ኤልሳ አሰፋ

ኤልሳ አሰፋ

ስራ ፈጣሪዋ ኤልሳ  አሰፋ

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡

በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡  በሚድያ ዘርፍ ታላቅ ጥረት ካሳዩና የራሳቸውን ኩባንያ ከከፈቱት መካከል ኤልሳ አሰፋ ትጠቀሳለች፡፡ ለአዲሱ ትውልድ ታሪኳ ስለሚያስተምር አቅርበነዋል፡፡

ትውልድና ትምህርት እና የንባብ ጅማሬ

ጋዜጠኛ ኤልሳ አሰፋ አዲስ አበባ በተለምዶ አብነት ኮካ ማዞርያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወልዳ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ባልቻ አባነፍሶ ፣ተስፋ ኮከብ እና ከፍተኛ አራት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትላለች።በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቋንቋና ስነ ፅሁፍ የመጀመርያ ዲግሪ ፣በስነ-ባህሪ ትምህርት ክፍል የስነ-ልቦና ኮርሶችንን ወስዳለች።

ከልጅነቷ ጀምሮ ልዩ የንባብ ፍቅር የነበራት ኤልሳ አሰፋ ፊደል በምትማርበት እድሜ ንባብ አቀላጥፋ የምትወጣ ፈጣን በመሆኗ ሁሉም የሚደነቅባት ነበረች። ይህን ተከትሎ የተለያዩ ስነ-ፅሁፋዊ ስራዎችን በለጋ እድሜዋ የመተዋወቅ አጋጣሚ ነበራት ።በወቅቱ በመንግስት መስሪያ ቤት ይሰሩ የነበሩት አባቷ አቶ አሰፋ ጌጠነህ የማንበብ ልምዳቸውን ልጃቸው እንድትከተል አብዝተው ይፈልጉ ስለነበር ከሚሰሩበት የመንግስት መ/ቤት ላይብረሪ መፅሀፍትን ተውሰው ያመጡላት ነበር።

ይህም የአንደኛ ደረጃ ት/.ቤት ተማሪ ከነበረችበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ልቦለዶችን በማንበብ ከስነ-ፅሁፋዊ ስራዎች ጋር ቅርበት እንዲኖራት አድርጓል።በተጨማሪ የንባብ ልምዷ በውስጧ ያለውን የስነ-ፅሁፍ ፍላጎት ለማዳበር ትልቅ አጋጣሚ ነበር። አጭር ልቦለዶች፣ ግጥሞችን በመኝታ ቤቷ ግድግዳ ላይ ጭምር በመፃፍ ዝንባሌዋን ለማሳደግ ትሞክር ነበር ።

ይህን ተከትሎ ከስነ-ፅሁፍ ጋር ያላት ትውውቅ እየጠነከረ ሲመጣ በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሳለች ግጥሞችን፣አጫጭር ልቦለዶችን በመፃፍ በት/ቤት የሰልፍ ስነ-ስርአቶች፣ለወላጆች ቀን በእል ላይ ታቀርብ ነበር ። በሂደትም ፣ በተለያዩ ክበባት ተሳትፋለች፡፡

በት/ቤት የክበባት ተሳትፎ

በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የጋዜጠኞች ፣የቤተሰብ ምጣኔ ፣የአካባቢ እንክብካቤ ክበባት ንቁ ተሳትፎ ታደርግ ነበር። በጋዜጠኞች ክበብ በሚኒ ሚዲያ የተለያዩ ስነፅሁፋዊ ስራዎችን ፣ በማቅረብ በት/ቤቱ ማህበረሰብ የታወቀች ነበረች።

በዚህ አጋጣሚ በሚኒ ሚዲያ ይሰሩ ለነበሩ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች የጋዜጠኛ የክበብ አባላት ፤ በሬድዬ ፋና በተመቻቸው እድል የመስራት አጋጣሚ በማግኘቷ ከሙያው ጋር በተለየ ሁኔታ እንድትተዋወቅ እድል ሰጥቷታል። መገናኛ ብዙሀንን የመከታተል ልምድ ስለነበራት የምታደንቃቸው ጋዜጠኞችን በቅርበት ማግኘት ፣የአሰራር ሂደቱን ማየት መቻሏ ከሙያው ጋር የበለጠ ለመተዋወቅ ልዩ አጋጣሚ ነበር። በተጨማሪ በአማተር የጋዜጠኞች ማህበራት የነቃ ተሳትፎ ታደርግ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ አማተር ጋዜጠኞች ማህበር ይታተም በነበረው ‹‹አዲስ አበባ›› ጋዜጣም ላይ በአዘጋጅነት ሰርታለች።

የጋዜጠኝነት ሀሁ

በሬድዬ ፋና ባገኘችው የሚኒ-ሚዲያ ፕሮግራም. የማቅረብ አጋጣሚ ድምፅ እና አቀራረቧ ጆሮ ገብ መሆኑን የተረዱ የስራ ሃላፊዎች በተለያዩ መሰናዶዎች ላይ አቅሟን እንድታሳይ እድሉን ፈጠሩላት፡፡ በዚህ አጋጣሚም በኢትዮጵያ ሬድዮ የመዝናኛ ፕሮግራም ፣ እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ? የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜና አንባቢ. ከሆነው ከተመስገን በየነ ጋር በአቅራቢነት ሰርታለች።በሂደት በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን ኦጄንሲ ኤፍ ኤም 96.3 በፕሮግራም አስተዋዋቂነት የትርፍ ሰአት ሰራተኛ በመሆን የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን እየተከታተለች ጎን ለጎን በጣቢያው ጥሩ ልምድ አካብታለች ።

ሬድዮ ፋና የኤልሳ አሰፋ ልዩ ህልም

በሚኒ-ሚዲያ ዝግጅት ድምጿን ለመጀመርያ ጊዜ የሰማችበት፣የምታደንቃቸው የተለያዩ ፕሮግራሞች እና ጋዜጠኞች የሚገኙበት በወቅቱ እጅግ ተደማጭ ወደነበረው ጣቢያ ለመግባት ህልሟ ነበር። ይህንንም ለማሳካት ችላለች።ሬድዮ ፋና ኤፍ ኤም 98.1 ላይ መስራት መጀመሯ ለጋዜጠኝነት ህይወቷ የማዕዘን ድንጋይ ያስቀመጠላት ነበር።የአሰራር ሂደቱ ራሷን እንድትፈትሽ እንዳደረጋት ታስታውሳለች።ፕሮግራሞች፣ ዜናዎች. ከመሰራታቸው በፊት የእቅድ ውይይት ፣ከተሰሩ በኋላ የነበረው የየቀን ግምገማ እስካሁን ለቀጠለው የጋዜጠኝነት ህይወቷ ትልቅ መሰረት የጣለ አጋጣሚ ነበር።

በሬድዬ ፋና የሰራችባቸው አመታት አካባቢን ማስተዋል፣ነገሮችን በትኩረት መመልከት ፣ለሚሰሩ ፕሮግራሞችና ዜናዎች ልዩ አቀራረብ መከተል ፣ የፕሮግራሞችና ዜናዎች ጠንካራና ደካማ ጎን ግልፅ ግምገማ ፣ከተሻሉ ስራዎችና ከተሰጡ ትችቶች በተግባር የተፈተሸ እውቀትና ልምድን በመቅሰም የማይረሱ ልዩ ጊዜያት ያሳለፈችበት የስራ ላይ ስልጠና ጊዜ እንደነበር ትናገራለች።

በፋና ኤፍ ኤም ዜናዎችን በመስራት፣ከኤፍኤም 89.1 ባሻገር በሀገር አቀፍ ስርጭት በዜና አንባቢነት ፣ዶክመንተሪ፣ በኤችአይቪ ላይ ያተኮረ ‘የተስፋ ደወል’ በተሰኘ ፕሮግራም አዘጋጅነት ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሰዎችን እና ሌሎችን በማነጋገር በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች በመዘዋወር ጭምር ሰርታለች።

በተጨማሪም ታዘጋጀው የነበረው የቤተሰብ ሰአት ፕሮግራም እጅግ ተወዳጅ የነበረ ዝግጅት ነው።ይህም በልጆች አስተዳደግ ላይ መፅሀፍ እንድታዘጋጅ እረድቷታል ።እንዲሁም በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ሰርታለች።በተለይ የፋና ኤፍኤም 98.1 የዘጠና ደቂቃ እና 120 ደቂቃ ሾው በልዩ አቀራረብ እና ለዛ የበርካቶችን አድናቆት ያገኘችበት ነበር።

በሬድዮ ፋና ቆይታዋ ከእኔ የተሻሉ ከምትላቸው ባልደረቦቿ ልዩ እውቀት የቀሰመችበት በጋዜጠኝነት ህይወቷ ልዩ ቦታ ያለው እንደሆነ አስረግጣ ትናገራለች። በሬድዮ ፋና በአዲስ አበባ እና የክልል ከተሞች በተቋሙ የተዘጋጁ የተለያዩ መድረኮችን በመምራት የተሟሸው የመድረክ አጋፋሪነት የመንግስትና የግል ድርጅቶች የተለያዩ መድረኮችን እንድትመራ አስችሏታል።

ከማትረሳቸው የስራ ላይ አጋጣሚዎች መካከል በፋና ኤፍ ኤም 98.1 የዘጠና ደቂቃ ተረኛ አቅራቢ ሆና ቀድማ ከተዘጋጀችባቸው ባሻገር አዲስ መረጃዎችን ለማዘጋጀት 7ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው ቢሮ ተፍ ተፍ ስትል የቀድሞ የሀገሪቱ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ህልፈት ጭምጭምታ 10ኛ ፎቅ በሚገኘው ስቱድዬ ደርሶ ነበር ።አንድ ሰአት ተኩል ተጀምሮ ሶስት ሰአት ለሚጠናቀቀው 90 ደቂቃ የዜና እና የመረጃ ሰአት ዝግጅቷን ጨርሳ ስቱድዮ ስትደርስ ሁኔታው አስደንጋጭ ነበር።

ወዲያው የጣቢያው ሀላፊዎች ምን እናድርግ እንዴት ይቅረብ? ግራ የተጋባ የስልክ ጥሪ ማቃጨል ጀመረ፣ወዲያው መግለጫዎች ተከተሉ። ልክ አንድ ሰአት ተኩል ሲሆን በ90 ደቂቃው የሀገሪቱን ጠ/ሚ ህልፈት ለህዝቡ አቅርባለች ።

የጠ/ሚ የህልፈት ዜና እንደሰው የሚያሳዝን፣ልብ የሚነካ የሚያስደነግጥ ቢሆንም ሀዘንን ዋጥ አድርጎ ሙያው የሚጠይቀውን አቀራረብ ለመከተል በዚያው ሰሞን መሪዋን አጥታ በሀዘን የሰነበተችውን ሰሜን ኮርያ ታዋቂ የዜና አቅራቢ እያለቀሰች ማቅረቧ በጋዜጠኞች መካከል አነጋጋሪ ነበር፡፡ የሻይ ሰአት የውይይት ፣የጨዋታ ርዕስም ነበር፡፡በመሆኑም ያንን ላለመድገም እና ለህዝቡ የሚተላለፉትን መልእክቶች ከስሜት በፀዳ መልኩ በአግባቡ ለማቅረብ እድል ፈጥሮላታል።በዚያን እለት ማለዳ ለፕሮግራሙ ዝግጅት ገብታ ሙሉ ቀን ከተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት የሀዘን መግለጫ ስታነብ እንደዋለች ታስታውሳለች፡፡

ከተቀጣሪነት ወደተባባሪ ፕሮግራም አዘጋጅነት

ኤልሳ አሰፋ ተቀጥራ ትሰራ በነበረበት ጊዜ አንድ ቀን የራሴን አየር ሰአት ወስጄ ብሰራ የተሻለ ይሆናል ብላ ታስብ ነበር፡፡ የራስን ስራ መፍጠር ከሚሰጠው የስራ ነጻነት ባሻገር የተሻለ ገቢም ስለሚኖረው ኤልሳ አሰፋ ይህን እቅዷን ከግብ ለማድረስ ሌት ተቀን የተለያዩ ዝግጅቶችን ማድረግ ጀመረች፡፡

ልዩ አቀራረብ የተለየ ይዘት ያለው ፕሮግራም የማቅረብ ሀሳቧ ብስራት ኤፍ ኤም 101.1 በ2006 ሲመሰረት እውን ሆነ። በቤተሰብ ላይ. ያተኮረ ፕሮግራምን ለመስራት ከጣቢያው ጋር ተዋውላ በሬድዬ ፋና የነበራትን የአምስት አመታት ስራዋን በገዛ ፍቃዷ በመልቀቅ ህልሟን ለማሳካት እርምጃዋን ጀመረች።

ለአንድ አመት ያህል ቤተሰብ ላይ ያተኮረው ፕሮግራም በብስራት ኤፍ ኤም ከተላለፈ በኋላ ኤልሳ አሰፋ በፋሽን እና በዲዛይን ላይ ያላትን ልዩ ፍላጎትና ክህሎት ያማከለ በፋሽን እና ውበት ላይ ያተኮረ ዝግጅት ሆኖ በሳምንት 3 ቀን ሰኞ ረቡዕ እና አርብ ከቀኑ 5-6:30 ለአድማጮች እየቀረበ ይገኛል።

‘ስለእኛ ‘የሚል መጠርያ ያለው በፋሽንና ውበት አጠባበቅ እና በጤናማ የአኗኗር መንገዶች ላይ ያተኮረው ዝግጅት ተወዳጅነቱን አስጠብቆ መዝለቅ. የቻለ የተለየ አቀራረብ፣የርእሰ- ጉዳይ አመራረጥ ያለው፣አድማጭ በመረጃ ላይ የተመሰረተ እውቀት እንዲኖረው በጥናት የሚሰራ ከ16አመት ጀምሮ ያሉ አድማጮችን ኢላማ አድርጎ የሚቀርብ ተወዳጅ ዝግጅት ነው። ይህ መሰናዶ በርካታ አድማጮችን ለመሳብ የቻለ ሲሆን አሁንም ከሚወደዱ ፕሮግራሞች አንዱ ለመሆን የቻለ ነው፡፡

ኤልሳ አሰፋ በተጨማሪ በጣቢያው በሚተላለፈው የመሴ ሪዞርት የሬድዬ ፕሮግራም ላይ እንዲሁ በአቅራቢነት እየሰራች የምትገኝ ሲሆን በልዩ አቀራረብ በአድማጮች ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፋበታለች።በብስራት ኤፍ ኤም 101.1 ሙያው ላይ ያላትን ፍላጎት በመጠቀም አቅሟን አውጥታ በነፃነት እንድትሰራ እና የተለያዩ ሙያዊ እና ቤተሰባዊ ድጋፍ በቀናነት በመስጠት የሚያበረታቷትን አቶ መሰለ መንግስቱን ታመሰግናለች ።

ኤልሳ እና ቴሌቭዥን

በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን በምትሰራበት ወቅት በኢቲቪ 2 በዜና አንባቢነት ሰርታለች ። በብስራት ቴሌቭዥን ስለእኛ በብስራት ቴሌቭዥን ስለእኛ የፋሽን እና ውበት ፕሮግራም ቴሌቭዥኑ እስኪቋረጥ ድረስ ለማህበረሰቡ በውበት አጠባበቅና በጤናማ የአኗኗር መንገዶች ላይ ያተኮሩ ዝግጅቶችን ስታቀርብ ቆይታለች ።እንዲሁም የብስራት ቴሌቪዥን ጣቢያ የእሁድ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን በአስተዋዋቂነት ሰርታለች።

መፅሀፍት

ኤልሳ አሰፋ የቤተሰብ ፕሮግራሞችን በሬድዬ ፋና ከዚያም በኋላ በብስራት ኤፍኤም ‘ስለእኛ ‘የተባለ የቤተሰብ ፕሮግራም ስታዘጋጅ ለልጆች አስተዳደግ የሚያግዙ መፅሀፍት በብቂ ሁኔታ አለመገኘታቸውን በመረዳቷ እና የሬድዮ ፕሮግራሞቹን ስታዘጋጅ ያገኘችውን የወላጆች ተሞክሮ፣ ከስነ-ልቦናዊና የተለያዩ ጥናቶች በመቀመር ስለእኛ የሚል ርዕስ ያለው መፅሀፍት አሳትማ ለንባብ አብቅታለች፡፡

በዚህ አጋጣሚ በአርትኦት ስራው ከፍፁም ትህትና ጋር ትልቅ እገዛ ያደረገላትን መላኩ ብርሀኑን ታመሰግናለች ።’ስለእኛ ‘መፅሀፍ በወላጆችና በአሳዳጊዎች ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ሁለት እትም በተከታታይ ታትሟል።ለ3ኛ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

አሁንም ሌላ መፅሀፍ እያዘጋጀች ሲሆን በቅርቡ ታትሞ ለገበያ ይቀርባል።

ኤልሳ አሰፋ እና የበጎፈቃድ ስራዎች

በብስራት ኤፍ ኤም በምታዘጋጀው የስለእኛ ፕሮግራም አድማጮችን እና በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር የትምህርት መሳሪያዎችን ፣ላለፉት ስድስት አመታት እያሰባሰበች ለሙዳይ የበጎ አድራጎት ፣በከተማዋ ዙሪያ ለሚገኙ የመንግስት ት/ቤቶች እያበረከተች ትገኛለች ።በተጨማሪ ለሜሪጆይ ኢትዮጵያ የአልባሳት ድጋፍ ፣በበጎ ፈቃደኞች ተከታታይ የደም ልገሳ ዝግጅቶች በማስተባበር ማህበረሰባዊ ሀላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች፡፡ በቀጣይ በተደራጀ መልኩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ብስፋት የመስራት እቅድ አላት።

የተለያዩ ስልጠናዎች

በሀገር ውስጥ እና በውጭ የተለያዩ ስልጠናዎችን የመካፈል እድል አግኝታለች ። የጋዜጠኝነትና ስነፅሁፍ ስልጠናዎችን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆና ጀምሮ በተለያየ ደረጃዎች ወስዳለች፡፡ ።በአዲስ አበባ.ዩኒቨርስቲ ጆርናሊዝም ስኩል፣በብሪትሽ ካውንስል እና በሌሎችም ተቋማት ፣በውጭ ሀገራትም በአሜሪካን ኤምባሲ የተዘጋጀ ስልጠና በዩጋንዳ ካምፓላ እንዲሁም በግብፅ ካይሮ የአንድ ወር ስልጠናዎችን ተከታትላለች።

የቤተሰብ ሁኔታ

ኤልሳ አሰፋ በትዳር ውስጥ 20 አመታት ያሳለፈች ሲሆን ከባለቤቷ ከአቶ ታደሰ አየለ ጋር ዳን ታደሰ እና ክርስቲያን ታደሰ የተባሉ የ17 እና የ12 አመት ልጆችን አፍርተዋል።

ምስጋና

የንባብ ፍላጎት እንዲኖራት የተለያዩ መፅሀፍትን በማምጣት ፣ካነበቧቸው ፣ከሰሟቸው አስገራሚ የታሪክ አጋጣሚዎች በልዩ አተራረክ በመግለፅ ፣ፍላጎቷን እንድታሳካ ፣ትችያለሽ የሚል ጠንካራ ስነልቦና ያሰረፁባት አባቷን አቶ አሰፋ ጌጤነህን አመስግና አትጠግብም። ከልጅነቷ ትፈልገው ትወደው በነበረው  ሙያ መሰማራቷ እና ውጤታማ መሆኗን እንደትልቅ እድል የምትቆጥረው ኤልሳ አሰፋ በሂደቱ የባለቤቷ የአቶ ታደሰ አየለን አስተዋፅኦ ትልቅነትን ታነሳለች ። በትዳር ውስጥ ልጆች ወልዶ መማር እና መስራት ያለባለቤቷ ድጋፍ የማይታሰብ ነበር ።በተጨማሪም ከ15 አመታት በላይ በዘለቀው የጋዜጠኝነት ህይወት ለሙያዋ መሳካት የበኩላቸውን ያበረከቱ ቤተሰቦች ፣ወዳጆች፣ ያልተቆጠበ ፍቅር እና ማበረታቻ የሚሰጧት አድማጮች ፣የተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦችን ታመሰግናለች።

ቀጣይ እቅዶች

በስለእኛ የዩቲዩብ ቻናል ላይ የበለጠ ዝግጅቶችን በማቅረብ፣ በቴሌቭዥን ፕሮግራም በድጋሚ የመምጣትና ፣መፅሀፍቶችን የማዘጋጀት እቅድ አላት ። በቅርብ ጊዜም ኤልሳ አሰፋ የተሰኘ ብራንድን አስተዋውቃለች፡፡ ይህን ብራንድን በመጠቀም ጌጣጌጦች ለግለሰብ እና ለመኖርያ ቤት የሚሆኑ ማስጌጫዎች እና የፋሽን እቃዎች ወደገበያው እያቀረበች ትገኛለች ።

ኤልሳ አሰፋ ከጋዜጠኝነቱ ጎን ለጎን ለውበት እና ለፋሽን ዲዛይን ልዩ ፍላጎትና ዝንባሌ አላት፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ወደ ስራው በስፋት የመግባት እቅድ አላት፡፡ አሁን ካላት አቅም ጨምራ ለሀገሯ አንድ ቁምነገር የማበርከት እቅድም አላት፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *