ጸሀፌ-ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ማናቸው?

አክሊሉ ሀብተወልድ ፣ መጋቢት 5 1904 የዛሬ 111 አመት ተወለዱ፡፡ እርሳቸው ከመወለዳቸው 12 ቀን በፊት ማለትም የካቲት 23 1904 የአራዳ ጊዮርጊስ የህንጻ ስራ ተፈጽሞ በአሉ በልዩ ሁኔታ ተከበረ፡፡ በአቤቶ ኢያሱ ዘመን ወደዚህ ምድር የመጡት አክሊሉ የሰገሌ ጦርነት ጊዜ የ5 አመት ልጅ ነበሩ፡፡ አቤቶ ኢያሱ በዘመናቸው 5ቱን ደንቦች ባሻሻሉበት አመተምህረት የተወለዱት አክሊሉ የአማርኛ ትምህርታቸውን በራጉኤል ቤተ-ክርስቲያን አጠናቅቀዋል፡፡

አክሊሉ ሀብተ-ወልድ የተወለዱት ከአዲስ አበባ 35 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው በቢሾፍቱ ወረዳ ‹‹ ደንቢ›› በተባለች ቀበሌ ነበር፡፡

አክሊሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ፈጽመው ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ፈረንጅ ሀገር እስከተላኩበት ድረስ ወንድማቸው መኮንን ሀብተወልድ ቤት በኖሩበት በ8 አመታት ውስጥ ‹‹ ምክር መስጫ›› የተባለ ፕሮግራም ይዘጋጅላቸው ነበር፡፡

አክሊሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በግብጽ ሀገር በሚገኘው የፈረንሳይ ሊሴ ትምህርት ቤት ከተማሩ በኋላ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ ፓሪስ ሄዱ፡፡ በፓሪስ ዝነኛ በሆነው የሶርቦን ዩኒቨርሲቲ በህግ በኤል ዔል ቢ ተመረቁ፡፡

በሊግ ኦፍ ኔሽን የኢትዮጵያ ዋና ጸሀፊ

አክሊሉ ፈረንሳይ ሀገር በመማር ላይ ሳሉ የሀገር ፍቅር ስሜታቸው ከስሜት ባለፈ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ሀገራችን ጥንታዊ ሀገር መሆኗን ፣ ነጻነቷንም ጠብቃ ማቆየቷን ያውቁ ነበር፡፡ ይህንኑ ለሚያገኙት ሁሉ ያስረዱና ይናገሩ ነበር፡፡ ጃንሆይም ይህን የአክሊሉን የወጣትነት ጥረት በወጉ ካጤኑ በኋላ በጄኔቭ የኢትዮጵያ ዴሊጌሽን ዋና ጸሀፊ አደረጓቸው፡፡ በመቀጠልም አክሊሉ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ በፕሬስ አታሼነት መስራት ጀመሩ፡፡

አክሊሉ ከእንግሊዞች ጋር የገጠሙት ግብግብ

ቀድሞውኑ በሀገር ጉዳይ ድርድር የማያውቁት አክሊሉ ለፈረንጅ የሚገዛ ልብ አልነበራቸውም፡፡ ከፈረንሳይ ጥልቅ የህግ እውቀት ቢቀስሙም በሀገራቸው የመጣን ግን እንዲህ እንደዋዛ አይመለከቱትም ፡፡ ይህን የሀገር ፍቅር ስሜት ደግሞ ከባለውለታቸውና ታላቅ ወንድማቸው ከመኮንን ሀብተ-ወልድ የወሰዱት ነበር፡፡ ከ1934 በኋላ ባንክ በሀገራችን በዘመናዊ መልክ ሲመሰረት እንግሊዞች እጃቸው ነበረበት፡፡ በተለይ ብሄራዊ ባንክ ሲመሰረት እንግሊዞች ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ቁጥጥር ስር የማድረግ ግብ ነበራቸው፡፡ እንዲህም ሲባል ዋና ጽህፈት ቤቱን እንግሊዝ፣ የቦርድ ሀላፊዋን ደግሞ የእንግሊዝ ንግስት የማድረግ ግብ ነበር የእንግሊዝ ዋና ፍላጎት፡፡ የባንኩ ዋና ጽህፈት ቤትና የባንኩ የቦርድ አባላት በሀገራችን ሰዎች በኢትዮጵያውያን እንዲሆን ያስደረጉት አክሊሉ ነበሩ፡፡

የተባበሩት መንግስታትና አክሊሉ

አክሊሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተመሰረተ፡፡ በዛን ጊዜ የ34 አመት ሰው የነበሩት አክሊሉ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር አንድ ላይ ሆነው ወደ ሳንፍራንሲስኮ አቅንተው ነበር፡፡

አክሊሉ በዚህ ጉባኤ ላይ አንድ ሀሳብ ያቀርባሉ፡፡ይህም የሴኩሪቲ ካውንስልን የሚመለከት ነበር፡፡ አንድ አገር ጥቃት ሊደርስብን ይችላል ብሎ ቅሬታ ቢያቀርብ ሴኩሪቲ ካውንስል መሰብሰብ አለበት ሲሉ አክሊሉ በጉባኤው ላይ ሀሳብ ያነሳሉ፡፡ይህ ሀሳብ ግን በአሜሪካኖቹ ተቀባይነት አልነበረውም፡

One thought on “ጸሀፌ-ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ማናቸው?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *