ይፍቱስራ ቱጂ ወልቀባ

ይፍቱስራ ቱጂ ወልቀባ

ኤፍ ኤም አዲስ  97 .1 ከጀመሩት አንዷ – ይፍቱስራ ቱጂ ወልቀባ

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸውን ሰዎች ጠቁሙን ፤ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪካቸዎን እናወጣለን፡፡

በ tewedajemedia@gmail.com ጥቆማዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡

ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ በተለይ ኤፍኤም አዲስ 97 ነጥብ 1 በ1992 ከጀመሩት መካከል አንዷ ይፍቱስራ ቱጂ ትነሳለች፡፡ ይፍቱስራ ባለፉት 21 አመታት በሚድው ዘርፍ ያሳለፈችው ታሪክ ተሰናድቶ ሲቀርብ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ውልደትና እድገት

ይፍቱስራ ቱጂ ከእናቷ ከወይዘሮ ፋኖስ ማሞ እና ከአባቷ ከአቶ ቱጂ ወልቀባ በአዲስ አበባ ቂርቆስ አካባቢ ተወለደች፡፡ ቤተሰቦቿ 8 ልጆች ሲኖራቸው እርሷ አራተኛዋ ናት፡፡  በወቅቱ መልመጃ ተብሎ የሚጠራውን ትምህርት የጀመረችው በአካባቢው በሚገኘው ጥበብ ገበያ በተባለው ተማሪ ቤት ነበር፡፡

እስከ ስድስተኛ ክፍልም በዚያው ትምህርት ቤት ተምራለች፤ የልጅነት ጊዜዋን ከአብሯደጎቿና ከትምህርት ቤት ጓደኞቿ ጋር ትርጉም ባለውና  በመልካም ሁኔታ አሳልፋለች፡፡ እግር ኳስንና መረብ ኳስን በጣም ትወድ ነበር፤ መምህራኖቿ ሲጫወቱ ከማየትና ከማድነቅ ባለፈም ጥሩ የእግር ኳስ ተጫዋችም ነበረች፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን የተማረችበት ጥበብ ገበያ ትምህርት ቤት ከስድስተኛ ክፍል በላይ የሚያስተማር ባለመሆኑ እንደዚሁም ቤተሰቦቿም መኖሪያቸውን ከቂርቆስ አካባቢ ወደ በቅሎ ቤት  በመቀየራቸው ምክንያት በመኖሪያ አካባቢያቸው ቀድሞ የቂርቆስ ታቦት ማደሪያ የነበረውና ቀበሌ 45 ሜዳ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ በተሰራው ወርሀ የካቲት ትምህርት ቤት የሰባተኛና የስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡

ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል በዚያው አካባቢ በሚገኘው በአብዮት ቅርስ ወይም በቀድሞ መጠሪያው ጂሲኤ ተብሎ በሚታወቀው ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች፡፡

አባቷ በርካታ መፅሀፍትን እያነበቡና ሬዲዮ ሲያዳምጡ እያየች ስላደገች ከልጅነቷ ጊዜ ጀምሮ የሬዲዮ አድማጭ እንድትሆን ረድቷታል፡፡

የትምህርት ሁኔታ

ከቆይታ በኋላ ግን ሙያዋን ይበልጥ ሊያጠነክርላት እንደሚችል በማመን በ2002 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሳ በመግባት በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በ2005 ዓ.ም ይዛለች፡፡

ይፍቱሥራ በአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ያመጣችው ውጤት በወቅቱ በቀን ዩኒቨርሲቲ ወይም ኮሌጅ ገብቶ ለመማር የሚያስችል ባይሆንም በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በማታው የትምህርት ክፍል ገብቶ ለመማር ስላስቻላት በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ -ጽሁፍ ዘርፍ ትምህርቷን ተከታትላ በ1989 ዓ.ም በዲፕሎማ ተመርቃለች፡፡

ዲፕሎማዋን ለማሻሻል በ1995 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብታ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ ዘርፍ መማር ብትጀምርም አድማስ ዩኒቨርሲቲ በአይሲቲ ዘርፍ ነፃ የትምህርት እድል ስላመቻቸላትና ትምህርቱም በወቅቱ አዲስ በመሆኑ አዲስ ነገርን ለማወቅ ካላት ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጀመረችውን ትምህርት አቋርጣ የአይሲቲ ትምህርቷን ቀጥላ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህንንም ለሶስት አመት ከተከታተለች በኋላ በነበረባት የስራ ጫና ምክንያት ልታቋርጠው ተገዳለች፡፡

የስራ ሁኔታ

ከ1990 ዓ.ም -1991ዓ.ም በብርሀነ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት  ከ6ኛ ክፍል እስከ 8ኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ ትምህርትን ስታስተምር የቆየች ሲሆን

በ1992 ዓ.ም ደግሞ በቀስተ- ደመና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በተመሳሳይ ከ6ኛ ክፍል እስከ 8ኛ ክፍል አስተምራለች፡፡ በመምህርነት ባሳለፈችባቸው ጊዜያትም ተማሪዎችን አሳታፊ የሆኑ የተለያዩ ክበባትን አስተባብራለች፡፡ ከማስተማሩ ጎን ለጎን ተማሪዎች መልካም ስነምግባር እንዲኖራቸውና ንፅህናቸውን የጠበቁ ንቁ ዜጋ እንዲሆኑ ካላት ጉጉት የተነሳ በትምህርት ቤቶቹ በቆየችባቸው አመታት የራሷን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች ፡፡ 

ይፍቱሥራ ምንም እንኳን የመምህርነትን ሙያ ብትወደውም ከልጅነቷ ጀምሮ የጋዜጠኝነት ሙያ ፍቅር ስለነበራት፣ በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቤት ቆይታዋም በሚኒ ሚዲያ ላይ መሳተፏ እንደዚሁም በወወክማ የአማተር የስነ ፁሁፍ ስልጠና መውሰድዋ በተጨማሪም በለገዳዲ የሬዲዮ ጣቢያ ስትሳተፍ መቆየቷና የረጅም ጊዜ የሬዲዮ አድማጭ መሆኗ ጭምር እንደዚሁም ለሙያው ፍቅር እንዳላት በሚያውቁ ጓደኞቿ ግፊት በ1992 ዓ.ም በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ሲቋቋም የጣቢያውን በር ልታንኳኳ ችላለች፡፡

በሙያው ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ለጣቢያው ሀላፊዎች ቢሯቸው በመሄድ ከነገረቻቸው በኋላ የድምፅ ፈተና ተሰጣት፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ የወቅቱ የጣቢያው አስተባባሪ ሰሎሜ ደስታ ከሰኔ 27 ቀን 1992 ጀምሮ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ‹‹ስልጠናውን ተከታተይና ስራውን መጀመር ትችያለሽ›› የሚል ምላሽ በስልክ ነገሯት፡፡ በወቅቱ የተማሪዎች ትምህርት እየተጠናቀቀ በመሆኑ ከማስተማሩ ስራዋ ጋር ሳይጋጭባት በኢትዮጵያ ሬዲዮ አንጋፋ ጋዜጠኞችና የቴክኒክ ባለሙያዎች አማካኝነት መሰረታዊ የጋዜጠኝነት ስልጠና በመውሰድ ጣቢያውን ተቀላቀለች፡፡

ከሰኔ 27 ቀን 1992 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ 4 ቀን 1998 ዓ.ም ድረስ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በቆየችባቸው ጊዜያትም የተለያዩ ፕሮግራሞችን ሰርታለች፡፡

የሰራቻቸው ፕሮግራሞች

የአዲስ መንደር ፕሮግራም ፤- የአዲስ አበባ መንደሮችን አመሰራረት፣ ስያሜና የማህበረሰቡን ማህበራዊ ህይወት የሚያስቃኘውን እንቡጦቹ ፤- የልጆች ፕሮግራምን ስታዘጋጅ ቆይታለች፡፡ በተጨማሪም

በተለያዩ ርዕሰ- ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የስልክ ውይይቶችንም ትመራ ነበር፡፡ ከውይይቶቹ መካከል ሊንኬጅ ፕሮጀክት የሚባል ድርጅት ለብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎች በተለይም በልጆች ፕሮግራም ላይ ለሚሰሩ ጋዜጠኞች የጡት ማጥባትና የህፃናት አመጋገብ ላይ በማተኮር በአዳማና በባህር ዳር በሁለት ዙር የሰጠው ስልጠናን መሰረት አድርጋ ከስልጠናው ያገኘችውን ልምድ ወደ ማህበረሰቡ ለመድረስ ከልጆችና ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ ተከታታይ የስልክና የስቱዲዮ ውይይቶችን ጣቢያውን እስከ ለቀቀችበት ጊዜ ድረስ አከናውናለች፡፡

በዚህም በ1999 ዓ.ም ‹‹በህፃናት መብት ዙሪያ ጉልህ አስተዋፅኦ›› በሚል ለመገናኛ ብዙሀን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ሴቭ ዘ ችልድረን ዴንማርክ ባወጡት ውድድር መሰረት በውይይቱ ላይ ከተሰሩት ስራዎች መካከል ‹‹ልጆችን ከአደጋ መጠበቅ›› በሚል የተዘጋጀው ፕሮግራም በሬዲዮ ዘርፍ ለመሸለም አብቅቷታል፡፡

ለይፍቱስራ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የጋዜጠኝነት የመጀመሪያ መስሪያ ቤት ከመሆኑም ባሻገር በኢትዮጲያ ሬዲዮ ከሚገኙ አንጋፋ የስራ ባልደረቦቿ ልምዷን የምታሳድግበት መሆኑ እንደዚሁም የሰራተኛው ማህበራዊ መስተጋብር የቤቷን ያህል እንድትወደው አድርጓታል፡፡ ይሁን እንጂ ባላወቀችውና ምክንያቱ ባልተገለፀላት ጉዳይ በወቅቱ በነበረው ስራ አስኪያጅ በተፃፈ ደብዳቤ  ታህሳስ 4 ቀን 1998 ዓ.ም ከምትወደው ስራዋና መስሪያ ቤቷ እንድትሰናበት ሆኗል፡፡

ያም ሆኖ በስራዋ የተፈፀመባት በደል ቢያሳዝናትም ለሙያዋ ካላት ፍቅር ተስፋ አልቆረጠችም፤ መቀመጫውን ለንደን ያደረገና በስካይ ቴሌቪዥን ፕሮግራሙን ያሰራጭ በነበረው አለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ቴሌቪዥን ውስጥ ተቀጥራ መስራት ጀመረች፡፡ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ድርጅቱ ቢሮውን እስከ ዘጋበት 2000 ዓ.ም ድረስ የአዲስ አበባ ወኪል በመሆን ስትሰራ ቆይታለች፡፡

እንደዚሁም ድርጅቱ በየሶስት ወሩ በሚያሳትመው ንስር በሚባለው መፅሄትም በአዘጋጅነት ሰርታለች፡፡አለማቀፍ የኢትዮጵያውያን ቴሌቪዥን የአዲስ አበባ ቢሮውን ሲዘጋና ስራዋ ሲቋረጥም ‹‹ይፍቱስራ አድቨርታይዚንግ›› የሚል የማስታወቂያ አገልግሎት በመክፈት የተለያዩ የሚዲያ ስራዎችን ስትሰራ ቆይታለች፡፡

  • ከመስከረም 2001 ዓ.ም – ጥር 2005 ዓ.ም ካገር ማዶ ፕሮግራም፡- የ30 ደቂቃ ርዝማኔ ያለውና ሳምንታዊ ፕሮግራም፡፡ ፕሮግራሙ ስለ ውጭ ሀገራት የተለያዩ መረጃዎችን የሚሰጥ (በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ) በፎረም ኦን ሰስተነብል ቻይልድ ኢንፓወርመንት የገንዘብ ድጋፍ የሚከተሉትን ፐሮግራም አዘጋጅታለች፡፡
  • በ2001 ዓ.ም የህፃናት ጉልበት ብዘበዛ መከላከል ላይ ያተኮረ የ20 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ፕሮግራም ለሦስት ወራት (በድሬ ኤፍ ኤም የተላላፈ )
  • በ2002 ዓ.ም የህፃናት ጉልበት ብዘበዛ መከላከል ላይ ያተኮረ የ20 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ፕሮግራም ለሦስት ወራት (በድሬ ኤፍ ኤም የተላላፈ)
  • በ2003 ዓ.ም በህፃናት ጉልበት ብዘበዛ መከላከል ላይ ያተኮረ የ30 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ፕሮግራም ለሁለት ወራት (በሸገር ኤፍ ኤም 102.1)
  • በ2004 ዓ.ም የህፃናት ጉልበት ብዘበዛ ላይ ያተኮረ የ30 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ፕሮገራራም ለ ሁለት ወራት (በሸገር ኤፍ ኤም 102.1)
  • በ2005 ዓ.ም ሴክስ ቱሪዝምን መከላከል ላይ ያተኮረ የ30 ደቂቃ ርዘማኔ ያለው የ6 ወራት ፕሮግራም (በኤፍ ኤም 96.3)

እንደዚሁም

  • በ2004 ዓ.ም በህፃናት ጉልበት ብዘበዛ መከላከል ላይ ያተኮረ የ30 ደቂቃ ርዝማኔ ዶክመንተሪ አዘጋጅታለች፡፡ ከሌሎች የሙያ አጋሮቿ ጋር መስራትን የምትወድና ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ስለምታምን
  • ከ2008 ዓ.ም – 2009 ዓ.ም ከኤፍ ኤም 96.3 ጋር በመተባበር ‹‹የኛ መስተንግዶ የሚል›› ትኩረቱን በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ያደረገ የአንድ ሰአት ርዘማኔ ያለው ሳምንታዊ ፕሮግራም ከጋዜጠኛ ዳንኤል ብርሁኑ እና ከጋዜጠኛ ርብቃ ታደሰ ጋር በመሆን ስታቀርብ ቆይታለች፡፡
  • ለተለያዩ ድርጅቶች ማስታወቂያዎችንም ሰርታለች፡፡

በራሷ የማስታወቂያ አገልግሎት ከምትሰራቸው ስራዎች ውጪም

  • ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ መስፍን አሰፋ የሚዲያ ፕሮግራም ዝግጅት ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በመተባበር በሚያቀርበው ‹‹አዲስ ገፅ›› ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ከዋና አዘጋጁ ከጋዜጠኛ መስፍን አሰፋና ከጋዜጠኛ ዳንኤል ብርሀኑ ጋር በመሆን በፕሮግራሙ ላይ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
  • ከየካቲት 2013 ጀምሮ በፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር እየተዘጋጀ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የሚተላለፍ የ30 ደቂቃ ርዝማኔ ያለውና በኮቪድ ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚያተኩር ‹‹ዙሪያ ሀሳብ›› የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራምንም ስታዘጋጅ ቆይታለች፡፡

በተጨማሪም ወደ ቴሌቪዥንም ዘርፍም በመመለስ

  • ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ አዲስ ቴሌቪዥን በዜና አንባቢነት እያገለገለች ትገኛለች፡፡
  • በአጠቃላይ ይፍቱሥራ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በመፅሄት ላይ አቅሟ በፈቀደ መጠን መረጃዎችን ለማህበረሰቡ ለማጋራት እየተጋች ያለች ባለሙያ ናት፡፡

ሙያዋን ለማሻሻል የወሰደቻቸው ስልጠናዎች

  • ሳፖርቲንግ ፐሮፌሽናል ጆርናሊዝም ፡- 2012 ዓ.ም ‹‹በዩ ኤስ ኤምባሲ››
  • ኢንተርፕርነርሺፕ ፡- የካቲት 2006 ዓ.ም ለ5 ቀናት ‹‹በዩኤን ዲ ፒ››
  • ሴክሹዋል ሪፕሮዳክቲቭ ኸልዝ ሪፖርቲንግ ፡- ህዳር 2003 ዓ.ም ለ3 ቀናት ‹‹በአይ ሲ ኤፍ ጄ እና ፒ ኤች ኢ››
  • ማናጅመንት ላይ ያተኮረ ስልጠና ፡- 2002 ዓ.ም ለ10 ቀናት ‹‹በደቡብ በአፍሪካ ግርሀም ስታወን ዩኒቨርሲቲ ››
  • ሬዲዮ ፊውቸር ሜኪንግ ፣ ኤች አይ ቪ ሪፖርቲንግ ኤንድ ዲጂታል ኤዲቲንግ ፡- መጋቢት 2001 ዓ.ም ለ5 ቀናት ‹‹በዩኤስ ኤድ››
  • አድሬሲንድ ጄንደር፡- 1998 ዓ.ም ለ5 ቀናት ‹‹በብሪቲሽ ካውንስልና አይሪሽ ኤድ››
  • ኤቲካል ሪፖርቲንግ ኦን ችልድረን ፡-ጥቅምት 1997 ዓ.ም ለ3 ቀናት ‹‹በሴፍ ዘ ችልድነር ስዊዲንና በኤፍ ኤስ ሲ ኢ››
  • ራዲዮ ፎር ኒውትርሽን ቢሄቪየር ቼንጅ ፡- ህዳር 1997 ለ5 ቀናት ‹‹ በሊንኬጅ ፕሮጀክት›› አንደኛ ዙር
  • ድራግ ኢንፎርሜሽን ፡- መጋቢት 1997 ለ3ቀናት ‹‹በዳካ እና ዳብሊው ኤች ኦ››
  • ሬዲዮ ፎር ኒውትሪሽን ቢሄቪየር ቼንጅ  ፡- ሰኔ 1997 ‹‹በሊንኬጅ ፕሮጀክትና በዩ ኤስ ኤድ›› ሁለተኛ ዙር
  • ዲጂታል ኦዲዮ ሪኮርዲንግ ኤንድ ኤዲቲንግ ፡- ሀምሌ 1996 ዓ.ም ለ5 ቀናት ‹‹በቢቢሲ ወርልድ ትረስት››
  • መሰረታዊ ጋዜጠኝነት ሙያ፡-  ጥቅምት 1995 ዓ.ም ለ15 ቀናት ‹‹በሴት የብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎች ማህበርና በማስ ሚዲያ ትሬሊንግ››
  • መሰረታዊ ጋዜጠኝነት ሙያ ፡- ህዳር 1994 ለ5 ቀናት ‹‹በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ኢኒስቲቲዩት››
  • የኤች አይ ቪ ዘገባ ፡- ሀምሌ 1994 ዓ.ም ለአንድ ወር ‹‹በዩኒሴፍ አትዮጵያና በሴት የብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎች ማህበር››

በሰራቻቸው ስራዎችና ባበረከተችው አስተዋፅኦ የተገኘ ሽልማትና የምስጋና የምስክር ወረቀት

  • የሬዲዮ አመትን በማስመልከት 2013  በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን
  • ‹‹የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ለአለም በማስተዋወቅ በተሰራ ስራ›› በሚል ከአለማቀፍ የኢትዮጵያውያን ቴሌቪዥን የምስክር ወረቀት 1998 ዓ.ም በአለማቀፍ የኢትዮጵያውያን ቴሌቪዥን በቀረበ ፕሮግራም
  • በአፍሪካ ህብረት መመስረቻ ወቅት ‹‹በሬዲዮ ንቁ አቅራቢነት›. በሚል ‹‹ ከአፍሪካ ህብረት›› የምስክር ወረቀት ሀምሌ 1996 ዓ.ም በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ላይ በቀረበ ፕሮግራም
  • ‹‹የኤች አይ ቪን መረጃዎችን በፊውቸር ፕሮዳክሽን በማዘጋጀት›› በሚል 2003 ዓ.ምበሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ላይ በተላለፈ ፕሮግራም የድምፅ መቅረጫ
  • ‹የህፃናት መብትን መጠበቅ በተመለከተ›› በሚል በሬዲዮ በተላለፈ ፕሮግራም ሴፍ ዘ ችልድረን ዴንማርክና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1999 ዓ.ም በኤፍ ኤም 97.1 በተላለፈ ፕሮግራም  የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት 

የቤተሰብ ሁኔታ

ይፍቱስራ ቱጂ  የሚድያ ባለሙያ ጌታቸው ማንጉዳይ ጋር ጋብቻ መስርታ  በሰላምና በፍቅር እየኖረች ትገኛለች፡፡

ማጠቃለያ

ይፍቱስራ ላለፉት 21 አመታት ላይ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ትገኛለች፡፡ በሙያዋ የበለጠ ለመስራት እንደምትተጋ ታምናለች፡፡ በራስ መተማመኗ ከልጅነቷ ጀምሮ ዛሬም አብሯት አለ፡፡ ቀና በመሆን የሌሎችንም ቀን መልካም ማድረግ የህይወት መርኋ ነው፡፡  በጋዜጠኝነት ዘርፍ ከዚህ በላይ አቅሜን አሳይቼ መገኘት ፈልጋለሁ የምትለው ይፍቱስራ ብዙ ህልሞችን ሰንቃለች፡፡ ምንም አይነት ውጣውረድ የማይበግራት ይፍቱስራ  በመስራት ብቻ ታምናለች፡፡ ባለፉት 21 አመታት ያለፈችባቸው መንገዶች ብዙ አስተምረዋታል፡፡ እስካሁን ያለፈችበት መንገድ ግን በእድሜ ታናናሽም ፤ እኩያም ለሆኗት አስተማሪ ስለሆነ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች የይፍቱ ስራ ታሪክ ለትውልድ እንዲቀመጥ እነሆ አድርገናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *