ዳንኤል አያሌው ካሳ

ዳንኤል አያሌው ካሳ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በመዝናኛው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችን አጭር ግለ-ታሪክ ባለፉት 2 ወራት እያወጣ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አሁን ደግሞ ከ1982-1995  በመዝናኛ እና በሬድዮ ድራማ ዘርፍ የበኩሉን ድርሻ ስለተወጣው ስለ ዳንኤል አያሌው ካሳ እናቀርባለን፡፡ ሌሎች ባለሙያዎችንም በመጠቆም ተባበሩን፡፡ tewedajemedia@gmail.com 

ትውልድ እና እድገት

ዳንኤል አያሌው ካሳ፣  መስከረም 19 ቀን 1957  ነበር የተወለደው፡፡  አባቱ አቶ አያሌው ካሳ እናቱ ወይዘሮ  ዘነበች ወልዴ  ይባላሉ፡፡ የተወለደውም በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ ዳንኤል የ7ወር ህጻን በነበረበት ጊዜ ነበር – አባቱን ያጣው :: በዚህም ምክንያት ከአባቱ ቤተሰቦች አንዷ ወይዘሮ ድንኳኔ ፋንታዬ ወስደው አሳድገውታል፡፡ አባቱን ባያገኝም – ባለሁለት እናት ሆኖ ነው ያደገው፡፡

እንደማንኛውም የጊዜው ህጻናት በአካባቢው በሚገኝ የቄስ ትምህርት ቤት ነበር -በቅድሚያ ፊደል የቆጠረው ::ከቄስ ትምህርት ቤት በኋላ ከመኖሪያው ብዙ ሳይርቅ በዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ነበር -መደበኛውን ትምህርት የጀመረው -እስከ 12ኛ ክፍልም የቀጠለው ፡፡

ቴአትር ጥበባት

በ1978 አ.ም  መጀመሪያም ላይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የቲያትር ጥበባት የትምህርት ክፍልን ተቀላቅሏል  ፡፡ በዚህ ክፍል ነበር ታላላቆቹን መምህራኑን ያገኘው  ፤ መንግስቱ ለማ፣ ተስፋዬ ገሰሰ፣ ደበበ ሰይፉን  እንዲሁም በወቅቱ ወጣት መምህራን የነበሩት ማንያዘዋል እንደሻው ፣በላይነህ አቡኔ፣ አቦነህ አሻግሬ ፣ ፍስሃ በላይ ይማም እንዲሁም የውጭ ሃገር አስተማሪዎችም ነበሩት ። 

በተማሪነት ዘመኑ በተለይ በትወና ላይ የተሳካለት እንደነበር የሚመሰክሩለት አሉ    የኪዩፒድ ቀስት  የሚባል አንድ በማህበረሳዊ ጥናት ላይ የተመረኮዘ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ህይወትን የተመለከተ ድራማ ላይ ከመሪ ተዋንያን አንዱ ነበር ፡፡   አባትየው    የስዊዲናዊው ኦገስት ስትሪንበሪ አዛማች ትርጉም ተውኔት ላይም የተጫወተው ይታወሳል ። ለተመልካች ባይቀርብም የኒኮላይ ጎጎል  ፟ዋናው ተቆጣጣሪ  ትያትር ላይም ተጫውቷል  ። በዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ ተርም ላይ የማክሲም ጎርኪ ፟ፔቲ ቡርዥዋ ፟ ሌላው የተሳካ ትወና ያደረገበት ነበር::

ኢትዮጵያ ሬድዮ

በ1981 መጨረሻ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቆ በተከታዩ አመት መጀመሪያ ላይ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ሬድዮ ተቀጠረ በኢትዮጵያ ሬድዮ ስቱዲዮ ስልጠና ላይበሬዲዮ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በታዋቂው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሃይለማሪያም ስር በዜናና መዋእለ ዜና ዋና ክፍል ውስጥ መሰረታዊ የሬድዮ ጋዜጠኝነት ስልጠናና ልምምድ ለማድረግ ችሏል፡፡   ከዚህ ጊዜ በኋላም በተለያዩ ጊዜያት  በሬዲዮ ውስጥም ሆነ ውጪ የተለያዩ ስልጠናዎችን አግኝቷል፡፡ከሃገር ውጭም በጀርመን ድምጽ በኮሎኝ ለ10 ወራት በተግባር ልምምድ ጭምር ያደረገው ስልጠና በጣም ጠቃሚ እንደነበር ደጋግሞ ያነሳዋል::

ዳንኤል ከጌታቸው ደስታ ጋር ዶቼ ቬሌ በቀጥታ ስርጭት በ1986 ግድም የሰራ ሲሆን ይህም ምስል ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብሮ ወጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ ሬድዮ የአማርኛ ፕሮግራም ክፍል ከ1982 አንስቶ ስራ ለቆ ወደ ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር እስከገባበት 1995 ድረስ ከፕሮግራም አስፈጻሚነት አንስቶ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ሲያዘጋጅና በኤዲተርነትም ሲመራ ነበር፡፡

የተለያዩ የሙዚቃ ፕሮግራሞችን በየሳምንቱ አቀናብሯል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ፦

  • ሰኞ ምሽት ቆየት ያሉ የአማርኛ ሙዚቃዎች
  • ቅዳሜ ምሽት የውጭ ሙዚቃዎች
  • እሁድ ምሽት የሃገር ውስጥና የውጭ ለስላሳ ሙዚቃዎችና የዘፈን ምርጫ አዘጋጅም ነበር፡፡

የወጣቶች ፕሮግራም አዘጋጅና ኤዲተርም ሆኖ አገልግሏል፡፡ ዳንኤል የወጣቶች ፕሮግራም አመታዊ በአል ሲያከብር ከአዘጋጆቹና ከቴክኒክ ባለሙያዎቹ ጋር  በአንድ ላይ በ1985 የተነሱትን ምስል ስንመለከት ያንን ዘመን ወደ ኋላ በትዝታ  እንድናይ የሚያደርገን ነው፡፡ ይህ ፎቶ 28 አመት ወደ ኋላ የሚወስደን ሲሆን በምስሉ ላይም የዛን ጊዜዎቹን  ስመጥሮች እናገኛለን፡፡

አስካለ ተስፋዬ፣ደረጀ ሀይሌ ፤ ብርሀኑ ገብረማሪያምና ዘውዱ ግርማ  በምስሉ ላይ ተቀምጠው የሚታዩ ሲሆኑ  ቆመው ያሉት ደግሞ ቴክኒሻን ሳህሉ በቀለ ፣ ተካ ወልደሀዋሪያት/ የቴክኒክ ሱፐር ቫይዘር ፤ እንዳልካቸው ፈቃደ ፤ ዮናስ ኪቲላና ባለታሪኩ ዳንኤል አያሌው ናቸው፡፡  በዚህ ምስል ላይ ያሉ በተለይ ባህር ማዶ ያሉትንና ሀገር ውስጥ ሆነው  የቀድሞ ትዝታ ሊያወጉን የሚችሉትን ብትጠቁሙን ደስታውን አንችለውም ፡፡

ዳንኤል ፣ የኪነ- ጥበባት ምሽት ፕሮግራም ከመጀመሪያው እስከ ጣቢያው ስንብት ድረስ በፕሮግራሙ አዘጋጅነትና መሪነት የሰራበት ነው፡፡ የኪነ-ጥበባት ምሽት በጣቢያው ከቆዩ ፕሮግራሞች አንዱ ሲሆን በቀደመው ጊዜ ብዙ የሃገሪቱ ታላላቅ የጥበብ ሰዎች   የተሳተፉበት ተናፋቂ ፕሮግራም ነበር፡፡ ዳንኤልም ወደዚህ ፕሮግራም የመጣው ፈልጎ ነው፡፡ 1984 ዓም መጀመሪያ ላይ ፕሮግራሙን የመምራት ዕድል እንዳገኘ የመጀመርያ ተግባሩ የነበረው ከወቅቱ አዘጋጆች ጋር በመሆን ፕሮግራሙ በኪነጥበባት ጉዳዮች ዙርያ ብቻ እንዲያተኩር የሚያስችለውን አቅጣጫ ማመላከት ነበር  ፡፡ ታላላቅ የኪነጥበብ ሰዎች በተለይም ኢትዮጵያውያን ከያንያን  ይዘከሩበታል- ይደነቁበታል  ፤ በተቻለ መጠን ሁሉም አይነት ጥበባት ይስተናገዱበታል፤፡ ኪነጥበባዊ ሃገር አቀፍ ጉዳዮች ይሸፈናሉ፡፡

