የምወድሽ የሚያስታውስ መርሀ ግብር ተደረገ
ነሐሴ 23 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው ደራሲና ጋዜጠኛ የምወድሽ በቀለን ለማስታወስ አርብ ነሀሴ 30 2017 አንድ መሰናዶ ተደርጓል።
በወመዘክር አዳራሽ ከቀኑ9 -11 በነበረው ዝግጅት የምወድሽን በልዩ ልዩ የሥራ አጋጣሚ የሚያውቋት ታድመው ነበር።
ከሴቶች ጋር የሚሠሩ ማህበራት ከተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ጋር በጋራ ዕውን ባደረጉት ዝግጅት የምወድሽን በቅርበት የሚያውቁ ባልደረቦች ምስክርነት ሰጥተዋል።
የህሊና ፀሎት በማድረግ በተጀመረው በዚህ መርሀ -ግብር በእምወድሽ በቀለ ላይ ትኩረቱን ያደረገ አጭር ዶክመንተሪም ቀርቧል።
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ ሰዎች ህይወታቸው ቢያልፍም መልካም ተግባራቸው ዘመን ተሻጋሪ ይሆናል ብሎ ስለሚያምን የሚታወሱበትን መንገድ ዕውን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የተወዳጅ ሚድያ ሥራ አስፈጻሚ ዕዝራ እጅጉ ተናግረዋል። እንደዚሁም ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን እና ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር በሴቶች ላይ የሚሠሩ ማህበራትን በመወከል የምወድሽ ከልባችን የማትጠፋ አርአያ የምትሆን እህታችን ናት ብለዋል።
የዕለቱን የማስታወሻ መሰናዶ ካዘጋጁት መካከል ተወዳጅ ሚድያ ባቀረበው ሀሳብ መሠረት የምወድሽን ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ አንድ ውሳኔ አለን ሲል ሀሣቡን አጋርቷል።
የመዝገበ አእምሮ የመማክርት አባላት በወሰኑት ውሳኔ መሠረትም tewedajewikipedia.com ድረ- ገፅ ላይ “የታላላቅ ሴቶች ዐምድ” የሚል ገጽ ለመክፈት ከውሳኔ ላይ ተደርሷል።
ይህ ዐምድ በ 7 በሕይወት በሌሉ ሴት የሚድያና የሥነ-ፅሁፍ ባለሙያዎች የሚሰየም ይሆናል። በዚህም መሠረት፣ ደራሲና ጋዜጠኛ የምወድሽ በቀለም ዐምዱ ከተሰየመላቸው ባለሙያዎች አንዷ ስትሆን ሌሎችም ተቋማት ኢትዮጵያዊያንን በማክበርና በመዘከር ተመሳሳይ ማስታወሻ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ የመዝገበ አእምሮ የመማክርት አባላት ገልፀዋል።
ከምወድሽ በቀለ ጋር በአንድ ዐምድ ምስላቸውና ታሪካቸው የሚሰፍርላቸው ባለሙያዎች ዓለምሰገድ ኅሩይ፣እሌኒ ፈጠነ፣እሌኒ መኩሪያ፣ዶክተር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ ፣እንግዳዘር ነጋ እና ዓይናለም ባልቻ ናቸው።
“የምወድሽን እናስታውስ” በሚል መሪ ሀሣብ ዕውን በሆነው በዚህ ዝግጅት ግጥሞች፣ሌሎች የሥነ ፅሑፍ ሥራዎችም የቀረቡ ሲሆን የደራሲዋ መፅሐፎችም ለዕይታ ቀርበዋል።