(ከእዝራ እጅጉ)
የ99 ዓመት የእድሜ ባለጸጋን ማውራት እንዴት ደስ ይላል
እስከዛሬ ዕድሜው 99 ከሞላ ሰው ጋር አውርቼ አላውቅም ። እናም ደጃዝማች ጋር ለመደወል ልቤ ተነሳሳ።
ከሰሞኑ ደጃዝማች ጋር ደወልኩ ። የጸሀፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ታሪክ በምስል ሲመረቅ ሀገር ፍቅር እንዲመጡ ነበር ሀሳቤ። አልቀርም አሉ። የ 99 አመቱ ሰው። እናም መርቁን ማለቴ አልቀረም።
99 አመት እዚህ ምድር ላይ መኖር ብዙ ያሳያል፡፡ ስመርቅ የኖርኩበት ጊዜ አንድ ክፍለ ዘመን በመሆኑ ያለፉትንም ያሳለፍኩትንም በማስታወስ ነው፡፡ በቅድሚያ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ልጆቼ እድሜ ይስጣችሁ ስል መርቃለሁ፡፡ እኔ እናንተን እንድመርቅ እድሉን የሰጠኝ ፈጣሪ ስለሆነ እድሜን እለምንላችኋለሁ፡፡ መኖር ደጉ እንዲህ ብሂሉ በመኖር በብዙ መንግስታት አልፌ ብዙ በማየቴ የሀገር እውነትን ውስጤ ሰርጾ እስከሚገባ ድረስ አውቄዋለሁ፡፡ ዘመን ተጠናቅቆ አዲስ ዘመን ሲመጣ ፈጣሪ አመስጋኝ ፍጡር ያድርጋችሁ ስል መርቃለሁ፡፡ ዛሬ በሽታ ሰውን እያሳጣን ባለበት ሰአት በጤና ሆኖ ወጥቶ መግባት ምንኛ እድለኛነት ነው፡፡ ሁሉ ነገር ለበጎ እንዲሆን ፤ ህመም ካጠገባችሁ ሳይኖር በሰላም ያሰባችሁት ይሳካ ዘንድ እመኛለሁ፡፡ እድሜና ጤና ከሰጣችሁ ይህንንም አሜን ብላችሁ ከተቀበላችሁ ለሌላው የምተርፉ ያድርጋችሁ፡፡ ፈጽሞ ማጣት ቤታችሁ አይግባ፡፡ በአሮጌው ዘመን በምሬት ትኖሩ ዘንድ ተስፋ እንድትቆርጡ ያደረገ የልግምና መንፈስ እንዳያገኛችሁ እመርቃለሁ፡፡ ፈጣሪ በተስፋ የምትሞሉ ያድርጋችሁ፡፡
መመረቅ/መራቂ መሆን/ ደስ ይላል፡፡ ምክንያቱም ተመራቂው አምኖ አሜን ይላል፡፡ ይህ ትልቅ ማስተዋል ነው፡፡ አባት መርቀኝ ባክህ ብሎ ልጅ ከተናገረ ልዩ አስተውሎት ተላብሷል ማለት ነው፡፡ ጥበባችሁ አይወሰድ፤ ማስተዋላችሁ ይጨምር-አርቆ አሳቢ ያድርጋችሁ፡፡ ቅርብ ከማሰብ ወጥታችሁ ነገን አላሚ ያድርጋችሁ፡፡ መጪው ዘመን ነገሮችን ባልተረጋጋ መንገድ የምታዩበት ሳይሆን በሰከነ መንፈስ ልቦናችሁ እንዲበራላችሁ ይሁን፡፡ ካልበራ መንገዱ ጨለማ ሆኖ የድንግዝግዝ ጉዞ ይሆናልና ብርሀን ወደ እናንተ ይምጣ፡፡
በኮሚኒስት ስርአቶች የፈረሰው እሴታችን ዳግም ተመልሶ ፈሪሀ እግዚአብሄር ያለን ህዝቦች ያድርገን፡፡ በአጉል የሶሻሊዝም እሳቤ እና በአዲሱ ዘመን ንቅናቄ / new age movement / ተወስደን ከመቅረት ያድነን፡፡ የአዲሱ ዘመን ንቅናቄ ኢትዮጵያ ካላት ባህል እና ለዘመናት አብሯት ከኖረው እምነት አንጻር የማያስኬዳት ስለሆነ በፈጣሪዋ የምትመካ ሀገር እንድትሁን ምክንያት ያድርጋችሁ፡፡
ኢትዮጵያን የምትወዱ ሁኑ፡፡ ይህች ፈጣሪ አስቀድሞ ያወቃት እና ተስፋ እንዳላት ቃል የገባላትን ድንቅ ሀገር የምትጠብቁ ሁኑ፡፡ ከማፍረስ ይልቅ ለማነጽ ቅደሙ፡፡ ኢትዮጵያን ከመሸሽ ይልቅ ቀርባችሁ የምታክሙ ሁኑ፡፡ ይህን ስመርቅ በአንድ በኩል ደስ እያለኝ በሌላ ደግሞ እውን የሚያክማት ታገኝ ይሆን እያልኩ ነው፡፡ ግን አንድ የተመረቀ ይደርስላታል ስል በ99 አመቴ ምርቃቴን አድርሻለሁ፡፡
ኢትዮጵያን ዞሬ ተዟዙሬ በማየቴ አንዳንዴ የሚደርስላት በማጣት ደክማ ስታገግም አያታለሁ፡፡ እና ነገሮችን ለመለወጥ አዳጋች ሲሆን አስተውላለሁ፡፡ እናንተ የዘመኑ እንቁዎች ፤ የጀግንነት ካባ የደረባችሁ ግን ኢትዮጵያን ለማዳን ሀኪም ያድርጋችሁ፡፡
እንደ አንድ ከባድ ነቀርሳ ክፉኛ ሀገሪቱን የተጠናወታትን የዘረኝነት በሽታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የምታስወግዱ መለኛ ያድርጋችሁ፡፡
እኔ ህዝብን ባገለገልኩባቸው 70 በላይ አመታት የምችለውን እና የተሰጠኝን በትጋት ከውኛለሁ፡፡ ሀገር በመቀባበል ነውና የምትቀጥለው ለቀጣዩ እነሆ አቀብያለሁ፡፡ ጥሩ ተቀባይ ያድርጋችሁ፡፡ በትክክል የሰማ በትክክል ለመጪው ትውልድ ያስተላልፋል፡፡ እና ለአዲሱ ትውልድ ትክክለኛ እውነት ለመስጠት የልቦናችሁ ብርሀን ይብራ፡፡ ከመቀበል ይልቅ ለኢትዮጵያ የምትሰጡ ያድርጋችሁ፡፡ ኢትዮጵያ በመጪው አዲስ አመት ተሰጥቶ የሚኖርላት ወገን ትሻለች፡፡ ሊበዘብዛት ሳይሆን ጎዶሎዋን ሊሞላ የተዘጋጀ ጀግና ትፈልጋለች፡፡ ለዚህም በተጠንቀቅ የቆማችሁ ያድርጋችሁ፡፡
ይህች ሀገር ብዙ ደም ሲፈስባት የነበረች ገና ከጉዳት ያላገገመች ጥላ ከለላ ፈላጊ ሀገር ነች፡፡አንድነቷን ጠብቃ ብትኖርም ልጆቿ እርስ በእርስ ተደማምተዋል፡፡ አንዳንዴ ይቅር ላይባባሉ የተማማሉ እስኪመስል ድረስ መጨካከኑ በዝቷል፡፡ የሚራራ ጓዙን ጠቅሎ ከሀገሪቱ የጠፋ እስኩመስል ድረስ ክፋት ነግሷል፡፡ በአዲሱ ዘመን 99 አመቴን በምጀምርበት ሰአት ይህን የነገሰ ክፋት ከንግስናው ወርዶ ማየትን እመኛለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ እናንተን ምክንያት ያድርጋችሁ፡፡
ሳይሰሩ መበልጸግን በአገልግሎት ዘመኔ ስዋጋ ኖሬአለሁ፡፡ አሁን ኢትዮጵያን ሊያስቀጥል የተሰናዳው ወገን ይህን የራስ ወዳድነት ስሜትን ዳግም እንዳይመጣ ጠራርጎ የሚያባርር እንዲሆን እሻለሁ፡፡ ወንድም ወንድሞ በጨከነበት በዚህ ኢትዮጵያ ራስዋ ንስሀ ካልገባች ፈጣሪ የሚከፋው ይመስለኛል፡፡ 99 አመቴ ላይ ሆኔ ሀገራችንን በንስሀ እና በይቅርታ እናቆይ ለዚህም አዲሱ ትውልድ በለስ ይቅናው ስል እመርቃለሁ፡፡
አንዳንድ እውነታዎች ስለ ደጃዝማች ወልደሰማእት
1. ደጃዝማች ወልደ ሰማያት በተፈሪ መኮንንና ኮተቤ ቀዳማቂ ሀ/ሥላሴ፣ በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ፣ በቤይሩት አሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን እና ፖለቲካል ሳይንስ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
2. ብዙዎች የሚያውቋቸው በወላይታ አውራጃ አስተዳዳሪነት ባከናወኑት የልማት ሥራ ነው፡፡ በ1917 በሐረርጌ የተወለዱት ደጃዝማች ወልደሰማያት በሸገር ስቱድዮ ለሃያ ያህል ጊዜ ሳይሰለቹ ተመላልሰው የሰጡት ቃለ መጠይቅ እጅግ ሰፊ ነው፡፡ እንዲያውም የሸገር ሪከርድ ይዘዋል ማለት ይቻላል፡፡
3. የዛሬ 63 አመት የ1953ቱ መፈንቅለ-መንግስት ከሽፎ 120 ቀኑን ባስቆጠረ ማግስት፣ የ36 አመቱ ወጣት ወልደሰማእት ገብረወልድ በገነት ሆቴል ጋብቻውን መሰረተ፡፡ ባለቤቱ ወይዘሮ ቀለመወርቅ ዘውዴም አምሮባት ዋለ፡፡ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ትልቅ ሚና አበርክተዋል የተባሉት አቶ ከተማ ይፍሩ ከሚዜዎቹ መሀል አንዱ ነበሩ፡፡ በ1950 በቤሩት የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ደጃዝማች ዲግሪ ይዘው ሲመጡ 33 አመታቸውን አክብረው ነበር፡፡
4.አሁን ቦሌ አድማስ ኮሌጅ ያለበት
ኦሎምፒያ የዛሬ 60 አመት በደን የተሞላ አካባቢ ነበር፡፡ ያኔ በ1951 ግድም ደጃዝማች ገና ከውጭ መምጣታቸው ነበርና ቦሌ ኦሎምፒያ 1000 ካሬ ሜትር በ250 ብር መሬት ይገዛሉ፡፡ መቋቋሚያ 3000ብር ተሰጣቸው፡፡ ይህ መቋቋሚያ ቤት ሰራላቸው፡፡ አሁን ደጃዝማች የሚኖሩበት ቤት የዛሬ 61 አመት በ250 ብር የተገዛ ቤት ነበር፡፡ በዚህ ቤት ነበር 6ቱ የደጃዝማች ወልደሰማያት ልጆች ተወልደው ያደጉት፡፡ ደጃዝማች ሰርጋቸውን በወጉ ካደረጉ በኋላ ኦሎምፒያ ወደ ሚገኘው ቤታቸው ገቡ፡፡
5.የዛሬ 60 አመት ሀዋሳ ከተማ እንድትቆረቆር ካደረጉ መስሪያ ቤቶች አንዱ ህዝባዊ የኑሮ እድገት ሚኒስቴር ነበር፡፡ ያኔ ደግሞ ደጃዝማች ወልደሰማያት ትልቅ ሀላፊነት ስለነበራቸው በሀዋሳ ምስረታ ላይ ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡በዚህ ጉዳይ ላይ በመጽሀፋቸው ላይ በዝርዝር ማስረጃ ጠቅሰው ጽፈዋል፡፡