ዙበይዳ አወል ኢብራሂም

ዙበይዳ አወል ኢብራሂም

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡

ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ አሁን ከሚድያ ዘርፍ ታሪኳ የሚቀርብላት ጋዜጠኛ ዙበይዳ አወል ኢብራሂም ናት-ህልሟን ያሳካች ብርቱ ሰው፡፡

ትውልድ ልጅነት እና ትምህርት

ጋዜጠኛ ዙበይዳ አወል ከአቶ አወል ኢብራሂም እና ከወይዘሮ ራህመት ኑሪ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ታህሳስ 13/1966 ተወለደች። ሴት አያቷ በተከታታይ 5 ሴቶችን በመውለዳቸው በአካባቢው ማህበረሰብ የደረሰባቸውን ውግዘት የሚያስታውሱት እናቷ “ጌታዬ ! የሴትን ልጅ አይኗን አታሳየኝ !” ብለው ዱአ ቢያደርጉም እስቲ የሴትን ልጅ ጣእም እይው በሚል ይመስላል ከ 5 ወንዶች መሀል የተገኘች ብቸኛ ሴት ሆነች። እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ በአካባቢው በሚገኝ መዋእለ -ህፃናት እንዲሁም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በሲቢስቴ ነጋሲ፣ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በንፋስ ስልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ተከታትላለች።

የጋዜጠኝነት ዝንባሌ

በልጅነቷ ከንባብ ጋር የተዋወቀችው ዙበይዳ አወል የ ሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሆና በኢትዮጵያ ሬዲዮ ጥያቄ በመላክ ስሟን ማስጠራት ጀመረች። የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆና በአዲስ ዘመን “አድማስ አምድ ” የመዝናኛ ፅሁፎች በመፃፍ ፣የ አስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ሆና ደግሞ በለገዳዲ ሬዲዮ “ቅዳሜን ከኛ ጋር ” እና “እሁድን ለአንድ አፍታ !” ላይ የመዝናኛ ፅሁፍ ፣ጭውውት እና ድራማ በማዘጋጀት እና በማቅረብ ። መደበኛ ትምህርት በሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ደግሞ የሬዲዮ መምህርት በመሆን ከ 1983-2000 በፍሪላንሰርነት ሰርታለች። በንፋስ ስልክ ት/ቤት በነበራት የሚኒ ሚዲያ ተሳትፎ አማካኝነት ከኢትዮጵያ ሬዲዮ የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ንቁ ተሳታፊና አድማጭ በመሆኗ “ወደፊት ጋዜጠኛ እሆናለሁ – ከጋዜጠኛም ደግሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና አንባቢ መሆን ነው የምፈልገው !” ማለት ጀመረች።

በ1984 የአዲስ አበባ አስተዳደር ባህልና ስፖርት መምሪያ ለአማተር የስነ ጥበባት ባለሙያዎች ያዘጋጀው ን የስነፅሁፍ ስልጠና በመከታተል ሙያውን ማዳበር ጀመረች። ከአቻ ጓደኞቿ ጋር ባቋቋሙት “ኪነ- ህይወት አማተር የስነ ፅሁፍ ክበብ ” አማካኝነት መጣጥፎች ፣ ግጥሞች ና ልብ ወለዶችን በመፃፍና በማቅረብ ማስገምገም፣ገንቢ ሀሳቦችን በመቀበልም ለሬዲዮ ፕሮግራሞች፣ለጋዜጣ እንዲሁም በጊዜው የነበሩ የግል መፅሔቶች ላይ እንደሳሌም፣ ፈለግ ጋዜጣና መፅሔት ፣ገነት(የሴቶች መፅሔት)፣ሀይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ቢላል መፅሔት እና ሂክማ ጋዜጣ ላይ ተሳትፋለች።

በተጨማሪም “ኒካህ ” እና “ምራት” የተሰኙ ሀይማኖታዊ ፊልም ላይ በተዋናይነት ፣”መርየም” በተሰኘ ፊልምም የተለያዩ ሴቶችን ድምፅን ወክላ ሰርታለች። የስልጤ ህዝብ የማንነት ጥያቄን መሰረት አድርጎ ባካሄደው እንቅስቃሴ በገጠር የብሔረሰቡን ተወላጆች ለማነቃቃት የሚካሄዱ ስብሰባዎችን የሚያስተዋውቀው “ሶጃት ” የተሰኘ ጋዜጣ ላይ በመስራት ለስልጤ ህዝብ ማንነት የተደረገ ትግል ላይ አሻራዋን አሳርፋለች።

የስራ አለም

በ 1992 የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜናና ጥቆማ ተቀባይ በሚል መደብ ያወጣውን የቅጥር ማስታወቂያ በማየት ለስነ ፅሁፍ ስራዎቿ ጥሩ መደላደል ይፈጥራል በማለት ተወዳድራ ተቀጠረች። ሆኖም የክፍሉ ስራ ውጥረት የሞላው መሆኑ ወዲህም የትዳር ህይወት ያሰበችውን ለማሳካት ሳያስችላት ቀድሞ በንቃት ትሳተፍባቸው የነበሩ ጋዜጣ እና መፅሔቶች ተረስተው የእለት እለት ኑሮ መምራት ጀመረች። ሆኖም ግጥሞችና አጫጭር ጭውውት ና ድራማ መሞከርና ንባብ ያልተቋረጡ ልምዶቿ ነበሩ። በ 2002 የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ባደረገው የውስጥ እድገት በቴሌቪዥን ዘርፍ የአማርኛ ዜና ክፍል ረዳት አዘጋጅ ሆና ተመደበች።

በቴሌቪዥን ዜና ክፍል ቆይታዋ በምታነሳቸው ማህበራዊ ጉዳዮች በ2005 የተሻለ አፈፃፀም ላላቸው ጋዜጠኞች የማበረታቻ ሽልማትና እድገት ሲሰጥ አንዷ ሆና ተሸለመች። በዚያው አመት በተደረገ ድልድል የኢትዮጵያ ሬዲዮ አማርኛ ዜና ክፍል ተመድባ የልጅነት ህልምና ምኞቷ የሆነውን “ጋዜጠኛ እሆናለሁ – የምሆነውም የኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና አንባቢ ነው !” ተሳክቶላት በመስራት ላይ ትገኛለች ። ክፍሉ እንድትሰራ ከሚመድባት በተጨማሪ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በማተኮር የአካል ጉዳተኞች ምቹ ያልሆነ መሰረተ ልማት እና ትምህርት ፣ለችግር የተጋለጡ አረጋውያን ፣የሴቶች እና ወንድ ህፃናት ጥቃት ፣ ዜናዎችን ሰርታለች።

ያጋጠሙ ችግሮች

ቤተሰብ የመገናኛ ብዙሃን በሚጠራ ስምዋ ምክንያት “መቼ ነው ደሞዝ የሚከፍሏችሁ ?” ከሚል አስደንጋጭ ጥያቄ ጀምሮ “ለምን ሌላ ስራ አትሞክሪም ?” ምክሮች እንደልብ “ገንዘብ ስጡኝ እዚህኛው ሚዲያ የማቀርበው ፅሁፍ አለ ” ወይም ” ለዚህ መፅሔት የፃፍኩትን ፅሁፍ ላድርስ ” ለማለት የሚገድባት እንቅፋቶቿ ነበሩ።

በዘመኑ የነበሩ መገናኛ ብዙሀንም ስም ከመጥራት ባለፈ ይህችን ለትራንስፖርት የማይሉ በመሆኑ ከንፋስ ስልክ ሜክሲኮ ፣ ፒያሳ፣አራት ኪሎ አንዳንዴ በእግር፣አንዳንዴ መሳፈሪያ በማጣት እንዳሰበችው ለ መጓዝ አላስቻላትም። ወዲህ እናትነት፣ወዲህ የሴትን ብቃት እና ችሎታ በማያምን ማህበረሰብ የገጠሟት ፈታኝ እና እልህ አስጨራሽ ችግሮች ጥርሷን ነክሳ “እችላለሁ !” እንድትል አጠነከራት እንጂ አልሰበራትም። በጋዜጠኝነት ሙያ አስቸጋሪ የመስክ ስራዎች ላይ መመደብ፣ለሴት የማይመቹ ተሽከርካሪዎች እና ማደሪያ፣ አንዳንዴ ለጤና እክል የሚያስከትሉ አስቸጋሪ ቦታዎች፣እናትነትንና የሙያ ፍቅርን እኩል ለማስኬድ የሚፈትኑ አጋጣሚዎች የየእለት ገጠመኟ ናቸው።

የበጎ አድራጎት ስራዎች

በስራ አጋጣሚ ያገኘቻቸውን ህፃናትና አረጋውያንን መርዳት፣ ለበጎ አድራጎት የተቋቋሙ ማህበራት ላይ በአባልነት መሳተፍ ለምሳሌ የእኔ ቤተሰብ፣አብሮነት የሴቶችና ህፃናት መርጃ፣ኢትዮጵያውያን ውመን ኢምፓወርመንት አሶሴሽን ለአብነት ይጠቀሳሉ። ሴቶች ባላቸው አቅምና ችሎታ መስራት አለባቸው ብላ የምታምነው ጋዜጠኛ ዙበይዳ አወል በዚህ ዘርፍ የሚሰሩ ማህበራት እንዲጠናከሩ የበኩሏን አስተዋፅኦ እያደረገች ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት የ 5 ልጆች እናት የሆነችው ጋዜጠኛ ዙበይዳ አወል በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላት ሲሆን አጋዥ ካገኘች ግጥምና አጫጭር ልብ -ወለዶቿን ማሳተምና በሴቶችና ህፃናት ድጋፍ ላይ የሚያተኩር የበጎ አድራጎት ማህበር ማቋቋም ህልሟ ነው። አላህ ያግዛት !

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *