ወይዘሪት ሆይ አርበኛ ከበደች ስዩም (1904 – 1976)

ወይዘሪት ሆይ አርበኛ ከበደች ስዩም

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በልዩ ልዩ ዘርፍ ሀገራቸውን ያገለገሉ ጀግኖችን ሲዘክር ታሪካቸውን በልዩ ልዩ መንገድ ሲያወጣ ነበር፡፡ በተለይም በማህበራዊ ድረ ገጽ ሲወጡ የነበሩት መረጃዎች ብዙ ቁምነገር ነበራቸው፡፡ እነዚህ ታሪካቸው የሚሰነድ ባለውለታዎች ለእናት ሀገራቸው ታላቅ ፍቅር የነበራቸው እና በትጋት ያገለገሉ ነበሩ፡፡ የእነዚህን ታላላቅ ሰዎች ታሪክ በተምሳሌትነት ማቅረብ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ተምሳሌት ከሆኑት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የዛሬ 40 አመት ህይወታቸው ያለፈው አርበኛ ወይዘሪት ሆይ ከበደች ስዩም ናቸው፡፡ አርበኛዋ በተለይ ጣሊያን ከ83 አመት በፊት ሀገራችንን በወረረ ጊዜ አንጸባራቂ ድል የፈጸሙ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ምንጊዜም የማይረሱትም ነው፡፡ እኒህ ታላቅ ጀግና ማናቸው? የሚለውን እዝራ እጅጉ የሚለው አለ፡፡

ጀግናዋ ከበደች ስዩም ጥቅምት 17 ቀን 1904 ዓመተ ምሕረት በትግራይ ጠቅላይ ግዛት በእንደርታ አውራጃ መቀሌ ከተማ ከልዑል ራስ ስዩም መንገሻና ከወይዘሮ ጀምበር በርሄ ተወለዱ፡፡ የዕድሜ ገደብ ሲፈቅድላቸው ንባብና ጽሕፈት እንዲሁም የባልትና ሙያ በወላጆቻቸው ቤት እንዳሉ ተማሩ፡፡

በተወለዱ በአሥር አመታቸው ከደጃዝማች አበራ ካሣ ጋር በሥርዓተ ተክሊል ተጋቡ፡፡ ሦስት ወንዶችና አንዲት ሴት ልጅም ወለዱ፡፡

ቅድመ አያታቸው አፄዮሐንስና አያታቸው ራስ መንገሻ ዮሐንስ በጀብዱ ታሪክ ያወቃቸው እንደመሆኑ መጠን በሳቸውም ላይ የሀገር ፍቅር ስላደረ ከትውልድ የተላለፈላቸው በመሆኑ እጅግ የሚያስደንቅ ሆኖ ታይቷል፤ ጀግናዋ ወይዘሮ ቀጠን ያሉና ዓይኖቻቸው የሚያስደነግጥ ኃይል ያላቸው ነበር፡፡

ፋሺሽት ኢጣልያ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለማድረግ በማይጨውና በተንቤን በአውሮፕላን ተወርዋሪ ቦምብና በሚረጭ ልዩ ልዩ መርዝ የግፍና የእብሪት ጦርነት ባካሄደበት ጊዜ ባለቤታቸው ደጃዝማች አበራ ካሣ ወደጦርነቱ ለመሔድ በሚዘጋጁበት ወቅት በሰላሌ አውራጃ ለጥበቃ የቀረበውን ጦር ጀግናዋ ከበደች ስዩም ሰብስበው የኢጣልያንን ጠላትነት በግልፅ እንዲያውቅና የውድ ሀገሩን ፀጥታ በጥንካሬ እንዲጠብቅ አጠናከሩ፡፡

ጠላት በሚጥለው ቦምብና አሰቃቂ የመርዝ ጢስ ጊዜያዊ ድል አግኝቶ ወደመሐል ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ከባለቤታቸው ከደጃዝማች አበራ ካሣ ጋር ሆነው በጎጃም፣ በመርሐቤቴ በኩል ከዘመቻ የተመለሰውን ጦር ፍቼ ከተማ ላይ በእንግድነት እየተቀበሉ በማስተናገድና ቁስለኞችን በማስታመም ያልተቆጠበ የርህራሄ ተግባር ፈጽመዋል፡፡

ባለቤታቸው ደጃዝማች አበራ ካሣና ደጃዝማች አስፋወሰን ካሣ በራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት አማካይነት ወደ ኢጣልያን ባለሥልጣኖች ለመሄድ ሲነሱ ከዚህ የሚከተለውን ደብዳቤ ጻፉላቸው፤ ቃሉም እንደሚከተለው ነው፡፡

‹‹በእኛ ምክንያት ሀገሬንና ሕዝቡን ለማጥፋት ጦር መምጣቱን ልጅ ኃይለማርያም ገዝሙና፣ ፊታውራሪ አሸከራቸው እጅ ማኅተማቸውን ልከዋል ይኸንን እየሰማን ለራሳችን ብቻ ስንል ሕዝቡን ማስጨረስ በኢጣልያኖችም ላይ ቃታ ያልፈለቀቁትን ብዙ ንጹህን ሰዎች ደም ይፍሰስ ብሎ መፍረድ ማንዘለው የእሳት ጉድባ ሆኖብናል፡፡

ስለዚህ እጃችንን አይደለም ነፍሳችንን መስጠታችን ነው፡፡ አንቺንም አደራ ሰጠሁሽ ለፈጣሪ ነው እንጂ ለፍጡር አለመሆኑን እንድታውቂው የአባቶቻችን አምላክ ጠብቅሽ ታኅሣሥ 12 ቀን 1929 ዓ.ም አጥቢያ ከሌሊቱ በዘጠኝ ሰዓት ተጻፈ፡፡

ደጃዝማች አበራ ካሣ፣ ደጃዝማች አስፋወሰን ካሣ በኢጣልያን ባለስልጣኖች በግፍ ተደብድበው ተገደሉ፡፡ ይኸንን አሰቃቂና መራራ መርዶ ጀግናዋ ወ/ሮ ከበደች ስዩም ከሰሙ በኋላ ትጥቃቸውን አጠንክረው በቆራጥነት ወደ አንሳሮና መርሐቤቴ እንዲሁም ወደ ሚዳ እየተዘዋወሩ ሕዝቡ ወደአርበኝነት እንዲሰማራ አስተባበሩት፡፡ ከኢጣልያን ፋስት ባለሥልጣኖችና ወደእነሱም ከተጠጉት አቀንቃኞች ወንዶቹ ያልቻሉትን አንቺ ሴቷ እንዴት ልትመክቺ ነው ይልቁንስ እጅሺን ስጭ በማለት ሀሳብ ሲሰጣቸው ሀሳቡን ከምንም ሳይቆጥሩ አርበኝነታቸውን ቀጠሉ፡፡

ግንቦት 25 ቀን 1929 ዓ.ም ሚዳ ወረዳ ቀኝ ገደል ከተባለ ስፍራ እንዳሉ ከበደች ስዩም በጣላት ጦር ተከበቡ፡፡በወቅቱም የትግል ጓደኞቻቸው የጦሩን ብዛትና ኃይል በማስመልክት እጃችንን እንስጥ በማለት ቢጠይቋቸው ይኸንን ሰንካላ ሀሳብ አልቀበልም በማለት ተኩስ ከፍተው እጅግ በሚያስደንቅ ጀግንነት ክቡን ሰብረው ወጡ፡፡

በሰኔ ወር መጀመሪያ 1929 ዓ.ም ከራስ አበበ አረጋይ፣ ከራስ መስፍን ስለሺ እንዲሁም ከደጃዝማች ዘውዴ አስፋው ጋር ተገናኝተው በአርበኝነት ከኢጣልያ ጦር ጋር ስለሚደረገው ፍልሚያ ምክክር አደረጉ፤ ጀግናዋ ከበደች ስዩም፡-

ሀ/ ወረጃርሶ መሽጎ የነበረውን የጠላት ጦር ክፉኛ አጥቅተዋል፡፡

ለ/ ጉዞ በሚያደርጉበት ጊዜ መልጮ ላይ ቀድሞ ይጠባበቃቸው የነበረውን ጦር ደምስሰዋል፡፡

ሐ/ ካቺሴ በዳ ጢና ላይ መሽጎ የነበረውን ጦር በሰኔ ወር 1929 ዓ.ም ባሰቃቂ ሁኔታ ደምስሰውታል፤ ይህ ሁሉ ሲፈጸም ነፍሰጡር ስለነበሩ ሐምሌ 1 ቀን 1929 ዓ.ም ወልደው የልጃቸውንም ስም ታሪኩ አበራ ብለው ሰየሙት፡፡

መ/ ወይዘሪት ሆይ ከበደች ስዩም ከሸዋ፣ ወደጎጃም ሄደው ቡሬ ዳሞት ላይ የከበባቸውን ኢጣሊያን ጦር አጥቅተው ከተባባሪ ጓዶቻቸው ጋር ለማምለጥ ቻሉ፡፡

ሠ/ ልበሙሉ ጀግና ወይዘሪት ሆይ ከበደች ስዩም በየመንገዱ እያደፈጠ የሚጠብቃቸውን የፋሺስት ጦር እየደመሰሱ በወንበራ በኩል አድርገው በ1931 ዓ.ም መጨረሻ ካርቱም ገቡ፤ በበርሃው ሀሩርና በኮርንችትና ባልጭት የተጎዳው እግራቸውና ሰውነታቸው ካገገመ በኋላ ተላልከው ባገኙት ፈቃድ ምድረግብፅ ካይሮ ገቡ፡፡ በዚያም እንደደረሱ ጋዜጠኞች ላቀረቡላቸው ጥያቄ በራሳቸው ላይ የደረሰውን የጦርነት መከራና በጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ፋሺስቶች የፈጸሙትን አሰቃቂ ግፍ አንድ ባንድ አስረዱ፡፡

ረ/ ጀግናዋ ወ/ሮ ከበደች ስዩም ከግብፅ መዲና ወደኢየሩሳሌም ሄደው ሁለት ዓመት በስደት ከቆዩ በኋላ ኢጣሊያኖች በድል ተመትተው ከመባረራቸው ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ይኸንን ዓለም በመናቅ በፀሎትና መንፈሳዊ ተግባር ተወስነው ከቆዩ በኋላ ታኅሣሥ 29 ቀን 1976 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው የአርበኝነትና የስደት ተባባሪዎቻቸውና ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ለሀገር ወዳድ የጦር መሪዎች በተዘጋጀው መካነመቃብር አስክሬናቸው በክብር አርፏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *