የሙሉጌታ ገሰሰ አብርሃ የመታሰቢያ ፕሮግራም ዛሬ እሁድ ተደረገ

ክፍል 4

የሬድዮ ፋና የመጀመሪያው ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ያገለገለው ሙሉጌታ ገሰሰ አዲስ አበባ በሚገኘው ሰዓሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን ዛሬ እሁድ ነሐሴ 4 2017 የመታሰቢያ ፕሮግራም ተደረገለት፡፡

ሙሉጌታ ገሰሰ እሁድ ከጠዋቱ 3 ጀምሮ ወዳጅ ዘመዶቹ በታደሙበት የማስታወሻ ዝግጅቱ ተደርጓል፡፡

በዕለቱ አብረውት ከሠሩት ባለሙያዎች መካከል አቶ ብሩክ ከበደ፣ ዶክተር መለስ ዓለምና አቶ ተተካ በቀለ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ የሥራ መሪ የሆኑት ዶክተር መለስ ዓለም ለሙልጌታ በስሙ ትልቅ ነገር መደረግ አለበት ብለዋል፡፡ የመሠረተው የሬድዮ ጣቢያ በስሙ ፣አንድ ስቱድዮ ሊሰይምለት ይችላል ሲሉም ሀሣብ ሰጥተዋል፡፡

በዕለቱ ቁጥራቸው በርከት ያለ የሙልጌታ ወዳጆች በአዳራሹ ታድመው የነበረ ሲሆን ብዙዎቹ ታላቅ የሚድያ ሰው ነው ያጣነው ሲሉ ሀሣብ ሰጥተዋል፡፡

የሙልጌታ ልጆችም አባታቸው ልክ እንደ ጓደኛ የሚመለከቱት የቅርባቸው ሰው እንደነበር መስክረዋል፡፡

በሚድያው ዘርፍ ትልቅ አሻራ እንዳኖረ የሚነገርለት ሙሉጌታ  ገሰሰ፣ ሬድዮ ፋና አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠ ባለሙያ መሆኑ በብዙዎች ይነገርለታል፡፡ 

አጫጭር ልቦለዶችን እና ግጥሞችን የመፃፍ ዝንባሌ የነበረው ሙሉጌታ በአመራር ፍልስፍናውና ስልቱ ብዙዎች ስሙን በበጎ የሚያነሱት  ታላቅ ሰው ነበር፡፡ 

ተወዳጅ ሚድያ ከሙልጌታ ገሰሰ ወዳጆች ጋር በመሆን ለመርሀ ግብሩ መሳካት የሠራ ሲሆን ወደፊትም መሰል የማስታወሻ መሰናዶዎችንም ዕውን የማድረግ ዕቅድ አለው።

ተወዳጅ ሚድያም ለሀገር የሠሩ ሰዎችን እያፈላለገ ሲሰንድ የሙሉጌታም ታሪክ ለትውልድ እንዲቀመጥ ያደረገ ሲሆን በቀጣይ በሚወጣው “መዝገበ አእምሮ” የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይም የሕይወት ታሪኩን እንደሚሰንድ ለማወቅ ተችሏል።በአሁኑ ሰዐትም በዝርዝር የተሰናዳው የሙሉጌታ ታሪክ ከምስል ጋር በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ፕላትፎርሞች ላይ ተፅፎ ይገኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *