ደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሰራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡

ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ  ደስታ ነው፡፡ ደራሲ  ፍቅረማርቆስ ደስታ ከቡስካ በስተጀርባ  በተሰኘ መፅሃፍ  ይታወቃል ። ዕዝራ  እጅጉ እና ሞሊቶ ኤሊያስ ታሪኩን አጠናክረውታል።

                 ትውልድ እና እድገት

ፍቅረማርቆስ ከህክምና ባለሞያ አባቱ አቶ  ደስታ የሻነው እና ከእናቱ ሽጉልትሽ አለማሁ በወርሃ ጥቅምት 1957 ዓ.ም በባህርዳር ተወለደ።

በልጅነቱ የማያውቀውን አዲስ ነገር ሁሉ ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት የነበረው ሲሆን እድሜው ከፍ ሲልም ይኼው ፍላጎቱ አብሮ እያደገ ሄደ።

ፍቅረማርቆስ በ1980ዎቹ መጀመሪያ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመግባት በኬሚስትሪ  የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።

                   የስራ ህይወት

ደራሲ ፍቅረማርቆስ ከዩኒቨርስቲ ከወጣ በኋላ በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል ወደምትገኝው ደቡብ ኦሞ ዞን በማቅናት በጂንካ ከተማ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር በመሆን የማስተማር ስራውን ጀመረ። በደቡብ ኦሞ በነበረው ቆይታ በዞኑ በሚገኙ 16 ብሄረሰቦች ቋንቋ፣አለባበስ፣አመጋገብ፣ባህላዊ ዳኝነት፣ሙዚቃ እና አፈታሪክ ተማረከ።  ይኼኔ ነበር ያየውን እና የሰማውን ድንቅ ባህል  በጥልቀት ለማጥናት እና በፅሁፍ ለማስፈር የወሰነው። ፍቅረማርቆስ  ለሚኖርበት አከባቢ ይቀርብ የነበረው የሀመር ብሄረሰብ ስለነበር ከመምህርነት ሙያው ጎንለጎን የሀመርን ህዝብ ባህል፣ቋንቋ፣ታሪክ እና ትውፊት በማጥናት ያገኛቸውን ውጤቶች እንደ ግብዓት በመጠቀም ኢትኖግራፊያዊ ፅሁፎችን መከተብ ጀመረ። 

የመጀመሪያ መፅሐፍ -ከቡስካ በስተጀርባ

ከደቡብ ኦሞዎች ምድር በተማረከበት ውብ ባህል የከሸነው የመጀመሪያ ድርሰቱ የሆነውን “ከቡስካ በስተጀርባ”ን 1987 ዓ.ም ለአንባቢያን አደረሰ። “ከቡስካው በስተጀርባ” ልቦለዳዊ ድርሰት ብቻ አልነበረም።የባህል እና የተፈጥሮ ህያውነት የተከተበበት ዘመን ተሻጋሪ ቅርስም ጭምር ሆነ። ይህንንም ስራውን ያነበቡ ኢትዮጵያዊያን በታሪክ ፍሰቱ እና በሀመሮች ባህል ተማረኩ።

በአንትሮፖሎጂ እና ታሪክ ጥናት ዘርፍ የተሰማሩ ምሁራን አካባቢውን እንዲያጠኑ መንገድ ከፈተላቸው።ወደ አካባቢው ተጉዘው በልቦለዳዊ ታሪኩ ውስጥ የተገለፁ መልክአምድራዊ መልኮችንና ባህሎችን ከተመለከቱ በኋላ  አድናቆታቸውን ችረውታል። አንዳንዶቹም በዚያ ዘመን በነበሩ ጋዜጣዎች እና መፅሄቶች ላይ መፅሀፉን በሚመለከት የተለያዩ ሂስ እና አስተያየታቸውን ፅፈውበታል። በሬድዮም ለመተረክ በቅቷል።

“ከቡስካው በስተጀርባ” በ1988 ዓ.ም በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ ስር በሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም “ፍኩይ”የተሰኘ ሽልማትን ማግኘት ችሏል። 

ዘመን አይሽሬዎቹ “ኢቫንጋዲ”እና ተከታዮቹ

ደራሲ ፍቅረማርቆስ ከዚህ በኋላ ነበር በ1990 ዓ.ም ከህዝብ ጋር በደንብ ያስተዋወቀውን ፣በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፈውንና የርሱን “Master piece” የሆነውን “ኢቫንጋዲ” የተሰኘውን መፅሀፉን ለህዝቡ ማድረስ የቻለው። 

በተከታታይ አመታትም “የዘርሲዎች ፍቅር፣ አቻሜ እና የንስር አይን የተሰኙ ልቦለዳዊ መፅሀፍትን ለንባብ ማብቃት ችሏል።

ፍቅረማርቆስ በ1995 ዓ.ም ገደማ በደረሳቸው አምስቱ መፅሀፍት ውስጥ የተገለፁ ባህል እና ታሪኮችን ያካተተ እና ለውጭ ሀገር አንባቢያን  በሚገባ መልኩ ገላጭ ሀሳቦችን አካቶ ሲያበቃ መፅሀፉን “Land of the yellow bull” የሚል ስያሜ ሰጥቶት  ለአንባቢያን አቀረበ።ይህም ሀገር ውስጥ ካለው አንባቢ በተጨማሪ በውጪው አለም ለሚገኙ አንባቢያንም በኢትዮጵያ ያሉ ያልታዩና ያልተሰሙ ባህሎችን ማስተዋወቅን አላማው ያደረገ ነበር። የፍቅረማርቆስ ተከታታይ ኢትኖግራፊያዊ ልቦለዶች የኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን የውጭ አገር ዜጎችንም ልብ መግዛት ችለው ለጉብኝት ኢትዮጵያን እንዲረግጡ ቀላል የማይባል አበርክቶ ነበራቸው።

“Land of the yellow bull” በሚል ርዕስ ለአንባቢያን የቀረበው  መፅሐፉ ለተቀረው አለም ባህሉን ከማስተዋወቅ አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ ነበረው።

ይህ የትርጉም ስራው በመላው አለም ካገኘው ትልቅ ተወዳጅነት የተነሳ “Becoming a man in Africa” እና “Black samurai” የተሰኙ ሁለት ዶክመንተሪ ፊልሞች ተሰርተው ለእይታ መብቃት ችለዋል። ከሁለቱ ዶክመንተሪዎች መካከልም “Becoming a man in Africa” የተሰኘው ዶክመንተሪ በ ግንቦት ወር 1997 ዓ.ም የአፍሪካ ቀን በሚከበርበት ዕለት ተመርጦ ቅርስ ተፈጥሮና ባህልን በሚያስሰው ” ዲስከቨሪ” በተሰኘው  የቴሌቪዥን ጣቢያ ለእይታ እንዲቀርብ ተደርጓል።

የውጭ ሀገር ትምህርት

የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በኬሚስትሪ አግኝቶ የነበረው ፍቅረማርቆስ ወደ አሜሪካን በማቅናት ሁለተኛ ዲግሪውን በ Liberal Art ማግኘት ችሏል።

ደራሲ ፍቅረማርቆስ የኢትዮጵያዊያንን ቱባ  ባህል እና አኗኗርን ያለመታከት ለአለም በማስተዋወቅ ላሳየው ትልቅ ትጋት በ1996 ዓ.ም የክብር ሽልማትን ማግኘት የቻለ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ነው።

የሀመሮችና የፍቅረማርቆስ ትስስር

ደራሲ ፍቅረማርቆስ በመፅሀፎቹ የሀመርን ህዝብ በማስተዋወቅ በቻ አልቆመም። በብሄረሰቡ ደንብ መሠረት የሀመሮች አካል ሆኖ ከእነርሱ ጋር ኖሮል። ሀመሮች ደራሲው በብዕሩ የዋለላቸውን ውለታ በደንብ በመገንዘባቸው እንደ አንጋፋ ልጃቸው ይመለከቱታል። 

ይሁንና በ2004 ዓ.ም ፍቅረማርቆስ እሄዳለሁ ብሎ ሳያሳውቃቸው ወደ አሜሪካ በመሄዱ አዝነውበት ነበር። በአሜሪካ ለ10 አመታት ከቆየ በኋላ 2013 ዓ.ም ወደሀገሩ ተመልሷል።

ታዲያ ከሚናፍቃቸው ከሀመሮች ዘንድ ሲደርስ በዝምታ አልታለፈም። “በባህላችን መሠረት ጠፍቶ የተመለሰ ሰው ወደ ህዝቡ የሚቀላቀለው ከተገረፈ በኋላ ነው” ሲሉት ለመገረፍ አላቅማማም። ቅጣቱን ከተቀበለ በኋላ ከሚወዳቸው የሀመር ብሄር አባላት ጋር ተቀላቅሏል ።

    የበጎነት ተግባር

ፍቅረማርቆስ ከደራሲነቱ ባለፈ በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ይታወቃል። ከበጎ ፈቃድ ተሳትፎዎቹ ውስጥም ስፔን በሚገኘው በአለማቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር በጎ ፈቃደኛ ሆኖ የተለያዩ ስራዎችን መስራት ችሏል።

ደራሲና ኢትኖግራፈር አፈንዲ ሙተቂ ስለ ፍቅረማርቆስ

“የኢትዮጵያ ልቦለዳዊ ድርሰቶች  ከሚታዩባቸው ድክመቶች መካከል አንዱ እንደሌሎች ሀገራት ድርሰቶች ፈርጀ ብዙ አለመሆናቸው ነው ። ደራሲዎቹ በአብዛኛው የሚያተኩሩት በሁለት ጭብጦች ላይ ነው ። ፍቅርና ወንጀል። ከዚያ ወጣ ብለው ሌሎች ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለመዳሰስ ሲሞክሩ እምብዛም አይታይም። 

ይሁን እንጂ ከተለመደው የድርሰቶቻችን አፃፃፍ ዘውግ ወጣ ብለው የራሳቸውን ልዩ የስነፅሁፍ ዘይቤ እና የአትኩሮት ፈርጅ ለማስተዋወቅ የደከሙ ጥቂት ደራሲያን አሉ። ከነዚህ ጥቂት ደራሲያን መካከልም ደራሲ ፍቅረማርቅስ ደስታ ተጠቃሹ ነው።

የብዕር ገበሬው ፍቅረማርቆስ ለየት የሚለው በርካታ ሰዎች ብዙም ትኩረት የማይሰጡትን የብሄረሰብ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ተንተርሶ ግማሽ ደርዘን ያህል መፅሃፍትን ለተደራሲያኑ ማበርከት ችሏል።

“ኢትዮጵያ ውብ ናት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የውበቷ ፈርጦች መካከል አንዱ ብሄርና ብሄረሰቦቻችን ፣ ከቋንቋዎቻችን፣ የብሄሮቻችን ቱባ ባህል፣ ትውፊት ፣ ኪነ ጥበብና ታሪክ ነው። በዚህ በኩል እንደ ኢትዮጵያ የታደሉት ጥቂት ሀገሮች ብቻ ናቸው። እነዚህ በፈጣሪ የተሰጡንን ውበቶች እንደትልቅ ፀጋ ቆጥረን በደንብ ከያዝናቸው እና ከተጠቀምንባቸው የፍቅር ማጎልበቻ ከማድረግ አልፈን ከፍተኛ ገቢ ልንዝቅባቸው እንችላለን ። ይህንን ለመረዳት የደራሲ ፍቅረማርቆስ ስራዎችን በምሳሌነት ማንሳት ይበቃል።

“.ሀመር የሚባለው ኩሻዊ ቋንቋ ተናጋሪ ቤተሰብ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ነው የኖረው። በቀድሞ ዘመናት ስለዚህ ህዝብ ባህል፣ታሪክ፣አኗኗር እና ትውፊት የነበረን እውቀት በጣም ውስን ነበር። የሀመር ማንነት ወለል ብሎ የታየን ደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ ባደረገው የብዕር ተጋድሎ ነው። ደራሲው ብዙ የለፋበት ብሄረሰቡን የማስተዋወቅ ስራ ውጤት ማምጣቱን በራሱ አይን መመልከት ችሏል። ለምሳሌ በድሮ ዘመን የ”ኢቫንጋዲ”ን ምንነት የሚያውቅ ህዝብ ውስን ነው። ባለፉት ሀያ አመታት ግን “ኢቫንጋዲ” በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ፅንሰ ሐሳብ ለመሆን ከመብቃቱ ባሻገር ለብዙዎች የስራ ፈጠራ መነሻ ሲሆን አይተናል። በዚህ ረገድ ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ የተጫወተው “ኢቫንጋዲ” የተሰኘው ተወዳጅ ሙዚቃ እንደ አብነት ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል።”

ምናብን ወደ ገሀድ የለወጡ ስራዎች

ፍቅረማርቆስ የደረሳቸው ስራዎች በኪናዊ ውበታቸው ከማማር አልፈው ብዙ ቱሪስቶች የሀመርን አካባቢ እንዲጎበኙ በማነሳሳት ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በ2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አንድ ታሪካዊ ጉዞ አዘጋጀ ።  “ህያው የጥበብ ጉዞ ወደ ቡስካ በስተጀርባ – ድንግል ውበት አገር” በሚል ሀሳብ የተዘጋጀው ጉዞ ደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ የፃፋቸው ስነ- ሰብዕ (Ethnographic) ድርሰቶችን መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ በርካታ የጥበብ ሰዎች ተሳትፈውበታል።በዚህ ታሪካዊ ጉዞ   በምናብ ብቻ የሚያውቁትን ድንግል ውበት  በቦታው  ተገኝተው በመመልከት ምናብና ገሀዱን እያዛመዱ እንዲደመሙ እድል የፈጠረላቸው ሲሆን መሠል የስነ-ሰብዕ ስራዎችን በፈጠራዎቻቸው እንዲያካትቱ መነሻ መሆን ችሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *