ዘነበ ወላ ወጋ

ዘነበ ወላ ወጋ

የማንዘነጋው  ብርቱ  ደራሲና  አንባቢ ዘነበ ወላ 

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸውን ሰዎች ጠቁሙን ፤ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪካቸዎን እናወጣለን፡፡

በ tewedajemedia@gmail.com ጥቆማዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በስነ-ጽሁፍና ድርሰት ዘርፍ  ታሪኩን የምንዘክርለት ሰው ዘነበ ወላ  የ 6 መጽሀፎች ደራሲና የማንበብ ባህል ለመላ ኢትዮጵያዊ አርአያ የሚሆን ሰው ነው፡፡ ዘነበ ለትውልድ ካበረከተው  አንጻር ብዙ ሊባልለት ቢገባም ለዛሬ ዘነበን እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

ትውልድ

ዘነበ ወላ  ፤የተወለደው አዲስ አበባ እንብርት ላይ በቅዱስ ቂርቆስ ደብር ነው ። እናቱ ወይዘሮ ወርቅነሽ ባላ እንደነገሩት ”  የሦስት አመት ልጅ ሆኖ ነበር የታህሳስ ግርግር የተነሳው ” ብለውታል ። ይህንን ስናሰላው በ1950ዓ.ም ጥር 6 ቀን ሆነ።

ከልጅነት -ምጽዋ 

ዘነበ ልጅነቱን ሲተርክ እንደዚሁም ምጽዋ ባህር ሀይል ያገለገለበትን ዘመን ሲያስታውስ ብዙ ትዝታዎች ይመጡበታል፡፡  ከልጅነቱ ጀምሮ ወጉን እንዲህ ይጀምርልናል ‹‹……. በወቅቱ  ከአራተኛ ክፍለ ጦር ተኩሱ ሲጧጧፍ በህጻን ልብ በጣም ደንግጨ ” ወላዬ የት ልግባ ! ” ብዬ እንደጮህኩ  እማዬ በኋላ ነግራኛለች ። ተማጽኖዬ በጣም ያስጨነቀው ወላጅ አባቴ አቶ ወላ ወጋ ቀልጠፍ ብሎ ሸማ በሚሠራበት ጉድጓድ ውስጥ ከተተኝና ከላይ  የሚቀመጥበትን አጎዛ  ከልሎኝ እላዬ ላይ ተኛ ። ምሽግ ሆነኝ ማለት ነው ።

ዓመታት እንዳለፉ  ሀሁን የተማርኩት  በቅዱስ ቂርቆስ ደብር ውስጥ  ነው ። ከፊደል እስከ ወንጌል ከተማርኩ  በኋላም፤  ከሳቴ ብርሃን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቼ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቀኩ ። መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃውንፊታውራሪ  ላቃ እድገት  ፣ ከዚያም ሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ት /ቤት ዘልቄ  ቀይ ባህር ጠራኝ።

በ1975ዓ.ም በኢትዮጵያ ባህር ኃይል ተቀጥሬ ወደ ኤርትራ ክፍለ ሀገር  ዘለኩ  ። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያውን ፈተናን  የተፈተንኩት አስመራ ከተማ ውስጥ  ነው።ለስምንት ወራት መሠረታዊ የመርከበኝነት ኮርስ ከጓደኞቼ ጋር ተሰጠኝ ። ባህር እና የብስ ላይ ለአራት አመታት ከሰራሁ በኋላ ለሙያ ስልጠና አስመራ ተመልሼ ማሰልጠኛ ማእከሉ ውስጥ በተሰጠኝ ትምህርት  ‘በሰፕላይ ማኔጅመት ከተቋሙ ተመርቄ፤ ለተጨማሪ ሥራ ምጽዋ ባህር ኃይል መደብ ተመልሼ አገልግሎት መስጠት ጀመርኩ ።›› በማለት ዘነበ ለዛ ባለው አንደበቱ ያጫውተናል፡፡

ዘነበ እና ድርሰቶቹ 

ዘነበ የሕይወቴ ‘ ዩኒቨርስቲ ‘ የሚለው ቀይ ባህር ጋር የተገናኘው በእንዲህ መልኩ ነበር ። ስለ መርከብ ፣ መርከበኛና ባህር  ‘ከሊቅ አፍም ከመጣፍም ‘ያገኘውን እየተጠበበ ለጦር ኃይሎች የሬዲዮ ፕሮግራም መጻፍ ጀመረ ።ይህ የሬዲዮ ፕሮግራም አያሌ ወዳጆች አፈራለት ፣ ከእነዚህ ወዳጆቹ መካከል አንዱ ከሆነው አቶ ወልደ ገብርኤል አባተ ጋር ሕይወት አገናኝታቸው ሲያወጉ ኮከባቸው ገጥማ ” አንድ መጽሐፍ ጻፍና እኔ ላሳትምልህ ፤ መጽሐፉን ጽፈህ እስከምትጨርስ ባህር ኃይል የሚከፍልህን ደሞዝ እኔ እከፍልሃለሁ ” አለው ። ወቅቱ 1983ዓ.ም ስለነበር ዘነበ ስራ ፈት ነበር ። ዘነበ በዚህ ሁኔታ ተገረመ፡፡ በደስታ መጠበብ ጀመረ ።

ዘነበ ያን የደስታ ባህር አይዘነጋውም፡፡ ዛሬ መለስ ብሎ ሲተርከው ብዙ ሀሳቦች ወደ ውስጡ ይብላሉ ነበር፡፡ አንድ ብሎ የተጀመረው የመጽሀፍ ስራ እነሆ ዛሬ ከፍ ባለ ደረጃ መቀጠሉን ዘነበ በእንዲህ መልኩ ይነግረናል:

  1.  ‹‹ ‘ሕይወት በባህር ውስጥ’ ጻፍኳት ።መጽሐፋ ከትንሽ ዓሳዎች እስከ ጉዙፉ ዓሳነባሪን ህይወት የምታወሳ ነች ።የመጀመሪያው ህትመት በ1985 ዓ.ም  ለህትመት በቃች ፤ ድጋሚ በ2011ዓ.ም አዳዲስ መረጃዎች ታክሎባት ዳብራ ታትማለች። በ1990ዎቹ የአዲ አበባ ከተማ አስተዳደር የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ እንድትሆን አንዷ ርእስ ተካታ ነበር ።
  1. ሰንበትበት ብዬ የገሀዱ ዓለም መምህሬ እና ጓደኛዬ የጋሼ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ሕይወት እና የኪነጥበብ ክህሎት ” ማስታወሻ “ጻፍኩ ። በ1993 ዓ.ም ለህትመት በቃች ፤ ከእርሱ እረፍት በኋላ የተቀሩት መረጃዎች ተሟልተው በ 2006 ዓ.ም ዳግም ለህትመት በቃች ። በአጠቃላይ ስድስት ጊዜ ለህትመት በቅታለች ።
  1. ‘ ልጅነት ‘ የልቦለድ ጥበብ በመጠቀም የ1960ዎቹ ትውልድ ህይወት የሚያሳይ ሥራ ነው ።በ2000ዓ.ም የመጀመሪያ ህትመት ወጥታ እስካሁን 12 ጊዜ ታትማለች ።
  1. መልህቅ ” 2010ዓ.ም ለህትመት በቅታለች፡፡ መጽሐፋ የምታወሳው የጦር መርከበኞችን ጀብዱና የወቅቱን የኤርትራን ጉዳይ የምትተርክ  ነች ። ስድስት ጊዜ በ30000 ሺህ ኮፒ ተደራሲያን እጅ ደርሳለች ።
  1. ” የምድራችን ጀግና ”  ስለስመጥሩ የሳይንቲስት ስለ ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር የተጻፈ መጽሐፍ ነው ።ይህ መጽሐፍ ሳይንቲስቱ ከልደት እስከ አዛውንትነት እድሜው ስለራሱ የሚያወሳው ነው።ዘርፉ ግለ-ታሪክን የሚወክል የአጻጻፍ ስልትን ተከትዬ ነው የጻፍኩት ።
  1. “ኢትዮጲያዊው ሳይንቲስት” የሚለው መጽሐፍ ከላይ የተጠቀሰውን የህይወት ታሪኩን ጨምሮ ፤ ሳይንቲስቱ የወለዳቸው እና ያሳደጋቸው ልጆች ፤አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያሥተማራቸው ተማሪዎቹን ( አሁን ሲኒየር ፕሮፌሰር ናቸው ) አክሎ የአስመራ ዩንቨርስቲ ተማሪዎቹን ጨምሮ የአስራ ሰባት ሰዎችን ቃለ ምልልስአካቷል።  በተጨማሪ ከሙያው ውጪ ያጠናቸው ጥናታዊ ጹሁፎች ፣ በአገር ውስጥም ሆነ ባህር ማዶ ያደረጋቸው የተመረጡ ንግግሮች ያካተተ ነው ። ይህ ዘርፍ ( እንደ አቅሚቲ ) ” ስኮላርስ ባዮግራፊ ” የሚሉትን ዘርፍ ተጠቅሜ የጻፍኩት ነው ።›› በማለት ስለ ድርሰቶቹ ነግሮናል፡፡

ተጨማሪ የዘነበ ጥረት 

ዘነበ ባለፉት 32 ዓመታት  በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ተቀላቅሎ  በርካታ መጣጥፎችን ፣ጋዜጦች ላይ ሲጽፍ ፤ እንዲሁም አያሌ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን በበርካታ የሬዲዮ ጣቢያዎች ሰርቷል ። በጄቲቪ ተወዳጅ ፕሮግራሞችን “ከፀሐይ በታች “በተባለ ስያሜ ሲያቀርብ ቆይቷል ። በአሁኑ ሰአትም አዲሱ የፈጠራ ሥራው ‘ መልህቅ 2’   ላይ  እየተጠበበ ሲሆን ፤  ቀደም ብሎ በየጋዜጣው ላይ የጻፋቸው መጣጥፎች ፣ በስነ ጽሁፍ ላይ ያደረጋቸው ቃለ-ምልልሶች ፤ አዲስ የጻፋቸው ወጎች ተሰባስበው ሊጠረዙ በመዘጋጀት ላይ ናቸው ።

 ዘነበ ‹‹ባለፉት 45ዓመታት በትጋት መጻሕፍት ገዝቼ አንብቤአለሁ›› ይላል፡፡  በዚህ ትጋቱ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ራሱን በራሱ በማስተማር ምንጊዜም እንደሚተጋ ለራሱ ቃል ገብቷል ።  አንድ ጉዳይ ይረባል ብሎ ካሰበ ይጽፈዋል ።ሲጽፍ የመጣለትን ሁሉ ሳይሆን ከምርጡ ምርጥ ላይ ያተኩራል ።

በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ተቀላቅሎ ከወይዘሮ ፀሐይ በላቸው ጋር በመስከረም ወር በ30ኛው ቀን   በ1991ዓ.ም በመሰረተው ትዳር  ከሁለት አስርት አመታት በላይ  በቆየው  ትዳር የአንድ ሴት ፣ የአንድ ወንድ ልጅ  ወላጆች ሆነዋል ።

ማጠቃለያ

ዘነበ ወላ በአንባቢነቱ ብቻ ሳይሆን በጥሩ አድማጭነቱ ብዙዎች ይመሰክሩለታል፡፡  ያወቀውን ደግሞ በጽሁፍ ለማካፈል  የተቻለውን ያደርጋል፡፡ ዘነበ ከደራሲነቱ ባሻገር አንደበተ-ርቱእ ተናጋሪም ነው፡፡ በእርሱ ንግግር ብዙዎች ይነቃቃሉ -ይታነጻሉ፡፡  ዘነበ “ከፀሐይ በታች  በተሰኘው የቲቪና የሬድዮ መሰናዶ ብዙ ሀሳቦችን አንስቷል፡፡ በዚህም የንባብ ክህሎት እንዲዳብር የተቻለውን አድርጓል፡፡ አንባቢ የሆነ ሰው የቲቪ እና የሬድዮ መሰናዶ ሲያቀርብ ምን አይነት ሀሳቦች እንደሚይዝ ከዘነበ አይተናል፡፡ ዘነበ ዛሬም 63 አመቱን እንደያዘ ይጽፋል፡፡ ይጠበባል፡፡ ደግሞ መጽሀፍን ከእጁ ሳይለይ  ከንባብ ባህር ውስጥ ይሰምጣል፡፡ ይህ ዘነበን ልዩ ያደርገዋል፡፡  ለመጪው  ትውልድ አንድ የሚቀመጥ ቅርስ ያስቀመጠ በመሆኑ ይደነቃል፡፡ ይህን የዘነበን የዊኪፒዲያ ታሪክ ባዘጋጁ ሰዎች እምነት ዘነበ  ሩቅ አስቦ እየሰራ ያለ የድርሰት ሰው ነው፡፡ በመሆኑ የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲያከብረው ጥልቅ እና ሰፊ ከሆነው ህይወት መጥነን ለታሪክ እንዲቀመጥ አድርገናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *