ዶ/ር ዮናስ አድማሱ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ተግባራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡
200 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ዶክተር ዮናስ አድማሱ ይጠቀሳሉ፡፡ ዶክተር ዮናስ አድማሱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስነ-ጽሁፍ መምህርነት ለ17 አመታት ያገለገሉ ሲሆን በ2005 አ.ም በ70 አመት እድሜያቸው ህይወታቸው ያለፈ ምሁር ናቸው፡፡ ዶክተር ዮናስ አድማሱ የታዋቂው ገጣሚ የዮሀንስ አድማሱ ታናሽ ወንድም ሲሆኑ በባህር ማዶ ለረጅም አመት የኖሩም ናቸው፡፡ የህይወት ታሪካቸውን እዝራ እጅጉ አጠናክሮ ሰንዶታል፡፡
ትውልድ እና ልጅነት
በዘመነ- ሉቃስ 1935 ዓ.ም ህዳር 6 ቀን ቅዳሜ ሌሊት 10 ሰዓት ለእሁድ አጥቢያ በዚያን ጊዜው የሸዋ ጠቅላይ ግዛት በመናገሻ አውራጃ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ደጃች ውቤ ሰፈር የአቶ አድማሱ ኃይለማርያም ጓሉ እና የወ/ሮ ጌጤኔሽ ቸኰል ፈንታ ሶስተኛ ልጅ ተወለደ፡፡
እንደ ቤተሰቡ የሀይማኖት ስነ-ስርዓት መሰረትም ይኸው ህፃን ልጅ በአርባ ቀኑ ክርስትና ተነስቶ ስመ- ጥምቀቱ ገብረ ተክለሃይማኖት ተባለ፡፡ ከዚህ በኃላም ዓለማዊ ስም መውጣቱ ግድ ስለነበር ዮናስ በሚል ስም እንዲጠራ ወላጆቹ ወሰኑ ፤ ህፃኑ ዮናስ አድማሱ በወላጅ እናቱ እቅፍ ውስጥ በመሆን ጡት በተገቢው መጠን እየጠባ በእንክብካቤ እና በሚገባ ተኰትኩቶ አደገ፡፡
ለወላጆቹ ሶስተኛ የሆነው ዮናስ አድማሱ 2 ታላላቅ ወንድሞች አሉት፡፡ እነርሱም በህይወት የሌሉት ዮሐንስ አድማሱ እና ይሄይስ አድማሱ ናቸው፡፡ ታናሾቹ ደግሞ ሶስት ወንዶች ኤርምያስ አድማሱ የወንድወሰን አድማሱ ዳንኤል አድማሱ እና አንድ ሴት ሶስና አድማሱ በህይወት ያሉ ናቸው፡፡
ህፃኑ ዮናስ አድማሱ 4 ዓመት ሲሞላው በዘመኑ ይሰጥ በነበረው ሀገራዊ የትምህርት ስርዓት መሰረት ትምህርት እንዲጀምር በቅድሚያ በጐላ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ በአለቃ የማነብርሃን አማካኝነት በመቀጠል ጐላ ሰፈር በሚገኘው የወላጆቹ ግቢ ውስጥ ከጐጃም በመጡ የኔታ ቁሩብ በሚባሉ መምህር ከሰፈር ልጆች ጋር ከፊደል እስከ ዳዊት እና ከዛም በላይ በመማር ንባብን አጠናቀቀ፡፡
አንደኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ
ዮናስ÷ የቄስ ትምህርት እንዳጠናቀቀ በ1944 ዓ.ም በኰከበ ፅባህ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ት/ቤት በመመዝገብ የዘመናዊ ትምህርቱን በመቀጠል የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ፡፡ በ1954 ዓ.ም ለአንድ አመት የማስተማር ግዴታ በቀድሞ የወለጋ ጠቅላይ ግዛት በአርጆ ከተማ በቢትወደድ መኰንን ደምሰው አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተመድቦ የማስተማር ግዴታውን ፈፅሟል፡፡
ዩኒቨርሲቲ
የማስተማር ግዴታውን ከፈጸመ በኋላ በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ባመጣው ውጤት በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለ፡፡ የከፍተኛ ትምህርቱን ተከታትሎ ከመመረቁ አንድ ዓመት በፊት አሁንም በድጋሚ የማስተማር ግዴታውን ለመወጣት በሐረር መምህራን ማሰልጠኛ ተመድቦ በ1958 ዓ.ም ግዴታውን አጠናቆ ወደ ነበረበት ዩኒቨርስቲ ተመለሰ፡፡ በ1959 ዓ.ም በኢትዩጵያ ቋንቋዎች እና ስነፅሁፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ፡፡ በቀጣዩ ዓመት በ1960 ዓ/ም እዛው ተምሮ እተመረቀበት ዩኒቨርሲቲ በምሩቅ ረዳት መምህርነት ተቀጥሮ አንድ ዓመት እንዳስተማረ የውጭ ሀገር የትምህርት እድል በማግኘቱ ከ1961 ዓ.ም እስከ 1962 ዓ.ም ድረስ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ አሜሪካ በመሄድ ትምህርቱን በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመከታተል በ1962 ዓ.ም እንግሊዝኛን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ በማስተማር ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪውን (M.A) አገኘ፡፡
መምህርነት
ወደ ሀገሩም ጊዜ ሳይባክን በመመለስ ቀድሞ ያስተምርበት በነበረው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት መምህርነቱን ቀጠለ፡፡ ጊዜውም 1963 ዓ.ም ነበር፡፡ ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ በማስተማር ላይ እያለ በ1966 ዓ.ም በፈነዳው አብዩት ምክንያት ደርግ በ1967 ዓ.ም ታህሳስ 12 ቀን ባወጀው የእድገት በህብረት የእውቀት እና የሥራ ዘመቻ መሰረት ዮናስ አድማሱ ከዩኒቨርሲቲው ለዘመቻው ወደ ዱብቲ አሳይታ በመዝመት ግዳጁን ጨርሶ ሲመለስ በ1968 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ደርግ ላቋቋመው የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት ውስጥ እንዲያገለግል ከስራ ባልደረባውና ከወዳጁ ከዶ/ር እሸቱ ጮሌ ጋር ተመደበ፡፡
ስደት እና ተጨማሪ ትምህርት
ዮናስ ጥቂት ጊዜ እንደቆየ በጽ/ቤቱ ውስጥ የሚካሄደው እንቅስቃሴ ስላላማረው ከወዳጁ ከዶ/ር እሸቱ ጮሌ ጋር ጽ/ቤቱን ትተው ተሰወሩ፡፡ ከዛም ዮናስ አድማሱ በወቅቱ ከደርግ ጋር ከፍተኛ ፍልሚያ ውስጥ በነበረው የፓለቲካ ድርጅት ኢ.ሕ.አ.ፓ ውስጥ በመግባት ከደርግ ጋር ትግል አደረገ፡፡ በወቅቱ የነበረበት ድርጅት የትግል ስልት እንዳሰበው ባለመሆኑ የነበረው አማራጭ ሀገር ጥሎ መሰደድ በመሆኑ በሱዳን እና በግብፅ ጥቂት እንደቆየ ወደ አሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ሂውስተን ከተማ አቀና፡፡ ለሁለት ዓመታት ያህል ከቆየ በኋላ ወደ ካሊፎርኒያ ግዛት በመሄድ ሎሳንጀለስ ከተማ በሚገኘው እና ቀደም ሲል ሁለተኛ ዲግሪውን ባገኘበት ካሊፎርንያ ዩኒቨርሲቲ ኰሌጅ በመግባት ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ በአፍሪካን ስተዲስ በድጋሚ ሁለተኛ ዲግሪውን (M.A) በመቀጠልም በኰምፓሬቲቭ ሊትሬቸር የዶክትሬት ዲግሪውን (P.H.D) አገኘ፡፡
ዳግም ወደ ሀገር ቤት
በ1988 ዓ.ም በስደት ከነበረበት አሜሪካ ወደ ሀገሩ በመመለስ ቀድሞ ባስተማረበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የመምህርነቱን ሥራ ቀጥሎ በማስተማር እና በምርምር ስራዎቹ የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝቷል፡፡
በትርፍ ጊዜውም ለተለያዩ ድርጅቶች የትርጉምና የአርታኢነት ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ከሁሉም በላይ የወንድሙን የዮሐንስ አድማሱን ስራዎች “እስቲ ተጠየቁ” የሚለውን ግጥም መፅሐፍ እና “የዮፍታሄ ንጉሴን የሕይወትና የፅሁፍ ታሪክ” መጽሐፍ አሰናኝቶ ታትመው ለንባብ እንዲበቁ አድርጓል፡፡
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ከተማሪነት እስከ አስተማሪነት በቆየባቸው ጊዜያትም “የኮሌጅ ቀን’’ በዓል ላይ የግጥም ውድድር ተሳታፊ የኮሌጅ የሙዚቃ ባንድ ’’ ግሊ ክለብ’’ አባል ነበር፡፡ /በተማሪነቱ/በተጨማሪም ያላቻ ጋብቻ ትያትር ላይም “አባ ማሚቶ” የተባለውን ጠጠር ጣይ ገፀ-ባህርይ ወክሎ ተጫውቷል፡፡በወቅቱ ትያትሩን ሊመርቁ አፄ ኃ/ሥላሴ በቦታው ተገኝተው ስለነበር አተዋወኑን አድንቀውለት ነበር ይባላል፡፡
ማስተማርና ምርምር
የግሊ ክለብ አባል እያለም ሩቅ ምስራቅ ሳለሁ የተባለውን የጥላሁን ገሠሠን ዘፈን በመዝፈን አድናቆትን አግኝቷል፡፡በመምህርነቱም ጊዜም አማርኛ በኮሌጅ ደረጃ የተባለውን የዩንቨርስቲውን የአማርኛ መማርያ መጽሐፍ ከወንድሙ ከዮሐንስ አድማሱ ጋር ለማዘጋጀት ችሏል፡፡በተጨማሪም የሴኔት አባል፤ የዩንቨርስቲው ስራ አመራር አባል፤የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ተጠባባቂ ዳይሬክተር፣ የአ.አ ዩኒቨርስቲ የፕሬስ ቦርድ አባል የኢትዩጵያ ቋንቋዎችና ስነፅሁፍ መፅሔት ዋና ኤዲተር ሆኖ አገልግሏል፡፡ በኖርዌይ ሀገር በተደረገው የሊቃውንት ጉባኤም ላይ ተሳትፏል፡፡ የኢትዩጵያ ስነ-ፅሑፍ የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርት ፕሮግራም ሲከፈት ስርዓተ ትምህርቱን በመቅረፅ፣ በማስተማር እና በማማከር አገልግሏል፡፡
በተለያዩ ጉባኤዎች ላይ ሥነ- ፅሑፍና ቋንቋን አስመልክቶ የተመረጡ ጥናቶችን አቅርቧል፡፡ዶ/ር ዮናስ አድማሱ ወንድሙ ዩሐንስ አድማሱ በሕይወት እያለ ብዙ የደከመበትን የዮፍታሄ ንጉሴ መፅሐፍ ለማሳተም የነበረውን ፍላጎት እውን አድርጎ መጽሐፍ ታትሞ በማለቁ የተሰማውን እርካታና ደስታ በመጽሐፉ የምርቃት ቀን ለማጣጣም እንደማይችል ከስሙ በስተቀር ነብይ ሆኖ ያወቀ ይመስል አስቀድሞ ፈጣሪውን እስከዛች ቀን ድረስ እድሜ እንዲሰጠው እንደተማፀነ ነብይነቱ እውን ሆኖ እሱን ብቻ ሳይሆን ዘመድ አዝማዱን ወዳጆቹን እና የሚያውቁትን ሁሉ ያሳቀቀ አስደንጋጭ ነገር ተከስቶ የጓጓለለት መጽሐፍ ሊመረቅ 12 ቀን ሲቀረው በእለተ አርብ የካቲት 1 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ በ8፡00 ሰዓት በተወለደ በ70 ዓመቱ ላይመለስ አሸለበ፡፡ የካቲት 3 ቀን በእለተ እሁድ ከቀኑ በ8፡00 ሰዓት ስርዓት ቀብሩ ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ፣ ወዳጆቹ፣ የሥራ ባልደረቦቹ፣ ተማሪዎቹና የሚያደንቁት ሁሉ በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል፡፡
ከህልፈቱ በኋላም የራሱ ግጥሞች ‹‹ጉራማይሌ›› በሚል ርእስ ታትመው ለንባብ በቅተዋል፡፡
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ዶክተር ዮናስ አድማሱ በተማሪዎቻቸው በጣም የሚከበሩ ፤ በማስተማር ስልታቸው የተደነቁ በተለይም በ1990ዎቹ ያስተማሯቸው በግልጽ እንደሚናገሩት ዶክተር ዮናስ ጥልቅ ንባብ ያካሄዱ በመሆኑ እውቀታቸውም የዚያኑ ያህል ጥልቅ ነው፡፡ ዶክተር ዮናስ አድማሱ ለጥበብ ስራም የቀረቡ በመሆኑ ኪነጥበብ ላይ በሚሰጡት ትንታኔም ብዙዎች ይደነቁባቸዋል፡፡ ከተለመደው የስነጽሁፍ የንባብና የጥናት ብሂል ወጣ በማለት አዲስ ግኝት ወይም እይታ በማምጣት ለአካዳሚክ አለሙ ልዩ ስጦታ አበርክተዋል፡፡
ዶክተር ዮናስ አድማሱ ካፈሯቸው ተማሪዎች መካከል በአብዛኛው የእርሳቸውን ፈለግ ተከትሏል ተብሎ የሚነገርለት ተባባሪ ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ ሲሆን እርሱም በተጠየቀ ጊዜ ስለ እርሳቸው አውርቶ አይጠግብም፡፡ ዶክተር ዮናስም ቢሆኑ ለቴዎድሮስ ገብሬ ልዩ ከበሬታ ስለነበራቸው ያቀርቡት ነበር፡፡
ዶክተር ዮናስ አድማሱ በስነ-ጽሁፍ መምህርነት የማይረሱ ናቸው፡፡ በጣም በማንበባቸው ተማሪዎቻቸው ለሁሉ መነሻ ንባብን እንዲያደርጉ ይመክራሉ፡፡ ዶክተር ዮናስ አድማሱን በዚህ ሰነድ ላይ ስናቀርባቸው ለአዲሱ ትውልድ የሚሰጡት ትምህርት ስላለ ነው፡፡ ደግሞም ብዙም ስለ እርሳቸው ማንነት የሚታወቅ ባለመሆኑ ይህ አጭር የህይወት ታሪካቸው በመጠኑም ቢሆን ይገልጻቸዋል፡፡ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ስለ ደራሲያን ሲያስብ የስነ-ጽሁፍ መምህራን ሚና ጎልቶ መታየት አለበት ብሎ ያምናል፡፡ የስነ-ጽሁፍ ምሁራን ሳይንሱን ሲያመላክቱ ደራሲያን ደግሞ እየጻፉ በጥበቡ አለም ላይ ይናኙበታል፡፡
ባለፉት አመታት ደግሞ ብዙ የስነ-ጽሁፍ መምህራን የደራሲያንን ስራ አቃንተዋል፡፡ እንግዲህ ሁለቱም ዘርፎች ለድርሰት አለም ምን ያህል ወሳኝ እና አስፈላጊ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ይህ የህይወት ታሪክ የዶክተር ዮናስ አድማሱን ቤተሰቦች በማስፈቀድ የተሰራ ነው፡፡ ለዚህ ጽሁፍ መሳካት የዶክተር ዮናስ አድማሱ ታናሽ ወንድም ዳንኤል አድማሱ ላደረገልን ትብብር ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠንም ማመስገን እንወዳለን፡፡
ይህ አጭር የህይወት ታሪክ በየጊዜው ማሻሻያ እየተደረገበት ይወጣል፡፡ ይህ የህይወት ታሪክ ዛሬ ነሀሴ 10 2015 ከሌሊቱ 6 ሰአት በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች ላይ ተቀመጠ፡፡ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ተጠናክሮ ተሰነደ፡፡