ደረጀ ኃይሌ (ኃይሌ ዘበቅሎ ቤት)

ዛሬ ግንቦት 25 2017 ዓ.ም ደረጀ ኃይሌ ጋር አብረን ነበርን። የቀድሞ ደራሲና ጋዜጠኛ መዝገቡ አባተ መፅሐፍ ሲመረቅ ደሬ በመኮንን አዳራሽ ተሰይሞ ነበር፡፡ ለልጃቸው ለፀሐይ መዝገቡ አባተ የተዘጋጀውን ስጦታ እንዲያበረክት የተመረጠው ደሬ ነበር፡፡ የመፅሐፍ ምረቃውን ደግሞ ተወዳጅ ሚድያ እንደማዘጋጀቱ የደሬ ስጦታ መስጠት ልዩ ትርጉም ነበረው፡፡ እናም ከጳግሜን የሽልማት ድርጅት ዳንኤል አርጋው የሰጠውን ስጦታ ደረጀ ለፀሐይ አበርክቶላታል፡፡

ደሬ ጋር የልብ የልባችንን ማውራት ጀመርን፡፡ መዝገበ አእምሮን አይቶ፣200 ሰው መሰነዴ አስደንቆት በብዙ አበረታታኝ፡፡ እኔም የእርሱን የደረጀን ታሪክ መዝገበ አእምሮ ቅፅ 3 ላይ እንደምሰንደው ነግሬው ፣መፅሀፌን ፈርሜ ሰጠሁት፡፡ ታሪኩ እንዲሰነድ ፋቃደኝነቱን ይገልፃል ብዬ አምናለሁ፡፡ ደሬ ወዳጄ ! መንገድህ ይቃና !!!!ያው የሕይወት ታሪክህን ለመሥራት ብዙ መረጃ እንዳሰባሰብኩ ታውቃለህ፡፡ ፍጠን፡፡ ለመፍቀድ፡፡አልኩት፡፡

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣እስከዛሬ የ400 የሚድያ እና የጥበብ ሰዎችን የሕይወት ታሪክ ሰንዷል፡፡ መዝገበ አእምሮም ላይ ታሪካቸው በመፅሐፍ ላይ ተከትቦ ለትውልዱ ተደራሽ እንዲሆን አድርገናል፡፡ታሪካቸው በቀጣይ ቅፅ 3 ኢንሳይክሎፒዲያ ከሚካተትላቸው የሚድያ ሰዎች አንዱ ደረጀ ኃይሌ ነው፡፡ የመዝገበ አእምሮ የመማክርት አባላት በሙሉ ድምፅ ታሪኩ እንዲሰነድ የወሰኑ ስለሆነ እነሆ ከሚከተበው በጨረፍታ እናቀርባለን፡፡ ይህ የሕይወት ታሪክ ፅሁፍ በቂ ምርምር የተደረገበትና አስፈላጊ ሰነዶችም የተካተቱበት ነው፡፡ በየጊዜውም አዳዲስ መረጃዎች ይታከሉበታል፡፡ ይህ ፅሁፍ በመዝገበ አእምሮ የሕይወት ታሪክ አዘጋጆች በዕዝራ እጅጉ እና በቤርሳቤህ ጌቴ የተሰናዳ ሲሆን 7 የምርምር አማካሪዎችም በሥራው ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ሌሎች የምርምር አማካሪዎችም የሚጨመሩ ሲሆን የጋዜጠኛ ደረጀን ታሪክ ለማጠናከር ያግዙናል ብለን እናምናለን።

  • አለባበሱ የተሽቀረቀረ ለእንግዶቹ ያለው ክብር በአለባበሱ ጭምር የሚገለፅ ነው። ለጋዜጠኝነት ሞገስ ካላበሱት ጉምቱ ሙያተኞች መካከል በዘመናችን በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ዋነኞቹ መካከል አንዱ ነው።

የአለባበስ ምርጫው እና ጥንቅቅ የማለቱ ምክንያት ምናልባትም ከብሔራዊ ውትድርና የተቀዳ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። በብሔራዊ ውትድርና ባሌ ጎባ ታጠቅ አራት ማሰልጠኛ የአራተኛ ዙር ሰልጣኝ ሆኖ ለስድስት ወራት ሲገባ ጥይት አተኳኮስ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ክብርና መስዋዕትነት መክፈልን ከሥነልቦናና ከሥነሥርአቱ ጭምር ተምሮ እንደሚወጣ ጥርጥር የለውም።

ቤተሰብ ማህበረሰብና ትምህርት ቤት ከሚገነቡት ባልተናነሰ እንደ ብሔራዊ ውትድርና ዓይነት ወሳኝ የስልጠና መስኮች ህይወትን በማቃናት ረገድ የሚኖራቸው ሚና ላቅ ያለ እንደሚሆን አያጠያይቅም። በአንድ ወቅት ደረጀ “ታካችነቴን ያረቀው ብሔራዊ ውትድርና ነው” ሲል መደመጡም ለዚሁ ነው። ከተወደዱት አባቱ ሽቅርቅርነትን እና ዝምታን ከተጫዋች እናቱ ጨዋታና ሳቅን የወረሰው ጉምቱው ጋዜጠኛ ደረጄ ኃይሌ ዛሬ ልደቱን ምክንያት አድርገን ስለ ሥራዎቹና አበርክቶው ጥቂት ለማለት ወደናል።

ትውልዱ ናዝሬት(አዳማ) ላይ ነው፤ በሰኔ 7/ 1957 ዓ.ም። እድገቱ ደግሞ አዲስ አበባ በቅሎ ቤት አካባቢ ነበር።የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ናዝሬት በቅዱስ ያሬድ የተማረ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አብዮት ቅርስ ተከታትሏል፡፡የጋዜጠኝነት ፍቅሩ ከፍሪላንስ ነበር የጀመረው። በኢትዮጵያ ሬድዮ በፍሪላንስ የቅዳሜ ወጣቶች ፕሮግራም ላይ እየሰራ የጋዜጠኝነት ፍቅሩን በሚገባ ተወጥቷል፡፡ በዚህ መሀል የብሔራዊ ውትድርና ስልጠና መጥሪያ ሲመጣለት በደስታ ተቀብሎ ወደ ባሌ ጎባ አቀና። ከስልጠናው ሲመለስም በ1980 ግድም የጦር ኃይሎች ሬድዮ ዝግጅት ክፍልን በመቀላቀል አቅሙን ማሳየት ጀመረ። ደረጀ በጦር ኃይሎች ሬድዮ አብረውት ከሠሩት መካከል ፀሐይ ተፈረደኝ፣ሲሳይ ታደሰ እና አክሊሉ ዘለቀ ይገኙበታል።

ደረጀ ፣ከጦር ኃይሎች ሬድዮ በመቀጠል ኢትዮጵያ ሬድዮ የወጣቶች ፕሮግራም ውስጥ በመግባት በአድማጮች ተወዳጅ ለመሆን ቻለ፡፡ ኢትዮጵያ ሬድዮ እስከ 1986 ዓ.ም ድረስ ሲሠራ ከቆየ በኋላ ወደ ህትመት ሚድያው ገባ። በህትመት ሚድያው ከኢትኦጵ ጀምሮ የተለያዩ መፅሔትና ጋዜጦች ላይ እንግዶችን እየጋበዘ ቃለመጠይቅ አድርጎላቸዋል።በተለይ ኢትኦጵ ጋዜጣ ላይ ከጥበብ ሲቆነጠር በተሰኘው አምድ በርካታ ፅሑፎችን አስነብቧል። ጦራ ጦርጦራ የብዕር ስሙ ሲሆን በጊዜውም ጠንካራ ፀሐፊነቱን ያሳየበት ጊዜ ነበር፡፡

ደረጀ፣ ከ1986-1992 ባሉት 6 ዓመታት በሕትመት ሚድያዎች ላይ ብዕሩን ያሳየ ሲሆን ኃይሌ ዘበቅሎ ቤት የተሰኘው ስሙ በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል፡፡ በአንባቢያን ዘንድም ያስከበረው ነው። በ1992 በ97.1 ላይ የቅዳሜ ጨዋታ በሚያቀርባቸው እንግዶችም አድናቆት ተቸሮታል፡፡

በጋዜጠኝነት ሙያ እያደገና እየበሰለ ሲሄድ ህዝብ ዓይኑን የጣለባቸውን ታላላቅ ሰዎች እያቀረበ በመጠየቅ ብቃቱን እያስመሰከረ መጣ። የሀገሪቷ ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ፣ የቱሪዝም አባቱ ጋሽ ሀብተስላሴ ታፈሰ፣ ሰለሞን ደሬሳ፣ አባዱላ ገመዳ፣ሙሀዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ፋሲካ ሲደልል፣ የመንግስቱ ኃይለማርያም ቤተሰቦች፣ ጀዋር መሀመድ ከእንግዶቹ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

ደረጀ ያልሠራው፣ያልዳሰሰው ርዕሰ- ጉዳይ ነበር ለማለት ያዳግታል። ከሰራቸው በርካታ ሥራዎች ለመጥቀስ ከቅርቡ ብንጀምር ‘በነገራችን ላይ’ የተሰኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም በአርትስ ቴሌቪዥን ሲያቀርብ፤ በተለይም በተለያየ ጊዜ በሀገራችን በኃላፊነት እና በፖለቲካ እንቅስቃሴ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩ ሙያተኞችን በእንግድነት በማቅረብ ባስለመደን የቃለመጠይቅ ለዛ ድንቅ ቆይታውን ሲያስኮመኩመን ቆይቷል። በፋና ኤፍ ኤም ‘የደራው ጨዋታ’ በተደራጀ ንባብና በበቂ ዝግጅት ታሪክን ፈልፍሎ አውጥቶ ለአድማጩ አጋርቷል፣ ታሜሶል ኮምዩኒኬሽን ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀውን የጥያቄና መልስ ውድድር በደማቅ አቀራረብ በመምራት በብዙሃኑ ዘንድ ተወዳጅነትን እንዲያተርፍ አስችሎታል። በጦር ሀይሎች የሬድዮ ፕሮግራም ፣ በኤፍ ኤም ዩኒቲ ድምፅ(በተለይም ቁምነገር አዘል የሆኑ በሴቶችና በህፃናት ላይ ያተኮሩ ይዘቶችን የሚያቀርብበት የነበረ) ፣ ከኤፍ ኤም 97.1 ጋር በመተባበር ይቀርብ በነበረው የጨዋታ ፕሮግራም ላይ ደረጄ ሀይሌ አንዱና ዋነኛው ድምቀት ነበር ማለት ይቻላል።

በህትመት ሚድያው በበርካታ የብዕር ስሞቹ ልዩ ልዩ ይዘት የነበራቸውን መጣጥፎች ሲያጋራን ቆይቷል። በተለይም በኢትኦጵ ጋዜጣ ላይ ‘ሃይለ ዘበቅሎ ቤትና ጦራ ጦጦራ’ በተሰኙት የብዕር ስሞቹ ምርጥ ቃለመጠይቆቹን አስነብቦናል። ከዚህ ውጪ በቃልኪዳን መፅሔትና ጋዜጣ ላይ ዘመን አይሽሬ ሥራዎቹን አኑሮልናል። ከብዕር ስም ጋር በተያያዘ በተለይ ‘ጦራ ጦጦራ’ የተሰኘው ስሙ ታሪካዊ መነሻ ነበረው። ሐምሌ 1995 ለኢንፎቴይመንት መፅሄት በሰጠው ቃለመጠይቅ ላይ የገለፀውን እንዳለ ልጠቀም።

” አንድ ቀን የሆነ ቦታ ቁጭ ብለን ስንጫወት አንድ ጓደኛችን መልካ ዋከና ፕሮጀክት ውስጥ ይሠራ ነበረና ስለስም ስናወራ.. እኛ ጋር ጦራ ጦጦራ የሚባል አለ ከየት እንደመጣ አይታወቅም..የት ነው ሀገርህ ስንለውም ሀገሩን አያውቀውም፡፡ ግን አንድ ነገር ያውቃል፤ ስሙ ገርሞን ምን ማለት ነው? ብለን ስንጠይቀው ‘ጋሻና ጦር ማለት ነው’ አለን በምንኛ ስንለው ግን አላውቀውም አለን ብሎ ሲያጫውተን በጣም ስለገረመኝ ለምን ይሄንን ስም አልጠቀምበትም አልኩ።” ብሏል።

ደረጀ፣ ምንም እንኳን በህትመትም ሆነ በኤሌክትሮኒክስ ሚድያው ላይ የማይዘነጉ በርካታ ሥራዎችን ቢያበረክትልንም እርሱም እንደሚያምነው ነፍሱ የሬድዮ ናት። ከአንጋፋዎቹ የኢትዮጵያ ሬድዮ ጋዜጠኞች መካከል ለደረጀ እንደ ሙያ አባትና መምህር የሚቆጠረው ታደሰ ሙሉነህ ሲሆን ለንጉሴ አክሊሉ ያለው አድናቆት ላቅ ያለ ነው። አዲሱ አበበ እንደ ታላቅ ወንድም ብዙ የተማረበት የሙያ አጋሩ ነው። በዶክመንት አያያዙ የሚደነቀው ደረጀ ቤቱ ትንሽዬ ቤተ-መፅሀፍት ነው ይባልለታል።

የሚሠራቸውም ሥራዎች ጮክ ብለው እንደሚመሰክሩት አደራጅቶ የያዛቸው ድምፆችና የት እንደተቀመጡ ጠንቅቆ የሚያውቃቸው የፅሁፍ ሰነዶች ለዝግጅቶቹ መዳበርና ተአማኒነት ትልቅ መሠረት ሲሆኑለት ተመልክተናል። ዛሬ ላይ ብዙ ጋዜጠኞች እንደ ምሳሌ የሚቆጥሩት ደረጀ ሀይሌ የአጠያየቅ ልምዱንና የንባብ ባህሉን ለመቅዳት ጥቂት የማይባሉት እየተፍጨረጨሩ ይገኛሉ። ለጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ አድማጭ ተመልካቹም ሆነ አንባቢው ብዙ ሊሉለት እንደሚችሉ ባያጠያይቅም ጥቂት ከሙያ አጋሮቹ የተቀበልነውን አስተያየት ማስነበብ እንወዳለን።

  ፀሀይ ተፈረደኝ

ጦር ሀይሎች ሬድዮ ላይ በ1980 ግድም በደርግ ጊዜ ሲሰራ አብረን የመሥራት እድሉ ነበረን። በጣም ቅርብ ወዳጆች ነበርን። ብሔራዊ ውትድርና ሰልጥኖ ለሚድያ ያስፈልጋል ተብሎ እንደ ሀገር ግዳጅ ነበር ወደ ጦርሀይሎች እንዲመጣ የተደረገው።
ጦርኃ ይሎች ሬድዮ ፕሮግራም ማለት በጊዜው ስላሴ ቤተክርስቲያን አካባቢ ነበር ቢሯችን። እሮብ ምሽትና እሁድ ጠዋት ነበር ፕሮግራማችን አየር ላይ ይውል የነበረው። ጀነራል ፈለቀ አለቃችን ሲሆኑ በርካታ ጋዜጠኞች አብረን ነበርን ብርሀኑ አሰፋ፣ ተፈሪ ፀጋዬ፣ ደረጄ ሀይሌ ነበርን። ደረጀ፣በድምፅና በፅሁፍ ዝግጅቶቹ ተወዳጅ ነበሩ። በተለይም ብሔራዊ ውትድርና የነበረውን አጋጣሚ ያቀርብ ነበር። ደረጄ ጎበዝ ጋዜጠኛ ነበር። በሥራ አጋጣሚያችን የማልዘነጋው ነገር የበላይ ዘለቀ ታሪክን መፅሀፈ ሲራክ ፅፎት እኔ ስተርከው፤ ደረጀ የበላይ ዘለቀ እህት በህይወት
መኖራቸውን ነገረኝና ቤታቸውን ፈልጎ ቀጠሮ ይዞ ምርጥ ዝግጅት እንድሰራ ያገዘኝ ባልደረባዬ ነው።

   ዘካሪያስ ብርሃኑ

በሙያው የማደንቀውና የማከብረው ጋዜጠኛ ሲሆን ከእኔ ጋር በቅርበት ለመገናኘት ምክንያት የሆነን ‘ የደራው ጨዋታ’ የተሰኘው በፋና ኤፍ ኤም 98.1 የሚቀርበው ፕሮግራም ነው ። በጊዜው የተባባሪ አዘጋጆችና የመዝናኛ ክፍል ኃላፊ ስለነበርኩ በሬድዮ የተሻለ አቀራረብ ይዘን ለመምጣት የምንሠራበት ጊዜ ነበር ፤ በመሆኑም በተባባሪ አዘጋጆች ሀገሪቱ ላይ አሉ የተባሉትን አፈላልጎ በማግኘት የማሳመን ሥራ መሥራትና ማምጣት ላይ በትኩረት እንሠራ ነበር። ጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ ምንም እንኳን የተወደደና የተከበረ ጋዜጠኛ ቢሆን በጊዜው የገጠመው የህይወት ፈተና ከሁሉም ነገር ተገልሎ እንዲቀመጥ አድርጎት ስለነበረ እርሱን አግኝቶ በማነጋገር የማሳመን ሥራ መሥራት በጣም ከባድ ኃላፊነት የሚጠይቅ ነበር። ደረጀን አግባባቶ ወደ ሥራው ለማምጣት ረዥም ጊዜ ወስዷል። በሀሳቡ ተስማምቶ ወደ ሥራው ሲመጣም እርሱ ከሥራው ትኩረት ውጪ የንግድ ፈቃድ፣የሬድዮ ፎርማት ቀረፃና ሌሎች ለሥራው አስፈላጊ አሰራሮችን ለማመቻቸት ሰው በመመደብ ደረጀ ሥራው ብቻ ትኩረቱ እንዲሆን አደረግኩ። የደራው ጨዋታ ከስያሜው ጀምሮ የዝግጅቱ ሀሳብ የደረጀ ሲሆን የሬድዮ ፎርማት ቅርፅ ማስያዝና ለፕሮግራሙ ካመጣቸው ስያሜዎች ማለትም ‘ የደራው ጨዋታና በነገራችን ላይ’ ከተሰኙት ውስጥ ደረጄ በነገራችን ላይ የሚለውን ቢመርጥም የደራው ጨዋታን የመረጥኩትና ያሳመንኩት እኔ ነበርኩ። ይህ ፕሮግራም እንዲጀምር ስንስማማ ደረጀ የመረጣት ረዳት አዘጋጁ በድርሰትና በድራማ የምናውቃት አዜብ ወርቁን ነበር። በሚድያ ላይ ያላትን ብቃት ባናውቅም “እኔ ያየሁት ነገር አለ” ያለንን በማመን አስጀመርናቸው። እንደጥረታችን እነርሱም አላሳፈሩንም፡ በአጭር ጊዜ ተወዳጅና ተፅዕኖ ፈጣሪ ፕሮግራም ለመሆን በቃ። መጀመሪያ በሳምንት አንድ ቀን ነበር አየር ላይ የሚውለው፡፡ ቀጥሎም ወደ ሁለት ቀን አደገ። ከፕሮግራሙ መጀመር ቀደም ብሎ ቃለ-መጠይቅ አድርጌለት በጣም ጥሩ ቆይታ አደረግን። ከአድማጩም የተሰጠን ምላሽ የሚያስደስት ነበር። ደረጀ በሥራው የምደነቅበት ነገር ዝግጅቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ለእያንዳንዱ ፕሮግራም የሚያደርገው ዝግጅት ነው። ሬድዮን ያከብራል፡፡ ለፕሮግራም ይጠነቀቃል ፣ አየር ከመጀመሩ ሁለት ሰዓት በፊት ቀድሞ ተገኝቶ የተዘጋጀውን ይከልሳል፣ አርካይቩም የዳበረ ነው። እንደቴሌቪዥን አዘጋጅ ወደ ስቱዲዮ ሲመጣ በአለባበሱ ተጠንቅቆ ፣ ሽቶም ሳይቀር ተቀብቶ ነበር የሚቀርበው። ፕሮግራሙ ላይ ያለውን ሀሳብ ሁልጊዜም ምሽት ላይ ደውሎ አስተያየት ይቀበለኛልና በዚህ በጣም እደነቅ ነበር።
ፕሮግራሙ ለ3 ዓመት አየር ላይ ሲቆይ የተወደደና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ የዘለቀ ነው።

በእኔ አስተያየት የደረጀ ልብም ክብርም ሬድዮ ላይ ቢሆንም በነገራችን ላይን በአርትስ ይዞ ሲቀርብ ደስ ነው ያለኝ ቆንጆ ሥራም ነበር።
ደረጄ በተለይም በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ የሆኑ ቃለ-መጠይቆችን በማቅረብ ከፍ ያለ ቁምነገር አዘል ዝግጅት የሚያቀርብ ስለሆነ ሰውን የሚጠይቅበት መንገድ ለሌሎች ግብአት ሊሆን የሚችል በመሆኑ በኢትዮጵያ ሚድያ ላይ ትልቅ አሻራ አሳርፏል ብዬ አምናለሁ።

ወሰንሰገድ ገብረኪዳን

ኢትዮጵ ጋዜጣ ላይ አብረው የመሥራት እድል ነበረን። ኢትዮጵ ጋዜጣና መፅሔት በየሳምንቱ ነበር የሚቀርበውና በመፅሄቱም ሆነ በጋዜጣው ላይ ‘የጥበብ ሲቆነጠር አምድ’ እና ‘ማንን ታዘቡ’ በሚለው አምድ ላይ በብዕር ስሙ ጦራጦጦራ አርቲስቶችንና ሌሎች ታዋቂዎችን እያቀረበ ጥራት ያላቸው ስራዎችን አስነብቦናል። ስራዎቹን በጥናት ሲያቀርብ ለተነባቢነቱም እያዋዛ ያቀርበው ነበር። በጊዜው ከነበሩ የተመረጡ ጋዜጠኞች መካከል ደረጄ አንዱ ነው። እኔ እንደሚገባኝ ደረጄ የሬድዮ ሰው ሳይሆን የህትመት ሚድያ ሰው ነው። የስነፅሁፍ ብቃቱ የሚደነቅ ነው።

ደረጀ ኃይሌ በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ሬድዮ የወጣበትን አጋጣሚ ሲያስታውስ እንዲህ ብሎ ነበር ፡
“….የኢትዮጵያ ሬዲዮን ስለቅ ጭቅጭቅ ነበር። በግምገማ 1986 ዓ.ም ላይ ነው የለቀኩት “ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች” የሚል አንድ ፕሮግራም ነበር፡፡ እዚያ ላይ በጣም ብዙ የባለጉዳዮች ኬዞች ይቀርቡ ነበር፡፡ ሰኞ ሰኞ ማታ ሦስት ተኩል የሚቀርብ ነው፡፡ እነዛ ፕሮግራሞች ከጥቅም ጋር የተያያዙ ናቸው እና አንዳንድ ደረጀ የሚሠራቸው ፕሮግራሞች ከጥቅም ጋር የተያያዙ ናቸው የሚል ነገር ነው በደምሳሳው የቀረበው እንጂ እነገሌ እንደዚህ ሆኖ በዚህ ጊዜ የተሠራ ነው ይሄ ፕሮግራም እንደዚህ ተገኝቶበት የሚል ነገር አልነበረም፡፡ በወቅቱ የነበሩት ኃላፊ ትንሽ ወጣ ያለ አነጋገር ሲናገሩ የትም ወጥቼ መሥራት እንደምችል የገለጽኩበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ እንዲያውም ሰዎች ቀዝቀዝ በል ብለው እስኪያረጋጉኝ ድረስ

ማለት ነው፡፡ ሌላ ቦታ ሄጄ መሥራትም እችላለሁ የሚል ሃሳቤን ተናግሬአለሁ፡፡ እናም አሁን እዚያ ቤት የሌሉት ኃላፊ በል ውጣ በል ሂድ ሥራ አሉኝ ወጣሁ፡፡

ጥበብን የተመለከቱ እና ኢንተርቪዎች የተለያዩ ፕሬሶች ውስጥ ሠርቻለሁ፡ በተለይ በበዛት ኢትዮጵ ላይ ሃይሌ ዘበቅሎ ቤት በሚለው የብዕር ስም የተለያዩ አርቲስቶችን ኢንተርቪው አድርጌአለሁ፡፡ እንዲሁም በጦራ ጦጦራ በቀለሜ፣ አርቲክሎችን አበረክት ነበር፡፡ ከዚያ ደግሞ በግል ማስታወቂያዎች ያው ጓደኞቼ የማስታወቂያ ድርጅት አሏቸው ባለፍ ገደም ሲገኝ አነባለሁ ።”በማለት ተናግሮ ነበር።

ይድረስ ለደረጀ ኃይሌ

ውድ ወንድሜና የቀድሞ የስራ ባልደረባዬ ደሬ እንኳን ተወለድክ ፡፡ መኖርህ ክብራችን ነው ፡፡ መወለድህ ለምናውቅህ ጌጣችን ያደርግሀል ፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ በወጣቶች ፕሮግራም አብረን በሰራንባቸው እነኚያ ውብ ዘመናት የቅዳሜ ውበት ነበርክ ፡፡ ያ የቅዳሜ ቀትር ድባብ አሁን ድረስ ውልብ እያለ ይታወሰኛል ፡፡ ድምጽህ ብቻ አይደለም ሙሉ ሉክ እጥፍ አድገህ ቀድደህ ማግባቢያ የምትጽፍበት ግማሽ ወረቀትና ፤ የቁም የእጅ ጽሁፍህ ሁሉ አይረሳኝም ፡፡ ዋውው… ጋሽ ታደሰ ሙሉነህን ደጋግመህ እያስታወስክ ስቱዲዮን የቤተ መቅደስ ያህል ክብርና ሞገስ ሊሰጠው እንደሚገባው ምትናገረውና ኖረህ ያከበርክበት ዘመን የህይወትህ ዓቢይ ገፅታ ነው ፡፡ ጠንቃቃነትህ ፤ ዝግጁነትህ ፤ መራማሪነትህ ፤ በምታውቀውና በተዘጋጀህበት ልክ ድፍረትህ ፤ ፅድት ያሉት የሥራዎችህ ውጤቶች ተቆጥረው አየማያልቁ የህይወትህ ብዕራፎች ናቸው ብየየ አስባለሁ ፡፡ ፡፡ ሀገራዊና ታሪካዊ ሰነዶችን እንዲሁም የድምፅ ግብዓቶችና ፕሮግራሞችን የማሰባሰብ አቅምህን ስለማውቅ ታስደምመኛለህ ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ እና ደረጀ ፤ ደረጀና ኢትዮጵያ ሬዲዮ … የ60 ዓመት ጉዞ የወጣትነት ቀለም ፡፡ በቃ እንኳን ተወለድክ ወንድሜ ፡፡ ረጅም ዕድሜና ጤና ተመኘሁልህ ፡፡

ብርሃኑ ገብረማርያም


+++++__¥

ሲሳይ ታደሰ

በጦርሀይሎች ሬድዮ አለቃቸው ነበርኩኝ። ከ1979 ወይም 80 አካባቢ ይመስለኛል ጊዜው። ብሔራዊ ውትድርና ሰልጥነው ለግዳጅ ሲወጡ ነበር በጦር ሀይሎች የተመደበው። ስራው የሀገር ግዳጅም ስለሆነ ክፍያው 100 ብር አካባቢ ነው ለምሳ የሚሰጥ ኩፖን ተጨምሮለት ነበር የሚሰራው። የመጀመሪያ ስራው
ደብዳቤዎችን ማቀናበር ሲሆን ቀጥሎም የፕሮግራም ማሻገሪያዎችን ማዘጋጀትና ግጥም ማቅረብ ላይ ይሳተፍ ነበር። ቀስ በቀስ ወደ ፅሁፍ ስራው ተሻገረና ‘ ህይወት በማሰልጠኛ ማዕከል’ የሚል ተከታታይነት ያለው መጣጥፉን በእረኛው ባለዋሽንት ክላሲካል እያጀበ ይተርክ ጀመር። በጣም ቆንጆ ስራ ነበር። በኋላም በየካቲት ችቦ ላይ በተከታታይ ታትሞ ወጥቶለታል። ደረጄ በስራው አይታማም ሲሰራ ይሰራል ሲጠፋም ይጠፋል። ጎበዝ ጋዜጠኛ ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *