ዘካርያስ ብርሃኑ ገ / አማኑኤል  

ዘካርያስ ብርሃኑ ገ / አማኑኤል

/ጋዜጠኛ እና ደራሲ)

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ መዝገበ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዱ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ዘካርያስ ብርሀኑ ነው፡፡ ዘካሪያስ ከ2000 አ.ም በኋላ ወደ ሚድያው አለም መጥተው የራሳቸውን ቀለም ከፈጠሩ ብርቱ ባለሙያዎች አንዱ ነው፡፡ ግርማ አድነው እና እዝራ እጅጉ ታሪኩን እንደሚከተለው አጠናክረውታል፡፡

ልጅነት

ጋዜጠኛና ደራሲ ዘካርያስ ብርሃኑ አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ሐምሌ 25/1974 ዓ.ም ተወለደ። እናቱ ወ/ሮ ስሂን ምናሴ፣አባቱ ሊቀካህናት ብርሃኑ ገ/አማኑኤል ይባላሉ።አብዛኛው የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው ቀበና በተባለው ሰፈር ነው። በቀበና ወንዝ ዋኝቷል፣አይረሴ የልጅነት ጨዋታና ቡረቃዎችንም አሳልፏል።”ታምሜያለሁና በእጅጉ በጠና ሀኪሞቹ ሰፈር ውሰዱኝ ቀበና” በሚል ታዋቂ ግጥምና በብዙ ከያንያን የጥበብ ሥራ ውስጥ ጎልቶ የሚታወቀው የቀበና ሰፈር አዲስ አበባ ቢገኝም በዙሪያ ገባው ወንዝ፣ጫካ፣ተራራ ይገኛል።

በአጠቃላይ የገጠርና የከተማ መልከአ- ምድር እና የአኗኗር ሁኔታን የያዘ ነው ሰፈሩ።በርከት ያሉ ኤምባሲዎችም ተቀራርበው የሚገኙበት ነው።የሩሲያ፣የኬንያ፣ የቤልጂየምና የእንግሊዝ ኤምባሲዎች በቀበና ሰፈር አሉ።ዓይነተ- ብዙ ህይወትና አኗኗር በቀበና እና ዙሪያው ይታያል።ዘካርያስ የቀበና ሰፈር ባፈራቸው መልከ ብዙ ተፈጥሮዎችና የአኗኗር ይትባህሎች ውስጥ አድጓል።ይህም በተፈጥሮ ጸጋው ካገኘው ልዩ ችሎታው ባሻገር በአካባቢውና በአኗኗሩ ምክንያት ጉራማይሌ የህይወት ልምድ እንዲቀስም አስተዋጽኦ አድርጎለታል።የቀበና ሰፈር በሙያቸው የላቁ ብዙ ታዋቂና ዝነኛ ሰዎችን ያፈራ እንደሆነ ይታወቃል።

ታዳጊ ወጣትነት

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በቀበና አድቬንቲስት ሚሽን፣ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ት/ቤት ተከታትሏል።በትምህርት ቤቶቹ በገና በዓል እና በሌሎች አውደ በዓላት ልዩ ልዩ የሚዲያና የኪነት ሥራዎችን አዘጋጅቶ በማቅረብ በእጅጉ ይታወቃል።

የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ የተማረባቸው ት/ቤቶቹ መሠረታቸው ሃይማኖት ነው።እርሱ በተማረበት ጊዜ በሁለቱም ት/ቤቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በመደበኛነት ይሰጣል።ግብረገብ እና መንፈሳዊ ዕውቀቶች ዋና እሴቶች ነበሩ።በዘካርያስ የሕይወት መስመር እና የሰብዕና ግንባታ ውስጥ የእነዚህ ት/ቤቶች ተጽዕኖ ቀላል አልነበረም።

የዘካርያስ አባት ካህን ናቸው።በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሊቀ ካህናት ማዕረግ አላቸው።በቤተክርስቲያኒቱ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር በአመራርና በአስተዳደር ዘርፍ እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ናቸው።በመንፈሳዊና በዓለማዊ ትምህርታቸውም የላቀ ደረጃ የደረሱ ሊቅ ናቸው።በቤተክርስቲያኒቱ የሚገኙ ልዩ ልዩ ተቋማትን በኃላፊነት መርተዋል፣በተለያዩ የውጭ ሀገራት ልዩ መልዕክተኛ በመሆን ቤተክርስቲያኒቱን አገልግለዋል።በማገልገል ላይም ናቸው።

እነ ዘካርያስ ቤት የቤተክህነት ትምህርት ኮመን ኮርስ ነው።ወንድሞቹ ሁሉ ካላቸው መደበኛ ዓለማዊ ሞያ ባሻገር የዲቁና ማዕረግም አላቸው።በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጎርጎርዮስ አስተዋጽዖ ትልቅ ስም ባገኘውና የማኅበረ ቅዱሳን መስራቾችን ጨምሮ በርካታ ደቀመዛሙርት በወጡበት የዝዋይ ሐመረ- ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ነው ዘካርያስ የቤተክህነት ትምህርት የተማረው።ከመደበኛ ትምህርትና ሥራው ጎን ለጎንም አዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በዲቁና ሞያ አገልግሏል።መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ፣ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ፣ደብረምህረት ቅዱስ ሚካኤል በበጎ ፈቃድ (በመደበኛነት ሳይቀጠር) በዲቁና ሙያ ካገለገለባቸው ቤተክርስቲያናት የሚጠቀሱ ናቸው።

ከፍተኛ ትምህርት

ዘካርያስ የከፍተኛ ትምህርቱን በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ (የቀድሞው ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ) ነው የጀመረው።በዚያ በቋንቋና ሥነጽሑፍ ዲፕሎማ አግኝቷል።በኮተቤ ዩንቨርስቲ ከመደበኛ ትምህርቱ ባሻገር ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በመሠረተው ወርሃዊ የኪነጥበብ ፕሮግራም ይታወቃል።ድራማና ግጥም እንዲሁም ታዋቂ የኪነጥበብ ሰዎች ይቀርቡበት ነበር በመድረኩ።በመቀጠል በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የቲያትር ጥበባትን በማጥናት የመጀመሪያ ዲግሪውን በከፍተኛ ማዕረግ አግኝቷል።በዩኒቨርስቲው የባህል ማዕከል የሥነጥበባት እንቅስቃሴዎች ላይ የጎላ አስተዋጽኦም ነበረው።

ሁለተኛ ዲግሪውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው የሰራው፤በሥነጽሑፍ እና ፎክሎር።በትምህርት ክፍሉ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸውና ከሚወዳቸው መምህራን መካከል ረ/ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ፣ዶ/ር ፍቃደ አዘዘ እና ረ/ፕሮፌሰር ሰላማዊት መካ ይጠቀሳሉ።የሁለተኛ ድግሪው የጥናት ወረቀት ትኩረት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና በፕሮቴስታንት እምነቶች የመዝሙር ግጥሞች ላይ የሚያጠነጥን ነው።ሁለቱ ሃይማኖቶች በመዝሙር ግጥሞቻቸው ያነሷቸውን ጭብጥና ርዕሰ- ጉዳይ በመመርመር ስነጥበባዊ ፍልስፍናቸውን ይተነትናል።የጥናቱ አማካሪ ረ/ፕሮፌሰር ሰላማዊት መካ ሲሆኑ ፈታኞቹ ከፎክሎርና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ዶ/ር ፍቃደ አዘዘ፣ከጥንታውያን ጽሑፎች ጥናት (ፊሎሎጂ) ዲፓርትመንት ረ/ፕሮፌሰር ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ነበሩ።በጥናት ወረቀቱ ከፍተኛ ውጤት በማግኘት ነው ማስትሬቱን ያገኘው።

የሥራ ዓለም

የዘካርያስ የሥራ ጅማሬና የረጅም ዓመታት ቆይታው ሬድዮ ፋና (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት) ነው።ጣቢያው በ1999 ዓ.ም FM 98.1 ሥርጭትን ለመክፈት ማስታወቂያ ባወጣ ጊዜ ከአንድ ሺህ በላይ ተመዝጋቢዎች ነበሩ። በአራት ዙር እና ዓይነት በተለያየ ጊዜ በተካሄደው ፈተና ዘካርያስ የላቀ ውጤት አምጥቶ በማለፍ ሬድዮ ፋናን ተቀላቀለ።

ፋና ኤፍ ኤምን ከጣቢያውና ከ10 ጋዜጠኞች ጋር በመሆን መሠረተ። ፋና ኤፍ ኤም በኢትዮጵያ የሬድዮ ታሪክ ልዩና የማይዘነጋ አሻራ ያለው ጣቢያ ነው።አዳዲስ የፕሮግራም ፎርማቶችን በማስተዋወቅ፣ ትኩስና አዝናኝ ፕሮግራምና ዜናዎችን በልዩ አቀራረብ ለአድማጭ በማድረስ ትልቅ ስም ያለውና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚድያ ነው።90 ደቂቃ፣ተጓዥ ነቃሽ፣ጥበብ በፋና፣ገጠመኝና ማስታወሻ፣ ፋና ምርጥ አስር፣ትዝ አለኝ የጥንቱ እና ሌሎች በርካታ የሬድዮ ፕሮግራሞች ከብዙዎቹ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው።ዘካርያስ ከሪፖርተርነት እስከ ከፍተኛ አዘጋጅነትና አርታዒነት በፋና ኤፍ ኤም ሰርቷል። በኋላም የጣቢያው ዋና አዘጋጅ በመሆን ለረጅም ዓመት አገልግሏል።በሬድዮ የዋና አዘጋጅ ኃላፊነት ድርሻው የዜና፣ የመዝናኛና የትምህርታዊ ይዘቶችን እንዲሁም የተባባሪ ፕሮግራሞችን በአንድ ላይ መርቷል።በዚህ ወቅት ገለልተኛ በሆነ የውጭ ተቋም በተሠራ ጥናት ጣቢያው በኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ተደማጭ ጣቢያ በመሆን ተመርጦ ነበር።

ዘካርያስ ከመደበኛ የጋዜጠኝነት ሥራና ኃላፊነቱ ባሻገር በርካታ የሬድዮ ድራማዎችን በመጻፍና በማዘጋጀት ያቀርብ ነበር።አንጋፎቹ አርቲስቶች ፍቃዱ ተ/ማርያም፣ሽመልስ አበራ፣ፍቅርተ ጌታሁን፣ዘውዱ አበጋዝና ከሃምሳ በላይ ተዋቂ አርቲስቶች የተሳተፉበትና ለሁለት ዓመት ያህል በየሳምንቱ ሲቀርብ የነበረው “ጠጣር ፍሬ” ተከታታይ የሬድዮ ድራማ፤እነ አርቲስት ሃና ዮሐንስ፣ ትዕግሥት ግርማ፣አበባው መላኩ፣መኮንን ተፈሪና በርካታ ከያንያን የተሳተፉበትን “ስውር መንገደኞች” ተከታታይ የሬድዮ ድራማ ለዓመታት በየሳምንቱ እያዘጋጀ ያቀርብ ነበር።ለአብነት ከተጠቀሱት የሬድዮ ድራማዎች በሻገር በርካታ አጫጭርና ረጃጅም ትረካዎችን በሬድዮ አቅርቧል።

“ጥበብ በፋና” በተሰኝው ሳምንታዊ የፋና ኤፍ ኤም ፕሮግራም ልዩ ልዩ የሀገር ውስጥና ዓለምአቀፍ ኪናዊ ይዘቶች ከትንታኔ ጋር ይቀርቡበት ነበር።ዘካርያስ በሀገራችን በሚከወኑና በሚጻፉ የኪነጥበብና የባህል ይዘቶች ላይ ከአድማጮችና ከባለሙያዎች ጋር ሰፊና ጥልቅ ውይይት በየሳምንቱ በማካሄድ ለኪነጥበብና ለባህል እድገት የበኩሉን ሚና ሲወጣ እንደነበረ አይዘነጋም።የከያንያንና የመንግሥት ዘልማዳዊና የቸከ አሰራርና አስተሳሰቦች ላይ ልዩ ትንታኔን የያዘ ሂሳዊ ፕሮግራም በቅንብርና በቀጥታ ሥርጭት ውይይት በማዘጋጀት እንዲፈተሹና እንዲሻሻሉ ትልቅ እገዛ አድርጓል።

”ትዝ አለኝ የጥንቱ” ከበርካታ ፕሮግራሞቹ በቀላሉ ትዝ የሚል ፕሮግራም ነው።ምክንያቱም ፕሮግራሙ ልዩ አቀራረብ ያለውና በብቸኛ አዘጋጅነት በየሳምንቱ ለአስር ተከታታይ ዓመታት በዘካርያስ ተዘጋጅቶ ይቀርብ ስለነበር ነው።ይህ ሁኔታ በፋናም ሆነ በሌሎች ሚዲያዎች ብዙም የተለመደ አይደለም።ትዝ አለኝ የጥንቱ አስገራሚ፣አዝናኝና ልዩ መረጃ ሰጪ የሆኑ ጽሁፎች ከቆዩ ሙዚቃዎች ጋር የሚቀርቡበት ፕሮግራም ነው።

ዘካርያስ ጽሑፉቹን የሚያቀርብበት ልዩ ለዛ አለው።ሙዚቃዎቹንም ከጽሑፍ ይዘት ጋር ስሜትና ትርጉም እንዲሰጡ የሚያደርግበት ልዩ ጥበብ አለው።ዘካርያስ በቢሮ ካልተገኘ መገኛው ወመዘክር ወይም IES(የአ.አ ዩንቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት ላይብረሪ) ነው።ለትዝ አለኝ የጥንቱ የሚሆኑ የቆዩ የህትመት መረጃዎችና ሰነዶች እየፈለገ ቢውልና ቢያነጋ አይታወቀውም።ፕሮግራሙን በልዩ ፍቅርና ትጋት ስለሚሰራም ልፋትና ድካሙ ትዝ ብሎት አያውቅም።

በፋና ቴሌቪዥን

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቴሌቪዥን ስርጭት ሲጀምር የመዝናኛ ፕሮግራሞች ዋና አዘጋጅ እና የተባባሪ ፕሮግራሞች ኃላፊ በመሆን የሥራ ክፍሉን መርቷል።አዳዲስ የፕሮግራም ፎርማቶችን በመፍጠርና በመቅረጽ የላቀ አስተዋጽኦ አድርጓል።በተለይ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ትልቅ ሚና ነበረው። ”ፋና ላምሮት”፣”ፋና ቀለማት” የመሳሰሉት በውስጣቸው ልዩ ልዩ ይዘቶችን የያዙ ትልልቅ የመዝናኛ ፕሮግራሞች የሱ ፈጠራና አቅም ውጤቶች ናቸው።ከፋና ጋር በትብብር የሚሰሩ ልዩ ልዩ ተቋማትና ፕሮግራም አዘጋጆችን በመምረጥ፣በመገምገም፣በማረቅ እና በየጊዜው ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የላቀ ሥራ ሰርቷል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አዘጋጅቶት በነበረው የታታሪ ሰራተኞች ውድድር አሸናፊ በመሆን የገንዘብ ሽልማትና ሰርተፍኬት አግኝቷል።ውድድሩ በየሥራ ክፍሉ የተለያዩ አሸናፊዎች ነበሩት።

በኃላፊነት

ዘካርያስ በሬድዮ ፋና ቆይታው መደበኛ ከሆነው የጋዜጠኝነት ሥራው ባሻገር የዜና፣የትምህርታዊ፣ የመዝናኛ እና የተባባሪ ፕሮግራም ክፍሎችን በተለያየ ጊዜ በኃላፊነት መርቷል።ጋዜጠኞች ያላቸውን አቅም በመለየትና በሁነኛ የሥራ ድርሻ ላይ በመመደብ፣ተከታታይ ድጋፍና ክትትል በማድረግ፣ከተለመደው የተለየ የአሰራርና የአቀራረብ መንገዶችን በማሳየት ይታወቃል።ከምንም በላይ ቀላልና አዝናኝ በሆነ አቀራረቡ ይወደዳል።ሥራው ይቅር እንጂ የሠራተኛው ስሜት በቅድሚያ ሳይሰራ ሥራ እንዲሰራ አያደርግም። ከሥራ በኋላ በሚኖሩ ስብሰባዎች ሥራን የሚገመግምበት መንገድም የተለየ ነው።ድክመቶች ላይ ሳቅ በመፍጠር እንዳይደገሙ ወይም እንዲሻሻሉ እርምቶችን ይሰጣል።ሰሪው ተዝናንቶ(ሳይሳቀቅ) እንዲገነዘበው፤ሌሎችም ስህተቱን እንዳይረሱትና እንዳይደግሙት ለማድረግ ምንግዜም ልዩ ብልሀት ይጠቀማል።የራሱን ጣቢያና የሌሎችን ልቅም አድርጎ ይከታተላል።ከሌሎች ጣቢያዎች በድክመትና በጥንካሬ የተሰሩ ፕሮግራሞችን እያነሳ የመወያያ ርዕስ ይፈጥራል።ጋዜጠኝነት ቀለልና ለቀቅ ባለ ስሜት ነው መሰራት ያለበት የሚል እምነት አለው።

መረጃና ዕውቀትን በልዩ ብልሀትና ክህሎት የማስተላለፍ ሞያ ስልሆነ ባለሙያው ከትምህርትና ልምድ ባሻገር መልካም ስሜት ላይ መገኘት የግድ እንደሚኖርበት ደጋግሞ ይናገራል።ሰራተኞች ሥራቸውን በአግባቡ እስከሰሩና መደበኛ ኃላፊነታቸውን እስከተወጡ ድረስ የቢሮ ዲሲፕሊናቸው ብዙም አያሳስበውም።በኃላፊነት ጊዜው ለአንድም ጋዜጠኛ የቅጣት ደብዳቤ ጽፎ አያውቅም።ጥፋትና አጥፊ መቼም ባይጠፉም መልካም ያልሆኑ አጋጣሚዎችንና ሰራተኞችን የሚያስተናግድበት ልዩ ብልሀት አለው።

ለአዳዲስ የፕሮግራም ፕሮጀክቶች እና በቀጥታ ሥርጭት ለሚቀርቡ መደበኛ ፕሮግራሞች ሰፊና ዝርዝር ሰነድ በማዘጋጀት ይታወቃል።ማንኛውም ሥራ በቅጡ የተጻፈ ዝርዝር እቅድና ትንታኔ እንዲሁም ቼክ ሊስት ሊኖረው ይገባል ብሎ ያምናል።ሥራው የተለመደና መደበኛም ቢሆን ሥራዎችን በዚህ መንገድ መሥራትና ማሰራት ሁሌም ምርጫው ነው።

በደራሲነት

የዘካርያስ የድርሰት ሥራዎች የሚጀምሩት በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነው።በትምህርት ቤቶቹ በልዩ ሁኔታ በሚከበሩት የገና እና የወላጆች በዓላት መንፈሳዊና ዓለማዊ ድራማዎችን እየጻፈና ተማሪዎችን እያስጠና ያቀርብ ነበር።

በምስካዬኅዙናን የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ የትምህርት ክፍሉ ማጠናቀቂያ ልዩ መርኃግብር የኮሚቴ አባል ነበር።መጽሔት ለማሳተምና የመሰናበቻ መርኃ ግብር ለማሰናዳት ገንዘብ ያዋጣሉ።ሆኖም የታሰበውን ዓይነት ፕሮግራም ለማዘጋጀት የተዋጣው ገንዘብ ያንሳል።ይሄኔ የኮሚቴው አባል የነበረው ዘካርያስ አንድ ዘዴ ያመጣል ።ድራማ አዘጋጅቶ በማቅረብ ገቢ መሰብሰብ።ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ላይ በመንተራስ ወጥ የሆነ አዝናኝ ድራማ ጻፈ።

ራሱን ጨምሮ ተማሪዎችን መልምሎ(cast አድርጎ) ድራማውን አዘጋጅቶ በትምህርት ቤቱ አዳራሽ በክፍያ አሳየ።ድራማው ተማሪዎችን ጨምሮ የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ በእጅጉ አስደሰተ።ተደጋግሞም ታየ።ከተጠበቀው በላይ ከፍተኛ ገቢም አስገኘ።በዘካርያስ ቲያትርና በሌሎችም የገቢ ማስገኛ ዘዴዎች በተሰበሰበ ገንዘብ በሒልተን ሆቴል ድል ያለ ድግስ ተደገሰ።የሦስት ክፍል የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከነወላጆቻቸው እንዲሁም የት/ቤቱ መምህራን በማይረሳው የመሸኛ ፖርቲ ታደሙ።ከምሽት እስከ ንጋት ከሙሉ የእራትና የሙዚቃ ባንድ ዝግጅት ጋር በፌሽታ አሳለፉ።

ፊልዮሶፍያ

ዘካርያስ ከአንድ ጓደኛው ጋር የመሠረተውና የቅርብ ጓደኞቹን ያሰባሰበበት የጥበብ ክበብ ነው።”ፊልዮ” ጥልቅ ፍቅር፣”ሶፍያ” ደግሞ ጥበብ ማለት ሲሆን የቃላቶቹ ሕብር የጥበብ አፍቃርያን የሚል ትርጉም ይሰጣል በግሪክ።በጥበብ ጥልቅ ፍቅር የወደቁ ዘካርያስና ጓደኞቹ የትርጉሙ አምሳያ በመሆናቸው በስያሜው እንዲጠሩ ወሰኑ።በተለያዩ ቀበሌና የት/ቤት አዳራሾች እንዲሁም በክልል ከተሞች እየተዘዋወሩ ትያትሮችን በነጻና በአነስተኛ ክፍያ ያቀርባሉ።በየጊዜው እየተገናኙ ላቅ ስላሉ የጥበብ ሥራዎች ይወያያሉ፣የቲያትር ስክሪፕት ያነባሉ፣ በሙያው ሁለንተናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳብ ይለዋወጣሉ።የቡድኑ አባላት በተለያየ የኑሮና የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ ቢሆኑም በቋሚነት የሚገናኙበትና የሚሰሩበት ጊዜ አላቸው።ከ15 ዓመት በላይም በጥበባዊና ቤተሰባዊ ወዳጅነት ዘልቀዋል።

በቴአትር ቤቶች

የመጀመሪያ የቲያትር ድርሰቱን በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ (ማዘጋጃ ቤት) በ1996 ዓ.ም ነው ያቀረበው።”የተረሳው ዕዳ” የቲያትሩ ርዕስ ነው።አንጋፋው አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ፣ሰብለ ተፈራ (እማማ ጨቤ)፣ትዕግስት ዓለሙ፣ሰሎሞን ሀጎስ፣ጌታሁን ኃይሉ፣ የትናየት ታምሩና ዳዊት መንግሥቱ የተሳተፉበት ቲያትር ነበር።

ሁለተኛ ቲያትሩን ጽፎ ያቀረበው በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በ1998 ዓ.ም ነው።”ናፋቂዎች” የተሰኘ ኮሜዲ ቲያትር ነው።ሦስተኛ ቲያትሩ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ነው የቀረበው።”ዕጣ ፈለግ” የሚል ርዕስ ያለው ይህ ቴአትር ከሌሎቹ የሚለየው ትያትሩን ከመጻፍ ባሻገር በትወና የተሳተፈበትና የፊልዮሶፍያ አባላትን በሙሉ ያሳተፈበት መሆኑ ነው።ዘካርያስ በቴአትር ቤት ደረጃ ካቀረባቸው ቲያትሮች ሁሉ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ቲያትር ነው፤”ዕጣ ፈለግ”።የራሱ፣የጓደኞቹና የሀገሩ ታሪክ በቲያትሩ በልዩ ጥበባዊ አቀራረብ ተዳሷል።ቲያትሩ በተለያየ ዓመታት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቀርቧል።የመጀመሪያው በቴአትር ቤቱ ፕሮዲውሰርነት (አቅራቢነት) በ1998 ዓ.ም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ዘካርያስ በግሉ ባቋቋመው ድርጅት አማካኝነት በ2004 ዓ.ም ነው። በአጠቃላይ ከሁለት ዓመት በላይ በቴአትር ቤቱ መድረክ በየሳምንቱ እየቀረበ ሲቆይ ከፍተኛ አድናቆትና ተወዳጅነት በተመልካች አትርፏል።

አራተኛውና በሀገር ፍቅር ቴአትር የቀረበው የዘካርያስ ቲያትር ለረጅም ጊዜ በመታየት ሪከርድ የሰበረ ነው። “የበዓል ዕንግዶች” የተሰኘ ሲሆን በ2004 ዓ.ም ነው መታየት የጀመረው።የትያትር ቤቱ ዝነኛ ተዋንያን ከተጋባዥ አርቲስቶች ጋር በመሆን ተጫውተውታል።አርቲስት ተስፉ ብርሃኔ፣ሸዊት ከበደ፣ዮናስ ጌታቸው፣ሃና ተረፈ፣ትዕግስት ግርማና አብዱልከሪም ጀማል ተሳትፈውበታል።ከ7 ዓመታት በላይ በሀገር ፍቅር ቴአትር መድረክ በየሳምንቱ እየቀረበ ተመልካችን ሲያዝናና የነበረ ነው።የአዲስ አበባ ከተማ የተመሠረተበትን 125ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በከተማ አስተዳደሩ የሚታዩ ቲያትሮችን አወዳድሮ ነበር።በምርጥ የቲያትር ጽሁፍ “የበዓል ዕንግዶች” ቲያትር 2ኛ ደረጃ አግኝቶ በማሸነፉ ዘካርያስ በከተማ አስተዳደሩ ተሸላሚ ነበር። ዘካርያስ ከቲያትርና የሬድዮ ድራማ ድርሰቶቹ ባሻገር ለህዝብ የቀረቡና ያልቀረቡ የፊልምና የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎችን ደርሷል።

በማህበራዊ አገልግሎት

ዘካርያስ በተለየ ከሚታወቅባቸው ባህሪዎቹ አንዱ ማህበራዊነቱ ነው።በበጎ ፍቃድ በሚሰሩ ሥራዎች፣ ማስተባበርና ማነሳሳት በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ንቁና መሪ ነው።በሬድዮ ፋና በሚካሄዱ ታላላቅ መድረኮች ምንጊዜም የኮሚቴ አባል ሆኖ ይመረጣል።ለምሳሌ ጣቢያው በልዩ ሁኔታ ባከበራቸው የ15፣የ20 እና የ25 ዓመት የምሥረታ በዓላት በዋና ኮሚቴነት ተሳትፎ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።በተለያየ ጊዜ ሰዎች ላይ ችግርና ደስታ ሲያጋጥም ከሀሳቡ እስከ ገንዘብ ማሰባሰቡ ቀዳሚ ነው።በፋና ውስጥ የመሠረታቸው ሦስት አራት የዕቁብና የመረዳጃ ማህራት አይጠፉም።ከመሥሪያ ቤቱ ውጭም ተመሳሳይ ነው።የኢትዮጵያ የቴአትር ባለሙያዎች ማህበር ለ2ኛ ጊዜ ሥራ አስፈጻሚ አባል ሆኖ በመመረጥ እያገለገለ ይገኛል። በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በርካታ ሥራዎችን በአባልነቱና በበጎ ፍቃደኝነት ሰርቷል።በሁለት ሺ ዓ.ም የሚልንየም በዓል ሲከበር የንባብ ባህልን የተመለከተ ትልቅ ዶክመንተሪ ፊልም እንዲሰራ በደራሲያን ማህበር ተመርጦ በጥሩ ሁኔታ አዘጋጅቶ ለማህበሩ አስረክቧል።ሌሎች የተለያዩ ማህበራትና የበጎ ነገር ስብስቦች ውስጥ ስብስቡን በመፍጠር አልያም በአባልነት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ይታወቃል።

ቤተሰብ

ዘካርያስ ብርሃኑ ለቤተሰቡ 4ኛ ልጅ ነው።ፍሬሕይወት የምትባል ተወዳጅና ብቸኛ እህት እንዲሁም አምሃ፣ዐቢይ እና ቴዎድሮስ የተሰኙ ወንድሞች አሉት።ከባለቤቱ ቤቲ ግርማ ጋር በ2007 ዓ.ም ትዳር መስርቶ ኖቤል እና ሚልካ የሚባሉ የሚያማምሩ ወንድና ሴት ልጆች አፍርቷል።

ስለ ዘካሪያስ ብርሀኑ ምስክርነት የሰጡ

ዘካሪያስ ብርሀኑ ማህበራዊ ግንኙነቱ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ይህ ማህበራዊ ግንኙነቱ ጠንካራ ስለሆነም የሚድያም ሆነ የኪነጥበብ ስራውን ቀለል አድርጎ ይሰራል፡፡ ዘኪ ከኪነጥበቡ ጋር በተያያዘ ከብዙዎቹ ጋር ትውውቅ ስለነበረው እኛ ብዙ ጊዜ ሰዎችን ለማግኘት ዘኪ ጋር መሄዳችን የግድ ነበር፡፡ እርሱ የማሳመን ልዩ ክህሎት የታደለ ስለነበር ለቃለ-መጠይቅ እንዲመጡ ያደርጋቸዋል፡፡ በጣም የሚደንቀኝ ስለምንጠይቀው ሰዎች በቂ መረጃ ነበረው፡፡ ሌላው ታላላቅ ሰዎች ህይወታቸው አለፈ ሲባል ስለ ሰዎች ታሪክ ከእነ ሰነዱ የሚገኘው ዘካሪያስ ጋር ነው፡፡ይህ ትልቅ ክህሎት ነው፡፡ ዘካሪያስ ከማንኛውም ሰው ጋር በቀላሉ ለመገናኘትም ሆነ ቀርቦ ለመስራት የታደለ ነው፡፡ እየሳቀ ፤ እየቀለደም ሳይጨናነቅና ሳያስጨንቅ ስራ ያሰራ ነው፡፡ ወደ ቁምነገሩ ሲገባ ግን ስራ ላይ ውልፍት የለም፡፡ ስራ ሲሆን ማዋዛት ቀልድ የለም፡፡ ስራውን አስቦበት ስራዮ ብሎ ሲሰራ ቀልድ ብሎ ነገር የለም፡፡ አንዴ ላመነበት ነገር መቆም ከጀመረ ወደ ኋላ የለም፡፡ ይህን እንደ ትልቅ ጠንካራ ጎን እወስድለታለሁ፡፡ በሙያውም ቢሆን አዳዲስ ነገር ለመፍጠር የሚተጋ ብርቱ የሚድያ ሰው መሆኑን አምናለሁ፡፡

ጋዜጠኛ ትእግስት በጋሻው ከታዛ የሬድዮ ፕሮግራም / የቀድሞ ባልደረባ/

ዘካርያስ ብርሃኑን በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ስራ ስጀምር ጀምሮ ላለፉት ሰባት አመታት አውቀዋለሁ፡፡ በፋና ኤፍ ኤም ሬዲዮ በመዝናኛ ክፍል ውስጥ በመሪነት በነበረባቸው ጊዜያትም ሆነ ከ2011 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ መካሄድ በጀመረው ፋና ላምሮት የባለ ተሰጥኦ የድምጻውያን ውድድር ውስጥ እስከ ምዕራፍ 8 በተጓዘበት ሂደት ላይ ፎርማቱን በመቅረፅም ሆነ ወደ ተግባር በመቀየር በኩል የሱ ሚና ወሳኝ ነበር፡፡

ፋና ላምሮት አንድ ብሎ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በቆየባቸው ስምንት ምዕራፎች እንዲሁም ባካሄድናቸው ሁለት ከባድ የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድሮች ላይም አዳዲስ ነገሮችን በማምጣት ውድድሩ ከመነሻው የሰዎችን አይን እንዲስብ በማድረግ በኩል የሱ ሚና በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡ በፋና ላምሮት የቀጥታ ውድድር ላይ የተወዳዳሪዎችን ፣ የዳኞችን፣ የሰራተኞችን ባህሪ በአግባቡ ተረድቶ እና ችሎ መምራት ትልቁ ፈታኝ ነገር እንደመሆኑ ይሄን በብቃት በመወጣት ያለምንም ችግር ውድድሩ እዚህ እንዲደርስ በማድረግ በኩል ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

በጋዜጠኝነት ብሎም ባጠቃላይ በመገናኛ ብዙሃን ስራ ውስጥ ከሌሎች የሙያ ዘርፎች ጋር የሚኖር ግንኙነት ለስራው ወሳኝ እንደመሆኑ በዚህ በኩል እሱ ያለው የግንኙነት አድማስ ሰፊ መሆን በተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶችና በፋና ላምሮት የውድድር ሂደቶች ላይ ሃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ እገዛ አድርጎለታል፡፡ በዚህ በኩልም ለብዙዎቻችን ምሳሌ መሆን ችሏል፡፡

በተለይ ውሳኔ የመስጠት እና ለችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠት አኳያ የተለየ የመሪነት ብቃት እንዳለው ማየት ችያለሁ፡፡ ሰራተኞችን ከማብቃት አኳያም በተለይ ከፋና ላምሮት ጅማሮ አንስቶ ሰራተኞችን ማመን ብሎም ሀላፊነትን ሰጥቶ ማሰራት ላይ ውጤታማ እንደነበር እኔ አንዷ ምስክር ነኝ፡፡ ቅድመ ዝግጅት በማድረግና በእቅድ ከመመራት አኳያም ጥንቁቅ የነበረ መሆኑ በስራዎቹ ሁሉ ውጤታማ አድርጎታል፡፡ የሰራተኞችን ችግር መረዳት፣ ሠራተኛው ያለውን ችሎታ ማወቅና በተገቢው ቦታ ማሰማራትም ካሉት ብቃቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በፋና የመዝናኛ ክፍል ውስጥ በሚኖሩን የግምገማ ሰአቶች ምክንያታዊ ሆኖ ሰዎችን መገምገምና ምክንያታዊ ሆኖ አስተያየቶችን መቀበልም የሱ መገለጫዎች እንደሆኑ አስታውሳለሁ፡፡ ጫናዎችን ተቋቁሞና ችግሮችን ተጋፍጦ በመስራት ፋና ላምሮት ሲነሳ ስሙ ሁሌም አብሮ የሚነሳበትን አይተኬ ሚና ተወቷል ማለት እችላለሁ፡፡ለምለም ዮሐንስ ከፋና ቲቪ

የመዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ዘካርያስ ብርሀኑ ገና በ22 አመቱ በቴአትርና ባህል አዳራሽ የራሱን ቴአትር ደርሶ ለማሳየት የቻለ ነው፡፡ ይህ ፍል አምሮት ወይም ፓሽን በየጊዜው እያደገ ሄዶ ትልልቅ ስራዎችን እንዲሰራ በር ከፍቶለታል፡፡ ዘካርያስ አሁን ባለው ወይም ባለፉት 15 አመታት በሀገራችን የኤሌክትሮኒክስ ሚድያ ላይ ለመጡት በጎ እንቅሳቃሴዎችና ለውጦች አንዱ ተመስጋኝ ነው፡፡ በተለይ የኤፍኤም ጣቢያዎች ከፍተኛ ፉክክር ላይ በነበሩበት ዘመን ብቅ ያለ ጋዜጠኛ ስለነበር በብዙ ሁኔታዎች ያለፈና በርካታ አሻራዎች ያሳረፈ ነው፡፡ የሚድያ ሰው ሌላውን ያሳውቃል እንጂ እርሱን ማን ያውቀዋል? ያከናወናቸውን አበይት ተግባራት ማን ይሰንድለታል? ዘካሪያስም ቢሆን ብዙ ስላልተባለት ወይም ራሱም ብዙ ስለማይናገር ነው እንጂ ስራዎቹ ብዙ ይናገራሉ፡፡

የመዝናኛ ፕሮግራሞች በጥሩ መልኩ መምራት ፤ እቅድና ፎርማቶችን ማቃናትና ማረቅ የዘካርያስ ልዩ መታወቂያው ነው፡፡ ሰርቶ ለማሰራትም ድንቅ ሰብእና ያለው ነው፡፡ የሚድያው ዘርፍ እንደ ዘካርያስ አይነት ሰው የግድ ያስፈልገዋል፡፡ ወይም የዘካርያስ ልምድ ጥሩ ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው፡፡ ይህንን ታሪክ ለማጠናከር በሚል ከዘካርያስ ጋር የሰሩ 15 ሰዎች ለማነጋገር ሞክረን ሁሉም በሚባል ደረጃ በጣም ጎበዝና ቀና ባለሙያ ነው ሲሉ ገንቢ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ይህም አስተያየት የዘካርያስን ግለ-ታሪክ በዚህ መልኩ እንድንሰራ እድል ፈጥሮልናል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ በኢንሳይክሎፒዲያ ይህን ታሪክ ሲሰንድ ትውልድ ከዘካርያስ አንዳች ቁምነገር ይቀስማል ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ ለዘካርያስ የተወዳጅ ሚድያ የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ ትልቅ ክብር ያለው መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ ይወዳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *