ዘከሪያ መሐመድ ያሢን
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡
የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡200 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡
በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ዘከሪያ መሀመድ አንዱ ነው፡፡ ዘከሪያ መሀመድ ባለፉት 30 አመታት በቢላል መጽሄት ፤ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በኢቲቪ እና በሸገር ያገለገለ ጎልማሳ ነው፡፡ በሳል ተርጓሚና የጥላሁን ገሰሰን ታሪክ ከእነ ሙሉ ክብሩ የጻፋ ነው፡፡ የህይወት ታሪኩን እንድንሰራ ፈቃድ ሰጥቶን እነሆ ብለናል፡፡ የዘከሪያን ታሪክ አይናለም ሀድራና እዝራ እጅጉ ሰንደውታል፡፡
ውልደትና ትምህርት
በጋዜጠኝነት፣ በሕዝብ ግንኙነት፣ በኮሚኒኬሽንና አድቮኬሲ ኦፊሰርነት በጥቅሉ ለ30 ዓመታት ያገለገለው ዘከሪያ መሐመድ ውልደቱና ዕድገቱ አዲስ አበባ ነው። በመጋቢት ወር 1962 ከአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴ አጠገብ፣ ሚንዳ ሠፈር የተወለደው ዘከሪያ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ ከተማ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማረው። ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ካጠናቀቀ በኋላ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባ። በ1984 ከዩኒቨርሲቲው በቴአትር ጥበባት የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ።
የሥራ ሕይወት
ሁለገቡ ዘከሪያ በብሮድካስትም ሆነ በህትመት ሚዲያ ዘርፍ አበርክቶው ከፍ ያለ ነው። በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና በሸገር FM በተለያዩ ኃላፊነቶች በጋዜጠኝነት አገልግሏል። ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ወደ ሥራ ዓለም እንደገባ፣ ነጃሺ አሳታሚ ድርጅት ያሳትመው በነበረው ቢላል ወርኃዊ የአማርኛ መጽሔት ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ በምክትል ዋና አዘጋጅነት ሠርቷል፡፡ በዚሁ ጊዜም፣ ከመጽሔት አዘጋጅነቱ በተጓዳኝ በመጻሕፍት ትርጉም እና አርትዖት ላይ ተሳትፏል፡፡
በ1988 ለአንድ ዓመት ገደማ በሕጻናት ቴአትር በስነ- ጽሑፍ ባለሙያነት ካገለገለ በኋላ፣ ከ1989 ጀምሮ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የእንግሊዝኛ ዜና ዴስክ ከረዳት አዘጋጅነት እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት በድምሩ ለአሥራ አንድ ዓመታት ያህል አገልግሏል፡፡ [በመሃሉ በ1996 አጋማሽ ኢዜኣን ለቅቆ በመውጣት በPerspective ሳምንታዊ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ላይ በዋና አዘጋጅነት ሲሠራ ቆይቶ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ በ1997 አጋማሽ ዳግም ወደ ኢዜአ ተመልሷል፡፡
በኢዜአ ቆይታው እንደ ጋዜጠኛ በአዲስ አበባ የተካሄዱ በዛ ያሉ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን፣ እና ሁለት ሀገር አቀፍ ምርጫዎችን (1992 እና 1997) ከመዘገቡ በተጨማሪ፣ ድርጅቱ ላሳተመው “የጋዜጠኝነት ሀሁ” የተሰኘ መጽሐፍ Feature Writing እና Sports Reporting በሚሉ ርዕሶች ጽሑፍ አበርክቷል።
ከባልደረባው መሳይ ምትኩ ጋር ያሰናዱት “A Longway to Peace & Justice” የሚል ርዕስ ያለውና በሁለት ዓመቱ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ላይ ያተኮረ ባለ 500 ገጽ መጽሐፍ በድርጅቱ ታትሞ ተሰራጭቷል፡፡ በተጨማሪም፣ ኢዜአ በታሕሣሥ 1996 ባሳተመው የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ቅኝት የተሰኘ ሒሳዊ መጽሔት ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የ‹ከሴቶች አድማስ› ዝግጅት ገጽታዎችን የሚቃኝ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርቧል፡፡
በ1997/98 መደበኛ ሥራውን በኢዜአ እየሠራ፣ በተደራቢነት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የእንግሊዝኛ ዜና ዴስክ ፍሪላንስ የምሽት ዜና ኤዲተር በመኾን ከአንድ ዓመት በላይ ሠርቷል፡፡ በተጨማሪም ዘከሪያ የራዲዮና የቴሌቪዥን ዶኩመንተሪዎችን፣ ጋዜጣ እና መጽሔቶችን በማዘጋጀት ይታወቃል። ከ1996 – 1997 አጋማሽ Perspective የተሰኘ ሳምንታዊ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመኾን ሠርቷል። Perspective ጋዜጣ ዮሐንስ አንበርብር፣ ዮሐንስ የኋላወርቅ እና ዮሐንስ አለነ የተባሉ ወጣቶች ከኮሌጅ ተመርቀው እንደወጡ በሪፖርተርነት በይፋ ሥራ የጀመሩበት፣ እንዲሁም ደራሲና የፖለቲካ ፀሐፊው (Political Commentator) ሙሉጌታ ጉደታ በአምደኝነት የተሳተፈበት ጋዜጣ ነበር፡፡
ዘከሪያ በ2000 ለመጨረሻ ጊዜ ኢዜኣን ለቅቆ በመውጣት፣ ከሙያ ጓደኞቹ ጋር ዛማስ ደቨሎፕመንት ኮሙኒኬሽንስ የሚሰኝ የግል ኩባንያ አቋቋመ፡፡ ኩባንያው ለተለያዩ ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች በሠራቸው ዶኩመንተሪ ፊልሞች ላይ የድርሻውን አበርክቷል፡፡ ኩባንያው ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋዜጠኞች በይርጋለም፣ ለድሬዳዋ ከተማ ጋዜጠኞች በድሬዳዋ የሰጣቸውን መሠረታዊ የጋዜጠኝነት ሥልጠናዎች አስተባብሯል፤ በአሠልጣኝነትም ተሳትፏል፡፡
ትርጉም እና አርትዖት (Editing) ዘከሪያ የተካነበት ዘርፍ ነው። የተለያዩ ጽሑፎችን እና የጥናት ውጤቶችን፣ እንዲሁም የዶክመንተሪ ጽሑፎችን ከአማርኛ ወደ እንግሊዝኛ፣ እንዲሁም ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ተርጉሟል፡፡ በተለያዩ የማጣቀሻ መጻሕፍት እና በዶክመንታሪ ፊልሞች ጽሑፍና ዝግጅት ላይ ሚናው የጎላ ነው። ፋሲልዳን ኮሙኒኬሽን የተሰኘ ኩባንያ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 30 የሚጠጉ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ገጽታ የሚያስተዋውቁ ዶኩመንታሪዎች ሲሠራ፣ ዘከሪያ ከ25 በላይ ስክሪፕቶችን በመጻፍ ተሳትፏል፡፡
የሥልጠና ማንዋሎችን ከማዘጋጀት ባሻገር፣ በተለያዩ ግለሰቦች እና የበጎ አድራጎት ተቋማት ለተዘጋጁ ጽሑፎች አርትዖት ሠርቷል። “አብሮ አደግ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ የመለሰው ተውኔትም በሜጋ አምፊቲያትር እና በብሔራዊ ቴአትር ለመድረክ በቅቶለታል። ለሁለት ዓመታት ለአሜሪካ ኤምባሲ የትርጉም ሥራ አገልግሎት የሰጠ ሲኾን፣ በዚሁ ጊዜ ፕሬዚደንት ኦባማ በካይሮ ዩኒቨርሲቲ ያደረጉትን ታሪካዊ ንግግር እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አካላት ያወጧቸውን ዓመታዊ የሰብኣዊ መብት እና ሌሎች ሪፖርቶችን ጨምሮ፣ በርካታ ጽሑፎችን ተርጉሟል።
ዘከሪያ በ2007 በጋዜጠኞች፣ በሐያሲያን እና በታሪክ ምሁራንም አድናቆት የተቸረውን “ጥላሁን ገሠሠ፡ የሕይወቱ ታሪክና ምሥጢር” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል፡፡ ይህ መጽሐፍ የጥላሁን ገሠሠን ሕይወት በምልዓት ከመተረክ ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ላይ ለሚሠሩ ጋዜጠኞች ዋና ማጣቀሻ በመኾን እያገለገለ ይገኛል፡፡ በሸገር FM በከፍተኛ አዘጋጅነት ለሰባት ዓመታት ያገለገለው ዘከሪያ፣ በቆይታው በሬዲዮ ዶክመንተሪ አዘጋጅነት፣ በዓለም አቀፍ ዜና ተንታኝነት እና በዜና ኤዲተርነት ሠርቷል፡፡ የጣቢያውን የ10ኛ ዓመት በዓል ልዩ መጽሔትም በዋና አዘጋጅነት አሥተባብሮ ለፍሬ አብቅቷል፡፡ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የሆነው ዘከሪያ መሐመድ ይህ ጽሑፍ በተሰናዳበት ጊዜ አማና የወጣቶች ልማት ኔትወርክ የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሲኾን፣ በተጓዳኝ የሁለት አንጋፋ ዜጎችን የሕይወት ታሪክ በመጻፍ ላይ ይገኛል፡
የዘከሪያ ተመራጭ መጽሐፍ
‹‹……. በእርግጠኝነት የእኔ ተመራጭ መጽሐፍ …. “ቅዱስ ቁርኣን” ነው፡፡ በሸኽ ሰዒድ ሙሐመድ ሳዲቅ እና በሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሀቢብ ተተርጉሞ በ1961 በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት የታተመው የቁርኣን [የፍቺው የአማርኛ] ትርጉም የእኔ የምንጊዜውም ምርጥ ድርሣን ነው። ቁርኣን ባነበብሁት ቁጥር፣ ሁሌም አዲስ ይኾንብኛል፤ ወይም ከዚያ በፊት ያላስተዋልሁት አዲስ ነገር አገኝበታለሁ። በዚህም ምክንያት በእጅጉ እደነቅበታለሁ። ደግሜ ባነበብሁት ቁጥር፣ ከአንዴም ብዙ ጊዜ፣ “ይህን እንዴት እስከዛሬ አላስተዋልሁትም?!” አሰኝቶኛል። በአጻጻፍ ስልቱ ቁርኣንን የሚመስል አንድም መጽሐፍ ዐይቼ አላውቅም።
የቋንቋ ክህሎቴን ያዳበርሁት ደግሞ በዋነኛነት የ1954ቱን የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ፣ በተጨማሪም የሀገራችን ታላላቅ የስነ ጽሑፍ ሰዎችን ሥራዎች በማንበብ ነው፡፡,,በማለት ነግሮን ነበር፡፡ ዘከሪያ ሀሣቡን በመቀጠል እንዲህ አለ ፣”ብዙ ሰዎች፣ ሙስሊሞችም ጭምር፣ የ”ተወለደ – አደገ – ጎለመሰ – አረጀ – ሞተ” ዓይነት፣ Beginning, Middle እና End ያለው የትረካ ስልት በመልመዳቸው፣ የቁርአን የፍቺው የአማርኛ ትርጉምን ማንበብ በጣም ይጠናባቸዋል፤ ይከብዳቸዋል። ቁርአን ከአንድ ሡራ [የዩሱፍ (ዮሴፍ) ምዕራፍ] በስተቀር፣ በዚህ ስልት የተዋቀረ አይደለም።”ብሎናል።
…ከተርጓሚዎች ተጨማሪ የማደንቃቸው ግለሰቦችን አስታወስሁ። ፀጋዬ ገብረ መድህን፣ መስፍን ዓለማየሁ እና ነቢይ መኮንን፣ እንዲሁም የሩስያ ደራሲዎችን ሥራዎች ከሩስኪ የተረጎሙትን ሰዎች።….በማለት ነግሮናል ።
ዘከሪያ ስለሚያደንቀው ሰው
የእኔ Role Model ወይም አርአያ ወደ ጋዜጠኝነት ዓለም እንደገባሁ የተዋወቅሁት ‹‹ጀሚል ከፍልውሃ›› እያለ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ ወግ ያቀርብ የነበረው የቢላል መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጀሚል ሸሪፍ ሰዒድ ይመስለኛል፡፡ ልቅም አድርጎ የመጻፍ ዝንባሌዬ ከእርሱ የተወረሰ ይመስለኛል፡፡
በዘከሪያ ላይ ምስክርነት የሰጡ
አዋድ አብዱልሰቡር የሰጠው ምስክርነት
በኢዜአ በምንሰራበት ወቅት የአርትኦት ስራውን ሲያከናውን በጥራት ነው፡፡ መረጃ አሰባስቦ ብቻ ቶሎ ጨረስኩ ጻፍኩኝ አይልም፡፡ አንዴ ጽሁፉን ከጻፈው በኃላ ደግሞ የማየት ልዩ ልማድ አለው፡፡ እኔ እጽፋቸው የነበሩትን የዜና ታሪኮች ኤዲት ሲያደርግ አንዳች እውቀት እቀስምበት ነበር፡፡ ዘከሪያ መሀመድ የትርጉም ስራዎችን ከሰራ በጥንቃቄ እና በእውቀት ተሞልቶ ነው የሚሰራው፡፡ በእንግሊዝኛም ሆነ በአማርኛ ጥሩ ክህሎት ስለነበረው የጽሁፍ ስራዎችን ከፍ ባለ ደረጃ ይሰራቸው ነበር፡፡ ስለ ጥላሁን ገሰሰ የጻፈውን ጽሁፍ ብንመለከት ድንቅ የኪነጥበብ ችሎታ እንዳለው እንረዳለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ተወዳጅ ሚድያ የህይወት ታሪኩን ለመስራት ተነሳሽነቱን ስለወሰዳችሁ አክብሮቴን መግለጽ እወዳለሁ፡፡ ዘከሪያ ሊነገርለት የሚገባ ሰው ነው፡፡ እርሱንም በዚህ አጋጣሚ የማደንቀው መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ፡፡
ጋዜጠኛ እና የስነ-ጽሁፍ ባለሙያ ሁሴን ከድር የሰጠው ምስክርነት
ለመጀመሪያ ጊዜ ከዘከሪያ ጋር የተገናኘነው በ1991 ይመስለኛል፡፡ ትውውቃችን ወደ 24 አመት ዘለቀ ማለት ነው፡፡በጊዜው [“The Message” ወይም “አሪሳላህ”]የሚል በነቢዩ መሀመድ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ፊልም ላይ የአክተሮቹን ድምጽ ሰርተን ነበር፡፡ ከዚያም ከ9 አመት በኋላ ዳግም የመገናኘት እድሉን አገኘሁ፡፡ ያኔ ነጃሺ መጽሄት ላይ በምክትል ዋና አዘጋጅነት እንድሰራ እድሉን ሰጠኝ፡፡ ዘከሪያን በስራ ካወቅኩበት ቀን ጀምሮ ያስተዋልኩት አንድ ነገር አንድን ስራ አምኖበት ከጀመረው እስከመጨረሻው የሚዘልቅ መሆኑ ነው፡፡ አንድ ጉዳይ ላይ ከተመሰጠ አይለቅም፡፡ ደግሞም የጀመረውን ነገር በጥልቀት ለመስራት ስለሚጥር ጥሩ ምርምር ያደርጋል፡፡
በ2001 አ.ም ላይ የጥላሁን ገሰሰን ታሪክ በእንዴት ያለ መልኩ ተግቶ እንደሰራ ማየት ይቻላል፡፡ በአጋጣሚ እጁ የገባውን የጥላሁን ቤተሰቦች ሰነድ መነሻ አድርጎ የጻፈውን ጥልቅ መጽሀፍ ማየት ይቻላል፡፡ይህ መጽሀፍ በብዙዎች የተደነቀ የህይወት ታሪክ አጻጻፍ ማስተማሪያ ሊሆን የሚገባው ነው ተብሎለታል፡፡ ታዲያ የጽሁፍ ስራን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለመስራት ምንጊዜም ተነሳሽነት የነበረው ዘከሪያ በዚህ ስራውን ከአንባቢያን ዘንድ እጅግ በጣም ጥሩ ምላሽ አግኝቷል፡፡
ዘከሪያ ሸገር በነበረበት ጊዜም የስራ ባልደረቦቹ በጣም የሚያከብሩት ሰው ነው፡፡ ሸገር አለቃ ሆኖ ይሰራ ስለነበረም ብዙዎቹ ይወዱት ነበር፡፡ ዘከሪያ አንዴ ስራ ከጀመረ በጥራት የሚሰራ ብዙ ሊነገርለት የሚገባ ሰው ነው፡፡ እኔ ሁል ጊዜ ስለ ዘከሪያ ተጽፎ ማየት እመኝ ነበር፡፡ በትርጉም እና በልዩ ልዩ የህዝብ ግንኙነት ስራዎች ከ30 አመት በላይ የሰራ ነው፡፡ እናም ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በመዝገበ-አእምሮ ሰነዱ የዘከሪያን ታሪክ በማስቀመጡ ማመስገን እወዳለሁ፡፡
አዲስ ጌታቸው ስለ ዘከሪያ
አዲስ ከዘከሪያ መሃመድ ጋር ከዜና አገልግሎት ቅጥር ጀምሮ የሚተዋወቁ ሲሆን የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥቷል። ዘከሪያ በባህሪው ሰውን ማቅረብ የሚወድ ስለነበር ማንንም በአጭር ቀን ውስጥ ጓደኛ ማድረግ የሚችል ሰው ነው። ከዚህም ባለፈ ትሁት፣ ጨዋ ፣ ደግ ፣ ተግባቢ ነው። ዘካሪያ ብዙ የተለየ ችሎታ ያለውም ጭምር ነው። ለስራ ቅርፅ እና ውበት ከይዘት ጋር አስታርቆ ልዩ የሆኑ ፅሁፎች እና ዜናዎችን የሚያመርት ጋዜጠኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በንባብ የበሰለ ሰፊ አድማስ ያለው የእውቀት ባለቤት እንደመሆኑ መጠን ከጋዜጠኛ አንፃር የበቃ የጋዜጠኝነት ችሎታ ያለው ሲሆን በትርጉም በኩል የበሰሉ ትርጉሞችን የሚሰራ ነው። ዜናዎችን ሲሰራ ከስር መሰረት ጀምሮ የሚያይ እና የሚያጣራ አውዱን ጠብቆ የሚሰራ ነው። ከዚህም ባለፈ አጀንዳ የመቅረፅ ትልቅ ችሎታ ያለው ሲሆን የትርጉም እና የፅሁፍ ችሎታም አለው። በፅሁፍ ችሎታውም የቃላት አጠቃቀም እና አመራረጥ ብቃት አለው። እንዲሁም የአርትኦት ችሎታውም የሚደነቅ ሲሆን ጠንቃቃ አርታኢ ነው።
ህይወት ፍሬስብሀት ስለ ዘከርያ
ዘከሪያ መሐመድን በአካል ያወቅሁት ሸገር ሬድዮ ጣቢያ በሚገኝበት ድልበር ያሰናዳውን የጥላሁን ገሰሰ መጽሐፍ ለጣቢያችን ሊሰጥ መጥቶ ነው፡፡ ከዚያ ቀደም በእንግሊዝኛ ይጽፋቸው የነበሩ ሥራዎቹን የማንበብ አጋጣሚ አግኝቻለሁ፡፡ ሸገር ከጥቂት ቀናት በኋላ በዜና ክፍል ውስጥ መመደቡን ስሰማ በጣም ከተደሰቱት መሀል ነበርኩ ፡፡ ከአለም አቀፍ ትንታኔ ባሻገር ልዩ ልዩ የዜና ሀሳቦችን ያካፍለን ነበር፡፡ በሂደት የዜና ክፍሉ ኤዲተር ሆኖ እኛ ወሬ ነው የምንለው በቅርበት መወያየት ጀመርን ፡፡ የወሬ ሀሳቡን በማበልጸግ ፣ ምንጮች በማከልና ከዚህ በፊት የሚያውቃቸውን ታሪኮች በማጎላመስ የወሬ ዐውድ ይፈጥርልናል፡፡
የሥራ ተነሳሽነት እንዲኖረን ጥበባዊ ጉዳዮችን እየቀላቀለ ጭምር ደስ የሚል ስሜት ይፈጥርልንም ነበር፡፡ በተለይ የውጪ ዜናዎችን በግሩም ሁኔታ ሲተነትንና ሲያቀርብ ብዙዎች ይመሰጣሉ፡፡ ዘኪ የአለቃ ባህርይ የሌለው በማገዝና ነገሮችን ቀለል አድርጎ በማሳየት ቤተሰባዊ ግንኙነትን መፍጠር የተቻለው ፍፁም ታዛዥና ቅን ኤዲተር እንደነበር ለመመስከር እችላለሁ ፡፡ በተለይም የንባብ ፍቅሩ ጥልቅና ያገኘውን ሁሉ ለማንበብ በመፈለጉ የሥራው ን ጊዜ ይሻመበት ነበር፡፡ ዘኪ ሰዎችን እንደ ባህርይና አቅማቸው የማስተናገድ ልዩ ተሰጥዖም ታድሏል፡፡ ጨዋታ ወዳድ ላዘኑ ለተቸገሩ ፈጥኖ ደራሽና አስታዋሽ ጓደኛ ነው ዘኪ፡፡ በጣም ከሚናፍቁኝ ሰዎች ዘኪ አንዱ ነው።
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላትን አቋም የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ ዘከሪያ 1980ዎቹ አጋማሽ ላይ በሀገራችን ብቅ ካሉ የመገናኛ ብዙሀን ሰዎች አንዱ ነው፡፡ በህትመት እና በኤሌክትሮኒክስ ሚድያ አቅሙን ያሳየ ነው፡፡ በእንግሊዝኛ እና በአማርኛም በመጻፍ ባለተሰጥኦ መሆኑንም ያስመሰከረ ነው፡፡ በአንድ በኩል ደግሞ የዜና ሰውም ነው፡፡ በአንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ውስጥም እስከ ኤዲተር የደረሰ በሳል ሰው ነው፡፡ 30ውን የስራ አመታት በአግባቡ ተጠቅሞበታል ማለት ይቻላል፡፡ አብረውት በኢዜአ እና በሸገር የሰሩ እንደነገሩን ዘከሪያ ስራ ወዳድነቱ የተመሰከረለት ነው፡፡ የንባብ ችሎታውም ከልጅነት የጀመረ በመሆኑ ስራው በእውቀት የታገዘ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
ዘከሪያ በርካታ የጽሑፍ ሥራዎችን የሠራ ጠንካራ የሚድያ ሰው ቢሆንም የበለጠ አቅሙን ያሳየበት ሥራ ግን በ2007 ታትሞ ለንባብ የበቃው “ጥላሁን ገሠሠ፡ የሕይወቱ ታሪክና ምሥጢር” የተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ከ1934 አንስቶ በተጻፈ የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ዘከሪያንም ብዙ ያደከመ እና ብዙ ርካታ ያገኘበትም ነው፡፡ ዘከሪያ ከ13 ዓመት በፊት ሳምሶን ፈይሣ የተባለ ሰው፣ ከ1934 ጀምሮ በወላጅ አባቱ በአቶ ፈይሣ የተጻፈን የቤተሰብ ታሪክ ሲሰጠው ተገርሞ ነበር፡፡ ምክንያቱም ታሪኩ የጥላሁን ገሠሠን መነሻ የሚያሳይ በመሆኑ፡፡
ታዲያ ዘከሪያ በዚያኑ ሰሞን ስለ ጥላሁን አንድ ነገር ለመሥራት ሐሳብ እያደረገ ባለበት ሰአት ይህ ማስታወሻ እጁ ሲገባ በነገሩ መገጣጠም ተደንቆ ነበር፡፡ ወዲያው የምርምር ሥራውን ቀጠለበት፡፡ ስለ ጥላሁን ገሠሠ ለማወቅ መረጃ ሲያገላብጥ ብዙም አርኪ የሆነ ምንጭ አላገኘም፡፡ “የእኔ መጽሐፍ ትልቅ ማጣቀሻ ይሆናል” ሲልም ሥራውን በትጋት ጀመረው፡፡ ዘከሪያ በዚህ መጽሐፍ ያገኘው እውቅና ብዙ ሥራዎችንም እንዲሠራ በር ከፍቶለታል፡፡ ከዚህ መጽሐፍ መታተም በፊትም ሥራ ያገኝ የነበረው ዘከሪያ ከ2007 በኋላ ነገሮች ብራ ሆኑለት፡፡ በእኛ አጭር ጥናት ዘከሪያ ብዙ እንዲነገርለት ጉጉት የሚያድርበት ሰው አይደለም፡፡ ይልቁንም ስራው ላይ የሙጥኝ ይላል፡፡ ነገር ግን ስለሰራው ስራ በሚገባ ያውቃል፡፡ እንደ ዘከሪያ አይነት የ1980ዎቹ ብርቆች በየቤቱ አሉ፡፡ ሊነገርላቸው ፤ የስራ ህይወታቸው ሊፈተሸላቸው የሚገባ ብቁዎች አሉ፡፡
እነዚህን ሰዎች ወደ መዝገበ-አእምሮ ላይ ማምጣት የእኛ ቀዳሚ ግብ ነው፡፡ ምክንያቱም ልምዳቸው መማሪያ ይሆናልና፡፡ በቴአትር ጥበባት ከእነ ዶክተር ተሻለ አሰፋ ፤ ከእነ በቀለ መንገሻ ፤ አቦነሽ መንግስቱ ጋር በ1984 የተመረቀው ዘከሪያ ዛሬም ትኩስ ጉልበት እንዳለው ያስታውቃል፡፡ የኢትዮጵያ እና የአለም ታሪክን ማንበብ ያስደስተዋል፡፡ በሀይማኖት እና በአለም አቀፍ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ማንበብ ርካታ ይሰጠዋል፡፡ ዘጋቢ ፊልሞችንም ሲመለከት ርካታ ይሰጠዋል፡፡ ዘከሪያ ቤተሰቡን ይወዳል፡፡ በትምህርታቸው ታታሪ የሆኑ ልጆቹን ያስጠናል፡፡ ይህም መልካም አባት ያሰኘዋል፡፡ ዘከሪያ የህይወት ተሞክሮውን እንዲያካፍል ስንጠይቀው በታላቅ ትህትና ታሪኩን እንድንሰራ ስለፈቀደልን እናመሰግናለን፡፡ በፎቶግራፍ የታጀበ ፤ መግለጫ የታከለበት የህይወት ታሪክ እንድንሰራ በር ስለከፈተልንም እናከብረዋለን፡፡ አንዳንዶች የልምድ በራቸውን መክፈት ሲገባ እርሱ ግን ወለል አድርጎ ከፍቶልናልና ለቀናነቱ አላህ መንገዱን ሁሉ የቀና ያድርግለት፡፡
እኛም እንዲህ አይነት ሰዎችን ስንሰንድ በከፍተኛ ንቃት እንሞላለን፡፡ አዲሱ ትውልድ የነቃ ትጉሀንን ይሻል፡፡ ባክዎ ታሪክዎ እንዲሰነድ በርዎን ይክፈቱ፡፡
ሀገር ማለት የሰው ታሪክ ነውና፡፡ ይህ ታሪክ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ እና በጋዜጠኛ አይናለም ሀድራ የተሰናዳ ነው፡፡ ለዚህ ስራ መሳካት የሁል ጊዜም ወዳጃችን ሁሴን ከድር ላደረገው ትብብር ምስጋናችን ጥልቅ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበት በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ እና በዊኪፒዲያ ላይ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ ነሀሴ 15 2015 በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች ተቀመጠ፡፡