እሸቱ በላይ- የአሐዱ ሬድዮ ባለቤት እና መስራች አቶ ማናቸው?

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣ መዝገበ-አእምሮ ( የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች ፣በመፅሀፍ፣በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመት ከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መፅሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

ከእነዚህ ውስጥ የሚድያ ሰዎችም ይገኙበታል። አጠቃላይ 74 ከፍተኛ የሚድያ አመራሮች፣ሚኒስትሮች ፣ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የግል ሚድያ መሥራቾች፣ዋና አዘጋጆች እና መካከለኛ አመራሮች ተካተዋል። 35 ያህሉ በዋና ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ ሲሆን የሁሉም ታሪክ በተሟላ ደረጃ ለመሰነድ ችሏል። የእነዚህን አመራሮች ታሪክ ሰንዶ ለአንባቢ ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም አሳክተነዋል። በዚህ ተግባራችንም ተጠናክረን እንቀጥላለን። አሁን በዚህ ፅሁፍ የምናስነብባችሁ የአሀዱ ሬድዮ መሥራች እና ባለቤት የሆኑትን የአቶ እሸቱ በላይን ታሪክ ነው።

አቶ እሸቱ የአሐዱ ሬዲዮን ቀጥሎም አሐዱ ቴሌቭዠን ለመመስረት በቅቷል ።አቶ እሸቱ በላይ ገና በ15 ዓመት ዕድሜው ትልቅ የሆነ የአፍሪካ ሚዲያ የማቋቋም ፍላጎት ያደረበት ሲሆን ይህ ህልሙ በውስጡ እየጎለበተ እና እየተብላላ ከዕድሜው እኩል አድጓል። ይህንንም እውን ለማድረግ እና ተደራሽ ለመሆን የአለም አቀፍ ፓለቲካ መቀመጫ በሆነችው በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከነጩ ቤተ መንግስት በ50 ሜትር እርቀት ላይ በታዋቂው ሮናልድ ሬገን ህንፃ ውስጥ 9000 ft² ላይ ያረፈ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌቪዥን ስቱድዮ ለመገንባት ችሏል። በዋሽንግተን ዲሲ “አሐዱ ግሎባል ኔትወርክ” በሚል ስያሜ ፍቃድ አግኝቶ የአፍሪካ የመጀመሪያ ሚዲያ በመሆን እየሰራ ይገኛል ።አቶ እሸቱ በላይ ብዙውን ጊዜ በሚድያዎች ላይ የማይታይ፣ቃለ-ምልልስ ላይም ሲቀርብ አይታይም። ለተወዳጅ ሚድያ ብቻ ኢንተርቪው ሰጥቶ የህይወት ታሪኩንም ለመሰነድ ችለናል። ዕዝራ እጅጉ ታሪኩን እንደሚከተለው አጠናክሮታል።

በአሁኑ ሰአት በከፍተኛ ደረጃ ተደማጭነት ያለውን አሐዱ የሬድዮ ጣቢያ የመሠረተ ነው፡፡ ከዚህ በፊት “አውቶሞቲቭ ጆርናል” የተሰኘውን ፕሮግራም በመጀመር ትልቅ አሻራ አኑሯል፡፡ አቶ እሸቱ በላይ ከ1990ዎቹ በኋላ የሚድያ አስተዋጽኦ ከነበራቸው ሰዎች አንዱ በመሆኑ ግለ-ታሪኩ በመዝገበ- አእምሮ ላይ እንዲሰፍር አድርገናል፡፡

ትውልዱ በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ቄራ አካባቢ ሲሆን ከእናቱ ወ/ሮ የሺ መለሰ እና ከአባቱ አቶ በላይ ወሌ በ1966 ዓ.ም ነሐሴ 24 ቀን ነበር የተወለደው ። የአሐዱ ሬዲዮ መስራች አቶ እሸቱ በላይ ።

እሸቱ፣ የመጀመሪያ ትምህርቱን በቅዱስ ያሬድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአቢዮት ቅርስ ( GCA) ተምሯል ። በወቅቱ በነበረው የተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር አለመጣጣም እሸቱ በኮታ የማትሪክ ውጤቱ ዝቅ ብሎበታል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ የተለመደ ስለነበር እምብዛም አልተገረመም ።

እንዲያውም ምን ብሠራ ራሴን ችዬ ለመቆም እችላለሁ ሲል ነበር ያሰበው ። ይሁን እንጂ በኋላ ላይ የማትሪክ ፈተናውን ወስዶ ውጤቱን አሻሽሎ በኮሌጅ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በተለያዩ ዘርፎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪውን በማርኬቲንግ በሊደርሽፕ፣ በጋዜጠኝነት አመራር ትምህርቱን አጠናቋል። እንዲሁም በሚዲያ ማኔጅመንት ዶክትሬት ዲግሪ በመማር ላይ ይገኛል ።

ተወልዶ ያደገበት አዲሱ ቄራ አካባቢ የብዙ ማህበረሰቦች መኖሪያ እና የልዩ ልዩ ሙያዎች መሞከሪያ ስለነበር እሸቱ 12ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀ ወደ ጋራዥ ሥራ ገብቷል ። በጋራዥ ውስጥ በርካታ የመካኒካል ሥራዎችን በመስራት ፣ የተበላሹ መኪናዎችን በመጠገን አጭር ጊዜን ካሳለፈ በኋላ 1986 ዓ.ም ተሳቢዎችን ሰርቶ ወደውጪ በሚልከው ማሩ የብረት ኢንዱስትሪ ውስጥ ተቀጥሯል ።

በዚህ የኢንጂነሪንግ ሙያው ውስጥ በርካታ ዕውቀቶችን ለማግኘት ችሏል ። በወቅቱም የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ፣ መካኒካል እና ዲዛይን ለመሥራት ስለሚያገለግሉ ሶፍትዌሮች ተምሯል ።
በማሩ ብረታብረት ኢንጂነሪንግ ውስጥ የዲዛይን ክፍል ኃላፊ እስከመሆንም ደርሷል። በኋላም የሴልስ ኢንጂነር ቀጥሎም በማርኬቲንግ ማኔጀርነት አገልግሏል። የተሞከረ ሳይሆን አዲስ ነገርን መፍጠር የሚቀናው እሸቱ “ኤዲ ስቴለር” የተሰኘ ድርጅት በመመስረት በዓይነቱ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የአውቶሞቲቭ ኤግዚቢሽን በ 1994 ዓ.ም ሲያካሂድ በ 4 ቀን ውስጥ 90,000 ሺህ በላይ ተመልካቾች ያገኘ ትልቁ ንግድ ትርኢት ለመሆን የበቃ ነው። በዚህ የመኪና ንግድ እና የሞዴል ትርኢት ከሀገረ- ጀርመን የተለዩ ባለሙያዎችን በማምጣት አለምአቀፍና ደረጃን የጠበቀ ኤግዚቢሽን ዕውን ማድረግ ችሏል።እሸቱ በራሴ ማደግ አለብኝ ብሎ ጊዜ ሰጥቶ የሚያስብ ማህበረሰቡን ከፍላጎት የሚያገናኘው ብልህ ሰውም ነው።

ታዲያ በዚያን ወቅት ከተለያዩ ሀገራት እንደ ስዊዲን ፣ ኖርዌይ፣ ጀርመን፤ራሺያ፣ፊንላንድ ፣ ካሉ የብዕር ጓደኞቹ ጋር በፖስታ ቤት ይፃፃፍ ስለነበር ጽሑፉ በሀገራት መካከል ያለውን ሁናቴ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሌሎቹ ሀገራት ጋር ያላትን ልዩነት ፖለቲካዊ ፣ማህበራዊ እና ሥነልቦናዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ የእድገት ደረጃ በሚመጡለት ደብዳቤዎች ይረዳና ያመዛዝን ስለነበር እኛ እንዴት ወደኃላ ቀረን ? ምንድነው የእድገታችን ማነቆ ? ሲል ደጋግሞ ይጠይቅ ነበር። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ቀዳሚ የሠለጠነች ሀገር በመሆኗ ነው።

ሀገራት ያላቸውን ባህል ፣ ታሪክና እሴት ጠብቀው እንዴት መቆየት እንደሚችሉ እርስ በርሳቸው እንዴት መተዋወቅ እና እንዴት መማማር እንዳለባቸው ሲያስብ ደብዳቤው እንደ አንድ ሚዲያ ሆኖ ማገልገሉን ያስተውላል ። ከዚያም በስራም እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች በአውሮፓ በሰሜን እና በደቡብ አሜሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ሲመለከት በሀገሩ መሰራት አለባቸው ያላቸውን ሀሳቦች ወደተግባር ለመቀየር የግዴታ ለህብረተሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በመፈለጉ ለዚህም ሚድያ ያስፈልጋል ብሎ በማመኑ በመጀመሪያ “አውቶ ፕላስ” የተሰኘ በእንግሊዝኛ የሚታተም መፅሔትን በዋና አዘጋጅነት ቀጥሎም አውቶሞቲቭ ጆርናል የሚል የሬድዮ ፕሮግራም በመሥራት ሀሳቦች ውሃ እንዲያነሱ እውቀቶች እንዲንሸራሸሩ መረጃዎች እንዲጎለብቱ ከታሰበ ቁልፍ ሊሆን የሚችለው ሚዲያ እንደሆነ እምነት ጥሏል።

ሚዲያ አራተኛ መንግሥት ከሆነ ዘንዳ ጠንካራ የሆነ ሚዲያ ለማቋቋም ያላሰለሰ ጥረት ያደረገ ሲሆን ታላላቅ የሚዲያ ሰዎችን እና ባለሙያዎችን በማሰባሰብ ጅማሮውን በሸገር ሬዲዮ አውቶሞቲቭ ጆርናል አድርጓል። ቢኒያም ከበደ ፣ ታገል ሰይፉ ፣ ጳውሎስ አለማየሁ ፣ ዳሪዮስ ሞዲ፤ ሰለሞን ጥኡመልሳን፤ ተስፋለም ታምራት ና ሌሎች ባለሙያዎችና ጋዜጠኞችን አሰባስቦ በሳምንት ለ4 ሰዓታት ከአንድ አመት በላይ በሸገር ሲቆይ ወደ በፋና ሬዲዮ በመዛወር ለ 8 ዓመታት ያህል በሙያና ሀሳብ በማፍለቅ በባለቤትነት አገልግሏል ።
በርካታ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪዎችን ችግሮች ቀርፏል።

በሥራ የቆየባቸውን ዕውቀቶች በማጋራት የመኪና ባለቤቶች እና ሾፌሮች ስለመኪና ማወቅ የሚፈልጉትን ማንኛውንም ጥያቄ የሚጠይቁበት ፣ መልስ የሚያገኙበት እና የሚማሩበት የሬዲዮ ዝግጅት በመጀመር ተወዳጅ ሆኖ የቀጠለ ዝግጅትን በመምራትና ባለቤት በመሆን ጎን በጎን በ Auto plus የተሰኘ መጽሔት በአውቶሞቢል ኢንዱስትሪ ላይ ያተኮረ መፅሔት ዋና አዘጋጅ በመሆን በመኪና ላይ ያተኮሩ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ አንኳር ነጥቦችን በመያዝ በመንገድ ላይ ያለ የመኪና አነዳድና የትራፊክ ፍሰት ስርዓት መኪናዎች በየጊዜው የሚፈጥሩት አደጋ እንዲቀንሱ የራሱን የሆነ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አድርጓል ።

የመኪና አስመጪዎች በሀገር ውስጥ መገጣጠም የሚችሉበትን አቅም እንዲያጎለብቱ የነበረው እገዛም ቀላል አልነበረም ። ሚዲያ አስፈላጊነቱን ለማሳወቅ ፣ ለማስተማር እና ለማዝናናት ከሆነ ዘንዳ እሸቱ በላይ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን ሚናውን እየተወጣ በቀጥታ የጥያቄና መልስ እንዲሁም የባለሙያ አስተያየትና ምክሮች ብሎም አዝናኝ ገጠመኞችን የያዘ መሰናዶ ላይ ቆይቷል ።

የመኪና ዕቃ መለዋወጫ ቋንቋዎችን አሽከርካሪዎች እንዲያውቁ እራሳቸው በራሳቸው የመካኒካል ሙያ ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ ብዙ ስራዎች እንዲሰሩ አድርጓል። ይህ በሌሎች ሚዲያዎች እና ባለሞያዎች ዘንድ እንደጥርጊያ መንገድ ሆኖ መነሳሳትን የፈጠረ ሲሆን የእሸቱም ዋነኛ ፍላጎት ይኸው ነበር ። እሸቱ በላይ የአውቶሞቲቭ ጆርናል የሬዲዮ ፕሮግራም እና auto plus ህትመትን ያስጀመረ ሰው ነው።

ወደሚዲያ የመግባት ፍላጎቱን በሸገር ከዚያ በፋና በኩል ያደረገው እሸቱ በላይ ትልቅ ሚዲያን እስከማቋቋም ደርሷል ። ለበርካታ ሰዎች ሰፋፊ ዕድልን በመፍጠር ፣ ፕሮግራም መስራት የሚችሉ ዕውቀቱ ያላቸው ነገርግን ያላቸውን ሀሳብ የሚያጋሩበት ሚዲያ ላጡ በርካቶች እንቅፋታቸውን በማንሳት ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን በነፃነት አሐዱ የሚሉበትና የሚናገሩበት የመገናኛ ብዙሃን ዕድል ፈጥሯል ። በዚህ ሀሳብ እንደ ድልድይ ሆኖም እያገለገለ ይገኛል ። ለረዥም ዓመታት ሀሳቦችን በማንሸራሸር ጉዳዩን በማብሰል ከስያሜው እስከ አሰራሩ ድረስ በማውጣትና በማውረድ ቆይቶ የተለየና የተሻለ ስራ ለመስራት አሐዱ ሬድዬን በ2009 የዛሬ 8 ዓመት የጀመረ ሲሆን አስከትሎም አሀዱ ቴሌቪዥንን ዕውን ማድረግ ችሏል። አሀዱ ሬድዮ ባለፉት 8 ዓመታት በአድማጮች ዘንድ በጎ ተፅዕኖ የፈጠረ የግል ሚድያ

እንደሆነ ይነገርለታል።ከዚህ ጣቢያ ስኬት ጋር ደግሞ እሸቱ በላይ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሥራ ፈጣሪ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *