድ ብሎ ጀመረ፡፡ መጽሀፍን ወደ ትረካ መውሰድ ራሱን የቻለ ሂደት ያለውና ፈታኝ ስራ ነው ከፍተኛ ጥንቃቄንም ይሻል፡፡በመሆኑም ከተራኪ መረጣ ጭምር ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ኃላፊነቱን በመውሰድ ታሪካዊ አደራውን መወጣት ችሏል፡፡ አንጋፋውን ተዋናይ ገጣሚና የሚድያ ሰውን ተፈሪ አለሙን ወደ ትረካው እንዲመጣ በማድረግ ጥሩ ስራ ሊሰራ ችሏል፡፡ ተፈሪ አለሙም የተሰጠውን ትልቅ አደራ በሙሉ ኃላፊነት በመወጣት በትረካው ላይ ነፍስ ዘርቶበታል፡፡ ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› በሲዲ የቀረበ ትረካ 26 ሰአት የፈጀ ሲሆን የራሱ ሳውንድ ትራክም የተሰራለት ነው፡፡ ኦድዮ ሲዲው በ250 ብር ለገበያ ቀርቦ በጊዜው በብዙዎች የተወደደ ነበር፡፡

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን መጽሀፍትን ወደ ድምጽ የመቀየር ስራ ላይ ጥሩ ስራ መስራቱ ታምኖበት ብዙዎች መጽሀፋቸው ወደ ድምጽ እንዲቀየር ፍላጎት በማሳየታቸው ተወዳጅም ለዚሁ ስራ ራሱን ዝግጁ አድርጎ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ስሙ ኦድዮ ቡክስ የተሰኘ መጽሀፎችን በድምጽ አፕሊኬሽን የሚያቀርብ ድርጅት በሰኔ 2012 በቀረበለትለተወዳጅ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት 9 መጽሀፎችን በ5 ወር ውስጥ ሰርቶ አስረክቧል፡፡ ስሙ ኦድዮ ቡክ መቀመጫውን ባህር ማዶ እና አዲስ አበባ ያደረገ ድርጅት ሲሆን ስራውን ገና ከመጀመሩ ከተወዳጅ ሚድያ ያገኘው ፈጣን አገልግሎት ደስ አሰኝቶት ነበር፡፡ በወቅቱ የኮቪድ ወረርሺኝ ሀገሪቱን ብቻ ሳይሆን ዓለምን በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በከተተበት ሰአት 9 መጽሀፎችን አስተርኮና ኤዲት አስደርጎ ማስረከብ ትልቅ ርብርብ የሚጠይቅ ነበር፡፡ በዚህም ተወዳጅ ሚድያ ድምጸ-መጽሀፍትን በእርጋታ ፈጥኖ መስራት እንደሚችል ያሳየበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በተጨማሪም 9ኙን መጽሀፎች እጅግ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ መስራቱ ምን ያህል ለስራው ቅድሚያ እና ትኩረት መስጠቱን ያሳያል፡፡ የስሙ ኦድዮ ቡክስ አንደኛ አመት ምስረታ እና የምረቃ በአል በተደረገበት እለት መስራቹ አቶ ጂሚ ሽፈራው ለተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ያላቸውን ትልቅ አድናቆት ሰጥተው ነበር፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለስሙ ኦድዮ ቡክ ሰርቶ ያስረከባቸው 9 ታዋቂ መጽሀፍት ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. ማህሌት በአዳም ረታ ተራኪ ጅላሉ አወል
  2. ማማ በሰማይ በህይወት ተፈራ ተራኪ ኤልዳ ግዛቸው
  3. የተቆለፈበት በዶክተር ምህረት ደበበ ተራኪ ጅላሉ አወል
  4. ጉንጉን በኃይለመለኮት መዋእል ተራኪ ኢሳያስ አስራት
  5. ነበር በገስጥ ተጫኔ ተራኪ እዝራ እጅጉ
  6. እመጓ በዶክተር አለማየሁ ዋሴ ተራኪ ኢሳያስ አስራት
  7. ሀዊ በኢሳያስ ወርዶፋ ተራኪ ሀሊማ ኡስማን
  8. መሀረቤን ያያችሁ—–በሙሉጌታ አለባቸው
  9. ምንትዋብ – በህይወት ተፈራ ኢሳያስ አስራት እነዚህን መጽሀፎች ተራኪዎችን ቀጥሮ ፣ የድምጽ አርታኢያንን ተከታትሎ በ5 ወር ጊዜ ውስጥ ያስረከበው ተወዳጅ ሚድያ ከዚህ የድምጸ-መጽሀፍ ፕሮጀክት ብዙ ትምህርት መቅሰም ችሏል፡፡ በዚህ ስራ ውስጥ በ 5 ወር ውስጥ በትረካ የተሳተፉ ባለሙያዎች ተፈሪ አለሙ ፤ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ፤ ኤልዳ ግዛቸው ፤ ጅላሉ አወል፣ኢሳያስ አስራት ፤ሀሊማ ኡስማን ፣ዕዝራ እጅጉ ሳምራዊት ተወልደ ነበሩ፡፡ ተወዳጅ ሚድያ ከዚህ በኋላ በራሱና በባለመጽሀፎቹ ፈቃጅነት በክፍያ የሰራቸው ድምጸ-መጸሀፍት ወደ 8 ይጠጋሉ፡፡ በድምሩ 17 መጽሀፎች በ3 አመት ውስጥ ወደ ድምጽ ለመለወጥ ችለዋል፡፡ ስምንቱ በባለታሪኮቹ ፈቃጅነት የተሰሩ / ፕሮዲዩስ/ የተደረጉ ስራዎችም ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፡፡
  10. ተድላ አበበ ዘመናዊ የእርሻ ፋና ወጊ – ትረካ በእዝራ እጅጉ
  11. ተናፋቂ ትዝታችን.የኮሎኔል መለሰ ተሰማ ታሪክ… ትረካ በእዝራ እጅጉ
  12. የኢትዮጵያ ታሪክ .በይልማ ዴሬሳ ትረካ በዕዝራ እጅጉ
  13. የአክሊሉ ማስታወሻ ትረካ በዕዝራ እጅጉ
  14. የሴቶች ሁለንተናዊ አበርክቶ – 5 ተራኪዎች የተሳተፉበት
  15. የአሰብ ወደብ ስራ-የኢንጂነር በየነ ወልደገብርኤል ማስታወሻ ተራኪ ዶክተር ጌታቸው ተድላ
  16. የሴትን ልጅን ህይወት የሚያበላሹ 10 ነገሮች -ተራኪ ሳምራዊት ተወልደ
  17. ኃይሌ ፊዳና የግሌ ትዝታ -በዶክተር አማረ ተግባሩ – ተራኪ ዕዝራ እጅጉ
  18. የጦር ሜዳ ውሎ ማስታወሻ ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ ….. ተራኪ ሻምበል አክሊሉ ዘለቀ

ተወዳጅ ሚድያ እነዚህን 18 መጽሀፎች ሲሰራ የባለሙያዎች ትረካ የመተረክ አቅምና ችሎታ እንዲወጣ አድርጓል፡፡ እንዲሁም ባለሙያዎች ተጨማሪ የስራ ዕድል አግኝተው በትርፍ ሰአታቸው መጽሀፎችን የድምጽ ኤዲቲንግ እንዲሰሩና በዚህም ወጣት የሆኑ ባለሙያዎች የንባብ ባህላቸው እንዲዳብር አድርጓል፡፡ የድምጽ አርትኦቱን ከሰሩት ባለሙያዎች መካከል ሳምራዊት ተወልደ ፤ በእምነት ዘላለም ፤ሜቲ ቢራሳ ፤ እመርታ አስፋው የሚዘነጉ አይደሉም፡፡ በተጨማሪም የፓፓራዚ ማስታወቂያ ድርጅት የስቱድዮ ባለሙያዎች ትልቅ አሻራቸውን ማኖር ችለዋል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ በአማካይ በአመት 5 መጽሀፎችን ወደ ድምጽ በመቀየር የራሱን የጎላ ሚና ለመወጣት ሞክሯል፡፡

6 . መድረክ ማዘጋጀትና ባለሙያዎችን የማክበር ስነ-ስርአቶች

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ‹‹ታሪክን በሲዲ›› የሚለውን ፕሮጀክት ከነደፈ አንስቶ 17 መድረኮችን በጥሩ ሁኔታ ሰርቶ ሁሉም ተደናቂነትን ማትረፍ የቻሉ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ከታተሙት 45 ሲዲዎች ውስጥ 15 ቱ በይፋ ከፍ ባለ መልኩ የተመረቁ ናቸው፡፡ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የምረቃ ዝግጅትና የመድረክ ቅንብር መርህ ቅድመ ዝግጅት ፤ይዘትና ምጣኔ በሚል መንገድ የሚገለጹ ናቸው፡፡ የምረቃ መርሀ-ግብሮቹ በቂ የሆነ ጥናት የሚደረግባቸውና የሚመጥኑ ባለሙያዎች የሚመደቡባቸው ናቸው፡፡ መርሀ-ግብሮቹ ለወራት ዝግጅት የሚደረግባቸውና ለታለመላቸው መሰናዶ ግብ የሚመቱ ናቸው፡፡ የዋና ስራ አስፈጻሚው የቅርብ ክትትል የሚደረግባቸው እና ጥሩ ውጤት የተገኘባቸው ናቸው፡፡የምረቃ መርሀ-ግብር ሲደረግ በዋናነት መድረክ የሚመሩ ፤ ከጉዳዩ ጋር ሰፊ እውቀት የያዙ መሆን እንዳለባቸው ይታመናል፡፡

6.1 የገጠሯ ሴት የቀን ውሎ

ተወዳጅ ሚድያ ከመንግስት ተቋማት ጋርም በጋራ የሰራቸው መርሀ-ግብሮች የሚጠቀስ ሲሆን በ2013ዓ.ም የተሰራው ‹‹የገጠሯ ሴት የቀን ውሎ›› የተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ይጠቀሳል፡፡ ይህ ዶክመንተሪ ከሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ጋር በትብብር የተሰራ ሲሆን የዶክመንተሪው ምረቃ ሙሉ መርሀ-ግብር በተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አማካይነት የተሰናዳ ነበር፡፡ከሚኒስቴር መስርያ ቤቱም ትልቅ ዕውቅና የተገኘበት ስራ ነው፡፡ የዚህ ፕሮግራም የመድረክ መሪና ዋና አማካሪ ጋዜጠኛ ፀጋ ታሪኩ ስትሆን አርታኢ ደግሞ ቤርሳቤህ ጌቴ ነበረች፡፡ በላይ እለፋቸው ፣ ዘሪሁን አሰፋ በሙያቸው ትልቅ እገዛ የሰጡበት ነበር፡፡

6.2 ተፈሪን እናክብር

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች በህይወት እያሉ መከበር አለባቸው ብሎ ስለሚያምን በራሱ ሙሉ ወጭ ከሰራቸው መርሀ-ግብሮች የሚጠቀሰው ‹‹ተፈሪ አለሙን እናክብር›› የተሰኘው ነው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ የተፈሪ አለሙን የልደት ቀን ምክንያት በማድረግ የተፈሪን ወዳጅና ቤተሰቦች በማሰባሰብ ትልቅ ማስታወሻ አዘጋጅቷል፡፡ በዕለቱ መድረኩን የመራችው ሀረገወይን አሰፋ ስትሆን በወቅቱ ከተፈሪ አለሙ ጋር አብረው የተወኑ ፣አብረው የሰሩ ባለሙያዎች ታድመው ነበር፡፡ በዚህ ዕለት በተፈሪ አለሙ ስራ እና ህይወት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዘጋቢ ፊልም ቀርቧል፡፡ ይህ ዘጋቢ ፊልም ቀደም ሲል በፋና ቲቪ በፋና ቀለማት ፕሮግራም ላይ አየር ላይ የዋለ ሲሆን ያሰናዳችው ደግሞ ጋዜጠኛ ዝናሽ ካልአዩ ናት፡፡ በመድረኩ ላይ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ፣ አርቲስት ጌትነት እንየው ወግ አዋቂው በኃይሉ ገብረመድህን ታድመው በተፈሪ ላይ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ተፈሪ አለሙም መድረኩ በመዘጋጀቱ ከእነ መላ ቤተሰቡ ደስ እንዳለው ተናግሯል፡

6.3 የዶክተር ጌታቸው ተድላ ዘጋቢ ፊልም ምረቃ

የዚህ ዶክመንተሪ ምረቃ መርሀ-ግብር በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር የካቲት 20 2013 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰአት የተደረገ ሲሆን ከ400 በላይ እንግዶችም ታድመዋል፡፡ ይህ ዘጋቢ ፊልም አንድ ሰአት ከ40 ደቂቃ የፈጀ ሲሆን አቤል እንዳቅሙ የዘጋቢ ፊልሙ ረዳት ፕሮዲዩሰር ሲሆን አንተነህ ዘለቀ እና አቢይ ተመስገን በቀረጻ እና በኤዲቲንግ ተሳትፈዋል፡፡ የዚህ ፕሮግራም የመድረክ መሪ ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ ስትሆን በዕለቱም ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የክብር እንግዳ በመሆን ለፕሮግራሙ ትልቅ ድምቀት ሰጥቶታል፡፡ በዕለቱ ጀግኖች አርበኞችን ለማስታወስ የአቢሲኒያ ወጣቶች ሽለላ እና ፉከራ ያሰሙ ሲሆን ይህ በታዳሚያን ዘንድ ለመወደድ የቻለ ነበር፡፡

6.4 የአሰብ ወደብ ስራ ኦድዮ ሲዲ ምረቃ

ከዛሬ 61 አመት ቀደም ብሎ በአሰብ የወደብ ፕሮጀክት ላይ በዋና መሀንዲስነት ያገለገሉት አቶ በየነ ወልደገብርኤል ይህን ሀገራዊ ግዴታ ለመወጣት አሰብ ሲያቀኑ የ27 አመት ወጣት ነበሩ፡፡ ይህ 26ሚልዮን ብር እንደፈጀ የሚነገርለት ወደብ በ1950 ጥር ወር ላይ ስራው ሲጀመር መሀንዲሱ በየነ ወልደገብርኤል ለሀገራቸው አንድ ውለታ ለመዋል ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር፡፡ ያ ወደብ 5 አመታትን ወስዶ ከተጠናቀቀ በኋላ ያንን ታሪካዊ እውነት በማስታወሻቸው ላይ አስፍረው ነበር፡፡ ይህ ከዚህ ቀደም ብዙም ያልተወራለት የአሰብ ወደብ አሰራር ታሪክ በአቶ በየነ ሲነገር ብዙ እውነታዎችን ይዟል፡፡ ይህ በመጽሀፍም ሆነ በየትኛውም ሚድያ ያልወጣ ታሪክ በኦድዮ ሲዲ ታትሞ የወጣ ነው፡፡

የዚህን ኦድዮ ሲዲ ሙሉ ወጪ በመቻል ያሳተመው ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን መሆኑ ይታወቃል፡፡ የድርጅቱ መስራችና ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰር እዝራ እጅጉ ይህ በ 1 ሰአት በሲዲ የሚወጣ ን ታሪክ ለማሳተም ሲነሳ ዋናው ግቡ ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ክብር ለመስጠት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በሀገራችን በቀደሙት ጊዜያት ታላላቅ ግንባታዎች፣ ህንጻዎችና ግድቦች ሲሰሩ የፈረንጅ ባለሙያዎች ስም ከፍ ብሎ ይጠራል፡፡ አሊያ የሰራው ኩባንያ ስም በስፋት ይነሳል፡፡ ይህ ቁጭት ውስጥ የሚከት ነው የሚለው እዝራ እኩል ከፈረንጆቹ ጋር የደከሙ ኢትዮጵያውያን አይታወሱም፡፡ ይህን ታሪክ ለመለወጥ የአቶ በየነን ሚና በሲዲ አጉልተን አውጥተናል ሲል ተናግሯል፡፡

በአቶ በየነ ወልደገብርኤል የተጻፈ ታሪክ ጣዕም ባለው ድምጻቸው ተርከው ያቀረቡት በተባበሩት መንግስታት በእርሻ ባለሙያነት ለአመታት ያገለገሉት ዶክተር ጌታቸው ተድላ ናቸው፡፡ ዋና መሀንዲስ በየነ ወልደገብርኤል መጽሀፉ በተመረቀ ጊዜ የ88 አመት አዛውንት ሲሆኑ የአሰብ ወደብ ስራ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከውጭ ሀገር ባለሙያዎች ጋር በጋራ በመስራት የሚታዩ ውጤቶችን ማስገኘቱን በትረካው ውስጥ ይናገራሉ፡፡ እንግሊዝ ሀገር የምህንድስና ትምህርታቸውን የተከታተሉት አቶ በየነ እንዴት የአሰብ ወደብን በዋና መሀንዲስነት ለማገልገል እንደተመረጡ በጽሁፋቸው ውስጥ ያስረዳሉ፡፡ በነገራችን ላይ አቶ በየነ ኦድዮ ሲዲው ከተመረቀ ከ8 ወር በኋላ ህይወታቸው አልፏል፡፡ የምረቃ መርሀ-ግብሩ በየካቲት 2011 በብሄራዊ ቤተመዛግብት ወመዘክር አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን ግርማ ቸሩን ጨምሮ በርካታ ታላላቅ እንግዶች ታድመዋል፡፡

6.5 የጸሀፌ-ትእዛዝ አክሊሉ የምረቃ መርሀ-ግብር

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ‹‹ታሪክን በሲዲ›› የሚለውን ፕሮጀክት ከጀመረ በኋላ እውን ያደረገው የመጀመርያው የዘጋቢ ፊልም ምረቃ የጸሀፌ-ትእዛዝ አክሊሉ ዘጋቢ ፊልም ምረቃ ነው፡፡ ጊዜውም ታህሳስ 2010 ነበር፡፡ በጊዜው የምረቃ መርሀ-ግብሩ በራስ ሆቴል የተደረገ ሲሆን መድረክ መሪውም ቴዎድሮስ ተሰማ ነበር፡፡ በዚህ ዕለት በአክሊሉ ሀብተወልድ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የ77 ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም የታየ ሲሆን ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ፤ደጃዝማች ወልደሰማእት ገብረወልድን ጨምሮ በርካታ ታሪክ ወዳድ ሰዎች በራስ ሆቴል ታድመው ነበር፡፡ እሁድ ታህሳስ 10 2010 አ.ም በተደረገው በዚህ ታላቅ ስነ-ስርአት የጸሀፌ-ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ቤተሰቦች ታድመው ነበር፡፡ ይህ መድረክ ተወዳጅ ሚድያ የታወቀበትና አድናቆት ያተረፈበት ነበር፡፡ አቶ አምዴ አካለወርቅ የዚህ ዘጋቢ ፊልም እና ምረቃ መርሀ-ግብር አሰሪ ነበሩ፡፡ በዕለቱ ታትሞ የነበረው 300 ቅጂ ዲቪዲም የዚያኑ ቀን ተሸጦ ሊያልቅ ችሏል፡፡

7. የኢትዮጵያ የእንስሳት ህክምና የ100 አመት ታሪክ

የኢትዮጵያ የእንስሳት ህክምና የ100 አመት ታሪክ በ3 ሰአታት የተሰናዳ የድምጽ ዶክመንተሪ ሲሆን የምረቃ መርሀ-ግብሩም የእንስሳት ሀኪሞች ማህበርና የግብርና ሚኒስትር በተገኙበት የተመረቀ ነው፡፡ የዚህ ምረቃ የመድረክ መሪ ቤርሳቤህ ጌቴ ስትሆን መሰናዶውም በጥር 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር የተደረገ ነው፡፡

ተወዳጅ ሚድያ ከዚህ ባሻገር ከታች የሚጠቀሱትን መርሀ-ግብሮች አሰናድቶ ነበር

  1. የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ስላይድ ኦድዮ በየካቲት 2010 አ.ም መድረክ መሪ አንተነህ ደግፌ
  2. የኦቲዝም ኦድዮ እና ሲዲ በጥር 2012
  3. የአማረ አረጋዊ ግለ-ታሪክ በኦድዮ ሲዲ በመስከረም 2014
  4. ሙሉጌታ ሉሌን እናክብር በህዳር 2014 መድረክ መሪ ቤርሳቤህ ጌቴ
  5. ፀሀይ ተፈረደኝን እናክብር በመጋቢት 2014 በብሄራዊ ቴአትር መድረክ መሪ አይናለም ሀድራ
  6. የደበበ ሰይፉ ግለታሪክ በግንቦት 2011
  7. የኤርትራ ጉዳይ በህዳር 2011 መድረክ መሪ አንተነህ ደግፌ
  8. የኢንጂነር በትሩ አድማሴ ታሪክ -መድረክ መሪ አንተነህ ደግፌ ግንቦት 2011
  9. መዝገበ-አዕምሮ ቅዳሜ ሀምሌ 30 2014 በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር የተደረገ መርሀ-ግብር ሲሆን መድረክ መሪዎቹም አንተነህ ደግፌ እና ሮማን ተገኝ ነበሩ፡፡

8. የትችላላችሁ ፕሮጀክት

ይህ ፕሮጀክት በተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ስር የሚገኝ ሲሆን ሰዎችን ለማብቃት እናነቃቃ እናበረታታ የሚል መርህን ያነገበ ነው፡፡ ‹‹…አጠገባችን ያሉ ባለሙያዎችን በተገኘው አጋጣሚ እናድንቅ›› የሚል ግልጽ ዓላማ ያለው ሀሳብ ነው፡፡ የተወዳጅ ሚድያ መሪ መርህ ለሌሎች መትረፍ የሚል ስለሆነ በዚህ የ‹‹ትችላላችሁ›› ፕሮጀክት ሰዎችን ካሉበት የአልችልም ስሜት አውጥቶ እንዲችሉ የሚበረታቱበት ነው፡፡ ሰዎች በሰሩት ስራ ልክ ቁምነገር ተሰጥቷቸው ወይም ተከብረው የሚደነቁበት መንገድ ነው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ በተለይ አብረውት ለሚሰሩ ቋሚና ኮንትራት ባለሙያዎች የትችላላችሁን ፕሮጀክት ተግባራዊ አድርጎ ውጤት አግኝቶበታል፡፡ ሰዎችን መርሀ-ግብር አዘጋጅቶ ማድነቅ ፣ ልዩ ልዩ ስጦታ ማበርከት፣የትርፍ ተካፋይ ማድረግ የሚሉት ስልቶች ተግባራዊ ተደርገው አዎንታዊ ለውጥ ያስገኙ ናቸው፡፡ በዚህ የ‹‹ትችላላችሁ ››ፕሮጀክት ውስጥ በተለያዩ ሚድያ ውስጥ የሚሰሩ 20 ባለሙያዎች ዕውቅና አግኝተዋል፡፡

ይህም ትችላላችሁ የሚል ፍሬም ሲሆን በፍሬሙ ውስጥ የባለሙያዎቹ ምስል ይታያል፡፡ በታህሳስ 2013 በሀሮን ኮፊ በተዘጋጀው የምሳ ስነ-ስርአት ባለሙያዎቹ በመደነቃቸው የተሰማቸው ታላቅ ደስታ ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ባለሙያን የማበርታት ልምዶች የተወዳጅን መልካም ገጽታ ከመገንባታቸው ባሻገር ሰዎች የረሱትን አቅም አሟጠው እንዲያወጡ ያስቻለ ነበር፡፡ በተጨማሪም ፣ባለሙያዎች ተወዳጅን እንደ ራሳቸው ድርጅት ወስደው ቆጥረው የእኔነት ስሜት ተሰምቷቸው እንዲሰሩ የሚያስችል መልካም ስልት ነው፡፡ በዚህ ዓይነት በርካታ የማትጊያ ስልቶችን በመጠቀም የታሰበውን ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ችለናል፡፡ የዚህ ጽንሰ -ሀሳብ ትልቅ ግብ በጎ አመለካከትን ሰዎች ውስጥ ማስረጽ ሲሆን እዚሁ ፕሮጀክት ውስጥ ያለ ሌላው ሀሳብ ፔይ ኢት ፎርዋርድ ወይም አንተ የተደረገልህን ደግሞ ለሌላ ሰው አድርግ የሚል ነው፡፡ በዚህ ሀሳብ መሰረት በጎ ይደረግላችኋል ፤ ትችላላችሁ ፤ እናንተም ሰውን አስችሉ የሚል ትልቅ መልዕክት ያዘለ በጎ ተግባር ነው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ የሚድያ ስራን እንደመስራቱ ሚድያ ደግሞ ሰውን ወደ መልካም ነገር የመውሰድ ትልቅ አደራ የተጣለበት በመሆኑ እንደ ትችላላችሁ አይነት ፕሮጀክት አስተሳሰብን የማንጻት እሳቤን ቀና የማድረግ እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል፡፡

8 . ተወዳጅ የአርካይቭ ማእከል

ይህ ማዕከል ተወዳጅ ሚድያ ከመመስረቱ 8 ዓመት በፊት የ11ኛ ክፍል ተማሪ በነበረው በዕዝራ እጅጉ መኖርያ ቤት ውስጥ የተጀመረ ነው፡፡ ጋዜጠኛ እና ታሪክ ሰናጅ የመሆን ትልቅ ህልም የነበረው ዕዝራ በልጅነቱ የቲቪ እና የሬድዮ ፕሮግራሞችን በቴፕ ካሴትና በቪድዮ ካሴት ይቀዳ ነበር፡፡ በተጨማሪም፣ የተለያዩ ሀገራትን ቴምብሮችን በማሰባሰብ አርካይቩን ማደራጀት ጀመረ፡፡ የታዋቂ ኢትዮጵያውያን ፎቶ በማሰባሰብ ገና የ14 አመት ልጅ ሳለ ዝክረ-አዕምሮ የሚል ደብተር በማዘጋጀት አርካይቭ የማደራጀት ስራውን ጀመረ፡፡ እንግዲህ ይህ ከሆነ 27 አመት ሞላው ማለት ነው፡፡ የዚያን ጊዜው ስብስብ ለአሁኑ የተወዳጅ የአርካይቭ ማዕከል እውን መሆን ትልቅ ሚና አበርክቷል፡፡ በአሁኑ ሰአት ተወዳጅ የአርካይቭ ማዕከል ሰነዶችን ወደ ዲጂታል በመቀየር በቀላሉ ሰው ማየት እንዲችልና የዘመኑ ቴክኖሎጂ በሚፈቅደው መሰረት እንዲቀርብ ማድረግ ይገባል የሚል ጠንካራ እምነት ይዟል፡፡ በዚህ መሰረት ከዚህ ቀደም በቪኤች ኤስ የነበሩ ቪድዮዎች ወደ ኤም ፒፎር በመቀየር በቀላሉ ሰዎች ማየት እንዲችሉ አድርጓል፡፡

የተለያዩ ታሪካዊ የቆዩ ቪድዮዎችንም በማሰባሰብ ለማግኘት በሚመች መልኩ እያስቀመጣቸው ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የድሮ ፎቶዎች እንዳይበላሹ ከነ መግለጫቸው ስካን በማድረግ ማእከሉን ውስጥ መቀመጥ ያለባቸውን ሰነዶች በወጉ እያደራጀው ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰአት በሀገራችን ውስጥ ሰነድ ከሚያሰባስቡ ሰዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ለሀገር የሚጠቅሙ ዶክመንቶችን በወጉ ለታሪክ እያስቀመጠ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰአት ከ1500 በላይ ብዙ ሰው ጋር በቀላሉ የማይገኙ የድምጽ እና የምስል እንዲሁም የቪድዮ ሰነዶች ተወዳጅ አርካይቭ ማዕከል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ተወዳጅ በኦድዮ ሲዲና በዲቪዲ ያቀረባቸውን ታሪኮች ወደ ተወዳጅ ሚድያ ቲዩብ ላይ እያቀረበ ዲጂታላይዝድ የማድረጉን ስራ አጠናክሮ እየሰራበት ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ልዩ ልዩ የቆዩ መጽሀፎችን ስካን በማድረግ ለታሪክ የሚቀመጡበትን ፣ዘመን ተሻጋሪ የሚሆኑበትን ስልት እየነደፈ ይገኛል፡፡እነዚህ አርካይቮች በአንድ ጉዳይ ላይ ምርምር ማድረግ ለሚፈልግ ሰው ትልቅ ግብአት የሚሆኑ ናቸው፡፡

9. ለሽልማት ድርጅቶች የእጩዎችን የህይወት ታሪክ ማዘጋጀት

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በህይወት ታሪክ ላይ አትኩሮ በመስራቱ የበርካታ በህይወት ያሉ ሰዎችን ታሪክ እንዴት ማሰባሰብ እንደሚቻል ያውቃል፡፡ በዚህም መሰረት፣ የበጎ ሰው የሽልማት ድርጅት ባወጣው ጨረታ ተወዳድሮ አሸንፎ የ10ኛውን የበጎ ሰው ሽልማት የ122 እጩዎች የህይወት ታሪክ በ50 ቀን ውስጥ አጠናክሮ ለማስረከብ ችሏል፡፡ በህይወት ያሉ ሰዎች ታሪክ በሚሰባሰብበት ሰአት ሰዎች እኔ ምን ሰርቼ ነው የምሸለመው? ስለሚሉ ታሪካቸውን አደራጅቶ ለማቅረብ ፈታኝ ይሆናል፡፡ ቢሆንም በ10 ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችን የህይወት ታሪክ ባለታሪኮቹን ወይም የቅርብ ሰዎቻቸውን በማሳመን ለመስራት ተችሏል፡፡ አንዳንዶቹ እኔ እዚህ ውስጥ ባልገባ ብለው ልመና ያቀረቡ ቢሆንም ፣ ተወዳጅ ሚድያ ግን የራሱን ዘዴ በመጠቀም ታሪካቸውን ልከው ለውድድር እንዲቀርቡ አድርጓል፡፡ የእጩዎቹን ታሪክ ራሳቸውን በመጠየቅ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘትም ሙከራ ተደርጓል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ ከበጎ ሰው የቀረቡለትን እጩዎች በፍጥነት በማግኘት በቶሎ ታሪኩን ለዳኞች ማቅረብ ችሏል፡፡ እሁድ ነሀሴ 30 2014 በተደረገው የበጎ ሰው ሽልማት ተወዳጅ ሚድያ የህይወት ታሪኩን በመስራቱ ተመስግኗል፡፡

ድርጅታችን ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በህይወት ታሪክ ላይ ምርምር የሚያደርግ ተቋም በመሆኑ እውቅና ከመስጠት በፊት የባለሙያዎች ታሪክ ተጠንቶ መቅረብ እንዳለበት ያምናል፡፡ በመሆኑም በየትኛውም ዘርፍ ላይ የባለሙያዎች አጭር ታሪክ ተሰርቶ እንዲቀርብላችሁ ለምትሹ ሁሉ ድርጅታችን የተለመደውን ሙያዊ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነው፡፡ የበጎ ሰው ሽልማት የቦርድ አባላትም የ10ኛውን የበጎ ሰው ሽልማት የእጩዎች ታሪክ እንድንሰራ እድሉን ስለሰጡን ልባዊ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡

10. ልዩ ልዩ ….

ተወዳጅ ሚድያ ከዚህ ቀደም ከ1993-2000 ባሉት ጊዜያት የጋዜጠኝነት ስልጠና በመስጠት ሚናውን ሲወጣ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ በ1999 ህዳር ወር ኢትዮቪዥን የችሎታ ማግኛ ተማሪ ቤትን በመመስረት ለ 2 አመት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ስለ ራዕይ ፣ህልምን ስለመኖር ፣ አቅምን ሳይቆጥቡ ስለመጠቀም እንዲሁም ስለ ኢንተርኔት ግብይት ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ በጊዜው ማለትም በ1999 ከትምህርት ጋር በተያያዘ አዲስ አይነት አስተሳሰብ ሲያራምድ ነበር፡፡ ይህም ሰው ከሁሉ ነገር ይማራል የሚል ነበር፡፡ ተወዳጅ ሚድያ በተጨማሪ በ2014 በኢካሽ የጋዜጠኞች ማሰልጠኛ ማዕከል ውስጥ ስለ አርካይቭ እና የጋዜጠኝነት ልምድ አሰልጥኗል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ የራሱ ቲዩብ ያለው ሲሆን በአሁኑ ሰአትም ተደራሽነቱ ከፍ እያለ መጥቷል፡፡

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *