ይታገሱ ጌትነት ገበየሁ
ምርምር እና ጽሁፍ የሚወደው ይታገሱ
የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡
ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ አሁን ከድርሰት ፤ከስነ-ጽሁፍና ከምርምር ዘርፍ ታሪኩ የሚቀርብለት ሰው ይታገሱ ጌትነት ነው፡፡
ውልደትና ዕድገት
ይታገሱ ጌትነት ገበየሁ የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ አካባቢ በቀድሞው ከፍተኛ 14 ቀበሌ 12 ባሻ ወልዴ (እሪ በከንቱ) በሚባለው ሰፈር ውስጥ ነው፡፡ ሰኔ 29 1967 የተወለደው ይታገሱ ጌትነት እናቱ ወ/ሮ መነን እሸቴ አባቱ አቶ ጌትነት ገበየሁ ይባላሉ፣ ሁለቱም በንግድ ማተሚያ ድርጅት ውስጥ ለዓመታ ሠርተዋል፡፡ አባቱ አቶ ጌትነት ገበየሁ በ1969 የዚያድባሬ ሠራዊት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ያስተላለፈውን የእናት ሀገር ጥሪን ተቀብለው ዘምተዋል፤ በመጨረሻው የጅግጅጋን ማስለቀቅ ጦርነት ወቅት ካራማራ ላይ ለእናት ሀገራቸው ህይወታቸውን ሰውተዋል፡፡
አባቱን በልጅነቱ ያጣው ይታገሱ ጌትነት ገና የ20ያዎቹ መግቢያ ላይ ከነበረችው እናቱ እና በአካባቢው ተወዳጅ ከነበሩት አዛውንት (ከአባቱ አጎት) ሻረው እንግዳ እና ከባለቤታቸው በለጡ ዳዲ ጋር የልጅነቱን ዘመን አሳልፏል፡፡ አቶ ሻረው እንግዳ ግሩም ጨዋታና ታሪክ አዋቂና አዝናኝ የሚባሉ አይነት ሰው ነበሩ፡፡ የሰላሌ ኦሮሞ የነበሩት ወ/ሮ በለጡም የልጅ ርሃብ ምትክ አድርገው አሳድገውታል፡፡ እናቱ ወ/ሮ መነንም ድመት ግልገሏን በጥርሷ ይዛ ሳስታ እንደምትጠብቅ ሁሉ የሙት ባል ማስታወሻ የምትለውን የበኩር ልጇን አሳድጋዋለች፡፡ ይታገሱ በአጠቃላይ ሦስት ወንድሞች አሉት፡፡ ደራሲ ይታገሱ ጌትነት ህጻናት አምባን እስኪቀላቀል ድረስ የልጅነት ዘመን አስተዳደጉ የተለመደውና መደበኛው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ አይነት እሚሉት አይነት ነው፡፡
የትምህርት ጅማሮ
ይታገሱ ጌትነት ከትምህርት ጋር የተዋወቀው እዛችው አራት ኪሎ በቄስ ትምህር ቤት ውስጥ ነው፡፡ በዘመኑ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ለመቀላቀል ዕድሚያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትን በቀበሌ አማካኝነት በአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይደለደሉ ነበር፡፡ የሰፈር ጓደኞቹ ወደቀዳማዊ ምኒሊክና ዳግማዊ ምንሊክ ትምህርት ቤቶች በዕጣ ሲደለደሉ ይታገሱ እድሜህ አልደረሰም በሚል ከጓደኞቹ ይነጠላል፡፡ ከጓደኞቹ መነጠሉ እና ትምህርት ቤት አለመሄዱ ያብከነከነውን መብከንከን በመመልከት እናቱ በወቅቱ የግል ትምህርት ቤት በነበረው ብርሃነ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት አንደኛ ክፍል ሆኖ ተቀላቀለ፡፡
ከዓመት በኋላ ግን መንግሥት በየቀበሌው ለትምህርት የደረሱ ተማሪዎችን ሲደለድል ይታገሱን የዳ/ምኒልክ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን አንደኛ ክፍል ሆኖ እንዲጀምር ዕጣ አወጣለት፡፡ በመሆኑም ዕድሉን ለመጠቀም ዳግም አንደኛ ክፍልን በዳ/ ምኒልክ ት/ቤት መማር ጀመረ፡፡ ሆኖም አጠቃላይ ከተማሪዎቹ ብልጫ ስላስገኘለት በግማሽ ሴሚስተር ወደሁለተኛ ክፍል ተዘዋወረ፡፡ ዓመቱ ሲጠናቀቅም ወደሦስተኛ ክፍል በማለፍ 1976 ዓ.ም ሦስተኛ ክፍልን ተቀላቀለ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን የይታገሱን የትምህርትም ሆነ የአስተዳደግ አቅጣጫ የሚለውጥ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡
ገና ከማለዳው 1973 ዓ.ም መንግሥት አባቱ በእናት ሀገር ጥሪ ካራማራ ላይ መስዋዕት በመሆኑ ልጁን ተንከባክቦ ለማሳደግ ቢጠይቅም እናቱ እምቢ ብላ በመከልከሏ ጫናው በርትቶባት 1976 የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ የኢትዮጵያ ህጻናት አምባን እንዲቀላቀል ፈቀደች፡፡ የይታገሱ አብዛኛው ጣፋጭ የልጅነት ዘመኑ ይሔው በአፍሪካ ግዙፍ የሚባለው ትምህርት ቤት ነው፡፡ በዚህም ድርጅት ውስጥ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ኦጋዴን አንደኛ መለሥተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተምሯል፡፡ ከዚህም ባሻር በአዲስ አበባ ከፍተኛ 12 እና ተፈሪ መኮንን በሚባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያና ማጠናከሪያ ትምህርቶችን ተከታትሏል፡፡
ይታገሱ ጌትነት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ክፍልን ተቀላቅሎ የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘ ሲሆን ይሄንኑ በማጠናከር የሁለተኛ ዲግሪውን በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍና ፎክሎር ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የሦስተኛ ዲግሪውን እዚያው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በማጥናት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ተከታትሏል፡፡
የጥበባዊ ስራዎች
ይታገሱ ጌትነት ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎች ላይ መሳተፍ በተለይም ሥነ-ጽሑፍ መጻፍ የጀመረው ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ ነው፡፡ ከፍ ካለም በኋላ ህጻናት አምባ እያለ የሥነ-ጽሑፍ መድረኮች ላይ ጽሑፉን ከማቅረቡ ባሻገር በቤተክርስቲያን ውስጥ የተተወኑ ቴአትሮችን መጻፍ ችሏል፡፡ “ቀይ ቃል ኪዳን”፣ “የሞት አያት”፣ “የፍጻሜው ስንብት” የተሰኙ ቴአትሮችን ጽፎ ለመድረክ ያቀረበውም በእነዚህ የወጣትነት ጊዜያት ነበር፡፡ ኋላም ኑሮውን ወደ አዲስ አበባ ካዞረ በኋላ በርካታ የኪነጥበብ ክበባት ውስጥ አባል በመሆን ተሳትፎውን አሳድጓል፡፡
በተለይም በፑሽኪን፣ በአሊያንስ ኢቲዮ ፍራንሴ እና በጎተ የጀርመን ባህል ማዕከል ይዘጋጁ በነበሩ የግጥም ምሽቶችና በመላው ሀገሪቱ በሚሰናዱ በልዩልዩ የሥነጽሑፍ መድረኮች ላይ ሥራዎቹን ለህዝብ አቅርቧል፡፡ የይታገሱ ጌትነት የበኩር መጽሐፉ ‹‹ጥቁር ነጥብ›› በ1993 ዓ.ም የታተመ የግጥም መጽሐፉ ነው፡፡ በጊዜው በርከት ያሉ የመገናኛ ብዙኃን ሂሳዊ ምልከታቸውን ለህዝብ አጋርተውበታል፡፡
ሁለተኛው ሥራው እንዲሁ በ1997 ለህዝብ የቀረበው “ደጅ ያደረ ልብ” ሲሆን በዘውግ ደረጃም ግጥም ነበር፡፡ ይሄኛውም መጽሐፍ እንደቀድሞው ሁሉ የጋዜጣዎች እና የሀያሲዎች ዕይታን ማግኘት ችሏል፡፡ ሌላው የይታገሱ መጽሐፍ “የደመና መንገድ” የተሰኘው የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ሲሆን በበርካቶች ዘንድ በጎ ምላሽን ያገኘና ጥሩ የተነበበ መጽሐፍ ነው፡፡ ይታገሱ ጌትነት ከድርሰቱ ዓለም ባሻገር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ታይቶ በጊዜው አድናቆትን ላተረፈው “ቁጭት” ለተሰኘ ዘገባዊ ፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ ያበረከተ ሲሆን፣ ለህብረ ዝማሬና ለልዩ ልዩ ማስታወቂያዎች የዜማ ስራዎችን ሰርቷል፡፡
ሥራ መስክ
ይታገሱ ጌትነት በተለያ ተቋማት ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ሠርቷል፡፡ አብዛኛው የህይወቱ ክፍልም በሥራ የተወጠረ ዓይነት ሰው ነው፡፡ አባትና እናቱ ይሠሩበት በነበረው ንግድ ማተሚያ ቤት ጥቂት የጉርምስና ጊዜውን ያሳለፈ ሲሆን በርከት ላሉ ዓመታት በአርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት ውስጥ አገልግሏል፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥ እያለም ደራስያንን ሊጠቅም የሚችሉ ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞች መገኘት እንዲችሉ የበኩሉን አስተዋጽዖ ከማበርከቱ ባሻገር ወጣት ጀማሪ ጸሐፍት ሥራዎቻው እንዲታተም ድጋፍ ለማድረግ ችሏል፡፡ ከእነዚህ የጥረቱ ውጤቶች ውስጥ “ሩብ ጉዳይ” የተሰኘው የወጣቶች የሥነጽሑፍ ስብስብ መጽሐፍ አንዱ ነው፡፡
ከዚህ ባሻር ይታገሱ በኢንፍራኔት ቴክኖሎጂና በማግኔት አድቨርታይዚንግ በተሰኙ ተቋሞችች ውስጥ በመሳተፍ የአይሲቲ ኤግዚቢሽንን፣ የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚረዱ ሃሳብ በማመንጨት የተሳኩ ሁነቶችን በማዘጋጀት ሰፊ ጥረት አድርጓል፡፡ በ2001 ዓ.ም ከወዳጆቹ ጋር ባቋቋመው አበያታ ኢንፎርሜሽን ሰርቪስ አማካኝነት በኤፍ.ኤም አዲስ 97.1 የሚሰራጭ “ዛሬ” የተሰኘ በኪነ-ጥበብ ላይ የሚያተኩር የሬዲዮ ፕሮግራም ሲያሰናዳ ቆይቷል፡፡
በሀገራችን የህጻናት መጽሐፍት ህትመትና ንባብ ላይ በጉልህ በሚሠራው አሜሪካ በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ኢትዮጵያ ሪድስን በመቀላቀል በመላው ሀገሪቱ ውስጥ አብያተ መጽሐፍትን በማቋቋም፣ ለመምህራንና የቤተ-መጽሀፍት ሠራተኞች ሰፊ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም የሚያኮራ ሥራ ውስጥ ተሳትፏል፡፡ በህይወቴ ሠራሁ ብሎ ከሚኮራባቸው ሥራዎች ውስጥም ይሔን የኢትዮጵያ ሪድስ የአብያተ መጻሕፍትን የማስፋፋት ሥራ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
ከዚህም ባሻገር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል የትርፍ ሰዓት መምህር ሆኖ አገልግሏል፡፡በ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ ሆኖ ተመርጦ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ያገለገለ ሲሆን ከእነዚህ ዓመታት ውስጥም ለአጭር ጊዜ ያህል የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሠርቷል፡፡ ኃላም በፍቃዱ ሥራ አስኪያጅነቱን ለቋል፡፡
በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር አገልግሎቱ ውስጥም ሊጠቀሱ የሚችሉ አበርክቶዎችን ያኖረ ሲሆን ለ7 ዓመታት እየተከናወነ ያለው የጀማሪ ጸሐፍያን ሥልጠና ከሀሳብ ጥንስሱ አንስቶ የይታገሱ ጌትነት ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራምም በርካታ ለሙያው ፍቅሩ ያላቸውና በትምህርት የታገዘ የሙያ ተሳትፎ ለሌላቸው ደራስያን ስልጠና በመሥጠት ትልቅ ፍሬ ማፍራት ተችሏል፡፡
ከዚህም ባሻገር የብሌን መጽሔትን በዝግጅት እና ጽሑፍ በማቅረብ የራሱን አበርክቶ አኑሯል፡፡በ50ኛ ዓመት የደራስያን ማኅበር የአፍሪካ ደራስያን ጉባዔ እንዲሁም ህያው ጉዞ ሂደቶች ውስጥ ጠንካራ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ከዚህ ባሻገር ከወዳጆቹ ጋር ባቋቋመው ኢጋ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን የተሰኘ ድርጅት ውስጥ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን የመጽሐፍት ማስተዋወቅና ህትመት፣ የህጻናት የንባብ ፌስቲቫሎችን የሥነጽሑፍ እና የበገና ምሽቶችን ማስታወቂያዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡
ማህበረሰባዊ ተሳትፎዎች
ይታገሱ ጌትነት ከመደበኛ ሥራዎቹ ባሻገር በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ተሳታፊ ነው፡፡ በ2001 ዓ.ም ከጓደኞቹ ጋር ያቋቋመውን አምባ ትምህርት ለተቸገሩ በጎ አድራጎት ማኅበርን በቦርድ ሰብሳቢነት እየመራ ይገኛል፡፡ በዚህ ድርጅት አማካኝነት ትምህርት ለማግኘት ለተቸገሩ እና ወደትምህርት ቤት ለመሄድ ችግር ያለባቸውን ህጻናት ሙሉ ወጪዎቻቸው ተሸፍኖ ትምህርት ይማራሉ፡፡ እስካሁንም ከ700 በላይ ህጻናትን ያስተማሩ ሲሆን ከቅድመ- መደበኛ ትምህርት አንስተው አሁን 12ኛ ክፍልን እያጠናቀቁ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር በአሁኑ ወቅት የጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል የቦርድ አባል በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡
ጥናትና ምርምር
ይታገሱ፣ በዩኒቨርሲቲ ትምህርት ውስጥ ለመመረቂያ የሠራቸው ጥናቶች በአብዛኛው ወደ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፎች ያደሉ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ዲግሪ ወቅት “የግብረ ህማማት አጻጻፍ ቅርጽና የጽሑፈ ተውኔት አጻጻፍ ንጽጽራዊ ዳሰሳ” ላይ ያጠነጠነ ሲሆን በሁለተኛ ዲግሪው ላይ “የአጼ አምደ ጽዮን ዜና መዋዕልና የአጼ ዘርዓያቆብ ዜናመዋዕል የአጻጻፍ ቴክኒክ” የተሰኘ ነው፡፡ በአሁኑም ወቅት ትኩረት አድርጎ የሚያጠናው የአማርኛ ዜና መዋዕሎች ላይ ነው፡፡
ይታገሱ ከዚህ ባሻር ሌሎች ጥናታዊ ጽሑፎችን በተለያዩ ጉባኤዎችና የሂስ መድረኮች ላይ አቅርቧል፡፡ “ፓሮዲ በዓለማየሁ ገላጋይ ወሬሳ ላይ”፣ “በይነቴክስታዊነት በማክዳ ንውዘት”፣ “አዝማሪ እንደታሪክ እማኝ ዘመነ አቤቶ ኢያሱ እንደማሳያ”፣ የህጻናት የንባብ ክህሎት ማዳበር ላይ ያተኮሩ እንደ “መጽሐፍ ተኮር የማስተማር ሥርአት አፈጻጸም ሀገር አቀፍ ጥናት”፣ “የኢትዮጵያ የመጽሐፍ ህትመት ዕድሎችና ተግዳሮቶች- የህጻናት መጽሐፍትን እንደማሳያ” እና ሌሎች በርካታ ጽሑፎችን አቅርቧል፡፡