ዶክተር ጌታቸው ተድላ አበበ
የእርሻ ኢኮኖሚስት፣ ገጠር ልማት ባለሙያ እና ደራሲ
ዶክተር ጌታቸው ተድላ አበበ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የቅርብ ወዳጅና አማካሪ ሲሆን ድርጅቱ የግለ-ታሪክ ስራዎችን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሁሉም ጉዳዮች አብሮ ያለ ሰው ነው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ በየካቲት 2013 ከ 4 ወር በፊት የዶክተር ጌታቸው ተድላ ግለ-ታሪክ በዘጋቢ ፊልም ሰርቶ ያስመረቀ ሲሆን የአባቱ የክቡር አቶ ተድላ አበበ ታሪክን ደግሞ በኦድዮ መጽሀፍ አውጥቷል፡፡ ዶክተር ጌታቸው የደራሲያን ማህበር ውስጥ የጎላ ድርሻ ያበረከተ ሲሆን ወደ 14 የሚሆኑ መጽሀፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡
አንድ ፊልምንም ፕሮዲዩስ አድርጓል፡፡ ዶክተር ጌታቸው የራሱን የግል ዶክመንት ጨምሮ የበርካታ የሀገር ባለውለታዎችን ምስል በማሰባሰብ ይታወቃል፡፡ ፎቶግራፍ የማንሳትም የተለየ ፍላጎት አለው፡፡ ከ15000 በላይ የቆዩ እና ያሁን ፎቶግራፎች ስብስቦች በእጁ ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ቀዳሚ የሆነው ዶክተር ጌታቸው ለወጣቶች የሚመች ሰብእና አለው፡፡ ራሴ አዋቂ ነኝ ብሎ ታናናሾችን ሳይንቅ ያደምጣቸዋል፡፡ ምክር ይቀበላል-ይሰጣል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ወጣት የጥበብ ሰዎች በድርሰት እና በምርምር ስራ ላይ ያሉ ሰዎች ዶክተር ጌታቸውን እንደቅርብ ወዳጅ ነጻ ሆነው ያወሩታል፡፡
ደራሲው ዶክተር ጌታቸው በሙያ ያጠናው የእርሻ ኢኮኖሚን ቢሆንም ለታሪክ ፤ ለቅርስ የተለየ ፍቅር አለው፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አሰናጆች ዶክተር ጌታቸውን አንተ እያልን ብንጠራውም የህይወት ታሪኩን አንቱ እያልን እናቀርባለን፡፡ ዶክተር ጌታቸው በድርሰት ዘርፍ ትልቅ ስራ የሰራ በመሆኑ ታሪኩን በዚህ መልኩ እናቀርባለን፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በቅርቡ ደረጃውን የጠበቀ ለቤተ-መጽሀፍቶች አገልግሎት የሚውል በጠንካራ ሽፋን የተጠረዘ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ አሳትሞ ያቀርባል፡፡ እስካሁን በዚህ ገጽ ያወጣናቸውን በጥራዝ መልክ አድርገን ለታሪክ የምናስቀምጥ ሲሆን ታሪካቸው በዚህ መልክ በክብር ከሚሰነድላቸው አንዱ ዶክተር ጌታቸው ተድላ ይሆናል፡፡
ስማቸው ዶክተር ጌታቸው ተድላ አበበ ይባላል፡፡ የተወለዱት በአዲስ አበባ፣ አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ ከአባታቸው ከአቶ ተድላ አበበና ከእናታቸው ከወ/ሮ ብዙነሽ ገደቡ ነው፡፡ በስድስት ዓመታቸው አሰላ በሚገኘው በቀድሞ ስሙ ራስ ዳርጌ ትምህርት ቤት ገብተው የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ከዚያም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ስዊድን ሔደው በመጀመሪያ ዲግሪ የእርሻ ትምህርት ተመረቁ፡፡ ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸው ወደ ሀንጋሪ ሔደው፣ ሁለተኛውንና የመጨረሻውን የፒ.ኤች.ዲ. ዲግሪያቸውን የእርሻ ኢኮኖሚስትና የገጠር ልማት ባለሙያ በመሆን በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቀቁ፡፡ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (የተ.መ.ድ.) ውስጥ ተቀጥረው ከ32 ዓመት በላይ አገልግለዋል፡፡ በሥራ ዓለም የሠሩበትና የቆዩበት ባጭሩ ሲዘረዘር በሚከተለው መልኩ ከመጨረሻው በመጀመር ወደታች እስካለው የሚከተለውን ይጠቀሳል፡፡ ሁሉም እ.ኤ.አ. ነው፡፡
- አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ) በሚገኘው የተ.መ. የእርሻ ልማት ድርጅት (ፋኦ) ቢሮ ውስጥ፣ ለድርጅቱ ተጠሪና ሥራ አስኪያጇ ዋና አማካሪ በመሆን አንድ ዓመት ከአራት ወር (07/2005 እስከ 10/2006) ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህም ሥራቸው ፋኦን እየወከሉ ኢ.ሲ.ኤ ወይም ኦ.ኤ.ዩ ብዙ ስብሰባዎችን በመካፈልና የስብሰባውን ፍሬ ነገር ሪፖርት በመጻፍ፣ የአጫጭርና የረጅም ጊዜ ፕሮጀክቶች በማጥናትና ሐሳብ በማቅረብ፣ የሥራ ጠያቂ አመልካቾችን ወረቀቶች እያጠኑና እየመረመሩ፣ ከብዙዎቹ ሥራ አመልካቾች ይሆናል ብለው የሚያስቡትን ብቻ ለዳይሬክተሯ በማስተላለፍ ከተሳተፍ በኋላ በራሳቸው ፈቃድ ከሥራው ተሰናበቱ፡፡
- በኢንዶኔዥያ መንግሥት ሥር ትተዳደር የነበረችው ምሥራቅ ቲሞር፣ ራሷን በራሷ ለማስተዳደር ነፃነትዋን በማወጇ፣ በኢንዶኔዥያ መንግሥት ከፍተኛ ጥቃት ስለደረሰባት በተባበሩት መንግሥታት ጣልቃ ገብነት በሀገሪቷ ሰላም እንዲሰፍን ባደረገው ሁሉገብ የማስተዳደርና የሥራ ተግባር፣ በእርሻና በኢኮኖሚው መስክ ለማገዝ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ ተመልምለው ሔደው ለሦስት ዓመታት ከ05/200 እስከ 05/2002 በአገሪቱ እርሻ ሚኒስቴር ውስጥ ለሚኒስቴሩ ዋና አማካሪና የአስተዳደር ቢሮ ዋና ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ሥራውም በሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤት የሚሠሩትን የአገሩ ተወላጆች በመቅጠርና ማስተባበር ሲሆን፣ በጠቅላላው ከ1300 በላይ ሠራተኞች ቃለ-መጠይቅ ማድረግና በመላ አገሪቱ የእርሻ ባለሙያዎች መቅጠር ነው፡፡ በመሥሪያ ቤቱ የተቀጠሩት ሠራተኞች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ማሰልጠን፣ በየወሩ አጫጭር የሥራውን ሂደት፣ በየስድስት ወሩ ደግሞ ከፍ ያለ ሪፖርት ለኒውዮርክ የተ.መ.ድ. ቢሮ ማቅረብን ያካትት ነበር፡፡
- ሱሉማንያ (ኢራቅ) በመባል የምትታወቀው የኩርዶች ጠቅላይ ግዛት ውስጥ የፋኦ ቢሮ ተጠሪ ሆነው ገበሬዎችን በሁሉም መስክ መርዳት፣ ማሰልጠንና የእርሻ ግብአቶችን ማቅረብ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ሥራውን ሲረከቡ በሥራው የተሰማሩ የአገሩ ተወላጅ ቁጥር 40 ብቻ የነበረውን ወደ 152 እንዲያድግ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የተ.መ.ድ. የላካቸው የውጭ ሀገር ባለሙያዎች ሁለት ብቻ የነበሩትን ሥራውን አስፋፍተው ወደ 14 ከፍ አድርገውታል፡፡ ከዚያም ዋናው በኢራቅ የፋኦ ተጠሪ ሥራ ስለበዛባቸውና ረዳት ስለአስፈለጋቸው ዶ/ር ጌታቸውን በመምረጣቸው፣ ከሱሉማንያ ወደ ባግዳድ እንዲዛወሩ አድርገው ዋና አስተባባሪና ለዓለም አቀፍ ሠራተኞች ኃላፊ አደረጓቸው፡፡ ስለዚህም ጠቅላላውን የዐረቦቹና የኩርዶቹን ሥራ መከታተል ዋናው ሥራቸው ሆነ፡፡ በኢራቅ አራት ዓመት ከ1997 እስከ 2000 ከሠሩ በኋላ፣ በአሜሪካ መሪነት ከምዕራብያውያን ጋራ የተነሳው ጦርነቱ ስለተፋፋመ የፋኦ ቢሮ ተዘግቶ፣ ዓለም አቀፍ ሠራተኞች ሲወጡ፣ ዶ/ር ጌታቸው ተድላም ሀገሩን ለቀው ሄዱ፡፡
- ለአምስት ዓመታት ማለትም ከ1991 እስከ 1996 ድረስ በልዩ ልዩ ድርጅቶችና ሀገሮች አማካሪ (ኮንሰልታንት) በመሆን እርሻ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይኸውም – ካምፓላ (ኡጋንዳ) ውኃ ማቆር ፕሮጀክት፡፡ ሮም (ጣልያን) በምግብ ዋስትና ፕሮጀክት፡፡ ብሩሴልስ (ቤልጀም) በአውሮፓ አንድነት ድርጅት ውስጥ ስለ ሴቶች ልማት፡፡ ዋርሶ (ፖላንድ) በአይ ኤል ኦ (በተ. መ. ድ. ውስጥ – ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት) ሁሉገብ የእርሻ ማሰፋፊያና ማሻሻያ ዘዴ አማካሪ፡፡ በአቡጃ (ናይጀሪያ) ለዓለም አቀፍ አሰልጣኞች ዋናው ኃላፊ ሆነው በማኅበራዊ እርሻ ሥልጠና በመስጠት አገልግለዋል፡፡
- ለአምስት ዓመት ማለትም ከ1987 እስከ 1991 ድረስ በሌጎስ (ናይጀሪያ) በአይ ኤል ኦ (ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ተቋም ) ውስጥ – የማህበራዊ እርሻ ኤክስፐርት በመሆን በመላው ሀገር ማህበራዊ እርሻን ማስፋፋትና የእርሻ ሥልጠና ኮርስ በመስጠት የሠሩ ሲሆን፣ በተጨማሪም በብሔራዊ ደረጃ አንድ ትልቅ የገጠር ልማት ሥልጠና መስጫ ኮሌጅ ተገንብቶ እንዲቋቋም በወጣው መርሐ-ግብር ተሳትፈዋል፡፡ ይህም ግንባታ ከአራት ዓመት በኋላ ተጠናቆ ለተግባር በቅቷል፡፡
- ማውን (ቦትስዋና) የክፍለ ሀገሩ የእርሻ ክፍል አስተዳዳሪና ሥራ አሰኪያጅ በመሆን ለአራት ዓመታት ማለትም ከ1983 እስከ 1986 ሠርተዋል፡፡ ይህም ለገበሬዎች የእርሻ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ መሬት የሌላቸውን የቁጥቋጦ ሰዎች (ቡሽ ሜን) መሬት ሰጥቶ በማስፈርና በማሠልጠን ማደራጀትን ያጠቃለለ ተግባር ነበር፡፡
- በሞሼ (ታንዛንያ) ለሦስት ዓመት ማለትም ከ1981 እስከ 1983 ሞሼ በሚገኘው የአፍሪካ የማኅበራዊ ድርጅት ዋና ጽ/ቤት የማኅበራዊ እርሻ ክፍል ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ሥራቸው በአፍሪካ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ሀገሮችን በሙሉ እየዞሩ ሥልጠና መስጠትና የሚገለገሉበትን መጽሐፍ በማዘጋጀት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡
- በማሴሩ (ሌሶቶ) ለአንድ ዓመት ተኩል ማለትም ከ1980 እስከ 1981 የእርሻ ኢኮኖሚስት በመሆን ከ240 እርሻዎች ላይ የተገኙትን ጭብጥ ማስረጃዎች በኮምፒተር በማስፈር ገበሬዎቹ ገቢና ወጭያቸውን አውቀው የተሸለ ትርፍ እንዲያገኙ ምክር በመስጠትና፣ የቢሮው ሠራተኞችን በማሠልጠን ተልዕኳቸውን ተወጥተዋል፡፡
- በስቶክሆልም (ስዊድን) ሲዳ / ሳሬክ ቢሮ የእርሻ ጥናት ተመራማሪ ከ1979 እስከ 1980 ሆነው ከሦስተኛው ዓለም፣ ማለትም ከአፍሪካ፣ እስያና ላቲን አሜሪካ የቀረቡ የእርሻ ምርምር ጥናቶች፣ የክለሳ ጥናት በማድረግ እያስተካከሉ በመምከርና መስመር በማስያዝ የእርሻ ተመራማሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑ ረድተዋል፡፡
- በወላይታ ሶዶ (ኢትዮጵያ) ከ1970 እስከ 1971 የዋዱ (ወላይታ የእርሻ ልማት ድርጅት) ድርጅቱን ማቋቋምና የእርሻው ክፍል ኃላፊ በመሆን በክፍለ ሀገሩ ያለውን የእርሻ ልማት ከፍ እንዲል በትጋት ሠርተዋል፡፡
- በአሰላ – አርሲ (ኢትዮጵያ) ከ1966 እስከ 1968 የካዱ (ጭላሎ የእርሻ ልማት ድርጅት) የፕላንና የእርሻ ግምገማ ምክትል ኃላፊ በመሆን በክፍለ ሀገሩ ያለውን የእርሻ ልማት ከፍ እንዲል በትጋት ሠርተዋል፡፡
በልዩ ልዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሠሩባቸው ሀገሮች የሚከተሉት ናቸው
ቤልጀም፣ ቦትስዋና፣ የቀድሞ ቼኮዝላቫኪያ፣ ጋና፣ ምሥራቅ ቲሞር፣ ኢትዮጵያ፣ ሀንጋሪ፣ ኢራቅ፣ ጣልያን፣ ኬንያ፣ ማላዊ፣ ሌሶቶ፣ ናይጀሪያ፣ ፖላንድ፣ ሮማንያ፣ ስዋዚላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ የቀድሞ ሶቭየት ዩኒየን እና ዛምቢያ ናቸው፡፡
ስለ ሥራቸው ዕውቅና ልዩ ልዩ የምስክር ወረቀትና ዋንጫዎች አግኝተዋል፡ በእርሻ ምርምርም ብዙ ሳይንሳዊ ጽሑፎችም አቅርበዋል፡፡ በርካታ እርሻ ነክ መጻሕፍት በእንግሊዝኛ አሳትመዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ በጥቂቱ:-
- “Agricultural Programme under SCR 986 – Sulaimaniyah Governorate, Northern Iraq“Baghdad, Iraq. 1998. (FAO)
- “Master Equipment List for vocational Training Programme: Rural / Farming.” Warsaw, Poland. 1994. (ILO)
- “Co-operative Education and Training arrangements in Nigeria” Lagos, Nigeria.1988. (FAO)
- “Data and Information on Agricultural Co-operation in Nigeria” Lagos, Nigeria. 1988. (FAO)
- “ALDEP In-service Training”, Maun, Botswana.1984. (FAO)
- Co-authored: “Strengthening National Agricultural Research” SAREC Workshop. Stockholm, Sweden. 1980. (SAREC)
- “Food Comes First” Research works published and presented at the Co-operative College, Moshi, Symposium on the occasion of the World Day. Moshi, Tanzania. 1982. (FAO)
- “PPP” (People’s Participation Programme) and AMSAC (Appropriate Management Systems for
- Agricultural Co-operatives). Research work published and presented at the ICA, Regional Council Meeting. Lusaka, Zambia.1982. (FAO)
- “Selected Agricultural Indicators for Selected Developing Countries” Sweden (SAREC).1980.
- Co-authored: “Tobacco and Alternative Crops” Uppsala, Sweden (SIDA). 1979.
በተጨማሪም ዕውቅ የሆኑ የአፍሪካ ታዋቂ ሰዎች በተመዘገቡበት Africa Who is Who (1991) በሚለው ታላቁ መጽሐፍ ላይ ስማቸውና ታሪካቸው ሰፍሯል፡፡ ሌላው ሊጠቀስ የሚገባው፣ በልዩ ልዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ በንቃት ከመሳተፋቸውም ባሻገር ያልተቆጠበ ዕርዳታ በማድረግና በበጎ ፈቃደኛነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ውስጥ “መቄዶንያ – የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል” እና “እድገት ለህፃናት የበጎ አድራጎት ማኅበር” ለአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
በአዛውንት ዕድሜያቸው ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው፣ የሚከተሉትን ……… መጻሕፍት ለኅትመት አብቅተዋልሁ፡፡ …….ግለ ታሪክ ሲሆኑ፣ …….ደግሞ ልብ ወለድ ትረካ ናቸው፡፡ ሁለቱ ደግሞ ሥዕላዊ መጽሐፍቶች ናቸው፡፡ እነኝህም:-
በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረቱ:-
- ተድላ አበበ – የዘመናዊ እርሻ ፋና ወጊ (አ.አ. ማስ ማተሚያ ቤት፣ 2002 ዓ.ም.) ይህ መጽሐፍ የአቶ ተድላ አበበን ዘመናዊ የእርሻ ሥራ የሚተርክ ነው፡፡ ጽሑፉን ለመጻፍ ያሰቡት አባታቸው በጣም የደከሙበት እርሻ በመንግሥት ከተወረሰ በኋላ፣ ዶ/ር ጌታቸው በተ.መ.ድ. ተቀጥረው ቦትስዋና በነበሩበት ወቅት፣ ለሁለት ወር ተኩል መጥተው ሲጎበኟቸው፣ ስለ ሕይወታቸው ብዙ ከተወያዩ በኋላ ነው፡፡ ስለዚህም የተወያዩባቸውን ነጥቦችን በወረቀት ላይ በማስፈር፣ የመጀመሪያውን ንድፍ በግንቦት 1979 ጻፉ፡፡ ፎቶግራፎችም መርጠው አስቀመጡ፡፡ ልዩ ልዩ ጋዜጦች ስለሳቸው የተጻፉትን ሰበሰቡ፡፡ ከሳቸው ጋር የሠሩ ወይም በቅርብ የሚያወቋቸውን ሰዎች ቃለ መጠይቅ አድርገው፣ በደርግ ዘመነ መንግሥት የነበረውን ውጣ ውረድ፣ ከብዙው የግል መዝገባቸው አሰባስበው፣ በተለምዶው በሬን በመጠቀም ብቻ ከሚታረሰው እርሻ እንዴት የእርሻ ትራክተሮችንና ኮምባይን በመጠቀም ወደ ዘመናዊ እና ትርፋማ የእርሻ ልማት እንደተደረሰ የሚያወጋ መጽሐፍ ለኅትመት አበቁ፡፡
- ቅንብርና ትርጉም – የአክሊሉ ማስታወሻ – ጠ. ሚ. ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ – የሕይወት ታሪክ (አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ፣ ሦስት ጊዜ ኅትመት 2002/3/9) ይህ መጽሐፍ በአምባ ገነኑ የደርግ መንግሥት ያለ አግባብና ያለፍርድ የተገደሉት፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የክቡር ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ታሪክ በደርግ የተቋቋመው የመርማሪ ኮሚሽን ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉን እስካሁን ምን እንዳከናወኑ፣ የሕይወትዎን ታሪክ ይዘክሩ ተብለው በታዘዙት መሠረት፣ የጻፉትን ነው፡፡ ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ባላቸው የረቀቀ የዲፕሎማሲ ችሎታ፣ የአገሪቱን ክብር በመጠበቃቸው፣ አገርን ሳያስደፍሩ መከታ በመሆናቸው በጣሙን የሚያኮሩ ሰው ነበሩ፡፡ ያም ቢሆን ለደከሙበት ሁሉ ‘እናመሰግናለን’ ሳይሆን፣ የተከፈላቸው ውለታ በጥይት መረሸናቸው ግን በጣም አሳዘኝ ነው፡፡ እናም ይህንን የታሪኮች ታሪክ፣ ለምን ወደ እንግሊዝኛ ተርጉሜ ሌላው የዓለም ሕዝብ እንዲያውቀው አላደርግም በማለት ዶ/ር ጌታቸው ተርጉመው አጠናቀቁ፡፡ መጽሐፍ መተርጎም የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1993 መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ የአ.አ.ዩ. ፕሬስ የአክሊሉ ዲፕሎማሳዊ ትግል ከማሳየቱም ባሻገር፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ታሪክ የሚዘክር ስለሆነ፣ በአንድ መጽሐፍ ውስጥ በአማርኛና በእንግሊዝኛ እንዲታተም ወስኖ፣ የመጀመሪያው ኅትመት በ2002 ዓ.ም. ወጣ፡፡ በአንባብያን በጣም ስለተወደደ ተደጋግሞ ታተመ፡፡
- የሕይወት ጉዞዬ እና ትዝታዎቼ – በውጭ ሀገር (አ.አ. 2003 ዓ.ም. ኢሜጅ ማተሚያ ቤት እና ሁለተኛ ኅትመት፣ 2008 ዓ.ም. ፋር ኢስት ማተሚያ ቤት) ዶ/ር ጌታቸው ተድላ ከልጅነት እስከ ትምህርት ዓለም፣ በተለይም በውጭው ዓለም ያለፉባቸውን ገጠመኞች እንደወረደ ለአንባብያን አቅርበዋል፡፡ ይህ መጽሐፍ በእሳቸው ትውልድ የነበሩ ወጣቶች ከተወለዱበትና ከአደጉበት ሀገር፣ ሥነ ጥበብና ሥልጣኔ እቀስማለሁ ብለው ወደ አውሮፓና ሌላም አህጉራት ተጉዘው ያሳለፉትን የኑሮና የባሕል ግጭት ውጣ ውረድ በሰፊው የሚያወጋ መጽሐፍ ነው፡፡ ብዙው የመጽሐፉ ታሪክ የተከሰተው፣ ዶ/ር ጌታቸው በአውሮፓ በትምህርት ዓለም ውስጥ በነበሩበት ወቅት ቢሆንም፣ በሌሎች አህጉራት በሥራ ዓለምና በጉብኝት ያጋጠማቸውን ክስተቶች ያወሳሉ፡፡ ‘ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ’ እንዲሉ፣ በወጣትነትና በጎልማሳነት ዘመን በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያና እስያ በመኖር፣ በትምህርት፣ በሥራ፣ በስብሰባና በጉብኝት ያዩትንና የሰሙትን፣ ያደረጉትንና ገጠመኞቻቸውን በዝርዝርና ደስ በሚል አዝናኝ ሁኔታ አቅርበውታል፡፡
- የሕይወት ጉዞዬ እና ትዝታዎቼ – በሀገር ቤት፣ ክፍል ሁለት (አ.አ. 2009 ዓ.ም. ፋር ኢስት ማተሚያ ቤት) ይህ መጽሐፍ ልክ እንደ መጀመሪያው የውጭ ዓለም ትረካቸው ወደ ሀገር ቤት ከመጡ በኋላ፣ እዚህ ሀገር ያሳለፉትን፣ ያጋጠማቸውን ትዝታዎች ተረከውበታል፡፡ መጽሐፉ ውስጥ ሕይወትን ለመግፋት መሯሯጥ፣ የታመመ መጠየቅ፣ ጧት ወዳጅ ቀብሮ፣ ማታ ሠርግ መሔድ፣ በጎ አድራጎት መሥራት፣ ስብሰባ መገኘት፣ አንዳንድ ቦታ ማስተማር፣ ለጥየቃ የሚመጡትን እንግዶችና ልጆቻቸውን ማስተናገድ፣ በሚያዝናና ሁኔታ አቅርበውታል፡፡ በተጨማሪም ከሀገር ቤት ወደ ውጭ ሀገር የጎበኙትን ሌላው እንዲጋራ ሊያስተምር በሚችል ሁኔታ አስቀምጠው፣ ለኅትመት አብቅተዋል፡፡
- My Days in the 1970s – Published in 2018 at Bereket Printing PLC ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በእንግሊዝኛ ነው፡፡ መጽሐፉ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ በአውሮፓ በተለይም በስዊድንና በሀንጋሪ ሀገሮች ተማሪ ሆነው ያሳለፉበትን በሰፊው ይተርካል፡፡ በሀያ ዓመት መጀመሪያ ላይ በነጮች ትምህርት ቤት እንዴት ትምህርት እንደቀሰሙ፣ እርሻ ላይ ያደረጉትን ልምምድ፣ የተገነዘቡትን የባህል ልዩነት በዝርዝር ይገልጻል፡፡ በመጨረሻም ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ለማግኘት በምስራቅ አውሮፓ ሲዞሩ ያጋጠማቸውን ሁሉ አንባቢ ብዙ ትምህርትና ግንዛቤ እንዲያገኝባቸው አድርገው
- ጀግናው ቃኘው ሻለቃ በኮሪያ (The Gallant Battalion in Korea) Published in 2019 at SSB Printing PLC ይህ መጽሐፍ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የተጻፈ ነው፡፡ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ በቀድሞው የክብር ዘበኞችና ብሎም በሕዝቡ ካስመሰገኗቸው መጽሐፍቶች ውስጥ ይህኛው ሊጠቀስ ይችላል፡፡ መጽሐፉ ጀግናው የቃኘው ሻለቃ በኮሪያ ያደረገውን የጀግንነት ትግልና ድል፣ ስለማረካቸው ጠላቶች፣ እንኳንስ በሕይወት ጦርነቱ ላይ ሕይወታቸው ያለፉት እንኳን አለመማረካቸውን ይገልጻል፡፡ ጀግናው የቃኘው ሻለቃ ሀገሩን ከማስኮራቱም በተጨማሪ በውጭ ዓለምም በዝናነቱና ስሙን በወርቅ ማስመዝገቡን በሰፊው ይተርካል፡፡
ልብወለድ መጽሐፍቶች
- ውጥረትን በተስፋ የተዋጠች ሕይወት (አ.አ. 2004 ዓ.ም. ኢሜጅ ማተሚያ ቤት)መጽሐፉ የሚያወጋው ስለ ሰባት ወጣት ኢትዮጵያውያን የውትድርና ሥልጠናና ከዚያም በኋላ ያሳለፉትን ጭንቀት ነው፡፡ የወታደርነት ሥልጠና ጨርሰው፣ ወደ የቤታችን እንመለሳለን ብለው ሲያልሙ፣ በወቅቱ የነበረው የደርግ መንግሥት፣ ወደ ቋሚ ወታደርነት ስለመደባቸው፣ አሻፈረን፣ አንፈልግም በማለት ለመጥፋት ይመካከራሉ፡፡ የተመካከሩትን እውን ለማድረግና ወደ ጂቡቲ ለመጓዝ ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊት ያዩት መከራ፣ ጥርት ባለ ልብ አንጠልጣይ ሁኔታ ተገልጿል፡፡ መጽሐፉ የተደረሰው በውጭው ዓለም በነበሩበት ወቅት በ1983 ቢሆንም፣ ከ22ዓመታት በኋላ በ2005 ለኅትመት በቅቷል፡፡
- እንደወጡ የቀሩት ኢትዮጵያዊ (አ.አ 2006 ዓ.ም. ኤች ዋይ ማተሚያ ቤት) ዶ/ር ጌታቸው ተድላ በምድረ ሀንጋሪ (ቡዳፔስት ከተማ) የተዋወቋቸው፣ የአንድ ግለሰብ ኢትዮጵያዊ የአቶ ሥዩም ጌታቸው (ጎይቶም) ታሪካዊ ልብ ወለድ ነው፡፡ ልብ ወለድ ይባል እንጅ፣ ትረካው በእውነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ደራሲው ከአቶ ሥዩም ጋር የተዋወቁት ለድሕረ-ምረቃ ትምህርት ቡዳፔስት (ሀንጋሪ) በሔዱበት ወቅት እ.ኤ.አ በ1972 መጨረሻ ላይ ነው፡፡ አቶ ሥዩም በአገሪቱ የመጀመሪያ ጥቁር ሰው ስለሆኑ፣ መንግሥትም ሆነ የግል ኩባንያዎች አጋጣሚውን በመጠቀም ልዩ ልዩ ማስታወቂያዎች ሲያሠሩዋቸው ኑረዋል፡፡ በ1902 የተወለዱት አቶ ሥዩም፣ ቁመታቸው አጭር፣ አካለ ደልዳላ፣ ሲሄዱም ሆነ ሲቀመጡ በቀስታ፣ በጣም ቁጥብ፣ ሲያወሩ ለስለስ ብለው፣ ከምሳሌ ጋር መምከር የሚያዘወትሩ፣ ለትውልድ አገራቸው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው ናቸው፡፡ አውሮፓን ከረገጡበት ከ17 ዓመታቸው ጀምሮ ያዩትን፣ የሠሩትን፣ በቆዳቸው ቀለም ምክንያት የደረሰባቸውን ጥቃት፣ አልፎ አልፎም ስለ ፍቅረኞቻቸው ፈገግ እያሉ ያጫወቷቸውን መጽሐፉ ላይ መዝግበውታል፡፡ ይህን መጽሐፍ ጽፈው ካሳተሙት በኋላ፣ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕመምተኞች መርጃ ማዕከል መጽሐፉን ሸጠው እንዲጠቀሙበት አበርክተዋል፡፡
- ከትዝታ ጓዳ (አ.አ 2006 ዓ.ም. ኤች ዋይ ማተሚያ ቤት)ምንም እንኳን እንደ ልብ ወለድ ቢተረክም፣ በሰባት ምዕራፍ የተዋቀረው መጽሐፍ፣ የሰባቱም ባሕር ማዶ የሚኖሩ የትውልደ ኢትዮጵያ ሰዎች እውነተኛ ታሪክን ተደግፎ የተጻፈ ነው፡፡ መጽሐፉ ብዙዎቹ እንደሚያስቡት በውጭ አገር የሚኖረው ትውልደ ኢትዮጵያዊ (ዲያስፖራው) ‘ሁሉ በጄ፣ ሁሉ በደጄ’ ሳይሆን፣ በባዕድ አገር ብዙ መከራና ፈተና እንደሚጠብቃቸውና እንደሚፈታተናቸው ቁልጭ አድርጎ ያስረዳል፡፡ በሕይወት ውስጥ ደስታና ሐዘን መፈራረቃቸው አይቀሬ ነው፡፡ ያልታሰበ ፈተና ሲመጣ የሚቋቋሙና የሚታገሉ እንዳሉ ሁሉ፣ ቶሎ ተስፋ የሚቆርጡም መኖራቸውንም መጽሐፉ እያዝናና ያስረዳል፡፡ ይህ 354 ገጾች ያሉት መጽሐፍ፣ በ2006 ታትሞ ለሕዝብ ቀረበ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ይህንን ከትዝታ ጓዳ የሚለውንም መጽሐፍ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ ለኅትመት አብቅተው፣ ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕመምተኞች መርጃ ማዕከል መጽሐፉን ሸጠው እንዲጠቀሙበት አበርክተዋል፡፡
- ዕቅድ 27 (አ.አ. 2009 ዓ.ም. ፋር ኢስት ማተሚያ ቤት) ይህ መጽሐፍ ሙሉ ለሙሉ ልብ ወለድ ትረካ ነው፡፡ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ አንዲት ጀግና ሴት መፍጠር ፈልገው ፈጠሯት፡፡ ይህች ሴት ቆነጆ ነች፣ ትሁት ነች፣ ቂመኛ ነች፣ ያሰበችውን ከግብ ካላዳረሰች፣ ዕንቅልፍ በዐይኗ አይዞርም፡፡ ግቧን ለመምታት ብዙ ችግሮችን ስታሳልፍ፣ ከዚህ በኋላ ምን መጣ እያስባለ የሚነበብ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ነው፡፡
ሥዕላዊ መጽሐፎች
- ሥዕላዊ የፎቶግራፍ አልበም – Ethiopia the Beautiful (ውቢቷ ኢትዮጵያ) ይህ ሥዕላዊ መጽሐፍ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉ ወጭው ተሸፍኖ የታተመ ነው፡፡ (ዱባይ ሴንትራል ማተሚያ ቤት፣ 2009 ዓ.ም) በውጭው ዓለም ከአርባ ዓመታት በላይ የተቀመጡት ዶ/ር ጌታቸው ተድላ፣ ሁል ጊዜም ስለ ትውልድ አገራቸው ስለ ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ሀገሮች፣ በተለይም በምዕራብ አውሮፓና በአሜሪካን ሀገሮች፣ በጋዜጦቻቸው የሚጻፈው፣ በራዲዮኖቻቸው የሚነገረው፣ በቴሌቪዥኖቻቸው የሚታየው ሁሉ ስለ ድህነቷ ነው፡፡ ጦርነት፣ የተንኮታከቱ ቤቶችና መንገዶች፣ ድሆች መንገድ ላይ ሲለምኑ፣ ወይም የተጎሳቆሉ ውሾች በየመንደሩ ውስጥ ሲዞሩ ማስነበብና ማሳየት ነው፡፡ ይህን በድግግሞሽ ሲያሳዩ እንኳንስ የውጭ አገር ሰዎች ቀርቶ እኛንም ኢትዮጵያውያንን ክፉኛ አስፈርቶናል፣ አሳዝኖናልም ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያን በሙሉ ዞረው የጎበኙት ዶ/ር ጌታቸው፣ በጣም ብዙ የኢትዮጵያን ገፅታዎችና ውብ የአገሪቱን ምስል በፎቶግራፍ ቀርፀዋል፡፡ ስለዚህም ‘ልክ እንደ ሌሎቹ የባዕድ አገር ሰዎች ስለ አገራቸው ውበት እንደሚያቀርቡት ሁሉ፣ ለምንስ እኔ ስለ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የሥዕል መጻሕፍት ጋር የሚወዳደር አላሳትምም?’ በማለት ፎቶግራፎቹን በዓይነት በዓይነቱ እያደረጉ፣ ውብ ገጸ ምድሩን፣ ታሪካዊ ሥፍራዎችን፣ ልዩ ልዩ አራዊቶች፣ የግብርና ሥራዎችና ውጤቶች፣ መንደሮች፣ ዘመናዊ ከተሞችና ገበያዎች፣ ባህላዊ ምግቦች፣ የብሔር ብሔረ ሰብ ምስሎች፣ ወዘተርፈ መርጠው፣ ይመጥናሉ ብለው ያሰቧቸውን ከሦስት መቶ በላይ አስደናቂና ዐይን የሚስቡ ምስሎች አዘጋጁ፡፡ እላይ እንደተጠቀሰው፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉ ወጭው ተሸፍኖ ግሩም የሆነ የኢትዮጵያ ሥዕላዊ መጽሐፍ ለኅትመት በቃ፡፡
- አባባ ጃንሆይ (በህትመት ላይ) ይህ ሥዕላዊ መጽሐፍ በቀድሞው የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን አጭር የሕይወት ታሪክ በምስል በአጭሩ የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው፡፡ አፄ ቀ.ኃ.ሥ ከትውልድ ጀምሮ እስከ ነገሡበት፣ በጦርነቱ ምክንያት የስደት ኑሩዋቸው፣ ከነፃነት በኋላ ሀገሪቷን ወደ ሥልጣኔ በመምራት፣ ኢትዮጵያን ከጠላት ለማዳንና ድንበር ለማስጠበቅ ጦር ኃይሎችን እንዴት እንዳዘጋጁ፣ የውጭ ሀገር መንግሥታት መሪዎችን እየተቀበሉ ያስተናገዱትንና ንጉሠ ነገሥቱም ብዙ ሀገራትን እየጎበኙ ከውጭ ሀገር መንግሥታት ጋር የተወያዩትን፣ በተለይም የአፍሪካ አንድነትን ለማቋቋም ያረጉትን ትግል፣ ኢትዮጵያን ገለልተኞች ማኅበር እንዳስገቧት እና በመጨረሻም በወታደሩ የደርግ አስተዳደር ከዙፋናቸው መውረዳቸውን በምስል የሚገልጽ መጽሐፍ ነው፡፡
ለኅትመት የተዘጋጁ
- የማታ እንጀራ
- መንታ ነፍሶች
ዶ/ር ጌታቸው ተድላ አበበ ከወ/ሮ ፀሐይ አስፋው ሳንድሮስ ጋር አብሮ በመኖር፣ ሁለት ወንዶችና አንድ ሴት ልጅ አፍርተዋል፡፡ አራት የልጅ ልጆችም ለማየት በቅተዋል፡፡
መዝጊያ
ዶክተር ጌታቸው ተድላ አሁንም ያነባል፤ ይጽፋል፡፡ የጠንካራ እና የቀና ሰው ተምሳሌት ቢባል ይቀላል፡፡ ዶክተር ጌታቸው አረንጓዴ ስፍራ መሄድ ታላቅ ደስታን ይሰጠዋል፡፡ ቤቱ ሆኖ አትክልት ሲንከባከብ ደስ ይለዋል፡፡ ሰውን መርዳት ከምንም በላይ ያስደስተዋል፡፡ ነገሮችን አዋዝቶ ማቅረብን ተክኖበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ድምጹ የተመቸ ነው፡፡ ዘና ማድረግንም ተክኖበታል፡፡ ከሁሉ በላይ ዶክተር ጌታቸው ለእናት ሀገሩ ታላቅ ፍቅር አለው፡፡ ይህንን ፍቅሩንም በመጽሀፎቹ አሳይቷል፡፡ የጸሀፌ-ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የግል ማስተወሻ ታትሞ እንዲወጣ ትልቁን ድርሻ በማበርከቱ ታላቅ ደስታ ይሰማዋል፡፡ የአክሊሉ ነገር አይሆንለትም፡፡ ተናግሮ አይወጣለትም፡፡ ስለ እርሳቸው ሲተነትን ደግሞ ከሰነዶች ተነስቶ ነው፡፡ ከ1000 በላይ የሚጠጉ የአክሊሉ ሀብተወልድ ምስሎች ዶክተር ጌታቸው ተድላ ጋር ስካን ተደርገው ተቀምጠዋል፡፡
ምርምር ለሚያደርጉ ሰዎች ይለግሳል፡፡ ዶክተር ጌታቸው ተድላ ሀገር ቤት ከመጣበት ካለፉት 13 አመታት ጀምሮ ለበርካታ ሚድያዎች ቃለ-ምልልስ ሰጥቷል፡፡ በተለይ በሸገር ሬድዮ ከመአዛ ብሩ ጋር ያደረገው ጭውውት በበርካታ አድማጮች የሚታወስ ነው፡፡
ዶክተር ጌታቸው ተድላ ለምርምር ፤ ለድርሰት ፤ ለበጎ አድራጎት እንጂ ለወሬ ጊዜ የለውም፡፡ በርካታ የአለም ሀገራትን በማየቱ ሁለገብ የሆነ ሚዛናዊ የሆነ እውቀት ቀስሟል፡፡ ዶክተር ጌታቸው ከ32 አመታት በላይ በተባበሩት መንግስታት ሲሰራ በርካታ ገጠመኞችን አስተናግዷል፡፡ ይህንንም በ2 በጻፋቸው የግለ-ታሪክ መጽሀፎቹ ላይ አካቶታል፡፡ በተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አማካይነት በተሰራው የዘጋቢ ፊልምም ውስጥ ስለ ዶክተር ጌታቸው ተድላ ሌሎች ምን አሉ? ለሚለው አጥጋቢ መልስ ያገኛሉ፡፡ ዶክተር ጌታቸው ተድላ በተጨማሪም ዕውቅ የሆኑ የአፍሪካ ታዋቂ ሰዎች በተመዘገቡበት Africa Who is Who (1991) በሚለው ታላቁ መጽሐፍ ላይ ስሙ በታላቅ ክብር ሰፍሯል፡፡
ይህ ለኢትዮጵያ ታላቅ ኩራት የሆነው ሰው ሙሉ አቅሙን መጠቀም ብቻ ሳይሆን በጽኑ ፍቅር ስራውን የሚያከናውን በመሆኑ የነካው ሁሉ ይባረክለታል፡፡ ቤተሰባዊ ህይወቱን በመልካም ሁኔታ እየመራ የሚገኘው ዶክተር ጌታቸው ለዚህ ሁሉ ስላበቃው አምላኩን እግዚአብሄርን ያመሰግናል፡፡ እኛም የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች ዶክተር ጌታቸው ተድላ ለመጪው ትውልድ እንደ ጀግና ተደርጎ መቆጠር ያለበት ሰው መሆኑን እናምናለን፡፡ ይህ የዊኪፒዲያ ጽሁፍ ከዘመናት በኋላ ሲነበብ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ሰው ነበራት ተብሎ የዶክተር ጌታቸው ተድላ ስም በትልቁ እንዲጠራ እንፈልጋለን፡፡ ይህ ጽሁፍ በተዘጋጀበት ጊዜ ዶክተር ጌታቸው ለወራት ስዊድን ያቀና ሲሆን በሄደበት ሁሉ መልካሙን ሁሉ እንዲገጥመው እንመኛለን፡፡ / ይህ ጽሁፍ ዛሬ እሁድ ሀምሌ 4 2013 ከቀኑ 8 ሰአት ከ43 ተጽፎ የተፖሰተ ሲሆን ጽሁፉን ያጠናከረው ደግሞ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ነው፡፡/