ፊታውራሪ ምዑዝ በየነ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

ፊታውራሪ ምዑዝ በየነ

ፊታውራሪው የአጼ ዮሐንስ አራተኛ ቤተሰብ ናቸው!

ፊታውራሪ ክቡር ምዑዝ በየነ ተድላ የፓርላማ የሕግ መምሪያ አባል እና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የሕግ መወሰኛ አባል እና ምክትል አፈ ጉባኤ እንዲሁም የግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ልዩ አማካሪ በመሆን በተለያዩ ኃላፊነቶች ሀገራቸውን ያገለገሉ የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን ቤተሰቦቻቸው ለDW ገልፀዋል። ከአባታቸው ደጃዝማች በየነ ተድላ እና ከእናታቸው ወይዘሮ አበባ ሓጎስ በ1911ዓ/ም በቀድሞው የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ክልተ አውላዕሎ አውራጃ ወንበርታ ወረዳ የተወለዱት ፊታውራሪ ክቡር ምዑዝ በየነ ተድላ ፤ሀገራቸው ኢትዮጵያን በተለያዩ የአስተዳደር ዘርፎች በታማኝነት አገልግለዋል።

  • በ1949 ዓ/ም በያኔው ስማቸው ልጅ ምዑዝ በየነ በምርጫ ተወዳድረው በማሸነፍ የፓርላማ አባል ሆነው ሰርተዋል።
  • ከ1950 -1953 ዓ/ም ደግሞ የቀኝአዝማችነት ሹመት አግኝተው አውራጃ ገዢ በመሆን አገልግለዋል።
  • በ1960 ዓ/ም የሕግ መወሰኛ አባል ሆነው ተሹመዋል።

ፊታውራሪ ክቡር ምዑዝ የክልተ አውላዕሎ እና የአጋመ አውራጃዎች አስተዳዳሪ ሆነውም ሰርተዋል። የፓርላማ የሕግ መምሪያ አባል እና ምክትል ፕሬዚዳንት የህግ መወሰኛ አባል እና ምክትል አፈ ጉባኤ እንዲሁም የግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ልዩ አማካሪ በመሆን አገልግለዋል። ሐምሌ 25 ቀን 2015 በተወለዱ በ104 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ቤተሰቦቻቸው ለDW ገልፀዋል። የቀብር ሥነ ስርዓታቸውም ብፁዓን ሊቃነ ጳጻሳት እና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ዛሬ ሐምሌ 29 ቀን 2015 ዓ/ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

“ሽበት ከልጅነቴ ነው”

ረጅሙ ሰው – ፊታውራሪ ምዑዝ በየነ ተድላ ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ሆቴል ነበር የተዋወቅነው፡፡ ሲያወሩ ረጋ ብለው፣ ሲያስተውሉ አተኩረው ነው፡፡ ብስለት ፣እውቀት፣ ክህሎት ከፊታቸው ይነበባል፡፡ ሰውየው በ1948 ዓ.ም በነበረው ሃገራዊ እንደራሴዎች ምርጫ ክልተ አውላዕሎ አውራጅን ወክለው የፓርላማ አባል ከመሆናቸውም በጠጨማሪ በዘውዳዊው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕረዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡

ጨዋታቸው በአንድ ቀን የሚልያልቅ አልነበረም፤ ሌላ ቀን ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘን ተለያየን፡፡ ሁለተኛው የመገናኛ ቦታችን መኖርያ ቤታቸው ሆነ፡፡ በነገራችን ላይ አያታቸው እንዳያምጹ በሚል እንደ ግዞት ወደ አዲስ አበባ ሄደው ይኖሩ የነበረው በአሁኑ ጊዜ ሳር ቤት አካባቢ ነበር፡፡ የፊታውራሪ ምዑዝም መኖርያ ቤታቸውን የሠሩት ከቫቲካን ኤምባሲ ጀርባ በሚገኝ ቦታ ሲሆን ከአያታቸው በውርስ ያገኙት ነው፡፡ ከቫቲካን በር ወደ ቤት የሚወስደኝ ሰው አዘጋጅተው ነበር የተቀበሉኝ፡፡ ቀኑን ሙሉ የህይወታቸውንና የሥራቸውን ዘመን ሁሉ አጫወቱኝ፡፡ ፊታውራሪው የአጼ ዮሐንስ አራተኛ ቤተሰብ እንደመሆናቸው ከአያት ቅድመአያታቸው በአስተዳዳሪነት የዘለቁ ናቸው፡፡ ፊታውራሪ ምዑዝ በየነም የክልተአውላዕሎ አስተዳዳሪነትን ጨምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሰው ናቸው፡፡ ዮሓና ሀይሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *