ይነገር ጌታቸው

ይነገር ጌታቸው

ከከተማው መናኝ እስከ ጠመንጃና ሙዚቃ (ዝምተኛ ታሪክን ፈላጊው ብዕረኛ)

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሰራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡

በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ወጣቱ የስነጽሁፍ ሰው እና ጋዜጠኛ ይነገር ጌታቸው(Yeneger Getachew) አንዱ ነው፡፡ ይነገር ለህትመት ባበቃቸው መጽሀፎች ያሳየው ትልቅ ጥረት እና በጽሁፍ አርትኦት ስራዎች ላይ እያሳየው ያለው ጥረት የህይወት ታሪኩን ለመሰነድ በቅተናል፡፡ ከባለታሪኩ የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ እዝራ እጅጉ ታሪኩን እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡

ማእረግ

ጊዜው 1981 ነው፡፡ በቀይና ነጭ ሽብር የቀለመው የኢትዮጵያ አብዮት አሁንም እልፎችን እየበላ ነው፡፡ አቶ ጌታቸው አሞኘ ለፖለቲካው ሩቅ ናቸው፡፡ ባለቤታቸው ይመኙሻል ሙሉም እንደዛው፡፡ ይሁንና አገራዊ ምስቅልቅሉ የንግድ ሥራቸው ላይ ኪሳራ ማስከተሉ አልቀረም፡፡ ወራት መጥተው ወራት ሲሄዱ እንደውም እየባሰበት ሄደ፡፡ አላመነቱም፡፡አቶ ጌታቸው ዘርፍ ቀየሩ፡፡ በመንግስት ቤት ቅጥር ፈጸሙ፡፡ ብቸኛ ወንድ ልጃቸው የተወለደው ከዚሁ ሁሉ ውጣውረድ በኋላ ነው፡፡ ባለቤታቸው ይመኙሻል ሙሉ ከሁለት ሴት ልጆች በኋላ ያገኙትን ብቸኛ ወንድ ልጃቸውን ማዕረግ አሉት፡፡

የአቶ ጌታቸው ወዳጆች ግን ያን ዘመን አስታውሰው የለም ይናገር ጌታቸው ! እንበለው ሲሉ ተሟገቱ፡፡ አቶ ጌታቸው ያንን ወቅት አልፎ ይናገራል እንደማለት ነበር፡፡ ማዕረግ የስሙን መብዛት ሲያስብ የእጅጋየሁ ሽባባውን ዜማ ያስታውሳል፡፡ “ስም የለኝም ስም የለኝ በቤት” ማለት ይቀናዋል፡፡ እናቱ ማዕረግ፣ማዕረጌ ነህ ይሉታል፡፡ እህቶቹ ብቸኛውን ወንድማቸውን ማርዬ ሲሉ ያቆላምጡታል፡፡ የአባቱ ጓደኞች ይናገር፣ይነገር፣ይናገራል ጌታቸው ሲሉ ይጠሩታል፡፡ በወርሃ መጋቢት 15ኛው ቀን 1981 ዓ.ም ጎጃም ፍኖተ ሰላም የተወለደው ይነገር ጌታቸው (ማዕረግ) የመዝገብ ስሙን የወሰኑለት የአባቱ ጓደኛ አቶ በላይ በየነ ናቸው፡፡ ከልጃቸው እርቅይሁን በላይ ጋር ትምህርት ቤት ወስደው ሲያስመዘግቡት አስቀድመው ያወጡለትን ስም አጸደቁለት፡፡ በዚህ የተነሳም የአባቱን ወዳጅ ስያሜ ለመዝገቡ አድርጎ በቤትና አብሮ አደጎቹ ማዕረግ እየተባለ ዘለቀ፡፡ ለሕትመት ባበቃቸው ሁለት መጻሕፍት ላይ ሁለት ስም መጠቀሙም ለዚህ ነው፡፡

ይነገር ጌታቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው ፍኖተ ሰላም በሚገኘው የባከል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ይህ ቆይታው ሲጠናቀቅም በ1994 ዓ.ም ወደ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አንደኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሸጋገረ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በዳሞት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተለ፡፡ የማዕረግ የልጅነት ትዝታ መነሻውም መድረሻውም ጨዋታ ብቻ ይመስላል፡፡ በቀዳሚው ዘመን ትምህርት ብዙ የሚወድ ልጅ አልነበረም፡፡ አንደኛና ሁለተኛ ክፍልን የጨረሰው በብዙ ማባበያ ነው፡፡ ወደ ትምህርት ቤት አልሄድም ይላል፡፡ ከቤቱ በስንት ሽንገላና ማስፈራሪያ ከሄደም በኋላ መምህራኑ አረፈድክ ብለው ይገርፉታል፡፡

ኋላ ላይ ወደ ትምህርት ቤት መሔጃ ሰዓቱ ሲቃረብ አፍንጫውን አሽቶ ‹‹ነስር ነሰረኝ ልተኛ›› ማለት ጀመረ፡፡ የታላላቆቹ ሐይማኖት ጌታቸውና መስከረም ጌታቸው የደረጃ ተማሪ መሆን ወኔ የሆናቸው ወላጆቹ ግን የሚሰሙት አልነበሩም፡፡ ፊትህን ታጥበህ ሂድ ይሉታል፡፡ በእንዲህ ያለው መልክ የተጀመረው የይነገር የትምህርት ሕይወት እየቆየ ሲሄድ መስመር ያዘ፡፡ ጓደኞቹ እንደሚሉት በልጅነቱ ትምህርት ቤት አልሄድም እያለ ቤተሰብ ያስቸግር የነበረው ማዕረግ በዩኒቨርስቲ ቆይታው ከፍተኛ ወጤት በማምጣት(ሰቃይ በመሆን) ቤተሰቦቹን ክሷል፡፡

ይነገር ሕፃንነቱ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያልፍም ነፍስ እያወቀ ሲሄድ ግን እጅጉን ዝምተኛና አስተዋይ ልጅ እየሆነ መሄዱን አብሮ አደጎቹ ይመሰክራሉ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን መከታተል ሲጀምርም የተላያዩ ጋዜጦችን በማንበብ የንባብ ልምዱን ማስፋት ያዘ፡፡ እዚህ ወቅት ላይ ሁለቱ እህቶቹ ሃይማኖት ጌታቸውና መስከረም ጌታቸው የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን በጋዜጠኝነት ስለተቀላቀሉ የሚነበብ ነገር ለማግኘት አልከበደውም፡፡ ይህ መንገድም የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያለ የትምህርት ቤቱን ሚኒ ሚዲያ ክበብ እንዲቀላቀል አደረገው፡፡ በሚሊኒየሙ ዋዜማም ሃይማኖትና መስከረም ጌታቸው በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ዝግጅቶች ስማቸው ሲናኝ ታናሻቸው ይነገርም በሚኒ ሚዲያ ዘገባዎቹ በትምህርት ቤቱ ስሙ ይጠቀስ ጀመር፡፡

ይነገር ጌታቸው(Yeneger Getachew) የመጀመሪያ ዲግሪውን ያጠናው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ በርካታ ወዳጆቹ እንደሚሉትም ሌላው ማዕረግ የተወለደው እዚህ ቅጽር ውስጥ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ረጅም ሰዓትን ማንበብ የሚወድ፤“የት ጠፋ?” ሲባል አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኬኔዲ ቤተ-መጻሕፍት ቤት “ስታክ” የተባለው የመጻሕፍት ክምችት ክፍል ውስጥ የሚገኝ አፍላ ወጣት ለመሆን በቃ፡፡ በዩኒቨርስቲ አብረውት የተማሩ ጓደኞቹ በግቢ ቆይታቸው “በይነገር ሰዓት” የሚል መግባቢያ የፈጠሩትም በዚህ ወቅት ነው፡፡ ይነገር በዩኒቨርስቲ ቆይታው ራት ሰቅሎ የመተኛት ልምድ ነበረው፡፡ ወዳጆቹ እንደሚሉት የእሱ ቀን የሚጀምረው ከእኩለ ሌሊት ስድስት ሰዓት በኋላ ነው፡፡ በመሆኑም ጓደኞቹ እኩለ ሌሊትና ከዛ በኋላ የሆነን ነገር ሲገልጹ በይነገር ሰዓት ማለት ይቀናቸው ነበር፡፡

ማዕረግ በትምህርት ቤት ቆይታዬ ፎክሎር (የባሕል ጥናት) መማሬ ብዙ ነገሮች ላይ ያለኝን ምልከታ ቀይሮታል ይላል፡፡ “ብዙ የጥናት ዘርፎች የሰውን ልጅ ሕይወት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚካሔዱ ናቸው፡፡ ፎክሎር ግን የሰውን ሕይወት ብቻ ሳይሆን ራሱን ሰውን የሚያጠና ዘርፍ በመሆኑ ለሃይማኖት፣ፍልስፍና፣ሥነ-ጽሑፍ ፣ታሪክ እና ሥነ-ልቦና ቅርብ እንድሆን ረድቶኛል፤” ሲል ይናገራል፡፡ በእርግጥም የይነገር ሕይወት በዩኒቨርስቲና ከዩኒቨርስቲ ቆይታው በኋላ በንባብ የታሸ መሆኑን መምህራኑም ይመሰክራሉ፡፡ አዲስ ማለዳ፣አዲስ አድማስ እና ሪፖርተር ጋዜጦች ላይ አልፎ አልፎ ይጽፋቸው የነበሩ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚተነትኑ መጣጥፎቹም ይህን ያሳያሉ፡፡ በ2006 የሁለተኛ ድግሪውን (M.A) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያገኘው ይነገር ጌታቸው በባሕል ጥናትና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪውን ከሰራ በኋላ በሙዚቃ ማሰብና አገሩን ዳግም መተርጎም ይቻላል ወደሚል አመለካካት ተሸጋግሯል፡፡

የከተማው መናኝ” እና “ጠመንጃና ሙዚቃ” በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቃቸው መጻሕፍት ላይም የሞከረው አንዱ ጉዳይ እሱ እንደሆነ ያምናል፡፡ ይነገር በታሪክ ጥናት ውስጥ የዋልተር ቤንጃሚን ትኩረት ይበልጥ ይስበኛል ይላል፡፡ ጊዜው የአሸናፊዎች ታሪክ የሚመረመርበት የተሸናፊዎች፣ድሆችና በስማቸው ምንም ነገር ያልተጻፈላቸው ሰዎች ድርሳን የሚቀርብበት መሆን አለበት ሲል ይገልፃል፡፡ “ጠመንጃና ሙዚቃ” የተሰኘው መጽሐፌ አገሩን ያቆሙ ድሆችና ታሪክ ያልተፃፈላቸው ዝምተኞች ድርሳን ነው፡፡ የኢትዮጵያን ነፃነት ካለ አዝማሪዎች ተሳትፎ ማሰብ ያዳግታል፡፡ ነገር ግን የአገሬው ታሪክ እነዚህ ባለውለታዎች ቁጥር ብቻ አድርጓቸው ቀርቷል፤ የእኔ ሙከራ እነዚህን አገር ያቆሙ ዝምተኛ ጀግኖች ታሪክ ማኖር ነው” ይላል- ይናገር፡፡ በእርግጥ ተግባሩ የሙዚቃችንን ታሪክ መመርመር ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁኑስ በሙዚቃችን ሀሳብ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ታሪክ በሌላ አንፃር እንድንመረምረው ዕድል ፈጥሯል፡፡

ይነገር ለአምስት ዓመታት ባገለገለበት ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ላይ “ትዝታን በዜማ” በተሰኘ የቆዩ ሙዚቃዎችን በሚዳስስ ፕሮግራሙ እውቅናን ያገኘ ቢሆንም ይበልጡኑ ስሙ መጠቀስ የጀመረው ግን የታዋቂውን ሙዚቀኛ ኤልያስ መልካ የሕይወት ታሪክ ለአንባቢያን ካደረሰ በኋላ ነው፡፡ በ2013 ለገበያ የበቃው “የከተማው መናኝ” የሚል ርዕስ ያለው ይህ ሥራ በወቅቱ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን ደራሲውንም ለተለያዩ ክብሮች አብቅቷል፡፡

ይነገር የኤልያስ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ዝግጅት አጋጣሚ የመጣ ሀሳብ ነው ይላል፡፡ “ጠመንጃና ሙዚቃ” ለንባብ ሊበቃ በተቃረበበት ጊዜ ኤልያስ መልካ ሕይወቱ አለፈ፡፡ እዚህ ላይ ሁለት አጋጣሚዎች ያለቀውን መጽሐፍ ወደ ጎን ገፍቶ የኤልያስን ሕይወት እንዲጽፍ ምክንያት ሆኑት፡፡ ቀዳሚው በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ኤልያስ መልካን አስመልክቶ ከሠርጸ ፍሬ ስብሃት ጋር ጽሑፍ ካቀረቡ በኋላ ታዳሚው ሰፋ ባለ መልኩ ወደ መጽሐፍነት ብትቀይሩት የሚል ጥያቄ በማቅረቡ ነው፡፡ ሁለተኛው ኤልያስ መልካ የቀደሙ ሙዚቀኞች ሕይወት መጎሳቆልና ታሪካቸው በወጉ አለመታወቅ ያሳስበው ስለነበር ሌሎችን የሚያከብርን አስቀድሞ ማክበር ያስፈልጋል ብሎ በማመኑ ነው፡፡

“የከተማው መናኝ” መጽሐፋ መነሻ እንዲህ ያለ ቢሆንም የዳሰሰው ጉዳይ ግን የኤልያስ መልካን ሕይወት ብቻ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይነገር ራሱ እንደሚለውም ኤልያስ ማዕከል ይሁን እንጂ ለመዳሰስ የሞከረው በአብዮቱ ማግስት የተወለዱ ኢትዮጵያዊያንን የሕይወት መልክና ሥነ-ልቦናዊ ጠባሳ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ተወዳጁ ሙዚቀኛ የዘመን መልክ ነበር ይላል፡፡ ደራሲው ስለ ድርሳኑ ይህን ቢልም “የከተማው መናኝ”ን አስመልክቶ ሀሳባቸውን የሰጡ ኃያሲያን ግን መጽሐፉ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከመዝናኛነት አላቆ ለሥነ-ልቦና፣ ለታሪክና ነገረ-መለኮት ማጥኛነት በመጠቀም በኩል ቀዳሚ የሚባል ሥራ ነው ይላሉ፡፡

ይነገር ጌታቸው(Yeneger Getachew) በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ውስጥ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በመቀላቀል ከ2003-2008 ዓ.ም አገልግሏል፡፡ ከ2008 እሰከ 2012 ዓ.ም ባሉ ዓመታት ሪፖርተር፣አዲስ አድማስ፣አዲስ ማለዳ፣ታዛ እና ድሬቲዩብን በመሰሉ ጋዜጦች፣መጽሔቶችና ድረገጾች ላይ በብዕር ስምና በራሱ ስም የወቅቱን ፖለቲካዊ ቀውስ የተመለከቱ በርካታ ጽሁፎችን ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ በእነዚህ ዓመታትም ከሙያ አጋሮቹ ስንታየሁ ብዙነህና ግዛቸው አሻግሬ ጋር በመሆን በብስራት ኤፍ ኤም 101.1 ላይ ማራኪ መዝናኛ የተሰኘ የራዲዮ ፕሮግራምን ለአድማጮቹ ሲያደርስ ቆይቷል፡፡

በዚህ ሳይወሰንም ከአንድ የጀርመን ድርጅት ጋር በመጣመር የቅደመ- አብዮቱ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ላይ ሰፊ ምርምር አድርጓል፡፡ በ2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና በ2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስት የኢትዮጵያ ባሕሎች አካዳሚ ዓለም አቀፍ የቋንቋና ባሕል ጉባኤ ላይ የመነሻ ጽሁፍና ጥናታዊ ጽሁፎችን አቅርቧል፡፡ የይነገር ልዩ መለያው ተጫዋችነቱ ነው፡፡ ጓደኞቹ ሲበዛ አንባቢ ብቻ ሳይሆን ጨዋታ አዋቂና ትሁት ነው ይሉታል፡፡ ይነገር ጌታቸው በ30ዎቹ የዕድሜ መባቻው ሁለት ተቀባይነትን ያገኙ ጥናታዊ መጻሕፍትን ለአንባብያን አድርሷል፡፡ በአርትዖት በኩልም ልዩ ልዩ መጻሐፍት ላይ ተሳፏል፡፡ በቀጣይ ዓመትም ሦስተኛ ሥራውን ለአንባቢያን ለማድረስ ተስፋ ያደርጋል፡፡

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ የቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቀበት ነው፡፡ ይነገር ጌታቸው በዚህ በወጣት እድሜው ላቀረባቸው መጽሀፎች እውቅና መስጠት እንፈልጋለን፡፡ ሁሉም የዘመኑን ታታሪ ፈልጎ ከሰነደ ሀገር ታሪክ ይኖራታል፡፡ የሀገር ታሪክ በሰዎች ጥረት ውስጥ ይታያል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በመዝገበ-አእምሮ የስነዳ ፕሮጀክቱ በቀዳሚነት የተሰራ በሳል ስራ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ሰዎችን ለመሰነድ ቀዳሚ መስፈርታችን ምን ተሰራ? የሚለውን መቃኘት ብቻ ነው፡፡ ይነገር ለህትመት ያበቃቸው መጽሀፎች በእኛም ሆነ በሌሎች አጥኚዎች ሲታዩ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡በተለይ በዚህ 2 አመት ያሳተማቸው መጽሀፎች በብዙዎች መደነቅ የቻሉ ናቸው፡፡ ለዚህ ጥረቱ ደግሞ እውቅና ብቻ ሳይሆን ከጎኑ ቆመን ልናበረታው ይገባል፡፡ የነገ መድረሻው ትልቅ እንደሚሆን እናምናለን፡፡ ነገ ትልቅ ቦታ የሚደርስን ሰው ደግሞ ጭላንጭሉን አይቶ ወደ ብርሀን ማቃረቡ ቀዳሚ የተመሰረትንበት ግብ ነው፡፡ ወጣቶች ምን ሰራው ገና ነኝ፤ ብለው ቤት እንዲቀመጡ አንሻም፡፡ ዛሬ የሰሩት ይሰነድ-ነገ ስራቸው ሲጨምር ዳግም ተጨምሮ እና ተሻሽሎ ይቀርባል፡፡ ይነገርም በዚህ አያያዙ እየቀጠለ እንደሚሄድ ተስፋ አድርገን የመዝገበ-አእምሮ የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ ታሪኩን ሰንደነዋል፡፡ ታላላቆችንም ታናናሾችንም የሚያስተምር የስራ ታሪክ አለውና በርታ ልንለው እንወዳለን፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ ነሀሴ 24 2015 በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች ተቀመጠ፡፡ በተጨማሪም በመዝገበ-አእምሮ ላይ ከሚሰነዱ 200 ባለሙያዎች አንዱ ይህ የይነገር ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *