የኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሯ እናትአለም መለስ ማናቸው?

ከመዝገበ አእምሮ ቅፅ ሁለት የተወሰደ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

መዝገበ -አእምሮ ቅጽ ሁለት ታሪካቸው ከተሰነደላቸው የሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ባለሙያዎች ውስጥ ወይዘሮ እናትአለም መለስ ይገኙበታል። በአሁኑ ሰዓት የኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር የሆኑት ወይዘሮ እናትዓለም መለስ ማናቸው የሚለውን ከመዝገበ አእምሮ የተወሰደውን ታሪክ እናቀርባለን።ቤርሳቤህ ጌቴ እና ዕዝራ እጅጉ እንደሚከተለው አጠናክረውታል።

፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨

እናትዓለም መለስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በድሬዳዋ እመቤታችን ትምህርት ቤት ጀምረው በኋላ በአባታቸው የሥራ ሁኔታ ምክንያት ከድሬዳዋ ወደ ቢሾፍቱ በመቀየራቸው፥ በአፄ ልብነ-ድንግል ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በቢሾፍቱ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል።

የመጀመሪያና ኹለተኛ ዲግሪያቸውንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኛነት ያጠናቀቁት ወይዘሮ እናትዓለም፥ ከልጅነታቸው ጀምሮ ማንበብ ያስደስታቸው ነበር።በትምህርት ቤት ቆይታቸውም በሚደረጉ የሥነ-ጽሑፍ ውድድሮች ይሳተፉ ነበር።

ወይዘሮ እናትአለም መለስ፣ ለ13 ዓመታት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከሪፖርተርነት እስከ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚነት ደርሰዋል።ከዜና ክፍል በተጨማሪ የፕሮግራም ዝግጅትን ደርበው ይሠሩ ነበር።

ወይዘሮ እናትዓለም፣በሥራቸው በሀገር ውስጥ የተለያዩ ክፍሎችና በውጭም የተለያዩ ሀገራት የመሄድ እድል አግኝተው ልምድ ቀስመው ተመልሰዋል።

ወይዘሮ እናትዓለም ፣የዝግጅቶችን አርኪነትና ማኅበረሰባዊ ተቀባይነትን ለመለየት ላይን አፕ ማዘጋጀት፣ ሠራተኞች የሚመሩበትን ሙያዊ የሥራ ክፍፍል መርህ ማውጣት ላይም ሠርተው፥ ወደ ትግበራ መግባቱን አረጋግጠዋል። የኢቲቪ የጋዜጠኞች ኢንዱስትሪያል አቨሬጅ ለማስተግበር በሚደረግበት ጊዜ መሬት ለማውረድና ከነበረው ባህላዊ አሠራር እንዲወጣ የበኩላቸውን አድርገዋል።

በኢቢሲ ያሉ ባለሙያዎች ሥራን በፕሮፌሽናል መንገድ እንዲሠሩ ለማድረግም የሥልጠና እና የክትትል ተግባራትን አከናውነዋል።

ወይዘሮ እናትዓለም ፣ በወቅቱ በተቋሙ ሙያዊ የሥራ ተዋረድ መዘርጋት፣ ተቋማዊ የሙያ ሂደትና ስታይል ቡክ መሥራት፣ ፎርማቶችና ፕሮዳክሽኖች በሰዓት ልኬት መርሃ -ግብር እንዲኖራቸው አድርገዋል። ጥናቶች እንዲሠሩም ሚናቸውን ተወጥተዋል።

ከአንድ በላይ ጣቢያ እንደሚያስፈልግ ለማኔጅመንቱ አሳውቀውም፥ ሐሳቡ ከብዙ ክርክር በኋላ ተቀባይነትን አግኝቶ ወደ ዋናው ጥናት ገብቷል።

በተቋሙ የሥራ መዘርዝር እንዲኖር ከማስቻላቸው ባሻገር ለተቋሙ በቀጣይ ሊጠቅም የሚችል፥ ከኤዲቶሪያል ፖሊሲ ጀምሮ የአሠራር ሕጎችን በተለይ የሥነምግባር ደንቦችን የያዘ ማኑዋል እንዲዘጋጅ አድርገዋል።

ወይዘሮ እናትዓለም፣በ2006 ዓ.ም የአመራር ለውጥ ሲደረግም በዲቪዥን ኃላፊነት የተሰየሙ ሲሆን፣ ከተቋሙ በ2010 ዓ.ም ለቅቀው እስኪወጡ ድረስ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የቴሌቪዥን ጣቢያው ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና የዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው አገልግሎት ሰጥተዋል።

      ከኢቢሲ በኃላ

ወይዘሮ እናትዓለም ከኢቲቪ በኋላ የአዲስ አበባ መስተዳደር ቴሌቪዥንን በኃላፊነት እንዲመሩ ተጠይቀው፥ ነሐሴ 16/2010 ዓ.ም አዲስ ሚድያ ኔትወርክ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሥራቸውን ጀመሩ። በዚያም በነበራቸው የኹለት ዓመታት ቆይታ፥ ተቋሙን የህዝብ ጣቢያ ከማድረግ ጀምሮ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይልና በይዘት የተሻለ ሆኖ እንዲቀርብ ሠርተዋል። በዛን ወቅት የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኅን ወደ ኤች.ዲ ስርጭት ደረጃ እንዲመጣ፣የ 24ሰዓት የስርጭት አገልግሎት እንዲጀመር በመወሰንም ወደ ሥራ አስገብተዋል። ተቋሙ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ወደሚል ብራንዲንግ በማምጣትም ሠርተዋል።

በኹለቱ ተቋማት በነበራቸው ቆይታ፥ ኢቲቪ ወደ ብሮድካስት ኮርፖሬት እንዲሸጋገር የቀረበውን ሐሳብ ወደ ወረቀት ቀይሮ ምክር ቤት እስከማስፀደቅና በፎርማቶች እንዲገለጽ ማድረግ ድረስ ድርሻቸው የነበረ ሲሆን፥ በተመሳሳይ በአዲስ ሚድያ ኔትወርክ ጣቢያውን የሕዝብ ለማድረግ አዋጁን ከማስቀየር ጀምሮ በማስጸደቅ ወደሥራ እስከማስገባት ሠርተዋል።

ከአዲስ ሚድያ ኔትወርክ በኃላ

ወይዘሮ እናትዓለም መለስ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለበጎ ፈቃድ ሥራዎች ሀብት ለማሰባሰብ በተቋቋመው ማኀበራዊ ትረስት ፈንድ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ለ2 ዓመታት አገልግለዋል ፡፡ ከዛም ቀጥለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ በመሆን፣ ብሎም ጠንካራ የኮምዩኒኬሽን መዋቅር እስከ ታች ድረስ እንዲዘረጋ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ።ዛሬ መስከረም 9 2018 ዓ.ም ደግሞ በሚኒስትር ማዕረግ የኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር በመሆን ተሹመዋል ።
ለበለጠ መረጃ፦መዝገበ-አእምሮ ቅፅ 2 ከገፅ165-168

አሳታሚ ዕዝራ እጅጉ

One thought on “የኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሯ እናትአለም መለስ ማናቸው?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *