ወ/ሮ ብርሃኔ አስፋው

ወ/ሮ ብርሃኔ አስፋው

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለሀገር የሰሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ በማስቀመጥ ላይ እንደሆነ ይታወቃል ። በአሁኑ ሰዓት የ 84 ዓመት እናት የሆኑት ወይዘሮ ብርሀኔ አስፋው ከእነዚህ ለሀገራችን ከሠሩ አገር ወዳዶች አንዷ ናቸው ። በሀገራችን ሴቶች በዲግሪ ሲመረቁ ከመጀመሪያዋ አንዷ የሆኑት ወይዘሮ ብርሀኔ 3 ልጆቻቸውን ለቁምነገር በማብቃት ስማቸው በክብር ይነሳል ። ዕዝራ እጅጉ የህይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው አጠናክሮታል ።

ወ/ሮ ብርሃኔ በ1931 ዓ.ም ውልደታቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ያደጉትም ከእናታቸው እና ከወንድ አያታቸው ጋር እንደነበር እና አሁን ላላቸው የማንነት መሰረት የገነቡዋቸው

እነሱ እንደሆኑ ይናገራሉ። እናታቸው በግብረገብ የታነፁ እንዲሆኑ እንዳደረጓቸው እና በኢትዮጵያዊያን ባህል እና ወግ ውስጥ በኖረ ቤተሰብ ውስጥ እንዳደጉ አማርኛ ፊደላትንም ሆነ ሃይማኖታዊ ፅሁፎችን ያስተማሩዋቸው የመጀመሪያ መምህሮቻቸው እናታቸው እንደሆኑ ያስታውሳሉ። እናታቸው እና አያታቸው ያደጉት በባህላዊ መንገድ ቢሆንም ለዘመናዊ ትምህርት ፅኑ እምነት ነበራቸው። የመጀመሪያ ኑሮዋቸው ጎንደር እና ደሴ በመጨረሻም ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ ይናገራሉ።

ወ/ሮ ብርሃኔ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ጎንደር በሚገኘው እቴጌ መነን እና በደሴ ወ/ሮ ስህን ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። በአካባቢያቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ሁለት ሴት ተማሪዎች አንዷ ነበሩ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ ገቡ። በወቅቱ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር በነበሩት ገናናዋ ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ ግፊት እና እገዛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው አራት መቶ ተማሪዎች በነበሩት በያኔው በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዮንቨርስቲ በጣት ከሚቆጠሩ ሴት ተማሪዎች አንዷ በመሆን በ1954 ዓ.ም ተመረቁ። በስራው ዓለም ከገቡም በኋላ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአራት ዓመት አስተምረዋል ።በአካል ጉዳተኞች ማገገሚያ ማዕከል ውስጥም ለአንድ ዓመት ሰርተዋል።በኋላም በኢትዮጵያ ሴቶች በጎ አድራጎት ማህበር ውስጥ መስራት ጀመሩ።

በ1962 ዓ.ም በጄኔቫ ሲዊዘርላንድ ትምህርታቸውን ቀጠሉ። በልማታዊ ጥናቶች ዲፕሎማ ያላቸው ሲሆን በአለም አቀፍ ጉዳዮች ደግሞ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል።ወ/ሮ ብርሃኔ ከልጅነታቸው አንስቶ ፍትህ ሲጓደል እያዩ የሚታገሱ ሰው እንዳልነበሩ እና ትክክል ያልመሰላቸውን ነገር የመጋፈጥ የልጅነት ልማድ አላቸው። በኋላም ላይ በኢትዮጵያ ያሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመቃወም መሳተፍ ጀመሩ። ይህን ተግባራቸውን በኢትዮጵያ ሴቶች በጎ አድራጎት ማህበር ውስጥ እያሉ መጀመራቸውን ያወሳሉ።

ገና በጅማሬያቸው ወቅት ከድጋፍ ይልቅ ተቃውሞ በአለም አቀፍም ሆነ በሃገር አቀፍ በብዙሃኑ ህብረተሰብ ዘንድ ገጥሞአቸው እንደነበር እንዲሁም በብዙዎች ዘንድ ባህል ታፈርሳለች በሚል በጥላቻ ይመለከቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመቃወም ኢንተር አፍሪካን ኮሚቴን በመሩበት 27 ዓመታት በተለይ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጎጂ ልማድ ደጋግመው ይናገሩ ነበር።ወ/ሮ ብርሃኔ ’’ ሰዎች ሲያዩኝ የግርዛቱዋ ሴትዮ መጣች ደግሞ ልትነዘንዘን ነው? ይሉኛል የኔ አቋም ደግሞ ስለጉዳዮ እንዳላወራ ከፈለጋችሁ ድርጊቱን ለማስቆም አንድ ነገር አድርጉ ይሉ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዶችን በመቃወም የሚንቀሳቀስ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በመቀላቀል በአስተባባሪነት ስራ ጀመሩ። የመጀመሪያ እርምጃቸው በመላው አፍሪካ በመዘዋወር ችግሩን ማጥናት መጀመራቸውን ይናገራሉ። ከጥናቱም በኋላ ወደ ጄኔቫ በመመለስ የጥናት ውጤታቸውን ለቡድን አባላቶቻቸው ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ጥናታቸውን አቅርበዋል። ታድያ በወቅቱ የአፍሪካ ተወካዮች ባህል እንዴት ይሞገታል በሚል ይቃወሟቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

በ1976/77 ዓ.ም በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ የሚመክር ስብሰባ በዳካር ከተማ በሴኔጋል ሃገር ሲያዘጋጁም ተቃውሞው አልበረደም ነበር ።ቀስ በቀስ ግን ሃፍረቱ እና መሸማቀቁ ቀርቶ ለጉዳዩ እውቅና ይሰጠው ጀመር። ይህ ደግሞ አሰቃቂ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ በእጅጉ አስፈላጊ ነበር። ዛሬ እነዚህን ልማዳዊ ድርጊቶችን ከምድረ-ገፅ ለማጥፋት በርካታ ዓለም አቀፍ አገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ለማየት ተችሏል።

ከብዙ ልፋት በኋላ ብዙ ሴቶች እና የዚህ ችግር ተጋላጮች ሪፖርቶችን ማዳመጥ እና መገንዘብ ጀመሩ። በስብሰባቸው ማጠቃለያ ይህን ጎጂ ልማድ ለመከላከል ኢንተር አፍሪካን ኮሚቴ የተባለውን ድርጅት መሰረቱ። ወ/ሮ ብርሃኔም የዚህ ድርጅት ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጥ ችለዋል።

በቀጠሉት 27 አመታት በ28 የአፍሪካ ሃገራት በድርጅቱ የተቋቋመና ያበቡ ብሄራዊ ኮሚቴዎች ለዘመናት ተሸፋፍነው የቆዩትን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ቀስ በቀስ በግላጭ እንዲታዩ ለማድረግ አስችለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ለዘመቻው እውቅና በመስጠት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጎጂ ልማድ የሚያግድ ውሳኔ አስተላለፈ፣በአለም አቀፍ የህፃናት መብት ስምምነት እና በአፍሪካ ህብረት የማፑቶ ፕሮቶኮል ውስጥ ህፃናትን ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሚከላከል አዲስ አንቀፅ እንዲገባ ተደረገ።

ጉዞው ፈታኝ ቢሆንም የሴቶች ግርዛትን መቃወም እንደነውር የሚቆጥረውን ባህል መስበር በመቻላቸው ኩራት ይሰማቸዋል።

ድርጅቱ በባህል ከለላ የሚፈፀሙ እንደሴት ልጅ ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዶች ላይ ብቻ ሳይሆን የሰዎች ህገ ወጥ ዝውውርንና በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ሌሎች ጥቃቶችችንም ለማጥፋት የሚሰራ ይሆናል። ‘’ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች በሃገር አቀፍ እና በአለም አቀፍ የአመራር ቦታ ላይ ተቀምጠው ማየት በእጅጉ እናፍቃለው ዝምታችን በዝቱዋል ለዘመናት ተለጉመን ቆይተናል ኢትዮጵያ የብሩህ ሴቶች መካን አደለችም አያሌ ብቃት ያላቸው እና ልምድ ያካባቱ ሴቶች አሉን’’ በማለት ወ/ሮ ብርሃኔ ይናገራሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *