ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ በስነ-ጽሁፍ በቴአትርና በፊልም ዘርፍ ያሉ የተወሰኑ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የስነዳው ስራ ተጠናክሮ እየቀጠለ ሲሆን ይህም 2ኛው ዙር መሆኑ ነው፡፡ እኛ በአቅማችን የሰሩ ሰዎችን እያፈላለግን ያኖሩትን አሻራ ለምርምር ግብአት እንዲሆን አድርገን እያስቀመጥን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ባህር ማዶ ቢሄዱ ወይም በህይወት ባይኖሩ እንኳን አሻራ እስካኖሩ ድረስ በህዝብ ዘንድ እንዲታወሱ እናደርጋለን፡፡
በዚህ ስራችን እንቀጥላለን፡፡ በተወዳጅ ሚድያ ቦርድ አጽዳቂነት የህይወት እና የስራ ታሪካቸው ሊሰራ ይገባል ያልናቸውን በተወዳጅ ሚድያ የዲጂታል መገኛዎችና በማህበራዊ ድረ-ገጽ ላይ እያስቀመጥን እንገኛለን፡፡ ትልቁ አላማችን በመረጃ እና በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ላይ እነማን አሉ እነማንስ ነበሩ? ብለን በጨረፍታ ለማሳየት ነው ትልቁ ሙከራችን፡፡ ያለቀለት ወይም የሁሉንም አሊያ የአብዛኛውን በዘርፉ ላይ ያለን ሰው ታሪክ ለማካተት ብንሞክር እንኳን ስራውን ከባድ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ አመት በ2015 መጨረሻ በምናሳትመው መዝገበ-አእምሮ ከ120 በላይ የመረጃ እና የመዝናኛ ዘርፍ ላይ ያሉ ሰዎችን ታሪክ ጠብቁ ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ከ3 ዓመት በፊት ህይወቱ ያለፈው ደራሲ ደረጀ በቀለ አንዱ ነው። ደረጀ በቀለ ልክ የዛሬ 3 አመት ሐምሌ 18 2012 ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ህያው ፍቅር በተሰኘው እና በሌሎች ድርሰቶችም ይታወቃል ። አይናለም ሀድራ እና ዕዝራ እጅጉ የህይወት ታሪኩን ሰንደውታል።
ትውልድና ዕድገት
ደረጄ በቀለ ከአባቱ ከአቶ በቀለ አበበና ከእናቱ ከወ/ሮ አልማዝ ከበደ በ1951 ዓ.ም በተለምዶ ፍል ውሃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወለደ፡፡ በቤተሰቡ ውስጥም የተለየ ፍቅርና እንክብካቤ ነበረው፡፡ ደረጄ እናትና አባቱን፤ እህቶቹንና ወንድሞቹን እጅግ የሚወድ የቤተሰብ ሰው መሆኑ ይነገራል፡፡ እርስ በእርስም ጥብቅ ቁርኝት ነበራቸው፡፡ አባቱ በንጉሱ አገዛዝ ጊዜ በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሙያተኛ ናቸው፡፡ አብዛኛው የቤተሰቡ አባላት የተማሩ ነበሩ፡፡ ደረጄ ግን የስነጽሁፍ ተሰጥኦውና ችሎታው ከሁሉ ይለየው ነበር፡፡ ዘወትር ማታ ማታ ቤተሰቡ ሲሰበሰብ አንድ መጽሃፍ መርጦ ለሁሉም የማንበብ ልማድ ነበረው፡፡ቤተሰቦቹ እንደሚመሰክሩት ደረጄ መጻህፍቱን ምስል በሚከስት መልኩ ጥሩ አድርጎ ይተርክ ነበር፡፡
ከቤተሰብ ጋር ካለው የጠበቀ ቅርርብ ባሻገር ወዳጅነታቸው በህይወት እስከነበረበት ጊዜ ድረስ ያልተቋረጠ የልጅነት የልብ ጓደኞችም አሉት፡፡ በቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን በጓደኞቹም ዘንድ ተወዳጅ ነበር፡፡ ሰው ወዳድ፣ ተጫዋችና ሁልጊዜም አዲስ ነገሮችን የሚያሳይ መልካም ወንድም እንጂ ጓደኛ ብቻ እንዳልነበረ በጋራ ጥሩ የልጅነት ጊዜ እንዳሳለፉም ጓደኞቹ ይናገራሉ፡፡
ከልጅነቱ ጀምሮ የንባብ ፍቅር የነበረውና ልዩ የስነጽሁፍ ችሎታ የተቸረው ስለመሆኑ አብሮ አደግ ጓደኞቹ አቶ አዲስ አለሙና አቶ ማቲዎስ ዘገየ ይመሰክራሉ፡፡ ደረጄ በ16ና በ17 አመቱ የጻፋቸው ጽሁፎችን ለማንበብ ዕድሉ የነበራቸው አቶ አዲስ በወቅቱ የጻፋቸው የድርሰት ስራዎቹ መንፈስን የሚይዙ፣ ማራኪና ልብ አንጠልጣይ ነበሩ ይላሉ፡፡ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳሉም ካልባሌ ዋዛ ፈዛዛ ይልቅ ከ500 እስከ 600 ገጾች ያሏቸውን ትልልቅ መጻህፍትን በማንበብ ለጓደኞቹ መልሶ ይተርክ እንደነበረም አቶ ማቲዎስ ያስታውሳሉ፡፡
ደረጄ በተማሪነት ጊዜው ከፍተኛ 21 ቀበሌ 19 ኪነት ቡድን ሲቋቋም ከመስራቾቹ አንዱ ነበር ።ተቀባይነት የነበረው ተወዳጅ ተዋናይም ነበር፡፡ እነ ደረጄ የመሰረቱት ይህ የኪነት ቡድን ስመ-ጥርና እንደነ ሙዚቀኛ አስፋው ጽጌ፣የሙዚቃ አቀናባሪ ነጋ አዲሱ፣ታዋቂው የመድረክ ሰው አየለ ማሞና ሌሎች ብዙ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ያፈራ ቡድን ነው፡፡በተለያዩ ቦታዎች እየተጋበዙ ስራዎቻቸውን ያቀርቡ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ደረጄ ጉልህ ሚና ነበረው፡፡ ስነ-ጽሁፍ ከስር ከልጅነቱ ያደገበት ከላይ የተሰጠው እንጂ ድንገት የተከሰተ ነገር አይደለም ለደረጄ፡፡
ህያው ፍቅርና ሌሎች ስራዎች
በታዳጊነቱ ከጻፋቸው ድርሰቶች ውጪ ደረጄ በ1982 ዓ.ም ለህትመት ያበቃው ህያው ፍቅር የተሰኘው ልቦለድ መጽሃፍ በብዙዎች የተወደደለትና በስፋት ከአንባቢያን ጋር ያስተዋወቀው ስራ ነው፡፡ ህያው ፍቅር በሬዲዮም ተተርኮ ብዙዎች ቤት ገብቷል፡፡ በባለሙያው ደራሲና ሓያሲ ደረጄ በላይነህ አተያይ የታሪኩ ሴራ፣ የገጸ ባህርያት አሳሳሉና ልብ አንጠልጣይነቱ ድንቅ የተባለ ስራ ነው፡፡ ባለቤቱ ወ/ሮ መቅደስ አሰግድ ደረጄ ከህያው ፍቅር በላይ የተጠበበባቸው በርካታ ያልታተሙ ስራዎች እንዳሉትም ነው የሚናገሩት፡፡
ህይወቱ ከማለፉ በፊትም ታንጀሪና ሆቴልና ሌሎች ታሪኮች የሚለውን ስራውን ጽፏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 20 የሚደርሱ ልዩ ልዩ መጻህፍትን ተርጉሟል፤ የአዲስ ኪዳን ማብራሪያን ጨምሮ በሌሎች 20 መጻህፍት ላይ ደግሞ በአርታኢነት ተሳትፏል፡፡ ጭላንጭል የሚለው ተውኔቱም በ1986 በብሄራዊ ቴያትር ለዕይታ በቅቷል፡፡ ደረጄ የሪቫይቫል መንፈሳዊ መጽሄት ዋና አዘጋጅ ሆኖም ሰርቷል፤ በርካታ መንፈሳዊ መጻህፍትንም ተርጉሞ ለአማኒያን አበርክቷል፡፡ጀነራሎቹ (በአገልጋዮች የህይወት ታሪክ ላል የተፃፈው)ሌላው እራሱ ተርጉሞ በስሙ ያሳተመው መፅሃፍ አለ ::
በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ እንደሚስማሙት ለደረጄ መጻፍ ጭንቅ አልነበረም፤ ስራዎቹም አንባቢና ተመልካቾችን መግዛት የቻሉ ናቸው፡፡ ይሁንና ደረጄ በስራው ልክ እዩኝ እዩኝ፣ ዘምሩልኝ፣ አሞግሱገኝ የማይል ደራሲ ነበር፡፡ ብዙ ጅምር ስራዎች እያሉት፤ ብዙም ለአንባቢና ለተመልካች ሊወልደው ሊያበረክተው የሚችለው እምቅ ችሎታውን እንደያዘ ደረጄ በቀለ በ2012 ዓ.ም ሃምሌ 18 ቀን ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