ኤልሳቤት እቁባይ

ኤልሳቤት እቁባይ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሰራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡

ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ? የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ህይወቱ ካለፈም በኋላበተቻለ መጠን የምንዘነጋው አይኖርም።ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡

በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ኤልሳቤት እቁባይ ትነሳለች፡፡ ኤልሳ ላለፉት 25 አመታት በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከ፣ በእለታዊ አዲስ በዘፕሬስ እና በአዲስ አድማስ ጋዜጦች በሳል ዜናዎችን በመስራት ትልቅ አሻራ አኑራለች። የኢትዮጲያ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤትን 3 የስራ ዘመን ለአስራአምስት አመታት ወጥነት ባለው መልኩ በተከታታይ ውሎውን ክርክሮቹን ያለማቋረጥ በዜናዋ ዘግባለች።ብርቱዋ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ። የህይወት ታሪኳን እዝራ እጅጉና ዘቢባ ሁሴን ሰንደውታል፡፡

ትውልድና እድገት

ኤልሳቤት እቁባይ፣ ከእናቷ ወይዘሮ ለተብርሃን ገብረየሱሰ፣ ከአባቷ ከአቶ እቁባይ ገብረማርያም በአፋር ክልል አዋሽ አርባ ተወለደች። እድገቷ ከሶሰት እህቶቿ እና ከአንድ ወንድሟ ጋር በአዲስ አበባ ጨርቆስ አካባቢ ነው። በልጅነቷ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ አባቷ የመካከለኛው አዋሽ እርሻ ልማት ሰራተኛ ስለነበሩ በአፋር ክልል በሚገኘው በአሚባራ አንገለሌ የልጅነት የክረምት ጊዜን አሳልፋለች። ኤልሳቤት እንደዘመኗ ልጆች በኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና በሚለው ዜማ ተሯሩጣ አድጋለች፡፡ ወደ ትምህርት ገበታዋም ተሰማርታ ከጓደኞቿ ጋር ሰፈር ለሰፈር ቦርቃ ልጅነትን በደስታ ኣሳልፋለች፡፡

ትምህርት

ኤልሳቤት ፣የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በፈለገ- ዮርዳኖስ አንደኛ ደረጃ የህዝብ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ፣ በዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች። ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በእንግሊዝኛ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪ ያገኘች ሲሆን ከኢንድራጋንዲ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን በሶስዮሎጂ ተመርቃለች።

ጋዜጠኝነት

ለኤልሳቤት ወደ ሚዲያ መሳብ ምክንያት ወላጅ እናቷ ናቸው። እናቷ ዜና አብዝተው ማዳመጥ የሚወዱ ብቻ ሳይሆኑ ከሁሉም የዜና ምንጭ መረጃን የማግኘት ልምድ እና ፍላጎት ያላቸው ናቸው ። ይህ የእናቷ የዘወትር ልማድ ለኤልሳቤት የዜና ፍቅር መሰረት የጣለ ነበር፡፡ በ1990 ዓ.ም የጋዜጠኝነት ሙያን በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል ጀመረች፡፡ በልጅነቷ በጣም የምትወዳችውና የምታከብራቸው እንደ ነጋሽ መሀመድ፣ ብርቱካን ሀረገወይን እና ንግስት ስልፉን ከእናቷ ጋር እያዳመጠች ላደገችው ኤልሳቤት ዋልታ ገብታ ዜና ስትሰራ አንግል አመራረጥም ሆነ ርእሰ ጉዳይ ልየታ አላስቸገሯትም። በዋልታ ቆይታዋ የመጀመሪያ ዜናዋ በፕራይም ታይም/ መጀመሪያ ረድፍ የተቀመጠ/ የተነበበ ነበር። ኤልሳቤት በኃላ ለረጅም አመታት የፓርላማ ዘጋቢ ሆና የሰራች ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ፓርላማ ለመዘገብ የተላከች ቀን የነበራትን ፍርሃት ዛሬ ድረስ ታስታውሰዋለች ።ከዋልታ የስድስት ወራት ቆይታ በኋላ በ1993 የአገሪቱ የመጀመሪያው እለታዊ የግል ጋዜጣ በመሆን በታሪክ የተመዘገበውን እለታዊ አዲስን ተቀላቀለች።

እለታዊ አዲስ

እለታዊ አዲስ የአገሪቱ የመጀመሪያው የግል እለታዊ ጋዜጣ ሲሆን ለጋዜጠኞች በየእለቱ ሳይሰለቹ መስራትና ብዙ ማምረት ያስተማረ ጋዜጣ ነው ። ጋዜጣው የተነበበው ለስምንት ወራት ቢሆንም አሻራውን ግን በጉልህ አሳርፎ አልፏል። ኤልሳቤትም በእለታዊ አዲስ ቆይታዋ ከነሄለን መሀመድ፣ ከነደረጀ ደስታ፣ ከነ ሙሉጌታ አያሌው፣ ከነ ደረጀ ሃብተወልድ እና ሎችም ጋር በመሆን በርካታ ዜናዎችን ሰርታለች።ኤልሳቤት እለታዊ አዲስ እያለች አይኗን ከፍታ የምትጓዝ፣ ያየችውን የሰማችውን ያነበበችውን ሁሉ እንዴት አድርጋ ወደ ዜና መቀየር እንዳለባት የምታስብ ዜናን የምታነፈንፍ ጠንካራ ጋዜጠኛ ነበረች።

ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ የትግርኛ ቋንቋ መቻሏ ደግሞ ከኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ጋር ተያይዞ በትግርኛ ይወጡ የነበሩ መረጃዎችን ለአንባቢ በማድረስ ጉልህ ሚና ነበራት። ከ150 በላይ ሰራተኞች የነበሩት እለታዊ አዲስ ጋዜጣ ከስምንት ወራት የህትመት ቆይታ በኋላ ለመዘጋቱ ምክንያት የሆነውን የህወሃት ክፍፍል ዜና የሰራችው ኤልሳቤት ነበረች፡፡ ጋዜጣው ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያከትም ምክንያት የሆነውን ዜና እና ሌሎች በትግርኛ ቋንቋ ታትመው ያገኘቻቸውን መረጃዎች ለአንባቢ እንደሚመች አድርጋ ለማዘጋጀት ቢሮ ቆይታ ሊነጋ ሲቃረብ ወደቤቷ እንደገባች እና ከጋዜጣው መዘጋት ጋር የነበሩ ውዝግቦችንም እንዳላየች ያዘጋጀችው ጋዜጣውም ተሸጦ አልቆ ስለነበር ገበያ ላይ እንዳላየችው ትናገራለች፡፡ እለታዊ አዲስ ከተዘጋ በኋላ ለተወሰኑ ወራት በዘፕሬስ ጋዜጣ በዜና ዘጋቢነት ሰርታለች።

አዲስ አድማስ

ከ 1994 እስከ 2007 በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ከሪፖርተር እስከ አዘጋጅ ባሉት የስራ ኃላፊነቶች ሰርታለች ። በወቅቱ የጋዜጣው ስራ አስኪያጅ እና ባለቤት የነበረው አሰፋ ጎሳዬ ለጋዜጠኞች ይሰጥ የነበረው ነፃነት እና አብረዋት የነበሩት ባልደረቦቿ የነበራችውን መተጋገዝ ዛሬም በመልካምነቱ ታነሳዋለች፡፡ ኤልሳቤት በአዲስ አድማስ ቆይታዋ በዜና ዘጋቢነት ብቻ ሳትወሰን በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ከኢትዮጵያ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች ጋር እያዋዛች በምትጠይቃቸው ደፋር ጥያቄዎቿ የጋዜጣው አንባቢዎች ያስታውሷታል፡፡ በአባይ ወንዝ ዙሪያም በተከታታይ ዘገባዎችን ሰርታለች።

በሶማሌ ባህላዊ አለባበስ ራሷን በመቀየር የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት የነበሩትን አብዱላሂ ዩሱፍ ቃለ-መጠይቅ ለማድረግ ችላለች፡፡ ፕሬዚደንቱን አጅበው ይከተሉ የነበሩ ሴቶችን ተቀላቅላ ፕሬዚደንቱ አጠገብ የደረሰችው ኤልሳቤት ለቃለ-መጠይቅ መቅረፀ- ድምፅ ስታወጣ ፕሬዚደንቱ የመገረም ሳቅ ስቀው ጠባቂዎቻቸውን ቃለመጠይቁን እንድታደርግ መፍቀዳቸውን አሳውቀው ቃለ-መጠይቁን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ አስነብባለች፡፡
በ1997 ክተካሄደው አገራዊ ምርጫ ጀምሮ እስከ እስር እና ፍቺ ድረስ በንቃት የዘገበች ሲሆን በብዙዎቹ በወቅቱ ይሰጡ በነበሩ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ስለምትገኝ እና በቲቪ ስለምትታይ ካንቺ የአየር ሰአት እንኳን ቀንሰው ቢሰጡን በማለት ይቀለድባት ነበር ።በምርጫው እለትም የፕሮፈሰር በየነ ጴጥሮስ የምርጫ ጣቢያ በነበረው ሃዲያ/ሾኔ በመሄድ ዘግባለች ።

የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ደፈር ያሉ ጥያቄዎች በመጠየቅ የምትታወቀው ኤልሳቤት ኢትዮጲያ በአሰብ ወደብ የመጠቀም መብቷን ያጣችው ኢህአዴግ ውስጥ በነበረው “ኢግኖራንስ እና አሮጋንስ“ ነው ይባላል እርስዎ ምን ይላሉ? በሰሜን አፍሪካ እና በአረብ አገሮች የታየውን አይነት ህዝባዊ አብዮት ይመጣል ብለው አይሰጉም ወይ? በሚሉት ጥያቄዎች ብዙዎች ያስታውሷታል?

ኤልሳቤት የአስራ አምስት አመት የፓርላማ ቋሚ ዘጋቢነቷን ስታስታውስ ከተወካዮች ምክርቤት አባላት ጋር ያላትን መግባባት ተንተርሰው በወቅቱ ከሌሎች ሚዲያዎች ፓርላማ ለመዘገብ የሚመጡ ጓደኞቿ “ የምክር ቤቱ አባላት አንቺን ሰላም ለማለት እጃቸውን ሲያወዛውዙ በድጋፍ ወይም በተቃውሞ እንዳታስቆጥሪባቸው እያሉ ይቀለዱባት እንደነበር የምታስታውሰው ኤልሳቤት የምክርቤቱን አባላት ጠንቅቆ ማወቅ ምን ላይ እንደሚጠቅም በተግባር ያሳየችበትን ቀን አትረሳውም፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ ይግባ አይግባ በሚል ድምፅ በተሰጠበት የምክርቤቱ ውሎ ላይ ከሶማሌ ክልል ተወክለው የመጡት የአብዱል መጂድ ሁሴን ባለቤት ወይዘሮ አነብ በወቅቱ በጉዳዩ ላይ ድምፀ- ተአቅቦ ማድረጋቸውን በዜናዋ አስነብባለች፡፡

እሁድ 2007 ሚያዚያ 11 አይ ኤስ አይ ኤስ በሊቢያ የባህር ዳርቻ ኢትዮጵያውያንን አንገት ሲቀላ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መለቀቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ድምፁን አጥፍቶ ከቆየ በኃላ ድርጊቱ የተፈፀመባቸው ኢትዮጵያውያን ስለመሆናችው አልተረጋገጠም በማለት ጉዳዩን በይፋ ለመቀበል እያንገራገረ ባለበት ሰአት ድርጊቱ የተፈፀመባቸውን የእያሱ እና የባልቻ ለቅሶ አፈላልጋ በመሄድ መርዶውን በይፋ ለኢትዮጵያ ህዝብ አሳውቃለች፡፡ የእርሷን ዘገባ ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግስት የጉዳቱ ሰለባዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው ሲል አምኗል፡፡ ከሊቢያው የባህር ዳርቻ ግድያ ጋር ተያይዞ ህይወታቸውን ያጡትን የአብዛኞቹን የህይወት ታሪክ ዘግባለች፡፡

በአሜሪካን ሀገር ኑሮዋን ያደረገችው የቀድሞ የስራ ባልደረባዋና ጓደኛዋ መታሰቢያ ተሾመ ኤልሳን እንዲህ ትገልፃታለች “ለኤልሳ ሚዛናዊነት ለሙያዋ የምታጠልቀው ቆብ ሳይሆን ማንነቷም ጭምር ነበር። የማይጠረቃ የማወቅ ጉጉቷ የማያስፈነቅላት ድንጋይ አልነበረም። ከሁሉ በላይ ግን ታማኝ ባልንጀርነቷ ጊዜ እና የቦታ ርቀት ያላወየበው የእንቁ ማንነቷ መገለጫዎች ናቸው። እለታዊ አዲስ ጋዜጣ ላይ በቅርበት አብረን ለመስራት በመታደሌ በስራ ትጋቷ እና የጋዜጠኝነት ብቃቷ ምሳሌያችን እንደነበረች አስታውሳለሁ።” በማለት መታሰቢያ ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡

የቀድሞ የስራ ባልደረባዋ አርጋው አሽኔ ኤልሳን እንዲህ ገልጿታል።” መልከ መልካሟ ኤልሳቤትን ለሀያ ሶስት ዓመታት አውቃታለሁ፣ በሴት ጋዜጠኞች የማይዘወተረው የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ማተኮሯን አደንቅላታለሁ። ኤልሳ ዜና የለም ከሚባልበት ሁነትና አካባቢ ዜና ማውጣት የምትችል፣ ለዜና ፍንጭ ረጅም አፍንጫ ያላት ጋዜጠኛ ናት። ስንገናኝ ከፖለቲካና ጋዜጠኝነት ውጪ የምናወራው አልፎ አልፎ ነው። አስቸጋሪ የሚባሉ የሀገራችን አካባቢዎች አብረን ተጉዘን ዘገባ ሰርተናል። ለአርብቶ አደሩ አካባቢ ልዩ ፍቅር አላት። ምናልባት አፋር መወለዷ ይሆናል። በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የፊት ገፅ ለዓመታት ስሟ ቤተኛችን ነበር። መኳኳል አትወድም ምናልባትም በተፈጥሮዋ አይነ ግቡ ስለሆነች ይሆናል።” በማለት ሀሳቡን ለግሶ ነበር፡፡

ኤልሳቤት በበፈቃዱ ሞረዳ አንደበት

እዚህም፣ እዚያም እንዳለው የእኔ ብጤ ተርታ ዜጋ ግምት፣ የጎበዝ ጋዜጠኝነት መስፈርት ወይም መገለጫ መረዋ ድምዕ፣ ርቱዕ አንደበት፣ የተባ ብዕር ብቻ አይደለም። ይልቁንስ፣ ጠንካራና አስተማማኝ የግንኙነት መሥመር ወይም ትስስር ወይም ” ኔትወርክ” ማበጀት መቻል ለአንድ ጋዜጠኛ ብርታት ዓይነተኛ መለኪያ ነዉ። ይህን ማድረግ መቻል በራሱ ተሰጥዖም ነው። ለጋዜጠኝነት መወለድ።
የሰፊ ኔትወርክ መኖር፦

  • ያልነፈሰባቸውን ሐሳቦች ለማግኘት ይረዳል
  • ሙያው የላቀ እንዲሆን ያደርጋል
  • አዳዲስ መረጃዎችን ለማከማቸት ያግዛል
  • የተሻለ የሙያ ድጋፍና ምክርን የማግኛ አድማስን ያሰፋል
  • በራስ የመተማመን ስሜትን ያጎለብታል
  • ነገሮችን/ሁነቶችን ከተለያየ ማዕዘን ለማየትና ጤናማ በሆነ ብያኔ ላይ ለመድረስ ያስችላል
  • ዘላቂነት ያለዉ ግላዊ ግንኙነትን/ወዳጅነትን ያሰፍናል።
  • ከምንም በላይ የሙያዉን ፍቅር ያደድራል።

እነዚህን ነገሮች እዉን ያደረገ/ያደረገች ጋዜጠኛ ደግሞ በእርግጥም የሙያው አድባር እጁን ዘርግቶ የተቀበለዉ ሰዉ ነዉ። “ጋዜጠኛ”መባል የሚያኮራቸው፣የሚያምርባቸዉ። ብሎም የሚያስከብራቸዉ። እንደኤልሳቤት ዕቁባይ ዓይነት። በኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ታሪክ ዉስጥ ፣ በመንግሥት መዋቅር፣ በተቃዋሚ፣ በሌሎች የሚዲያ ተቋማት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የሀገሮች ኅብረት ተቋማት…ዉስጥ ጤናማና ዉጤታማ ድርን በመዘርጋት ሂደት ኤልሳቤጥ ዕቁባይ ለእኔ የሠልፉ መሪ ናት። አርአያ።

ኤልሳቤጥን በሥራ ዓለምም ሆነ በኮሌጅ ለዓመታት ሳዉቃት ሁሌም ጥያቄ ይሆንብኝ የነበረዉ ነገር፣ ” መቼ አኩርፋ አያት ይሆን?” የሚለዉ ነዉ።
ግን ይህም እዉነት ነዉ። ያቺ አኩርፋ መታየቷ ይናፍቀኝ የነበረዉ ኤልሳ ፣አይደለም ኩርፊያ ፣ ፊቴ ቁጭ ብላ፣ በርቀት ስልክ ደዉላ ስቅስቅ ብላ ስታለቅሰ ለማየትም፣ ለመስማትም የበቃሁበትን አጋጣሚ በሕይወት እያለሁ አልረሳዉም። ማንስ ነዉ ስለሰዉ አልቅሶ ያስለቀሰን ሰዉ የሚረሳ? ይህም እዉነት ነዉ። ያ ዘመን፣ ያ ያለቀስንበት ሁነት አለፈ። እምባዉና ሕመሙ ግን ለታሪክ ተረፈ። ባለችበት ቦታ ከእነ ቤተሰቧ ሠላምና ጤናን እመኝላታለሁ።

ኤልሳቤጥ እቁባይ አሁን ላይ ኑሮዋን በውጭ ሃገር ያደረገች ሲሆን ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነች። ወደፊት በህይወቷ ያለፈችባቸውን፣ የገጠሟትን መልካምም ሆነ አሳዛኝ አጋጣሚዎች ወደ መፀሃፍ የመለወጥ ህልም አላት። ወደምትወደው የዜና ስራም ተመልሳ ዜና ላይ ያላትን ትልቅ አቅም ተጠቅማ ለሀገራችን ህዝብ ጥሩ ነገር ታበረክት ይሆናል ማን ያውቃል ?

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ የቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ኤልሳቤጥ መለያ ቀለሟ ዜና ነው፡፡ ዛሬ ድረስ አንድ ጽሁፍ ወይም ጥናት አቅርቢ ስትባል ዜና በምትሰራበት እጥር ምጥን ባለ መንገድ ማቅረብ ይቀናታል፡፡ ባለፉት 25 አመታት በሚድያው አለም ከዜና ጋር የቆየችው ይህች ጋዜጠኛ ብዙ ሰዎች ስለምታውቅ ዜና ማግኘት ለእርሷ አዳጋች አልነበረም፡፡ ከ1994 ጀምሮ የሰራቻቸውን ዜናዎች ቤተ-መጽሀፍት ሄደን ስንመለከት በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለጊዜው ዜና ለአሁን ደግሞ ታሪክ ሰርታለች፡፡ ኤልሳ ዛሬ ስለዜና አውሪ ስትባል በሀሴት ትሞላለች፡፡ ስላሳለፈችው የዜና አዘጋገብ ገጠመኝ ማንሳት ታላቅ ርካታ ያኖርላታል፡፡ ኤልሳ በአብዛኛው የህትመት ሚድያ የዜና ጋዜጠኛ የነበረች ሲሆን በተለይ የቅዳሜው አዲስ አድማስ ለዜና ሲባል ተነባቢ እንዲሆን ጥረት አድርጋለች፡፡ ይህ ጥረት በእርግጥ የእርሷ ብቻ ሳይሆን የባልደረቦቿም ሆኖ የእርሷ ልፋት ግን በልዩነት በብዙዎች ይነሳ ነበር፡፡ ኤልሳ በዜና ጋዜጠኝነት ፈጽሞ ሊዘነጋ የማይችል ትልቅ አሻራ አኑራለች፡፡ አንድ ሰው ኤልሳ ምን ሰርታ ነው ታሪኳ የተከተበው ብሎ ቢጠይቅ ቤተ-መጽሀፍት ሄዶ የቆዩ የህትመት ውጤቶችን ያገላብጥ፡፡ ለዋቢነት ለማሳያ በሚል ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብረን አውጥተነዋል፡፡ ሁል ጊዜ የታላላቅ እና በእድሜ አንጋፋ የሚባሉትን የሚድያ ሰዎች ታሪክ ብቻ ስንከትብ የቅርባችን ብርቆች እንዳንረሳ በሚል ነው ኤልሳን መሰነዳችን፡፡ ደግሞም ቀዳሚ ግባችን ከ1970-1990 ያለውን ያልተነካ የሚድያ ሰዎች ታሪክ መዳሰስ ነውና በኤልሳ በኩል ይህን ታሪካችን ን ማግኘታችንን ልብ ይሏል፡፡ ኤልሳ እንደ ሌሎቹ ምን ታሪክ አለኝ ልትለን ብትችል እንኳን እኛም መልሱን ሰጥተናል፡፡ ካሰብንበት ብዙ የሚነገር ታሪክ አለን እንላለን፡፡ ይህን የኤልሳን ታሪክ እንድንሰራ ሀሳብ በመስጠት ላበረታቱን እና ለጠቆሙን ለኢዮብ እሸቱ እና ለኢሳያስ መኩሪያ የከበረ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ እና በጋዜጠኛ ዘቢባ ሁሴን የተዘጋጀ ሲሆን ዛሬ መስከረም 10 2016 ከሌሊቱ 7 ሰአት ከ26 በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ተጫነ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *