ገስጥ ተጫኔ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡
ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ደራሲ ገስጥ ተጫኔ አንዱ ናቸው፡፡ የበርካታ ልቦለድ እና ኢ-ልቦለድ ስራዎችን ለንባብ ያበቁት ደራሲ ገስጥ ተጫኔ ዛሬም ከስነጽሁፍ አልራቁም፡፡ የድርሰት እና የአርትኦት ስራቸውን በፍቅር እየሰሩ ሀገራዊ አደራቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ የደራሲ ገስጥ ተጫኔን ታሪክ እዝራ እጅጉ ሰንዶታል፡፡
ገስጥ ተጫኔ ከዱ
በሰሜን ሸዋ፣ እንሣሮ ወረዳ፣ ለሚ ከተማ በ1942 ዓ.ም ተወለደ፡፡ አባቱ ተጫኔ ከዱ፤ እናቱ አልማዝ ለማ ይባላሉ፡፡ ለወላጆቹ ሁለተኛ ልጅ ነው፡፡ ገስጥ፣ ለሚ ከተማ ቢወለድም አላደገበትም፡፡ አባቱ ወታደር ስለነበሩ ከእናቱ ጋር ወስደውት ያʼደገው ደብደረ ብርሃን፣ ጠባሴ ጦር ሠፈር ውስጥ ነው፡፡ በጦሩ ‹‹ንስሐ አባት›› ቄስ የ፲ አለቃ ከበደ አማካይነት እዚያው ጦር ሠፈሩ ውስጥ ፊደል ቆጠረ፡፡
ወንጌል ንባብ ጨርሶ ዳዊት ደገማ ሊጀምር እንደተሰናዳ፣ ከጓደኛው ጋር ስለተጣላ መምሬ ከበደ ክፉኛ ገረፉት፡፡ እንደ ትንሽ ልጅ አልቅሶ ዝም አላለም፡፡ አድልዎ የአደረጉ ስለመሰለው ተቀየማቸው፡፡ የቄስ ትምህርቱን ትቶ ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት (አፄ ዘርዓ ያዕቆብ አንደኛ ደረጃ) ሄደና አንደኛ ክፍል ገባ፡፡ ይሁን እንጂ ትምህርት ቤት የገባው ለሦስተኛው ‹‹ተርም›› የፈተና ጊዜ ሁለት ወር እንደቀረው ነበር፡፡ ስለዚህ በአዲሱ ዓመት የትምህርት ዘመን ወደ ቀጣዩ ክፍል መዛወር አልቻለም፡፡
በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ትምህርት ቤት አንድ ዓመት እንደተማረ፣ የአባቱ ታናሽ ወንድም ከበርሁ ከዱ ወንድማቸውን (የገስጥን አባት) ሊያዩ ደብረ ብርሃን ሄዱ፡፡ ምሽት ላይ ሲጨዋወቱ ‹‹ሥራ ውዬ ስገባ እሚያጫውተኝ ልጅ የለኝም፤ እባክህ አንድ ልጅ ስጠኝ?›› ብለው ጠየቁ፡፡ በዚያን ጊዜ ሁለቱ እህቶቹ ከአያቶቻቸው ዘንድ (ከለሚ) ወደ ደብረ ብርሃን መጥተው እና ከሕፃን ወንድሙ ጋር አራት ነበሩ፡፡
የገስጥ አባት ልጆቻቸው እንዲለዩአቸው አይፈልጉም ነበርና የወንድማቸውን ጥያቄ በዝምታ ተቃወሙ፡፡ በዚህ ጊዜ ከበርሁ ከፋቸው፡፡ ‹‹አንተን አምላክ የልጅ ፀጋ ሰጠህና መኩራትህ ነው?›› በማለት በቀየሜታ ተናገሩ፡፡ የገስጥ አባት ወንድማቸውን ማስቀየም ስለከበዳቸው ‹‹ወንድሜ ከሚከፋህ ገስጥን ውሰድ፤ ግን አደራህን….›› በማለት ገስጥ ከአጎቱ ጋር እንዲኖር ፈቀዱ፡፡ ይሁን እንጂ ወዲያው ከአጎቱ ጋር ወደ አዲስ አበባ አልተጓዘም ነበር፡፡ ክረምቱ እንደገባ የእናቱ ዘመድ በሚያሽከረክሯት የወታደር ጂፕ መኪና ከእናቱ ጋር ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡
በአጎቱ ቤት መልካም አቀባበል ተደረገለት፡፡ በተለያዩ መልካም አጋጣሚዎች የአጎቱን ቤት ወደደው፡፡ እናም በዚህ ሁኔታ ገስጥ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሆነ፡፡አጎቱ ይኖሩ የነበሩት በላም በረት በኩል ቁልቁል ወርዶ በሚገኝ በወቅቱ ለአዲስ አበባ ከተማ የሕንፃ ግንባታ የሚውል ድንጋይና ጠጠር በማምረት በሚታወቀውና በተለምዶ ‹‹ኮተቤ ካባ›› እየተባለ ይጠራ በነበረው፣ የአዲስ አበባ ዳርቻ ነበር፡፡ አጎቱ በሆቴል ንግድና ቁም ባሕር ዛፍ እየገዙ አጣና በመሸጥ ይተዳደሩ ስለነበር በወቅቱ ገንዘባምና የተከበሩ ሰው ነበሩ፡፡ እርሱ በማያውቀው ምክንያት አጎቱ በዚያ ሰፈር ‹‹አበበ ከበደ›› እየተባሉ ነበር የሚጠሩት፡፡
በ1950 ዓ.ም መስከረም፣ አጎቱ ወደ ደጃዝማች ወንድራድ ትምህርት ቤት ወስደው አስመዘገቡት፡፡ የአባቱን ስም በእርሳቸው ስም ለውጠው ‹‹ገስጥ አበበ›› ብለው በማስመዝገባቸው ከፍቶት ሲያለቅስ ዋለ፡፡ ያለቀሰው በዚህ ብቻ አልነበረም፤ የደብረ ብርሃኑን አንደኛ ክፍል ትምህርቱን ስለአልተቀበሉትና ‹‹ማዘጋጃ›› እሚባል ክፍል ስለአስገቡት ነበር፡፡ የማዘጋጃው ክፍል ወለሉ አዋራ፣ ግድግዳው ሠጠራ ከመሆኑ በቀር፣ ትምህርቱ ለእሱ ቀላል ስለነበር ከመንፈቅ በኋላ ወደ አንደኛ ክፍል ተዛወረ፡፡
በአዲስ አበባ ኑሮው የአገኘው ደስታ ከስድስት ወራት በላይ አልቆየም፡፡ ቀስ በቀስ የአጎቱ ቤት ሲዖል እየሆነበት መጣ፡፡ የአጎቱ ሚስት ከዕድሜው ጋር የማይመጣጠን ሥራ ያሠሩት ጀመር፡፡ ንፅሕናው የማይጠበቅ፣ ጭቅቅታምና በአልጠፋ እህል ረኀብተኛ ሆነ፡፡ አጎቱ ደግና ገር ሰው ቢሆኑም፣ ይህንን ስቃዩን ማስተዋል አልቻሉም፡፡ ወላጆቹም ለምን መጥተው እንደማያዩት በልጅነት አዕምሮው መብሰልሰሉ አልቀረም፡፡ የስቃይ ሕይወት እየገፋ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ወደ ሁለተኛ ክፍል ቢዛወርም፣ ሁሉም ነገር ከጫፉ ደረሰ፤ ኑሮ አንገፈገፈው፡፡ ስለዚህ ጠፍቶ ወደ ወላጆቹ ለመሄድ ወሰነ፡፡ ያንዬ የአሥር ዓመት ልጅ ነበር፡፡
ወደ አዲስ አበባ በመኪና ስለመጣ፣ አጎቱ ቤት የደረሰው ግማሽ ቀን በአልሞላ ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ መጥፋት ሲያስብም አስፋልቱን መንገድ ተከትሎ ቢገሠግሥ፣ ወላጆቹ ዘንድ በአንድ ቀን የሚደርስ መሰለው፡፡ ስለዚህ በመስከረም ወር ማለቂያ ላይ ትምህርት ቤት የሚሄድ መስሎ በማለዳ ተነስቶ ጉዞውን ወደ ደብረ ብርሃን ጀመረ፡፡ መንገዱን ይዞ ሮጠ፤ መከራ ከኋላው ተከትሎ እያባረረው ስለመሰለው ሲደክመው እያረፈ ሮጠ፡፡ አሌልቱ ከተማ እንደ ደረሰ ራበው፡፡ ሁለት አዳዲስ ደብተሮች ስለነበሩት በአሥር ሳንቲም ሸጣቸውና ዳቦ ገዝቶ በላ፤ ውሃ ለምኖ ጠጣ፡፡ ከዚያም ግሥጋሤውን ቀጥሎ ከምሽቱ 12 ሰዓት ግድም ሸኖ ከተማ ደረሰ፡፡
‹‹አንድ ሙሉ ሰው በቀን መጓዝ የሚችለው በአማካይ 30 ኪ.ሜ ነው›› ይባላል፡፡ እርሱ ግን በልጅ አቅሙ 70 ኪ.ሜ. ያህል ተጓዘ፡፡ ከዚህ በኋላ እሚገባበት አልነበረውምና ግራ ገብቶት ከጎዳናው ዳር ቆመ፡፡ ሁኔታውን ያስተዋለ አንድ ሰው ‹‹አንቺ ልጅ ከቤተሰብሽ ጠፍተሸ ነው?›› አለው፡፡ ጭንቀቱን የሚካፈለው ያገኘ መስሎት ሳያቅማማ ሁሉንም ነገረው፡፡ ሰውዬው ‹‹ነይ ተከተዪኝ›› አለውና ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰደው፡፡ ከዚያም ‹‹ከቤተሰቡ የጠፋ ልጅ አግኝቻለሁ›› ብሎ አመለከተ፡፡ በዚህ ጊዜ ገስጥ፣ አጠገቡ መብረቅ የወደቀ ያህል ደነገጠ፡፡ ምክንያቱም ፖሊሱ በውዴታም ሆነ በግድ አስለፍልፎ ከየት እንደመጣ ከአወቀ በኋላ ወደ አጎቱ ቤት እንዲመለስ ያደርጋልና ነው፡፡
ፖሊሱ ‹‹ማሳደሪያ ቦታ ስለሌለ አንተ ዘንድ አሳድረውና ጧት አምጣው›› አለው፡፡ ከዚህ በኋላ ሰውየው በየሱቁ እያዞረ ‹‹የጠፋ ልጅ አግኝቼ እራቱን እማበላበት…..›› እያለ ገንዘብ ሲለምንበት አመሸ፡፡ አሥር ብር ያህል እንደአገኘ ገስጥ ታዝቧል፡፡ ሆኖም ለእራቱ አንድ ስንዴ እንጀራ ያለወጥ ነበር የገዛለት፡፡ ሰውዬው ይህንን በማደረጉ አልተቀየመውም፡፡ ይልቁንም በዚያ ሁኔታው ‹‹ትልቅ ውለታ ውሎልኛል›› ብሎ አምኗል፡፡
ሌሊት ላይ ሰውዬው ‹‹አንቺ ልጅ፣ ጠዋት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ብወስድሽ ወደ አጎትሽ ይመልሱሻል፡፡ ወደ ወላጆችሽ መሄድ ከፈለግሽ ጠፋችብኝ እላለሁ፤ አንቺ ማልደሽ ተነሽና መንገድሽን ቀጥዪ›› አለው፡፡ ገስጥ ሰውዬው እንደአለው በማግሥቱ ጠዋት ተነስቶ ጉዞውን ለመቀጠል ቢሞክርም እግሩ አብጦ አላራምድ ስላለው፣ መሄድ የቻለው ከአደረበት ቤት እስከ መኪና መንገዱ ብቻ ነበር፡፡
መንገዱ ዳር እንደ ተቀመጠ፣ እኩለ ቀን ላይ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ብርሃን የሚሄድ አውቶቡስ አገኘ፡፡ ሾፌሩን ለምኖ ፈቀደለትና ከቀኑ 9 ሰዓት ግድም ደብረ ብርሃን (ጠባሴ) ወላጆቹ ቤት ገባ፡፡ ያ ይሳሱለት የነበረ ልጃቸው እንደዚያ ተሽመድምዶና ተጎሳቁሎ ሲያዩት በሐዘንና በፀፀት አነቡ፡፡
ገስጥ ስለአጎቱ ሲናገር ‹‹….እኔ ትቼው ወደ ወላጆቼ ብመለስም አጎቴ ልጅ እንደ አማረው አልቀረም፡፡ የኋላ ኋላ ሌላ ሚስት አግብቶ የብዙ ልጆች አባት ለመሆን በቅቷል…›› ብሏል፡፡
ከአዲስ አበባ እስከ ሸኖ በእግሩ በአደረገው ጉዞ ምክንያት የያዘው ጣመን ከሁለት ወር በላይ አስተኛው፡፡ በቅጡ ከአገገመ በኋላ፣ በ1952 ዓ.ም አጋማሽ ግድም እንደ ገና አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ትምህርት ቤት ገብቶ ከሦስተኛ ክፍል ትምህርቱን ጀመረና እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ተማረ፡፡ መለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም እዚያው ደብረ ብርሃን ኃይለ ማርያም ማሞ ትምህርት ቤት ቀጥሎ እያለ በ1959 ዓ.ም አጋማሽ ወደ ውትድርና ዓለም አምርቶ የአየር ወለድ ጦር አባል ሆነ፡፡
አንዳንድ ጊዜ፣ የአካባቢ ሁኔታ በወደ-ፊት ሕይወት፤ ወይም አኗኗር ላይ ተፅዕኖ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በገስጥ ላይ የደረሰውም ይኸው ነበር፡፡ በጦር ሠፈር ውስጥ አደገ፤ የውትድርና ሕይወት ማረከው፤ እናም ወታደር ሆነ፡፡ እርሱ እንደሚለው ‹‹…በአደግሁበት ጦር ሠፈር ውስጥ ሁል ጊዜ እማየው ውትድርና፣ ሲነገር እምሰማው ስለውትድርና፣ ለአገርና ለባንዲራ ክብር ስለመሞት፣ ስለመተሳ ሰብና ስለመከባበር ወዘተ… ነበር፡፡ ይኸ ሁሉ ወደ ውስጤ እየሠረፀ አደግሁ…
‹‹…በየሳምንቱ ሐሙስ ከቀትር በኋላ የባንዲራ አከባበር ሥነ ሥርዓት ነበረ፡፡ ወታደሮች ጠብመንጃ ይዘው፣ በሙዚቀኞች ታጅበው፣ በሠንደቅ ዓላማው ዙሪያ ይሠለፉና ሥነ ሥርዓቱ ይጀመራል፡፡ በተቃራኒው ወገን የወታደር ልጆች እንኮለኮልና እናያለን፡፡ የአርበኞችን ተጋድሎ የሚዘክረው መዝሙር በሙዚቀኞቹ ይዜማል፡፡ በወታደሮቹ የብረት ሠላምታ ባንዲራው በሥርዓት ይወርዳል፡፡ ስሜትን እሚስብ ትዕይንት ነበረው….
‹‹….እኔና ጓደኞቼ፣ ወታደሮቹ የውጊያ ስልት ሲማሩ እናያለን፣ የውጊያ ስልት መማሪያ ሲኒማ ሲመለከቱ አብረን እንታደማለን፤ በማግስቱ በቡድን ተከፋፍለን በሲኒማው ያየነውን ሜዳ ላይ እንጫወተዋለን፡፡ እሚቃወመን አልነበረም፡፡ እንደሚመስለኝ በዚህ ተቀርፀን እንድናድግና ዝንባሌያችን ወደ ውትድርና እንዲሆን የአባቶቻችን አለቆች ፍላጎት ሳይሆን አይቀርም፡፡ እንግዲህ በዚህ ውስጥ ስለአደግሁ ወታደር መሆን ውሳኔዬ ሆነ፡፡ወድጄውና አምኜበት ስለገባሁበትም የተሰጠኝን ግዳጅ እማከናውነው ከልቤ ነበር፡፡
በዚህም ምክንያት ገና የሃያ ሁለት ዓመት ወጣት እንደአለሁ ʻየቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጦር ሜዳ ጀግና ሜዳይ ባለ ዘንባባʼ ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ ለመቀበል በቃሁ፡፡ ይህ እንደ አንድ ወታደር ለሀገሬ ላʼደርገው እሚገባኝን የፈጸምሁ መሆኔን የአረጋገጥሁበት በመሆኑ፣ ለʼኔ አኩሪና ታላቅ ስኬት ነበር….›› በማለት ወደ ውትድርና ዓለም የሳበውን አጋጣሚ እና ከገባም በኋላ የአገኘውን ስኬት ገልጿል፡፡ የሥነ ጽሑፍ ተሰጥዖው ብቅ ሊል የቻለው፣ ከልጅነቱ ጀምሮ ተግቶ በማንበቡ እንደሆነ ገስጥ ይናገራል፡፡ የንባብ ልምዱ መነሻ በጦር ኃይሎች ማስታወቂያ ክፍል እየታተመ ይወጣ የነበረ፣ ‹‹ወታደርና ዓላማው›› ጋዜጣ፣ በልጆች ዓምዱ ላይ ያሠፍረው የነበረ መጣጥፍ ነበር፡፡ ከጋዜጣ ንባብ አልፎ ወደ መጽሐፍ ንባብ እንዲገባና ትጉህ አንባቢም እንዲሆን የረዳው እዚያው ጠባሴ፣ በሻለቃ ጦር ውስጥ ጸሐፊ የነበረ አዕምሮ የሚባል ወታደር መሆኑን ያስታውሳል፡፡
አንድ ጊዜ ወታደር አዕምሮ፣ ‹‹የብሉይ ኪዳን ታሪክ›› የተሰኘ መጽሐፍ ‹‹አንብበው›› ብሎ አዋሰው፡፡ መጽሐፉን ወደደው፡፡ ታሪኩን በቃሉ እስከሚያነበንበው ድረስ ደጋግሞ አነበበው፡፡ ከዚያ በኋላ ሌላ መጽሐፍ እንዲያውሰው ወታደር አዕምሮን ጠየቀው፡፡ ታሪክና ምሳሌን፣ አርሙኝን፣ አርአያን፣ እንደወጣች ቀረችን፣ ገልጠን ብናየውንና ሌሎችንም ልብ ወለድና የታሪክ መጻሕፍትን ሁሉ ከሰዎች እየተዋሰ አስነበበው፡፡ የንባብ ትጋቱን በማየቱም መጽሐፍ በአገኘ ቁጥር ያውሰው ጀመር፡፡ በተጨማሪም ራሱን መግለፅ የሚያስችለውን ያህል የሥዕል ሥራ ከወታደር አዕምሮ ተማረ፡፡
በልምድ ያዳበረውን መለስተኛ የሥዕል ችሎታ፣ ቀድሞ በሠራበት የአየር ወለድ ጦር ትምህርት ክፍልና በሌሎችም አጋጣሚዎች ተጠቅሞበታል፡፡ ይህንኑ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አዛምዶ ወደ ኮምፒዩተር ‹‹ግራፊክስ›› አሸጋግሮታል፡፡ ገስጥ፣ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በነበረባቸው ዓመታት በ‹‹ቦይ ስካውት›› ክበብ ተሳታፊ ስለበር የሥነ ጽሑፍ ዝንባሌውን ለማየት ዕድል አግኝቷል፡፡ በተለይ ከስድስተኛ ክፍል በኋላ፣ አማርኛ አስተማሪዎቹ በድርሰት ደብተሩ ላይ ‹‹እጅግ በጣም ጥሩ…›› የሚል ማነቃቂያቸውን በአሠፈሩና በክፍል ውስጥ ለጓደኞቹ እንዲያነብላቸው በአደረጉ ቁጥር እየተደፋፈረ ዝንባሌውን ተከትሎ ክሂሎቱን የማሳደግ ጥረቱን ቀጠለ፡፡
የሥነ ጽሑፍ ክሂሎቱን አደባባይ ያወጣው በተውኔት ድረሰት ነበር፡፡ በአየር ወለድ ጦር ውስጥ በነበረባቸው ዓመታት በርካታ አጫጭርና ረጃጅም ተውኔቶችን ጽፏል፡፡ ከረጅሞቹ ‹‹እማዬ ማሪኝ››፣ ‹‹ጭሰኛው››፣ ‹‹የውርስ ዕቃ›› እና ‹‹እንዲህ መሆን ላይቀር›› የተባሉት ተውኔቶቹ በወቅቱ በትላልቅ ቴአትር ቤቶች ይታዩ ከነበሩት አገርኛ የተውኔት ድርሰቶች ያልተናነሱ ነበሩ፡፡ ተውኔቶቹ የደኻውን ኅብረተ ሰብ ጎስቋላ አኗኗር የሚያሳዩ፣ የአገዛዝ ሥርዓቱንና ስለአገሩ ግድ የለሽ የሆነውን የኅብረተ ሰብ ክፍል በአሽሙር የሚሄሱ ነበሩ፡፡ በእነዚህ የተውኔት ድርሰቶቹ ከአየር ወለድና ከአየር ኃይል ሠራዊት አልፎ በከተማው ማኅበረሰብ፣ በተለይም በተማሪዎች አካባቢ ተዋቂነትን አተረፈ፡፡
‹‹ጭሰኛው›› የተሰኘው ተውኔቱ በመድረክ ላይ በታየበት ዕለት፣ በወቅቱ የምድር ጦር ዋና አዛዥ የነበሩት ሌፍተናንት ጀኔራል ድረሴ ዱባለ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡ ይህ ለእርሱ (ለገስጥ) ታላቅ ክብር ነበር፡፡ ተውኔቱ ታይቶ እንዳበቃ፡፡ ጀኔራሉ ‹‹የጻፈውን እስቲ ላግኘው?›› ብለው ጠየቁ፡፡ ተጠርቶ እፊታቸው ቀረበ፡፡ ‹‹….ባʼንተ መስተዋትነት ይህ ጦር ምን እንደሚያስብ ለማየት ችያለሁ፤ ችሎታህ ጥሩ ነው፡፡ ለወደፊቱ ተንኮል የሌለበትን ጻፍ.…›› ካ’ሉት በኋላ፣ ወደ አየር ወለድ ጦር አዛዥ መለስ ብለው ‹‹የዓለም ዘውድ፣ ቁጭ አድርጎ ሲሰድብህ ዝም ብለህ ትስቃለህ…›› አሏቸው፡፡ የአነጋገር ድምፀታቸው ለገስጥ ጥሩ ቃና አልነበረውም፡፡ በዚያን ወቅት ሁለቱም ባለእርሻ ነበሩ፡፡
ኮሎኔል የዓለም ዘውድ፣ ‹‹መቼም ልጁ የታየውን ጽፏል፤ ክፉ ነገር አላየሁበትም›› ብለው በአክብሮት መልስ ሰጡ፡፡ ጀኔራሉ ‹‹ነገ ጠዋት እቢሮዬ ይዘኸው ና›› አሏቸውና ሄዱ፡፡ በማግስቱ ኮሎኔል የዓለም ዘውድ፣ ምድር ጦር አዛዡ ዘንድ አብሯቸው እንዲሄድ ገስጥን ጠየቁት፡፡ እሱ በጀኔራሉ አነጋገር ፈርቶ ነበርና አብሯቸው እንዳይሄድ ለመናቸው፡፡ ኮሎኔሉም ልመናውን ተቀብለው ትተዉት ሄዱ፡፡ ሲመለሱ ሁለት መቶ ሃምሳ ብር ይዘውለት መጡ፤ ሽልማት መሆኑ ነው፡፡ ገንዘቡ ከሁለት ወር ደመወዙ ይበልጣል፤ ሆኖም ተውኔቱን ከተወኑ ጓደኞቹ ጋር ቢራ ጠጡበት፡፡
ገስጥ፣ በተውኔት ድርሰት የሥነ ጽሑፍ ክሂሎቱን ቢያሳይም፤ መሥመሩን ወደ ዝርው ድርሰት ያስለወጡት ሦስት ዋና ዋና አጋጣሚዎች ተከስተዋል፡፡
የመጀመሪያው አጋጣሚ፣ በ‹‹ወታደርና ዓላማው›› ጋዜጣ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዩች ላይ መጻፉና በካርቱን ሥዕሎች ንቁ ተሳትፎ ማድረጉ፣ እንዲሁም በዚሁ ጋዜጣ ላይ ይካሄዱ በነበሩ የሥነ ጽሑፍ ውድድሮች ተሳታፊ እየሆነ በአሸናፊነት ለመሸለም መብቃቱ ነበር፡፡ በጅምር የቀረ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደብረ ዘይት ቢያጠናቅቅም፣ አየር ወለድ ጦር ውስጥ ሆኖ ከፍተኛ ትምህርት መቀጠል እማይቻለው ሆነ፡፡ በዚህ ምክንያት ተበሳጭቶ ወደ ተስፋ መቁረጥ አዘቀዘቀ፡፡
ሆኖም ራሱን መክሮ ከመጻሕፍት ለመማር ታጥቆ ተነሣ፡፡ ከዚያም የሙያና የቀለም ትምህርት መርጃዎችን፣ ልብ ወለድ ድርሰቶችንና የታሪክ መጻሕፍትን ማንበቡን ቀጠለ፡፡ እርሱ እንዳለው፣ ትምህርት ቤቱን መጻሕፍት ውስጥ አድርጎ፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሳይሄድ እዚያው ባለበት አዕምሮውን በዕውቀት አነፀ፡፡ ይህም ወደ ዝርው ድርሰት እንዲያዘነብል ያደረገው ሁለተኛው አጋጣሚ ነበር፡፡ ወደ ሦስተኛው አጋጣሚ፣ ከማለፋችን በፊት ወደዚህኛው አጋጣሚ ያሸጋገሩት በአገሪቱ ላይ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች መታየታቸውን እንመለከታለን፡፡ አንደኛው በወሎ አውራጃዎች በደረሰው ድርቅ ምክንያት ሕዝቡ በችጋር መርገፉ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በሠራዊቱ ውስጥ የለውጥ እንቅስቃሴ መፈጠሩ ነበር፡፡ በተለይ በጥር ወር 1966 ዓ.ም. ነገሌ የሚገኘው የ12ኛ ብርጌድ ጦር አባላት ለመላው ጦር ኃይል የአደረጉትን የአመፅ ጥሪ በመቀበል በአየር ወለድ ውስጥ የለውጥ አንቀሳቃሽ ለመሆን ልቡ አቆበቆበ፡፡ አለቆቹም በጥርጣሬ ያዩት ጀመር፡፡
በረኀብ የተጎዳውን ሕዝብ ለመርዳት የአየር ወለድ አንድ ሻምበል ጦር ወደ ወሎ እንዲዘምት ሲታዘዝ እሱም አብሮ እንዲሄድ ታዘዘ፡፡ ከሥራ ምድብ አኳያ ዘመቻው ባይመለከተዉም፣ በለውጥ አንቀሳቃሽነት መቅበጥበጡን አለቆቹ ስለአጤኑ ‹‹ጦሩን ሊያነሳሳ ይችላል›› የሚል ስጋት አድሮባቸው ከሠፈር ገለል ለማድረግ የወሰዱት ርምጃ ነበር፡፡ ዘማቹ ጦር ደሴ ገብቶ ጢጣ አረፈና እዚያ ለጥቂት ሳምንታት ቆየ፡፡ ረኀቡ በጎዳቸው የጠቅላይ ግዛቱ አውራጃዎች ከ40 በላይ ማደያ ጣቢያዎች ተቋቋሙ፡፡ ጦሩ በአንድ ቡድን አምስት እየሆነ ተመደበና በእነዚህ ጣቢያዎች ተበተነ፡፡ ገስጥም የቡድን መሪና የጣቢያ ኃላፊ ሆኖ ከ4 ወታደሮች ጋር በአውሳ አውራጃ (አፋር ውስጥ)፣ ወራንሶ እሚባል ማደያ ጣቢያ ላይ ተመደበ፡፡ ከአራቱ ወታደሮች በተጨማሪ 3 የቀይ መስቀል በጎ ፈቃድ ሠራተኞችና በተባባሪነት 4 አባላት ያሉት አንድ ፖሊስ ጣቢያ በሥሩ ነበሩ፡፡
ከደብረ ዘይት ሲነሳ ፊደል የማስተማር እቅድ ስለነበረው ደብተሮችን፣ እርሳሶችንና ጠመኔዎችን፣ ገዝቶ ተሰናድቶ ነበር፡፡ በይበልጥም የቁም ጽሕፈት ችሎታውን ተጠቅሞ ‹‹በቻርት›› ወረቀት ላይ ጥሩ የፊደል ገበታ ሠርቶ፣ እንዲሁም ለራሱ ንባብ የሚጠቅሙት መጻሕፍትን ይዞ ነበር፡፡ ስለዚህ ወራንሶ በደረሰ ጥቂት ቀናት በኋላ ግድግዳዉ የእንጨት፣ ጣሪያው የዘንባባና የቁጥቋጦ ዝንጣፊ ርብራብ የሆነ ባለ አንድ ክፍል የዳስ ትምህርት ቤት በጓደኞቹ እገዛ ሠርቶ 25 ሕፃናትን ማስተማር ጀመረ፡፡ ስሙንም ‹‹ምናልባት ትምህርት ቤት›› ብሎ ሰየመው፡፡
ስለትምህርት ቤቱ ለየት ያለ ትውስታውን ሲያወጋ ‹‹…አንድ እለት ረፋድ ላይ የወሎ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ደጃዝማች ለገሰ በዙ ጣቢያውን ሊጎበኙ በሄሌኮፕተር ወራንሶ ደረሱ፡፡ እኔና ባልደረቦቼ ተቀበልናቸውና ለዕደላ የተዘጋጀውን የእህል ክምችት ከአዩና ስለዕደላው ሂደት በ’ኔ አማካይነት ከተገለፀላቸው በኋላ፣ በምናልባት ትምህርት ቤት እየተማሩ ያሉ ሕፃናትንም ጎበኙ፡፡ በዳስ ትምህርት ቤቱ ግንባር ላይ የተለጠፈውን ‘ምናልባት ትምህርት ቤት’ የሚል ጽሑፍ አንብበው ‘ምን ልትል ፈልገህ ነው?’ ብለው ጠየቁኝ፡፡ ‘ምናልባት አንድ ቀን፣ እዚህ ቦታም፣ ትምህርት ቤት ይከፈት ይሆናል’ ለማለት ነው›› አልኋቸው፡፡ እርሳቸውም በመገረም አትኩረው እያዩትና ጭንቅላታቸውን እየወዘወዙ ‘ምናልባት…’ ብለው ቃሉን ደገሙና ‘…እናንተ ወታደሮች፣ ከዚህ ቀደም ልብ ብለን ያላስተዋልነው ብዙ ምስጢር በውስጣችሁ አለ…’ ያሉኝን አልረሳዉም፡፡ ስለ‘ምናልባት’ ምን እንደተሰማቸው ባላውቅም መልዕክቴን ግን የተገነዘቡት መስሎኛል …›› ብሏል፡፡
ገስጥ፣ ለራሱ ንባብ ከያዛቸው መጻሕፍት ውስጥ ሁለቱ በየማነ ገብረ ማርያም የተጻፉት ‹‹የፍልስፍና ትምህርት›› ፩ኛ መጽሐፍ እና ፪ኛ መጽሐፍ ነበሩ፡፡ እነዚህን እና ሌሎችንም ለማንበብ ሰፊ ጊዜ አግኝቷል፡፡ በተጨማሪም የሥነ ጽሑፍ አድማስን ሊያሰፉ የሚችሉ አያሌ የሕይወት ልምዶችን ከአፋር ማኅበረሰብ ሊቀስም ችሏል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለ የየካቲቱ ሕዝባዊ አመፅ ተቀሰቀሰ፡፡ ዜናውን ከጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ጣቢያ ይከታተል ነበር፡፡ የለውጥ ስሜቱ ረፍት ነሳው፡፡ አጠቃላይ የሕዝብ መነሳሳት በተፈጠረበት ወቅት ወራንሶ (አውሳ) ቆላ ውስጥ መቀመጡን ጠላው፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እንደአለ ለጽሕፈት ሥራ በማስፈለጉ በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ ወደ ደሴ ተዛወረ፡፡ (የዘመቻው ጽሕፈት ቤት፣ በመርሆ ቤተ መንግሥት ውስጥ ነበረ)
ዘማቹ ጦር የመጣበትን ግዳጅ በማጠናቀቁ ወደ ደብረ ዘይት እንዲመለስ ተወሰነና በየጣቢያው ተበትነው የነበሩ ወታደሮች በሚያዚያ ወር መጨረሻ ላይ ደሴ (ወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት ግቢ) እንዲሰባሰቡ ተደረገ፡፡
ይህን አጋጣሚ በመመርኮዝ እርሱና 6 ግብረ አበሮቹ እዚያ የተሰበሰበውን አንድ ሻምበል ጦር አሳምፀው የጦሩን አመራር ተረከቡ፡፡ ከዚያም ደሴ ከተማን ለአንድ ምሽት ተቆጣጠሩ፡፡ ኃይል ለመሳየት ከአልሆነ በቀር፣ ደሴን ለአንድ ሌሊት ከፖሊስ ቁጥጥር ሥር ማውጣት ለአመፁበት ዓላማ ፋይዳውን ውሎ አድሮ ሲያስበው ሞኝነት እንደ ነበር ገስጥ ይናገራል፡፡ አማፂው ጦር በማግሥቱ ወደ ደብረ ዘይት ጉዞ ጀመረና ደብረ ሲና ላይ አዳር ሆነ፡፡ ገስጥ እና ጓደኞቹ አመፃቸው ምክንያትና ዓላማ እንዲኖረው ተመካክረው ጥቂት ነጥቦችን ነደፉ፡፡ ዓላማቸው በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የአነጣጠረ ነበር፡ ይኸውም ኮሎኔል ዓለም ዘውድ ተሰማ፣ የአየር ወለድ ጦር፣ የአየር ኃይል ሠፈርን እንዲይዝ በማድረጋቸውና ሁለቱ ክፍሎች በጠላትነት እንዲተያዩ በማድረጋቸው ከአየር ወለድ ጦር አዛዥነታቸው እንዲነሱ፣ የአየር ወለድ ጦር የአየር ኃይል ሠፈርን በአስቸኳይ ለቅቆ እንዲወጣና ከአየር ኃይል ጋር ተባብሮ ሕዝባዊዉን አመፅ እንዲደግፍ ማድረግ ሲሆን፣ በውስጡ ሌሎች ከ10 በላይ መሥረታዊ ጥያቄዎችን ያቀፈ ነበር፡፡
አማፂው ጦር ደብረ ዘይት እንደደረሰ በሠፈር ውስጥ የነበረው የአየር ወለድ ጦር አብዛኛው ለኮሎኔል ዓለም ዘውድ ወግኖ ስለአገኘው የእርስ በእርስ ግጭት እንዳይነሳ በመፍራት ጥያቄውን እርግፍ አድርጎ ተወው፡፡ የእነ ገስጥ ዓላማም ከሸፈ፡፡ ይሁን እንጂ የአጠቃላዩ የአየር ወለድ ጦር ስሜት ከሕዝባዊው አመፅ ጋር ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ በሕዝቡም፣ በሠራዊቱም ውስጥ ያለው የሥርዓት ለውጥ እንቅስቃሴ እያየለ ሄደ፡፡ በተለይ በሠራዊቱ ውስጥ በመካሄድ ላይ የነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ ብዙ ውጣ ውረድ ገጠመው፡፡ ‹‹ለውጡን ያራምዳሉ›› ተብለው በተለያየ ጊዜ ሁለት ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሁለቱም በተለያየ ምክንያት ከሸፉ፡፡ በዚያው ሰሞን በአየር ኃይል እና በአየር ወለድ ጦር መሀል የከረረ ጠብ ተፈጠረ፡፡ ነገሩን ለማለዘብና እርቅ ለመፍጠር በሁለቱም ወገን አስታራቂ ኮሚቴዎች ተቋቋሙ በአየር ወለድ በኩል በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ ገስጥ ነበረበት፡፡ ነገሩ በዚህ ሁኔታ ላይ እንደአለ ‹‹የጦር ኃይሎች፣ የብሔራዊ ጦርና የፖሊስ ሠራዊት አስተባባሪ ኮሚቴ›› ተቋቋመ፡፡
የአየር ወለድ ጦር፣ በአስተባባሪ ኮሚቴው ውስጥ የሚወክሉትን መኮንኖችና የበታች ሹሞች ሲመርጥ ከተጠቆሙት አንዱ ገስጥ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹እሱ የያዘውን ይጨርስ›› (አስታራቂነቱን) ተብሎ ቀረ፡፡ ሆኖም በራሱ ተነሳሽነት ሰኔ 21 ቀን አራተኛ ክፍለ ጦር በተደረገው የአስተባባሪው ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተገኝቶና የተነገረውን ሁሉ አድምጦ በማግሥቱ ጠዋት ወደ ደብረ ዘይት (አየር ወለድ) ተመለሰ፡፡ ይህ በሆነ ጥቂት ቀናት በኋላ በአየር ኃይልና በአየር ወለድ መሀል እርቅ ወረደ፡፡ ወዲያው አስተባባሪ ኮሚቴው በሥራ አስፈላጊነት ገስጥን ጠራው፡፡ በዚህ ሁኔታ የደርጉ ማስታወቂያ ኮሚቴ አባል ሆነ፡፡ ይህ እንግዲህ የድርሰት ክሂሎቱ ከጸሐፊ ተውኔት ወጥቶ ወደ ዝርው ድርሰት የገባበት የሦስተኛው አጋጣሚ መጀመሪያ ነበር፡፡
በማስታወቂያ ኮሚቴ አባልነቱ የደርጉን መግለጫዎችንና ንግግሮችን የመጻፍ ዕድል አገኘ፡፡ ለፖለቲካ ትምህርት ወደ ቀድሞዋ ቼክስሎቫኪያ (ፕራግ) በመሄዱ፣ እንዲሁም ለሥራ ጉብኝት ወደ ቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን (ምሥራቅ በርሊን) እና ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት (ሞስኮ) የመጓዝ ዕድል በማግኘቱ በፕሮፓጋንዳ ሥራና በሥነ ጽሑፍ መስክ ጠቃሚ ነገሮችን ለማስተዋል ቻለ፡፡
በ1969 ዓ.ም፣ በደርጉ ወታደራዊ ፖለቲካ ጉዳዮች ጠቅላይ መምሪያ የፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ኃላፊ ሆኖ ስለተመደበ የሠራዊቱን (ታጠቅ ጦር ሠፈር ውስጥ ይሠለጥን የነበረውን ሕዝባዊ ሠራዊት ጨምሮ) ብሔራዊ ስሜት ለመገንባትና ማርክሲዝምን ለማስተማር የሚጠቅሙ የትምህርት መርጃዎችን፣ እንዲሁም በሬዲዮ፣ በጋዜጣና በበራሪ ወረቀቶች የሚሠራጩ የፕሮፓንዳ ጽሑፎችን ያዘጋጅ ነበር፡፡ በዚህም የሥነ ጽሑፍ ችሎታውን ለማዳበር ሰፊ ዕድል አግኘ፡፡
በ1972 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሠፓአኮ) በመቋቋም ላይ ነበር፡፡ በጎጃም ክፍለ ሀገር የኮሚሽኑ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሆኖ እንዲሠራ ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም ሲነግሩት ከውትድርና ሕይወት መለየት እንደማይፈልግ ለማሳሰብ ሞክሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በማንኛውም ሁኔታ ሕዝቡን ማገልገል አስፈላጊ መሆኑን በብዙ አመክንዮ ስለአሳመኑት ምደባውን ተቀበለ፡፡ በዚህም ከደርጉ መዋቅር ወጥቶ የፓርቲ ሠራተኛ ሆነ፡፡
ወደተመደበበት (ባሕር ዳር) ሥራ በመሄድ ላይ እያለ የመኪና መገልበጥ አደጋ ደርሶበት ከአንድ ዓመት በላይ ሆስፒታል ተኛ፡፡ ከሆስፒታል እንደወጣ በአዲስ አበባ ከተማ የቀጣና ኢሠፓአኮ አንደኛ ጸሐፊ ሆኖ ተመደበ፡፡ ፓርቲው ከተደራጀ በኋላም ‹‹የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ፣ (ኢሠፓ) የቀጣና ኮሚቴ አንደኛ ጸሐፊ››፤ ከዚያም የአዲስ አበባ ኢሠፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆኖ ቀጠለ፡፡ ይህ መስክ ከቀድሞው የበለጠ ማንበብን፣ መጻፍንና መናገርን ይጠይቅ ስለነበር የሥነ ጽሑፍ ክሂሎቱን ለማሳደግ አገዘው፡፡ እነዚህና ሌሎችም አጋጣሚዎች፣ የተውኔት ድርሰት ዝንባሌውን ሙሉ በሙሉ ወደ ዝርው (ልብ ወለድ) ድርሰት እንዲለውጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ አድርገውበታል፡፡ በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ አብዮት መከሰትና በደርግ መዋቅር ውስጥ የፕሮፓጋንዳ ጽሑፍ ተሳትፎውን አሳድጎ የፓርቲ ሠራተኛ ሆኖ መመደቡ የድርሰት ዘውጉን ብቻ አልነበረም የአስለወጠው፤ ከላይ እንደተጠቀሰው እሚወደውን ውትድርና ትቶ፣ የመኮንንነት ልብሱን አስቀምጦ፣ ሲቪል እንዲሆንም አስገድዶታል፡፡
ገስጥ፣ ከዚህ በኋላ በፓርቲ የፕሮፓጋንዳ ጽሑፎች ብቻ መወሰኑ ቀርቶ ልብ ወለድ መጻሕፍትን ለማበርከት ታጥቆ ተነሣ፡፡ እናም በ1973 ዓ.ም ‹‹የናቅፋው ደብዳቤ›› የተሰኘ አነስተኛ ታሪካዊ ልብ ወለድ መጽሐፉን ለንባብ አበቃ፡፡ በ1979 ዓ.ም ደግሞ ‹‹እናት ሀገር›› የተሰኘ ታሪካዊ ልብ ወለድ መጽሐፉን ደገመ፡፡ ከዚህ በኋላ በሥራ ብዛት ስለተወጠረ የድርሰት ሥራውን ለጊዜው አቋረጠ፡፡ በ1983 ዓ.ም ግንቦት ወር በተከሰተው የመንግሥት ለውጥ ምክንያት ታሠረ፡፡ በእሥር ላይ በቆየባቸው ዓመታት ብዙ መጻሕፍትን ለማንበብና የድርሰት ችሎታውን ከፍ ለማድረግ በቅቷል፡፡ በ1990 ዓ.ም ነሐሴ ላይ ከእሥር ሲለቀቅ በርካታ ረቂቅ መጻሕፍትን አሰናድቶ ለመውጣት ችሏል፡፡
ገስጥ፣ በእሥር ላይ የቆየባቸውን ዓመታት ሲገልጽ ‹‹…መንፈስን በሚያደቅና ዕድሜን በሚያነትብ፣ በዚያ ሥፍራ በርካታ ዓመታትን ማሳለፌ…፣ በአንድ በኩል ነፃነት አጥቼ በመጎሳቆሌ፣ በባለቤቴ፣ በልጆቼና በአጠቃላይ ቤተሰቤ ላይ በደረሰው ችግርና መከራ የመረረ ሐዘን ቢሰማኝም፣ በሌላ በኩል ግን የጎደለኝን የሕይወት ልምድ ለማሟላት ወደዚያ እንድገባ በእግዚአብሔር የታዘዘ እንደሆነ አምኛለሁ፡፡ ለድርሰት ሥራዬም ሆነ ለአጠቃላይ አኗኗሬ ጠቃሚ ትምህርት አግኝቸበታለሁ›› ብሏል፡፡
ከእሥር ቤት እንደወጣ፣ ለአንድ ዓመት በሥራ አጥነት የሰቀቀን ኑሮ ገፍቷል፡፡ ከዚህ በኋላ በአንድ የግል ባንክ ውስጥ ተቀጥሮ ሥራ ጀመረ፡፡ በመጠኑም ቢሆን የመረጋጋትና የመደላደል ጊዜ ሆነለት፡፡ እናም እሥር ቤት በነበረበት ጊዜ ከሠራቸው ረቂቅ መጻሕፍት ውስጥ ‹‹የፍቅር ቃንዛ›› የተሰኘ የወንጀል ምርመራ መጽሐፉን በወጉ አጠናቅቆ በ1992 ዓ.ም አሳተመ፡፡ ሳያቋርጥ ቀጠለና ‹‹ጦማር›› በተሰኘ ተወዳጅ የግል ጋዜጣ ላይ ‹‹ዘነበ ፈለቀ›› በተባለ የብዕር ስም አጫጭር መጣጥፎችን በማሥፈር ከእሥር ቤት ውጪ ያለውን፣ የወቅቱን የሥነ ጽሑፍ አየር ተለማመደ፡፡
ከእሥር በኋላ የጻፋቸው ድርሰቶቹ ከቀድሞዎቹ በአጻጻፍ ስልታቸውም ሆነ፣ በይዘታቸው የተለዩ ሆነው ታይተዋል፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ ራሱ ሲገልፅ ‹‹….እሥር ላይ በቆየሁባቸው ዓመታትና ከዚያ በኋላም የጻፍኋቸውን አብስዬ ለመሥራት በቂ ጊዜ አግኝቻለሁ፡፡ ቀድሞ ከነበረኝ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ተፅዕኖ ተላቅቄ ወደ ሚዛናዊ አጻጻፍ ገብቻለሁ፡፡ ብዙ ማንበቤና የዕድሜዬ መጨመርም ለለውጡ ታላቅ አስተዋፅዖ አድርጓል….›› በማለት የኋለኛ አጻጻፉን ከፊተኛው ጋር አነፃፅሯል፡፡
ገስጥ፣ በሥነ ጽሑፍ አምባ በአሳለፋቸው አያሌ ዓመታት፣ በርካታ አጫጭርና ረጃጅም ልብ ወለድ ድርሰቶችን የጻፈ፣ እንዲሁም ኢ-ልብ ወለድ መጻሕፍትን የአዘጋጀ ቢሆንም፣ ይህ ማስታወሻ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ ለኅትመት የበቁለት የሚከተሉት ናቸው፡፡
- ልብ ወለድ፡-
1.1 የናቅፋው ደብዳቤ፡- በ1973 ዓ.ም፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፣
1.2 እናት ሀገር፡- 1979 ዓ.ም፣ ንግድ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፣
1.3 የፍቅር ቃንዛ፡- በ1992 ዓ.ም፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፣
1.4 የማክዳ ንውዘት፡- በ2001 ዓ.ም፣ ኢሌኒ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፣
1.5 የረገፉ ቅጠሎች፡- በ2003 ዓ.ም፤ ፋር ኢስት ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግ. ማኅበር፤ አዲስ አበባ፣
1.6 የእማዋዬ እንባ፡- በ2005 ዓ.ም፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፣
1.7 የበቀል ጥላ፡- በ2010 ዓ.ም፣ ፕሮግረስ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፣ - ኢ-ልብ ወለድ፡-
2.1 ነበር ክፍል አንድ፡- ከ1996 ዓ.ም.፣ እስከ 2006 ዓም ድረስ፣ በፊንፊኔ መተሚያ ቤት፤ በአልፋ አታሚዎች እና በንግድ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፣ አሥር ጊዜ፤
2.2 ነበር ክፍል ሁለት፡- ከ2001 ዓ.ም.፣ እሰከ 2005 ዓ.ም ድረስ፣ በኢሌኒ ማተሚያ ቤት እና በአልፋ አታሚዎች፣ አዲስ አበባ፣ ሰባት ጊዜ፣
2.3 የቀድሞው ጦር፡- በ2006 ዓ.ም፣ ዜድ.ኤ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፣
2.4 ዶክተር ስሜ ደባላ፣ታላቁ የግብርና ምርምር ሥርዓት መሪ፡- ግለ ታሪክ፣ 2015 ዓ.ም፣ አሳታሚ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣
2.5 ጀግናው 18ኛ ተራራ ክፍለ ጦር፣ የጦር ሜዳ ውሎ ታሪክ፤ 2016 ዓም. ታትመው ወደ ሕዝብ የደረሱ ሲሆኑ፣ ለ12 መጻሕፍትም ሙሉ አርትዖት ሠርቷል፡፡ ገስጥ፣ የአጻጻፍ ስልቱ፣ የቃላት አጠቃቀሙና የሁነቶች አገላለጽ ችሎታው መጻሕፍቱን ተወዳጅ አድርጎለታል፡፡ በይበልጥ ከልብ ወለድ ዘውግ ‹‹እናት ሀገር››፣ ‹‹የፍቅር ቃናዛ››፣ ‹‹የማክዳ ንውዘት››፣ እና ‹‹የእማዋዬ እንባ››፣ ከኢ-ልብ ወለድ ዘውግ ደግሞ ‹‹ነበር›› (ክፍል አንድና ሁለት) የተሰኙት መጻሕፍቱ በአንባብያን ዘንድ ተዋቂነትንና አድናቆትን አትርፈውለታል፡፡ ከኢ-ልብ ወለድ መጻሕፍቱ ውስጥ ‹‹ነበር›› ክፍል አንድና ክፍል ሁለት፣ ለንባብ የበቁት “ዘነበ ፈለቀ” በሚል የብዕር ስም ነበር፡፡ በኋላ ግን በስሙ አሳተማቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲናገር ‹‹….በብዕር ስም የተጠቀምሁት ራሴን እምደብቅበት ምክንያት ኖሮኝ አይደለም፡፡ መጽሐፉን የአገኙ ሁሉ ለማንም ሳይወግኑ አንብበው ብያኔ እንዲሰጡ አስቤ ነው፡፡ ሆኖም በርካታ አንባብያን በተለያየ አመክንዮ እኔ እንደጻፍሁት ስለአወቁና ዓላማዬም ግቡን ስለመታ የብዕር ስሙ ተልዕኮውን ማጠናቀቁ ተሰማኝ፡፡ ልጆቼና የቅርብ ወዳጆቼም በብዕር ስም መቀጠል እንደሌለበት ደጋግመው አሳሰቡኝ፡፡ ስለዚህ የብዕር ስሙን ገፍፌ በስሜ እንዲታተም አደረግሁ…›› በማለት ገልጾታል፡፡
ገስጥ፣ በ2002 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ላይ ከሚሠራበት የግል ባንክ በጡረታ ተሰናበተና የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ ሆነ፡፡ ‹‹…ጡረታ መውጣቴን በእጅጉ ወደድሁት፡፡ የአንድ ሙሉ ሰው ስሜትና እፎይታም ተሰማኝ፡፡ ከመታዘዝ ተላቅቄ የራሴ አዛዥ ሆንሁ፡፡ በአካል ‘ጡረተኛ’ ብባልም፣ አዕምሮዬ ግን ጡረተኛነትን ስለአልተቀበለ፣ በእርግጥም በአካልም ሆነ በአዕምሮ ጠንካራ ስለነበርሁ የድርሰት ሥራዬን በአንድ ልብ ያዝሁት…›› በማለት ለሙሉ ጊዜ ጸሐፊት ያበቃውን የጡረታ ጊዜውን አመስግኗል፡፡
ይህን ጊዜውን በጽሑፍ ሥራ ብቻ አላሳለፈውም፡፡ ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ የበርካታ አገሮች ከተሞችንና ታሪካዊ ሥፍራዎችን ጎብኝቷል፡፡
- ከአፍሪካ፡-
- ጋምቢያን፡- (በ18ኛው ክፍለ ዘመን የባሪያ ንግድ ይካሄድበት የነበረውን ኪንታኩንቲ/ጁፍሪ ደሴት)
- ሴኔጋልን፡- (በዚሁ ዘመን ተመሳሳይ ድርጊት የተካሄደበትን ጎሬ ደሴት እና በውስጡ ትልቅ ሙዚየም የአቀፈውን ብሔራዊ ሐውልት፣ እንዲሁም ልዩ ወታደራዊ ሙዚየም)
- ደቡብ አፍሪካ፡- ሮቢን ደሴትንና በኬፕታውን አካባቢ፣ መጀመሪያ የደቡባዊ አፍሪካን ምድር ከረገጡ ቅኚ ገዢዎች ጋር የዙሉ ኢንካታ ትግል የተካሄደበትን ሥፍራና ሙዚየም)
- ከአውሮፓ፡-
- በርሊን፣ ፈራንክ ፈርት፣ እና ኡትስናብሩክ፣ (ጀርመን)
- አመስተርዳም፣ (ሆላንድ)
- ኦስሎው፣ (ኖረዌይ)
- ስቶክሆልም፣ (ስዊድን)
- ብራስልስ እና ኦስቴንዴ፣ (ቤልጂየም)
- ፓሪስ፣ (ፈረንሳይ)
- አላንዲያ ወደብ (ፊንላንድ)
- ከደቡባዊ ኤሺያ፡-
- ባንግ ኮንግ፤ (ታይላንድ)
- ሲንጋፖር፣
‹‹…እነዚህን ታሪካዊ ሥፍራዎች እና በኪነ ጥበብ የተዋቡ፣ በሥልጣኔ የደመቁ ከተሞችን በመጎብኘቴ በእጅጉ ዕድለኛ ብሆንም፣ በተለይ በደቡብ አፍሪካ ኒልሰን ማንዴላ ታስሮበት የነበረውን ሮቢን ደሴትን፣ በሴኔጋልና በጋምቢያ፣ አፍሪካውያን እህቶቻችንና ወንድሞቻችን እንደከብት እየተነዱ በባርነት ሲሸጡባቸው የነበሩ ደሴቶችን ማየቴ አፍሪካ ያሳለፈችውን መከራ በምናቤ ስሎብኛል….
‹‹….በአውሮፓ ከተሞች አስደማሚ የሆኑ የተሀድሶ (የሬነሳንስ) ዘመን ኪነ ጥበብ ያስጌጣቸውን ሕንፃዎችን፣ ሐውል ቶንችና ሙዚየሞችን፣ በተለይ ፓሪስ ውስጥ የኤፍል ማማንና የቪክቶር ሁጎን መኖሪያ ቤት የነበረውን ሕንፃ መመልከቴ፣ ለአንድ ደራሲ ሊሰጡ በሚችሉት ደስታና የአዕምሮ ስንቅ ውስጤን ሞልተዉታል…..
‹‹….ሲንጋፖር ትንሽ ደሴት ናት፤ ከሕዝቧም ውስጥ ብዙዎቹ በቁመት ትናንሽ ናቸው፡፡ ሆኖም እነዚያ ቁመተ ትናንሽ ሰዎች፣ ያችን ትንሽ ደሴት በሥራቸው ትልቅ (ሀብታም) አገር አድርገዋት ሳይ ‘የኔስ አገር ለምን…?’ በሚል ስሜት እንደ አንድ አገሩን ወዳድ ሰው እንድቀና አድርገዉኛል….›› በማለት በጉብኝቱ የገበየውን እሴት ገልፆታል፡፡
እርሱ ድምፃቸውን አጥፍተው ከሚሠሩ ደራስያን ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ‹‹ለምን…?›› ሲባል ‹‹ደስ እሚለኝና ምቾትም እሚሰጠኝ እንደዚህ ሆኜ ስሠራ ነው፡፡ ሥራዎቼ ከአንገታቸው ቀና፣ ከደረታቸው ኮራ ብለው ከታዩልኝ ይበቃኛል›› ባይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹…ቤተሰቤ፣ በተለይም ልጆቼ የድርሰት ሥራዬ እንዲቃና በተቻላቸው ሁሉ ስለሚደግፉኝ ዕድለኛ ነኝ›› ይላል፡፡
ሕይወት በብዙ ገጠመኞች የታጀበች ናት፡፡ የገስጥ ሕይወትም ገና የአሥር ዓመት ልጅ በነበረበት ጊዜ ጀምራ በአያሌ ገጠመኞች ታጅባለች፡፡ በጦር ሠፈርና በጦር ሜዳ፣ በፖለቲካና በአስተዳደር፣ በእሥር ቤትና በሥራ አጥነት የአያቸው መልካምና መጥፎ ገጠመኞች አሉት፡፡ ከዚህ ጽሑፍ ጋር አግባብነት ያለውን የድርሰት ሕይወት ገጠመኙን እንዲህ እያለ ያወጋናል፡፡ ‹‹…በ1972 ዓ.ም የመኪና አደጋ ደርሶብኝ በነበረ ጊዜ ቀኝ እግሬና ቀኝ እጄ ተሰባብረው ከጥቅም ውጪ ሆኑ፡፡ በቀኝ እጄ ላይ ከስብራቱ በተጨማሪ የነርቭ ችግር ስለተከሰተ መጻፍ እንኳ አዳገተኝ፡፡ የእሱ ጉዳይ በዚሁ የአከተመ መሰለኝና በግራ እጄ ለመጻፍ ልምምድ ጀመርሁ፡፡ በመሐሉ ʻለምን መጽሐፍ እየጻፍሁ አልለማመድም?ʼ የሚል ሐሳብ መጣልኝ፡፡
እናም በውስጤ ሲጉላላ የነበረውን ʻየናቅፋው ደብዳቤʼ መጽሐፌን በግራ እጄ ጻፍሁት፡፡ በድርሰት ሥራዬ ውስጥ ይህ አጋጣሚ አይረሳኝም፡፡ እንዲሁም ከደረሰብኝ አደጋ ድኜ፣ በእግሬ ቆሜ እንድሔድና እንደገና በቀኝ እጄ እንድሠራ የአበቁኝን ብርጋዲየር ጀኔራል ዶክተር ግዛው ፀሐይን፣ ብርጋዲየር ጀኔራል ዶክተር ጋጋ ኦልጃንና ኮሎኔል ሲስተር ደመቀች ታደሰን ከዚህ ገጠመኜ ጋር በምስጋና ጭምር አስታውሳቸዋለሁ….›› ብሏል፡፡ ገስጥ፣ የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ ከመሆኑ በአሻገር በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር፣ በጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢነት (ለሁለት ጊዜ)፣ የማኅበሩ የመማክርት ጉባኤ አባል፣ በማኅበሩ “የጥበብ እልፍኝ” የሬዲዮ ዝግጅት እና ማኅበሩ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመስማማት በተዘዋዋሪ ሒሳብ ድጋፍ ለሚያሳትማቸው መጻሕፍት የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) ቦርድ አባል፣ እንዲሁም በሌሎችም ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች በመሳተፍ ማኅበሩ በአባላቱ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዲወጣ አቅሙን ለማጐልበት ጥሯል፡፡ ለበርካታ ደራስያንም የምክር እገዛ በማድረግ ለአገራችን ሥነ ጽሑፍ እድገት የበኩሉን አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