ዳዊት አለሙ
ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ እስካሁን መስፈርቱን የሚያሟሉ ባለታሪኮች ግለ-ታሪካቸውን እየጻፉ እየላኩልን ነው፡፡ እርስዎም tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡
ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ6 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከስነ-ጽሁፍ ዘርፍ ዘርፍ ታሪኩ የሚቀርብለት ሰው ዳዊት አለሙ ይሆናል፡፡
ትውልድ ፤ ልጅነት እና ትምህርት
ዳዊት አለሙ ሰኔ 30 19 76 በመቱ ከተማ ተወለደ፡፡ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚያዉ መቱ ከተማ ተከታትሏል፡፡የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖ በትምህርት ቤቱ ሚኒ ሚዲያ ይሳተፍ ነበር፡፡ በ1994 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት ዩኒቨርሲት ገባ፡፡በዩኒቨርሲት ቆይታው በመቅረዝ የስነ ጽሁፍ ህብረት አባል በመሆን የተለያዩ የጽሁፍ ስራዎችን ለተማሪዎች ያቀርብ ነበር፡፡በኋላ ላይ በሬድዮ ጭምር የተተረኩት ሞቲ አባ ጆርጋ፤ሳምራዉ እና የመሳሰሉ ገጸ -ባህሪያት መነሻቸዉ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ነዉ፡፡
በዩኒቨርሲተው መድረክ ላይ ብዙ ሺህ ተማሪዎች በታደሙበት አዳራሽ እያሳቀ፤እያዝናና ደግሞም በሀዘን ስሜት ው ስጥ እየከተተ ስራውን ያቀርብ ነበር፡፡በመጨረሻም ” የአራቱ አመት የስነጽሁፍ ኮከብ” የሚል ሽልማት ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተበርክቶለታል ፡፡ አራተኛ አመት ሲደርስ አዲስ በተከፈተው በደቡብ ኤፍ ኤም ላይ ስራዎቹን በማቅረብ የጋዜጠኝነት ስራውን ገና በተማሪነቱ ዘመን ጀመረ፡፡በ1997 ከሀዋሳ ዪኒቨርሲቲ በዉጭ ቋንቋ እና ሥነጽሁፍ ከተመረቀ በኋላ የጋዜጠኝነት እና የስነ-ጽሁፍ ስራውን ቀጥሏል፡፡
የስራ አለምና ልቦለዶች
ከሀምሌ 1998 ጀምሮ በአንጋፋው የ ኢትዮጵያ ሬዲዮ በመቀጠር በርካታ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ትረካ፤አስደናቂ ታሪኮችን፤የጥያቄና መልስ ፤መጣጥፎችንና ትንታኔዎችን እያዘጋጀ በማቅረብ ከአድማጭ ሰፊ ተቀባይነትን ማግኘት ችሏል፡፡ ከአድማጮችም ብዙ ደብዳቤዎች ይደርሱት ነበር፡፡ ከጋዜጠኝነት ስራዉ ባሻገርም በርካታ የአጫጭር ልብ- ወለዶችን እራሱ እየደረሰ በኢትዮጵያ ሬድዮ፣በኤፍ ኤም 97.1፣በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተርኳል፡፡
ሀናን፤ሁለት ብር ካለህ ?፣ሳምራዉ ፣አዳኙ በአዳኟ ሲታደን(አቼቤ) ፣ያኔ ና ዛሬ ፣ምሳሮቹ ፣ጠባቧ ክፍል (ካሮሊና)፣ፕሮጀክቱ፣አይኖቿ ፣ያቺ ሌሊት ፣ለሊቲቷ ፣ የመጽሀፉ ረቂቅ ፣በርባን፣ስምኦንና ልደቱ፣ቅዱስ ሰይጣን፣ የሸረሪት ድር (በሰባት ክፍል በኤፍ ኤም 97.1 ላይ የተተረከ ነዉ)እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡አጫጭር ልብወለዶቹ ባልተጠበቀ አጨራረስ (Surprise Ending) የመጠናቀቅ ባህሪ አላቸው፡፡
ልቦለድ ድርሰት ማሳተም -የአውሎ ንፋስ ዳንኪረኞች
በንግስት መጽሄት ቅጽ 4 ቁጥር 43 ሀምሌ 2000 እትም ላይ እንደተናገረው ለመጀመሪያ ጊዜ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ ያነበበው ‹‹ብርቅርቅታ›› የተሰኘ መጽሀፍ ገና በልጅነቱ በንባብ ፍቅር እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡እንዲህ ሲልም ለመጽሄቷ ተናግሮ ነበር… ‹‹እኛ ቤት መጽሀፍ የተሸከመ አንድ ሼልፍ ነበር፡፡ ለነገሩ አሁንም እዚያ መቱ አለ …አንድ ቀን ዝም ብዬ አንድ መጽሀፍ አነሳሁ፡፡
ሰው ቤት ውስጥ አልነበረም፡፡ርእሱ ‹‹ብርቅርቅታ›› ይላል፡፡ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ የተተረጎመ የዳኒኤላ ሰቲል መጽሀፍ ነዉ፡፡እንደ ቀልድ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ያኔ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነኝ፡፡ቀስ በቀስ ስገፋ ታሪኩ ስሜቴን መያዝ ጀመረ፡፡ደስ እያለኝ አንብቤ ጨረስኩት፡፡ከዚያ በኋላ ከእነ ዘሩጣ ዘረጥራጣ የተረት መጽሀፎች ወጥቼ ወደ ትልልቆቹ ተሻገርኩ፡፡›› ብሎ ነበር፡፡
ዳዊት አለሙ በ2000 አ.ም ‹‹የአውሎ ንፋስ ዳንኪረኞች›› የተሰኘ ረዥም ልብወለድ ለህትመት አብቋቷል፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተሰሩ ጥናቶች መጽሀፉ አድናቆትን አግኝቷል፡፡ለምሳሌ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገብሩ ወልዱ በሰራዉ “Equilibrium analysis of the novel Yeawlo Nefas Dankiregnoch” በሚል የመመረቂያ ጽሁፍ በሴራ አወቃቀሩ በሀገሪቱ የስነ- ጽሁፍ ጉዞ አዲስ ቅርጽ ይዞ መምጣቱን ጽፏል፡፡ዘልማዳዊ የሴራ አወቃቀር በሚከተሉና ዘመናዊ በሆኑት መሀል ያለዉን ልዩነት ጥናት አቅራቢው እንዲህ ሲል ገልጾታል….
It is wise to remark that there exists a big difference between the traditional writers and the modernists Dawit is the case in point here concerning their equilibrium organization .In other words ,the equilibrium structuring process that most of the traditional writers used is traditional type, which develops through exposition ,rising action, climax ,falling action and resolution. Abbie Gubegna’s Defiance and Bealu Girma’s Oromay are examples of such plot arrangement. In this case, the book ye awlo nefas dankiregnoch is, constructed differently and seems against this rule.
ጎግል ጋዜጣ በነሀሴ 9 ቀን 2000 አ.ም
አዲስ ስልት ያስተዋወቀ ልቦለድ
የልብ- ወለዱ የሴራ አወቃቀር ታሪኩን ከገጽ ገጽ ሳንደክም እንድንከታተል ያደርገናል፡፡እያንዳንዱ ምእራፍ አጠር ተደርጎ በጥናት የተዋቀረ በመሆኑ ‹‹ልብ አንጠልጣይ›› የምንለውን የልብ ወለድ ዘር በማሟላት ና የታሪኩን ፍሰት በሚገባ መስመር እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ለጥ ብሎ ከ ‹‹ሀ›› ወደ ‹‹ፐ››የሚሄደዉን የተለመደዉን የታሪክ አወቃቀር በመተዉ ደራሲዉ ዳዊት ከ‹‹ፐ›› ወደ ‹‹ሀ›› በመምጣት አንዳቸዉ በመገለባበጥ መስመር ሳይስት በሚገባ እንዲነበብ ያደርገዋል፡፡የደራሲዉ የቋንቋ አጠቃቀም ደግሞ የመጽሀፉ ሌላዉ ዉበት ነዉ፡፡
አጫጭር ልቦለዶች በሲዲ
ዳዊት ለ10 አመት ቀደም ብሎ በ2002 ‹‹ለዚያች ከተማ›› የሚል የአጫጭር ልብወለዶች ስብስብ በሲዲ አቅርቧል፡፡አይኖቿ፣ሌሊቲቷ፣በዩኒቨርሲቲ መድረክ ላይ የተረከዉ ያልተነበቡ ገጸ ባህሪያት (ሳምራዉ) የሚሉ አጫጭር ልብወለዶችና ለዚያች ከተማ የተሰኘ መጣጥፍ ተካተዉበታል፡፡መጋቢት 2001 በብእር ስም በተጻፈ መጽሀፍ ተጠርጥሮ ማእከላዊ እስር ቤት ለሁለት ሳምንት በያኔዉ መንግስት ታስሯል፡፡ምንም ሊያስከስሰዉ የሚችል ነገር ባለመገኘቱና በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት ግን ከሁለት ሳምንት በኋላ በነጻ ተለቋል፡፡
የስራ መሪ
ከግንቦት 2003 ጀምሮ ደግሞ በ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እየሰራ ይገኛል፡የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶቸን ፣አለም አቀፍ ዜናዎች የሚተነተኑበት ዳሰሳ ፣አነጋጋሪና ያልተሰሙ የመሪዎችን ታሪክ ፣ፖለቲካዊ ትንተናዎችን ትረካዎችን በማዘጋጀትና ከማቅረብ ባሻገር አርታኢና ዋና አዘጋጅ በመሆን በፋና ብሮድካስቲንግ እያገለገለ ይገኛል፡፡ብዙ ወጣት ጋዜጠኞችም እርሱን በመከተል ለሙያው ፍቅር እንዳደረባቸዉ ይናገራሉ፡፡በ2007 የማስተርስ ድግሪው ን በሶሻል ዎርክ ሰርቷል፡፡
ቤተሰባዊ ሁኔታ
ዳዊት አለሙ በ2010 ጋብቻ መስርቶ አንዲት ሴት ልጅ አፍርቷል፡፡
ማጣቀሻዎች
- ንግሥት መጽሄት (2000) ፡፡ቅጽ4 ቁጥር43፡፡ አዲስአበባ፡፡
- ጎጎል ጋዜጣ (2000)፡፡ቅጽ2 ቁጥር 045፡፡አዲስ አበባ፡፡
- አዲስ አዲማስ ጋዜጣ (2001) ፡፡ቅጽ9 ቁጥር 494፡፡አዲስ አበባ፡፡
- መኮነን ሞጎሴ(2006)፡፡ የአስተናጋጁ ማስታወሻ፡፡አዲስአበባ፡:
- Woldu.G(2015).Equilibrium analysis of the novel ye awlo nefas dankiregnhoch; Gonder University
- www.socepp.de (2009); Radio Reporter Dawit Alemu Illegally Jailed; Canada
- ኤፍ ኤም 97.1፡፡ የሳምንቱ እንግዳ፡፡አዲስአበባ፡፡
- ዋጌታ ኤፍ ኤም 96.3፡፡የጥበባት እንግዳ፡፡ሶዶ፡፡
- ኢቢሲ፡፡የጥበብ ዳሰሳ፡፡አዲስአበባ፡