ፍሰሀ በላይ ይማም

ፍሰሀ በላይ ይማም

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሰራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡

በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ፍሰሀ በላይ ይማም አንዱ ነው።ፍሰሀ በላይ ትውፊታዊ ቴአትሮችን በመስራት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከተ ነው።

በ1992 ህይወቱ ያለፈው ፍሰሀ አዲስ አበባ በማስተማሩ ብዙዎች የሚያከብሩት ባለሙያ ነበር። ሰላማዊት ተስፋዬ ህይወት ታሪኩን ሰንዳዋለች። አማረ ደገፋው ደግሞ ስለ ፍሰሀ የተሰጡ ምስክርነቱን አጠናክሮታል ።

የረዥሙ ቴአትረኛ አጭር የህይወት ታሪክ

ሁለገቡ ከያኒ የሚለው ስም ፍሰሃ በላይ ይማም ከሚለው ስሙ ጋር አብሮ ይነሳል ፡፡100 አመታትን ባስቆጠረው በኢትዮጵያ የትያትር ጥብበ ውስጥ በትውፊታዊ ቴያትር አፃፃፍ አና ዝግጅት እንዲሁም በምርምር ስራዎቹ ስሙ በደማቅ ተፅፏል፡፡

ፀሀፌ ተውኔት እና ተዋናይ ፍሰሃ በላይ ይማም በወሎ ክፍለሃገር በደሴ ከተማ ነሃሴ 5 ቀን በ1946 ዓ.ም ነበር የተወለደው፡፡የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በእቴጌ መነን ት/ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በወ/ሮ ሲህን ት/ቤት በ1963 ዓ.ም አጠናቆ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችል ውጤት ቢመጣለትም ቤተሰቦቹ ባጋጠማቸው ችግር እነሱን ለመርዳት ሩጋ ወደሚባል ሃገር ሄዶበመምህርነት፣በዳይሬክተርነት እና በፅህፈት ቤት የቢሮ ሰራተኝነት አገልግሏል፡፡ በመህርነት ጊዜው የሚከፈለውን ደሞዝ በሙሉ ለቤተሰቦቹ እየላከ ለእራሱ መተዳደያ ደግሞ የእጁ ስራ ወጤቶች የሆኑትን ክራር ፣ማሲንቆ እና ሌሎችንም የሙዚቃ መሳሪያዎች እየሰራ ይሸጥ ነበር፡፡ ከመስራትም አልፎ ደግሞ ራሱ የሙዚቃ መሳሪያዎቹን ይጫወት ነበር፡፡

ከሩጋ ወደ ደሴ በዝውውር ከመጣ በኋላ በወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን ውስጥ በመቀላቀል የቡድኑ ፈርጥ ለመሆን በቅቷል፡፡ በሙዚቃ፣ በውዝዋዜ፣ በቴያትር እና በጥናትና ምርምር የቡድኑ ደጀን ሆነ፡፡ ፍስሃ ተወዳጅ የሆኑትን አብዛኛውን ስራዎቹን የተውኔት ስራዎቹን ስራ የሰራው በወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን እያለ ነው፡፡ ቁመተ ሎጋው ና መልከ መልካሙ ፍስሃ ታዋቂነትን ያተረፈለት ላሊበላ ኪነት ውስጥ እያለ በከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው በፈረስ ነበር በዚህም የብዙዎች የልጅነት ትዝታና አርአያ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡

ምርምር ስራዎች

በወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን ውስጥ የሚሰሩት ሙዚቀዎች እና ውዝዋዜዎች ባህላቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ትክከለኛ ቦታዎቻቸው መገኛቸው ላይ እየሄደ ጥናት ያደርግ ነበር፡፡ ለምሳሌ እሪኩም በተሰኘው የህዝብ ሙዚቃ ስራ በቡድኑ ሲሰራ አልባሳቱን ጌጣጌጦቹን እና ውዝዋዜውን ያጠናው እሱ ሲሆን ከጥናቱ በኋላም አልባሳቱን ራሱ ዲዛይን አድርጎ ሰርቷቸዋል፤ በውዝዋዜም ተሳትፎበታል፡፡ ከአንጋፋዎቹ ከነ መሃመድ ይመር (ከመከም)፣ማሪቱ ለገሰ እና ከሌሎች አንጋፋ ሙዚቀኞች ጋር ሰርቷል፡፡

ፍስሃ ከባህል ውጭ የሆነ ዘመነኛ ነገር አይማርከውም። የአነጋገር ለዛው ፍጹም ኀገርኛ ሲሆን መገኛው ደግሞ ጥበብ ባለበት ቦታ ሁሉ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የቲያትር አበርክቶ

ፍሰሃ በላይ ይማም በ1974 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት ሲገባ የተመደበው በታሪክ ትምህርት ክፍል ውስጥ ነበር። ነገር ግን የፍስሐ የነፍስ ጥሪ ህይወቱን ሙሉ ለቲያትር ጥበብ ለመስጠት ነበርና በብዙ ጥረት ወደ ቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ተዛወረ፡፡በትምህርቱ በጣም ጎበዝ ከመሆኑም ባሻገር በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ቴያትር በመድረስ ፣በማዘጋጀት እና በመተወን በርካታ ቲያትሮች በግቢው ውስጥ ብሎም በቴያትር ቤቶች ለማሳየት በቅቷል፡፡ሁለተኛ አመት ተማሪ እያለ በትርፍ ጊዜው በብሄራዊ ቴአትር ቤት የሰራተኞች መዝናኛ ክበብ ውስጥ በሂሳብ ሰራተኝነት ሰርቷል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቆ ከ1978 — 1984 ዓ.ም እዛው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፐርፎረማንስ ስኪል እና ትውፊታዊ ድራማ መምህር ሆነ፡፡ በሚያስተምርበት ጊዜም ይሁን በቴያትር ዝግጅቱ ወቅት ተዋናዮች መስለው ሳይሆን ሆነው መተወን እስኪችሉ ድረስ ብቁ ያደርጋቸው ነበር፡፡ከመምህርነቱ ባሻገር በቴያትሩ ነግሶ በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ባሉት ቴያትር ቤቶች በሙሉ ማለትም ( በሀገር ፍቅር፣በራስ ቴያትር ፣በብሄራዊ እና በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ) ቴያትር ቤቶች የእሱ 4 የተለያዩ ቲያትሮች በተመሳሳይ ቀን ይታዩ ነበር፡፡

የኢትዮጵያን ትውፊታዊ ቲያትር አፃፃፍን ለማስተማር የፍስሀ ስራዎች ከበቂ በላይ ናቸው። ከ43 በላይ ትውፊታዊ ቲያትሮችን ፅፏል፡፡ አስደማሚ ከነበረው ችሎታው መካከል ደግሞ ያለው ፈጣን እና በፈጠራ የተሞሉ ስራዎችን መስራት መቻሉ ነው፡፡ ለእይታ በቅተው ተወዳጅነትን ካገኙ ትውፊታዊ ተውኔቶቹ መካከል ደግሞ፡-

ስመኝ ስንት አየሁ፣ አልቃሽና ዘፋኝ፣ ሆድ ይፍጀው፣ አሻግሬ መሰረታ፣ መካሻ፣ የወፍ ጎጆ ፣ የጨረቃ ቤት፣ የሁለት እናት ልጅ፣ በግ ተራ፣ ከያንያን፣ የኪፒውድ ቀስት፣ ጅራት ይዞ ሙግት እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡አብዛኛዎቹ ስራዎቹ ባህላዊ ትውፊትን የጠበቁ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በኮሜዲ ዘውግ የሚያሳዩ ናቸው፡፡

የፍስሐ ቴአትሮች ፍፁም ኢትዮጵያዊ እና ባህላዊ ናቸው ሲባል አስገዳጅ ካልሆነ በቀር ዘመናዊ ቁሳቁስ ሳይቀር አይጠቀምም፤ በቀን ከቀን ህይወቱም ከአነጋገሩ እስከ አኗኗሩ ድረስ ለህግ እና ስነ ምግባር ትልቅ ቦታ ነበረው። ቴአትሮቹ ላይ ሀገርኛውን ስነቃልን መነሻ አድርጎ ይጠቀማል።

