ኤን.ኤም. ሲ ሪል ስቴት የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋርቷል፣ የቁሳቁስ ድጋፍም አድርጓል

ማዕድ መጋራት እንግዳ ባህል አይደለም፥ የኢትዮጵያዊያን ቤተኛ ነው። ሐሳቡም እንደዛው አብሮን ኖሯል። ያደመጠ ሁሉ እንደሚረዳው፥ ማዕድ ማጋራት ተባለ እንጂ ማዕድ መስጠት ወይም ማዕድ መርዳት አልተባለም። ማጋራት በመተሳሰብ፣ በመከባበርና አንዱ ለሌላው በበጎነት ከማሰብ የሚነሳ ነውና። ጎረቤት ከጎረቤቱ፣ ዘመድ ከዘመዱ የሚያደርገው፣ ሲያደርግ የኖረው የገዛ ባህልና ወጉ ነው።
ይህ የኖረ ባህል አዲስ በሚመስል መልክ ከመጣ ወዲህ፣ ባለሀብቶችና ተቋማትም በዚህ የማጋራት ባህል ውስጥ እየተሳተፉ ነው። ይህ በደስታ ሊያልፉ፣ በፈገግታ ሊኖሩ የሚገቡ በዓላትና የጋራ የደስታ ቀናትን ማንም ከደስታ ሳይጎድልበት እንዲያሳልፍ ያስችላል። አለፍ ያለ የበጎ አድራጎት ሥራንም ያነቃል።

መንግሥትም ይህን የኅብረተሰቡን እሴትና ባህል ተውሶ በማሳደግ፥ ባለሀብቶችና ተቋማት ለወገናቸው እንዲደርሱ ለማድረግ የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብርን ሰፊ እውቅና ሰጥቶታል። ባለሀብቱንና ተቋማትን በማስተባበርም በየበዓላቱ ችግር ለጸናባቸው ወገኖች መድረስ እንዲቻል ሲንቀሳቀስ ታይቷል።

ኤን.ኤም.ሲ ሪል ስቴትም በዚህ ከማኅበረሰብ በተወረሰና እንደ ሀገር ገዝፎ ለብዙዎች ደስታን በሰጠ የማዕድ ማጋራት አገልግሎት ውስጥ በደስታ ተሳትፏል። ከዚህ ቀደምም የድርጅቱ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሠረት መኮንን፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባቀረበላቸው ጥሪ መሠረት፥ ለአቅመ-ደካሞችና ለድሀ ድሀ ነዋሪዎች የሚያገለግሉ ቤቶች ሠርተው አስረክበው ነበር።

አሁንም ይኸው በቤቶች ልማት ዘርፍ ላይ ተሠማርቶ የሚገኘው ኤን.ኤም ሲ ሪል ስቴት፣ የትንሣኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ዛሬ እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ለ1000 አቅመ ደካሞችና ወላጅ አልባ ሕጻናት የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

ቱሉ ዲምቱ በሚገኘው የኤን. ኤም. ሲ የግንባታ ሳይት ላይ የማዕድ ማጋራት እንዲሁም የቁሳቁስ ድጋፍ ያደረጉት አቶ መሠረት መኮንን በበኩላቸው፥ ድርጅታቸው የመረዳዳትና አንዱ ሌላውን ደግፎ የመኖር ባህል እንደነበረው ያወሳሉ። ይህም በተለይ አቅመ ደካሞች እንዲሁም ወላጅ አልባ ሕጻናት በዓሉን ደስ ብሏቸው እንዲያሳልፉ ያደርጋል ብለዋል።

በዚህ የማዕድ ማጋራትና የቁሳቁስ ድጋፍ መርሃ ግብር ላይ የወረዳ 13 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደስታ ለማ የተገኙ ሲሆን እርሳቸውም የባለሀብቱ ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን መወጣታቸውን አድንቀዋል፡፡ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች እንዲሁም መገናኛ ብዙኀን በመርሀ ግብሩ ላይ ታድመዋል፡፡

የመርሀ ግብሩ አስተባባሪእና የሚድያ ዘገባዎችን ያከናወነው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ሲሆን ከዚህ ቀደም የኤን ኤም ሲ ሪል ስቴት የግንባታ መርሀ ግብርን ዕውን ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *