‘የትዝታዬ ማሕደር’ ሚያዝያ 5 2017 ዓ.ም ተመረቀ

የህትመት ዋጋ መናር አሳሳቢ ደረጃ ላይ
ደርሷል
(ከዕዝራ እጅጉ)

ዳግላስ ጴጥሮስ “በሚለው የብዕር ስሙ የሚታወቀው፣ በርካታ እና መጣጥፎችን ያስነበበው ደራሲ ጌታቸው በለጠ ‘የትዝታዬ ማሕደር’ በሚል ርዕስ የሕይወት ታሪኩን ፅፎ ዛሬ ሚያዝያ 5 2017 ዓ.ም በብሔራዊ ወመዘክር አዲሱ አዳራሽ 13ኛ ፎቅ ላይ አስመርቋል፡፡

ደራሲ ጌታቸው በለጠ፣ የደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገለ ሲሆን በየጊዜው በሚሰጣቸው የማህበራዊ እና የኪነ -ጥበባት ሂሶችም ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ሚድያዎች ላይ በመቅረብ ቃለ- መጠይቆች በመስጠት ከበሬታን ያገኘ ደራሲ ነው።

ደራሲ ጌታቸው በለጠ፣ ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በጋዜጦች ላይ በመፃፍ አቅሙን ያሳየ የብዕር ሰው ነው፡፡

በዕለቱ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አበረ አዳሙ የዕለቱን መልዕክት ያሰሙ ሲሆን የደራሲው ወዳጆችና አብሮ አደጎች ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

ዶክተር ወዳጄነህ ማህረነ፣ዶክተር ንጉሴ ተፈራ፣ መምህር ስሜ ታደሰ ፣ ደራሲያን ጥበቡ በለጠና ኃይለመለኮት መዋዕል ንግግር ያደረጉ ሲሆን ለደራሲው ያላቸውንም ከበሬታ ገልፀዋል፡፡

አብሮ አደጋቸው አቶ ኃይለልዑል ይልማ ጎረቤታቸው አቶ አረጋ ጌላ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡
የዕለቱ መድረክ መሪ የኪነ ጥበብ ሰው ደራሲ ተስፋዬ ማሞ ሲሆን ለመፅሀፍ ምረቃ መርሀ ግብሩ ልዩ ድምቀት ሰጥቶታል፡፡

በዚህ የመፅሀፍ ምረቃ ላይ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን የታደሙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ዶክተር አረጋ ይርዳው፣ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣አምባሳደር መሀሙድ ድሪር፣አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን፣ መጋቢ መስፍን ሙልጌታ፣ዶክተር ቤተ መንግስቱ እና ሌሎችም ታድመዋል፡፡

ደራሲ ጌታቸው በለጠ፣በዕለቱ ባስተላለፈው መልዕክት የህትመት ዋጋ መናር በራሳቸው ለሚያሳትሙ ደራሲያን ፈታኝ ሆኖባቸዋል ሲል ተናግሯል፡፡ ይህን ፈታኝ ሁኔታ የሚመለከታቸው አካላት መፍትሔ ቢፈልጉለት ሲል ሀሣቡን ሰንዝሯል፡፡

በዕለቱ፣ በጠንካራ ሽፋን የታተሙ የመፅሀፉ ቅጂዎች ከ10,000-100,000 ብር የተሸጡ ሲሆን ይህም ደራሲው ለህትመት ያወጣውን ወጪ በከፊል ለመመለስ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

ደራሲ ጌታቸው በለጠ ያስመረቀው መፅሀፍ፣448 ገፆች ያሉት ሲሆን ከልጅነት እስከ አዋቂነት ዕድሜ ያሳለፈውን ሕይወት በመፅሀፉ ላይ አካቷል፡፡

የምረቃ መርሀ -ግብሩን በማስተባበርና የሚድያ ዘገባዎችን በመከታተልና በማዘጋጀት ተወዳጅ ሚድያና ኮምዩኒኬሽን(ዕዝራ እጅጉ) ኃላፊነቱን የተወጣ ሲሆን ደራሲ ጌታቸውም በመፅሀፍ ህትመት ሥራው ርሆቦት ማተሚያ ቤትን እና ሌሎችንም አመስግኗል።

ደራሲ ጌታቸው በለጠ በገጣሚነት ፤በጋዜጣ አምደኝነት፤በመጽሀፍ ደራሲነት ጉልህ አሻራ ካኖሩ የብእር ሰዎች አንዱ ነው፡፡ በልጅነቱ ወላጆቹ ናፖሊዮን ሊሉት ነበር፡፡ በሂደት ግን ጌታቸው የመዝገብ ስሙ ሆነ፡፡ በ1976 የዛሬ 41 አመት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀው ደራሲ ጌታቸው በ1981 ስሞተኛው የተሰኘ የአጭር ልቦለድ መድበሉን በማሳተም ከ መጽሀፍ አንባቢያን ጋር ተዋወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርን ለ8 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የመራው ደራሲው ዛሬም ብእር ከወረቀት አቆራኝቶ መጻፉን ቀጥሎበታል፡፡

One thought on “‘የትዝታዬ ማሕደር’ ሚያዝያ 5 2017 ዓ.ም ተመረቀ

  1. የተመጠነ ግልጽና እውነት የሆነ ዘገባ ነው::ጌታቸው በለጠ ደራሲ መምህር አገር ወዳድ እና የክርስቶስ አምባሳደር ነው::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *