ዳዊት መስፍን

ዳዊት መስፍን

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሰራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡

በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ጋዜጠኛ ዳዊት መስፍን ነው፡፡ ዳዊት መስፍን በአሁኑ ሰአት በፋና ብሮድካስቲንግ የጽ/ቤት ሃላፊ በመሆን እያገለገለ ሲሆን በተለይ በፋና ወቅታዊ ፕሮግራሞችን በመስራት አቅሙን ያሳየ ነው፡፡ ከ2000 በኋላ ወደ ጋዜጠኝነት ገብተው የራሳቸውን ቀለም ከፈጠሩት መካከል ዳዊት በመሆኑ የስራ ታሪኩን እነሆ እናሰፍራለን፡፡ እዝራ እጅጉ ከባለ ታሪኩ የተገኘን መረጃ መሰረት በማድረግ እንዲሁም የቅርብ ሰዎቹን በማነጋገር የህይወት ታሪኩን አጠናክሮታል፡፡

ውልደት እና ዕድገት

ዳዊት መስፍን የወሎ ምድር ፍሬ ነው። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሰኔ ግም ብሎ ስፍራውን ለሀምሌ ሲያስረክብ፤ በሀምሌ ወር የመጀመሪያ ሳምንት አንድ ልማድ አለ። በአካባቢው “ርሚጦ” ተብሎ የሚጠራ በመሃል ሀገር አካባቢ “አነባብሮ” የሚባለው ጣፋጭ ባህላዊ ምግብ በየቤቱ የሚዘጋጅበት ጊዜ አለ። ሃምሌ አምስት፤ ወይም በክርስትና እምነት ተከታዮች ሃምሌ አቦ ይባላል። ዳዊት መስፍን በዚህች ቀን ሃምሌ 05 19 80 ዓ ም፤ በደቡብ ወሎ መዲና በፍልቅልቋ ከተማ ደሴ ተወለደ።

ዳዊት መስፍን ከአስር እህት እና ወንድሞች መካከል የተገኘ የቤቱ ስምንተኛ ልጅ ነው። የዳዊት ወላጅ አባት መስፍን ገብረ ብርሓን፤ በዋግ ህዝብ፤ “ለአገው ህዝብ የተሰጠ ቤዛ” ተብለው እስኪሞገሱ ድረሰ በክፉ ጊዜ ህዝቡን የታደጉ፤ በተለያየ የስልጣን እርከኖች የዋግ እና የወሎ ህዝብን ያገለገሉ መሪ ነበሩ። እርግማን ሆኖብን ባበሻ ምድር ላይ ደግ አይበረክትም” እንዳለ ገጣሚ አበባው መላኩ አለማያ በሚለው የግጥም ስንኙ ላይ፤ በጎልማሳነት እድሜያቸው ይህችን አለም በሞት ተሰናበቱ። ይህ ሁነት የዳዊትን የልጅነት መልክ የቀየረ ሆነ። አንዲት መልከ መልካም ቀይ ደግ ሴት ሁለት ልጆቿን ዳዊት መስፍን እና ቤተልሄም መስፍንን ብቻዋን የማሳደግ ኃላፊነት በስስ ትከሻዋ ላይ ወደቀ። የዳዊት እናት አሰገድ ሚሰው ደሴ የተወለዱ ሁለት ልጆቿን አንዱን አቅፋ፤ አንዷን አዝላ ከወሎዋ የፍቅር ከተማ ደሴ፤ ወደ ዋግሹሞች ከተማ ሰቆጣ ተሰደደች። የዳዊት የትምህርት ህይወት በዋግ ኸምራ ልዩ ብሄረሰብ ዞን መናገሻ ከተማ ሰቆጣ ተጀመረ።

ዳዊት መስፍን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በሰቆጣ ከተማ አዝባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ አራተኛ ክፍል ከዘለቀ በኃላ፤ እናቱ አሰገድ ሚሰውን በሞት ተነጠቀ። ዳዊት መስፍን መቼም የማልረሳት በሚላት ቀን እናቱ አርፈው አስክሬናቸው ከቤት ወጥቶ ወደ ትውልድ ቀያቸው ሲወሰድ፤ ህፃኑ ዳዊት መስፍን በባዶ ቤት ብቻውን ተረሳ፤ ይህንን ጊዜ ዳዊት የብቸኝነት ዘመን መጀመሪያ ይለዋል። አጎቱ አቶ ሞገስ (ማሞ) መልስ መሄጃ አጥቶ አንድ የጠጠር ጥርጊያ መንገድ ተከትሎ የሚባዝነውን ህጻን አግኝተው ወደ ቤታቸው እስኪያስጠጉት ድረስ ዳዊት የምድር ባይተዋር ህጻን ሆኖ ነበር። ከእናት እና አባቱ ሞት በኃላ ዳዊት ትምህርቱን ከሁለት አጎቶቹ እና እድገት አስፋው ጋር ተማረ። በሰቆጣ የተጀመረው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በወልዲያ ከተማ የወልድያ ሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተጠናቀቀ። በ19 99 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰደው ዳዊት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ነጥብ በማምጣት፤ አርባ ምንጭ ዩንቨርሲቲ ተመደበ።

ከፍተኛ ትምህርት

ዳዊት መስፍን በኢትዮጵያ ሚሊኒየም 2000አ.ም በአርባ ምንጭ ዩንቨርስቲ የጀመረውን ትምህርት በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ፤ በዋናው የትምህርት ዘርፍ አራት ነጥብ በማስመዝገብ በእጅግ በጣም ከፍተኛ ደረጃ፤ በአማርኛ ቋንቋ እና ስነ ፅሁፍ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።

ጠመኔ እና ሰሌዳ በሆሳዕና

ልጅ ሆኖ ከእኩዮቹ ጋር እቃእቃ ሲጫወት፤ አስቀድሞ እኔ አስተማሪ እሆናለሁ ብሎ እመር ብሎ ይነሳና እንጨት ይዞ ፊደል ያስቆጥር ነበር። ይህ የልጅነት ህልም ተሳካ። የዳዊት መስፍን የመጀመሪያው ስራው አስተማሪነት ነበር። በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ ቪዥን አካዳሚ በተባለ የግል ትምህርት ተቋም ሁለት አመታትን በመምህርነት አገልግሏል።

የመጀመሪያዋ ዜና

ከቀናት መካከል በአንዷ ማለዳ ሰቆጣ ከተማ በሚገኘው መድሃኒዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሰልፍ ስነ ስርአት ላይ አንድ መምህር፤” ተማሪዎች ዛሬ ዜና ይኖረናል”፤ ብለው ዜናውን እንዲያቀርብ አንድ የ5ኛ ክፍል ተማሪን ወደ መድረክ ጠሩ፤ ያ ታዳጊ ዳዊት መስፍን ነበር። ያቺም ዕለት ዳዊት መስፍን በዜና አፉን ያሟሸባት ዕለት ሆና በህይወት መዝገቡ ላይ ሰፈረች። ከአስራ አራት አመት በኋላ ዳዊት መስፍን የልጅነት የጋዜጠኝነት ህልሙን የሚያሳካ ዕድል አገኘ። በ2006 ዓም ወርሃ የካቲት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሬድዮ ጋዜጠኛ ሆኖ ተቀጠረ።

ከአፋር በረሃ እስከ ቤተ- መንግስት

ዳዊት መስፍን፣ በጋዜጠኝነት ሙያው ህገ- ወጥ የሰዎች ዝውውርን ካጋለጠበት የምርመራ ዘገባ ሁለት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትሮች( አቶ ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ እና ዶክተር ዐቢይ አሕመድን) እስካናገረበት የአንድ ለአንድ ቃለ መጠይቅ ድረስ ብዙ ስራዎችን አበርክቷል። ዳዊት መስፍን በስፋት የሚታወቀው በምርመራ ዘገባዎቹ፤ በኮስትራ የፊት ገጽታ፤ በጠንካራ ቃላት በሚያቀርባቸው ብርቱ ጥያቄዎች እና በ2013ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ ባዘጋጃቸው የምርጫ ክርክር ፕሮግራሞቹ ነው። ብዙዎች ባልተለመደ ሁኔታ የሀገሪቱን መሪ ደፈር ብሎ የጠየቀበትን የ2013 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአንድ ለአንድ ቃለ- መጠይቅ እና የምርጫ ዘመኑ ክስተት የሚል ሙገሳ ባስገኘለት የምርጫ 2013 የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክር ስራዎቹ ዳዊት መስፍን በስፋት ያውቁታል። ዳዊት መስፍን ብዙ የሙስና ቅሌቶችን ያጋለጡ፤ የህዝብ ሮሮዎችን አደባባይ ያሰጡ፣ ለተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን ያፋጠጡ፤ የመንግስት ባለስልጣናትን ያስቆጡ ዘገባዎች እና ቃለ- መጠይቆችን በማከናወን በጋዜጠኝነት ሙያ ይህቺን ታክል አበርክቶ እንዳለው ይናገራል።

በአፋር ሰማይ ስር

አንድ ሌሊት በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን መዲና ኬሚሴ ከተማ ባለመናኸሪያ ተገኘሁ። ጊዜው 2006 ወርሃ ህዳር ነው። ወደ ኮምቦልቻ፤ ደሴ፣ ባቲ፤ ወልድያ መርሳ ወዘተ ለመሳፈር የሚሹ ተሳፋሪዎች የመናኻሪያውን ቅጥር ጊቢ ሞልተውታል። ካሉት ተደሳፋሪዎች ሁሉ፤ ወደ ባቲ እና ሎጊያ ለመሳፈር የሚጠብቁት ብዙ ምስስሎሽ አላቸው። በመናኛ ፌስታል ልብሳቸውን ሸክፈው ይዘዋል፤ ለአካባቢው እንግዳ እንደሆኑ ይስታውቃሉ፤ አይናቸው ማረፊያ አጥቶ ወዲያ ወዲህ ይላጋል። ጋዜጠኛ ዳዊት መስፍን በመናኛ ፌስታል ልብሶቹን ቋጥሮ በመካከላቸው አለ። ጉዟቸው ወደ ሳኡዲ አረብያ ነው፤ መነሻቸው ከሚሴ መድረሻቸው በኮምቦልቻ ባቲ ሎጊያ፤ አስራ አምስት ለሚሆኑ ተጓዦች ሁለት ጠርናፊዎች ተመድበዋል። ሁሉም ተጓዦች በነብስ ወክፍ አምስት ሺህ ብር ከፍለዋል ። ይህ ብር የአፋርን በረሃ አቋርጠው ጂቡቲ እንዲገቡ የተከፈለ ቀብድ ነው። ከሌሊቱ አስር ሰአት አስራ አምስቱም ተጓዦች ኤፍ ኤስ አር ተብሎ በሚጠራው የጭነት መኪና የዕቃ መጫኛ ላይ እንዲጫኑ ተደረገ። ጉዞው ወደ ባቲ ከተማ ነው፤ ሰው እንደ ቁሳቁስ ሰው እንደ እንስሳ፤ በዕቃ መጫኛ ወደ ወደ ባቲ ተሸኝቶ ኮምቦልቻ በደረሰ ጊዜ፤ የጸጥታ ሃይሎች ተሽከርካሪዎች አስቆሙት። መኪናው እንደቆመ የተጓዥ ቡድኑ ጠርናፊዎች ከጋቢና እመር ብለው ወርደው፤ ፖሊሶቹን ከመኪናው ትንሽ ርቀት ካሸሿቸው በኋላ ድርድር ተጀመረ። ፖሊሶቹ” ህገ- ወጥ የሰው ዝውውር እየፈፀማችሁ ነው ሁሉንም በመኪናው ላይ የተጫኑ ሰዎች አውርዷቸው የሚል ድንፋታ አሰሙ። ጠርናፊዎቹ ልምምጥ እና ማባበላቸውን ቀጠሉ። ከብዙ ንትርክ በኃላ በፖሊሶቹ እና ደላላዎቹ መካከል ስምምነት ሆነ። ጠርናፊዎቹ በመኪናው ላይ በተጫኑት ሰዎች ልክ በአንድ ሰው አንድ ሺህ ብር እጅ መንሻ ከፍለው፤ ጉዞው ተፈቀደ። ይህ የህገ- ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ እና የፖሊሶቹ ድርድር እና የገንዘብ ልውውጥ ከህገ- ወጥ ተዘዋዋሪዎች ጋር አብሮ እየተጓዘ ባለው ጋዜጠኛ ዳዊት መስፍን መቅረጸ- ድምፅ ተቀርጿል። ጋዜጠኛ ዳዊት ደላሎቹ እና ፖሊሶች ለድርድር ከመኪናው ትንሽ ራቅ እንዳሉ ከአፍታ በኋላ እርሱም ከመኪናው በመውረድ ጨለማውን ተገን፤ አጠገቡ ያለውን ግንብ መከለያ አድርጎ በቅርብ ርቀት ድርድራቸውን ቀርፆ ወደ መኪናው ተመልሷል።

የኮምቦልቻው ፍተሻ፤ የባቲው መንገድ አለቀ፤ እነዛ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጡ 15 ወጣቶች በአፋር ክልል ሎጎያ ከተማ ደረሱ፤ ማደሪያቸውም ለእነርሱ በተዘጋጀ መጋዘን ውስጥ ሆኖ፤ በማግስቱ ከሌሊቱ 10 ሰአት የመጋዘኑ የቆርቆሮ በር በሃይል ተንኳኳ፤ ሁሉም ሰው በመደናበር እና መደናገጥ ከአንቅልፉ ነቅቶ ማረፊያው በአንዲት ሚኒባስ ሆድ ውስጥ መከተት ሆነ፤ ጉዞ ወደ ኢትዮ ጅቢቱ ድንበት ከተማ ዲችኦቶ፤ ሰውነት በሚጋረፍ ወበቅ፤ ልብን በሚሰልብ የመኪና ፍጥነት፤ ዲቾኦቱ ተደረሰ። ከዚህ በኋላ ጉዞው በእግር ነው። ኢትዮጵያን ለቆ ወደ ጅቢቲ፤ ሳኡዲን እያሰቡ፤ ጅቡቲን እና የመንን ማቋረጥ። ጋዜጠኛ ዳዊት መስፍን ተጓዥ መስሎ የጀመረው የምርመራ ዘገባ የትንቅንቅ ምዕራፍ ላይ አደረሰው። ዲቾኦቶ መቅረት ነብሱን ይታደጋል፤ የምርመራ ዘገባውን ግን ያጎድላል። የኢትዮጵያን ድንብር አልፎ ወደ ጅቢቲ ግዛት መግባት ህይወትን አደጋ ላይ ይጥላል። በዚህ ሃሳብ መሃል ሲዋልል የነበረው ዳዊት ወሰነ። የምርመራ ዘገባውን ከማጉደል፤ የመጣውን ተጋፍጦ ታሪኩን ማሟላት። የእግር ጉዞው ተጀመረ፤ 15ቱ ተጓዦች አምስት አምስት ሆነው ለሶስት ተከፈሉ። ዳዊት ምድቡ ከሁለተኛው ቡድን ሆነ። ከዚህም ቡድን ጋር የኢትዮጵያን ግዛት 15 ኪሎ ሜትር ርቆ የጅቡቲ በረሃን አቋረጠ። በዚህ መሃል አንድ ዱብ እዳ ተከሰተ። የመጀመሪያው ቡድን ላይ ካሉት ተጓዦች፤ ጠብመንጃ በወደሩ ሁለት ሰዎች ተከበው፤ ውክቢያ ተጀመረ። የታጠቁት እነዛን ምስኪን ተጓዦች አሁኑኑ አምስት አምስት ሺህ በር ካልከፈሉ በዚህ በረሃ ላይ ደም ከልብ ሆነው እንደሚቀሩ ሲያስጠነቅቋቸው፤ ሁለተኛው ቡድን የመጀመሪያው ቡድን ተከቦ በተቀመጠበት ስፍራ ላይ ደረሰ። ይህ ቡድን ከመድረሱ ታጣቂዎቹ የአንዱን ምስኪን ጭንቅላት በጥይት በተኑት።

ይህ እርምጃ ሌላውን ማስደንገጫ ነበር። በዛ ጭው ያለ በረሃ የአንድ ምስኪን ኢትዮጵያዊ ደም አፈሩን አረጥቦ፤ መልኩን አቀላው። ያኔ ሁሉም መንገደኛ ብርክ ያዘው። የመጀመሪያው እና ሁለተኛው ቡድን ተጓዦች በአስቸኳይ ያላቸውን ገንዘብ እንዲከፍሉ ታዘዙ። ሁሉም ያለውን አራገፈ። ዳዊት መስፍንም ያለችውን አንድ ሺህ ብር ለታጠቁት ሰዎች አቀበለ። ሶስት ሺህ ብር እና ከዛ በላይ የከፈሉት ወደ ፊት እንዲሄዱ ተፈቀደላቸው። ከሶስት ሺህ ያነሰ የሰጡት ባሉበት እንዲቆዩ በታጠቁ ሰዎችም እንዲጠበቁ ተፈረደባቸው። ዳዊት መስፍን ከእነዚህ ፍርደኞች መካከል ሆነ። ቀኑ እየጨለመ ሲሄድ አጋቶቹ የመደራደሪያ ሃሳብ አቀረቡ፤ ጉዟችን እንቀጥል እና ጅቡቲ ስንደርስ በባንክ የቀረውን ገንዘብ ታስልካላችሁ የሚል ሃሳብ አቀረቡ። ስምምነቱ ሆነ፤ ለጋዜጠኛ ዳዊት ይህ የመጨረሻ የውሳኔ ምእራፍ ነበር። ጉዞውን ለመቀጠል ግን ላለማጠናቀቅ ወሰነ።

ካረፉበት ቦታ አንድ 5ኪሎ ሜትር ከተጓዘ በኋላ ዳዊት ደከመኝ ብሎ ወደ ኋላ ቀረ። ይህንን ያደረገው ካሁን ቀደም ደከመኝ ብለው ወደ ኋላ የቀሩትን መንገደኞች አጋቶቹ ሲበረታ ይመጣል ብለው ትትው ስለሚሄዱ ነው። ዳዊትም ስትችል ተከተለን የሚል ትእዛዝ ተቀብሎ፤ ጉዞውን አቋረጠ፤ የበረቱት ወደ ጅቡቲ ዘለቁ፡፡ ከዚህ በላይ መጓዝ የለብኝም ያለው ዳዊት 15 ኪሎ ሜትር ወደ ኋላ ወደ አፋር ክልል ተመለሰ።

ዳዊት መስፍን የፀጥታ ሃይሎች በቀጥታ የሚሳተፉበት፤ ደላሎች በሰው ልጅ ላይ የሚያሳርፉትን ቃላት የማይገልጡት ጭካኔ የተመለከተበት “ደላላው ምን ይላል”፣ “ጠባቂ አልባ ምስኪኖች”፤ ከአፋር ሰማይ ስር እና እስከ በፀጥታ ሃይሎች የሚያገዘው ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፤ የራህመት እንባ የሚሉ ተከታታይየሬድዮ ዘገባዎችን ያጠናቀረው በዚህ መልክ መረጃ በማሰባሰብ ነው። ጋዜጠኛ ዳዊት መስፍን፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አሻጥሮች እና የገንዘብ ብክነት፤ የግድቡ ፕሮጄክት አመራር ጉድለት እና የመዘግየት መንስኤ ያሳዩ ፤ የመንግስት መሬት ወረራ እና የባለስልጣናትን ተሳትፎ ያጋለጡ፤ በአዳሜ ቱሉ ፀረ ተባይ ኬሚካል ማምረቻ ፤ የአገልግሎት ዘመናቸው ያለፈ ግብኣቶችን በመጠቀም የህብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል ምርት ማምረታቸውን ያጋለጡ እና ሌሎች የምርመራ ዘገባዎችን በመስራት የሚታወቅ ጋዜጠኛ ነው።

ስለ ዳዊት መስፍን ባልደረቦች የሰጡት ምስክርነት

አላዛር ታደለ በአሁኑ ሰአት በፋና ብሮድካስቲንግ በዜና እና ወቅታዊ ዳይሬክቶሬት ውስጥ በምክትል ዋና አዘጋጅነት ያገለግላል፡፡

አላዛር ታደለ ወደ ፋና ሲመጣ በቀዳሚነት አድናቆት ከቸራቸው ጋዜጠኞች መካከል ዳዊት መስፍን አንዱ ነበር፡፡ የእውነትም ዳዊት እውቀቱን ለማካፈል የሚሰስት አልነበረም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነበር ዳዊትና አላዛር ትውውቃቸው የሰመረው፡፡ በአላዛር እይታ ዳዊት ለስራው ቅድሚያ የሰጠና ደግሞም የሚሳካለት ሰው ነበር፡፡ አላዛር እንዲህ ይላል‹‹….ስለ ህዳሴ ግድብ በበቂ ሁኔታ መረጃ የሰጠው ዳዊት ነበር፡፡ ግድቡ ላይ ታይተው የነበሩ ብክነቶችን ሁሉ ተንትኖ ያስረዳ ነበር፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ ሲሰራ እንደመርማሪ በጥልቀት ነበር፡፡›› በማለት አላዛር ያስረዳል፡፡

ዳዊት በየሚድያው የሚሰጠው መግለጫም በሳል ነበር፡፡ በወቅታዊ የሀገር ጉዳይ ላይ ዳዊት በንባብ ራሱን ያደረጅ ነበር፡፡ አላዛር ይህን የዳዊትን ችሎታ ያደንቀዋል፡፡ አላዛር እንደሚናገረው ዳዊት በሚሰራው ስራ ላይ ጥንቃቄ ስለሚወስድ ሚስጥር ይጠብቃል፡፡ ስለሚሰራው ስራ እንደ ቀልድ ለማንኛውም ሰው የማውራት ልማድ የለውም ፡፡

‹‹… ዳዊት የአንድ ለአንድ ቃለ-መጠይቅ ላይ የተካነ ነው፡፡ ቃለ-መጠይቅ ከማድረጉ በፊትም በቂ ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ከጥያቄ አወጣጡም ጋዜጠኞች ሊማሩ ይችላሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድን የአንድ ለአንድ ቃለ-መጠይቅ አድርጎ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዳዊት በፊት ሌሎች ቃለ-ምልልሶችን ሰጥተዋል፡፡ ከዳዊት ጋር ያደረጉት ቆይታ ግን ብዙ ሀሳቦች የተነሱበት ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ የጠያቂው የዳዊት ጥረት የሚያሳይ ነው፡፡›› በማለት አላዛር ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

ዳዊት በ9 አመት ውስጥ ከሪፖርተርነት የጣቢያው የጽ/ቤት ሃላፊ ለመሆን መቻሉ ብዙዎች ይህ ቦታ ይገባዋል እንዲሉ አስችሏቸዋል፡፡ ዳዊት የጽ/ቤት ቤት ሃላፊ ከሆነ በኋላ ብዙ የይዘት ለውጦች ተስተናግደዋል፡፡ በዚህ ሀሳብ አላዛር ይስማማል፡፡ ዳዊት የጽ/ቤት ሃላፊ ከሆነ በኋላ ፋናን ለቅቀው የነበሩ ሰዎች መመለስ ችለዋል፡፡ አላዛር ይህ የዳዊት ጥረት እንደሆነ ያምንበታል፡፡ የፋና ማኔጅመንትም ለዳዊት ይህን እድል ሰጥተው በስራ ችሎታውን እንዲያሳይ በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል ይላል አላዛር ታደለ፡፡

‹‹…..ዳዊት ለስራው ካለው ተነሳሽነት የጽ/ቤት ሃላፊ ሆኖ እንኳን የወቅታዊ ክፍልን ደርቦ ይሰራል፡፡ ይህ ለስራው ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳይ ነው፡፡ዳዊት ከጋዜጠኝነቱ በፊት ለ 3 አመት መምህር ሆኖ አገልግሏል፡፡ እናም ሲያስተምር ከልቡ እንደሆነ ያስተማራቸው ይመሰክራሉ፡፡ ዳዊት ቲቪ ላይ ስታየው ኮስታራ ይመስልሀል፡፡ ነገር ግን ቀረብ ስትል ለዛ ያላቸው ጨዋታዎችን ይችላል፡፡በሰው መስመር የማይገባ የራሱን ስራ ብቻ የሚሰራ ጠንካራ ለብዙዎች አርአያ መሆን የሚችል የሙያ ሰው ነው፡፡ደግሞም ባለበት የስራ ሃላፊነት ደከመኝ የማይል ጣቢያውን ለማሳደግ የሚችል ሰው እንደሆነ አልጠራጠርም…›› ይላል አላዛር ምስክርነቱን ሲሰጥ ፡፡

ትእግስት ስለሺ በፋና ብሮድካስቲንግ በዜና ክፍል ውስጥ በምክትል ዋና አዘጋጅነት እያገለገለች ትገኛለች፡፡ ትእግስት፤ ዳዊት ሲቀጠር ጀምሮ ከ2006 አንስቶ ታውቀዋለች፡፡ በተለይ አብረውት ከተቀጠሩ ሰዎች አንጻር ለየት ያለ መሆኑ አቀራርቦናል ትላለች፡፡

‹‹ ዳዊትን በማወቄ ደስ ይለኛል›› ትላለች ትእግስት፡፡ እንደ ባልደረባ ብቻ ሳይሆን እንደ ታናሽ ወንድሜ ነው የማየው የምትለው ትእግስት ለሙያው የሚሰጠውን ክብር ታደንቃለች፡፡

‹‹ …. ዳዊት ሰርቶ የሚያሰራ የባልደረቦቹን ጠንካራ ጎን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነው፡፡ ላመነበት ጉዳይ ደግሞ እስከ መጨረሻው ድረስ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው ነው፡፡ ሰዎች ያላቸው ልዩ ችሎታንና በጎ ነገርንም የማየት ችሎታ ያለው ሰው ነው፡፡ ስራ ሲሰራ ይሄ ስራ ይጎዳኛል ብሎ አያስብም፡፡ ይሄን ፕሮግራም ብሰራ ከሆነ አካል ጉዳት ይደርስብኛል ብሎ ለራሱ አይሰጋም፡፡ዳዊት አንድን ስራ ከጀመረ የፈጀውን ያህል ጊዜ ፈጅቶም ቢሆን እስከፍጻሜው ይሰራዋል፡፡ማታም ሆነ ቀን ለመስራት ሙሉ ፈቃደኛ ነው፡፡ዳዊት በቶሎ ያደገ ነው፡፡ በእኔም እምነት በልፋቱ ያገኘው ነው ስል አስባለሁ፡፡ ስራውንም ሲሰራ በጥንቃቄ ነው፡፡ ገና ሲቀጠር አንስቶ በሳል ልጅ እንደነበር አይቻለሁ፡፡ ብሪፍ ላይ ይሰጣቸው የነበሩ ሀሳቦች ለሁላችንም የሚገርሙ ነበሩ፡፡ በቶሎ ስራውን መልመዱም አርታኢዎችን ደስ ያሰኘ ነበር፡፡ አሁን ባለበት የስራ ደረጃም እንደ ጽ/ቤት ሃላፊ ስራውን በአግባቡ እየተወጣ ነው፡፡ በተለይ ጣቢያው ይዘት ላይ እንደ ዳዊት አይነት ሰው ስለሚያስፈልገው ይህን አደራውን እየተወጣ ለመሆኑ አንዳች ጥርጥር የለኝም፡፡›› በማለት ትእግስት ስለሺ ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ጋዜጠኛ ዳዊት መስፍን ለሙያው ያለው ክብርና ፍቅር በስራዎቹ ይገለፃል። ህይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል ጉዳይ እንኳን ቢሆን የምርመራ ዘገባውን ከዳር ሳያደርስ ፈፅሞ አይመለስም። በተለይም ከህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ከፒራሚድ ንግድ ጋር በተያያዘ በሀገሪቷ የሚታየውን ችግር በጠለቀ የምርመራ ስራ ዘገባ በመስራት ብቃቱን አስመስክሯል። ዳዊት የሚሰራውን ስራ በእውቀት ነው የሚሰራው።

መረጃ የመተንተን ብቃቱን ብዙዎች ያደንቃሉ።ደግሞ የመምራት አቅሙም ከፍ ያለ ነው። ዳዊት ጋር ስራዎች ሳይንጠባጠቡ ጥንቅቅ ብለው ይከወናሉ። በራስ መተማመኑ የሚያኮራ ነው። ዳዊት መስፍን ግዜውን በአግባቡ የተጠቀመ በሳል ወጣት ነውና በእርሱ እድሜ ለሚገኙትም ሆነ ለመጪው ትውልድ መልካም አርአያ የሚሆኑ በርካታ በጎ ገፆች ያሉት ትጉ ጋዜጠኛ ነው ብለን እናምናለን። ዳዊት ወደ ሚድያ ስራ ከዘለቀ ገና 9 አመት ቢሆነውም እነዚያን 9 አመታት በአግባቡ እንደተጠቀመ አብረውት የሰሩ ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡ በየዘመኑ ያሉ የሚድያ ሰዎችን ቦርዱ የመረጣቸውን እየሰነድን ስለሆነ ዳዊት በወጣትነቱ ተስፋ የሚሰጥ ሙያዊ ተግባር እያከናወነ በመሆኑ ታሪኩን ለትውልድ አስቀምጠነዋል፡፡ ዳዊት መስፍን በአሁኑ ሰአት በፋና ብሮድካስቲንግ በጽ/ቤት ሃላፊነት ተመድቦ እያገለገለ ሲሆን ተሰሚነት ያለው በሚያፈልቃቸው ሀሳቦችም ተጽእኖ ፈጣሪ መሆን የቻለ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ደግሞ ወደ መድረኩ ወጥተው እውቅና እንዲያገኙ እንሻለን፡፡ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚዩኒኬሽን እንደ ዳዊት አይነት ንቁና ትጉ ወጣቶችን ታሪክ በመሰነድ ለትጋታቸው እውቅና ስንሰጥ ሌሎች ይበረታታሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ፡በመሆኑም ጋዜጠኛ ዳዊት መስፍን ከ2006 በኃላ የተገኘ ጎበዝ ጋዜጠኛነቱን ስንመሰክር በኩራት ነው። የነገ ተስፋውም ትልቅ መሆኑን በመተማመንነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ ነሀሴ 26 2015 በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች ተሰነደ፡፡ እንደዚሁም በቅርቡ በሚታተመው መዝገበ-አእምሮ ላይ የህይወት ታሪኩ ይሰነዳል፡፡