ዓለማየሁ ገብረህይወት

ዓለማየሁ ገብረህይወት

ከአባይ ማዶ ወደ ባህር ማዶ የኮበለለው ጥበበኛ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡

ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ “የ200 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል የቴአትር ባለሙያ ዓለማየሁ ገብረህይወት አንዱ ነው፡፡ እርሱም ከ40 አመት ቀደም ብሎ በቴአትር ጥበባት ተመርቆ በልዩ ልዩ የስራ ሃላፊነቶችና በድርሰት እና ዝግጅት ስራዎች ላይ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፡፡ መኖሪያውን በባህር ማዶ ያደረገው ዓለማየሁ ሀገሩ በሚመጣበት ጊዜ ለኪነጥበብ እድገት ይጠቅማሉ ብሎ ያመናቸውን ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ የህይወት ታሪኩን እዝራ እጅጉ እና አማረ ደገፋው እንደሚከተለው አጠናክረውታል፡፡

ትውልድ ልጅነት

የ1955 መስከረም ጠብቶ አስራ ዘጠነኛው ቀን ሲደርስ ጎንደር ከተማ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ጓሮ ልደቱ ለዓለማየሁ ገ/ሕይወት ሆነ። ህፃኑ ዓለማየሁ መዳህና ድክድኩን አልፎ ቀለም የመቁጠር ቁመና ላይ ሲደርስ ዘመናዊውንም የቄስ ትምህርቱንም ጎን ለጎን ማስኬድ የሚችል ቀለሜ ሆነ።
3ኛ ክፍል እስኪደርስ ጧት ጧት ፃድቁ ዮሐንስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርቱን እየተማረ ከሰዓት ደግሞ የቄስ ትምህርቱን ዘልቆ ዳዊት ደግሟል።

ወደ ንባብ ጉዞ

ንቁ እና ቀልጣፋው ዓለማየሁ ስለጉብዝናው መምህሮቹ ባለ ቀለም ጠመኔዎችን (ቾክ) ይሸልሙት እንደነበር ያስታውሳል። ይህ የለጋ እድሜ ቅልጥፍናው ወደ ንባብ እንዲሻገር አባቱ አቶ ገ/ሕይወት እንግዳ ሚናቸው ትልቅ ነበር። መጻሕፍት በዙሪያው እንዲገኙ ጥረዋል፤ የዘመኑ የህትመት ውጤቶችንም እንዲሁ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው ጎንደር ከተማ ባለው በእውቁ የፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቀጠለ። የፋሲለደስ መምህሮቹ የአባቱን ጥረት ቀጥለውለት የተለያዩ መጻሕፍትን በተማሪዎች ፊት እንዲያነብ እና ራሱም የተለያዩ ድርሰቶችን እንዲጽፍ አበረታተውታል።

12ኛ ክፍል

በ1974 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማትሪክ ሲወስድ ህልሙ የነበረው ዓለማያ እርሻ ኮሌጅን ለመቀላቀል ነበር። እዚያው ጎንደር የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያለ አንድ ቃለ-ምልልስ በሬዲዮ ሰምቶ ነበር። ቃለ- መጠይቁ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለተሰራ “እንባ አይሆን መፍትሔ” የተባለ ቴአትር ነበር። የልጅነት የማወቅ ጉጉቱ አብሮት አድጎ ኖሮ በጋውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲማር ቆይቶ ክረምቱን ወደ ጎንደር የዘለቀ ወዳጁን ጌታቸው መንግስቴን አጥብቆ ጠየቀው፤ ጌታቸውም እነማን እንዴት ያሉ ቴአትር እንደሚሰሩ አብራርቶ ነገረው።

ዩኒቨርሲቲ

በ1975 ዓ.ም ምደባ ይፋ ሲሆን እንደሃሳቡ ዓለማያ ሳይሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደረሰው። አዲስ አበባ ደርሶ የዩኒቨርሲቲውን እንቅስቃሴ ሲያይ፣ አስቀድሞ ከወዳጁ የሰማውን የቴአትር ገድል ሲያስታውስ… የቴአትር ትምህርት ክፍልን ለመቀላቀል ወሰነ። ውሳኔውም የአሰፋ ወርቁ፣ የጌታቸው ማንጉዳይ፣ የአስፋው ወ/ገብርኤል፣ የዘካርያስ ኃይለማርያም እና የሌሎች ጉምቱዎች የክፍል ተጋሪ ጓደኛ እንዲሆን አደረገው። በቴአትር ትምህርት ቤት ቆይታው ትርጉም፣ ትወና እና ማስተባበርን ጨምሮ በርካታ ስራዎችን እንደሰራ ያስታውሳል። ከክፍል ጓደኞቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ከታላቆቹም ከታናሾቹም ጋር እየተቀናጁ ቴአትሮችን ይጽፉና ይመደርኩ እንደነበር ይናገራል። ለዚህ አባባሉ ምስክር ዛሬም ድረስ የማይረሳውን የጀማነሽንና የኤልሳቤጥን የመጀመሪያ መድረክ ስራ ያስታውሳል። ዓለማየሁና ጓደኞቹ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሆነው መስራት ላሰቡት ቴአትር ሁለት ሴት ገፀ ባህሪያት ያስፈልጓቸዋል። ክፍላቸው ውስጥ ለመድሃኒት እንኳ አንዲትም ሴት ባለመኖሯ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የነበሩት ጀማነሽ ሰለሞን እና ኤልሳቤጥ መላኩን ጋብዘው መድረኩን ሞሉት። ለሁለቱም እንስቶች ይህ መድረክ የመጀመሪያቸው እንደነበር ዓለማየሁ ይናገራል።

የመመረቂያ ጽሑፉን ከመምህሩ ከደበበ ሰይፉ ጋር ተማክሮ ጎንደር ከተማ የፋሲል ግቢ ውስጥ በሚገኝ ጥንታዊው “የአፄ ዳዊት የቴአትር አዳራሽ” ላይ ለማድረግ አስቦ የነበረ ቢሆንም… መረጃዎች እንደልብ ባለመገኘታቸው የልቡን ሊሰራ አልቻለም። ይልቁንም በፋሲለደስ ኪነት አመሰራረት እና የቴአትር እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ የመመረቂያ ጽሑፍ አቅርቦ በ1978 ዓ.ም ተመረቀ።

ወደ ስራ አለም

ከምረቃ በኋላ አስቀድሞ ይደረግ የነበረው በባህል ሚኒስቴር በኩል ተመራቂዎችን ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች መመደብ ነበር። ዓለማየሁ ሥራ የጀመረበት ዓመት ግን የዶጋሊ ድል 100ኛ ዓመት የሚከበርበት በመሆኑ ምደባው ለተወሰነ ጊዜ ዘግይቶ ሁሉም ተመራቂዎች በባህል ሚኒስቴር ስር ሁነው እንዲሰሩ ሆነ። ስራው በሀገሪቱ የነበሩ የተለያዩ ጀግኖችን ታሪክ በማጥናት ለቴአትር ጸሐፍት መነሻ የሚሆን ጽሑፍ ማቅረብ ነበር።

ዓለማየሁ ስለበላይ ዘለቀ ምርምር እንዲያደርግ ተመድቦ በርካታ ጥናቶችን አገላብጦ ያዘጋጀውን ጽሑፍ የሚቀበለው ቢያጣ ‘ለምን ራሴው አልጽፍም’ ብሎ አሰበ። አስቦም “አባ ኮስትር” የሚል የሬዲዮ ድራማ ጻፈ። ሥራውም ለሕዝብ ተላለፈለት፡፡ የዶጋሊ ድል ክብረ በዓል ሲጠናቀቅ ሌሎች ጓደኞቹ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲመደቡ እርሱና ኤፍሬም በቀለ የተባለ የክፍል ጓደኛው እዚያው ባህል ሚኒስቴር ውስጥ በሥነ ጥበባትና ቴያትር መምሪያ የቴያትር ገምጋሚ ሆነው ስራቸውን ቀጠሉ። ከግምገማው ጎን ለጎን ደግሞ የራሱን ስራዎች ይጽፍ ነበር።

በሬዲዮ ድራማ የጀመረውን ስራ በመድረክም በቴሌቪዥንም በርትቶ ቀጠለ፤ “የገንፎ ተራራ” የተሰኘ አበበ ከበደ፣ ኩራባቸው ደነቀና ጀማነሽ ሰለሞን የተወኑበትን የሕፃናት ቴአትር ጻፈ፤ ጌትነት እንየው ያዘጋጀውን “ፈላስፋዋ” የህፃናት ቴአትርም እንዲሁ አበርክቷል። ፍሰሃ በላይ ይማም እና እንግዳዘር ነጋ የተወኑበት “ቃለ-መጠይቅ” የሚል የሬዲዮ ድራማም አየር ላይ አውሏል። ለመሰረተ ትምህርት 10ኛ ዓመት ክብረ በዓል ተወዳድሮ ያሸነፈበት “አምሳያ ልጅ” የተሰኘ ቴአትርም በመድረክና በቴሌቪዥን ታይቶለታል። ሮቢን ዋይት የተባለ የቢቢሲ ጋዜጠኛ የናይጄሪያን የእርስ በእርስ ጦርነት መሰረት አድርጎ የጻፈውን “The Soldiers” የተባለ የራዲዮ ድራማ “ወቴዎቹ” ብሎ ተርጉሞታል፡፡ ተወዳድሮም አሸንፎበታል። ለሕዝብም ቀርቦለታል፡፡

ውለታ ያሰረው፣ ብረትና ሙግት፣ ውርክብ፣ ስጦታ፣ መንታ መንገድ፣ የአባ ወራ ጉዞ፣ “ምን ምን ስራዎችን ሰርተህ ነበር?” ብለን ድንገት ስንጠይቀው ያስታወሳቸው ስራዎቹ ናቸው እንጂ ለሕዝብ ያልቀረቡ ሌሎች ሥራዎች እንዳሉት ራሱም ይናገራል።

የስራ መሪነት

ከእነዚህ ሁሉ የመሃል አገር አበርክቶው በኋላ አለማየሁ አባይ በረሃን ተሻግሮ ባህርዳር ከተመ። የመጀመሪያውን አንድ ዓመት ተኩል የአማራ ክልል ባህል መምሪያ ሃላፊ በመሆን ቀጣዮቹን ስድስት ዓመታት ደግሞ የክልሉ የባህል፣ ቱሪዝምና ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ በመሆን ዘመን የዘለቀ አበርክቶ እና የደመቀ አሻራውን አኑሯል። አበርክቶዎቹ ከሁለት አስርታት በላይ እንኳ ሁኗቸው ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ ስራዎች ናቸው። የክልሉ ሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች የሚሳተፉባቸው የሥነ ጽሑፍና የቴአትር ውድድሮችንና ፌስቲቫሎችን በቢሮው በኩል ያደርግ ነበር። በሕፃናት፣ በልጆችና በአዋቂዎች ተከፍሎ የሚደረገው የስነ-ጽሑፍ ውድድር አሸናፊዎች ከሚያገኙት ሽልማት ባሻገር ሥራዎቻቸው “መቅረዝ” በተሰኘች መጽሔት ታትመው ለህዝብ ይደርሱላቸው ነበር።

ይህች መጽሔት የተወዳዳሪዎችን ስራ ለህዝብ ከማድረስ ባለፈ ለበርካታ ተመራማሪዎች እንደ መረጃ ምንጭነት አገልግላለች። በመቀጠል ዛሬም ድረስ (ከ25 ዓመታት በኋላ) ክልሉ የሚኮራበትን የሙሉዓለም የባህል ማዕከልን በ11.8 ሚሊያን ብር አስገንብቷል። ኤሲ የተገጠመለት፣ በወቅቱ በሃገሪቱ ከነበረው ትልቁ ቴአትር ቤት የተሻለ ጄኔሬተር ያለው ግዙፍና ማራኪ የባህል ማዕከል ነው ሙሉዓለም። ለግንባታው ብቻ ሳይሆን ለጥበቡም አብዝቶ የተጨነቀው ዓለማየሁ ሕፃናቱንም አዋቂውንም የሚያዝናኑ ፊልምና ቴአትሮችን ያለመዛነፍ እንዲቀርቡ ለፍቷል። ራሱ የባህል ቢሮው ከሚሰራቸው ስራዎች በተጨማሪ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሙያተኞችን በመጋበዝና ቢሮክራሲውን በማቅለል፣ ለስራ ጉዳይ ባህር ሲሻገር ፊልሞችን ሰብስቦ በማምጣት፣ የተለያዩ ጥበባዊ ውይይቶችን በማካሄድ ማዕከሉ እንዲጠናከር አድርጓል።

ከእነዚህ ሁሉ የመሃል አገር አበርክቶው በኋላ አለማየሁ አባይ በረሃን ተሻግሮ ባህርዳር ከተመ። የመጀመሪያውን አንድ ዓመት ተኩል የአማራ ክልል ባህል መምሪያ ሃላፊ በመሆን ቀጣዮቹን ስድስት ዓመታት ደግሞ የክልሉ የባህል፣ ቱሪዝምና ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ በመሆን ዘመን የዘለቀ አበርክቶ እና የደመቀ አሻራውን አኑሯል። አበርክቶዎቹ ከሁለት አስርታት በላይ እንኳ ሁኗቸው ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ ስራዎች ናቸው። የክልሉ ሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች የሚሳተፉባቸው የሥነ ጽሑፍና የቴአትር ውድድሮችንና ፌስቲቫሎችን በቢሮው በኩል ያደርግ ነበር። በሕፃናት፣ በልጆችና በአዋቂዎች ተከፍሎ የሚደረገው የስነ-ጽሑፍ ውድድር አሸናፊዎች ከሚያገኙት ሽልማት ባሻገር ሥራዎቻቸው “መቅረዝ” በተሰኘች መጽሔት ታትመው ለህዝብ ይደርሱላቸው ነበር።

ይህች መጽሔት የተወዳዳሪዎችን ስራ ለህዝብ ከማድረስ ባለፈ ለበርካታ ተመራማሪዎች እንደ መረጃ ምንጭነት አገልግላለች። በመቀጠል ዛሬም ድረስ (ከ25 ዓመታት በኋላ) ክልሉ የሚኮራበትን የሙሉዓለም የባህል ማዕከልን በ11.8 ሚሊያን ብር አስገንብቷል። ኤሲ የተገጠመለት፣ በወቅቱ በሃገሪቱ ከነበረው ትልቁ ቴአትር ቤት የተሻለ ጄኔሬተር ያለው ግዙፍና ማራኪ የባህል ማዕከል ነው ሙሉዓለም። ለግንባታው ብቻ ሳይሆን ለጥበቡም አብዝቶ የተጨነቀው ዓለማየሁ ሕፃናቱንም አዋቂውንም የሚያዝናኑ ፊልምና ቴአትሮችን ያለመዛነፍ እንዲቀርቡ ለፍቷል። ራሱ የባህል ቢሮው ከሚሰራቸው ስራዎች በተጨማሪ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሙያተኞችን በመጋበዝና ቢሮክራሲውን በማቅለል፣ ለስራ ጉዳይ ባህር ሲሻገር ፊልሞችን ሰብስቦ በማምጣት፣ የተለያዩ ጥበባዊ ውይይቶችን በማካሄድ ማዕከሉ እንዲጠናከር አድርጓል።

ከነዚህ በተጨማሪ የቢሮ ኃላፊ ሁኖ ባገለገለባቸው ዓመታት በተለያዩ የክልሉ ቦታዎች ቤተ መጻሕፍትን በማቋቋም፣ የአፄ ፋሲል ግንብን በማሳደስ፣ የላሊበላንና የጣና ገዳማትንና ቤተክርስቲያናትን በመንከባከብ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል። የቀድሞው የአማራ መገናኛ ብዙኃን የአሁኑ አሚኮ እንዲጠናከርም ከክልሉና ከስዊድን መንግሥት ጋር ተባብረው መሥራታቸውን ዛሬም ያስታውሳል።

ጉዞ ወደ አሜሪካ

ከአባይ ጓዳ ሁኖ ለጥበብ ሲለፋ የቆየው ጥበበኛ ልፋቱን ወደ ራሱ በማዞር ዳግም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ የድህረ ምረቃ ትምህርቱን በእንግሊዝኛ ሥነጽሑፍ መስክ መማር ጀመረ። ለሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከቆየ በኋላ በዲያስፖራው ላይ የሚያተኩረውን የመመረቂያ ጽሑፍ ለመጻፍ ወደ አሜሪካ አቀና። ሆኖም ለአምስት ወራት ያህል ካቅማማ በኋላ ወደ ሀገር ላለመመለስ ወስኖ ኑሮውን በዚያው በአሜሪካ አደረገ። ባህር ተሻግሮ እንኳ ሊለቀው ያልቻለውን ጥበብ ወደ ጣይቱ የባህል ማዕከል ብቅ እያለ ያስታግሰው ያዘ። በጣይቱ የተለያዩ ወርክሾፖችን ያዘጋጃል፣ የግጥም ምሽቶች ላይ ይሳተፋል፣ የመጽሐፍ ዳሰሳ ያደርጋል። ከፍ ሲልም የማዕከሉ የቦርድ አባል ሁኗል።

ታዛ መጽሄት

በአንድ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እየሠራ እያለ ወደ ኢትዮጵያ ተመድቦ ሲመጣም ከመኩሪያ መካሻ እና እቁባይ በርኸ ጋር በመሆን ወርኃዊዋን “ታዛ” መጽሔት መሰረተ። መጽሔቷ በ48 እትሞቿ አንባቢያን ዘንድ ደርሳለች። ዓለማየሁ ልክ እንደቴአትሩ ሁሉ ህትመቱም ላይ አሻራው አለበት፤ በ1999 የታተመች “እታለም” የምትል የግጥም መድብል አለችው፣ “በፍቅር መንገድ” የተሰኘ ልቦለድም ከሁለት ዓመት በፊት አሳትሟል፣ በተስፋዬ ለማ የተጻፈውንና በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው መጽሐፍም አርታኢ ነው። ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገው ጥበበኛ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን አሁንም በተለያዩ ስራዎቹ ወደ ተደራስያኑ ለመድረስ እየጣረ እንደሆነ ነግሮናል።

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ዓለማየሁ ገብረህይወት፣ ባለፉት 37 አመታት በሀገራችን የቴአትር እድገት እንዲመጣ ከለፉት መካከል ተጠቃሹ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ካጠናቀቀበት ከ1978 ጀምሮ ከቴአትር ገምጋሚነት አንስቶ እስከ ደራሲነት የተቃረበ ባለሙያ ነው፡፡ ስነ-ጽሁፍ እና ቴአትር በመጠ ኑም ቢሆን ትኩረት አግኝቷል በሚባልበት በደርግ ዘመን እንደ ዓለማየሁ አይነት ባለሙያዎች ጥበብን ከእውቀት አንጻር ለማስኬድ የተቻላቸውን አድርገዋል፡፡ በተለይ በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው ሙሉአለም የባህል አዳራሽ አሁን ላለበት የእድገት ደረጃ እንዲደርስ የአለማየሁ ሚና የጎላ ነበር፡፡ በድርሰት እና በዝግጅትም ያለውን እያዋጣ ሲደክም የኖረ ባለሙያ ነው፡፡ ባህር ማዶም ከሄደ በኋላ ከጥበቡ አለም መራቅ ስላልሆነለት በጣይቱ የባህል ማእከል ሙያዊ አደራውን ሲወጣ የኖረ ነው፡፡ አለማየሁ የቀደሙ የቴአትር ጥበባት ተማሪዎችንም ጥንቅቅ አድርጎ በማወቅ መረጃ ለሚፈልጉ ሰዎች ያለ አንዳች ስስት በመለገስ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም እጁ ላይ ለሰዎች የሚጠቅም ሰነድ ካለ ለመስጠት አይሰስትም፡፡ ለዚህ መዝገበ-አእምሮ አዘጋጆችም ይህን ቸርነቱን አሳይቷል፡፡ እንዲህ አይነት ባለሙያዎች ታሪካቸው በዚህ መልክ ቢሰነድ ለምርምር መነሻ የሚሆን ግብአት ይገኝባቸዋል፡፡ በምስልና በበቂ አስረጂ ሰነዶች የታጀበው ይህ የህይወት ታሪክ 37 አመት ወደ ኋላ ተጉዘን እንድናስብ የሚያደርገን ነው፡፡ በመሆኑ አለማየሁን እያመሰገንን ታሪኩን ለትውልድ በዚህ መልኩ አስቀምጠናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *