ጥበቡ በለጠ

ጥበቡ በለጠ

ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በፊልም ፤ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እናስተዋውቃለን፡፡ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ በ5 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ አሁን የምናስከትለው ከሚድያ ዘርፍ ይሆናል፡፡ ታሪኩ የሚቀርብለትም ሰው ጥበቡ በለጠ ነው፡፡

ጥበቡ በለጠ፣ የተወለደው በአሁኑ ኦሮሚያ ክልል በክብረ-መንግስት ከተማ /አዶላ/ ውስጥ ነው። የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን በትውልድ አካባቢው እና በአዲስ አበባ ከተማ ተከታትሏል። ከልጅነቱ ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የጋዜጠኝነት ሙያ ፍላጎት ስለነበረው በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና በልዩ ልዩ ብዙሐን መገናኛዎች ውስጥ ሲሳተፍ ቆይቷል። የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን ሲያጠናቅቅ፣ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በስነጽሐሁፍ የመጀመሪያ ድግሪውን አግኝቷል። ከዚያም በዶክመንተሪ ሊንጉስቲክስ & ካልቸር ማስተርስ ዲግሪ አግኝቷል። ከዩኒቨርሲቲም ከተመረቀ በኋላ በአዲስ ብሮድካስቲንግ ኩባንያ የጋዜጣ እና የሬዲዮ ጋዜጠኛ በመሆን ስራ ጀመረ። አዲስ ዜና የተባለን ጋዜጣም ከአዘጋጆቹ አንዱ ነበር። በስራ ገበታውም እያለ የውጭ አገር የትምሕርት እድሎችን አግኝቶ የሬዲዮ ጋዜጠኝነትን በደቡብ አፍሪካ እና በጀርመን አገራት ተምሯል።

የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ በሐገራችን በተነሳ አለመረጋጋት የሚዲያ ተቋሙ ሲዘጋ፣ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር አዲስ ጥበብ እና ባሕል የተሰኘ ኩባንያ ከፍተው የተለያዩ አለማቀፍ ዘጋቢ ፊልሞችን ሠርቷል። ከነዚህም ውስጥ ስለ ቅዱስ ላሊበላ ታሪክ እና ኪነሕንጻ የሚዘክረውን ዶክመንተሪ ሠርቷል። ፊልሙ በ2000 ዓ.ም ለንደን ብሪትሽ ሙዚየም ውስጥ Best African Documentry በሚል ተመርጧል።
– ሁለተኛው ፊልም የጎንደርን ታሪክና ኪነሕንጻዎቿን የሚዘክር Gonder an African Civilization የተሰኘ ዶክመንተሪ ሰርቶ በልዩ ልዩ አገራት ታላላቅ መድረኮች ላይ አሳይቷል።
– ሶስተኛው ዶክመንተሪ በሐረር ከተማ እና በውስጥዋ ለማዳ ሆነው በሚኖሩት ጅቦች ላይ መሠረት ያደረገው ፊልሙ ነው።
– አራተኛው ስለ አክሱም ታሪክና ጥንታዊ ስልጣኔ የሠራው ዶክመንተሪ ነው።
– አምስተኛው ዶክመንተሪው በዑጋንዳ፣ በኬኒያ፣ በታንዛኒያ እና በኢትዮጵያ በመዘዋወር፣ ጥናትና ምርምር በማድረግ በከፍተኛ ማሕበራዊ ቀውስ ውስጥ ስላሉት ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ Abuse Innocence የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ሰርቷል።

በመጽሐፍ ሕትመትም

1- የፈላስፎች ጉባኤ /አጫጭር ልቦለዶች/
2- ሕይወቴ /የተመስገን ገብሬን ታሪክ/
3- Jublee የተሠኘውን የአፍሪካ ሕብረት የ50 አመታት ጉዞ ታሪክ።
4- ስለ ረጅሙ ወንዝ አባይ ላይ የተደረጉ የምሁራን የምርምር ስራዎች አሰባሳቢ፣ ብሎም አዘጋጅና አሳታሚ ሆኖ አቅርቧል።
5- የክፍሉ ታደሰን ያ ትውልድ የተኙትን ሁሉኑም መጽሐፍት አርታኢና አሳታሚ ሆኖ ሰርቷል።
በርካታ የጥናት እና የምርምር ስራዎች አሉት።
– አሁን የአሐዱ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖ እየሠራ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *