ሮዝ መስቲካ ነጋሽ

ሮዝ መስቲካ ነጋሽ

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡

በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ ባለፉት 10 አመታት የራሳቸውን አሻራ ካኖሩት መካከል ሮዝ መስቲካ ነጋሽ ትጠቀሳለች፡፡

የልጅነት አለም

ሚያዝያ 5 1970 ከመምህራን ወላጆቿ የተወለደችው ጋዜጠኛ ሮዝ መስቲካ ነጋሽ  ለወላጆቿ የመጀመሪያ ልጅ ናት፡፡ ትውልዷ በደቡብ ጎንደር በነፋስ መውጫ ሲሆን 6 አመት ሲሆናት ከወላጆቿ ጋር ወደ አዲሰ አበባ መጣች፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በአፍሪካ አንድነት ቁጥር ሁለት የህዝብ ትምህርት ቤት 2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቅቃለች፡፡

ልጅነቷ ከቴሌቪዥን የራቀ ከሬዲዮ፣ ከጋዜጣ፣ ከመፅሔት እና ከመፅሐፍ ጋር የተቆራኘ በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እሁድ ማታ 3 ሰአት በጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን የሚቀርበው “ከመፃሕፍት ዓለም” የቅዳሜ ከሰአት መዝናኛ እንዲሁም የለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ ዝግጅቶች ከልጅነት ጨዋታ ይልቅ ልቧንና ቀልቧን ወስደውት ነበር፡፡

ወላጆቿ ደግሞ የአገር ፍቅርን፣ ለአላማ ፅኑ መሆንን በተግባር እያሳዩ አሳድገዋታል፡፡ ለትምህርት ከፍተኛ ቦታ ያላቸው እናቷ በትምህርቷ እንድትበረታ በራሷ የቆመች ጠንካራ ሴት እንድትሆን እየመከሩ ሲያሳድጓት፤ በለገዳዲ የትምህርት በሬዲዮ አዘጋጅነታቸው የሚታወቁት አባቷ አቶ መስቲካ ነጋሽ  ደግሞ ጋዜጣና መፅሔት አብረዋት እያነበቡ፣ የሬዲዮ ዝግጅቶችን አብረዋት እያዳመጡ፣ ከእደሜዋ በስላ እንድታድግ  አድረገዋታል፡፡

“ምን መሆን ትፈልጊያለሽ?” ስትባል “ደራሲ እና የዓይን ሀኪም” ብላ ህልሟን ትናገር የነበረችዋ ሮዝ፤ እያደር ግን የጋዜጠኝነት ሙያ ፍቅር በውስጧ እያደገ መምጣቱን አስተዋለች፡፡

የትምህርት አለም

“የማልፈልገውን አልማርም”

የአስራ ሁለተኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተናን በ1989 ብትፈተንም ውጤቱ እንዳሰበችው ሳይሆን ቀረ፡፡  ወደ ዩኒቨርሲቲም መግባት አልቻለችም፡፡” በዚህ ደግሞ አልተከፋችም፡፡ እንደ ገና ፈተናውን ወሰደች፡፡ አለፈችም፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ የገጠማት ሌላው ችግር በየዩኒቨርሲቲው ያሉት የትምህርት አይነቶች እሷ ልትማራቸው የምትፈልጋቸው አለመሆናቸው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት “የማልፈልገውን አልማርም” በሚል የጸና አቋሟ ሌላ ተጨማሪ አንድ አመት አሳለፈች፡፡ እሷ መማር የምትፈልገው ጋዜጠኝነት ነበርና፡፡

በዚህ ጊዜ ትፍላሜ አማተር የጋዜጠኞች ማህበር ተቋቁሞ የጋዜጠኝነት ስልጠና መስጠት ጀምሮ ስለነበር እርሷም በደስታ ስልጠናውን ወሰደች ፡፡መልካም አጋጣሚ ሆነ እና ብዙም ሳይርቅ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በዲፕሎማ መርሀ ግብር ጋዜጠኝነትን ማስተማር ጀመረ፡፡ ሮዝም የመጀመሪያው አመት ተማሪ በመሆን በማታው መርሀ -ግብር መማር ጀመረች፡፡ ከነበሩት ጥቂት ተማሪዎች መካከል የምትወደውን ጠብቃ የተማረች ብቸኛ ተማሪ ነበረች ማለት ይቻላል፡፡

የጋዜጠኝነት ትምህርቱን አጠናቀው ከተመረቁት ስምንት ተማሪዎች መካከልም ብቸኛ ሴት ናት፡፡ ከአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ ፊት ለፊት በሚገኘው በቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጊቢ ውስጥ አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና ህትመት ጋዜጠኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ ማስተማር ሲጀምርም የመጀመሪያው ዙር ተማሪ ሆናለች፡፡ 

ከነዚህ መካነ-ትምህርት ካገኘቻቸው ዲፕሎማ እና ዲግሪ በተጨማሪ የሬዲዮ ፕሮግራም ቀረፃ እና ኤዲቲንግ እና የምርመራ ጋዜጠኝነት የሚሉ ስልጠናዎችን ወስዳለች፡፡

የሥራ አለም

ከአባቷ ከአቶ መስቲካ ነጋሸ ጋር ወደ ለገዳዴ ሬዲዮ ጣቢያ መሄድ የምታዘወትረው ሮዝ የጋዜጠኝነት ሙያዋን አሀዱ ብላ የጀመረችው በለገዳዲ የሬዲዮ ጣቢያ “ቅዳሜን ከእኛ ጋር” በሚለው ዝግጅት ላይ ከማስታወቂያ ባለሙያው ከብርሃኑ አየለ ጋር በመሆን የአድማጮችን ደብዳቤ በማንበብ ነበር፡፡

ሮዝ መስቲካ የልቧ የሚደርሰው፣ ሰርታም የምትኮራበት፣ ዋጋ ብትከፍልም የማትቆጭበትን  የጋዜጠኝነት ሙያዋን ሥራዬ ብላ መስራት ከመጀመሯ በፊት በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና አለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በፀሐፊነት ሰርታለች፡፡ በተለይ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ እየተማረች በነበረችበት ወቅት የገጠማት ነገር የህይወቷን አቅጣጫ፣ አላማዋን እና የወደፊት የሥራ ጎዳናዋን እንዲሁም ልትታገለው የሚገባ ጉዳይ እንዳለ በግልፅ ያሳወቃት ነበር፡፡

የማታ እየተማረች ቀን ደግሞ በፀሐፊነት ሙያ በተባበሩት መንግስታት ሥር ባለ አንድ መስሪያ ቤት ውስጥ ትሰራ ነበር፡፡ የዚህ ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሮዝ “እሺ ወይም እምቢ” የሚል መልስ የሚያስፈልገው ፆታዊ ጥያቄ ያቀርብላታል፡፡ መልሷ “እምቢ” በመሆኑ ምክንያት ከሥራዋ ትባረራለች፡፡ በዚህ ጊዜ አለቃዋ አሁንም የማትረሰውን ንግግር ተናገራት “እዚህ አገር ሰው በተማረበት አይሰራም”፡፡ ይህ የሆነው ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በምትመረቅበት ሰሞን ነበር፡፡

ከምርቃት በኋላ በቀጥታ ወደ ፎርቹን ጋዜጣ ቢሮ አቀናች፡፡ ጋዜጠኛ ታምራት ሀይለ ጊዮረጊስ (የፎርቹን ጋዜጣ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ) በቢሮው ገብታ አነጋገረችው፡፡ ጋዜጠኛ ታምራት  ጥቂት ጥያቄዎችን አቀረበላት፤ እሷም መለሰች፡፡ እሱም እንዲህ አላት “የነበረሽበት መሥሪያ ቤት የሚከፍልሽን ያህል ልከፍልሽ አልችልም” አላት፡፡ “ችግር የለም” አለችው “እንኳን ደህና መጣሸ” ብሎ ተቀበላት፡፡

በደስታ ፈንድቃ ሥራዋን ጀመረች፡፡ ሰኞ ማለዳ የመጀመሪያ ዜናዋ በፎርቹን ጋዜጣ ላይ ስሟን ይዞ እንደወጣ፤ የፍላጎቱን ስላላሟላችለት ከሥራ ወደ አባረራት የቀድሞ አለቃዋ ቢሮ ሄደች፡፡ ቢሮውን አንኳኩታ ገባች እና ጋዜጣውን  ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠችለት፡፡ “እዚህ አገር ሰው በተማረበት ይሰራል” ብላው ወጣች፡፡

በዘዴይሊ ሞኒተር ጋዜጣ በሪፖርተርነት ያገለገለችው ሮዝ፤ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀውን እና በኤች.አይ.ቪ ላይ ትኩረት ያደረገውን “ይበቃል” የተሰኘውን የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢም ሆና ሰርታለች፡ በፎርቹን፣ በዘዴይሊ ሞኒተር እንዲሁም በኢትዮጵያ ሬዲዮ የሚተላለፈውን “ይበቃል” የነበራትን ቆይታ ስትገልፀው “ገንዘብ እየተከፈለኝ ተማርኩ” በማለት ነበር፡፡ በተለይ በፎርቹን ጋዜጣ የነበራትን ቆይታ ስታወሳ ጋዜጠኛ ታምራት እና በወቅቱ የፎርቹን ኤዲተር የነበረው ጋዜጠኛ ሚኪያስ ወርቁ አለቆቼ ሳይሆኑ የተግባር መምህራኖቼ ነበሩ በማለት ነው፡፡ ብዙም ባትሰራበትም ከጋዜጠኝነት ወደ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊነትም በመሸጋገር በኢትዮጵያ ኢምፕሎየርሰ ፌዴሬሽን ትሰራ ነበር፡፡ 

አብነት – የሴቶች መፅሔት

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች “ሮሀ” የምትባል በነፃ የምትታደል “ኒውስ ሌተር” ታዘጋጅ ነበር፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያን ትምህርቱም ተግባሩንም ከቀሰመች በኋላ የራሷን መፅሔት ለማዘጋጀት አሰበች፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታዋ፣ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በምትሰራበት ጊዜ እንዲሁም በምትወደው የጋዜጠኝነት ሙያ ባሳለፈቻቸው ጊዜያት ሁሉ እንደ ጥላ ይከተላት የነበረው ፆታዊ ትንኮሳ እንዲሁም ሴቶችን ከፋሽን፣ ከውበት፣ ከዳንስ እና ከሌሎች አካላዊ ቁንጅናዎች ጋር ብቻ አያይዞ የማሰብ ነገር እጅጉን ያበሳጫት ነበር፡፡

እነዚህ ነገሮች መነሻ ሆነዋት “ሴቶች ከአካላዊ ቁንጅና በላይ ነን” በሚል የሴቶችን ጥንካሬ፣ እውቀት፣ ብርታት፣ ትጋት በተጨማሪም የአገር የጀርባ አጥንት መሆናቸውን የምታሳይ “አብነት” የተባለች መፅሔት ማሳተም ጀመረች፡፡ ይህንን አይነት ቁም ነገር ያለው በሳል እና የናፈቁት የሴቶች መፅሔት መምጣቱ ያስደሰታቸው ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ከአዟሪዎች ጀምሮ “የአሮጊቶች” “የቺኮች” የሚል ቅፅል በመስጠት የሚያጣጥሏትም ነበሩ፡፡

ሮዝ የጋዜጣው አሳታሚ ብቻም አልነበረችም፡፡ በቂ የገንዘብ አቅም ስላልነበራት ብዙውን ነገር እርሷው ትሸፍን ነበር፡፡ ስንዱ አበበ፣ እቱ ገረመው(በህይወት የለችም)፣ መሳይ ዘገየ (የዘፕሬስ ጋዜጣ ጋዜጠኛ የነበረ)፣ ቶማስ ለማ (የዘፕሬስ ጋዜጣ ጋዜጠኛ የነበረ)፣ አብነት አሰፋ (አሁን በህይወት የለችም)፣ አዲስ ዘላለም (የፎርቹን ጋዜጠኛ የነበረች) ያለ ምንም ክፍያ በሙሉ በጎ ፈቃድ ለመፅሔቷ ይፅፉ የነበሩ ናቸው፡፡

የነዚህ የሙያ አጋሮቿ ቀናነት እጅግ ያስደንቃታል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ መልካም ነገሮች ሲመጡ አናቂያቸው ብዙ ነው እና አብነት ከሁለት እትም አልዘለለችም ነበር፡፡

ስለ አብነት መፅሔት ስታወራ የአዟሪዎቹ ስለ መፅሔቷ የነበራቸው በጎ ያልሆነ አስተያየት እና ገበያው ላይ የሚያሳድሩት ጫና ምን ያህል ከባድ እንደሆነ፤ ሴቶችን እናበረታታለን፣ ስለ ሴቶች ከፍ እናደርጋለን፣ እንደገፋለን የሚሉ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን አብነትን እንደ ሴቶች መፅሔት ሮዝንም እንደ ሴት አልቆጠሯቸውም ትላለች፡፡ 

እናትነት እና ፀሐፊነት

“የህይወቴ ሌላኛው ፈረቃ” በማለት ትገልፀዋለች እናትነቷን፡፡ እናትነት የሮዝን ጥንካሬ ከተደበቀበት ያወጣው ነውም ትላለች፡፡ የመጀመሪያ ልጇን እንደ ፀነሰች ከምትወደው ሙያዋ ተለያይታ ወደ ቤቷ ገባች፡፡ ጋዜጦችን እና መፅሔቶችን በማንበብ ጊዜዋን ብታሳልፍም፡፡ ጋዜጦቹን ባገላበጠች ቁጥር ሀዘንም ቅናትም ይሰማት ነበር፡፡ “ወደ ሙያዬ እመለስ ይሆን?” በማለትም ሀሳብ ውስጥ የገባችበትን ጊዜ ታስታውሳለች፡፡

በወቅቱ ተወዳጅ የነበረችው “አዲስ ጉዳይ” መፅሔትን በጉጉት ጠብቃ ታነባለች፡፡ ባነበበች ቁጥር ደግሞ የመፃፍ አምሮቷ ይጨምራል፡፡ አንድ በወቅቱ የአዲስ ጉዳይ አዘጋጅ ወደ ሆነው ጋዜጠኛ መላኩ ዘንድ ደውላ “ለአዲስ ጉዳይ መፃፍ እፈልጋለሁ፡፡ እችላለሁ ወይ?” በማለት ጠየቀችው፡፡ እንደ ሀሳቧም ሆነ እና በአዲስ ጉዳይ ላይ የመጀመሪያው ፅሑፏ ታትሞ ወጣ፡፡ ለራሷ እስኪደንቃት ድረስ ተደሰተች፡፡ ከዚያ በፊት ፅፋ የምታውቅ አትመስለም ነበር፡፡

ቤት ውስጥ የተቀመጠችበት አላማ ደግሞ ሌላ ነገር አስመለከታት፡፡ የእናትነት ውጣ ውረድን የሚያሳይ፣  ሴቶች ወደ እናትነት ከመግባታቸው በፊት እንዲዘጋጁ፤ በእናትነት ህይወት ውስጥ ያሉት ደግሞ እንዲበረታቱ ለማድረግ የሚረዳ መፅሐፍ ለመፃፍ ተነሳች፡፡ ከእርግዝና ጀምሮ በእናትነት እና በልጆች ማሳደግ ዙሪያ “ሁለት ሦስት መልክ” የሚል መፅሐፍ አሳተመች፡፡ የመጀመሪያው እትም በ2006 የተሻሻለውን እትም ደግሞ በ2010 አሳተመች፡፡

የወሊድ ፈቃድ ዘመቻ

“ለውጥ እንደዋዛ አይመጣም፡፡ እንደዋዛ ግን ይጀመራል፡፡”

“እናትነት ለአዲስ ህይወትና ትግል አዘጋጅቶኛል” የምትለው ሮዝ መስቲካ በቂ የወሊድ ፈቃድ ባለመኖሩ ምክንያት እኔና መሰሎቼ ከምንወደው ሙያ፣ ለአገር በጎ አስተዋፅኦ ከምናደርግበት፣ ቤተሰባችንን ከምናስተዳድርበት ሥራ አርቆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በቂ የወሊድ ፈቃድ ባለመኖሩ ምከንያት “ቤቴ ይጎድልብኛል” በማለት እናት ጨቅላዋን ከቤት ጥላ ወደ ደጅ ሥራዋ ትመለሳለች፡፡ ጨቅላዎቹም ያለበቂ  ፍቅርና እንክብካቤ በብዙ ጉስቁልና ያድጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቤተሰብን እና አገርን ይጎዳል በሚል ሀሳብ በፌስ ቡክ “ለውጥ እንደዋዛ አይመጣም፡፡ እንደዋዛ ግን ይጀመራል” በማለት ተጨማሪ የወሊድ ፈቃድ ለኢትዮጵያ እናቶች የሚለውን ዘመቻ ጀመረች፡፡ ይህ ዘመቻዋ በብዙዎች ዘንድ እንድትታወቅ ያደረጋት ሲሆን እንደ ሀሳቧ ስድሰት ወር ባይሆንም ሠራተኛ እናቶች አራት ወር የወሊድ ፈቃድ እንዲያገኙ ሆነዋል፡፡

ምቹ ቤት

ልጆቿን ለማሳደግ በሚል የደጅ ሥራዋን ታቁም እንጂ ላለፉት ሦስት አመታት በዩቱዩብ “ምቹ ቤት” የሚል ቤተሰባዊ ቻናል ከፍታ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ቻናልም ወደ 200 የሚጠጉ ቪዲዮዎችን ሠርታለች፡፡ እንዲሁም በቴሌግራም የምቹ በቤት ቻናል  “የቤተሰብ መድረክ” በሚል በየሳምንቱ ቅዳሜ ለምቹ ቤት አባላት እንግዳ በመጋበዝ ታቀርባለች፡፡ ለአስርት አመታት በቤት በመሆን ልጆቿን እያሳደገች ማህበራዊ ድረ -ገፆችን በመጠቀም ለወላጆች በተለይ ደግሞ ለእናቶች የሚጠቀም ብዙ ሥራዎችን ሰርታለች፡፡

አሁን ደግሞ ወደ አደባባይ ሥራዋ በመመለስ ምቹ ቤት መልቲ ሚዲያ የሚል ድርጅት መስራችና ሥራ አስኪያጅ ሆናለች፡፡

ከሁሉ በላይ እግዚአብሔርን የምታመሰግነው ስለ አራቶች ስጦታዎቿ ነው፡፡ ከባለቤቷ ከዶ/ር ፍቅሩ ተስፋዬ ሁለት ሴት እና ሁለት ወንድ ልጆችን አፍርታለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *