ኮሎኔል ብርሃነመስቀል ሃይሌ

ኮሎኔል ብርሃነመስቀል ሃይሌ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሀገራቸውን በአየር ሀይል አብራሪነት እንዲሁም በከፍተኛ የውትድርና ሙያ ያገለገሉ ሰዎች በደማቅ ብእር ተጽፈው ታሪካቸው ለትውልድ እንዲቀመጥ ያደርጋል፡፡ እነዚህ በዚህ የዊኪፒዲያ ገጽ ላይ ታሪካቸው የሚሰፍርላቸው ሰዎች ለሀገር ሰርተው ብዙም የሚድያ ሽፋን ያላገኙና ሊጻፍላቸው የሚገባቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ መሀልም የዐየር ሀይል አብራሪው ኮሎኔል ብርሀነ መስቀል ሀይሌ ናቸው፡፡ እኒህ ታላቅ ሰው ታህሳስ 14 2014 የቀብር ስነስርአታቸው ስላሴ መንበረ ጸባኦት ቤተክርስቲያን የተፈጸመ ሲሆን ግለ-ታሪካቸውን ቤተሰቦቻቸውን ብሎም የቅርብ ባልደረቦቻቸውን በማነጋገር እንደሚከተለው አጠናክረነዋል፡ ፡

ኮሎኔል ብርሃነመስቀል ሃይሌ ከእናታቸው ከወ/ሮ ባልታወርቅ ሃይሌ እና ከአባታቸው ከአቶ እያሱ ደበሳይ ነሃሴ 13 ቀን 1930 አ.ም አዲስ አበባ ቤላ አካባቢ ተወለዱ ፡፡ የልጅነት ዘመናቸውን ያሳለፉት በቤተክህነት ትምህርት ነው ፡፡ የዘመናዊ ትምህርት የጀመሩት እድሜያቸው ለትምህርት ካለፈ በኋላ ነው፡፡ ገና ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚሰጠውን ትምህርት የጨረሱት እያጠፉ በማለፍ በ4 ዓመት ውስጥ ብቻ ነበር፡፡ ይህንን ትምህርት የተከታተሉት በአምሃ ደስታ ት/ቤት ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በተፈሪ መኮንን ተከታትለዋል ፡፡

ጥር 14 ቀን 1952ዓ.ም በኢትዮጵያ አየር ኃይል በአውሮፕረን አብራሪነት ሙያ ተቀጠሩ፡፡ ኮሎኔል በኢትዮጵያ አየር ኃይል የአውሮፕላን በረራ ትምህርታቸውን ተከታትለው በበረራ ዲፕሎማ የተመረቁና የም/መ/አ ማእረግና የበረራ ክንፍ ያገኙ ሲሆን የበረራ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በተለያዩ አውሮፕላኖች ላይ አብራሪ በመሆን በተለያዩ የአየር ኃይሉ የሥራ ከፍሎች በመመደብ ግዳጃቸውን በአግባቡ የተወጡ ሲሆን ተዘዋውረው ከሰሩባቸው ኃላፊነቶች መካከልም ፡-

  • የኤል -19 አውሮፕላን አብራሪ
  • የሲሲና-185 አውሮፕላን አብራሪ
  • የሲንግል ቤል ሂው አውሮፕላን አብራሪ
  • የዳሽ-3 አውሮፕላን አብራሪ
  • የዳሽ-6 አውሮፕላን አብራሪ
  • የሚ -8 ሄሊኮፐተር አብራሪ
  • የሚ -24 ሄሊኮፐተር አስተማሪና አብራሪ
  • የተዋጊ ሄሊኮፐተር ሬጂመንት አዛዥ
  • የአየር ኃይል ኢንስፔክተር ጀነራል ኃላፊ
  • በባህር ላይ የስለላ አውሮፕላን ፕሮጀክት መኮንን በመሆን ያገለገሉባቸው ይጠቀሳሉ፡፡

በ 1955 ዓ.ም ወደ አርሚ አቪዬሽን በመዘዋወር እስከ 1972 ዓ.ም የተለያዩ አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮችን ሲያበሩ ነበር ፡፡ እንደገና በ 1972 ዓ.ም የካቲት ወር ወደ አየር ኃይል በመመለስ በተዋጊነት በአስተማሪነት በተቆጣጣሪነት ሰርተዋል፡፡ በሥራቸው በነበራቸው ትጋት በ 1961 ዓ.ም ከግርማዊ ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ እጅ ሜዳልያ ተቀብለዋል ፡፡ ለበረራ ትምህርት ወደበርካታ ሃገራት የተጓዙ ሲሆን ከ አሜሪካ ከካናዳ ከሶቪየት ህብረት ካገኟቸው የምስክር ወረቀቶች ውስጥ :-

  1. የፓይለት ሪክሩት ኮርስ
  2. የአብራሪነት ኮርስ
  3. የአስተማሪ ፓይለት ሰርተፍኬት
  4. የታክቲክና የመሳርያ በረራ ሰርተፍኬት
  5. የበረራ ሴፍቲ መኮንን ኮርስ
  6. የሄሊኮፕተር በረራ ኮርስ
  7. የትዊንኦተር ኤንጅን በረራ ስልጠናዎች ጥቂቶቹ ናቸው ፡፡ ከ 1972 ዓ.ም ጅምሮ የአምስተኛ አጥቂ ሂሊኮፍተር ወይም የ5ኛ ተዋጊ ሄሊኮፕተር ሬጅመንት አዛዥና አብራሪ ነበሩ ፡፡ በ1973 ዓ. ም በደርግ መንግስት ላይ በህውሃት በተከፈተ ጥቃት አብይ አዲን ና ቃርቃ አምባን በተዋጊ አውሮፕላን እንዲደበድቡ ከአለቆች ትእዛዝ ቢሰጣቸውም ከ10-15 ወንበዴ መቀሌ ገባ ብለን ህዝብ አንደበድብም በማለት አስተማሪ ወረቀቶችን ከሂሊኮፕተር ላይ በትነው በመመለሳቸው በወቅቱ ለእስር ተዳርገው ነበር ፡፡ ኮሎኔል ብርሃነመስቀል ሀይሌ በአጠቃላይ በ34 አመት ውስጥ ከ9000 በላይ የበረራ ሰአት አስመዝግበዋል፡፡ በዚህም ወቅት በፈፀሙት የጦር ሜዳ ጀግንነት የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳልያ ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ትምህርት እና በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ በተጨማሪም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ የበረራ ክፍል ውስጥ ለአጭር ጊዜ አገልግለዋል፡፡ በ 1986 ጥር ወር በወቅቱ የነበረውን መንግስት ለኢትዮጵያ አንድነት የማይበጅ ያሉትን ሃሳብ በመቃወማቸው እና በማውገዛቸው በክፉ ታዩ፡፡ ከዚህ በኋላ የወዳጆቻቸውና የጓደኞቻቸው ተግሳፅ‹‹ ልጆችህን አርፈህ አሳድግ ተመሳስለህ ኑር ››የሚል ምክር ቢሆንም እሳቸው ግን ይህንን አሉ፡፡ ያሉትን ቃል በቃል ከራሳቸው ማስታወሻ እንዲሁም ከጦቢያ ጋዜጣ 7ተኛ እትም ቁጥር 43 ጥር 24/1993 ከታተመው ፅሁፍ ቃል በቃል እንደሚከተለው አነበዋለሁ፡፡ ‹‹ከሰዓት በኃላ ዘመድ ለመጠየቅ ወደ ከተማ ሄጄ ስመለስ በወረዳ መስሪያ ቤት የሚሰራ ጓደኛዬ በመንገድ ላይ አግኝቶኝ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ እንደ ምክር አድርጎ “ምን አለበት አፍህን ሰብስበህ ልጆችህን ብታሳድግ? ዛሬ ስምህ ፀረ ቻርተርና ፀረ ህገመንግስት ተብለህ ወደላይ ተላልፏል, አለኝ እኔም አንድ ኢትዮጵያን መገነጣጠያ ህግ ላፅድቅ? አላደርገውም ! በዚህ ምክንያት እኔን ማስፈራራት ማሰር አደለም ትገደላለህ ቢሉኝ እንኳን አልቀበልም ፡፡

በመቃብሬ ላይ “ኢትዮጵያ አትገነጣጠልም” የሚል ሃውልት ይተከልልኛል”፡፡ ይላል የኮሎኔል ማስታወሻ ከታተመው ጋዜጣ የተወሰደው፡፡ ይህ እውነተኛ የሀገር ፍቅራቸው ከለውጡ መንግስት ጋር ሊያስማማቸው አልቻለም፡፡ ኢትዮጵያ አትፈርስም ለህዝቡ የሚጠቅመውን እንጂ ለእናንተ የሚመቸውን አልወስንም በማለተቸው የካቲት 30, 1986 ዓ.ም ለእስር ተዳረጉ፡፡ ኮሎኔል በባህሪያቸው ፍርሃት አያውቁም በፀባያቸው እልኸኛ ናቸው፡፡ በእስራቸው ወቅት የሃገራቸው ጉዳይ እንቅልፍ ነስቷቸው ካደረ በጠዋት ወደ ኃላፊ ቢሮ ሄደው ስለኢትዮጵያ አንድነት መፈክር ያሰማሉ መንግስትን ያወግዛሉ ለተወሰነ ቀን በእግረ ሙቅ ታስረው ይከርማሉ ከዛ ይፈታሉ፡፡ ከጥቂት ቀን በኋላ ያው ይደገማል፡፡ ለዚህ ሁሉ ያበቃቸው የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ነበር፡፡ ኮሎኔል ያላቸውን የሃገር ፍቅር በቃላት ለመግለፅ ያስቸግራል፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ሲተርኩም አፍ ያስከፍቱ ነበር፡፡ ልጆቻቸውን ሲድሩ የአያትነትን ወግ ሲያዩ እዛው እስር ቤት ውስጥ ነበሩ፡፡ በእስር ወቅታቸው ከጣብያ ጣብያ ከማረሚያ ወደ ማረሚያ ቤት ያለፍትህ ሲዘዋወሩ

ቆይተው ለ17 አመት ከ8 ወር ያህል ተንገላተው ህዳር 29, 2003 ዓ.ም ከወህኒ ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ተቀላቀሉ፡፡ በእስር ቤት ቆይታቸው የተለያዩ ስልጠና የወሰዱ ሲሆን በግብርና ዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ ከእስር ከተለቀቁ በኋላአቅማቸው እሰከፈቀደ ድረስ የታመመ ሲጠይቁ አቅመ ደካሞችን ሲጎበኙ ቆይተዋል፡፡ በዚህም ወቅት ከቀድሞየኢትዮጵያ አየር ሃይል አባላት እና ቤተሰቦች ህብረት (ETAF-GLOBAL) ለአገልገሎታቸው እና ለከፈሉትመስዋዕትነት የምስክር ወረቅት እና ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡ኮሎኔል ብርሃነመስቀል ሃይሌ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ግዳጃቸውን ሲወጡ በነበሩበት ወቅት ከበላይ አለቆቻቸውሆነ ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ተግባብተው በመስራት በሚያሳዩት መልካም ባህሪ የሚወደዱ መኮንን ነበሩ፡፡

ኮሎኔልብርሃነመስቀል ሃይሌ ባለትዳር እና የ15 ልጆች አባት ሲሆኑ 8 የልጅ ልጆች አይተዋል፡፡ ባደረባቸው ፅኑ ህመም ምክንያትህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ታህሳስ 12, 2014 ዓም ከጠዋቱ 2፡00 ሰአት በተወለዱ በ84 አመታቸው ከዚህ አለም በሞትተለይተዋል፡፡

ስለ ኮሎኔል ብርሀነ መስቀል ሀይሌ የተሰጡ አስተያየቶች

ትእግስት ብርሀነ መስቀል የኮሎኔል ብርሀነ መስቀል ልጅ ስትሆን አባቷ ለሀገር ያላቸው ፍቅር ጥልቅ መሆኑን ትናገራለች፡፡ ከቤተሰብ በላይ ለሀገር ቅድሚያ የሚሰጠው አባቴ ሀገሩን በንቃት ያገለገለ ታላቅ ሰው ነው ስትል ሀሳቧን ትሰጣለች፡፡ ‹‹ እርግጥ ነው አባቴ ላመነበት ነገር ሁሌም ግትር ነው፡፡ ይህን ደግሞ ብዙ ሰው ያውቃል፡፡ በዚህ መልካም ሰብእናውም ሰዎች ያከብሩታል ›› በማለት ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

ካፒቴን ሰለሞን ክፍሌ እና ኮሎኔል ሰለሞን ከበደ በሰጡት ምስክርነት ኮሎኔል ብርሀነ መስቀል በስራቸው ደከመኝ የማያውቁ ሀገር ወዳድ የአየር ሀይል አብራሪ መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ መዝጊያ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አቋምን የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚዋደቁላትን ልጆች አላጣችም፡፡ ሁሉም ሲጠየቁ የመዋደቃችሁ ዋና ምክንያት ምንድነው ሲባሉ ኢትዮጵያ ሲሉ በሙሉ ኩራት ይናገራሉ፡፡ ኮሎኔል ብርሀነመስቀል ሀይሌ ፤ ኢትዮጵያ ብለው ሲታገሉ ርካታ ከሚሰጣቸው መካከል ይመደባሉ፡፡

ዘመናቸውን ሁሉ ኢትዮጵያን ከፍ እንዳደረጉ ያለፉ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ የኮሎኔል ብርሀነ መስቀል ታሪክ ለአሁኗ እና ለወደፊቷ ኢትዮጵያ እጅግ የሚጠቅም ብቻ ሳይሆን የማነቃቃት ድንቅ አቅም ነው፡፡ ይህ ታሪካቸው ለመጪው ትውልድ ሲቀመጥ ለካስ ሀገራችን እንዲህ አይነት ታላቅ ሰው ነበራት ያሰኛል፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ ዋና አላማ ለሀገር ውለታ የዋሉ ሰዎችን ማስታወስ ነው፡፡ ከሚታወሱት እና ከሚከበሩት መሀል ደግሞ በቀዳሚነት ኮሎኔል ብርሀነ መስቀል ሀይሌ ይጠቀሳሉ፡፡ / ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተጠናከረ ሲሆን ዛሬ ታህሳስ 15 2014 አ.ም በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽና በዚህ ዊኪፒዲያ ላይ ተጫነ፡፡ አስፈላጊው ማሻሻያ ተደርጎም በየጊዜው እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *