ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በልዩ ልዩ ሙያ ላይ ሀገር ያገለገሉ ሰዎችን የህይወት ታሪክ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ስናቀርብ ነበር፡፡ በህክምና ዘርፍ ሀገራቸውን በትጋት ካገለገሉት መካከል ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ይጠቀሳሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ በብዙዎች የሚወደዱ የዛሬ 24 አመት ህይወታቸው ያለፈ ታላቅ የኢትዮጵያ ባለውለታ ናቸው፡፡ ይህ የህይወት ታሪካቸው በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ እና ዊኪፒዲያ ላይ ሲወጣ ቀኑ የፕሮፌሰር አስራት የልደት ቀን ሰኔ 12 ነበር፡፡ እነሆ ታሪካቸው እንዲህ ይነበባል፡፡
ስለ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሳስብ አንድ በግል የጻፉት የስራ ልምድ ደብዳቤ አለ፡፡ ይህ በታይፕ የተተየበና ሀኪሙ ለቤት ውስጥ የቤት ሰራተኛቸው የጻፉት የስራ ልምድ ደብዳቤ አስገራሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ አንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ለነባር ሰራተኛው አልፎ አልፎ የስራ ልምድ ደብዳቤ ለሚመለከተው ሁሉ ብሎ ለመጻፍ ወደ ኋላ በሚልበት ዘመን ፕሮፌሰር አስራት ባማረ እና ለዛ ባለው አማርኛ የጻፉት የስራ ልምድ ማራኪ ነበር፡፡ ልምዱ የተጻፈላት ሴት ወይዘሮ ብርክቲ አለም ስትባል ፕሮፌሰር አስራት ቤት ወጥ በመስራት፣ልብስ በማጠብና በመተኮስ ታገለግል ነበር፡፡
ታዲያ 9 አመት በትጋት ያገለገለችው ወይዘሮ ብርክቲ ከሀኪሙ ቤት መስራቷን ስታቆም ፕሮፌሰር አስራት ለወደፊቱ መልካም እድል እንዲገጥማት ብለው በማሰብ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ጥሩ የስራ ልምድ ጽፈውላታል፡፡
በታይፕ በራሳቸው በፕሮፌሰር የተጻፈውን ጽሁፍና ፊርማ ብትመለከቱ ይህን እንዴት አሰቡት? ያሰኛል፡፡‹‹…..ወይዘሮ ብርክቲ በጣም ጎበዝና አዋቂ የወጥ ቤት ሰራተኛ ከመሆኗም በላይ በልብስ አጠባና መተኮስም ችሎታዋ ያላነሰ ነው፡፡ በጠቅላላም ጎበዝ ሰራተኛ ከመሆኗም በላይ ከሰው የመስማማትና የመግባባት ጸባይ ያላት ንጽህናን ጠባቂ ነች፡፡ከሁሉም በላይ ታማኝና እምነት የሚጣልባት ጨዋ ሴትዬ በመሆኗ ለተመሳሳይ ስራ ሁሉ ድጋፌን የምሰጣት መሆኑን አረጋግጣለሁ…›› ሲሉ ፕሮፌሰሩ ትህትና በተላበሰ መንገድ የስራ ልምዱን ጽፈውላታል፡፡ ይህ ደብዳቤ በራሳቸው በፕሮፌሰር የተጻፈ ለመሆኑ ኦሪጅናል ደብዳቤውን በማየት መረዳት ትችላላችሁ፡፡
ሀሳቤን ቀለል ባለ ጉዳይ መጀመር የፈለግኩት ምሁሩ ምን አይነት ሰው እንደሆኑ ለማሳየትና ደብዳቤውም እጄ ስለገባ ለማሳየት በመፈለጌ ጭምር ነው፡፡ እኒህ ሰው ህይወታቸው ካለፈ 20 አመት ቢያልፋቸውም በህይወት ቢኖሩ ትናንት ሰኔ 12 2011 አ.ም 91 አመት የልደት በኣላቸውን ያከብሩ ነበር፡፡ ይህን የልደት ቀናቸውን ምክንያት በማድረግ የሀገራችን የህክምና አባት የሚባሉትን ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ለመዘከርና የሰሩትን በጎ ስራ ለማስታወስ ወደድኩ፡፡
የህክምና ምሁሩ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ አባታቸው አቶ ወልደየስ አልታየ ሲባሉ ወላጅ እናታቸው ደግሞ ወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌ ይባላሉ፡፡ ሰኔ 12 1920 አ.ም የተወለዱት የህክምና ምሁሩ አዲስ አበባ የትውልድ ከተማቸው ነች፡፡ የፕሮፌሰር አስራት የዘር ሀረግ ከወደ ሰሜን ሸዋ ይመዘዛል፡፡እንደአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ምሁሩ የተገኙት ከደሃ ቤተሰብ ነበር፡፡ አባታቸው አቶ ወልደየስ አልታየ በጸሀፌ-ትእዛዝ ሀይሌ ወልደስላሴ አስተዳደር ውስጥ በጸሀፊነትና በአስተዳደር ተግባር የተሰማሩ ነበሩ፡፡ወላጅ እናታቸው ወይዘሮ በሰለፍ ይዋሉ ጽጌም በአነስተኛ ንግድ የሚተዳደሩ ነበሩ፡፡
ሕጻኑ አስራት የ3 አመት ታዳጊ እያለ ማለትም በ1923 አ.ም ወላጆቹ በፍቺ ምክንያት ተለያዩ ፡፡ ይህን ተከትሎም ህጻኑ አስራት ከእናቱ ጋር ድሬደዋ ለመሄድ ተገደደ፡፡ በድሬዳዋ ከተማም ከእድሜ እኩያዎቹ ጋር ልጅነቱን በደስታና በቡረቃ ማሳለፍ ጀመረ፡፡ አስራት የ8 አመት ልጅ እያለ ጣሊያን ሀገራችንን ወረረ፡፡ በአመቱ በ1929 አ.ም የወራሪዎቹን አለቃ ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገው ሙከራ ፋሽስቱ ባስተላለፈው ቀጭን ትእዛዝ የአስራት ወላጅ አባትን ጨምሮ ከ30 በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በግፍ እንዲገደሉ ተደረገ፡፡
ህጻኑ አስራትም የወላጆቹ በፍቺ መለያየት ሳያንሰው ወላጅ አባቱን በነፍሰ- በላ ጨካኞች ተነጠቀ፡፡ ይህ ሁሉ በሚሆንበት ሰአት አስራት ድሬደዋ እናቱ ጋር ፊደል እየቆጠረ ነበር፡፡ በመከራ ላይ መከራ የተፈራረቀበት ልጅም ብዙም ሳይቆይ እናቱን በሞት ተነጠቀ፡፡ በዚህ ሰአት አንድ ለእናቱ የነበረው ትንሹ አስራት ወላጅ አልባ ሆኖ ብቻውን ቀረ፡፡ ወላጅ እናቱ ወይዘሮ በሰልፍይዋሉ እንደሞቱ ህጻኑ አስራት ለአያቱ ለወይዘሮ ባንቺወሰን ይፍሩ ጋር መኖር ጀመረ፡፡አጎቱ አቶ ዘውዴ ወረደወርቅ እዚያው ድሬዳዋ ይኖሩ ስለነበር የቄስ ትምህርትን እንዲከታተል አደረጉት፡፡ምንም እንኳን ወላጆቹን በህጻንነቱ ቢያጣም ሕጻኑ አስራት ግን ልበ-ብሩህ ልጅ ነበር፡፡
አስራት በልጅነቱ በጣም ጎበዝ በመሆኑ አመት ሳይሞላው ወንጌሉን ከቁጥር ጋር አንበልብሎ ከፍካሬ እስከ ነቢያት ደግሞ ድቁናን ተቀበለ፡፡
አያቱ ቀኛዝማች ጽጌ ወረደወርቅ ታዋቂ አርበኛ ነበሩ፡፡ ወራሪው ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመግዛት የሚያስቸግሩትን አርበኞች በግዞት ወደ ጣሊያን በማሻገር ለጊዜውም ቢሆን እፎይታ አገኛለሁ ብሎ ያምን ነበር፡፡ ስለሆነም አርበኛው የአስራት አያት ቀኛዝማች ጽጌ ወደ ጣሊያን ተግዘው በዚያው እንዲቆዩ ተደረገ፡፡በኋላ አርበኛው ጽጌ ወረደወርቅ 3 አመት ተኩል በግዞት ከቆዩበት በክብርና በድል ተመለሱ፡፡በተመለሱበት ወቅትም የልጅ ልጃቸውን ህጻን አስራትን ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ አስመጡት፡፡
ከ5 አመቱ መራር የአርበኞች ትግል በኋላ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት በ1933 አ.ም ጣሊያን ከሀገራችን ሲወጣ ታዳጊው አስራትም በአዲስ አበባ በተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት ዘመናዊ ትምህርት ለመማር ተዘጋጀ፡፡በትምህርቱም ላቅ ያለ ሆኖ ተገኘ፡፡ ተፈሪ መኮንን በተመዘገበ በ2 አመቱ ከአጠቃላይ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች አንደኛ ሆኖ ስለተገኘ በወቅቱ ከፍተኛ ዋጋ የነበረውን የካሜራ ሽልማት ሊሸለም ችሏል፡፡ ሁሉንም ክፍሎች በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ የኖረው ታዳጊው አስራት ውጭ ሄደው እንዲማሩ ከተመረጡ ተማሪዎች አንዱ ለመሆን ቻለ፡፡በዚህም መሰረት ለሁለተኛ ትምህርት ግብጽ ቪክቶሪያ ኮሌጅ ተላከ፡፡
ወጣቱ አስራት፣ ቪክቶሪያ ከተማ በሚገኘው የእንግሊዞች ኮሌጅ ትምህርቱን ጀመረ፡፡በነገራችን ላይ፣ አስራት ከጣሊያን ተባርሮ መውጣት በኋላ ወደ ውጭ ከተላኩት ተማሪዎች መካከል 42ኛው ነበር፡፡ከሀበሻ ምድር የተገኘው ወጣቱ አስራት በቪክቶሪያ ኮሌጅ ስሙ ናኘ፡፡ይህ ልጅ የክፍሉን ተማሪዎች ከኋላ እያስከተለ ወደ ፊት ሽምጥ ጋልቧል፡፡ ከድሬዳዋ አብነት ተማሪ ቤት የሚመዘዘው ጉብዝና አብሮት ባህር ተሻግሯል፡፡ በእስክንድሪያ ቪክቶሪያ ኮሌጅ ለ5 አመታት የቆየው ባለብሩህ አእምሮ ወጣት ለተጨማሪ ከፍተኛ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሀገር እንዲያመራ ሁኔታዎች ተመቻቹለት፡፡
እንግሊዞች በዛን ወቅት ላቅ ያለ ውጤት ላስመዘገቡ ነጻ የትምህርት እድል ይሰጡ ነበርና አስራትም መስፈርቱን በሚገባ ያሟላ በመሆኑ ወደ ዩኒቨርሲቲያቸው እንዲገባ መርጠውታል፡፡ በዚህም መሰረት ስኮትላንድ ወደሚገኘው በአለም ግዙፉ የእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲ ኤደንብራ እንዲገባ ተደረገ፡፡ አስራትም የስኮትላንዱ ኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ እንደገባ ህግ እንዲያጠና ከትምህርት ሚኒስትሩ ዘንድ ደብዳቤ ተልኮለት ነበር፡፡ እርሱ ግን ዋና ፍላጎቱ ህክምና ማጥናት ነበር፡፡ በመሆኑም የስኮትላንዱን ኤደንብራ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለ፡፡ አስራት ወልደየስ በስኮትላንድ ኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርቱን በማጠናቀቅ ወጣት ሀኪም ሆኖ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡ በጊዜው ማለትም በ1946 አ.ም የ26 አመት ወጣት የነበረው ዶክተር አስራት ሀገሩን ለማገልገል ታላቅ ናፍቆትና ፍላጎት ነበረው፡፡
ፕሮፌሰር አስራት፣ በመጀመሪያ ሀኪም ሆነው ስራ የጀመሩት በልእልት ጸሀይ የዛሬው ጦር ሀይሎች ሆስፒታል ውስጥ ነበር፡፡ትምህርታቸውንም ጨርሰው እንደተመለሱ በወቅቱ ስመ-ጥሩ የነበሩት አርበኛ ደጃዝማች ጸሀይ እንቁስላሴ ወጣቱን ዶክተር አስራትን አስጠርተው:
‹‹…… እኛ በአርበኝነት ይህችን ሀገር ከኢትዮጵያ ጠላቶች ስንጠብቃት ከረምን፡፡ አሁን የተማራችሁ ኢትዮጵያውያን ተገቢውን አመራርና ሀላፊነት ለመውሰድ ስለመጣችሁ በጣም ተደስተናል፡፡እኔም ከፈረንጆቹ እጅ እንዳይወድቅ ስጠብቅ የነበረውን ይህንን የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነቱን ቦታ ተረከብኩ፡፡ለአስረካቢነት ያበቃኝንም አምላክ አመሰግነዋለሁ፡፡
በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ይህንንም ለግርማዊ ጃንሆይ አስረዳለሁ›› በማለት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ሀላፊነቱን ለዶክተር አስራት ለመስጠት ሀሳብ አድርገው ነበር፡፡ ዶክተር አስራት ግን የሀገሬን ህዝብ በተማርኩበት የህክምና ሙያ የተሻለ ላገለግለው እችላለሁ በማለት የወንበር መረከቡን ጥያቄ ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ ከ1946-1951 ድረስ ለ5 አመታት ዶክተር አስራት በጦር ሀይሎች ሆስፒታል/በቀድሞው ልእልት ጸሀይ ሆስፒታል/ ካገለገሉ በኋላ ለተጨማሪ ትምህርት ኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በቀዶ ህክምና ስፔሻላይዝድ አደረጉ፡፡
ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ከሰለጠኑ ምሁራን መካከል የመጀመሪያው የቀዶ ጥገና ሀኪም እንደመሆናቸው በሀገራቸው የተከፈቱ ብዙ መሰረታዊ ክፍተቶችን መሙላት ነበረባቸው፡፡ ፕሮፌሰር አስራት ከኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ አድርገው እንደመጡ በ1954 ግድም ከቅርብ ጓደኞቻቸው ጋር ሆነው ዶክተሮችን የሚያሰለጥን ኮሌጅ እንደሚያስፈልግ ለቀዳማዊ ሀይለስላሴ ያመለክታሉ፡፡ነገር ግን የውጭ ሀገር ሰዎቹ ይህ ሀሳብ በፍጹም የማይሞከርና አዳጋችነቱንም ለንጉሱ ያማክራሉ፡፡እነ ፕሮፌሰር ግን የኮሌጁን አስፈላጊነት የግድ መሆኑን በማመን ንጉሱን ወተወቱ፡፡ ከብዙ ትግል በኋላም የኮሌጁ መከፈት አይቀሬ ሆነ፡፡
ምስጋና ለፕሮፌሰር አስራትና ለባልደረቦቻቸው ይድረሳቸውና ‹‹ አይሆንም›› የተባለው ነገር በከፍተኛ ትግል የኢትዮጵያውያን የመጀመሪያ የህክምና ኮሌጅ በ1957 በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ስር ተከፈተ፡፡ ከፕሮፌሰር አስራት ጋር እንደ ፕሮፌሰር እደማሪያም ጸጋ ፣ዶክተር ጳውሎስ ቀንዐ፣ዶክተር ነቢያት ተፈሪ፣ እና ዶክተር ደምሴ ሀብቴ በመሳሰሉ የቁርጥ ቀን ልጆች ትምህርት ቤቱ ተጀመረ፡፡ፕሮፌሰር አስራት ‹‹ብረት ለበሱ ዶክተር›› የሚል ቅጽል ስም አግኝተዋል፡፡ ይህም ስም የተሰጣቸው ካለእረፍት በመስራታቸው ነው፡፡ሲሰሩ ውለው ሲሰሩ ቢያድሩ ይደሰታሉ እንጂ ምሬት ማሰማት የለም፡፡ ይህ በባልደረቦቻቸው ሁል ጊዜም የሚነሳ ነው፡፡
ፕሮፌሰር አስራት በሰኔ 24 1983 አ.ም በተደረገው ኮንፈረንስ ላይ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በመወከል ንግግር አድርገው ነበር፡፡በተለይ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በተለያየችበት ወቅት ውሳኔው መጽደቅ የለበትም ብለው በጽናት ከተከራከሩት ውስጥ ፕሮፌሰር አስራት በቀዳሚነት ስማቸው ይነሳል፡፡
ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ በቀዶ ህክምና ሙያቸው በኢትዮጵያ ምድር ብቻ ሳይሆን በአለምም ስማቸው የናኘ ነበር፡፡ ታዲያ እኒህ ሰው ከህክምና ወደ ፖለቲካ ሲገቡ ብዙ አስተያየቶች ተስተናግደዋል፡፡ በ1986 አ.ም ፕሮፌሰር አስራት በዚህ ጉዳይ ላይ ‹‹ማህሌት›› ለተባለ መጽሄት የሰጡትን ቃለ-ምልልስ ማየት ያስፈልጋል፡፡
‹‹….. መአህድ የተመሰረተው የሽግግር መንግስቱ ከተመሰረተ ከ7 ወራት በኋላ ነበር፡፡ እኔ የሰኔው ኮንፈረንስ ተካፋይ ነበርኩ፡፡ ለኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ስጋቴን ግልጽ አድርጌያለሁ፡፡ እንዲመዘገብም ተደርጓል፡፡ ያኔ ያልኩት ብዙም ሳይቆይ ይታይ ጀመር፡፡ የጎሳ ግጭትና እልቂት ተስፋፋ፡፡ ይበልጥ የተጋለጠው ደግሞ አማራው ሆነ፡፡ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅትንም እንዲመሰረት ያደረግነው ከዚህ በመነሳት ነው›› ብለው ነበር፡፡
ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ለ 8 አመታት የመላው አማራ ህዝብ ድርጅትን ሲመሩ ብዙ እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ በተለይም እርሳቸው በጎሳና በቋንቋ ላይ የተመሰረተውን አወቃቀር ክፉኛ በመተቸት ይታወቃሉ፡፡ በ1985 አ.ም 42 የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ሲባረሩ ከተሰናበቱት መሀል እርሳቸው አንዱ ነበሩ፡፡
ፕሮፌሰር አስራት ግንቦት 6 1991 አ.ም በ70 አመታቸው በሞት ከተለዩ በኋላ ‹‹ ዘ ጋርዲያን›› ጋዜጣ የሚከተለውን ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
‹‹……. ፕሮፌሰር አስራት፣ ከቀዶ ህክምና ጠበብትነታቸው ባሻገር የዩኒቨርሲቲ ዲንም ነበሩ፡፡ሰውየው በተለይ በአነጋጋሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪነታቸውና በኋላም በፖለቲካ እስረኛነታቸው ይታወቃሉ፡፡ የንጉስ ሀይለስላሴ የግል ሀኪም ሆነውም አገልግለዋል፡፡ አስራት በመንግስቱ ሀይለማሪያም ወታደራዊ አስተዳደር የማስተማርና የህክምና ተግባራቸውን በወጉ ተወጥተዋል፡፡ አስራት ባላቸው ሙያዊ ብቃት በተሻለ የኑሮና የሙያ ነጻነት በምእራቡ አለም በመስራት ብዙ ጥቅም ማግኘት ይችሉ ነበር፡፡ እርሳቸው ግን የግል ጥቅምና ድሎት ሳያጓጓቸው ህዝባቸውን ማገልገል መርጠዋል፡፡…..›› ሲል ጋዜጣው ሰፊ ሀተታ አቅርቦ ነበር፡፡
የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ኮፊ አናን በህልፈታቸው ሰሞን መልእክት አስተላልፈው ነበር፡፡ ‹‹………. የዶክተር አስራት ወልደየስን ሞት የሰማሁት በታላቅ ሀዘን ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ እኒህ ተሰጥኦ ያላቸው ቀዳጅ ሀኪምና ሩህሩህ የኢትዮጵያ ልጅ ሊረሳ የማይችል መልካም ተግባርና አርአያ ቅርስ ትተውልናል፡፡ ዶክተር አስራት ለዲሞክራሲ ምስረታ ጥርጊያውን በሚከፍቱት በሰላም ፣በሰብአዊ መብት ጥበቃና በመድብለ- ፓርቲ በማመን ብቻ ሳይሆን ህይወታቸውንም ሰውተዋል፡፡ ስለዚህ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስም ልባዊ ሀዘኔን ለቤተሰባቸው እንዳስተላልፍ ይፈቀድልኝ፡፡በዚህ በሀዘናችሁ ወቅት በጸሎት አንረሳችሁም፡፡ የዶክተር አስራትን አርአያ እንከተላለን ›› በማለት ኮፊ አናን መልእክታቸውን አድርሰው ነበር፡፡
ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንም፣ በጊዜው በፕሮፌሰር አስራት ሞት ካዘኑት መሀል አንዱ ናቸው፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ፕሮፌሰር አስራትን ሲገልጧቸው ከኢትዮጵያዊነት በስተቀር ሌላ ወንጀል የሌለበት ብለዋቸዋል፡፡ ሎሬት ጸጋዬ በፕሮፌሰር አስራት አስከሬን ሽኝት ላይ እንዲህ ብለውም ነበር፡፡
‹‹……….አስራት ዛሬ እንደሚባለው በሀረርጌ ፣ድሬዳዋ ልጅነትህ ወይም በመንዜነትህ ሳይሆን ለቁርጠኛ ኢትዮጵያዊነትህ ነው መላው የኢትዮጵያ ልጅ እጅ የሚነሳህ፡፡ ጨቋኝነትን ታግለህ አንድ ሰው አንድ ድምጽ የሚለውን ዴሞክራሲያዊ መርህ በማራመድህ ነው መላው የኢትዮጵያ ልጅ የሚኮራብህ ›› በማለት ሎሬት ጸጋዬ ተናግረው ነበር፡፡
ፕሮፌሰር አስራት በህክምናው አለም በጠቅላላ ከ35 አመት በላይ ያገለገሉ ነበሩ፡፡ ብዙ ታካሚዎች ስለ ፕሮፌሰር አውርተው አይጠግቡም፡፡ የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍል የቀድሞ ባልደረባ የነበረው ሰለሞን ክፍሌ በፕሮፌሰር አስራት ከታከሙት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ሰለሞን በጦር ሀይሎች ሆስፒታል ሲታከም ፕሮፌሰር አስራት ትልቅ ውለታ እንደዋሉለት ይናገራል፡፡ በወቅቱ ተገቢውን ህክምና ያደረጉልኝ ታላቅ ሀኪም ናቸው ሲል ለእርሳቸው ያለውን ታላቅ አክብሮት ገልጦ ነበር፡፡
የህክምና ትምህርታቸውን እንግሊዝ ሀገር የተከታተሉት እውቁ የህክምና ሰው ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ፊላደልፊያ በሚገኘው ፔኒሲለቪንያ ዩኚቨርሲቲ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው ነበር በእለተ-አርብ ህይወታቸው ያለፈው፡፡ህይወታቸውም ሲያልፍ የ70 አመት ሰው ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሀገራቸውን በህክምና ሙያ ያገለገሉ ታላቅ የሀገር ባለውለታ ሲሆኑ እኒህ ሰው በህይወት ቢኖሩ ዛሬ ሰኔ 12 2014 የ94 አመት የልደት በአላቸውን ያከብሩ ነበር፡፡