“ስመኝ ስንትአየሁ” ቴያትር

ከፍስሐ ዝነኛ ቲያትሮች አንዱ ስመኝ ስንትአየሁ ሲሆን አንዲት ሴት በ3 ወንዶች ስትጠየቅ የሚያሳይ ነው። ሴቶች ላይ የሚደርሠውን ጫና በማጉላት የመረጠችውን ህይወት እንዳትኖር የሚደርስባትን ተፅእኖ በግልፅ ያሳያል። በተጨማሪም በዚሁ ቴያትር ላይ ባህላዊ የሆነው የሸንጎ ስርአት ተካቶበታል። መቼቱን ገበያ ላይ ያደረገውና ባህላዊ ችሎት ለተመልካች ሀሳብ እና አሰተያየት ክፍት በማድረግ ተመልካቹ እየተሳተፈበት የተሠራ አዲስ ሀሳብና አቀራረብ የነበረው ነው። የቋንቋ አጠቃቀሙ የገጠር ዘዬ የተከተለ ነው።

ስመኝ ስንታየሁ ቲያትር ከአፍሪካ ምርጥ የቴያትር ፅሁፎች መካከል ተመርጦ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉሞ እንዲገባ ተጠይቆ የነበረ ቢሆንም ፍስሐ ግን ሌላ ቴያትሩን እንዲመርጡ እንጂ ይሄንኛውን ለመስጠት ፈቃደኝነት ሳያሳይ ቀርቷል።

“አልቃሽእና ዘፋኝ” ቴያትር

ከተፃፈ ከ40 አመታት በላይ ያስቆጠረው ይሄ ቴያትር ዘመኑን ከዋጁት የፍስሐ በላይ ስራዎች መካከል ነው። ትልቅ የፍልስፍና አውድ ያለው ይሄ ቴያትሩ በአንድ ጎጆ ሁለት ተቃራኒ ስራ ያላቸው አዝማሪና አስለቃሽ ገፀባህርያት ያሉበት ትውፊታዊ ቲያትር ነው። አስለቃሿ ጠዋት ማታ ፈጣሪዋን ሠው ግደልልኝ እና ገንዘብ ላግኝ እያለች የምትማፀን ናት፤ የአዝማሪው ምኞት ደግሞ ደስታና ተድላ ሁኖ እየዘፈነ ገንዘብ ማግኘት ነው። በዚህም የአንዱ ውድቀት ለአንዱ ህይወት መቀጠል ምክንያት ይሆናል የሚል እንዲሁም በሠዎች ልቦና ያለውን አንዱን ጥሎ የማለፍ ጉዞ ያሳያል።

አልቃሽ እና ዘፋኝ ቲያትር ፍስሐ በህይወት በነበረበት ጊዜ ራሱ የአዝማሪውን ገፀባህርይ ተላብሶ በረጅም ቁመቱ በሚስረቀረቀው ድምፁ ማሲንቆውን ይዞ በአሰደማሚ ግጥም እና ዜማ ታጅቦ ተውኖበታል። ከፍስሐ ህልፈት በኋላ ደግሞ በቲያትር ባለሙያው አዳፍሬ ብዙነህ አዘጋጅነት በብሔራዊ ቲያትር ለእይታ በቅቶ ዘመን አይሽሬነቱን አስመስክሯል።

ፍልስፍና ባህሪ

መካሻ ቴያትር ከአመታት በፊት የተፃፈ ሲሆን ከገጠር ወደ ከተሜ የመጣ ገፀባህሪ ሲሆን ከተማ መጥቶ የሚያየው ከባህል እና ስርአት የፈነገጠ ድርጊት ሁሉ የሚያበሳጨው የሚያገርመው ነበር። እሱን የሚያናድድ ድርጊት ያኔ ለማህበረሰቡ ሩቅ የነበር፤ በአሁኑ ዘመን ግን እውን የሆነ በመሆኑ ፍስሐ መጪውን ጊዜ የተነበየ የጥበብ ሠው አስብሎታል። በቲያትሩ ላይ እድሜያቸው ከ40 አመት በላይ የሆኑ አዛውንቶች ከወጣት ፍቅረኞቻቸው ጋር ሆነው ሲዝናኑ የልደት ፓርቲ ሲያዘጋጁ እና ከህግና ስርአት ያፈነገጠ እድሜያቸውን የማይመጥን ድርጊት ሲፈፅሙ የሚያሳይ ነበር።

የፍስሐን ከተሜነትን መጠየፍ ሀገርን እና ባህልን የማግዘፍ ባህሪ ለጥበብ የተሠጠ መሆኑም ጭምር በአኗኗሩ ውስጥ ይገለፅ ነበር። የከተማ ግርግር ጥሎ ማለፍ አሰመሳይነት ምቾቱን የሚነሱት ነገሮች ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ የእሱ ባህሪ የዋህነት፣ ቅንነት፣ ታማኝነት ናቸው። በወሎ የአነጋነር ለዛው በተቃኘው አንደበቱ ሲያወራ አፍ ያስከፍታል ።ለቤቱ አንድ መቀመጫ ቀይ ሶፋ ቢገዛም እሱ ግን የሚቀመጠው ፍራሽ ላይ ነበር። ድንገት በእንግድነት አልያም ድግስ ተጠርቶ እንጀራ በቁርጥ ቢያቀርቡለት አይበላም ምክንያቱ ደግሞ ስስት የማያውቀው እጁ ከአንድ እንጀራ ያነሠ ለሠው ሲሰጥ አይቶ አያውቅም።

ሲከፋው ክራር እየደረደረ እያንጎራጎረ ያለቅሳል ሲለው ደግሞ ቼ በለው እያለ ይፎክራል። በመንገዱ ላይ ሀዘንተኞች በሙሾ አውራጆች ታጅበው ሲሄዱ ካየ በፍፁም አልፎ አይሄድም፤ ይልቁንም ቆም ብሎ ግጥማቸውን ያዳምጣል። ለጓደኝነት እና ለቤተሠብ ትልቅ ፍቅር እና ቦታ ይሰጣል። አንድ ጊዜ ጓደኛው ለማግባት አሰቦ የገንዘብ ችግር ያጋጥመዋል ፍስሃ አልቃሽ እና ዘፋኝ ቴያትርን አበረከተለት እና በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ተዘዋውሮ አሳይቶ ገቢውን ለሠርጉ አዋለ።

ሁለገቡ ከያኒ ፍስሐ በላይ ይማም ዘመኑን ሁሉ ለጥበብ እና ለቤተሠቦቹ የሠጠ በለጋስነት የኖረ ነገር ግን ለራሱ ያልኖረ በመሆኑም አላገባም አልወለደም። ከአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ መምህርነቱ በራሱ ፈቃድ ከለቀቀ በኋላ ባደረበት ህመም በአዲስ አበባ እና በትውልድ ከተማው ደሴ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በሀምሌ 24ቀን 1992ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።

ምስክርነቶች

ፍስሃን በህይወት እያለ የሚያውቁት ሁሉ ስለ ገር ወሎዬነቱ፣ ጀግና የትውፊት ቴአትሮች ጸሐፊ ተዋናይና አዘጋጅነቱ፣ ስለ ድንቅ መምህርነቱ በአንድ ድምጽ ይመሰክሩለታል። ደግሞ ለእነሱ ብቻ በገጠላቸው መልክ ወይም ሌሎች ባላዩት ብቃቱ በተናጠል ያሞካሹታል።

ገነት አጥላው የተባለች ጓደኛው ስለጥበብ ሰውነቱ ከመሰከረች በኋላ ስለሰዓሊነቱ እና ስለባህል ህክምና አዋቂነቱ ትናገራለች። አልቃሽና ዘፋኝ የተሰኘ ቴአትሩን ለማሳየት ወደ ክፍለ ሃገር ከሄዱ በኋላ ለቴአትሩ አስፈላጊ የነበረ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስዕል በመጉደሉ ፍሰሃ እርሳስና ነጭ ወረቀት ይዞ ስዕሉን በፍጥነት የማድረሱን ታሪክ ስለሰዓሊነቱ እማኝ እንዲሆናት ትጠቅሳለች።

ስለቁመተ መለሎነቱ፣ ስለባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ሰሪና ተጫዋችነቱ ሁሉም ይስማማል። የቀድሞ ተማሪው እና በኋላ አልቃሽና ዘፋኝ ቴአትሩን ያዘጋጀለት አዳፍሬ ብዙነህም ፍሰሃን እርሱ በገባው ልክ ይገልጠዋል። በመምህርነቱ ከፍ ያለ ተፅእኖን በእርሱና በብዙዎች ላይ ማሳደሩን አይረሳም። ጽፎ ባዘጋጃቸው የትኞቹም ቴአትሮቹ ላይ ሶፋ፣ ስልክ እና ሌሎች ከተማ ቀመስ ቁሳቁሶች ዝር አለማለታቸውን ታዝቧል።

ሌላኛው የጥበብ አጋሩ ሃይሉ ጸጋዬ ስለፍሰሃ ማውራት የሚጀምረው ስለመጀመሪያ ቀን ትውውቃቸው አንስቶ ነው። በ1974 ዓ.ም የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያሉ ከጎረቤት ዶርም የተሰማውን የክራር ድምፅ ተከትሎ ሲሄድ ነበር ፍሰሃን ከነመሳሪያው ያገኘው። ሃይሉ ፍሰሃን “ከጥበብ ሰማይ ላይ ድንገት ያጣበው ኮኮብ” ሲል ይገልጸዋል። መድረክ ላይ ሲተውን ድንገቴ ፈጠራ(ኢፕሮቫይዜሽን) ላይ የነበረውን አቅም ለመግለጽም የድንገቴ ፈጠራ ንጉስ ነበር ይለዋል።

ሌላኛው ወዳጁ ተስፋዬ ማሞም በፍሰሃ የጥበብ ሰውነት ይስማማል። ጀግና ፈረስ ጋላቢነቱንም ታዝቧል፤ የባህል ሰው ሳይሆን ራሱ ባህል ነው ብሎ ያሞካሸዋል። የፍስሃን ህልፈት ሲሰማ ወሎ ውስጥ አንድ የጥበብ ጎተራ እንደጠፋ ቆጠርኩ ይላል። ከፍሰሃ በኋላ እርሱን ሊተካ የሚችል ሰው አለመገኘቱ እንደሚያስቆጨውም ይናገራል።

ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ወርቁ ደግሞ ጎበዝ ተመራማሪነቱ ይበልጥባቸዋል። የወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን እንዲህ እንዲታወቅ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የፍሰሃ ጥናትና ምርምሮች እንደሚገኙበት ይጠቅሳሉ። ለዚህ የኪነት ቡድን ያበረከተውን አስተዋፅኦ ከ እስከ ተብሎ የሚተመን አይደለምም ይላሉ። ከጎበዝ ተመራማሪነቱ ባሻገር ጎበዝ የኮስቹዩም ዲዛይነርም እንደነበር ያስታውሳሉ።

ፍሰሃን የሚያውቁት ሁሉ ስለ ጥበብ ሰውነቱ ብቻ ሳይሆን ስለፍፃሜውም እኩል ያዝናሉ። ጸብና ጥል አለመውደዱን በአንድ ድምጽ ይመሰክራሉ፤ ጥል ሲገጥመው ደግሞ ትቶ ዘወር ማለትን እንደሚመርጥ አይተዋል። በተለይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የወጣበትን መንገድ ያነሳሉ። ሃይሉ ጸጋዬ ይህ ባህሪውን እንደማይወድለት ይናገራል። ጥሎ ከሚሸሽ ዞሮ መማታት ቢችል ብዬ እመኛለሁም ይላል።