ዳንኤል ፤  በዚህም መሰረት ነበር ፕሮግራሙን ሲያዘጋጅና ሲመራ የነበረው  ። እጅግ የበዙ ባለሙያዎች የፕሮግራሙ እንግዳ ነበሩ -ደራሲያን አዘጋጆች ተዋንያን ሙዚቀኞች ሰአሊያን ኪነህንጻ ባለሞያ ወዘተርፈ አነጋግሯል፡፡ ስራቸውንም አስተዋውቋል፡፡ እንዲሁም ታላላቅ ኪነጥበብ ነክ እንቅስቃሴዎች በየተካሄዱበት እየተገኘ ዘግቧል -በፕሮግራሞቹ አቀናብሮአል :- ለመጠቃቀስ ያህል

የባህል ፖሊሲው ከቀረጻው አንስቶ እስከ ጸደቀበት ድረስ ፣ የስነጥበባትና የመገናኛ ብዙሃን የሽልማት ድርጅት በተከታታይ ከተካሄዱት ውይይቶች አንስቶ እስከ ሽልማቱ ድረስ ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ ጥናት ፋካልቲ አመታዊ ጉባኤ ዳሰሳ ፣የተለያዩ የግጥም ምሽቶች ፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ፣ የስዕል ኤግዚቢሽኖች ፣ የትያትርና የመጻህፍት ምረቃዎችና የመሳሰሉት የፕሮግራሙ  ርዕሰ ጉዳዮች  ነበሩ ።

ከዚህ ሌላ አስተዋጽኦ ያደረገበት  የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም ነበር ። እዚህም የፕሮግራሙ አዘጋጅና ኤዲተር ነበር ። የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም የብዙ ወጣቶችን አይን የገለጠ ሲሆን የአጭር ልብወለድ ትረካ፣ መጣጥፎች (ወጥና ትርጉም)፣ግጥሞች፣ጭውውቶችና ድራማዎች የሚቀርቡበት አዝናኝ ፕሮግራም ነው ። 

የቅዳሜ መዝናኛ

የቅዳሜ መዝናኛ፣ በአድማጩም ዘንድ በጣም ተናፋቂ ነበር ። ለዚህ እንደማስረጃ ሊሆን የሚችል አንድ የበጎ ፈቃደኞች ኪዳን የተባለ የሽልማት ድርጅት የህዝብ ድምጽ አሰባስቦ የአመቱ ምርጦች ሽልማት በ1994 ዓ. ም በዋቢሸበሌ ሆቴል ባካሄደበት ጊዜ የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም የዓመቱ ምርጥ መዝናኛ ተብሎ ተመርጦ ነበር ።ከአዘጋጆቹ ጋር በመሆን ዋንጫውን የተቀበለው ዳንኤል ነበር።

እርግጥ የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም  የተሳታፊዎች ፕሮግራም ቢባል ስህተት አይሆንም ።  እጅግ ብዙዎች ያላቸውን ይዘው  ለመሳተፍ በየሳምንቱ ይቀርባሉ- በነጻ ። ትንሽም ቢሆን ክፍያ የነበረው ድራማው ነው – እሱም ቢሆን ከታክሲ የሚያልፍ አልነበረም ። የፕሮግራሙ አዘጋጆች የሚቀርቡ ዝግጅቶችን (ጽሁፎችን )የመምረጥ የመቅረጽና አቀናብሮ ለህዝብ የማድረስ ውክቢያ ውስጥ ነው ስራቸውን የሚያከናውኑት ። ለፕሮግራሙ ከሚደርሱት ዝግጅቶች ብዛት አንጻር ፈጣን ውሳኔዎች ይጠይቃሉ፡፡ በተለይም ዳንኤል ድራማው ላይ ዋና ትኩረቱን አድርጎ ነበር ።

የሬዲዮ ድራማ ዝግጅት የሚጀምረው ለፕሮግራሙ የሚሆን ድራማ ከመምረጥ ነው ፡፡ከባዱና ጊዜ የሚወስደውም  ይህ እንደሆነ ዳንኤል ይገልጻል። በጣም የበዛ የተውኔት ጽሁፍ ይቀርባል ።ያልተመረጡትን  መመለስ አታካች ነበር ።የኤዲቶርያል ፖሊሲውም አንዱ መመዘኛ ነበር ።በጣም አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ተውኔቶቹን ታይፕ ማድረግ/መተየብ/ አይቻልም ነበር ።

ከዚህ ጊዜ ቀጥሎ ተዋናይ መመደብ ይከተላል፡፡ ከዚያ በፊት ከነበረው በተለየ ሁኔታ በየድራማው ተዋናይ እየለዋወጡ ማቅረብ ተጀምሯል፡፡ የተዋናይ መረጣ አንዱ ፈተና ነበር፡፡  እንደሚታወቀው የራዲዮ ድራማ ይደመጣል እንጂ አይታይም፡፡ ስለዚህም ድምጽ ወሳኝ ነው የአንዱ ድምጽ ከሌላው በጉልህ ተለይቶ የሚታወቅ መሆን አለበት ።ጥሩ ማንበብ የቻለ ሁሉ የራዲዮ ድራማ ተዋናይ አይሆንም፡፡

ራድዮ ድራማ ለአድማጩ ሳቢ ካልሆነ ተከታታይ አያገኝም ብቻ ሳይሆን ሰዉ ሬድዮኑን ሊዘጋ ወይም ጣቢያ ሊለውጥ ይችላል፡፡ ስለዚህም ነው የአዘጋጁ ሃላፊነት ትልቅ የሚሆነው ።የድራማውን ዋና ጭብጥና እንዲሁም እያንዳንዱ ተዋናይ የሚጫወተውን ገጸ -ባህሪይ ጊዜ ወስዶ ማጥናት ባለመቻሉ የተነሳ   ቢያንስ አንድ ጊዜ ከቀረጻ በፊት በሚደረገው  ልምምድ  አዘጋጁ የመግለጽ የማብራራት ሃላፊነት አለበት ። እናም ካለእረፍት በየሳምንቱ በዚህ መንገድ ነበር ድራማ የሚዘጋጀው ቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም በአንድ ክፍል ወይም እስከአራት ክፍል የሚደርሱ ድራማዎች ነበሩ የሚቀርቡበት ።ይህ በዚህ እንዳለ እሁድ ጠዋት የሬድዮ ፕሮግራም ላይም ያሉትን ረጅም ተከታታይ ድራማዎች በተደራቢነት እንዲያዘጋጅ ሆኗል፡፡

እዚህ ደግሞ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ የነበሩትን እንደ ጥንዶቹ ፣የማእበል ዋናተኞች የልደት ጧፍ የመሳሰሉት ይታወሳሉ።ዳንኤል ካዘጋጃቸው የሬድዮ ድራማዎች መካከል በአድማጭ ዘንድ የሚታወቀው  የልደት ጧፍ ፤ እንዲሁም የማእበል ዋናተኞች ይጠቀሳሉ፡፡

የቀን ቅኝት-አዘጋጅ 

ዳንኤል በ1994  ዓም መጨረሻ ከኢትዮጵያ ራድዮ ተሰናብቶ የራድዮ ድራማን ይሁነኝ ብሎ ለህብረተሰብ ማስተማርያነት ሊያውል የተቋቋመው መንግስታዊ ያልሆነው ድርጅት Population Media Center የአማርኛ ራድዮ ድራማ አዘጋጅ ሆኖ ተቀጠረ ። በጊዜው ባነሳው ጭብጥ ፣ባካሄደው ጥናት ፣በተሳታፊ ብዛት/ በርካታ ደራሲያንና ተዋንያን /አጥኚ ባለሙያ፣ ጸሃፊ ሁሉ ሳይቀር የተሟላለት መሰረቱን አሜሪካ ያደረገው መስርያ ቤት ለሃገራችንም ቢሆን የመጀመርያውን ረጂም ድራማ የቀን ቅኝትን ያስመረቀው በትልቅ ደረጃ ነበር፡፡

የቀን ቅኝት ድራማ በሳምንት 2 ጊዜ በኢትዮጵያ ራዲዮ እንዲሁም በFM 97.1 ሌላ መግቢያ ተሰርቶለት ይተላለፍ ነበር፡፡ ይህም በአይነቱ አዲስ ነበር፡፡ የአድማጩም ከፍተኛ ሁኔታ መጨመር መስርያ ቤቱ ከሚደርሰው የደብዳቤ ጎርፍ መረዳት ይቻላል ። የሆነ ሆኖ   አዘጋጁ ዳንኤል አያሌው አንድ ዓመት ያህል ከሰራ በኋላ በግል ምክንያት ስራውን ለቆ ስዊድን ኑሮውን አድርጓል ። ዳንኤል በአሁኑ ሰአት መኖሪያውን በስዊድን ጉተንበርግ ያደረገ ሲሆን ቤተሰባዊ ሁኔታውን  በተመለከተ ባለትዳር እና የ 2 ልጆች አባት ነው፡፡

ዳንኤል በሌሎች ሰዎች እይታ…

ዳንኤል በቅዳሜ መዝናኛ እና በሬድዮ ድራማ አዘጋጅነቱ ብዙዎችን ያፈራ ፤ ያበቃ እንዲሁም   አንዳንድ የጥበብ ሰዎችም እንዲያድጉ ዋና ምክንያት ሆኗል፡፡ በአሁኑ ሰአት የራሷን ታዛ የተሰኘ የሬድዮ ፕሮግራም እየሰራች የምትገኘው ጋዜጠኛ ትእግስት በጋሻው ገና ታዳጊ በነበረች ጊዜ ቅዳሜ መዝናኛ ላይ ትሳተፍ በነበረበት ጊዜ ዳንኤል እንድትጽፍ ብሎም በሬድዮ ላይ ተሳትፎ እንድታደርግ ያበረታታት ነበር፡፡ ያኔ በቅዳሜ መዝናኛ ላይ ብዙ ወጣቶች ዳንኤል ጋር ጽሁፍ ይዘው ይመጡ ነበር፡፡ ታዲያ ዳንኤል ትእግስትና ጓደኞቿንም  አይዟችሁ ፤ አትፍሩ እያለ በማደፋፈር ጽሁፋቸውን አየር ላይ ያውል ነበር፡፡  በዚህም  ትእግስት የማልረሳው ታላቅ ባለውለታ ነው ስትል ምስጋናዋን ማቅረብ ትሻለች፡፡  ሌላዋ የዳንኤል አቅም ትልቅ ነው ስትል ሀሳብ የሰነዘረችው አርቲስት ሀረገወይን አሰፋ ናት፡፡ ሀረገወይን በቀን ቅኝት ተከታታይ የሬድዮ ድራማ ላይ ስትተውን የዳንኤልን ልዩ የዝግጅት ብቃት አይታለች፡፡ ያንን ሁሉ ሰው አስተባብሮ 2 አመት የቆየ ድራማን መስራት የዳንኤልን ልዩ ክህሎት ያሳያል ስትል ሀረገወይን ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡

ስለ ዳንኤል አያሌው -ሰአዳ መሀመድ ከተናገረችው…….

‹‹……….በ1990/91 በኢትዮጵያ ሬድዮ ቅዳሜ መዝናኛ  ድራማዎች በማቀርብበት ወቅት አዘጋጅ የነበረው ዳንኤል አያሌው ነበር። “ጥልልፎሽ፣ ያበቃ ህልም ያልተደፈነ ጉድጓድ፣ ሶስቱ መስኮቶች እና መክሊት ” የተሰኙ የድራማ ስራዎችን አዘጋጅቷል። ዳንኤል ከአዘጋጅነቱም በላይ የድራማ ፅሁፎቼን ገምግሞ የሚያያቸውን ችግሮች እንዳሻሽል አስተያየቱን በመስጠት ያግዘኝ ነበር። በተለይ ድራማ ፅሁፎች ላይ የምጠቀማቸውን ረጃጅም ቃለ -ተውኔቶች በአጭርና ቀለል ባለ ቋንቋ እንድፅፍ ደጋግሞ ይነግረኝ ነበር። በተጨማሪም በ30 ደቂቃ መተላለፍ ያለበትን ስክሪፕት መጥኜ  እየተቸገርኩ እስከ 40 ደቂቃ አደርሰው ስለነበር በአንድ ወቅት ” ስክሪፕትና ዲያሎግን በሚፈለገው መጠን መጥነሽ ፃፊ እንጂ ሰአዳ! ሌላ ግዜ አትፅፌም እንዴ!” የሚል አስተያየት ሰጥቶኝ ነበር።  ይህ የዳንኤል አስተያየት ዛሬም ድረስ ድራማ ስፅፍ የስክሪፕት ርዝመትንና የዲያሎግ መመጠንን እንዳስብበት አድርጎኛል።

ዳንኤል ስክሪፕት ከማቅናት አንስቶ የድራማ ርዕስ ለተውኔቱ ካልመጠነ ርዕሱን እንድቀይር ያደርግ ነበር። በአንድ ወቅት  አንድ የድራማ ፅሁፍ ሳስረክበው  ርዕሱን አይቶ እንድቀይረው ጠየቀኝ። በወቅቱ ምንም ርዕስ ሊመጣልኝ ስላልቻለ ” ምንም ርዕስ አልመጣልኝም”  አልኩት። ወዲያው ” መክሊት የሚለውን ርዕስ ልስጠው ይስማማሻል? ” አለኝ። ተስማማሁ ። ድራማው ተቀርፆ ሲተላለፍ ርዕሱ መክሊት መሆኑ ተገቢ እንደሆነ ተረዳሁ።  ዳንኤል አያሌው ጀማሪ ፀሐፊ ሆኜ ያገኘሁት ጎበዝ አዘጋጅና መልካም መምህር ነበር።  ዳንኤልን በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ።     

መዝጊያ

ትናንት ለሀገራቸው የሰሩ ዛሬ መታወስ አለባቸው፡፡ በህይወት እያሉ ያበረከቱት በዝርዝር እየተነገረ ታሪክ ሊያወሳቸው ይገባል፡፡ ዳንኤል አያሌው ፣ ለ 14 አመታት በቆየበት ሙያ አቅሙን ሳይቆጥብ ስራው እና ስራው ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥቶ ደከመኝ ሳይል ሰርቷል፡፡ ለእርሱ ብዙ የሰራ ላይመስለው ይችላል፡፡ ነገር ግን በ1980ዎቹና 1990ዎቹ በመዝናኛው ዘርፍ የተሳተፉ ሰዎችን ስናይ ዳንኤል የእነርሱ አቅም ሳይቆጠብ እንዲወጣ ማድረጉን እናስተውላለን፡፡ ብዙ የሰሩ ሰዎች  በሚረሱበት እና እከሌ ግን የት ነው ያለው? በሚባልበት ሀገር ዳንኤል አያሌውን ስናቀርብ  ስለሚገባው እና ስለሚችል ነው፡፡ የእናት ሀገር ፍቅሩ ታላቅ እንደሆነ የሚናገረው ዳንኤል ዛሬም የጥበብ ፍቅሩ ውስጡ እንዳለ ነው፡፡ ወቅትና ሁኔታዎች ሲመቻቹ የዳንኤልን የጥበብ ስራ  ማግኘታችን አይቀርም፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች የዳንኤልን ታሪክ  በዚህ መልኩ ስናወጣ መጪው ትውልድና አብረው የሰሩትም እንዲያውቁትና እንዲያከብሩት እንፈልጋለን፡፡ ዳንኤል ባለበት ስዊድን እንዲቀናውና ለጥበቡም አንድ ነገር እንዲያበረክት ምኞታችን ነው፡፡ / ይህ ጽሁፍ ዛሬ ሰኔ 30 2013 የተጻፈ ሲሆን ጽሁፉም የተጠናከረው በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ሲሆን ዳንኤልም ከስዊድን ሆኖ ያለፈበትን ታሪክ ተናግሯል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *