ወጋየሁ ንጋቱ

ወጋየሁ ንጋቱ

ተወዳጅ የሚድያና የኮሚኒኬሽን ማእከል ለሀገር ውለታ የሰሩ ሰዎችን ይዘክራል፡፡ በህይወት ሳሉ፣ በሞት ሲለዩ ታሪካቸው በየአጋጣሚው እንዲታወስ ያደርጋል፡፡ ድርጅታችን ስለ ወጋየሁ ንጋቱ በርካታ ምርምሮች እየሰራ ሲሆን በቅርቡ ይፋ ይሆናል፡፡ ዛሬ ግንቦት 28 2010 ወጋየሁ ንጋቱ በህይወት ቢኖር 75ኛ አመቱን ያከበር ነበር፡፡ እኛም የወጋየሁን ልደት በፌስ ቡክ እናክብር በሚል ርእስ እነሆ ከአሁን አንስቶ ልደቱን በዚህ መጣጥፍ አማካይነት እያሰብን እንገኛለን፡፡

ወጋየሁ ሄሊስታኮቭን ሁኖ ሲተውን

ወጋየሁ መድረክ ላይ ሲተውን የመመልከት እድል አልነበረኝም። ነገር ግን የሰራቸው የመድረክ ቴአትሮች በቴሌቪዥን የመቀዳት እድል ስለነበራቸው ያኔ ነበር ወጋየሁ ምርጥ ተዋናይ እንደነበር ያወቅሁት ። በተለይ የኒኮላይ ጎጎል ድርሰት የሆነው ”ዋናው ተቈጣጣሪ” የተባለውን ቴአትር ስመለከት ወጋየሁ ሄሊስታኮቭን ሁኖ ሲተውን እንዴት እንደተመቸኝ ልነግራችሁ አልችልም ። ታዲያ ዛሬ ስለ ወጋየሁ ይህን ለመጻፍ የተነሳሁት ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 28 2010 ወጋየሁ በህይወት ቢኖር 75ኛ አመት የልደት በአሉን ያከብር ስለነበር አሁን በዚህ ሰአት እርሱን ለማስታወስ ነው፡፡

የወጋየሁ የልደት ቀን በመሆኑ ነበር ። የመድረኩ ጸዳል በህይወት ቢኖር ኖሮ 73 አመቱን ያከብር ነበር ። እናም ይህን ቀን አስመልክቼ ስለ ወጋየሁ ያልተሰሙ ፣ ያልተባሉ ፣ ለየት ያሉ ነገሮችን ላነሳሳ ወደድኩ። ወጋየሁ በዚህ ቀን ተወልዶ ይህን ሰርቶ ፣ ልጅ ወልዶ ከማለት የሆነ አዲስ መንገድ አመላክቼ የምወደውን አርቲስት ብዘክር ደስ ይለኛል።

አረንጓዴዋ የወጋየሁ አጀንዳ

ፍራንክ እጁ ሲገባ

አቶ ዘመዴ ንጋቱ የወጋየሁ ታላቅ ወንድም ናቸው ።እርሳቸው የወጋየሁን ታዛዥነት ያደንቃሉ። ያኔ በልጅነት ወጋየሁ መረበሽ የሚባል ነገር እንደማያውቅ ወንድሙ ይናገራሉ ። ወጋየሁ አንደኛ ደረጃን እንጦጦ ሚሲዮን ሲማር ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ተፈሪ መኮንን ጨርሷል ።

ከሀይስኩል በኋላ ነበር የወጋየሁ የትወና ፍቅር መውጣት የጀመረው። ያን ጊዜ ወጋየሁ ተራ ወሬ ነው ብሎ ለጓደኞቹ የሚያወራቸው ነገር እነሱን በጣም ያስቃቸው ነበር ። ወጋየሁ በዚህ ተበረታታና ቀልዶቹን አሳመረ። የእነ አለቃ ገብረሀናን ቀልድ ሲያቀርብ ወጋየሁ ይበልጥ ተደናቂ ለመሆን ቻለ።
ኮሚኩ ወጣት ፊልም አብዝቶ ይወዳል ። ሮጦ ወደ ፊልም ቤት ይገባል። በተለይ ቅዳሜ ሲመጣ ምንም ቢሆን ከፊልም ቤት አይቀርም ። ያያትን ፊልም አንድም ሳያስቀር ገልብጦ ለተማሪዎች ያቀርባል ።

94 ቴአትሮችን ሰርቷል

ወጋየሁ በ21 አመት እድሜው የመጀመሪያውን ቴአትር ከተጫወተ በኋላ በ24 አመቱ ሀንጋሪ ቡዳፔስት ተምሮ ከመጣ በኋላ የመድረክ ሰው ሆነ ።

ወጋየሁ በህይወቱ 94 ቴአትሮችን ሰርቷል። ሰላሳ ያህሉ የመድረክ ሲሆኑ 18ቱ የቲቪ ፣ 46 ያህሉ ደግሞ የሬድዮ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ በሎሬት ጸጋዮ የተደረሰው ሀሁ በስድስት ወር ተደናቂው ነው።

ሰአሊ እሸቱ ጥሩነህ ”መላ አካሉ ቋንቋው” በሚል ርእስ የወጋየሁ የሰውነት፣ የቁመት ፣ የፊት ፣ቅርጽ ሁኔታ ላይ ጠለቅ ያለ ሂሳዊ ጽሁፍ አቅርበዋል። ታዋቂው ሀያሲ ስዩም ወልዴም” ገጸ ብዙ ጠቢብ” በሚል ርእስ የወጋየሁን ሁለገባዊ የተዋናይነት ብቃት አብራርቶ ጽፎአል።

ረዳት ፕሮፌሰር ሀይማኖት አለሙ ወጋየሁ ለመድረክ የተፈጠረ መሆኑን ያስባል ። ወጋየሁ ለረዳት ፕሮፌሰር ሀይማኖት ትራጄዲንም ፣ኮሜዲንም ፤ ማይምንም የመስራት ብቃት ያለው ተዋናይ ነው ።

ፍቃዱ ተክለማሪያም ከወጋየሁ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ነበረው። ፍቃዱ እንደሚያስታውሰው ወጋየሁ ከእርሱ በኋላ ለሚመጡ ተዋናዮች እውቀቱን ለማካፈል ፍጹም የማይሳሳ ነበር ።

የወጋየሁ ሴት ልጅ ሪታ ወጋየሁ በአሁኑ ሰአት አሜሪካ ነው ያለችው ።በነገራችን ላይ ወጋየሁ ህይወቱ ያለፈችው ከዛሬ 26 አመት በፊት በህዳር 6 1982 ነበር ።

ስለ ወጋየሁ ይህን ብዬ ሳበቃ ብዙ ሊባል እንደሚችል አስባለሁ ቆየት ብዬ በሌላ መንገድ ወጋየሁን ማስታወሴ አይቀርም ። ለዛሬ ግን 75ኛ አመቱን አስመልክቼ ይህን ጣል አድርጌአለሁ። ስለ ወጋየሁ የምታውቁ ደግሞ የምታውቁትን በሉ ። ወጋየሁ ውስጤ ነው ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *