ዮሀንስ ክፍሌ (1931-2013)

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሰራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡

ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ? የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ ፣ታሪካቸው ከተካተተ ሰዎች መካከል አቶ ዮሀንስ ክፍሌ ይጠቀሳሉ። አቶ ዮሀንስ በታህሳስ 2016 በ 82 ዓመታቸው ህይወታቸዉ ያለፈ ሲሆን ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲመሰረት ከተቀጠሩት መካከል እንዱ ነበሩ። የማክሲም ጎርኪ ሥራ የሆነውን “እናት”መፅሀፍም ተርጉመዋል።

ዕዝራ እጅጉ የህይወት ታሪካቸውን ሰንዶታል።

ኃይል

አቶ ዮሐንስ ክፍሌ ዳዲ ሰኔ 27 ቀን 1931 ዓ.ም. ነበር የተወለዱት።

አባታቸው ክቡር ደጃዝማች ክፍሌ ዳዲ እናታቸው ክብርት ወ/ሮ አጥናፈወርቅ ከበደ ነገዎ ይባላሉ።

አቶ ዮሀንስ ታቤታ በሚባል ወረዳ፣ በሀገረ ኬንያ፣ በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ነበር የተወለዱት፡፡

በአራት ዓመት እድሜያቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲማሩ ቆይተው፣ ገና በልጅነታቸው፣ ለአምስት ዓመት ያህል፣ እንግሊዝ ሀገር ሄደው ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡

በአስራ ስድስት ዓመታቸው ወደ እናት ሀገራቸው ተመልሰው ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ገብተው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብተው የመጀመሪያ ዲግሪ በፖለቲካል ሳይንስ በ1955 ዓ.ም. ተቀበሉ፡፡ ከዚያም፣ ስኮላርሺፕ በማግኘታቸው፣ ወደ አሜሪካን ሀገር ሄደው፣ በ1957 ዓ.ም. በጋዜጠኛነት (ጆርናሊዝም) የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

አሜሪካን አገር በነበሩበትም ወቅት በዩ.ሲ.ኤል.ኤ. (UCLA) ፒስ ኮሮችን የአማርኛ ትምህርት አስተምረዋል፡፡ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተጀመረ በሁለተኛው ሳምንት በ1957 የመጀመሪያው የዜና መምሪያ ኃላፊ ሆነው ተመደቡ፡፡ ከስድስት ዓመት አገልግሎት በኋላ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጥረው የማስታወቂያ መምሪያ ዲሬክተር፣ ከዚያም የሽያጭ ፕሮግራም መምሪያ ዲሬክተር ሆነው ሠርተዋል፡፡ ወታደራዊ ደርግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ፣ በ1969 ዓ.ም.፣ ምንም ጥፋት ሳይገኝባቸው፣ ለአራት ዓመት ተኩል በሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያና በዋናው ወህኒ ቤት፣ በዓለም በቃኝ ውስጥ፣ ታስረው ነበር፡፡ ከእስርም ሲለቀቁ፣ የተሠጣቸው ብጣሽ ወረቀት “አብዮቱን ይቃወማሉ በሚል ጥርጣሬ፣ በጥበቃ ላይ ውለው፣ በዋስ ተለቀዋል” የሚል ነበር፡፡ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው በነበረበት ወቅት በማክሲም ጎርኪ የተደረሰውን “እናት” የተባለ መጽሐፍ፣ በቲሹ ፔፐር ላይ በመጻፍ፣ በስምንት ወራት ውስጥ ወደ አማርኛ ተርጉመዋል፡፡ በሥራ ብዛት ምክንያት እና በኋላም በጤና እክል የተነሳ፣ መፅሀፉን ሳያሳትሙ ቆይተው፣ መካተት የሚገባውን የግል ታሪካቸውን አክለው በሐምሌ 2012 ዓ.ም. መጽሀፉን አሳትመዋል፡፡

ወህኒ ቤት እያሉም ከ3ኛ ፖሊስ ጣቢያ አብረዋቸው ወደ ወህኒ ቤት የወረዱት ወጣቶች እና ሌሎች አለም በቃኝ ውስጥ የነበሩ እስረኛ ልጆች፣ የእንግሊዘኛ ቋንቋ እንዲያስተምሯቸው እርሳቸው ወደታሰሩበት ክፍል ይጎርፉ ነበር፡፡ የተማሪዎቹም ቁጥር እየተበራከተ በመሄዱ፣ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ወህኒ ቤቱ ውስጥ እንዲከፈት አስፈቅደው፣ ርእሰ መምህር በመሆንና የእንግሊዘኛ ቋንቋ በማስተማር፣ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በዚያንም ወቅት የወህኒ ቤቱ ተማሪዎች የአስራ ሁለተኛ መልቀቂያ ፈተና ሲወስዱ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ከመላው ኢትዮጵያ አንደኛ ወጥተዋል፡፡

በመሆኑም፣ ብዙ ጎበዝ ተማሪዎችን በማፍራታቸው በሕይወታቸው ሙሉ ከሠሯቸው ሥራዎች ሁሉ እንደዚህ ፍሬያማና የሚያስደስት ውጤታማና አቻ የሌለው ተግባር ገጥሞኝ አያውቅም ይሉ ነበር፡፡ ከእስር እንደተፈቱም፣ በቱሪዝም ኮሚሽን ሥር በነበረው የብሔራዊ አስጎብኚ ድርጅት (NTO) በአማካሪነት፤ በምክትልና በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሠርተዋል፡፡

በ1981 ዓ.ም. የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የፕሮቶኮል ሹም ሆነው ተሾሙ፡፡ ከአስራ አንድ ዓመት አገልግሎት በኋላ፣ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት በጡረታ ወጡ፡፡

ጡረታም እንደወጡ፣ ሸበሌ ኢትዮጵያ የስብሰባ አገልግሎት የሚባለውን ድርጅት አቋቁመው፣ ለአስራ አምስት ዓመታት ብዙ የዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን፣ ሴሚናሮችንና ሥልጠናዎችን አዘጋጅተዋል፡፡

በዚህም ወቅት፣ ብዙ አዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን በሥራ ላይ አሰማርተው፣ እንዳለቃም፣ ወጣቶቹ ሠራተኞቻቸው በሥራቸው ላይ ታታሪ እንዲሆኑ በማበረታታት እና ሕይወታቸውንም በአግባቡ እንዲመሩ አባታዊ ምክራቸውን ይለግሱ ነበር፡፡ በተጨማሪም፣ ይመሩት የነበረው ድርጅት ለኢትዮጵያ የማይናቅ የውጪ ምንዛሪ አስገብቷል፡፡ አቶ ዮሐንስ ክፍሌ ዳዲ በሮተሪ አዲስ አበባ ዌስት መስራችና ፕሬዚደንት በመሆን፣ በአሜሪካን ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ በምክትል ፕሬዚዳንትነት፣ በአፍሪካ ሂዩማኒቴሪያን አክሽን የቦርድ አባል (Africa Humanitarian Action) እንዲሁም በኢትዮጵያ ኤኮ ቱሪዝም አሶሲዬሽን በአባልነት አገልግለዋል፡፡ እንዲሁም የታሪኩ እና ደስታ ቴኒስ ክበብ የቦርድ ሰብሳቢ ነበሩ፡፡ አቶ ዮሐንስ ክፍሌ ዳዲ ፈርሀ እግዚአብሔር የነበራቸው እጅግ በጣም ደግ፣ ርህሩህ፣ ለደሀ አሳቢ፣ አጉራሽና አልባሽ፣ ለኅብረተሰቡ አለኝታ፣ የቤተሰብ ሰብሳቢ፣ መካሪና አፍቃሪ ነበሩ፡፡ ደግነታቸውንም የሚገልጸው ልጆቻቸው ብቻ ሳይሆኑ ባብዛኛው የዘመድ አዝማድ ልጆች “ዳዲዬ ደጉ” የሚል የቅጽል ስም ሰጥተዋቸዋል፡፡

በእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም ከ1984 ዓ.ም. – 2009 ዓ.ም. ድረስ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ የልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው በመሥራት፣ ለገዳሟ የሚያስፈልጉትን እንደ ቤተልሄም፣ ማህሌት መቆሚያ አዳራሽ፣ ሙዚየም፣ ቢሮዎችና ከ350 የሚበልጡ ፉካዎች ከባለቤታቸው ወ/ሮ የምሥራች ፈለቀ እና ከኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን አሠርተዋል፡፡ እንዲሁም፣ ቤተ ክርስቲያኗን በጠቅላላ አሳድሰው በአቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ፣ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንት አስመርቀዋል፡፡ ለዚህች ገዳም እና ለተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በርካታ የገንዘብ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በእናታቸው ክብርት ወ/ሮ አጥናፈወርቅ ከበደ ትውልድ ቦታ ልዩ ስሙ አመንቴ በሚባለው ስፍራ ከባለቤታቸው ከወ/ሮ የምሥራች ፈለቀ ዕርገቱ ጋር አንድነት በመሆን የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን በ2001 ዓ.ም. አሳንጸው ለምእመናኑ አስረክበዋል፡፡ ለዚህም ቤተ ክርስቲያን ከዓመት እስከ ዓመት የሚያስፈልገውን መገበሪያና የቤተ ክርስቲያኑን እድሳት እርሳቸው እያሟሉ ኖረዋል፡፡ በተጨማሪም፣ አመንቴ ውስጥ ለሚገኘው የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የኬሚስትሪ ላቦራቶሪ፣ መጻህፍት ቤትና የአስተማሪዎች ክፍል (staff room) ከወንድማቸው ከዶ/ር ሄኖክ ክፍሌ ዳዲ ጋር አንድነት በመሆን በእናታቸው በወ/ሮ አጥናፈወርቅ ከበደ ስም የሚጠራ ህንፃ አሠርተው ለት/ቤቱ አስረክበዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ ክፍሌ ዳዲ ሚያዝያ 26 ቀን 1961 ዓ.ም. ወ/ሮ የምሥራች ፈለቀ እርገቱን በተክሊል አግብተው አራት ልጆች አፍርተዋል፡፡ እነርሱም ምስራቅ ዮሐንስ ክፍሌ፣ ተሾመ ዮሐንስ ክፍሌ፣ ቡኒ ዮሐንስ ክፍሌ እና እንደ ልጃቸው የሚያዩት ቴዎድሮስ መጨጊያ ቢራቱ ናቸው፡፡ ከነዚህም ፍሬዎች ስድስት የልጅ ልጆች አፍርተል፡፡ አቶ ዮሐንስ ክፍሌ ባደረባቸው ህመም በሆስፒታል ሲረዱ ቆይተው፣ አርብ ታህሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም.፣ በኪዳነ ምሕረተ ዕለት፣ ፈጣሪያቸው ወደ አዘጋጀላቸው ወደማያልፈው ዓለም ሄደዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *